ከደቡብ ኦሞ እስከ መተማ፤ ከጅጅጋ እስከ ጋምቤላ፤ ከመቀሌ እስከ ባሌ፤ ከወልቃይት እስከ ኮንሶ!
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ቅድመ-አያቶች፣ አያቶች፣ ወላጆችና ልጆች፤ ሦስትና ከዛም በላይ የሆነ ትውልድ ተመሳሳይ በሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መሃል ተተብትቦ የሚማቅቅ ከሆነ የዛ ማህበረሰብ ጉዞ ጤናማነትና አቅጣጫ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በእንዲህ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ መሰረታዊ የሆኑና የጎሉ ለውጦች ብዙም አይስተዋሉም፡፡ አንዳንዶቹም ለውጦች የቁልቁለት ጉዞ ውጤቶች ይሆኑና በራሱ ብቻ ሳይሆን በአያቶቹም ቁስል የሚማቅቅ፣ መቃብር ቆፋሪና ሸክሙ የከበደው ትውልድ ይፈጠራል፡፡ ይህ አይነቱ ትውልድ የተጫነውን ሸክሙን አራግፎ በነገ ህይወቱና ጥቅሞቹ ዙሪያ ላይ በማተኮር ለፈጠራና ለምርምር ሊያውለው የሚችለውን አቅሙንና ጊዜውን ያልኖረበትን ትላንትን እያመነዠከና የወረሰውን ቁስል እየጎደፈረ ይቆዝማል፣ ያቄማል፣ እርስ በእርሱ ይጎነታተላል፤ ሲከፋም ወደ እልቂት ያመራል፡፡ እንዲህ አይነቱ አዙሪትም ከመስመር በወጣ ጊዜ በሌላው አለም እንደተስተዋለው ለአገራት መበታተንና ውድቀት፤ በሚሊዮኖችም ለሚቆጠሩ ሰዎችም እልቂት መንስዔ ይሆናል፡፡
ግፍ በገፍ የሆነባት አገራችን፤ በዚህ አይነቱ የመከራ አዙሪት ውስጥ ከሚሽከረከሩ ጥቂት አገራት አንዷ ነች፡፡ በእርግጥ እርሃብ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ጭቆና እና አፈና፣ የጎሣ ግጭቶችና ሌሎች መሰል አደጋዎች ለኢትዮጵያ አዲስ ነገሮች አይደሉም፡፡ ባለፉት 50 እና 60 አመታት ውስጥ እንኳ እነዚህ አደጋዎች ተደጋገመው፤ አንዳንዶቹም ያለማቋረጥ ተከስተዋል፡፡ እነዚህ አደጋዎች ኢትዮጵያን አራቁተዋታል፣ አዋርደዋታል፣ ከሥልጣኔና እድገት ጎዳናም አሽሽተዋታል፡፡ በእነዚህ አደጋዎችም ዜጎቿ አንገቸውን ደፍተዋል፣ ለስደት፣ ለግዞት፣ ለእርሃብና እርዛትም ተዳርገዋል፤ የብዙዎችም ሕይወት ተቀጥፏል፡፡
ግፍ በገፍ የሆነባት አገራችን፤ እኩይ በሆኑ ልጆቿ እጅግ ሰቅጣጭና አስነዋሪ የሆኑ ድርጊቶችንም በተደጋጋሚ ጊዜያት አስተናግዳለች፡፡ ግፈኛን በግፈኛ የሚተካው የፖለቲካ አዙሪታችንም የግፉአን ልጆች ግፈኛ፤ የግፈኛም ልጆች ግፉአን እየሆኑ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ብዙም ሳንርቅ አንባገነንነትን፣ አፈናን እና ጭቆናን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋትና ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ቆርጦ የተነሳውን እና በብሶት ተጸንሶ፣ በብሶት ተወልዶ፣ በብሶት ያደገውን የ60ዎቹን ትውልድ ጉዞ በቅጡ ማጤንም ይቻላል፡፡ ከዛ ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ከብሶቱ ጋር አብሮያረጀ ሲሆን ብዙዎቹም ካለሙበት ሳይደርሱና የአገራቸውንም ትንሳዔ ሳያዩ አልፈዋል፡፡ ጥቂቶቹም በለስ እየቀናቸው ሆድ አስባሽ እየሆኑ አዙሪቱን የአንድ ጎልማሳ ሰው እድሜን እንዲያስቆጥር አድርገውታል፡፡
ግፍ በገፍ የሆነባት አገራችን፤ ዛሬም በከፋ የርሃብ አደጋ እየተለበለበችና በአስር ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቿ በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ችጋር እያሰቃያቸው ይገኛል፡፡ አሥር አመታትን እያሰለሰ ይከሰት የነበረው ችጋርም በየሁለት እና ሦስት አመታቱ እየተከሰተ በአለም አቀፉ ማህበረሰቡ ዘንድ የተሰጠንን የእርሃብተኝነት መለያ እያደሰልንና የምጽዋት ጠባቂውንው ቁጥር በብዙ እጥፍ እያሳደገ ከእኛነታችን ጋር ተጣብቶ ብዙ ዘመናትን አብሮን እየተሻገረ እዚህ ደርሰናል፡፡ የወያኔ ‘የልማት’ ፕሮፓጋንዳ ሊጋርደው ያልቻለው ይህ የችጋር አደጋ የስንት ወገኖቻችንን ሕይወት እንደቀጠፈ ቤት ይቁጠረው፡፡
ግፍ በገፍ የሆነባት አገራችን፤ በሁሉም አቅጣጫ የአገዛዝ ሥርዓቱ ጭቆና እናአፈና ባንገሸገሻቸው ብሶተኞች አመጽ እየተናወጠች ትገኛለች፡፡ ሦስት አመታትን ያስቆጠረው የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት እንቅስቃሴ፣ ከአራት ወራት በላይ ያስቆጠረውና የበርካታ ንጹሃን ወገኖቻችንን ደም ያፈሰሰውና ሕይወት የቀጠፈውበኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ ቁጣና የነጻነት ጥያቄ፤ እንዲሁም የማንነት ጥያቄን መሰረት ያደረገው የወልቃይት ሕዝብ ንቅናቄና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩት የፖለቲካ ኃይሎች መነቃቃት ሥርአቱን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም ስጋት ውስጥ ከተውታል፡፡ ከዚያም ባለፈ አገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት አለመኖሩን እና ችግሩ በዚሁምከቀጠለ አስፈሪ የሆነ አቅጣጫን ሊይዝ እንደሚቻል የሚያመላክቱ በርካታ ነገሮች ከወዲሁ እየተስተዋሉ ነው፡፡
ግፍ በገፍ የሆነባት አገራችን፤ የብሄር ብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ተረጋግጧል እየተባለ ለ25 አመታት ሲደሰኮርና ሲጨፈርባት እንዳልኖረ ዛሬም ማንነታችን ይታወቅልን፣ እንደ ሕዝብም እንደሰውም እየተቆጠርን አይደለም የሚሉ ወገኖች ጥያቄ አንስተው መልስ የተነፈጉባት አገር ሆናለች፡፡ የወልቃይትና የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ ከብዙዎቹ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የመብት ጥያቄዎቹን ያነሱ የሕዝብ ተወካዮችም ለእስርና እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ለብሔረሰቦች መብት ቆሜያለው የሚለው ወያኔ የድል በዓሉ ሲደርስ በአመት አንዴ የሚያስታውሳቸውና ከያሉበት በውሎ አበል እያባበለበየአደባባዩ የሚያስጨፍራቸውናየበዓሉ ማድመቂ ያደረጋቸውህዳጣኖች በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በቅርቡ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨውና የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የሱርማ ብሔረሰብ አባላት ላይ የደረሰው ዘግናኝ ሁኔታ የበደላቸውን መጠን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ምስሉ ለሰው ልጅ ክብር ከሚገባው አያያዝ ውጭ እጅና አንገታቸውን አቆራኝተው በሲባጎ እያሰሩ ድብደባ የፈጸሙባቸው መሆኑንና የአድራጊዎቹንም ማንነት በግልጽ ያሳያል፡፡ በአገዛዙ የጎሣ ፖለቲካ ሳቢያም ኢትዮጵያውያን በዘር ተቧድነው ወደ ግጭት እያመሩ ያሉበትና እርስ በእርስም በጥርጣሬ የሚተያዩባት አገር ሆናለች፡፡
የወያኔ ሥርዓት በሂደት ይለወጣል፣ ለሕግና ለሥርዓትም ተገዢ ይሆናለ፣ ያጠበበውንም የፖለቲካ ምህዳር በሂደት የእያሰፋና የሕዝቡን የፖለቲካ ተሳትፎ እያበረታታ አገሪቱ ወደ ዲሞከራሲያዊ ጎዳና እንድታቀና ያደርጋል የሚለው የብዙዎች ተስፋ የተሟጠጠበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ የመብት ጥያቄ ለሚያቀረቡ ሕፃናት ተማሪዎችም ሆነ ሥርዓቱን በአደባባይ በሃሳብ ለሚሞግቱ ጎምቱ ፖለቲከኞች የሥርዓቱ ምላሽ ጡንቻና ጠመንጃ ነው፡፡ ወያኔ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ዘር፣ ጾታ፣ ኃይማኖት፣ እድሜ፣ የፖለቲካ ምልከታ ወይም ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድቡት በጠላትነት የፈረጃቸውን ሁሉ ሲያስር፣ አስሮም ሲያሰቃይ፣ ሲገድልና ሲያስገድል፣ ሲያሳድድና ሲያፈናቅል፣ ሲዘርፍና ሲያዘርፍ፣ በሃሰት ሲከስና በሃሰት ሲያስፈርድ ቆይቷል፡፡ የሥርዓቱ ጡንቻ የሕግም ሆነ የሞራል ልጓም እንደሌለው ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡
ይህ አይነቱ ሁኔታ ግን ሊቀጥል እንደማይችል ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየታዩ ያሉት ሕዝባዊ ቁጣዎችና የለውጥ መነቃቃቶች ጠሩ ምልክቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲል በሙስሊሙ ማህበረሰብ የተጀመረው የሰከነ የተቃውሞ ንቅናቄ ተገቢውን ምላሽ ሳያገን እጅግ ከፍተኛ ቁጣ በተቀላቀለበት የኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ አመጽ ታጅቦ ሥርዓቱን ሊወጣ ወደማይችለው አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡ በወልቃይት፣ በኮንሶ እና በጋምቤላም የተቀሰቀሱት እሳቶችም ተደማምረው የአገዛዙን እድሜ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም ዘላቂ ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ ሊጥሉ እንደሚችሉ አደጋዎች አንጃበዋል፡፡
የአገዛዝ ሥርዓቱ ላለፉት 25 ዓመታት የገነባው አጥርና ያሰመረው ቀይ መስመር ዛሬ ግፍ ባሰከራቸው ግፉዋን እየተጣሰና እየተደረመሰ ነው፡፡ ባደባባይ በሰለጠነ መንገድ የተቃወሙትን፣ የሃሳብ ልዩነት ያላቸውን፣ የተቹትንም ይሁን ለሥርዓቱ አገልጋይ ሆነው የቆዩትንና በጥርጣሬ ያያቸውን ሁሉ በፈረጠመ ጡንቻው እየደቆሰ እዚህ የደረሰው ወያኔ ፈተና ላይ የወደቀ ይመስለኛል፡፡ጡንቻ ልብን ቢያደነድንም፣ ማናለብኝነትን ቢያነግስም፣ አእምሮን አዶልዱሞናየማሰብ ችሎታን አቀጭጮ ለሌላው የሰው ዘር እንዳንራራ ቢያደፋፍርም መሰረቱ ግን ጥልቅ ፍርሃት ነው፡፡በፍርሃት ውስጥ የሚኖር የፖለቲካ ሥርዓት ብቻ ነው ጡንቻውን በሕዝብ ሃብት እያሳበጠ መልሶ ቀለቡን የሚሰፍርለትን ሕዝብእየጨፈለቀና እያስፈራራ መኖር የሚፈልገው፡፡
አገሪቷ ላይ ያንጃበቡት እነዚህ አደጋዎች የኢትዮጵያን ቀጣይ ጉዞ የሚወስኑ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ትርምስና አስፈሪ ሁኔታ በቀላሉ አገግመንና በድል አድራጊነት ልንወጣ የምንችለው እንደ እኔ እምነት ከዚህ በሚከተሉት ሃሳቦች ዙሪያ መግባባትና አብሮ መስራት ሲቻል ይመስለኛል፡፡
1ኛ. ከአፋኝና ታፋኝ የፖለቲካ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልንላቀቅና ጭቆናን ታሪክ አድርገን ወደ ዲሞክራሲያዊ ጎዳና ለንሸጋገር የምንችለው ግፉአን ብቻ ሳይሆኑ ግፍ ፈጻሚዎቹም አብረው ነጻ ሲወጡ ብቻ ነው፡፡ስለዚህም አገርን የማዳን ትግሉ ለአገዛዝ ሥርዓቱ የመጨቆኛ መሳሪያ በመሆን እያገለገሉ ያሉ አጋር ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን ከወያኔ ጉያ ማውጣትና የሕዝብ ወገንተኛ እንዲሆኑ ማድረግን ዋና ግቡ ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህም በመሳሪያ አቅም፣ በፖለቲካ አደረጃጀት፣ በገንዘብም አቅም ይሁን ሰፊውን የአገሪቱን ክፍል በማስተዳደር ዕረገድ የማይናቅ ድርሻ ያላቸውን ኦህዴድ (የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት)፣ ብአዴን (የብሔራዊ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) እና ሌሎች አጋር ድርጅቶችን የትግሉ አካል እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ከወዲሁ ማመቻቸት ትግሉን ከማፋጠን ባለፈም ሊደርስ የሚችለውን የጥፋትና እልቂት አደጋም የመቀነስ ኃይል ይኖረዋል፡፡ የህዝብ እሮሮዎችና ትያቄዎች ሆኖ በማያውቅ ምልኩ በእነዚህ ሁለት ድርጅቶች ውስጥ በይፋ እየተንጸባረቀ እንደሆነ በየጊዜው ከድርጅቶቹ እያፈተለኩ የሚወጡት መረጃዎች በግልጽ ያሳያሉ፡፡ በምን መልኩ እነዚህን ድርጅቶች ከወያኔ ጉያ ማላቀቅና ነጻ ማውጣት እንደሚቻል ዝርዝሩን በጉዳዩ ላይ ለመስራት ፍላጎቱና አቅሙ ላላቸው አካላት እተወዋለሁ፡፡
2ኛ. ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከተሰነቀሩበት ቅርቃር ለማማቀቅና ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ሰላም የተረጋገጠባት እና የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን ለማምጣት የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች መቀናጀት ባለመቻላቸው የተነሳ ለለውጥ አመቺ የሆኑ በርካታ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ ሊጠቀምባቸው የሚችል ኃይል ባለመፈጠሩ እልም እየሆኑ አልፈዋል፡፡ ዛሬ ግን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ሁኔታ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ በመላ አገሪቷ ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ መነቃቃት እየተስተዋለ ነው፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ አመራር ኃይሎች በተለይም በውጭ የሚገኙ ድርጅቶች በየመድረኩና በየመገናኛ ብዙሃኑ ከመነታረክ፣ አሰልቺ የሆኑና የተለመዱ የፖለቲካ ትንታኔያቸውን ከመስጠት፣ እርስ በእርስ ከመናቆርና አንዳንዴም በባዶ ሜዳ ‘ወሬ የፈታው’ አይነት ፉከራና ቀረርቶ ከማሰማት ተቆጥበው ለጋራና የተቀናጀ ትግል ቢሰሩ እና ያለመሪ በተበታተነ መልኩ በየቦታው የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ንቅናቄና የለውጥ ጥያቄም አቅጣጫ ቢያሲዙት ለውጡም ይፋጠናል፤ ያንጃበቡትም አደጋዎች ብዙ የህይወት ዋጋ ሳያስከፍሉ የኢትዮጵያ ትንሳዔ እውን ይሆናል፡፡
ለመብታቸውና ለነጻነታቸው ሲታገሉ የተሰዉትን ሰማዕታት ነፍሳቸውን ይማር!
በቸር እንሰንበት!
ያሬድ ኃይለማርያም፤ ቤልጂየም
መጋቢት 14፣ 2016 እ.ኤ.አ
yhailema@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
eunetu says
አቶ ያሬድ!ይበል የሚያሰኝ በሳል እይታ!!!
ጥላቻ ላይ ብቻ ያላጠነጠነና አገርን በማዳኑ ሥራ ላይ የሁሉንም /በዳይንም ተበዳይንም/ ኃላፊነት የጠቆመ የበሳል አእምሮ ውጤት የሆነ ጽሁፍ!!!
አዎ! እኔም እንደ ወንድሜ ያሬድ እውነትን በፍቅር እየተናገርን ጥፋተኞችን ሁሉ ወደ መልካም ሥራ በመጸጸት እንዲመጡ ማድረጉ ይሻላል። ሲጠሉት የሚወድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ የሚመራ እውነተኛ ክርስቲያን ብቻ እንጂ አስመሳይ ክርስቲያንና ወተሊከኞች የበቀል ሰዎች ናቸው። ስለዚህ የያሬድን በሳል ምክር በማሰተዋል እንጠቀምበት!!!
ያሬድ እንደ ባለ ድጓው ያሬድ የዚህ ዘመን የእርቅና የሰላም ድጓ በቅንነትና በጥንቃቄ አብረን ለመደጎስ አንታክት!!! በርታ! ከዓይንም ያውጣህ!!!
በበሳል ሃሳብ የተሞላው ጽሁፍህ አድናቂ
እውነቱ ነኝ