ከአድዋ ወደ ራያ የዞረው የትግራይ አስተዳደር አዲስ መሪና ከመሪው ጀርባ የሚያጦዝ አዲስ ስብሃት ነጋን አግኝቷል። አዲሱ የስብሃት ነጋ ምትክ ንጉሥ ፈጣሪ (kingmaker) ጻድቃን ገብረ ትንሳኤ ሲሆን፣ የትግራይ ቲቪ ይፋ እንዳደረገው የትግራይ መሪ የሆነው ጌታቸው ረዳ ነው – ሁለቱም ከአማራ ከተወሰደው ራያ!!
በይፋ በሚታዩ መረጃዎች ጌታቸው ረዳ በትግራይ ታጋይ ሳይሆን ትግራይን የመራ ብቸኛ ካድሬ ሆነው ይመዘገባል። ጌታቸው ረዳ ሌላ የሚያስመዘግበው ሪኮርድ ደግሞ በጥላቻና “እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚል መርህ የተፈለፈሉ ሚዲያ፣ አክቲቪስቶች፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልል የብሔራቸው ተቆርቋሪ መስለው ሲንቀሳቀሱና ጥላቻን ሲያሰራጩ የነበሩ፣ በየክልሉ የክልልነት ጥያቄ በማስነሳት ግጭት እና አገር ብጥበጣ ውስጥ የገቡ፣ ሁሉ በጌታቸው አመራር ሥር ስለነበሩ ቆጣሪያቸው ይነቀላል።
ጌታቸው ረዳ የትግራይ መሪ እንደሚሆን ከተሰማ በኋላ የጥላቻውና የሁከቱ ሥርጭት መቀነሱን ኃይለማሪያም ጥበቡ ይናገራሉ። ስማቸው እንዳጠቀስ የጠየቁ አንድ የሰሜን አሜሪካ ነዋሪ “ሃብታሙና ሌሎቹን ኮተቶች ተዋቸው ይላሉ” ምክንያቱም እንደ በርሜል ተራ ጩኸት ይመስሏቸው – “ባዶዎች ናቸው” ይላሉ። አክለው “ኤርሚያስ ግን ሰግቷል” በማለት ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው ይገልጻሉ። እሱ ብቻ ሳይሆን “ቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ ጃዋር መሀመድ፣ ጃል መሮ፣ አድፋጩ ኦነግና አማራ ክልል ሤራ የሚያመርቱት ሁሉም በጌታቸው ሥር ናቸው” በማለት ይህንን ሁሉ ሤራ ጠማቂ ድባቅ በመምታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ማድነቅ አለመቻል ተራ ምቀኝነት እንደሆነ ያሰምሩበታል።
የበረከት ስምዖን “ልጅ” የ360ው ኤርሚያስ፤ ከትህነጉ ጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው
ከትህነግ ቅርብ ሰዎች እንደተሰማው ከሆነ ቀደም ሲል የእነ ደብረጽዮን ቡድን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሹመት ዝርዝር አቅርበው ነበር። ይህን ዝርዝር ለሪፖርተር ቅርበት ያላቸው የእነ ደብረጽዮን ቡድን አቀብሎ “ውስጥ አዋቂዎች ነገሩኝ” ሲል ጋዜጣው ዘግቦ ነበር።
ጻድቃንና ጌታቸው ግን ከሰላም አማራጭ የፕሪቶሪያው ስምምነት ውጭ የተደረገ መሆኑንን ገልጸው ዜናው ውሸት እንደሆነ ቢገልጹም ዜናውን የለኮሱትም ሆነ የተከፋፈሉት ይቅርታም ሆን ማስተባበያ ሳይሰሩ የአሁኑን ሹመት በነካ እጃቸው ጌታቸው የትግራይ መሪ መሆኑን በቀድሞው የውሸት ዜና ላይ ደርበው አቅርበውታል።
ጌታቸው ረዳ ጭልጥ ያለ ካድሬ ነው። ይህ ካድሬነቱ በዚህች ሁለትና ሦስት ዓመታት በሠራው ሰርከሶች የታየ በመሆኑ ዝርዝር ማብራሪያ አይጠይቅም። በአጭሩ ዐይን አውጣ ካድሬ ነው። “ከወር በኋላ ብልጽግና ወይም ሞት” ሲል ቢሰማ የሚሳቀቀው እርሱ ሳይሆን አድማጮችና ተመልካቾች ናቸው። ከዚህ በዘለለ አሁን አጓጊ የሆነው የጌታቸው ብልጽግና መሆን ሳይሆን፣ እርሱ የሚመራቸው የተቃውሞ ሚዲያዎችና በማሸበር ተግባር የተሰማሩ ተከፋይ አክቲቪስትና እዚያም እዚያ ጥይት የሚተኩሱ ወረበሎች ናቸው – ምንጫቸው ከሥሩ ሊደርቅ ነው።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አርብ መጋቢት 08/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ምርጫ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር ዋና ኃላፊ እንደሆን ይፋ ሲያደርግ ሁለት ዐበይት ጉዳዮች ወደ ፊት ብቅ ብለዋል። አንደኛው ሥልጣን ወደ ራያ ማምራቱና የትህነግ ተፈጥሯዊ ሞት መሞቱ ነው። ይህ ደግሞ የዐድዋ የበላይነትን ብቻ ሳይሆን “ተራሮችን አንቀጠቀጠ” ተብሎ የሐሰት ትርክት የተሠራለትን ልብ ወለድ ታሪክም ጭምር ወደ መቃብር የሚከት ነው።
መንግሥት ከትህነግ ጋር ድርድር በጀመረበት ወቅት ደብረጽዮን ከመድረኩ መጥፋቱና በምትኩ ጌታቸው በመሪ ተዋናይነት ብቅ ማለቱ በብዙ መልኩ የአሁኑን ጊዜ ጠቋሚ ነበር። ሆኖም በገፊና ጎታች ፖለቲካ የተጠመደው ሠራዊት አገር በማፍረስ ተጠምዶ ስለነበር የብዙዎችን ትኩረት እዚያ ላይ እንዳይሆን እንዳደረገ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል። ስምምነቱ ሲደረግም ትግራይንና ትህነግን ወክሎ የፈረመው የአድዋ ሰው ሳይሆን የራያው ጌታቸው ረዳ መሆኑ የህወሓት የፖለቲካ ሞት ጅማሬ እንደሆነ ይነገራል። በጥር ወር መገባደጃ ላይ በሃላላ ኬላ የትህነግ መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡና በተገመገሙ ወቅት በጠቅላዩ በስተግራ ተቀምጦ ሲያስረዳ የነበረው ጌታቸው መሆኑ መሪው ማን እንደሚሆን ሌላ ጠቋሚ ነበር። ከጌታቸው ቀጥሎ ጻድቃን መቀመጡ ስብሃትን ተክቶ አዲሱ ንጉሥ ፈጣሪ (kingmaker) ማን እንደሆነ በግልጽ ያመላከተ ነበር።
አፍቃሪ ትህነጉ ሰለሞን ገሪማ ይህን ይፅፋል፤ “ከዚህ በፊት ዶ/ር ደብረፅዮን በስራ ኣስፈፃሚ ተሽሞው በብዙ ተቃውሞ በማእከላይ ኮምቴ ኣይሆንም ቢባሉም “ግድ የላቹም ለኣብዪ በኣካል ሄጄ እለምነዋለሁ እምቢ ካለ ሌላ ትመርጣላቹ” ማለታቸው ሁላችን የምናስታውሰው ነው። ይህ በፌደራል መንግስት ተቀባይነት ሲያጣ በስራ ኣስፈፃሚ መሾም ቀርቶ በቀጥታ በማእከላይ ኮምቴ ትላንት የተደረገ ምርጫ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ለምርጫ የተወዳደሩትና ውጤታቸው እንሆ፤
ጌታቸው ረዳ 18 ድምጽ
ዶ/ር ፍሰሃ ሃብተፅዮን 17 ድምጽ
ዶ/ር ኣማንኤል ሃይለ 3 ድምጽ
ፕሮፌሰር ህንደያ ገ/ሂወት 2 ድምጽ
ዶ/ር ሓጎስ ጎዲፋይ 0 ድምጽ
ረዳኢ ሓለፎም 0 ድምጽ ይህ ምርጫስ ተቀባይነት ያገኝ ይሆን? ኣብረን የምናየው ይሆናል” ብሏል ሰለሞን ገሪማ።
ትህነግ መንግሥት ነበር። ከአራት ኪሎ ሲወጣ ጌታቸው አሰፋን አስረክብ ሲባል ለአንድ ሰው ብሎ እምቢ በማለት ይልቁንም “እኔም ጌታቸው አሰፋ ነኝ” ብሎ ወደ መቀለ ሄደ። ከመቀለ ወደ ተፈጠረበት በረሃ ሸሸ። ከዚም አንሰራራና ተመልሶ እንዳይድን ሆኖ ተመታ፤ ከወታደራዊ ብቃት አኳያ ዱቄት ሆነ። መመታቱ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን መከራና ስቃይ ውስጥ ከተተ። ጨለማ ውስጥ ገባ። ወጣቱን አስጨረሰ። ሲመሽበት ድሮ በፊት እምቢ ያለውን ሁሉ ትቶ “ያሻችሁን ሁሉ እሺ” ብሎ ህይወት አትርፍ ስምምነት ፈረመ። “በሒደት አብቦ ጠወለገና እንደ ቅጠል ወይቦ ሞተ” ተብሎ ከስምምነቱ በኋላ ተጽፎበት ነበር። አሁን የታየውም ይኸው ነው።
ጌታቸው መመረጡ ይፋ ከመሆኑ በፊት የፌደራሉ መንግሥት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። የኢትዮ 12 መረጃ ምንጮች እንዳሉት መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ባስቸኳይ ጊዚያዊ አስተዳደር የማይቋቋም ከሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታውን አሳውቆ፣ ለትግራይ ህዝብ አስረድቶ ራሱ የሚያምንበትን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም እንደሚገደድ ነግሯቸው ነበር። መንግሥት ለዚህ እርምጃ ያደረሰው በጀት ለቅቆ የመንግሥት ሠራተኞች ያልተከፈላቸው ደሞዝ ተከፍሎ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ በሚል ነው።
መንግሥት ይህ የማይሆን ከሆነ ጥይት ሳይተኩስ እምቢ ያሉትን በአውሮፕላን አሳፍሮ ወደ ማረፊያ እንደሚያስገባቸውም አስጠንቅቆ እንደነበር የገለጹት የመረጃው ባለቤቶች “የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አዲስ አበባ የትህነግ ሰዎችን ሰብስቦ ‘ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚሏችሁን አክብሩ። ከዚህ ውጭ ምንም የምናደርገው ነገር የለም’ ብለዋቸዋል። ያደረጉትም ያንን ነው” ሲሉ ነግረውናል። አዲሱ ሹመት የሚጸናው በፌደራል መንግሥቱ ቅቡል ሲሆን ብቻ እንደሆነ የፕሪቶሪያው ስምምነት ያስረዳል። እናም መንግሥት ሹመቱን ሲያጸድቀው የጌታቸው ረዳ ወንበር ይጸናል። እንደሚሰማው ከሆነ ሁሉም ነገር የመንግሥት ቅርብ ክትትል ያለበት በመሆኑ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ከሚያውቀው ውጭ የተለየ ፍላጎት ይስተናገዳል ተብሎ አይገመትም።
ሌላው አጓጊ ጉዳይ ትህነግ በሌላ ሰው ወይም በደብረጽዮን እንዲመራ የሚደረግ ከሆነ ነው። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ትህነግን ከትግራይ አስተዳደር ለመገንጠልና በቀደመው አካሄድ እንዲቀጥል ከተመረጠ ዕድሉ ልክ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ወይም ሊሎች የቤተሰብ ፓርቲዎች መሆን ነው። በስም አስተያየት ለመስጠት ጊዜው ገና እንደሆነ የገለጹ ለኢትዮ12 የአዲስ አበባ ተባባሪ “ትህነግ አሸባሪነቱ አልተነሳም። ምርጫ ቦርድ ሰርዞታል። ሕጋዊ ዕውቅና የለውም። እዚህ ላይ ቆሞ ከትግራይ አስተዳደር ልነጠል ካል ሞቱን ሳይሆን ራሱን ተረት ወደ ማድረግ ወዷል ማለት ነው። ብዙ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል” ሲሉ ገልጸዋል። እኚህ የቀድሞ የትህነግ አባል ሰሞኑን ጉዳዩ እየጠራ ሲሄድ ዝርዝር አሳብ እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
ጻድቃን ወታደራዊ ክንፉን የሚመራና የቀድሞውን የስብሃት ነጋን ቦታ በመያዝ ከጀርባ ሆነው የጌታቸው ረዳን አስተዳደር አባላት እንደሚያቋቁም ተወርቷል። በጻድቃን አጋዥነት ከአዲስ አበባ የቢሮ ሃላፊ ሆነው የሚሄዱ የተቀናቃኝ ፓርቲ አመራሮች እንደሚኖሩ ተሰምቷል። በትግራይ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ይወከላሉ ተብሏል። ወታደሩም ይገባል። (ኢትዮ 12)
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትግራይ የነበሩ ከባድ መሣሪዎች በሙሉ ከምድር በላይ እና ከምድር በታች ተቀብረው የነበሩትንም ጨምሮ ወደ መከላከያ እየገቡ መሆኑ ተገልጾዋል። ከዚህ በታች በፎቶ እንደሚታየው የረጅም ርቀት ተተኳሾችና በክልል ደረጃ ሊኖሩ የማይገባቸው ከባድ መሣሪያዎች ገቢ እየተደረጉ ነው። በጻድቃን እና ታደሰ ወረደ የሚመራው ወታደራዊ ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሥራቸውን በሚገባ እያከናወኑ ይገኛሉ። በፖለቲካው ክንፍ በኩል ሲታይ የነበረው መዘግየትና ሽኩቻም በጌታቸው ረዳ ምርጫ ወደ መጠናቀቁ የደረሰ ይመስላል።
ከማኅበራዊ ሚዲያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የጌታቸው ረዳ በትግራ መሪነት መመረጥ የህወሃትን መንደር ለሁለት ከፍሎ እያናቆረ ነው። አንዱ ወገን ጌታቸው የቀድሞ የህወሃት/ትህነግ ታጋይ አለመሆኑ እና ህወሃትን ከበረሃ ታጋይነት ሳይሆን ከመምህርነት በቅርቡ መቀላቀሉን እያነሱ ክህደት ተፈፀመ እያለ ነው። እነዚህ በአብዛኛው የአድዋ የበላይነት ፖለቲካ አቀንቃኞችና አሁንም በመለስ የሚምሉ ሲሆኑ በአማራ አንመራም እያሉ ነው። ጌታቸው ከአማራ ክልል ከሆነው የራያ አካባቢ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር “በአማራ አንመራም” ማለታቸው ራያን መሬቱን እንጂ ሰዉን አለመፈለጋቸውን ማሳበቁን የተረዱት አይመስሉም።
በሌላ በኩል የጌታቸውን መመረጥ የደገፉ በርካቶች ናቸው። መለስ ራሱ “እስከ እንጥላችን በስብሰናል” እንዳለው ህወሃት በስብሳለች ስለዚህ እንደ ጌታቸው ያለ ወጣቶችን እና ምሁራንን ያቅፋል፣ ያስጠጋል፤ የፖለቲካ ንቃቱና አረዳዱም እንደ ሽማግሌዎቹ አይደለም፤ የመናገር ችሎታውና በእንግሊዝኛ የማስረዳትና የማሳመን ችሎታው መለስን ጨምሮ ከማንኛውም የህወሓት/ትህነግ ታጋይ እጅግ የበለጠ ነው በማለት ለውጡን የደገፉ በርካታ ናቸው። የህወሃት ሥልጣን ከአድዋ መውጣቱ ብዙዎችን አስደስቷል። ይህ ካስደሰታቸው መካከል የስብሃትን አገዛዝ እጅግ የሚቃወመው ሊላይ ኃይለማርያም፣ የሰባ አንደርታ ሰዎች፣ የሽሬ ፖለቲከኞች እና በአድዋ የበላይነት ለበርካታ ዓመታት ግፍ የደረሰባቸው ሁሉ በደጋፊነት የሚጠቀሱ ሆነዋል።
የትግራይ ጉዳይ በዚህ መልኩ መጠናቀቅና የህወሓት/ትህነግ መፃዒ ዕድል ወደማይቀረው መክሰም መሄድ በቀጣይ በሻዕቢያ የበላይነት እና በለውጥ ናፋቂነት ተቆልፋ ሦስት ዐሥርተ ዓመታትን ያሳለፈችውን የኤርትራንም ቀጣይ ኅልውና በግልጽ የሚጠቁም ሆኗል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply