በኤርሚያስ ለገሰ እና በሃብታሙ አያሌው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ውዝግብ በርካታዎችን ሲነጋግር የቆየ ነበር። በተለይ በመካከላቸው ጥል እንዳለ በግልጽ በሚታይ መልኩ በአደባባይ እየወጡ የሚናገሩት ከበስተጀርባ ምን እየተደረገ ነው የሚል ጥያቄ ብዙዎች እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። አሁን ግን ሁኔታው ግልጽ እየሆነ የመጣ ይመስላል።
በኤርሚያስ እና በሃብታሙ መካከል ሰሞኑን የታየው ልዩነት አስመልክቶ ጥቂቶቹን ቪዲዮዎች እንመልከት፤
ከዚህ ሌላ የጌታቸው ሹመት በተሰማበት ቅዳሜ ዕለት እንደተለመደው ከሃብታሙ ጋር ለውይይት መውጣት የነበረበት ኤርሚያስ አልወጣም። ሃብታሙ ከሌላ ግለሰብ ጋር ለወሬ የወጡ ሲሆን በበረከት እና ጌታቸው ሥልታዊ የካድሬ ትንታኔው የበርካታዎችን ቀልብ የሚስው ኤርሚያስ በዚህ ወሳኝ ቀን ለትንታኔ አለመከሰቱ ምናልባት ለጌታቸው “ሹመት ያዳብር” ለማለት ሥራ በዝቶበት ሊሆን ይችላል በማለት አንዳንዶች ተሳልቀዋል። ሌሎች ደግሞ በፖለቲካዊ አክሮባት የተካነው ጌታቸው በነካ እጁ ወደ ዐቢይ ጠጋ እንዲያደርገው መማለጃ ለማቅረብ ደፋ ቀና እያለ ሊሆን ይችላል በሚል ተሳልቀዋል።
ይህ በኤርሚያስ ለገሰ እና በሃብታሙ አያሌው መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከጌታቸው ረዳ ጋር የተያያዘ ለመሆኑ በአንዳንዶች ዘንድ ጥያቄ እያስነሳ ያለ ጉዳይ ሆኗል። ይህም ከዚህ በፊት በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ኤርሚያስ ለገሠ ምሥጢራዊ ግንኙነት ከጌታቸው ረዳ ጋር ያደርግ እንደነበር የዘገብነውን ደግመን እንድናትም አድርጎናል። መረጃው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ በፊት የወጣ ቢሆንም አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በግልጽ የሚገናኝ በመሆኑ ምንም ሳንቀይር እንደገና አትመነዋል።
የበረከት ስምዖን “ልጅ” የ360ው ኤርሚያስ፤ ከትህነጉ ጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው
የቀድሞው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ (ትህነግ) ይመራው የነበረው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ደኤታ የነበረው ኤርሚያስ ለገሰ ከትህነጉ አሸባሪ ጌታቸው ረዳ ጋር በተናጠል ግንኙነት እንደሚያደርግ መታወቁ ተሰማ። ቀደም ሲል ጀምሮ “እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚለው የዲጂታል ወያኔ መዋቅር የሚፈሰውን “የተመረጠ የካድሬ ቃል” ኤርሚያስ ሲጠቀም መቆየቱን የሚናገሩ በዜናው እንዳልተገረሙ ገልጸዋል። መረጃውን ይፋ ያደረገው ኢትዮ 12 ነው።
በ360 “ዛሬ ምን አለ?” ዝግጅት ላይ ከሃብታሙ አያሌው ጋር በጣምራ ላለፉት ሁለት ዓመታት የትህነግን አቅጣጫ እንደሚያራቡ የከሰሷቸው የነበሩ ሃብታሙም ሆነ ኤርሚያስ ከትህነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በተለያዩ አውዶች ሲናገሩና ሲጽፉ እንደነበር ይታወሳል። ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ኢትዮ 360 የወያኔ ሚዲያ መሆኑ ተረጋገጠ” በሚል ርዕስ July 2, 2020 ያስነበበው ዜና እዚህ ላይ ይገኛል።
የኢትዮ 12 መረጃ አቀባዩን ጠቅሶ እንዳለው ቀደም ሲል ከተለመደው አግባብ በተለየ ኤርሚያስ ተደብቆ ለብቻው ከጌታቸው ረዳ ጋር በስልክ እንደሚገናኝ ሃብታሙ አያሌው አውቋል። ሰሞኑንን ሁለቱ “ተንታኞች” እየተካረሩ የመጡትም በዚሁ ምክንያት ነው። ሃብታሙ ብዙ ጊዜ ሲል ባይሰማም “ለትንታኔ“ በሚወጡበት ጊዜ ኤርሚያስ አሸባሪውን ጌታቸው “አቶ ጌታቸው“ እያለ “እርሳቸው“ በማለት ያለምንም መሸማቀቅ እንደሚጠራው ፕሮግራሙን የሚከታተሉ የሚያውቁት ብቻ ሳይሆን ሃብታሙም የታዘበው ነው።
ዘወትር አንዱ ሌላኛውን እየደገፉ መንግሥትን፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ከሕዝብ ለመነጠል ዘመቻ ሲያካሂዱ የሚታወቁት ሃብታሙና ኤርሚያስ፣ ባለፈው ዓርብ ዱላ ቀረሽ ዘለፋ ውስጥ የገቡበት ዋና ምክንያት ኤርሚያስ ሃብታሙን ተደብቆ ከጌታቸው ረዳ ጋር በምሥጢር መግጠሙ እንደሆነ ተባባሪያችን አመልክቷል።
አርብ ዕለት በተላለፈው የ“ዛሬ ምን አለ?” ዝግጅት ላይ ሃብታሙ “ስለወያኔ ሲነሳ ያንቀጠቅጥሃል” በሚል ኤርሚያስን ክፉኛ ሲዘልፈው ተሰምቷል። ይህን ከማለቱ በፊትም “እኔም ሆንኩ አንተ ኢህአዴግ በነበርንበት ወቅት ለፈጸምነው እንደ ድርሻችን እንጠየቃለን” ካለ በኋላ ተቃዋሚ ናቸው ተብለው የሚገመቱ ዜጎችን ለመምታት በተደነገገው የጸረ ሽብር ህግ የኤርሚያስ ሚና ጉልህ እንደነበር በይፋ አስታውቋል። ከዚህም የዘለለ ተናግሮት ነበር። “እኔ እዛው ሆኜ ታግያለሁ” ሲልም ኤርሚያስ “ሲፋጅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ በጄ” እንዲሉ አይነት መሆኑንን አመልክቷል።
የአርብ ዕለቱ መስመር የለቀቀ ሁኔታ ያወራጨው ኤርሚያስ፤ ሃብታሙ ተናግሮ ሲያበቃ “እኔም ያልኩት ይህንኑ ነው” በማለት ከሃብታሙ ጋር ሃሳቡ ተመሳሳይ እንደነበር ለመናገር የሞከረ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በመቀጠለም “ወደ ኋላ በመሄድ ይህ ተደርጓል ያ ተደርጓል ማለቱ ብዙም አስፈላጊ አይደለም” በማለት የሃብታሙን ክስ ለማጣጣል ሞክሯል። በዕለቱ ሁለቱን ያጣላቸው ዋና ሃሳብ ኤርሚያስ በአማራ ክልል ትህነግ እያደረሰ ላለው ጉዳት ዐቢይም ተጠያቂ ነው፤ ምክንያቱም ዐቢይ ጄኖሳይደር (ጅምላ ጨፍጫፊ) ነው በማለቱ ነበር። በአንጻሩ ሃብታሙ አማራን እየጨፈጨፈ እና ፈንጂ እየተኮሰ ንፁሃንን እየገደለ ያለው ዐቢይ ሳይሆን ትህነግ ነው ብሏል። ሁኔታው እየከረረ ሲሄድ ሃብታሙ በግልጽ ኤርሚያስን በመዝለፍ “ስለህወሃት ሲነሳ ያንቀጠቅጥሃል” ብሎታል። የዚህ የሃብታሙ ንግግር የኤርሚያስን የበፊት ሁኔታ የሚገልጽ ብቻ ሳይሆን አሁን የተደረሰበትና ከእነ ጌታቸው ጋር የሚያደርገውን ምሥጢራዊ ግንኑነት ያካተተ እንደሆነ ተነግሯል።
ሰኞና ማክሰኞ ከኢየሩሳሌምና ከብሩክ ጋር 360 ላይ “ለትንታኔ” የቀረበው ኤርሚያስ ለገሰ ብቻ ሲሆን፣ ሃብታሙ ያልቀረበበት ምክንያት ለጊዜው አልታወቀም። ሃብታሙ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ “አሁን አማራን እየጨረሰ ያለው ትህነግ ነው” በሚል አቋሙን አጥርቶ የመጣ ሲሆን፣ ኤርሚያስ “አዎ፣ ግን …” እያለ የትህነግን በደለና ወንጀል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ሲያጋራ ተስተውሏል። ይህ አካሄድ አዲስ ባይሆንም ኤርሚያስ አሁንም ሆን ብሎ የሚያደርገው እንደሆነ ከ360 አካባቢ ተሰምቷል።
ቀደም ሲል በስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ለይቶ በማሳጣትና የትህነግን ሃጢያት ተካፋይ በማድረግ ተግባር ላይ ተሳትፎው የጎላ እንደሆነ የሚጠቀስለት 360፣ ከጀርባ ሆነው ከሚረዱት አጋሮቹ በተጨማሪ 360ን በገሃድ የሚደግፈው የመረጃ ቴሌቪዥን ባለቤት በቅርቡ ሚናቸውን ይለያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ተናግረዋል። “ከአማራ ጋር ሂሳብ አወራርዳለሁ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ከሆነ እንገባለን” ከሚል ድርጅትና የድርጅት አመራር ጋር ግንኙነት ካለው ሚዲያና አዘጋጆቹ ጋር የመረጃ ቲቪ ባለቤት ሚናቸውን ሳይለዩ የት ድረስ እንደሚዘልቁ ግራ የገባቸውም አሉ።
ጌታቸው ረዳ፤ አንሙት አብርሃምን በቅርቡ “ሰላም ስበክ ወንድም ዓለም” እንዳለው በማህበራዊ ገጹ ማንሸራሸሩን ያስታወሱ “ኤርሚያስ ከጌታቸው ጋር የስልክ ግንኙነት አለው መባሉ አያስገርምም” ባይ ናቸው።
አንሙት አብርሃም ቀደም ሲል ENN (ኢኤንኤን) በሚባለውና ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቦርድ እየመራው በነበረው የቴሌቪዥን ላይ ይሰራ የነበረ፣ አሁን የአማራ አክቲቪስት መሆኑን በይፋ ያስታወቀ ነው።
ሲያስረዱም “360 ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ይቀርቡ የነበሩት ፕሮግራሞች በሙሉ የትህነግ ሃሳብና ዓላማ ላይ የተቸከሉ ነበሩ። በተለይ ኤርሚያስ ሌላው ‘በረከት ስምዖን’ ነው ሲባል በጅምላ ሲጮሁ የነበሩ ይህ መረጃ አዲስ ይሆንባቸው ካልሆነ በቀር ለሌሎች ከድሮም ግልጽ ነበር” ብለዋል።
ኤርሚያስ “ከኦሮሚያ ዘርፋለች” ብሎ ለሰደባት ከተማ፣ በባለ አደራ ምክትል ሊቀመንበር የሆነላት እንደሆነ ያስታወሱ፣ ሃብታሙ በደረጃ ዝቅ ቢልም ከትህነግ ጋር ግንኙነት እንደነበረው አይጠራጠሩም። ሆኖም ግን ትህነግ “ከአማራ ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለ” በሚል በሰላማዊ ዜጎች ላይ ወረራ ካካሄደ በኋላ ምክር ሰምቶ ወደ ቀልቡ መመለሱን በበጎ ተመክተዋል።
ሰኞና ማክሰኞ ብቻውን የቀረበው ኤርሚያስ ለገሰ ቃሊቲ አቃቂ መምህር እያለ ካድሬነትን ሲጀመር በመድረክ የትህነግ ታጋዮችን “ጀብድና ማንነት” እያነሳ ያለቅስ እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት መምህራን ባለደረቦቹ ምስክርነት መስጠታቸው አይዘነጋም። በ1997 ምርጫ አፈ ቀላጤ ሆኖ ህዝብ ሲፈጅ ትህነግን ይከላከል እንደነበር በውል የሚታወስ ነው። ጀግና ብርቁ የሆነው ዲያስፖራ ሁሉን ረስቶ ያጨበጨበለት ኤርሚያስና የ360 ቀጣይ ግንኙነት ምን ሊሆን እንደሚችል ለጊዜው መረጃ የለም።
ጎልጉል የሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው በሁለቱ የቀድሞ የትህነግ አገልጋዮች ላይ የሚሰጠው ሃሳብ የተለያየ ነው። አንድ አስተያየት ሰጪ እንዲህ ይላሉ፤ “የኤርሚያስ ለገሰና የሀብታሙ አያሌው በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያላቸው አስተሳሰብ፤ ኤርሚያስ በእውቀትና በአርቆ አስተዋይነት አስተያየት የሚሰጥ ሲሆን ሀብታሙ ደግሞ የጥላቻና የእልህ ነው። ሀብታሙ ግራ ተጋብተዋል ህክምናና እረፍት ያስፈልገዋል”። እንዲህ ዓይነቶቹን የሚዲያ አስተያየቶችን በ360 ውስጥ ያሉት ሠራተኞች “ኤርሚያስ ቀድሞም ካድሬ ስለነበር የቀድሞውን ድርጅታዊ አሠራር ሥልት በመጠቀም የራሱን ሰዎች እያሰማራ እኛን ለማንኳሰስ የሚበትነው መረጃ” በማለት ለማጣጣል ሲሞክሩ ይደመጣሉ። ሆኖም ኤርሚያስ በሚያራምደው አቋም በርካታ ትህነጎች እንደሚደግፉት ከሚሰጡት አስተያየቶች ለመመልከት ይቻላል። በዚህ አፍራሽ አቋሙ ኤርሚያስ ከ360 እና ከሃብታሙ ጋር እንዴት እንደሚቀጥል በቀናት ውስጥ የሚታይ ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply