ከመግቢያው በፊት
ይህንን ዘገባ በቴድሮስ አድሃኖም ላይ የሠራነው ከዓመት በፊት April 12, 2020 ነው። ትህነጉ ቴድሮስ አገራችንን ወክሎ የዓለም ጤና ጥበቃ ሃላፊ መሆን እንደሌለበት ገና ለምርጫ ሲወዳደር ጀምሮ አጥብቀን ተቃውመናል። አሁን ወቅቱ የደረሰ ይመስላል። ጥያቄው እየቀረበ ነው። ቴድሮስ አሸባሪውን ህወሃት እስካሁን እየደገፈ ያለ በመሆኑ ብቻ ከሥልጣኑ መወገድ ብቻ ሳይሆን ለፍርድም መቅረብ ያለበት ነው። ዘገባውን በድጋሚ አትመነዋል።
እንደ መግቢያ
ሰሞኑንን ከኮቪድ – 19 ጋር ተያይዞ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሓኖም አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ካወደመው፣ የዘር ፖለቲካን ከሚያራምደው ፍጹም ጽንፈኛና ዘረኛ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያንን በዘራቸው፣ በፖለቲካ እምነታቸው ካኮላሸ፣ ከጨፈጨፈ፣ ቶርቸር ካደረገ፣ በጅምላ ሴቶች እንዲደፈሩና ከነነፍሳቸው ለአውሬ እንዲጣሉ ካደረገ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር/ትህነግ ቴድሮስ የተቀዳ አመራር እንደነበር አይዘነጋም። የተመረጠው በኃያላኑ ዓላማና መልካም ፈቃድ ነበር፤ ኃያላኑ አሁን ፍጥጫ በሚመስል ውዝግብ ውስጥ ይገኛሉ፤ የተመረጠበትን ዓላማ የፈጸመ ከሆነ መወገዱ የማይቀር ይሆናል፤ ካላለቀ ደግሞ ዕድሜ ማራዘሚያ ይሰጠዋል።
የቴድሮስ የWHO ምርጫ
ወቅቱ የዛሬ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ገደማ፣ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተርን ለመምረጥ እጩዎች የሚያወዳድርበት ጊዜ ነበር። ከአውሮጳ ደቡብ ማለትም ከሰሃራ በታች አፍሪካንና መላውን ታዳጊ አገር ወክያለሁ በማለት ይወዳደር የነበረው ቴድሮስ አድሓኖም ገብረየሱስ (ዶ/ር) ነበር። የዕጩ ምልመላው ቃለመጠይቅ ቀጥሎ የቴድሮስ ጊዜ ይደርሳል፤ ከአልጄሪያ፣ ከጀርመን፣ ከአውስትራሊያ፣ ከህንድ ተወካዮች የቀረቡለትን ጥያቄዎች ጥቂቶቹን በቀጥታ ከመመለስ በስተቀር ለአብዛኛዎቹ ተገቢ ምላሽ ሳይሰጥ ያልፋል – በተለይ ከህንድና ከጀርመን ተወካዮች የቀረቡትን ጥያቄዎች ዘለላቸው።
በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደነበር የሚያሳብቅበት ቴድሮስ በሁለተኛው የጥያቄ ዙር ከፍተኛ ችግር ገጠመው። ኤርትራ የተወለደውና ለድርጅቱ ባስገባው የማመልከቻ ቅጽ ላይ እንግሊዝኛ እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋዬ አቀላጥፌ እናገራለሁ በማለት የተናገረው ቴድሮስ፤ ከብራዚል ተወካይ የተሰነዘረለትን ቀጥተኛ ጥያቄ ለመመለስ አንዴ “ይብራራልኝ”፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ይደገምልኝ ግን ደግሞ ይብራራልኝ” በማለት ራሱ ግራ ተጋብቶ በርካታዎችን ግራ ሲያጋባ ተደመጠ።
የብራዚሉ ጠያቂው ያቀረቡት ጥያቄ ከሰሃራ በታች ካለች የምታድግ አገር (ከአውሮጳ ደቡብ) የመጣህ ሆነህ ድርጅቱን እንዴት እንደምትመራ ያቀረብከው የማብራሪያ ጽሁፍ ደግሞ የምዕራቡን ዓለም (የሰሜኑን) አጀንዳ የሚያንጸባርቅና የሚደግፍ ነው ይህንን እንዴት ታስታርቀዋለህ የሚል ነበር። ጠያቂው በግልጽ እንግሊዝኛ ነው የጠየቁት፤ ጥያቄውን ዕጩ ተወዳዳሪ ያልሆነ ማንም ሰው ሊረዳው የሚችል ነበር። ቴድሮስ ግን “አልገባኝም ይደገምልኝ” አለ። ጠያቂው ባጭሩ ጥያቄያቸውን ደገሙ። ቴድሮስ አሁንም “ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማያያዝ ነው የጠየከኝ” በማለት ጠያቂውን መልሶ ይጠይቃል፤ ብራዚላዊው ጠያቂ በጠየቁት ቀላል ጥያቄ የቴድሮስ መንተባተብ አስፈገጓቸው “እኔ የሁለትዮሽ ንግግር (ዳያሎግ) ለማድረግ አይደለም …” በሚሉበት ወቅት ሰብሳቢው ጣልቃ በመግባት ለሦስተኛ ጊዜ ጥያቄውን ያስረዳሉ፤ በሁኔታው እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን ደፍተዋል፤ አፍረዋል። (በወቅቱ ጎልጉል የሠራው ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)።
በቀጣይ በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ታሪክ የሕክምና ዲግሪና ትምህርት የሌለው የመጀመሪያው የዓለም ሕዝብ “ሐኪም” ሆኖ ቴድሮስ አድሃኖም በዳይሬክተርነት ተመረጠ። ያልተመለሰ ጥያቄ ግን አለ፤ ቴድሮስ ለዳይሬክተርነት ያቀረበውን የማብራሪያ ጽሁፍ የጻፈው ማነው?
በፍጥነት ዛሬ ላይ ስንመጣ ማርች 25፤ 2020 ፕሬዚዳንት ትራምፕና የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቡድናቸው በነጩ ቤተመንግሥት (ኋይት ሐውስ) መግለጫ እየሰጡ ነው፤ ጋዜጠኛው ይጠይቃል፤ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛና የምክርቤት አባላትን ስም በመጥቀስ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትና ቻይና ያላቸው ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፣ እንደ ፖለቲከኞቹ አባባል የሁለቱ ግንኙነት ቀይ መብራት እያሳየ ነው፤ ድርጅቱ ለቻይና ወገንተኝነት እያሳየ ነው ብለው ያምናሉ? የዚህ በሽታ ጉዳይ ሲሰክን አሜሪካ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነት መመርመር ይገባታል ብለው ያምናሉ? በማለት ጋዜጠኛው ፕሬዚዳንቱን ይጠይቃል።
ትራምፕ ይመልሳሉ፤ ወገንተኝነት እንዳለ በደንብ የሚታወቅ ነው፤ ይህንን ማንም የሚክደው እንዳልሆነ አስረግጠው ከተናገሩ በኋላ ዕድሉን ለዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ይሰጣሉ፤ ይህንን ሲያደርጉ ትራምፕ፤ “በዚህ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ መግባት ትፈልጋለህ?” በማለት ፋውቺን እየጠየቁ ነበር መነጋገሪያውን የለቀቁት።
የ2020 ዓመታዊ በጀቱ 6ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚጠጋውን የአሜሪካን የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ኤጀንሲን (National Institute of Allergy and Infectious Diseases) በአሜሪካ ባልተለመደ ሁኔታ ያለተቀናቃኝ ላለፉት 36ዓመታት ሲመሩ የኖሩት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ወደመነጋገሪያው መጥተው ተናገሩ። ንግግራቸው ዋነኛ ትኩረቱ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ለቻይና አድልዖ ስለማድረጉ ሳይሆን ቴድሮስ አድሃኖምን ስለ መከላከል ነበር። “ቴድሮስን ገና የ(ኢትዮጵያ)ጤና ጥበቃ ሚ/ር የነበረ ጊዜ አውቀዋለሁ፤ …” በማለት ገድለ ቴድሮስ ተናገሩ። ሞጋቹ ጋዜጠኛ “እና ቻይና በሽታውን በተመለከተ ግልጽነት ነበራት ተብላ (በቴድሮስ መሞገሷ) እሱስ እንዴት ነው?” ይላል። ፋውቺ ሲመልሱ “ስለ ቻይና እያወራሁ አይደለም፤ የጠየቅኸኝ ስለ ቴድሮስ ነው” በማለት ጋዜጠኛው ያልጠየቀውን ነገሩት። ጋዜጠኛው አላቆመም፤ “የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ይህንን ወረርሽኝ በመከላከል ቻይና ያሳየችውን ግልጽነትና አመራር አሞግሷል” ይላል። ፋውቺም “በዚያ ላይ አስተያየት መስጠት አልችልም፤ እንዲያውም አመለካከትም የለኝም፤ እንዲያውም ጥያቄህ ራሱ ምን እንደሆነ አልገባኝም” በማለት ጉዳዩን ለማወዛገብ በመሞከር ከቴድሮስ ጋር ከጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱ ጀምሮ የተወዳጁ መሆናቸውን ባልተገመተና ባልተጠበቀ ሁኔታ ይፋ አደረጉ። ይህ መልሳቸው ቴድሮስ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተር እንዲሆን የተጫወቱት ምሥጢራዊ ሚና ምን ይሆን? ብሎ የሚያስጠይቅ ነበር።
ቴድሮስና በኢትዮጵያ የተከሰተው ኮሌራ ምሥጢር
ወቅቱ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ነበር፤ ከቻይና ጋር በመተባበር በተደረገ ከፍተኛ የህወሓት ድጎማና ድጋፍ ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ዘመቻ ላይ ነው። በዚህ ወቅት አንድ ያልታሰበ ዱብዕዳ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አወጣ። ርዕሱ እንዲህ ይነበባል፤ “የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን ለመምራት የሚወዳደረው እጩ ወረርሽኝ በመደበቅ ተከሰሰ”።
ምሥጢሩን ይፋ ያደረጉት በወቅቱ የቴድሮስ ተፎካካሪ የሆኑት የዶ/ር ናባሮ ኢ-መደበኛ አማካሪና በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ የኦኒል የብሔራዊና ዓለምአቀፍ የጤና ሕግ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ሎውረንስ ጎስቲን ናቸው። ጎስቲን እንደሚሉት እኤአ 2005 – 2012 ቴድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረበት ዓመታት ውስጥ በ2006፣ 2009 እና 2011 በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ይፋ እንዳይሆን በምሥጢር እንዲያዝ አድርጓል፤ ይህም ዓለምአቀፉን የጤና ጥበቃ ድርጅት እንዳይመራ ከበቂ በላይ ምክንያት መሆን ይችላል የሚል መከራከሪያ ነው።
ቴድሮስ አድሃኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረባቸው ዓመታት ጎስቲን በሚመሩት ተቋም ጥሪ እየተደረገለት በጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ “የተከበሩ” ተብሎ ንግግሮችን ሲያደርግ ቆይቷል። ይህ ዓይነቱን የምዕራባውያን “ወዳጅነት” ነበር ቴድሮስ እንደ ብቃት መለኪያ አድርጎ ሲያቀርብ የነበረው።
የዛሬ ዐሥራ ሦስት ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ የኮሌራ በሽታ ተነስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 700 ያህል ሕዝብ ሲያልቅና ከ60ሺህ በላይ በበሽታው ሲጠቃ የህወሃት ሹሞች “ውሃ ተቅማጥ” ነው ከማለት ባላለፈ የበሽታውን መከሰት ሲክዱ ነበር። ዜናው በዓለምአቀፍ ሚዲያ ላይ ቢዘገብም “የድርብ አኻዝ” ዕድገት ስሌቱን የሚያዛባና ቱሪዝምን የሚደናቅፍ ሆኖ በመገኘቱ የሰዎች መሞት ለህወሃት ብዙም አላስጨነቀውም። ቴድሮስም በወቅቱ ከአውሮጳና አሜሪካ የሚሰጠውን ትዕዛዝ በመፈጸም ተግባር ተጠምዶ “ዛሬን (ምርጫውን)” አላሰበም ነበር። ይኸው በሽታ በቀጣይ“አተት” (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) የሚል የቁልምጫ ስም ተሰጥቶታል። ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺም “ቴድሮስን ገና የጤና ጥበቃ ሚ/ር የነበረ ጊዜ አውቀዋለሁ” በማለት የሰጡት ምስክርነት ይህንን ጊዜ የሚጠቀልል እንደሆነ ልብ ይሏል።
የኮሌራ ወረርሽኝ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት ወቅት ከህወሃት/ኢህአዴግ የበላይ ሹሞች ሚዲያውም ሆነ የጤና ሠራተኞች “ኮሌራ” የሚለውን ቃል እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም በድብቅ እንዲወጣ በተደረገ የሰገራ ናሙና ምርመራ በርግጥ የኮሌራ ወረርሽን ለመከሰቱ ዓለምአቀፍ የጤና ባለሙያዎች ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ዘገባው በዝርዝር እንደሚያስረዳው ከዚህ በፊት የበሽታው ወረርሽ ታይቶባቸው በማይታወቀው በጉጂ፣ በባሌ እና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች እኤአ ከሴፕቴምበር 15 እስከ ኦክቶበር 9፣ 2006ዓም (መስከረም5 እስከ 29፤1999ዓም) ቦታዎቹን የቃኙና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች ኮሌራ በአካባቢዎቹና አጎራባች ክልሎችና ዞኖች መከሰቱን አረጋግጠዋል። (ኒው ዮርክ ታይምስ የጠቀሰውን የባለሙያዎቹን ዘገባ እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ጎልጉል ያቀናበረው ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)።
ቴድሮስ ስለ አይሲስ ሰለባዎች – “ድርጊቱን እያጣራነው ነው”
ወቅቱ የአገራችን ሕዝብ በሐዘን ቅስሙ የተሰበረበት ነው፤ ቴድሮስ አድሓኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር። አይሲስ የተባለ በቃላት ለመግለጽ የማይቻል ቡድን ከአእምሮ በላይ የሆነ ግፍ በመፈጽ ዓለምን ያስጨነቀበት ጊዜ ነበር።
በወቅቱ በሊቢያ የሚገኘው የአይሲስ ተወካይ ቡድን 30 ኢትዮጵያውያንን አረደ፤ በጥይት ረሸነ። የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ዘገባውን አቀረቡ፤ ኢትዮጵያውያን መታረዳቸውን አወጁ፤ ዓለም ቪዲዮውን ተመለከተው፤ ዜናውን አነበበው። ጎልጉልም ዜናውን እዚህ ላይ ዘግቦታል።
የዓለም ሕዝብ አዘነ፤ ኋይት ሃውስ እንኳን ወዲያው መግለጫ ሰጠ፤ ድርጊቱን ኮነነ፤ ከሰብዓዊነት በታች፤ ዘግናኝ፣ ፍጹም አረመኔያዊ፣ ጨካኝና ስሜት አልባ በማለት አወገዘው። ኢትዮጵያውያኑ የተገደሉት በሃይማኖታቸው ምክንያት መሆኑን በግልጽ ተናገረ፤ ሆኖም ይህ የአሸባሪዎች ድርጊት የእምነት ተከታዮችን በአንድነት አሸባሪነትን እንዲታገሉ የሚያስተባብራቸው ሊሆን ይገባል በማለት በሃይማኖቶች መካከል ተጨማሪ ግጭትና መከፋፈል እንዳይፈጠር አሳሰበ።
የመስቀል ማተብ ያሰሩ መልካቸው፣ ገጽታቸው፣ ሁለንተናቸው አበሻ መሆናቸውን በሚመሰክረው የ29 ደቂቃ ቪዲዮ ኢትዮጵያውያን ለዕርድ ሲሰለፉ፤ ለጥይት ሲማገዱ ዓለም ተመለከተ። በወቅቱ ጎልጉል በቀጥታ ከቤተሰብ ማጣራት ባይችልም ባገኘው መረጃ መሠረት በቪዲዮው ላይ ወንድሟን የተመለከተች ኢትዮጵያዊት መኖሯን መረጃ ደርሶን ዘግበናል።
በወቅቱ በህወሃት የሚመራው ኢህአዴግ በእሁድ ምሽት ዜናው ላይ በጣም ተዝናንቶ ጉዳዩን እንደ አንድ ተራ ዜና ከረጅሙ የዜና እወጃው ሰዓት ውስጥ ጥቂት ደቂቃዎችን ሰጥቶታል። ያውም የቀደመው ሌላ ዜና አለ – “የልማት ዜና!”
በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ዜናውን ልክ ሁላችንም በዓለም የዜና ማሰራጫዎች እንደሰማነው ህወሓት/ኢህአዴግም በዚያው ሁኔታ መስማቱን ተናገረ፤ የዜናው አቀራረብ ሰላሣ ዜጋ የሞተበት መንግሥት ስሜት የሚታይበት አልነበረም። የራሱ ዜጎች ይቅርና በሌላ የዓለም ክፍል ሰው እንደሞተ ያልቆጠረ አቀራረብ ነበር። በወቅቱ “የፌስቡኩ ፍንዳታ” እየተባለ ይጠራ የነበረው ቴድሮስ አድሓኖም አይሲስን ደውሎ ለመጠየቅ ያሰበ ይመስል ስለ ሟቾቹ ሲጠየቅ የመለሰው “ድርጊቱን እያጣራ ነው” በማት ነበር።
ቴድሮስ – “እኔ ወያኔ ነኝ”
ወቅቱ በህወሓት አፋኝነት የተማረሩ ኢትዮጵያውያን ከአገር ወጥተው፤ ልክ የሌለው የመከራ ግፍ የተቀበሉበት ነበር። ወቅቱ አረመኔው አይሲስ በግፍ የጨፈጨፋቸው ወገኖቻችን መርዶ ከመሰማቱ ጥቂት ሳምንታት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጊዜው ተገንጣዩ የወንበዴዎች ቡድን ህወሓት አገር ለመገንጠል የተመሠረተበት ክብረበዓልም ነበር። የዛሬውን አያድርገውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንኑ ክፋት የተጠነሰሰበትን ቀን በግድ እንዲያከብር ይደረግ ነበር።
ጊዜው መሳ ለመሳ ደቡብ አፍሪካውያን በ“መጤ ጠል” መንፈስ ተነሳስተው ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ጎማ ውስጥ እያስገቡ ያቃጠሉበት፤ ንብረት የዘረፉበት፤ አሰቃቂ ግፍ የፈጸሙበት ሲሆን፣ እንደዛሬው በደል የተፈጸመበት አገር ድረስ ሄዶ የሚታደግ ጠቅላይ ሚኒስትር የሌለባት አገር ነበረች ኢትዮጵያ። ይህ ሁሉ ሲሆን ቴድሮስ አድሓኖም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር።
ቴድሮስን ከሌሎቹ የህወሓት አንጋፋ ነፍሰበላዎች ለየት አድርጎ በማየት፤ ዘመናዊና ‘‘የገባው’’ ነው ብለው በማሰብ ሰዎች ብዙ ተስፋ የጣሉበት ጊዜ ነበር። ሌሎች ደግሞ ዋጋ የሌለው ወያኔ ነው በማለት የስድብ ናዳ የሚያወርዱበትም ነበር። በደቡብ አፍሪካው የጭንቅ ጊዜ ቴድሮስ አፋጣኝ ዕርምጃ ካለመውሰዱና ሁኔታውን አቅልሎ በማየት የተናገረው ነጭ ውሸት እጅግ ያሳዘናቸው ወገኖች “ወያኔ ነው” በማለት ድምጻቸውን እያሰሙ የነበረበትም ጊዜ ነበር።
ለዚህ ምላሽ በሚል በረከት ስምዖንን በመጥቀስ ቴድሮስ አፕሪል 18, 2015 በፌስቡኩ የጻፈውን በኦፊሺያል የትዊተር ገጹ ላይም ሼር አድርጎት ነበር። አሁን ፌስቡኩ ላይ ያወጣውን ሠርዞታል። የቴድሮስ መልስ እንዲህ ይል ነበር፤
“አንዳንድ ወገኖች ደቡብ አፍሪቃ ላሉት ወገኖች እየሰጠን ያለውን ድጋፍ ሳስረዳ ስድብ መስሏቸው “ወያኔ አሉኝ”። ከጥቂት አመታት በፊት ለተመሳሳይ ጉዳይ በረከት ስምዖን ያለውን አስታወሱኝ “ሁላችንም ወያኔ ነን” አዎ አሁንም ሁላችንም ወያኔን ነን። ወያኔነት ልማት፣ ኩራትና ዴሞክራሲ ነው። እኔ ወያኔ ነኝ! ሁላችንም ወያኔ ነን! ይህን ችግር የሚፈታውም ወያኔነት ነው! በትክክለኛ የእድገትና የልማት አቅጣጫ ነው ያለነው” የሚል ምላሽ ነበር ፖስት ያደረገው። ይህ እንደ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳይሆን እንደ አንድ ጎሠኛ የተሰጠ መልስ፤ ፖለቲካዊ አመለካከት ሳይሆን በደም የዘለቀ፤ ከሥጋና ነፍስ ጋር የተዋኻደ ዕምነት ነው። ይህ ማንነት ነው እንግዲህ ዛሬ ላይ ደርሶ ዘረኝነትን ተቃዋሚ ለመምስለ የሚፍገመገመው። በብዙ መልኩ የተጋመደን ያንድ አገር ማንነት በቋንቋና በጎጥ ከፋፍሎ ሲያምን የኖረ ግለሰብ አሁን የጥቁር ሕዝብ መብት ተነካ ብሎ ለመሟገት የሞራል ብቃቱን የሚያገኘው ከየት ይሆን?
ቴድሮስና በአማራ ላይ የደረሰው ግፍ
ወቅቱ ከአንድ አገር ውስጥ አንድ ሕዝብ ተነጥሎ “ጠላት” ተብሎ ተሰይሞ ከቀዬው ማፈናቀል እስከ ጅምላ ጭፍጨፋ የተካሄደበትና ይህም የግፍ ጥግ ላይ የደረሰበት ነበር። ቴድሮስ አድሓኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተብሎ ለህወሃት እየሠራና የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን በርቀት የሚያይበት ነበር።
ሐምሌ 2007ዓም ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ትዝታ በላቸው ለቴድሮስ ቃለ መጠይቅ ታደርጋለች፤ ቴድሮስ ይመልሳል፤ ትዝታ አትሞግትም፤ ይልቁንም ደጋፊና አዛኝ ቃላትን በማቀበል በመደመም ትሰማለች።
በዘር፣ በብሔርና በጎሣ ላይ ተንጠልጥሎ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የቆየው ህወሓት/ኢህአዴግ፣ በ1983 ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በገሃድ አማርኛ ተናጋሪዎችን ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በማናከስ፣ ቂም በማቋጠር፣ የስርዓተ ማኅበር ችግሮችን ከነፍጥ ጋር በማያያዝ እያላከከባቸው፣ “ነፍጠኛ” የሚል ስም በመስጠት የሕዝብ ንብረት በሆነው መገናኛ የጥላቻ ዘመቻ በማራገብ ያደረሰው ጥፋት ሰፊ ነው። የኢህአዴግ የቀድሞ አመራሮች በተለያዩ አጋጣሚዎቸ ይፋ እንዳደረጉት ይህንኑ አማርኛ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍል ለይቶ የማጥፋትና የማጥቃት ዕቅድ በማኒፌስቶና ፕሮግራም ደረጃ የተቀመጠ ነው።
ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለኅልፈት የተዳረጉት “አማራው ተሟጋች አጣ” በሚል ስለ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በቂም ተወልዶ፣ በቂም እዚህ የደረሰው ህወሓት/ትህነግ ከዚህ ከማይደበቀው ታሪኩ ፊት ለፊት ቆሞ “እንዴት ቂመኛ አይደለሁም ሊል ይቻለዋል” የሚሉ ወገኖች ቴድሮስ አድሃኖምን ለመታዘብ ጊዜ አልወሰዱም።
“ደርግ ያለ ርህራሄ 60 ሚኒስትሮችን ረሸነ፣ የውሻ ያህል እንኳን ክብር አልሰጣቸውም … ኢህአዴግ በመሆኔ ደስ የሚለኝ ቂመኛ ድርጅት ባለመሆኑ ነው” በማለት ቴድሮስ ሲመጻደቅ ትዝታም እንደ ለቅሶ ደራሽ አብራ ታስተዛዝን ነበር። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከተማ ሽርሽር እንደሚወጣና የአዳማን ልማት ተመልክቶ መደሰቱን በቃለ ምልልሱ የጠቆመው ቴድሮስ ይህ ሁሉ ኢህአዴግ ቂመኛ ድርጅት ላለመሆኑ ማሳያ ይሆን ዘንድ ማስረጃ ሲያደርግ አሁንም እንደ ሰልስተኛ የድጋፍና የምስጋና እንጂ የሙግት ዐውድ አልገጠመውም።
ቴድሮስ በቃለምልልሱ የጠቀሰው ሌላ ጉዳይ የአርበኞች ግንቦት ሰባት እና የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ኤርትራ መሄድ ነበር፤ “(ብርሃኑ) የሚያመጣው ነገር የለም። እርግጠኛ ነኝ የሚፈይደው ነገር የለም። ዜሮ፣ ፕሮፓጋንዳ ከመሆን ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም” ሲል ግንቦት 7ንና ዶ/ር ብርሃኑን አጣጥሎ ነበር።
የአማራን ሴቶች በማምከን የዘር ጭፍጨፋ በአማራው ላይ ተካሂዷል ብለው የሚሞግቱ ይህንን ተግባር በመፈጸሙ ሥራ ላይ ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረበት ጊዜ ከነቢል ጌትስ የሚሰጠውን መመሪያ የሚያስፈጽም የግሎባሊስቶች “ተላላኪ” ነው በማለት የሰላ ሒስ ያቀርባሉ።
ቴድሮስ – የሕክምና ዶክተር ሳይሆን የመጀመሪያው የዓለም “ሐኪም” የሆነ
በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት የ70ዓመታት ታሪክ የሕክምና ዶክተር ሳይሆን የድርጅቱ ዳይሬክተር የሆነው ብቸኛው ቴድሮስ አድሓኖም ነው። ድርጅቱን ባለፉት ዓመታት የመሩት የተለያዩ ዳይሬክተሮች የሕክምና ዲግሪ ያላቸው በመሆኑ ምክንያት ነው “ዶክተር” እየተባሉ የሚጠሩት።
ቴድሮስ አድሓኖም በተወለደበት የኤርትራ ክፍልሃገር (በዚያን ጊዜ አጠራር) የመጀመሪውን ዲግሪ ከአስመራ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ካገኘ በኋላ ወደ እንግሊዝ አገር በመሄድ ከሎንዶን ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ በሳይንስ እንዲሁም በኖቲንግሃም ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በማኅበረሰብ ጤና የዶክትሬት ዲግሪ ተቀብሏል። ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያው የጻፈው ዋና ትኩረቱ በትግራይ ክልል ማሌሪያ (ወባ) እንዲሰራጭ ግድቦች ያስከተሉት ተጽዕኖ በሚል ነው።
በአገራችን ዶክትሬት ዲግሪ (ፒኤችዲ) ያላቸውን ሰዎች “ዶክተር” ብለን መጥራት የተለመደ ቢሆንም በዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት የ70 ዓመታት አሠራር መሠረት የሕክምና ዲግሪ (ዶክተር ኦቭ ሜዲሲን ዲግሪ) የሌለው “ዶክተር” ተብሎ አይጠራም። ይህንን እያወቀ ቴድሮስ ግን ራሱን “ዶክተር” እያለ መጥራቱን እንደ ማጭበርበር በመውሰድ የሰላ ነቀፋ የሚያቀርቡ የሚዲያ ተቋማት ጥቂት አይደሉም። የቴድሮስ የማኅበራዊ ገጾች መጠሪያ “@DrTedros” የሚል መሆኑ “በግድ ዶክተር” ተብዬ ልጠራ የማለት ያህል አድርገው በመውሰድ በርካታዎች ድርጊቱን ይነቅፋሉ።
ቴድሮስና የቻይና ፍቅር በነቢል ጌትስና የክትባት ኩባንያዎች ደጋሽነት
አምስተኛዋ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኖርዌይቱ ዶ/ር ግሮ ሐርለም ብረንትላንድ ነበሩ። ዶ/ር ግሮ ድርጅቱን በመሩበት ወቅት እኤአ በ2003 ዓም ከአሁኑ ኮቪድ-19 ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሳርስ (SARS) የተባለ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ቫይረስ በቻይና ይከሰታል። ይህ በሆነበት ወቅት በድርጅቱ የ55 ዓመት ታሪክ ባልተለመደ ሁኔታ ዶ/ር ግሮ ወደ ቻይና ደቡባዊ ክፍልና ከዚያ ወደሌላው የዓለም ክፍል የሚደረግ የጉዞ ዕቀባ አወጁ። ይህም ለወራት የቆየው ዕቀባ ቻይናን የተዳፈረ ተግባር ተደርጎ በኮሙኒስት መሪዎቹ ተወሰደ።
ቻይና በጤና ጥበቃ ድርጅቱ ላይ ዓይኗን በማድረግ ከእንግዲህ ወዲህ በሽታ በተከሰተ ቁጥር ጥቅሟን አደጋ ላይ የማይጥል ዳይሬክተር በማስቀመጡ ተግባር ላይ መትጋት ያዘች። በቀጣይ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሊ ጆንግ-ዉክ ሲሆኑ እርሳቸው በድንገት ሲሞቱ ለስድስት ወር ድርጅቱን በተጠባባቂነት ስዊድናዊው ዶ/ር ኖርድስትሮም መርተዋል፤ እርሳቸውም የሕክምና ዶክተር ነበሩ።
በቀጣይ ቻይና ተጽዕኖዋ የጨመረ ሲሆን ከቴድሮስ በፊት ድርጅቱን የመሩት ቻይናዊቷ የካናዳ ዜጋ ዶ/ር ማርጋሬት ቻን ናቸው። ዶ/ር ቻን በሥልጣን ዘመናቸው ከሚጠቀሱላቸው አሳዛኝ ተግባራት የበፊቷ ዳይሬክተር ዶ/ር ግሮ “በመደርመስ ላይ ያለ” በማለት የጠሩትን የሰሜን ኮሪያን የጤና ሥርዓት ዶ/ር ቻን “ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ አገራት ሊቀኑበት የሚገባ ሥርዓት” በማለት ማሞካሸታቸው ነበር።
ከዚህ ሌላ የዶ/ር ቻንን የሥልጣን ዘመን ጥላሸት የቀባ አሣፋሪ ተግባር ተፈጽሟል። የአሣማ አንፍሉዌንዛ “H1N1” በመባል የሚጠራ በሽታ ትኩረት እየሳበ በመጣበት ወቅት ማርጋሬት ቻን በሽታውን “ወረርሽኝ ነው” በማለት አስቸኳይ የጤና አዋጅ ያውጃሉ። ይህንን ተከትለው መንግሥታት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማፍሰስ ክትባት እንዲገዙ ይሆናሉ። አቧራው ጨሶ ካባራ በኋላ ሁኔታው ሲታይ በጣም የተወራለት የአሣማው ኢንፍሉዌንዛ የገደለው ሕዝብ ብዛት ከመደበኛው ኢንፍሉዌንዛ በምንም እንዳልተለየ ይደረስበታል። ጉዳዩ ሲመረመር የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን በኢንፍሉዌንዛ ጉዳይ የሚያማክሩት ፕሮፌሰር አልበርት ኦስቴራሆስ እና ሌሎች የድርጅቱ አማካሪዎች ከትልልቅ መድኃኒት ማምረቻ ድርጅቶች (GlaxoSmithKline, Novarti ወዘተ) ቀጥተኛ የገንዘብ ጥቅም የሚያገኙ መሆናቸው ይረጋገጣል። አስቸኳይ አዋጁም የሐሰት መሆኑ ይፋ ይወጣል።
ይህ በጤና ድርጅቱ፣ በአማካሪዎቹና በመድኃኒት አምራቾቹ መካከል ያለው የጥቅም ትሥሥርና የጥቅም ግጭት ቴድሮስ ዳይሬክተር በሆነበት ዘመንም ቃል እንደገባው ሊያጸዳው ያልቻለ የሙስና “አጀንዳ” ሆኖ ቀጥሏል። የጤና ጥበቃ ድርጅቱን በሳይንሳዊ ምርምር ረገድ ምክር የሚሰጠው Scientific Advisory Group of Experts (SAGE) የሚባለው ቡድን አባላት ከክትባት አምራች ድርጅቶች ወይም ከቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጎማ የሚያገኙ ናቸው። ከ15ቱ የSAGE አባላት 8ቱ ከቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋንዴሽን እና ከሌሎች የመድኃኒት እና የክትባት ማምረቻዎች (መርክ (Merck & Co. (MSD)፤ ጋቪ (Gavi) የክትባት ኅብረት ኩባንያ (the Vaccine Alliance (የቢል ጌትስ ድርጅት የገንዘብ ድጎማ የሚያደርግለት ነው)፤ የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የጤናና ሳይንስ አማካሪ ኮሚቴ (BMGF Global Health Scientific Advisory Committee)፤ ፋይዘር (Pfizer)፤ ኖቮቫክስ (Novovax) ጂኤስኬ (GSK)፤ ኖቫርቲስ (Novartis) እና ጊልዓድ (Gilead) በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገንዘብ ጥቅም የሚያገኙ ናቸው።
ባለንበት ዘመን የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን በገንዘብ የሚደጉሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ሳይሆኑ “የሕዝብና የግል ትብብር” “ፒፒፒ” (public-private partnership) በሚባለው መርህ መሠረት የግል ድርጅቶች እንደ ጌትስ ፋውንዴሽን ዓይነቶች ናቸው። ቴድሮስ አድሓኖም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ለዕጩነት በቀረበበት ጊዜ ይህንን የፒፒፒ ግንኙነት በመከተል የድርጅቱን የበጀት ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚሠራ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል።
የጤና ጥበቃ ድርጅቱ የ2017 የፋይናንስ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአጠቃላይ የበጀት ፈንድ ካገኘው 2ቢሊዮን ዶላር ከግማሽ የሚበልጠውን ያገኘው ከግል ለጋሾችና ሌሎ ተቋማት ነው። መንግሥታዊ ካልሆኑ የግል ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የጌትስ ፋውንዴሽን እና ከዚያ ጋር ቁርኝት ያላቸው (GAVI Vaccine Alliance, the Gates-initiated Global Fund to Fight AIDS, Tuberculosis and Malaria (GFATM)) ኩባንያዎች ናቸው። እነዚህ ሦስት ድርጅቶች በድምሩ 474 ቢሊዮን ዶላር ለጤና ጥበቃ ድርጅቱ “ለግሰዋል”፤ ከዚህ ውስጥ የጌትስ ፋውንዴሽን 324,654,317 ዶላር “ለግሷል”። ከዚህ ጋር ሲነጻጸር በአገር ደረጃ ትልቁን ገንዘብ የምትሰጠው አሜሪካ ለድርጅቱ በ2017 የሰጠችው 401 ሚሊዮን ዶላር ነው።
የቻይና አገራዊ የጥቅም ፍላጎትና የድርጅቱ “ለጋሾች” የጥቅም ትሥሥር ቴድሮስ አድሓኖምን ለመመረጥ እንዳበቃው የሚስማሙ ጥቂቶች አይደሉም። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበረበት ወቅት ቴድሮስ የጌትስ ፋውንዴሽን ከሚመራቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነው Global Fund Against HIV/AIDS, TB and Malaria የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ሲያገለግል በትንሹ በዓመት የሩብ ሚሊዮን ዶላር ተከፋይ ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጨረፍታ ቢሆን ጠቁሞ ለማለፍ የቢል ጌትስ ልጅ ኢትዮጵያ ስትመጣ የምታርፈው ቴድሮስ በሠራው ባለፎቅ ቤት ውስጥ እንደሆነና ከቴድሮስ ቤተሰቦች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላት፣ እንደማይለያዩም ጎልጉል ከህወሓት ታማኞች በቅብብል የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ቴድሮስ፣ ኮቪድ-19 እና ቻይና
ድህረ የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ምርጫ፤ የቻይና እና የቴድሮስ ወዳጅነት በህወሓት ገመድ ተደራርቦ የተገመደና የታሠረ ነው። ቻይና የምትፈልገውን ለማከናወን በኢትዮጵያ ፈቃድ የሰጣት ህወሓት በመሆኑ የወደፊቱ የዓለም ጤና ድርጅት መሪ እሷ የምትፈልገው ሰው እንዲሆን መሥራት ከጀመረች ቆይታለች። ቻይና ከዚህ በፊት በዶ/ር ግሮ የተጣለባት የጉዞ ዕቀባ በምንም ዓይነት ሁኔታ እንዲደገም አትፈልግም። ስለዚህ ከህወሓት ጋር ተዋውላ ቴድሮስን ወደ ሥልጣን ማምጣት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖላታል። ስለዚህ ቴድሮስ እንዲመረጥ በርካታ ውስወሳና መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ቻይና ቁልፍ ሚና መጫወቷን ዋሽንግተን ፖስት በዓምዱ አስነብቧል።
ብዙም ሳይቆይ ቻይና ውለታዋን ማስከፈል ጀመረች። ቴድሮስ ዳይሬክተር በሆነ ጥቂት ወራት የዚምቧብዌውን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን የድርጅቱ “የበጎ ፈቃድ አምባሳደር” በማለት መምረጡን አስታወቀ። የካናዳው ጠ/ሚር ትሩዶ “መጥፎ የኤፕሪል ፉል ዴይ ቀልድ” ነው በማለት የቴድሮስን ምርጫ ሲሳለቁበት ሌሎች ግን አሳፋሪ፣ አስደንጋጭ፣ ግራ የሚያጋባ፣ ወዘተ በማለት ተቃውሞ አሰሙ። የተቃውሞ ውርጅብኙን ያልጠበቀው ቴድሮስ እስካሁን ለውሳኔው ይቅርታ ባይጠይቅም ተግባሩን ግን ሳይፈጽም ቀርቷል፤ ሃሳቡን ሰርዟል።
ችግሩ ያለው ሙጋቤ መመረጥ አለመመረጣቸው ላይ ሳይሆን ገና ከጥንስሱ ቴድሮስ እንዴት የቻይና ጥቅም አስጠባቂ እንደሆነ የሚመላክት መሆኑ ነው። ለሙጋቤ መመረጥ አሳማኝ ሆኖ የሚቀርበው መከራከሪያ ቻይና ወዳጃቸው ስለሆነች ሙጋቤን ለማስደሰት፤ የደረሰባቸውን ዓለምዓቀፍ ውግዘት ለማለስለስ፤ ያጡትን ድጋፍና ዕውቅና ለማስገኘት ቴድሮስን መጠቀሟ ነው።
ኮሮና ቫይረስ በዉሃን ቻይና ታይቷል በማለት የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት የተናገረው በዲሴምበር (ታህሣሥ) 2019 ነበር። ታይዋን በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ እንደሆነ ጉዳይ አስፈጻሚው ቴድሮስ ለሚመራው የጤና ጥበቃ ድርጅት በዲሴምበር ወር አስታወቀች። በሽታውን “የሳምባ ምች” በማለት የጠራው ድርጅቱ፤ የቻይና ባለሥልጣናት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ስለመተላለፉ ምንም ማስረጃ አላገኙም በማለት ለቻይና ጥብቅና ቆመ። ከሁለት ወራት በኋላ ነበር “ወረርሽኝ” በማለት በዓለምአቀፍ ደረጃ አዋጅ ያስነገረው። በዚህ መሃል በሽታው እየተስፋፋ በርካታዎችን እያሳመመ ሲመጣ የጤና ጥበቃ ድርጅቱ ግን በሽታው ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም በሚለው አቋሙ ጸንቶ ነበር። ይህ ሲሆን በቻይና የሚገኙ ሐኪሞችና የመረጃ ባለቤቶች በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና አደገኛ መሆኑን ሲናገሩ በኮሙኒስት አመራሮች ጸጥ ተደርገው ላይመለሱ አሸልበዋል።
ለቴድሮስ መመረጥ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰችውና ውስወሳ ያካሄደችው ቻይና እንደበፊቱ በሽታው በኢኮኖሚዋ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ቴድሮስን መጠቀም የግድ ስለሆነባት ቴድሮስ ቫት የሚከፍልበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም ጃኑዋሪ 30 ላይ ቴድሮስ “ለበሽታው ምላሽ ይሆን ዘንድ ቻይና አዲስ መመሪያ አውጥታለች” በማለት ተናገረ። ከዚያው ጋር አያይዞ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ጋር ከተገናኘ በኋላ ይህንን ንግግር አደረገ፤ “ይህንን በሽታ ትኩረት ሰጥታ ቻይና እያደረገች ያለውን ሁሉ ሳናደንቅ አናልፍም፤ በተለይ የበላይ አመራሮች ያሳዩት ቁርጠኝነትና ግልጽነት የሚያስመሰግናቸው ነው”። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የቻይናውን ፕሬዚዳንት ዢ ጂን ፒንግ ስለ በሽታው ያላቸውን ዕውቀት በማድነቅ “ቻይና (በሽታውን በመቆጣጠር) ዓለም ጊዜ እንዲገዛ አስችላለች” በማለት ሌላ የቫት ክፍያ አቀረበ። ሌሎች አገራት ቫይረሱን አስመልክቶ የሚያደርጉት ሲተች ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎች እንዳይቋረጡ ጥሪ አቀረበ፤ የቻይና ሚዲያም ቅኝቱ “ቴድሮስ! ቴድሮስ!” ሆነ። ይህም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እነ ተወልደ ገብረማርያም ወደ ቻይና የሚደረግ በረራ እንዳይቋረጥ ደጋፊ ምክንያት ሆነላቸው።
የጤና ድርጅቱ በሽታውን በቶሎ “ዓለምአቀፋዊ ትኩረት የሚያስፈልገው የበሽታ ወረረርሽ ነው” በማለት መወሰን በሚገባው ጊዜ ሳይፈጥን ቀረ፤ ሕዝብ ማለቅ ጀመረ፤ ሕይወት እንደ ቅጠል መርገፍ ጀመረ። ለዚህም ዋናው ምክንያት ቴድሮስ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር እንደመሆኑ በሽታውን “በቻይና አስቸኳይ ትኩረት የሚሻ” ብቻ በማለቱ፤ በዓለምአቀፍ ደረጃ ግን ይህንኑ ጠንከር ያለ ውሳኔ ሳያስተላልፍ በመቅረቱና ከዚያ ይልቅ “እንጠብቅ” በማለቱ ነበር። ሆኖም ከአንድ ሳምንት በኋላ ኮቪድ-19 ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ ነው ብሎ ቴድሮስ መግለጫ በሰጠበት ወቅት በሽታው በአስር ዕጥፍ ጨምሮ በ18 አገራት ተስፋፍቶ 7,781 ኬዞችን ያስመዘገበ ሆኖ ነበር። በድርጅታቸውና በቴድሮስ ውሳኔ ካዘኑት መካከል የድርጅቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ጆን ማኬንዚ ውሳኔው አስቀድሞ ይፋ ቢደረግ ኖሮ የዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ አጸፋ ምላሽ የተለየ ይሆን ነበር ብለዋል።
ቴድሮስና የተከፈተበት “ዘመቻ” (ፔቲሽን)
ቻይና ቴድሮን በመጠቀም ሊደርስባት የሚችለውን መገለልና የኢኮኖሚ ጉዳት ለመቋቋም ብትችልም በሽታው እየተስፋፋ መጥቶ በርካታ ሰዎችን ማሳመምና መግደል የቻለው ቴድሮስ ዋና ዳይሬክተር ሲሆን በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ቃሉን ሳይተገብር በመቅረቱ ነው፤ ከሥልጣኑ ሊወርድ ይገባዋል፤ በማለት ቻይና ሄዶ ከመጣበት የጃኑዋሪ ወር መጨረሻ ላይ የ1,000,000 ሰዎችን ፊርማ የሚጠይቅ ፔቲሽን ከተጀመረ በአሁኑ ጊዜ ከ850ሺህ በላይ ፊርማዎች ተሰብስበዋል።
ለዚህ ፔቲሽን መነሻ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ ቴድሮስ ለቻይና የሚያሳየው ወገንተኝነት ነው። ይህም በኮሮና ቫይረስ ሽፋን ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን የታይዋንንም ጉዳይ የሚመለከት ነው። ቻይና ላለፉት 40ዓመታት በላይ ታይዋን የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት አባል አገር እንዳትሆን ዕገዳ ስታደርግ ኖራለች። የምታቀርበው ዋና ምክንያት ደግሞ ታይዋን የቻይና ግዛት ነች የሚል ነው።
ይህ የቻይና አቋም ታይዋን ከድርጅቱ እንድትገለል ያደረገ ብቻ ሳይሆን ሌላም ከፍተኛ ጉዳት አለው። የጤና ጥበቃ ድርጅቱ መረጃ የሚለቅቀው ለአባል አገራት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤቶች በመሆኑ እንደ ታይዋን አባል ያልሆኑ አገራት የመረጃ ዕጥረት አለባቸው። ታይዋን ከድርጅቱ የሚሰጠውን መረጃ ለማግኘት በግድ የቻይናን ጤና ጥበቃ መለማመጥ አለባት። ሌላው የታይዋን ጉዳት የጤና ጥበቃ ድርጅቱ ታይዋንን እንደ አንድ የቻይና ግዛት አድርጎ በማየቱ በቻይና የደረሰው የበሽተኞችና የሟች ቁጥር የታይዋንም ተደርጎ በመወሰዱ ነው። ለምሳሌ በቻይና ቁጥሩ 70,000 ኬዝ እና ከ2,500 በላይ ሟቾች በነበረበት ጊዜ ታይዋን 0 (ዜሮ) ሟችና 32 ኬዝ ብቻ ነበራት። ከዚህ ጋር ተያይዞ እጅግ በርካታ አገራት በቻይና ላይ የበረራ ዕገዳ ሲጥሉ ታይዋንንም ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ በማድረግ ዕገዳ አድርገውባታል።
ይህ እና ሌሎች የጤና ጥበቃ ድርጅቱ መሪ ቴድሮስ ከቻይና ጋር በመመሳጠር የሚያደርገው የፖለቲካ ደባ ያስመረራቸው ታይዋናውያን የፔቲሽኑ ግንባርቀደም ደጋፊ ሆነው ወጡ። ቴድሮስ ሰሞኑን የሚያራግበው “የዘር ካርድ” እና ደጋፊዎቹና ጥቅመኞቹም እየተቀባበሉ የሚዘፍኑበት ጉዳይ ፈጽሞ ከታይዋን ጉዳይ ጋር የተገናኘ አይደለም። በቴድሮስ ላይ ዘመቻ የጀመሩት የታይዋን ዜጎች በቻይና ከደረሰባቸው ግፍ በመነሳት ያወጡት እንጂ በምንም ዓይነት ሁኔታ ከዘርና ከጥቁርነት ጋር የተገናኘ አይደለም። ለዚህ ማስረጃ ለሌለው የቴድሮስ ክስ ነው የታይዋን መንግሥት የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ታዋንን ይቅርታ መጠየቅ አለበት በማለት መግለጫ ያወጣው።
“እኔ ወያኔ ነኝ፤ መፍትሔውም ወያኔነት ነው” በማለት ሲመጻደቅ የኖረ ግለሰብ ዘረኝነትን ለማውገዝ የሚያስችል የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም። ዘረኝነት በደም የሚዘዋወር የልብ ተርታ፤ መቅኒ ድረስ የሚዘልቅ ረቂቅና ክፉ በሽታ ነው፤ የሥልጣን ጉልቻ ሲቀያየር አብሮ የሚቀየር ሊሆን አይችልም።
አሜሪካ አምርራለች
ቫይረሱ ቻይናንና አውሮጳን እያጠቃ በነበረበት ወቅት “ሁሉ ሰላም ነው፤ አታስቡ” በማለት ሕዝባቸውን ሲያረጋጉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ወቀሳ ከፖለቲከኞቻቸው እየመጣ ሲሄድ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመሩ። ሆኖም ገና ከጅምሩ ከቻይና ጋር በንግድ ጦርነት ውስጥ ገብተው የነበሩት ትራምፕ በሽታውን “የቻይና ቫይረስ”፤ “የዉሃን ቫይረስ” እያሉ ለመጥራት ፈጽሞ አላፈሩም ነበር።
የበሽታው መስፋፋትና በአውሮጳ ያደረሰው ጉዳት ያሳሰባቸው የአሜሪካ ፖለቲከኞች በቴድሮስና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ላይ የሰላ ትችት መሰንዘር ጀመሩ። የሕግ መወሰኛ ምክርቤት አባል ሴናተር ቴድ ክሩዝ የቴድሮስ ጉዳይ “በጥልቅ የሚያሳስብ ነው” በማለት ትዊት አደረጉ። ሴናተሩ ሲቀጥሉም ቴድሮስ “ገና የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚ/ር ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ከቻይና ጋር በቅርብ ይሠራ” የነበረ ሲሆን “የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚ/ር የነበረ ጊዜ ሦስት ጊዜ የኮሌራ ወረርሽኝን በመደበቅ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበት” የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተር የሆነ ነው ብለዋል። አያይዘውም ቴድሮስ ገና የሥልጣን መንበሩን እንደተቆናጠጠ ቻይናን ለማስደሰት ሲል አምባገነኑን ሙጋቤ “የበጎፈቃድ አምባሳደር” አድርጎ በመምረጡ ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ሃፍረት የተከናነበ፤ በተላላፊ በሽታዎች ሥልጠና የወሰደ ነገርግን የህክምና ዶክተር ያልሆነ ግለሰብ ነው ብለዋል።
ሴናተር ሩቢዮ እና እንደራሴ ማክኮል ደግሞ ሌሎቹ በቴድሮስ ላይ የ“ሥልጣን ይልቀቅ” ዘመቻ አራማጆች ናቸው። ሴናተር ሩቢዮ እንዳሉት “ቴድሮስ የዓለምን ጤና ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ሲገባው ለቻይና ሲያደላ ነው” የቆየው ብለዋል፤ የፈጸመው ተግባር “በጣም የሚረብሽና የሚያሳስብ” ነው በማለት አክለዋል። እንደራሴ ማክኮል ደግሞ የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ሰለባ ሆኗል ካሉ በኋላ “አሁን በመቶና በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከታመሙና ከሞቱ በኋላ የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ሙገሳ ሳይሆን ወቀሳ ነው የሚገባው፤ ይህንን ቀውስ የድርጅቱ ዳይሬክተር ቴድሮስ ደካማ በሆነ ሁኔታ መፈጸሙ ሥር የሰደደ የብቃት ችግር እንዳለ የሚጠቁምና የእርሱን ሐቀኛነት አደጋ ላይ በመጣል ቀይ መብራት የሚሳይ ነው” በማለት ቴድሮስን ከስሰዋል።
ጉዳዩ እየተፋፋመ ሲሄድ በቴድሮስ ላይ ሌላ የሰላ ሒስ ከመተቸት አልፈው ከሥልጣኑ መውረድ አለበት በማለት የተናገሩት ሴናተር ማርታ ማክሳሊ ናቸው። እርሳቸው እንደተናገሩት ቴድሮስ “ግልጽነት በጎደለው” አሠራሩ “ለቻይና ሽፋን በመስጠት ዓለምን አጭበርብሯል” ካሉ በኋላ “ይህ ለቻይና የተደረገው ሽፋንና ድበቃ ያልተፈለገ ሞት በአሜሪካና በዓለም ላይ እንዲከሰት ያደረገ በመሆኑ ዶ/ር ቴድሮስ ከሥልጣኑ መልቀቅ አለበት” በማለት ትዊት አድርገዋል።
ከእነዚህና ሌሎች የአሜሪካ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ዘመቻ በኋላ ቀድሞውኑ የቻይና ጉዳይ ያልጣማቸው ፕራምፕ አገራቸው ለጤና ጥበቃ ድርጅቱ የምትሰጠውን ዓመታዊ ድጎማ እንደገና እንደምትመረምር ተናግረዋል። ትራምፕ በንግግራቸው ድርጅቱ በጣም ለቻይና ያደላና ቻይና ላይ ትኩረት ያደረገ፤ ከለላና ሽፋን የሚሰጥ የተንሻፈፈ አመለካከት ያለው በማለት ከሰዋል። ይህ ጉዳይ በበርካታ የሕግመወሰኛና የምክርቤት እንደራሴዎች ግፊት ሲደረግበት የነበረ ሲሆን አሁን ያለው የቫይረሱ ሁኔታ አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ ምክርቤቱ በጤና ጥበቃ ድርጅቱ ላይ ምርመራ በማድረግ ውሳኔ ማስተላለፍ አለበት በማለት ሲወተውቱ የነበረውን የሚያጠናክር ሆኗል።
ለጤና ጥበቃ ድርጅቱ ድጎማ ከሚሰጡ አገራት የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው አሜሪካ በመሆኗ ይህንን ገንዘብ ከምትቀንስ ወይም ከምታቆም ቴድሮስ መልቀቅ እንዳለበት የጠነከሩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛል (በ2016-2017 ብቻ 945.6 ሚሊዮን ዶላር ለድርጅቱ ለግሳለች፤ ይህም ለድርጅቱ ከሚገባው የፈቃድ ልገሳ 76በመቶ ነው)። የቴድሮስና የቻይና ውለታ ግን በጤና ጥበቃ ድርጅቱ ብቻ የሚቆም ስላልሆነ ግፊቱ መቀጠል አለበት በማለት በስፋት የሚነበበው ፖለቲኮ (POLITICO) የተሰኘው ድረገጽ ተናግሯል። እንደ ድረገጹ አስተያየት ከሆነ ቴድሮስ ከዚህ በኋላ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የመሆን ፍላጎት አለው የሚባል ግምት ስላለ ለዚያ ደግሞ በመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ተጽዕኖ እያመጣች ያለችውን ቻይና ማሳዘን ስለማይፈልግ ጭምር ነው በማለት አዲስ መረጃ ጨምሮ አትሟል።
የኃያላኑ ፍጥጫና የቴድሮስ መጨረሻ
የ2020ዓም በጀቱ 6ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋው የአሜሪካንን የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ብሔራዊ ተቋም ላለፉት 36ዓመታት ያለተቀናቃኝ ሲመሩ የነበሩትና በእነዚህ ዓመታት ስድስት ፕሬዚዳንቶችን ያማከሩት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ናቸው። ባለቤታቸው ክሪስቲን ግሬዲም (ዶ/ር) የብሔራዊው የጤና ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸው። በየዓመቱ በአሜሪካ የሚከሰተውን ኢንፍሉዌንዛ ከዚያም ሲያልፍ ተላላፊ የሚባሉ በሽታዎችን ኤችአይቪ ኤድስ፣ ኢቦላ፣ ሳርሰ፣ ዚኪ፣ ወዘተ በተከሰተ ቁጥር ክትባት እንዲመረትና ዜጎች እንዲከተቡ መመሪያ በመስጠት የሚታወቁ ናቸው ዶ/ር ፋውቺ። መሥሪያ ቤታቸው ኃያላን ከሚባሉት ከታላላቅ የዓለማችን የክትባት መድኃኒት አምራቾችና የመድኃኒት ኩባንያዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው። እነዚህ ኩባንያዎች ደግሞ በተለይ የአሜሪካንን የምርጫ ፖለቲካ በሚፈልጉት መንገድ ቅኝቱ በማስተካከል ወደ እነርሱ ያጋደሉ ፖሊሲዎች እንዲወጡ የሚያደርጉ ፖለቲከኞችን እንዲመረጡ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ለምርጫ የሚያወጡ ናቸው (የመድኃኒት ፋብሪካዎች እኤአ ከ2008-2018 አጋማሽ 80ሚሊዮን ዶላር ለምርጫ ፖለቲካ አውጥተዋል፤ ባለፉት 20ዓመታት ደግሞ ፖለቲከኞችን ለመወስወስ 6ቢሊዮን ዶላር አፍስሰዋል)።
ፖለቲካና ጤና በጣም የተሣሠሩ መሆናቸው በርካታ ዜጎች የሚያስተውሉት ጉዳይ ባይሆንም አሁን በተለይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሕይወት ጉዳይ ፖለቲካን ባሳለጡ የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ላይ የወደቀ ለመሆኑ በግልጽ አሳይቷል። እነዚህን በየአገሩ የሚገኙ የጤና ተቋማትን እንደፈለጉ የሚያሽከረክሩት ኃያላኑ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎችና ከእነርሱ ጋር በተጓዳኝ የሚሠሩና በጥቅም የተሣሠሩ እንደ ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፣ የክሊንተን ግሎባል ኢንሺዬቲቭ፣ ወዘተ የመሳሰሉ የረድዔት ድርጅቶች ናቸው። የዓለም የጤና ጥበቃ ድርጅትን በተመለከተ ደግሞ ዋንኛ ተዋናዮቹ እነዚህ ታላላቅ ገንዘብ በቀላሉ ማምረት የሚፈልጉ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎችና ከእነርሱ ጋር የተስተጋበሩት ፖለቲከኞችና የጤና ተቋማት ናቸው።
ለአብነት ለመጥቀስ ያህል የኢቦላ በሽታ እየጨመረ መጣ በተባለበት ወቅት ዶ/ር ፋውቺ ኦክቶበር 6፤ 2014ዓም ዘ ካናዲያን ፕሬስ (The Canadian Press) ከተባለ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ክትባት አሠርተን አገራትን በሙሉ ማስከተብ ሊኖርብን ይችላል፤ ይህ ምናልባት አይተገበርም ሊባል ቢችልም መሆኑ ግን አሳማኝ ነው ብለው ነበር። የትኞቹን አገራት እንደሆኑ በስም ባይጠቅሱም ክትባትን በስፋት የማሰራጨት ሃሳብ በዓላማ ደረጃ የተቀመጠ ለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ ነው።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአሣማ ፍሉ (H1N1) ተነሳ በተባለበት ወቅት የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የሃሰት ማስጠንቀቂያ በማውጣትና ከክትባት አምራቾች ጋር በመመሳጠር ክትባት በማሠራት ቢሊዮን ዶላር እንዲመዘበር ምክንያት መሆኑን በተለያዩ ሚዲያ የተዘገበ ጉዳይ ሆነ አልፏል። ድርጊቱም የወቅቱ የጤና ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ማርጋሬት ቻንን አንገት ያስደፋ ሆኖ ነበር። ለዚሁ በሽታ ክትባት ይሆን ዘንድ የአሜሪካ መንግሥት 7.65 ቢሊዮን ዶላር በጀት መድቦ 6.15 ቢሊዮን ዶላር ለክትባት እና ከዚያ ጋር ለተገናኙ ቁሳቁሶች (መርፌና ሌሎች) እንዲወጣ መደረጉ በማስረጃ ተዘግቧል።
ቴድሮስ አድሓኖም ሲመረጥ ከፍተኛውን ድጋፍ ያደረጉት በሁለት የተለያየ ዓላማ ላይ ያሉ ቡድኖች ናቸው፤ እንደነ ቢል ጌትስ ያሉ ከክትባትና የመድኃኒት ኩባንያዎች ጋር የተወሳሰበ መስተጋብር ያላቸው ኃያላን እና በዓለም ላይ እያገኘች ያለውን ገናናነት ላለማጣት እየጣረች ያለችው ኃያል አገር ቻይና ናቸው። ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ድርጅቱ ዳሬክተር ለመሆን የምረጡኝ ጽሁፍ አድርጎ ያቀረበው ከምዕራባውያን ንጽረተዓለም የተጻፈ የሆነው ከዚህ አንጻር ነው የሚል አስተያየት የሚሰጠውም ለዚህ ነው። (በዚህ ዘገባ መጀመሪያ አካባቢ የተጠቀሰው ልብ ይሏል)። ከዚህ ጋር ተቆራኝታ የራሷን ጥቅም ለማስከበር ቻይና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰችው፤ ከእነዚህ ኃያላን የተባበረችው የዓላማ ሳይሆን የጥቅም ግንኙነት ስላስተሳሰራት ነው።
ዶ/ር ፋውቺ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር በመጻረር ስለ ቴድሮስ የሰጡት ምስክርነት በአሜሪካ የቀኝ ክንፍ ሚዲያ ዘንድ ከፍተኛ ነቀፋ እየቀረበበት ነው። ይህ የቀኝ አክራሪ ሚዲያ ደግሞ ለትራምፕ መመረጥ ቀኝ እጅ ሆኖ የሠራ ነው። በተጨማሪም የግራና የለዘብተኛውን ሚዲያ ትችት በማምከን ለፕሬዚዳንቱ ትልቅ ውለታ የሠራና እየሠራ ያለ ነው። በዚህ ምክንያት ይህ ክንፍ በዶ/ር ፋውቺ ላይ ጣት እየቀሰረ ይገኛል። ከዚህ ሲያልፍ ዶ/ር ፋውቺ የቻይና ጠበቃ ለሆነው ቴድሮስ የሰጡት ሙገሣ ምሥጢራዊና አነጋጋሪ በመሆኑ ዶ/ር ፋውቺ ይህንን ንግግራቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል በማለት የቀኝ ክንፍ ሚዲያው እየወተወተ ይገኛል። ከዚሁ የሙገሳ ንግግር በኋላ ለቃለምልልስ የተጠሩት ፋውቺ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በመቆም ለጤና ጥበቃ ድርጅቱ የሚሰጠው ገንዘብ እንዲቆም ይተባበራሉ ወይ ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱ የመደናገጥና የመጨነቅ ፈገግታ እያሳዩ “እውነቱን ለመናገር በእንደዚህ ዓይነት ውይይት ላይ ለመነጋር አልፈልግም፤ እኔ ሥራዬን መሥራት ነው የምፈልገው … ከዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ እዚያ ውስጥ መግባት አልፈልግም” በማለት መልሰዋል። ይህ መልስ በራሱ ሌላ ሙግት ያስነሳ ሲሆን ፋውቺ አስቀድመው ራሳቸው ናቸው ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ድጋፍና ሙገሣ ሲያካሂዱ የነበሩት ስለዚህ አሁን ይልቁንም ይህንን ጭፍን ድጋፋቸውን ቢያስተካክሉ ይሻላል በማለት ቀኝ ዘመሙ ሚዲያ ግፊት እያደረገ ይገኛል።
የቀድሞው የሕዝብ እንደራሴ የነበሩትና በሙያቸው ሐኪም የሆኑት ሮን ፖል በኢንተርኔት በተደረገ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዶ/ር ፋውቺን ሊባርሯቸው ይገባል ብለዋል። በዚሁ ንግግራቸው በተደጋጋሚ ፋውቺን የተቹት ዶ/ር ፖል በዚህ ቫይረስ ምክንያት የዜጎች መብት ተረግጧል፤ እጅግ ብዙ ገንዘብ ባክኗል፤ በዚህም ምክንያት ገበያው ሾቋል ብለዋል። ስለዚህ አሉ የቀድሞው እንደራሴና የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ዶ/ር ፖል፤ “ስለዚህ (ፋውቺ) መባረር አለበት፤ ነገርግን (ትራምፕ) ይህንን የማያደርግ ከሆነ ሕዝቡ ፋውቺን ሊያባርረው ይገባል፤ “አንተ አጭበርባሪ” በማለት ሕዝቡ ሊያባርረው ይገባል” ብለዋል።
በመጪው ምርጫ (ኖቬምበር 2020) በመራጩ ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ለመመረጥ የሚፈልጉት የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴዎች ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከመራጩ የሚመጣባቸውን ግፊት ዝም ለማለት አይፈልጉም። ይህ ፕሬዚዳንት ትራምፕንም የሚጨምር ነው። ከዚህ ጋር አንድ ሚሊዮን የሚደርሰው ፔቲሽን ሌላ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኗል። እነዚህን ፖለቲከኞች በምርጫ መዋጮ ገንዘብ የሚደጉሙት የመድኃኒት አምራች ኩባንዮች ናቸው። ስለዚህ ቴድሮስ አድሓኖም ዳይሬክተር እንዲሆን የተፈለገበት ዘመን ካለቀና ተፈላጊነቱ (ኤክስፓየር ካደረገ) ጭዳ መደረጉ የማይቀር ነው። ነገር ግን ቴድሮስ ገና ማስፈጸም የሚገባው ቀሪ ጉዳይ ካለ ፖለቲከኞቹና ኩባንያዎቹ ከመጋረጃው በስተጀርባ በሚያደርጉት ስምምነት የቻይናን ፖለቲካ በማርገብ እንደ ኤች.አይ.ቪ. የህይወት ማራዘሚያ መድኃኒት ለቴድሮስ አድሓኖም በመሥጠት ጥቂት የሥልጣን ማራዘሚያ ጊዜ ሊሰጡት ይችላሉ። የቴድሮስ ጉዳይ የማስፈጸም ተፈላጊነት ያከተመ ከሆነ ግን የቻይናን ጉዳይ በማራገብ ለቴድሮስ የመውጫውን በር ወለል አድርገው ይከፍቱለታል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply