የኢትዮጵያ ልዩ መጠሪያዎች ከሚባሉት መካከል “ሰው አክባሪነት” አንዱ ነው፡፡ በበርካታው የአገራችን ባህል ሰዎች በዕድሜያቸው የአንቱነትን ማዕረግ ይጎናጸፋሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በሥራቸው፣ በሙያቸው፣ በሕዝብ ዘንድ ባላቸው ከበሬታ ይህ የአንቱነት ማዕረግ ይሰጣቸዋል፡፡ በዕድሜያቸው በጣም ልጆች የሆኑ እንኳን ባላቸው መንፈሣዊ አገልግሎት ወይም ልዕልና በታላላቆቻቸው ሳይቀር አንቱ ይባላሉ፡፡
የመንግሥት ባለሥልጣናትን አንቱ ብሎ መጥራት ለኢትዮጵያዊ የሚነገረው ወይም የሚማረው ግብረገብ አይደለም፡፡ እንደ ህወሃት ዓይነቱን ግን “መንግሥት”፣ “አስተዳደር” ብሎ መጥራት በሕዝብ መቀለድ ነው፡፡ የሕዝብ ይሁንታ የሌለው፤ ሕዝብ አንቅሮ የተፋው፣ በግድ መቶ በመቶ እወደዳለሁ ብሎ ሥልጣን በአፈሙዝ የነጠቀ ወንበዴና የወንበዴዎች ስብስብ “አገዛዝ” መባል ሲበዛበት ነው፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለሕዝብ አገልግሎት መሥጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ህወሃት/ኢህአዴግን “መንግሥት” ብሎ ጠርቶ አያውቅም፡፡ እስካሁን ባወጣናቸው የዜና ዘገባዎች ላይ “የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ” ከማለት ያለፍንበት ጊዜ የለም – በእኛ ዕምነት ተገቢው መጠሪያ ይኸው ነው፡፡ ወደፊትም በዚሁ እንቀጥላለን፡፡
“በቃ፤ አልፈልግህም፤ ውረድ” የተባለን አንድ የወንበዴ ቡድን አባላት እንደ ባለሥልጣን እስካሁን “አንቱ” እያልን ስንጠራ ቆይተናል፡፡ ሆኖም በእሁዱ የኢሬቻ በዓል ላይ የወንበዴው ቡድን አባላት በሕዝብ ላይ በፈጸሙት በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ግፍ ታሪካቸውን በሕዝብ ደም ጽፈዋል፡፡ እያንዳንዳቸውም “ነፍሰ ገዳይ ወንበዴ እንጂ አንቱ መባል የሚገባኝ የመንግሥት ባለሥልጣን አይደለሁም” የሚል እንድምታ ያለው ተግባራቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳይተዋል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ በብሔራዊ ሚዲያ “በስብሰናል፣ ገምተናል፣ …” እና ሌሎች እዚህ ላይ መጥቀስ የማንችላቸውን ጸያፍ ንግግሮች በማድረግ ወጣቱን ትውልድ ብልግና፣ ውሸት፣ ስድብ፣ … በተደጋጋሚ ያስተማሩ በመሆናቸው፤ ዕድሜ ሊለውጣቸው የማይችል እንኳን አገርን መምራት ራሳቸውን ለመምራት የማይችሉ ብልሹዎች በመሆናቸው፣ የሰውነት ስነምግባር የሌላቸው፣ እንደ ሰው የማያዝኑ፣ የሰው ስቃይ የማይሰማቸው፣ ሰው መሆን ከውስጣቸው ተመጥጦ የወጣና በራሳቸው አምሳያ ሌሎችን እየቀረጹ የመጡ ለርኩሰታቸው ወደር የሌላቸው ውርደትና ፍጹም ራስወዳድነት ጠፍንጎ የያዛቸው መሆናቸውን በድርጊታቸው ያለ አንዳች ጥርጣሬ የመሰከሩ ሆነዋል፡፡
በመሆኑም ከህወሃት አገዛዝ በይፋ ተላቅቀው ከወጡት በስተቀር ከአሁን ጀምሮ የህወሃት/ኢህአዴግ ወንበዴ ሹመኞችን “አንቱ” የሚለውን የኢትዮጵያዊነት የከበሬታ ስያሜ የነፈግን መሆኑ የተከበራችሁ አንባቢዎቻችን እንድታውቁልን እንወዳለን፡፡ ይህንን አሠራር ከእሁድ መስከረም 22፤ 2009ዓም ጀምሮ ተግባራዊ አድርገናል፡፡
ለመከበር “ሰከን በሉ”!
“የዜጎችህን እምነት ካጣህ በኋላ አክብሮታቸውንም መቼም ቢሆን መልሰህ ማግኘት አትችልም፡፡” አብርሃም ሊንከን
Leave a Reply