
ልደቱ አያሌው ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ያስተባበረው “አየር አንቀጥቅጥ” ትዕይንት ቅዳሜ ቀን ተካሂዷል። ልደቱ በስተመጨረሻ እንዳለው ከታሰበው በላይ የተሳካው የአየር ትዕይንት 15 ሰዎች ተናግረዋል፤ ሕዝብ በሳተላይት እና በተገኘው መንገድ ሁሉ ሰምቷል ብሏል። አገዛዙ ፈርቶ ኢንተርኔት አፍኗል፤ ዳታ ታቅቧል፤ ዩትዩብ እንዳይሠራ ተደርጓል ብለው ልደቱም፣ ቴዎድሮስም እየደጋገሙ ሲናገሩ ተሰምተዋል።
ይህ የአየር ላይ ትዕይንት “ስልቴዎች” ማለትም ስብሃት፣ ልደቱ፣ ቴዎድሮስ በልዩ ሁኔታ የቀመሩትና ትህነግን በመታደግ ለሻዕቢያ የተሠራ ልዩ የስልቴዎች ስልት ነው።
ንግግር ያደረጉት ሰዎች ጥቂቶቹን ስንቃኝ፤ …
የድግሱ መሪ ቴዎድሮስ መደረጉ በራሱ ብዙ የሚለው ነገር አለ። ቴዎድሮስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወገኖቼን (የትግራይ ተወላጆችን በተለይም ወያኔዎችን) የፈጀች ኢትዮጵያ ጥንቅር ብላ ትጥፋ እያለ በኢትዮጵያ ላይ ዕለታዊ የእርግማን ድግምት ሲያሰማ የነበረ ነው። ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ የነበረውንና አሁንም ያለውን ጥላቻ ልደቱ ምን ዓይነት ጠበል አጥምቆ እንዳበረደለት ባይታወቅም፤ በዘመነ ወያኔ ሚዲያ ላይ ሲሠራ “ኢትዮጵያችን” ሲላት የነበረችውን ሀገር ከሰባት ዓመት ጥላቻና እርግማን በኋላ “አገራችን” እያለ በድጋሚ ሲጠራት መስማት አስፈሪ ነው። ቴዎድሮስ እነ ደብረጽዮንን “የተገረደዱ፣ ገረዶች” እያለ ቀን ተሌት ሲያዋርዳቸው እንዳልነበር በዚህ ፕሮግራም በስብሃት በኩል ለሻዕቢያ “ሲገረደድ” ነበር የዋለው።
ልደቱ አያሌው፤ ትህነግ/ወያኔ ሊሞት ሲጣጥር ሲፒአር መስጠት የልደቱ ልዩ ብቃቱ ብቻ ሳይሆን በደሙ የገባው ቃለ መሃላ ነው። ልደቱ በብዙ መልኩ ሊገለጽና በ97 ምርጫ ወቅት በፈጸመው ክህደቱ ሊታወቅ ይችላል። አንድ ግን መቼም እና በየትኛውም አየር ንብረት ቢሆን የማይቀየር ባሕርዩ፤ ወያኔ ሊሞት ሲቃ ውስጥ ሲገባ “አለሁልህ” ብሎ ደረቱን የሚሰጥ መሆኑ ነው። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ድምፁን አጥፍቶ ብቅ ሲል የታየው ትህነግ መሞቻው ሲቃረብ ነበር፤ ጥቂቶቹም … ትህነግ/ኢህአዴግ ሲፈርስ፣ ወያኔ በትግራይ ጦርነት ቀስቅሶ ሊሞት አንድ ሐሙስ ሲቀረው፤ ከዚያ በኋላ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዋስትናውን ሲያጣ፤ አሸባሪ ተደርጎ በፓርላማ ሲፈረጅ፤ አሁን ደግሞ እንደገና በምርጫ ቦርድ ኅልውናውን አጥቶ አልሞትሁም እያለ በሚያጣጥርበት ሰዓት ነው ልደቱ ይህንን የመሰለ አየር ላይ ትዕይንት ፈጥሮና ቴዎድሮስን በሃሳቡ አጥምቆ ስብሃት ነጋን ይዞ ብቅ ያለው።
ስብሃት ነጋ፤ በፕሮግራሙ እንደሚገኝ በይፋ ያልተነገረው ስብሃት ነጋ ፕሮግራሙ እየተካሄደም ድምፁንም መልኩንም አጥፍቶ ነው የቆየው። ብዙዎች ስብሰባው ለነሱ ታስቦ የተካሄደ ነበር የመሰላቸው። ሆኖም ግን ስብሃት ብቅ ሲልና አፉን በእጁ እየጠረገ መናገር ሲጀምር የሁሉም ነገር ምሥጢር ይፋ ሆነ፤ ጭምብሉ ሲገለጥ ሻዕቢያ ዕርቃኑን ወጣ። ምክንያቱም ሻዕቢያ በስብሃት ተወክሏል። መወከል ብቻ ሳይሆን የስብሰባው ስፖንሰር ራሱ ሻዕቢያ ነው፤ ስፖንሰር ሲባል ወጪ እስከመሸፈን ድረስ ያለውን የሚጠቀልል ነው።
ስብሃትን ጠንቅቀው ከሚያውቁት ሰዎች መካከል ሌ/ጄ ዮሐንስ ገ/መስቀል ተጠቃሽ ናቸው። ገና በረኻ እያሉ ነው ስብሃት ትህነግን ሲመራ የሚያውቁት። ትህነግ ለሻዕቢያ ሎሌ እንዲሆን ከማድረግ አልፎ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆች ለሻዕቢያ እንዲዋጉና ሳሕል በረኻ በወጡበት የቀሩት በስብሃት ትዕዛዝ ነበር ይላሉ ጄኔራል ዮሐንስ። እንዲያውም የስብሃትን የሻዕቢያ ወኪልነት ሲናገሩ፤ በቋሚነት ስብሃትን የመሰለ ወኪል ሻዕቢያ አዲስ አበባ ለምን ኤምባሲ እንደከፈተ አላውቅም ነበር ያሉት። ስለዚህ የስብሃት በቅዳሜው ስብሰባ መገኘት የሚያሳየው ዋናው የጉዳዩ ባለቤት ሻዕቢያ እንደሆነና ከቴዎድሮስ እስከ ጃዋር ያሉት “ተገርዳጆች” መሆናቸውን ነው።
ጃዋር ሲራጅ መሐመድ፤ ራሱን የ21ኛው ክፍለዘመን አሕመድ ግራኝ ነኝ እያለ ሲፎክር ስለ ነበረው ጃዋር በጎልጉል ብዙ ተጽፏል። በተለይ አልፀፀትም ብሎ ስለጻፈው የተዘገበውን እዚህ ላይ ማንበብ ስለ ጃዋር የፖለቲካ ጉዞ ብዙ ትምህርት ይሰጣል። ከቅዳሜው የአየር ላይ ትዕይንት አኳያ ግን አንድ ነገር ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው። “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” (Ethiopia out of oromia) በሚለው መፈክሩ ለኢትዮጵያ ያለውን የጥላቻ ልክ ያሳየው ጃዋር በቅዳሜው የአየር ላይ ትዕይንት ልሙጡን ሠንደቅ ለብሶ መምጣት ሲቀረው ነው “ኢትዮጵያችን፣ አገራችን፣ ኢትዮጵያ” እያለ ያቺን ከኦሮሚያ ያባረራትን ኢትዮጵያ ሲሞካሻት የተሰማው። “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” የሚለው አካሄዱ ከፖለቲካው ትርፍ ሌላ በትንሹ ግማሽ ቢሊዮን ብር ያገኘበትን ኢንቨስትመንት ነበር። ከቅዳሜው የሚያተርፈውን ደግሞ በለመደው ስልት በዙሪያው ያሉትን አንድ በአንድ መንጥሮ የተባለውን የአየር ላይ ትግሉን ለብቻው ሲጠቀልለው የሚታወቅ ይሆናል።
ጃዋር ከስልቴዎች ጋር ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድ በጥቂት ሳምንታት የሚታይ ጉዳይ ነው። ሆኖም ይህንን የስልቴዎችን ስብስብ በለመደው ብቃቱ ወደራሱ ሊቀለብሰውና ወደ ጃል-ስቴ ሊወስደው እንደሚችል ፍንጭ አለ። ምክንያቱም ጃዋር ከቴዎድሮስና ከስብሃት ጋር መቼም ቢሆን የማይታረቅ ቅራኔ አለው፤ ከወያኔው የነፍስ አባት ስብሃት ጋር የማይታረቀው ቅራኔው፤ ወያኔን ከሥልጣን እንዲወርድ በማድረግ ረገድ በተከሰት ሲሆን ከቴዎድሮስ ጋር ደግሞ ወንድሙን ያጣበትን የትግራዩን ጦርነት ጃዋር የደገፈ በመሆኑ ነው (ይህ ጉዳይ ቴዎድሮስ ጃዋርን ኢንተርቪው ባደረገው ጊዜ የታየ ነው)።
ትህነጋውያን እንደ ድርጅታቸው ባህርያቸው በደልን የሚረሳ ሳይሆን የሚበቀል ነው። ይህንን የተረዳው ጃዋር በንግግሩን ሁለት ነገሮችን አድርጓል አንዱ ከላይ የተጠቀሰውና ኢትዮጵያን “እማዬ” ያለበት ንግግሩ ነው። ሌላው ግን በንግግሩ መጀመሪያ ልደቱን በልዩ ሁኔታ የሰላማዊ ትግል ሊቀካህን አድርጎ የሳለበት ነው። ፕሮግራሙን ያስተባበሩት ልደቱና ቴዎድሮስ ሆነው ሳለ ጃዋር ነጥሎ ልደቱን ብቻውን የካበው ስልቴን ወደ ጃል-ስቴ ሲሰነጥቀው እየታየውና ያለ ልደቱ ደግሞ ምንም ተስፋ እንደሌለው ስለሚያውቅ ነው።
ከገዱ እስከ ዘመነ ያሉትን አጇካሚዎች ድግሱን ለማሟሟቅ የተጠሩ እንጂ ብዙም ሥፍራ የሚሠጣቸው አይደሉም። ለምሳሌ ሕዝቅኤል ገቢሳ የቀድሞ ወዳጁ ጃዋርን ንግግር ሳይሰማ ነው የለቀቀው፤ ሌላኛው የጃዋር ወዳጅ ጸጋዬ አራርሳ ይመጣል ተብሎ ሳይከሰት ቀርቷል። ስለዚህ ሌሎቹም እንዲሁ ናቸው – ለበዓሉ ድምቀት የመጡ ግጥም አቀባይና አንጋሾች ናቸው።
ሌላው መጠቀስ የሚገባውና በትልቁ የተሳተ ነገር አለ። ሃሳቡ የጃዋር ይመስላል፤ እናም ስብሰባው እንደተጀመረ ቴዎድሮስ አገር ቤት ዩትዩብ እየተቋረጠ ነው፤ አገዛዙ ተጨንቋል፤ ርዷል፤ አረፋ እየደፈቀ ነው የሚመስል ማስታወቂያ ደጋግሞ ተናገረ። በኋላ ግን ሲያየው እዚያው የአየር ትዕይንት ላይ ሚስጥረሥላሴ ከኢህአፓ፣ ራሔል ባፌ ከደቡብ ፓርቲ ኢንተርኔት ተቋርጧል ከተባለባት ኢትዮጵያ ላይቭ እየተከታተሉ ቁጭ ብለዋል። ነገሩ ሲባነንበት ወዲያው ቴዎድሮስ መጠነኛ ማስተካከያዎች ማድረግ ጀመረ።
ከዚህ በተጨማሪ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ወይም ውሱን ሲሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ ይታወቃል። ለነልደቱ ማሳመን የሚያስችለውና ተቀባይነት የሚኖረው እዚያው “ትዕይንቱን” ስክሪን ላይ እየመሩ ባሉበት ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔቱ የተስተጓጎለባቸውን ቦታዎች ማሳየት ነበር። ግን እነ ሚስጥረና ራሔል ላይቭ እያሉ አይሆንም፤ በተለይ ሚስጥረ እስከመጨረሻው ቆይታ እየታየች ራስን ማጋለጥ ነው የሚሆነው። ፕሮፓጋንዳውና የተመልካች ቁጥር መጨመር ስለሆነ የተፈለገው በዚሁ መልኩ ቀጥሏል። ሌላው የተመልካች ቁጥር (ቪው) ስለመጨመር ደግሞ በቴዎድሮስ ርዕዮት ቱቦ ላይ የሚታየው የተጋነነ ቁጥር በተመለከተ የምናወጣው መረጃ ይኖራል።
የኢንተርኔት ችግር የሌላቸው እስክንድር ነጋ (ሰሞኑን ለልጁ ምረቃ የተቀዳ መልዕክት እንደላከው)፣ እነ ሃብታሙ አያሌው፣ ዘመድኩን በቀለ፣ ወዘተ በዚህ የአየር ላይ ትዕይንት ላይ አለመሳተፋቸው ስብሰባው እንዳለቀ አየሩን የሞላ ጉዳይ ሆኗል። ስብሰባውን ሲያፋፍም የነበረው አበበ ገላውም በስብሃት መከሰት ደንግጦ ነገሩ በጽሞና ይታይ የሚል የተሸኮረመመ “ተቃውሞ” ፌስቡኩ ላይ ለጥፏል።
በመጨረሻም ሁለት የተነሱ አስተያየቶችን እንጥቀስና እናብቃ፤ አንዱ ይድነቃቸው ከበደ በገጹ ላይ ያስቀመጠው ሃሳብ ነው። “ከአገዛዙ በተፃራሪ የቆሙት ተቀዋሚ ኃይሎች አገዛዙን በብቃት ታግለው ለውጥ በማምጣት ህዝቡንና ሀገሪቱን ከህልውና አደጋ ለመታደግ በሚያስችላቸው የትብብርና የጥንካሬ ደረጃ ላይ አይደሉም” የሚለውን የልደቱን መግለጫ ጠቅሶ ይህንን ጥያቄ አቅርቧል፤ ጥያቄ (1) በመርኃግብር ላይ የተሳተፉት በሙሉ – ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልሆኑ አምነዋል ማለት ነው?! (2) ህዝቡንና ሀገሪቱን ከህልውና አደጋ ለመታደግ የሚያስችል የጥንካሬ ደረጃ ላይ እንዳልሆኑ ያምናሉ?! (3) በትብብርና እና በጥንካሬ ለመስራት በመርኃግብር ላይ የተሳተፉት የጋራ ዓላማቸው ምንድነው?! (4) የተናጠል ፍላጎታቸው ምንድነው?! (5) አንዱ በአንዱ ላይ የፖለቲካ መተማመን አለ ወይ?!”
ሌላው ቴዎድሮስ አስፋው ኢትዮ-ሰላም ሚዲያ ደግሞ ይህንን ትዝብታዊ ጥያቄ በማኅበራዊ ገጹ ጠይቋል፤ “እነ ፋኖ አስረስ ዳምጤ ከ85 በመቶ በላይ የሆነውን የአማራ ክልል ተቆጣጥረው እያስተዳደሩ ከሆነ ለምን ሕዝቡን በአካለ-ስጋ ሰልፍ አያስወጡትም?”
ለማጠቃለያ፤ ኢንተርኔት እስከማቋረጥ የተጨነቀውን አገዛዝ የሚመሩት ዐቢይ አሕመድ በዕለቱ ከሕዝብ ጋር እየተጋፉ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከሹሞቻቸው ጋር በእግራቸው ሲጓዙ ነው በተጻራሪው የታዩት። ምናልባት ለቀጣዩ የአየር ትዕይንት እንደ ግብዓት የሚወሰድ ጉዳይ እንዲሆን ይህንን የአጀንዳ ሃሳብ ለስልቴዎች በነጻ እንሰጣለን።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
በተራ እንግዛ ማለት አሁን እየተገዛን ነው እንዴ
SNO CAS S CT C.SIZE TO.A PR.DA R.D EX.DA MSDS
ሰው ስንት የሚሰራ ነገር በፊቱ እያለ እንዴት ዝንተ ዓለሙን ፓለቲካ ሲያኝክ ይኖራል? መጥኔ ለእነዚህ አኞ የእድሜ ልክ ሙታኖች። በቢሆን ዓለም ውስጥ ራሳቸውን ዘፍቀው ሌላውን ወደ መከራና ሰቆቃ እየማገድ ባከማቹት ሃብት ዛሬ ላይ ተንደላቀው የሚኖሩት እነዚህ የደም ነጋዴዎች ያኔም ዛሬም ማንንም ነጻ ማውጣት አልቻሉም። የራሱን ባህሪ ያልተቆጣጠረ ሰካራም ፓለቲከኛ እንዴት ባለ ሂሳብ ነው ለሌላው መልካም የሚሆነው? ስናሳዝን! እንዴት ሰው ከመገንጠል፤ ከብሄርተኝነት ትርፍ ይገኛል ብሎ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በማይድን ደዌ ይለከፋል? አሁን ማን ይሙት በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ ቢኖር ስብሃት ነጋ ቆሞ መሄድ ነበረበት? በጭራሽ! ግን ምድሪቱ የሚያስቡላትንና የሚያሳስቧትን መለየት ከተሳናት ቆይቷልና አያስደንቅም።
ህዝባዊ አስተዳደርና መንግስትን በተራ ወረፋ እንደ ሰንበቴ ለማድረግ የሚጥሩ ሁሉ የቁም ሙቶች ናቸው። ጥያቄው መሆን ያለበት አማራ፤ ትግሬ ወይም ኦሮሞ ወይም ከሌሎች የሃገሪቱ ብዙሃን ወገኖች መካከል ማን ስልጣን ላይ ይውጣ ሳይሆን በስልጣን ላይ ያሉትና አሁንም የተቀመጡበት እንዴት ያስተዳድራሉ ተብሎ ነው መጠየቅ ያለበት። የትግራይን ልጆች በህዝብ እንዲጠሉ ያደረጋቸው ከትግራይ መሆናቸው አይደለም። አድሎአዊ አሰራራቸውና መሰሪ የፓለቲካ ተግባራቸው እንጂ። ኢትዮጵያዊነት ትግራይን አልባ ኑሮ አያውቅምና እነዚህ የፓለቲካ ጉንድሾች ግን ሃገሪቱን ለሻቢያ አስረክበው፤ ምድሪቱን በብሄርና በጎሳ እንዲሁም በቋንቋ ሸንሽነው እንሆ አሁን ቀስ በቀስ አፈር እየተመለሰባቸው ይገኛል። ግፍን ያልፈራ በግፍ ያልፋል። የቆየ ታሪካችን የሚያስተምረን ይህኑ ነው። ሌላው የአሁኑ የክልልና የብሄር ጫጫታ ሁሉ ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ እንዲሉ ነው። የዓለም የፓለቲካ ንፋስም አይቀበለውም፤ ህዝባችንም እየነቃ ሲሄድ የጠባብ ብሄርተኞችን አተላ የዘር ፓለቲካ አክ እንትፍ ብሎ በሰውነት ቁመናው ብቻ ደምቆ እንደሚታይ ጥርጥር የለውም።
ብልጽግናን ከፈጣሪ የተላከ ሁሉ የሰመረለት መንግስት ነው የሚሉ ሁሉ ስተዋል። ብልጽግና እንደማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ ይስታል፤ ያሳስታል፤ ህዝብ ያልወደዳቸው ነገሮችን ያደርጋል፤ አድርጓልም። ግን በዓለም ላይ ካሉ በመቶ የሚቆጠሩ መንግስታት መካከል እንከን የሌለበት ማንም መንግስት የለም። የእኛን መሪዎች ከብዙ ሃገራት መሪዎች የሚለያቸው ሁሉን ነገር በማሰር፤ በማሳደድ፤ በመግደልና በማፈናቀል ችግራቸውን ለመፍታት ስለሚጥሩ ትርፉ ዘንተ ዓለም መገዳደል ሆኗል። ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻውን ተጠያቂ አይደለም። ህዝቡም፤ ከህዝቡ የወጡ ሾተሌ ታጣቂዎችና የብሄር ተፋላሚ ነን የሚሉ የውጭ ጥገኛ ሃይሎችም ከመጠየቅ አይድኑም። ለዚህ ነው ለመንግስት በተደጋጋሚ ነገርን ከማካረር ይልቅ የታሰሩትን መፍታት፤ ሰላምን ለማስፈን መጣር፤ ዋናውና ቀዳሚው ተግባር መሆን አለበት የምንለው። ለአንድ መንግስት ጠበቃው/በክፉ ጊዜ መደበቂያው ህዝብ ነው። ኦሮሞ ስለሆንክ ክፋትን የተላበስክ ከሆነክ ነገር ሲጨልም የኦሮሞ ህዝብ ያስጠልለኛል ማለት አይቻልም። የሰው ልጅ በከፋ ጊዜ መውጫ ቀዳዳው አይታወቅምና የሃገሪቱ መላ ህዝቦች በእኩልነት ታይተውና ተከብረው በፈለጉት የሃገሪቱ ምድር እንደ ልብ ተዘዋውውረው ሰርተ/ተምረው/ቤተሰብ አፍርተው እንዲኖሩ የሚያደርግ ህገ መንግስት አሰፈላጊ ነው። ያ ሁሉን ወደ ሰዋዊ አቋም ያስጠጋልና! ይህ የወያኔ የአፓርታይድ ህገ መንግስት ስንቱን መጠለያ አልባ እንዳደረገው ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቃል። በቅርቡ አንድ ሰው ከውጭ ወደ ሃገር ቤት ለመሄድ ይነሳና በመሃሉ አይ ወደዚያ እማ መሄድ አትችልም ክልሉ ትግሬ ጠል ነው ይባላል። ከብዙ ምክክር በህዋላ እንዲሄድ ይደረጋል። በስፍራው ሲደርስ ማንህ ከየት መጣህ ምን አመጣህ ያለው አልነበረም። በሰላም ዘመዶቹን ጠይቆ/ትውልድ ስፍራውን አይቶ ተመለሰ እንጂ! የወያኔና የሻቢያ ወሬ ሰው መከፋፈል ነው። አብሮ የኖረን ህዝብ በፍርሃት ማሰር ነው። ግን ህዝባችን እየነቃባቸው ነው። ለእነርሱም ጊዜው እየመሸ እንደሆነ እንገነዘባለን።
በየዓመቱ ሻቢያ በጀግንነት ኤርትራን ነጻ አወጣን ብሎ ከበሮ ሲመታ የእድሜ ልኩ መሪ አሜሪካን ሳይዘልፍ ያለፈበት ጊዜ የለም። በሻቢያው መሪ እይታ የኤርትራ ወጣቶች ሃገር እየጣሉ የሚጠፉት በሲ አይ ኤ ሴራ ነው ብሎ ያምናል። የሻቢያ ፓለቲካ የተንሻፈፈበት ብዙ ስፍራ ቢኖርም ይህ ግን እጅግ ከእውነት የራቀ ነው። በቅርቡ አሜሪካና ልዪ ልዪ የአውሮፓ ሃገሮች ህዝብህን ተቀበል እነዚህ አንፈልጋቸውም በማለት ያገቷቸውን ወደ ኤርትራ ለመላክ ሲሞክሩ አልቀበልም ያለው ሻቢያ ለምን ይሆን? ጉራና እውነት ለየቅል ናቸው። ኢትዮጵያና ኤርትራ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ወይም የአረብ ሃገራት በአንድነት ማንም ሃበሻ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ማስተላለፍ አይችልም በማለት ሁሉን ቢዘጉት ስንት ጦም አዳሪ እንደሚኖርና መንግስት ነኝ ባዪችም በውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሚሽመደመድ ግልጽ ነው። የኤርትራ ወጣት ከአዲሲቱ ኤርትራ የሚፈረጥጠው ሳይወድ በግድ የሻቢያን የመከራ ዶፍ ለማምለጥ እንጂ አሜሪካ ማንንም ወደ እኔ ኑ ብላ ታውቅም። ለዚያውም ጥቁር ህዝቦችን! ገልቱ የሻቢያ ፕሮፓጋንዳ ግን ይህን አምኖ ይቀበላል!
በመዝጊያው ዝም ብሎ ሁሌ በፈሰሰ ወተት እየየ ከማለት ሃበሻ በሃገርም ሆነ በምስራቅ አፍሪቃ ሰላምን ፈጥሮ፤ በሰላም መኖርን መርጦ ቢረዳዳ ችግራችን ከመቀረፍ አልፎ እልፈትን ያገኝ ነበር። አንድ እውቅ የኢኮኖሚ ምሁር እንዳለው ወለጋ ብቻ ግማሽ ኢትዮጵያን መመገብ ይችላል። ሌላውን የጎጃም ምርት ይሸፍነዋል ነበር ያለው። ብንስማማ ታላቅ ህዝብ መሆን እንችል ነበር። እድሜ ልክ ጠበ የለሽ በዳቦ ግን በየዘመናቱ ህዝባችን እንዲቆረቁዝና እንዲታረዝ አድርጓል። ጦርነት ይብቃ። ለሰላም ሁላችንም እንቁም። ብልጽግናም ከስልጣን የሚወርደው በአፈሙዝ ሳይሆን በምርጫ ነው። ሌላው ሁሉ ወሬ ትርምስ ፈጣሪና ሃገር አፍራሽ ትረካ ነው። ልብ ይስጠን!