ፍርድ ቤቱ አቶ ልደቱ አያሌው በህክምና ምክንያት ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሲያደርግ፥ መርማሪ ፖሊስ ለመጨረሻ ጊዜ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የሰባት ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
በምስራቅ ሸዋ ዞን የቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ በቀረቡት አቶ ለደቱ አያሌው ላይ መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ተጨማሪ 14 ቀናት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን የምርመራ ስራዎች ገልጿል።
አቶ ልደቱ እጅ ላይ የተገኙ ሁለት ሽጉጦች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንዲሁም የተላላኳቸውን የስልክ መልዕክቶች በፎረንሲክ እያስመረመረ መሆኑን ተናግሯል።
በእጃቸው ላይ የኢትዮጵያ ህዳሴ እርቅና አንድነት የሽግግር መንግስት ማቋቋም የሚልና ሌሎች የፖለቲካ ሰነዶችን ማግኘቱን የገለፀው መርማሪ ፖሊስ በሰኔ 23 ቀን 2012 ዓመተ ምህረት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ መንግስት ለመገልበጥ እቅድ ይዘው ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በቢሾፍቱ ሁከትና አመፅ እንዲፈጠር ሲቀሰቅሱ ነበሩ ብሎ እንደጠረጠራቸውና ለዚህም የምስክሮችን ቃል መቀበሉን ገልጿል።
ለጀመርኩት ምርመራ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ለማምጣትና ተጨማሪ ሰነዶቸን ለማሰባሰብ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
አቶ ልደቱ ዛሬም በጠበቃ ያልተወከሉ ሲሆን፥ ፍርድ ቤቱ ለምን በጠበቃ እንዳልተወከሉ ለጠየቃቸው ጥያቄ ሁለት ጠበቆች ፍቃደኛ አለመሆናቸውን፤ አንድ ፍቃደኛ ቢያገኙም በዚሁ ሰዓት በሰበር ችሎት ቀጠሮ ስላለው እኔው ለዛሬ ልከራከር ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ፍርድ ቤቱም ፈቅዶላቸዋል።
በዚሁ መሰረት ፖሊስ ባቀረበው ምርመራ ላይ መቃወሚያ አሰምተዋል።
ሽጉጡን በተመለከተ 1998 ዓመተ ምህረት ላይ መንግስት ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት እንደሰጣቸው አንደኛው ሽጉጥ ደግሞ ከአባታቸው በውርስ ያገኙት እና ፍቃድ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
በ1998 ዓመተ ምህረት ማስፈራሪያዎች ይደርስባቸው ስለነበር በወቅቱ የነበረው መንግስት ችግሩ ሲያልፍ ትመልሳለህ ብሎ እንደሰጣቸው ነው ያስታወቁት።
ሰነዶቹንም በተመለከተ የፖለቲካ ጉዳዮች ሆነው በመገናኛ ብዙሃን እና በአደባባይ ሲገልጿቸው የነበሩ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት ከነበረኝ ቀጠሮ ጋር ተመሳሳይ የሆነ መርመራ ነው የቀረበው፤ አዲስ አልቀረበም በማለት ተጨማሪ ጊዜ ለመርማሪ ፖሊስ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።
በፈረንጆቹ ነሃሴ 6 የልብ ቀዶ ጥገና ምርመራ ለማድረግ እሁድ ወደ አሜሪካ ለመብረር ትኬት ቆርጠው አርብ እለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀው፥ አሁንም የልብ ህክምና ያሰጋኛል የፖሊስ ጣቢያው ውስጥም ማስክ ሳያደርጉ ከመንገድ ላይ የሚያዙ ሰዎች ሳይመረመሩ እየገቡ ናቸው፤ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ እንዳልሆን ስጋት አለኝ ሲሉ አቤቱታ አስመዝግበዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው መንግስት አምስት ጊዜ አስሯቸው ነገር ግን ማስረጃ ስላልተገኘ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ የተናገሩት አቶ ልደቱ፥ አሁንም ማስረጃ ከተገኘብኝ ይጣራ በውጭ ሆኜ ህክምናዬን እንድከታተል ፍርድ ቤቱ የጤናዬን ሁኔታ ከግምት አስገብቶ በዋስ ይልቀቀኝ ሲሉ ጠይቀዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ፖለቲካ ሳይሆን የወንጀል ጉዳይ ነው፤ እንደ ሀገር መንግስት ለመገልበጥ በተደረገ ሙከራ በቢሾፍቱ ወጣቶችን አደራጅተው አመፅና ሁከት በመቀስቀስ ነው የተጠረጠሩት፤ በመሆኑም ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም ሲል ተቃውሟል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ከዛሬ ጀምሮ አቶ ልደቱ በሀገር ውስጥ የልብ ህክምና ማእከል ህክምና እንዲያገኙ እንዲያደርግ አዟል።
የወረርሽኙን ሁኔታ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው ያዘዘው ፍርድ ቤቱ፥ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የመጨረሻ ሰባት ቀን ጊዜ ፈቅዶለታል። (ምንጭ፤ ፋና)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply