ራሱን ከሚገባው በላይ መካብ የማይበቃው ጃዋር ሲራጅ መሐመድ የ21ኛው ክፍለ ዘመን አህመድ ግራኝ ነኝ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነኝ፤ “የአማራ ብሔርተኝነት ማነሳሳታችን ትልቁ ስኬታችን ነው”፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለሥልጣን ያበቃሁት እኔ ነኝ፤ የምርጫውን ቀመር (ካልኩሌሽን ሠርቼዋለሁ)፣ ቁርአን ይዤ ዐቢይን ጅማ ላይ እንዳይመረጥ አደርገዋለሁ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግሥት ነው ያለው – የዐቢይ እና የቄሮ መንግሥት፣ እኔ ከታሰርሁ ኦሮሚያ ድብልቅልቁ ነው የሚወጣው፣ የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ፣ ብዙ ዕውቀት አለኝ፤ ብዙ ችሎታ አለኝ፤ ወዘተ በማለት ያለማቋረጥ ከመትፋት አልፎ “ተከበብኩኝ፤ ልገደል ነው” የሚል የሃሰት መረጃ በማውጣት፤ ከህወሓት ጋር በመመሳጠር ለመተግበር የሞከረውን ዕቅድ እንደፈለገ የሚነዳውንና ማሰብ የተሳነውን የቄሮ ኃይል በመጠቀም ለማስፈጸም ባደረገው ሙከራ እጅግ በርካቶች በግፍ እንዲጨፈጨፉ ያስደረገው የመለስ ዜናዊ አድናቂ ጃዋር አሁን ደግሞ “አልጸጸትም” የሚል መጽሐፍ በሁለት ቋንቋዎች ማውጣቱ ተሰምቷል።
ኢትዮሪቪው የተሰኘው ድረገጽ እንደዘገበው መጽሐፉ በዚህ ሳምንት ለገበያ ይውላል፤ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነጻ ይዞታ ናቸው በሚባሉ አካባቢዎች ጭምር ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ “የሰላም ያለህ” ማለቱን “የሰላም ድርድር ጥሪ የገፋ መንግሥት ስለምን ሕዝብ ያሰልፋል” በሚል የተቃወመው ጃዋር ያሳተመው መጽሃፍ በኦሮሚኛና በአማርኛ መሆኑ ታውቋል።
ዜናውን ያጋሩን ወገኖች ጃዋር ለመጽሐፉ “አልጸጸትም” የሚል ርዕስ የመረጥበትን ምክንያት ለጊዜው ግልጽ አላደረጉም። ይሁን እንጂ በከፍተኛ ደረጃ ተከታዮችና አባላት አስከትሎ፣ ከመንግሥት ባልተናነሰ በይፋ አገር ቤት ተቀምጦ ሲመራው የነበረውን ትግል ወደ አሰበበት የሥልጣን ማማ ላይ ሳያደርስ መቅረቱና የሠራውን ወንጀል እንደ ጽድቅ በመቁጠር ለመጽሐፉ ርዕስ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ። “አልጸጸትም” ለሚለው ጃዋር ወደኋላ መለስ ብሎ እጅግ የሚያጸጽት ታሪኩን መመልከት ያስፈልጋል። ዓቅም ሰጥቷችሁ የጃዋርን የደም መጽሐፍ ለምታነቡ ይህንን አጭር የግርጌ ማስታወሻ አቅርበንላችኋል።
ጃዋር የሚዲያ ሰው ነው፤ ትምህርቱም ሚዲያን የተመለከተ ነው፤ ስለዚህ በተቻለ መጠን ሚዲያው ላይ አለሁ በማለት መወያያ አጀንዳ መሆን የሁልጊዜ ምኞቱ ብቻ ሳይሆን ማስረጃ ሊጠቀስበት የሚችል ተግባሩም ጭምር ነው። የO-Pride አዘጋጅና የአልጃዚራ ዘጋቢ ከነበረው መሐመድ አዴሞ (Pride የሚለው ቃል ለግብረሰዶማውያን የሚውል ቃል በሆነበት ዘመን) ጋር ወዳጅነት የጀመረው ጃዋር ወደ ሚዲያ ለመምጣት የቻለው መሐመድ አዴሞ ከአልጃዚራ ጋር ያለውን ትሥሥር በመጠቀም ነበር። በዚህም ያለማቋረጥ “ተንታኝ” እየተባለ አልጃዚራን ቤቱ አደረገው።
በቀጣይ አንድ የኦሮሞ ሚዲያ እናቋቁም የሚለውን የሌሎችን ሃሳብ እን ደ ጊንጥ ተጣበቀበት፤ ከዚያም ወደ ራሱ ጠልፎና እነ መሐመድ አዴሞ ተጠቅሞ “Oromo First” የሚል ዘመቻ በተለይ በሰሜን አሜሪካ በማካሄድ እጅግ በርካታ ብር በመሰብሰብ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ የተባለ ሚዲያ ከፈተ። ከዚህ በኋላ የሆነው ግን ለጃዋር ጠላቶች ብቻ ሳይሆን ለደጋፊቹም አስደንጋጭ የሆነ ተግባር ነው – አብረውት ሚዲያውን የከፈቱትን ቀስ በቀስ መነጠራቸውና ሚዲያውን የግሉ ንብረት አደረገው። ከዚያ አልፎም ሠራተኞቹን በሙሉ ቁጥጥር ሥር በማዋል፣ ስልካቸውን ጠልፎ በማዳመጥ፣ ምሥጢራቸውን እንደ ማስረጃ በመያዝ የግሉ ሎሌ አደረጋቸው።
ለግሉ መጥለፍና መጠቀም ካልቻለ ጃዋር ትግል በማበላሸት የሚወዳደረው የለም። “ድምጻችን ይሰማ” የሚለውንና በኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ አስደናቂ የሆነ የሰላማዊ ትግል ተምሳሌት የነበረውን የሙስሊም እንቅስቃሴ ያከሸፈው ጃዋር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ በብዙ መስዋዕትነት ቀስ እያለ የክርስቲያኑን ሕዝብ ድጋፍ እያገኘ የመጣና የመሠረተው መስተጋብር (ኔትዎርክ) እጅግ አስደናቂ የነበረ ትግል ጃዋር የሜንጫ ፖለቲካ ሰንቅሮበት ከጥቅም ውጪ አደረገው።
ጃዋር ከሚዲያ ምሥረታ በፊት ከተወናቸው ቀዳሚው የድምጻችን ይሰማ የሙስሊም እንቅስቃሴን መቀላቀል ነው። ሙስሊምም ኦሮሞም ስለሆነ አልከበደውም። ሆኖም ዓላማው ሙስሊሙን የለውጥ እንቅስቃሴ ለውጤት ማድረስ ሳይሆን ትግሉን ቀልብሶ ለራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ነበር።
በሙስሊሙ እንቅስቃሴ እንዲሳብ ያደረገው አንዱ ነገር የሙስሊሙ ኅብረተሰብ የዕዝ ሠንሠለት ተከትሎ የነበረው አደረጃጀትና ትዕዛዝ አፈጻጸም ነበር። ለምሳሌ በወቅቱ በድምጻችን ይሰማ አንቂዎች የተሠራው መስተጋብር ከውጪ እስከ አገር ውስጥ ከተሞች ከዚያም ሲያልፍ እስከ ትንንሽ ወረዳና የገጠር ቀበሌ ተሰናስሎ የሚደማመጥ ነበር። ለምሳሌ ሃሙስ ማታ ለጁምዓ ተብሎ የተጠራ ተቃውሞ አርብ ጠዋት ከሶላት በፊት ከተቀየረ ሁሉም ሙስሊም በተዋረድ መቀየሩን ሰምቶ ይተገብራል። የሚወጣው መፈክር እንዲሁ ከተቀየረ ያለአንዳች ችግር ወዲያውኑ በኔትዎርኩ እንዲቀየር ይደረጋል።
እንዲህ ያለውን መስተጋብር ሲመኝ የነበረው ጃዋር ሙስሊሙን ያገዘ መስሎ እንቅስቃሴውን ተቀላቀለና ትልቅ ፋዎል ሠራ። አስቦበት ይሁን ወይም ለዓላማው ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ይሆናል። ሆኖም የዛሬ 11 ዓመት አካባቢ ፈርስት ሒጅራ በጠራው ትልቅ ስብሰባ ላይ ጃዋር እሱ ባደገበት ቦታ ሙስሊም ያልሆነ በሜንጫ አንገቱ ይቀነጠስ እንደነበር በመናገር ተመሳሳይ ጥሪ አሁንም እንዲደረግ አወጀ። በውጤቱም የሙስሊም ትግል ቀዝቃዛ ውሃ ተደፋበት፤ ታላላቅ የሙስሊም መሪዎች እጅግ አዘኑ፤ አሁን ስም ጠቅሶ መናገሩ ባያስፈልግም በሚዲያ ላይ ያልወጣ ብዙ ነቀፋ አወረዱበት።
ጃዋር ግን ይህንን ከመናገሩ በፊት በዚያን ወቅት በየሚዲያው እየወጣ ትግሉ የሙስሊም ብቻ ሳይሆን የኦሮሞም ነው በማለት የክርስቲያን ኦሮሞዎችን ድጋፍ ለማግኘት ሲታትር ነበር። እንዲያውም ኦሮሞ እስከ ጎንደር ድረስ ነው ያለው፤ ሙስሊምም እንደዚያው፤ ስለዚህ የጎሣና የሃይማኖቱን ጥምረት ማፋፋም ያስፈልጋል ሲል በስፋት ተሰምቷል። አስልቶ በዋጠውና ብር በገፍ ባመረተበት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በኩል “ደጋፊ ለማግኘት የብሔርና የሃይማኖት ቅሰቀሳ ተመራጭ ነው” ሲል አምልጦት ይሁን አውቆ በራሱ ላይ በቁሙ ኑዛዜ አሰምቷል።
ኢህአዴግ ምርጫ ሊያደርግና መሪ ሊሾም ባለበት ወቅት ላይ ዐቢይ አህመድ እንደሚመረጥ ግልጽ እየሆነ ሲመጣ ጃዋር ባይሳካለትም በዐቢይ ምትክ ለማ መገርሳ እንዲመረጥ ትልቅ ውስወሳ በሚዲያው አድርጓል። እንዲያውም በዚያን ወቀት በኦ.ኤም.ኤን. ላይ ከሕዝቅኤል ገቢሳ ጋር ሆኖ የፓርላማው ሕግ ተቀይሮ ለማ ከክልል ተመራጭነት ወደ ፌደራል ፓርላማ እንዲገባ መደረግ አለበት ብለው ብዙ ጥረት አድርገው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ለውጥ መጥቶ ጃዋር ወደ አገር ሲመለስ ዋነኛ ዓላማው በወቅቱ አዲሱ አረጋ ይዞት የነበረውን የኦሮሚያ ገጠር አደረጃጀት ዋና ቢሮ መምራት ነበር። ዓላማው የገባቸው የኦህዴድ ሰዎች ሥልጣኑን ሲነፍጉት ነቀለ። በከፈተው ሚዲያና ይዞት በገባው ግማሽ ቢሊዮን ብር በርካታ የአገር ውስጥ የሚዲያ ቡድኖች ከፈተ። እነዚህም በአማርኛ፣ በወላይትኛ፣ በሲዳምኛ፣ በአገው፣ ወዘተ የሚዘግቡና በእርሱ ድጎማ የሚደረግላቸው ነበሩ።
ጃዋር አልሞና አስቦ በከፈታቸው የሚዲያ አውታሮች የሚረጨው መርዝ ኢትዮጵያን አፈናት። ምድሪቱ በዘር ፖለቲካ ጦዘች። ሰዓት እየከፋፈለ አንዴ ቅማንት ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤጀቶ እያለ አገርና ሕዝብን አወከ። የሲዳማ በደል እንዲወራ ያደርግና ሲዳማዎችን ከወላይታዎች ጋር ያባላ ጀመር። ከዚህ ሌላ ያለማቋረጥ ስለ አገውና ቅማንት ሕዝብ እንዲወራ፣ አጀንዳ እንዲሆን፣ ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን በኦኤምኤን እንዲሰራጭ እረፍት እስኪያጣ ደከመ። ከሚሴ ገብቶም ሁከት ነዛና አብረው ለዘመናት የኖሩ ወገኖችን እሳትና ጭድ አድርጎ አጫረሳቸው።
በአንድ ወቅት አገር ቤት የገባ ሰሞን በራሱ ሚዲያ ቀርቦ ስለ ለውጡ ብዙ ከተናገረ በኋላ በቀጣይ ስለሚሆነው ወይም መሆን ስለሚገባው ነገር የተናገረውን አሁን ደግሞ ቢሰማው ራሱ ጃዋር ይደነቃል። ቃል በቃል ያለው “አሁን ዐቢይ የሚመራው የሽግግር መንግሥት ነው … ማንም ያለ ምርጫ በሽግግር መንግሥት ስም ሥልጣን በአቋራጭ መሞከር አይችልም” ነበር ያለው።
ይህንን ሲል የነበረው ጃዋር ወዲያውኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግሥት እንዳለ ሲናገር ቆየ፤ አንዱ አራት ኪሎ ያለው ሲሆን 2ኛው ደግሞ የቄሮ መንግሥት እንደሆነ አስታውቆ ራሱን ሾመ። የመደበኛው መሪ ዐቢይ ከሆነ የቄሮው ደግሞ ራሱ መሆኑ ነው። በዚሁ ጊዜ “ብንፈልግ አራት ኪሎን መቆጣጠር አያቅተንም” ሲል በገሃድ ገለጸ።
በዚህ ልክ የሥልጣን ጥማቱን በአደባባይ ሲናገር የነበረው ጃዋር የመጨረሻ የሚባለውን መተግበር ግድ ሲሆንበት በቅድሚያ የፖለቲካ ድርጅት መቀላቀል አስፈላጊ መሆኑን በመረዳቱ መረራ ጉዲናን ከነፓርቲው በበቀለ ገርባ አሻሻጭነት ጠቀም ባለ ብር ገዛው። በስፖርቱ ቋንቋ ለጠቅላይ ተጫወተበት። ቀጥሎም የኦሮሞ ፓርቲዎች ውኅደት ብሎ የዳውድ ኢብሣን ኦነግና የከማል ገልቹን ፓርቲ ከኦፌኮ ጋር ለማጣመር ሌላ ድራማ ተወነ። ዳውድ የጥምረቱ መሪ ተብሎ ተሾመ፣ የፊርማ ሥነሥርዓት ተደረገ፣ ዳውድ ዲስኩር ሰጠ። በነጋታው ግን ጃዋር ዳውድን “እውነት መሰለህንዴ?” ማለት ሲጀምር ከማል ገልቹ ከውህደቱ ወጣ፣ በዚያው ሁሉም ፈረሰ።
ጃዋር እየተገለባበጠ ያደረገው ሙከራው ሁሉ የእንቧይ ካብ እየሆነበት ሲመጣ የመጨረሻ መጨረሻውን ውሳኔ መተግበር ግድ ሆነበት። ሥልጣን እንዳሰበው በቀላሉ የሚያዝ እንዳልሆነ እንዲያውም በጣም እየራቀው እንደመጣ ሲያይ ኦፐሬሽን ሃጫሉን ተገበረ። ሃጫሉ ኦኤምኤን ላይ ወጥቶ የተናገረው እሱ ባልገመተው መንገድ ቀለበት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርገው ነበር። የሃጫሉ መገደል የሚቀሰቅሰው ቁጣ ለጃዋር የአራት ኪሎን በር ወለል ብሎ የተከፈተ እንዲመስለው አደረገ። ሃጫሉ ከተገደለ በኋላ በአስከሬኑ ላይ የተፈጸመው ድራማ እና ፖለቲካ ያለ ቅንብር፣ ያለ ዕቅድ ነው የሆነው የሚለውን የሚያምን የጃዋርን ማንነት የማያውቅ ወይም ፖለቲካ ያልገባው ነው። በተለይ ከግድያው በኋላ በቀለ ገርባ፣ ጃዋር መሐመድ፣ ሃምዛ ቦረና፣ … ዞን እና ቀጣና ተከፋፍለው መረጃ እየበተኑ ዕልቂት እንዲነሳ፣ አገሪቷ እንድትናወጥ በማድረግ የፈጸሙት ተግባር ቢሳካ እሳቱ ዛሬ ድረስ የሚንቦገቦግ በሆነ ነበር።
ከሃጫሉ ግድያ በፊት የቁማሩ ካርድ እያለቀበት ሲመጣ ጃዋር አንድ ድራማ ተውኖ ነበር። የኦሮሞ ወጣቶች እንዲነሱ ታፍኛለሁ፣ ታግቻለሁ፣ ብሎ አገር በማናወጥ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ፤ ንብረት ያወደመ እጅግ አሰቃቂ የግፍ ድራማ ተጫውቷል። ግን መንግሥትን ገልብጦ ሥልጣን ማማ ላይ መውጣት አልተሳካም። ይልቁኑ ከዚያች ቀን ጀምሮ በሩቅ ሸብ የተደረገበት ገመድ ጠበቀ። ገመዷ ጠብቃ ሳለ በሃጫሉ አስከሬን ሥር ቁማር ፈጸመ። አስከሬን ከቤተሰብ ነጥቆና አስነጥቆ ከበቀለ ገርባና ከጀርባ ካሉት ጋላቢዎች ጋር ሆኖ አዲስ አበባን በነውጥ ሊያበራይ የያዘው ዕቅድ እንደ ጭስ ተነነበት። የጠበቀውም ገመድ አነቀውና “ብዙ ዓመት ሳወራ ኖርኩ። እስኪ ላዳምጥ ብዬ ዝም ብዬ ተቀመጥኩ” ብሎ የሚናገር እንደበተ ልስልስ ሆኖ የወጣበት ማረሚያ ቤት ውስጥ ተከረቸመ።
ዐቃቤ ሕግ ክስ አቋርጦ ጃዋርን ከእስር እንዲወጣ ከፈቀደለት በኋላ ለወራት ምንም ነገር ሳይናገር ቢቆይም በእነዚያ ወራት አንድ የፈጸመው ወሳኝ ተግባር አለ። ረመዳንን ጠብቆ ለሐጂ ዑምራ ወደ መካ ነበር የሄደው። ከሃይማኖቱ ጋር በጣም ተጻራሪ (ሃራም) የሆኑ ተግባራትን ሲፈጽም የኖረው ጃዋር ባልታሰበ ሁኔታ ሐጂ ማድረጉ ሃይማኖታዊ ግዴታውን ለመፈጸም ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
ከአሜሪካ ወደ አገር ቤት ከመጣ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲቆይ ለሐጂ ብዙ ትኩረት ያልሰጠው ጃዋር በዚያን ወቅት ማድረጉ የጤና እንደሆነ አድርጎ መቀበል አይቻልም። ጃዋር ይህንን ሃይማኖታዊ ተግባር የፈጸመው እንደ ሌሎች ሃይማኖቱን ናፍቆ፣ ሥርዓቱን አክብሮ ለመቀደስ እንዳልሆነ ከduty free ብሉ ሌብል (Blue Label) ዊስኪና ኤሌክትሮኒክ ኮንዶም የሚያግዙለት የነበሩ ቀኑ ሲደርስ ምስክርነት የሚሰጡበት ጉዳይ ይሆናል። እናም አያ ጃዋር “ሐጂ” የሚለውን ማዕረግ የተጎናጸፈው ፊቱን ወደ ሃይማኖታዊ ፖለቲካ ሊገለብጥ እንደሆነ በርካታ ጠቋሚዎች አሉ።
እኔ ከታሰርሁ ይቺ አገር ድብልቅልቋ ይወጣል፤ ቄሮ ይነሳል፤ ዳያስፖራው በውጪ ታላላቅ ከተሞችን በሰልፍ ያናውጣል፤ ለዚህ ነው የማልታሰረው፤ ወዘተ የሚሉ ድንፋታዎችን ሲያሰማ የኖረው ጃዋር እስር ቤት የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈጽሞ እንደማያውቀው በበቂ ሁኔታ አስተምሮታል ማለት ይቻላል። ይህ ደግሞ በራሱ የሚፈጥረው የቅስም መሰበር ስሜት በቀላሉ የሚለቅ አይደለም። ስለዚህ ጃዋር ማሰብ አለበት።
እስር ቤት በነበረበት ወቅት መዓዛ መሐመድ ለምትባለው የዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ቅልብ፣ “ጃዋርን ቃሊቲ ልትጠይቀው ሄዳ የአንድነት ኃይሎች ጉድ አደረጉኝ” ያለው ጃዋር ከእስር በኋላ አገር ውስጥ ብዙም ስላልተሳካለት፣ ኦፌኮም ፊቱ ስላዞረበት፣ በገለቶማ ዘመቻው ብዙዎቹ የቀድሞ አምላኪዎቹ ከእስር ቤት በምሕረት መውጣቱን በመጠራጠር “ከዐቢይ ጋር ነው የምትሠራው” በማለት ፊት ከነሱትና በቀለ ገርባም አሜሪካ ገብቶ ፓስተር ከሆነ በኋላ የሸኔ ጠንካራ ምሽግ ነው ወደሚባልበት ኬኒያ በመሄድ ነው የመሸገው። እዚያም በርቀት ሆኖ የሚፈልገውን ለማድረግ ብዙም እንዳልቀናው እንዲያውም ያለው ተደማጭነት እጅግ የወረደ መሆኑ በቅርቡ ሲወጡ የነበሩ ቃለ ምልልሶች ጠቋሚዎች ናቸው።
ቤተልሔም ታፈሰ የዛሬ አምስት ወር አካባቢ በጻፈችው መጽሐፍ ዙሪያ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ስለ ጃዋር ብዙ ተናግራ ነበር። ጃዋርን “ቀበሮ መጣ” እያለ ሲያፌዝ በነበረው እረኛ የመሰለችው ቤተልሔም ጃዋር ሲታሰር አገር ይተራመሳል ብላ ገምታ እንደነገር ተናግራለች። በተለይ እርሱ በታሰረበት ወቅት እናቷ አርፈው ወደ አርሲ ለቀብር ስትሄድ የጃዋር ቄሮች “ይጨርሱናል” ብላ ሰግታ እንደነበር አልደበቀችም። ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰችም በኋላ እንዲሁ “ይገድሉናል ብዬ ጠብቄ ነበር” ስትል ተናግራች። አሁን ግን የተረዳችው ነገር ጃዋር ከእንግዲህ ወዲህ አራት ኪሎን የሚያናውጥ ዓቅምም ቄሮም ሆነ ድጋፍ የሌለው፣ ኢነርጂውን የጨረሰ እንደሆነ በወቅቱ በተከሰተ የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ መታዘቧን ታስረዳለች።
ጃዋር በጣም ወደሚመኘው ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ከሁሉ ሰው ጋር ሲጣላ መኖሩን በማሰብ “እንደው መሪ እንኳ ቢሆን ምን ዓይነት ይሆናል? ከማን ጋር ተስማምቶ ይሠራል? ብዬ አስባለሁ” የምትለው ቤተልሔም፤ ጃዋር ደጋፊ ዓልባ መሆኑ በታሰረበት ወቅት በማኅበራዊው ሚዲያ የተማመነባቸው ቄሮዎች ጃዋርን ረስተው የከንፈር ቻሌጅን መጀመራቸውን ታስውሳለች። አገር ይገለባበጣል ተብሎ ሲጠበቅ የጃዋር ቄሮ ግን ከንፈር እያሞጠሞጡ ፎቶና ቪዲዮ እያወጡ የከንፈር ማሞጥሞጥ ቻሌንጅ ውስጥ ገብተው ነበር። ከዚያ ሲቀጥሉ ደግሞ የጥፍር መቀባት ቻሌንጅ ጀመሩ የምትለው ቤተልሔም ወንዱም ሴቱም ጥፍሩን የተለያየ ቀለም እየተቀባ ሲፎካከር ጃዋር ግን እስር ቤት ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በከፍተኛ ምሬትና ተስፋ መቁረጥ ተውጦ ነበር።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ ጃዋር “አልጸጸትም” የሚል መጽሐፍ አሳትሜአለሁ እያለ ያለው። መጽሐፉ አገር ውስጥ እንዳይሰራጭ ዕገዳ ይደረግብኛል ብሎ ስለሰጋ በድንበር በኩል በድብቅ እያስገባ እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ አገኝበታለሁ ብሎ እየፎከረ ያለው ጃዋር መጽሐፉ የኤሌክሮኒክ ሚዲያ ሰለባ ሆኖ 30 ሳንቲም ብቻ “ትርፍ” እንዳያስገኝለት ሰግቷል። “መጽሐፉ እጃችን ይግባ እንጂ አንድም ሳይሸጥ በማኅበራዊ ሚዲያ እንበትነዋለን” ብለው የዛቱም አሉ። እንደ ማስረጃም ሟቹ ሻዕቢያው ተስፋዬ ገብረአብ “ሻዕቢያን የሚያጋልጥ መጽሐፍ ጽፌአለሁና አናግሩኝ” እያለ በዳያስፖራ ያሉትን ሚዲያ ሲለምንና በራቸውን ሲያንኳኳ የነበረው ተስፋዬ መጽሐፉን ሸጦ ራሱንና ሻዕቢያን ሳይጠቅም በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቅቆበት ከስሮ መቅረቱን ያስታውሳሉ። ለጃዋርም “አልጸጸትም” ተመሳሳይ ዕቅድ ተይዞለታል።
ከርዕሱ ጀምሮ እጅግ ያናደዳቸው የጎልጉል የዘወትር አንባቢ ደግሞ አንድ የራሳቸውን ታሪክ በመጥቀስ ንዴታቸውን ገልጸዋል። በደርግ ዘመን በምስራቅ ሐረርጌ አካባቢ መርከቡ የሚባል የኢሠፓ ፓርቲ የወረዳ ምክትል ኃላፊ ነበር። ልጅ ሲወለድለት ተደስቶና ግብዣ አድርጎ “በሉ ለልጄ ስም ስጡ” ብሎ ሲጠይቅ አንዱ የመርከቡ ካድሬያዊ አሠራር ያስመረረው ከአዲስ አበባ የመጣ ያራዳ ልጅ “ስሙ ሰመጠ” ይባል ብሎ ሃሳብ ያቀርባል – ከአባት ስሙ ጋር “ሰመጠ መርከቡ” እንዲባል ማለት ነው። የጃዋርም መጽሐፍ “አልጸጸትም” ሳይሆን “አሲዱ ጃዋር” ቢባል ይሻላል ብለው የርዕስ ማሻሻያ አቅርበዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply