- “የትምህርት ጥራቱ እጅግ አሳፋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል” ዶ/ር መስፍን
- “ከኮሌጅ ተመርቀው 7ኛና 8ኛ ክፍሎችን ለማስተማር ዝግጁ ከሆኑ መምህራን የ12ኛ ክፍል ፈተናን ብቻ ሳይሆን የ8ኛ ክፍል ፈተና ማለፍ አልቻሉም”
- “የኢትዮጵያ 7ኛና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ፣ አሜሪካ፣ ሲንጋፖርና መሰል አገራት የ1ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ ጋር እኩል ነው”
የግንቦት 20 መርዛማ ፍሬዎችን በተከታታይ ባተምንበት ጊዜ ከፍሬዎቹ መካከል “ትውልድ አምካኝ የትምህርት ፖሊሲ” አንዱ እንደነበር መግለጻችን ይታወሳል፡፡ ሕወሓት ሆን ብሎ በሚከተለውና አዲሱን ትውልድ ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ አመለካከት ለመነጠል በሚያራምደው ፖሊሲ በድንቁር ተገዢ አድርጎ የመግዛቱን ዓላማ በፖሊሲ ደረጃ ሲተገብረው ቆይቷል፡፡ በድንቁርና ጭለማ ውስጥ ያሉትን ሹማምንቱን “ተፈጭና ተመረቅ” በሚለው “የመለስ አስተምሮ” መሠረት “ከታወቁ” “የዲግሪና የዲፕሎማ ወፍጮ ቤቶች” “ባለ ዲግሪ” አድርጓቸዋል፡፡ (ጎልጉል በዚህ ዙሪያ የሠራውን ዘገባ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)
ዕውቀት ጠልና ድንቁርና አፍቃሪ የሆነው ህወሓት በመለስ ትዕዛዝና በዱሪ መሐመድ አስፈጻሚነት አገሪቱ በብዙ ልፋትና የውጭ ምንዛሪ ያስተማረቻቸውን 42 የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች በሁለት መስመር ደብዳቤ በማባረር ነበር ዓላማውን ማሳካት የጀመረው፡፡ በቀጣይም በተለምዶ “ድንጋይ ማምረቻ” የሚባለውን የሲቪል ሰርቪስ “ኮሌጅ” አቋቁሞ ካድሬዎችንና ተገዢ “ምሁራንን” በማምረት ጀመረ፡፡ በሌላ አቅጣጫ የትግራይን የትምህርት ፖሊሲ ከአገሪቱ በተለየ ሁኔታ በመቅረጽ “የወርቅ ልጆችን” ለማምረት ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ ለትግራይ ተወላጆች ልዩ የትምህርት ዕድል እንዲከፈትላቸው አደረገ፡፡ የኢትዮጵያን ወጣቶች በድንቁርና ጨለማ ውስጥ ሲያስገባ የትግራይ “ልጆቹን” አቀማጥሎ ማስተማሩን ተያያዘው፡፡
ያልተዘራ እንደማይታጨድ ሁሉ ይህ ዓይነቱ ትውልድ አምካኝ የትምህርት ፖሊሲ በመተግበሩ አሁን ፍሬው “በሚያጠግብ” ሁኔታ እየጎመራ ነው፡፡ “በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ደረጃ በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ሰሞኑን ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት አመለከተ” በማለት አዲስ አድማስ ከሁለት ቀናት በፊት ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ ጥናቱ “የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከእንግሊዙ ዱርሃም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያደረጉት” ሲሆን በጥናቱ የተካተቱት “በአማራ፣ በደቡብ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ 10 ኮሌጆች” መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ጥናቱ በሌሎች ክልሎች በተለይም በትግራይ ለምን እንዳልተካሄደ የገለጸበት ምክንያት ባይኖርም ምናልባት የክልሉ የትምህርት ደረጃ ከሌሎቹ በእጅጉ ያነሰ ወይም ለንጽጽር በሚያስቸግር መልኩ እጅግ የተመነጠቀ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቶበታል፡፡
“ጥናቱን በኮተቤ ኮሌጅ አዳራሽ ያቀረቡት የፊዚክስ ተመራማሪና መምህር ዶ/ር መስፍን ታደሰ፣ “ተማሪዎች በተለይም በፊዚክስና በሂሳብ ትምህርቶች እጅግ ደካማ ሆነዋል” ብለዋል፡፡ የትምህርት ጥራቱን አስመልክቶ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና አጥኚዎች ያደረጉትም ሆነ በራሱ በዩኒቨርሲቲው የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ የአገሪቱ የትምህርት ጥራት ከዓለም አቀፉ መስፈርት እጅግ ያነሰ ደረጃ ላይ ይገኛል በማለት ዶ/ር መስፍን አብራርተዋል”፡፡
“በ2013 እ.ኤ.አ በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የተሰራውን አንድ ጥናት ዋቢ በማድረግ ተመራማሪው እንደገለፁት፤ በአገሪቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ብዙ ተማሪዎች ወደ ት/ቤት ይገባሉ፤ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ዕድልም በስፋት አለ፤ ሆኖም ተማሪዎቹ ከት/ቤት ሲወጡ ማንበብና መፃፍም ሆነ ሂሳብ ማስላት አይችሉም፡፡”
“የትምህርት ጥራቱ እጅግ አሳፋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ የልጆቹ የዕውቀት ደረጃም በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሰፈረው አማካይ ቫልዩ አንፃር 150 ዓመታት ወደ ኋላ መቅረቱ በጥናት ተረጋግጧል፤ ዓለምአቀፍ ፈተናዎችን በመስራት ረገድም ቢሆን በኢትዮጵያ የተመዘገበው ውጤት በጣም ዝቅተኛ (ሆኗል)፡፡ … ከኮሌጅ ተመርቀው 7ኛና 8ኛ ክፍሎችን ለማስተማር ዝግጁ ከሆኑ መምህራን መካከል ለዚሁ ጥናት የተመረጡት የ12ኛ ክፍል ፈተናን ተፈትነው ማለፍ አለመቻላቸውንና የ8ኛ ክፍል ፈተናንም በብቃት ማለፍ እንዳልቻሉ” ዶ/ር መስፍን ጥናቱን ባቀረቡበት ወቅቱ መግለጻቸውን አዲስ አድማስ ዘግቧል፡፡
“የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል በሚል ከእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቅርቡ የተደረገው ይሄው ጥናት፤ የተማሪዎችን የአስተሳሰብ አቅም ከሌሎች አገራት ጋር በማነፃፀር ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በውጤቱም መሠረት “በኢትዮጵያ የሚገኙ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ፣ አሜሪካና ሲንጋፖር በመሳሰሉ የአደጉ አገራት ከሚገኙት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ ጋር እኩል ነው” ይላል ዘገባው፡፡
“መርዛማ ፍሬ 2፡ ትውልድ አምካኝ የትምህርት ፖሊሲ” በሚል ርዕስ ጎልጉል ባወጣው ዘገባ ላይ ይህንን ብለን ነበር፤
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በራሱ በአገዛዙም ሆነ የትምህርት ተቋማቱን በማስፋፋት ከፍተኛ እርዳታ እያደረጉ ባሉ ድርጅቶች ጭምር እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች የትምህርት ፖሊሲውን ክሽፈት የሚያስረዱ ሆነዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የሰራዉ ዘገባ እንደሚያስረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ማጠናቀቂያ (8ኛ ክፍል)፣ የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል (10ኛ ክፍል) እና የሁለተኛ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል (12ኛ ክፍል) ፈተናዎችን የሚያልፉ ተማሪዎች 40% በላይ መሻገር አልቻለም፡፡ በዩኤስኤይድ እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር “Ethiopia Early Grade Reading Assessment” በሚል ርዕስ የወጣው ሪፖርት ደግሞ የፖሊሲውን ሥርዓተ ቀብር የሚያረዳ ነው፡፡ በስምንት ክልሎች ላይ በተዘጋጀው በዚህ ጥናት መሰረት 80% የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (1-4) ተማሪዎች በሚጠበቅባቸው ልክ ማንበብ አይችሉም፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የክፍል ደረጃ ብቻ እየቆጠሩ እና እየተገፉ አልፈው (Promote) በአማካይ ከስምንት ዓመታት በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ መሆናቸው ሲታሰብ የፖሊሲውን መርዛማነት (ትዉልድ አምካኝነት) ለመረዳት ዕድል ይሰጣል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም ባንክ ከፍተኛ የትምህርት ባለሙያዎች “Secondary Education in Ethiopia; Supporting Growth and transformation” በሚል ርዕስ የተሰራው ጥናት ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡት መካከል 61% የሚሆኑት ከ80% በታች የሆነ ውጤት የሚያመጡ ናቸው፡፡ በቀደመው ዓመት የኤስኤይድ (USAID) የአፍሪካ ተማሪዎችን የማንበብ አቅም በተመለከተ ባወጣው የጥናት ዘገባ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የ2ኛ ክፍል ተማሪ ከሆኑት አንድ መቶ ተማሪዎች ውስጥ በአማካይ 33ቱ አንድ ቃል እንኳ ማንበብ አይችሉም፡፡ አረፍተ ነገር እና አጭር ምንባብ ማንበብ የማይችሉት ደግሞ 80% ይሆናሉ፡፡
የዚህ ሁሉ ውድቀት ሥረ-ምክንያት የሆነው በዋንኛነት ሕወሓት በክልል ስም የሚከተለው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሲሆን በቀጣይ በትምህርት ፖሊሲው መሰረት የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት የተማሪዎችን የመማር አቅም ያላገናዘበ መሆኑ፣ መምህራን በሥራቸው ደስተኛ አለመሆናቸው፣ መምህራን ከሚያስተምሩበት ጊዜ ይልቅ ንቃትና ስብሰባ የሚያደርጉባቸው ሰዓታት እጅግ እየበዙ በመምጣታቸው፣ የትምህርት ግብዓት አቅርቦት አለመኖር፣ ትምህርት የሕወሓት ዝቃጭ የአፓርታይዳዊ ዘረኛ ፖለቲካ አመለካከት ማራመጃ በመሆኑ፣ የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ማጣት (ማርፈድ፣ መቅረት፣ ማቋረጥ) ወዘተ ተጠቃሽ የውድቀት ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎች በስልት ሡሰኞች እንዲሆኑ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ አብሮ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከ45ሺ በላይ ዕድሜያቸው ከ4-15 ዓመት የሆናቸው ህጻናት አደገኛ ሱሰኛ መሆናቸውን የዘገብንበትን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡
“የትምህርት ተደራሽነት ላይ አተኩራለሁ” የሚለው ህወሓት/ኢህአዴግ ተደራሽነትን አሻግሮ እያየ የትምህርት ጥራትን ሲደፈጥጥ ይታያል፡፡ ከሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ በኋላ የአገሪቱን የትምህርት ሽፋን 100% ማድረስ አልሆንልህ ብሎታል፡፡ ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ተሳትፎ ከ35 በመቶ ከፍ ማለት አልቻለም፡፡ የትምህርት ዕድልን በስፋት የሚያገኙት የከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (9-10) የከተማ ድርሻ 86% ሲሆን፤ የገጠሩ ክፍል 14% ላይ እንደቆመ ቀርቷል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ሁለተኛ እርከን (11-12) የከተማ ድርሻ 92% ሲደርስ፤ የገጠሩ ድርሻ በሚያሳዝን መልኩ 8% ሆኗል፡፡ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ዞን የዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች “የምንቀመጥበት ድንጋይ ይቆረቁረናል፤ መኪና ሲያልፍ አቧራና ጭስ ያለብሰናል፤ ከጐን ያሉት ተማሪዎች ድምጽ ይረብሻል” ማለታቸውን እዚህ ላይ ተዘግቦ ነበር፡፡
በዚህ መጠነ ሰፊ የሽፋን ክፍተት የተነሳ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ከ9ኛ -12ኛ ክፍል የሚማሩ የገጠር ተማሪዎች ትምህርት ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ በመምጣት በቤት ኪራይ ትምህርት ለመማር ይገደዳሉ፡፡ በዚህ እንግልት የበዛበት ማህበራዊ ውጣ ውረድ ከኢኮኖሚ አቅም ማነስ አኳያ በየአመቱ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ድንቁርናን በፖሊሲ ደረጃ በኢትዮጵያ በማስፋፋት፣ አንድን ክልል ከሌላው በመነጠል “የራሴ” የሚለውን ትውልድ በትምህርት በማበልጸግ፤ የተቀረው የኢትዮጵያ ወጣት በድንቁርና በመጋረድ፣ በተስፋ መቁረጥ በመሸበብ አገር ለቅቆ ወደ ሞት ሸለቆ እንዲሰደድ በማድረግ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሕገወጥ የሰው ዝውውር ሰለባ እንዲሆን በማድረግና ከዚህም ንግድ በማትረፍ፤ አገር ውስጥ የቀረው ተምሮ ለአገሩ እንዳይጠቅም በአገሪቱ ያሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “የተማሩ መሃይማን” እንዲያፈሩ በማድረግ መጪው ትውልድና ሌሎች ተከታታይ ትውልዶች መክነው እንዲቀሩ በማድረግ የማያቋርጥ አዙሪት ተጠቃሚው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ነኝ በማለት ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም በግፍ እየገዛ ያለው ሕወሓት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
መስታወት says
ታድያ ይህ ችግር ማን አመጣው?ተምረናል ብለው ከአሜሪካ ወይም ሲንጋፓር ሻንጣቸውን ሸክፈው የመጡ ኢትዮጽያውያን አይደሉ፡፡