ጠመዝማዛ ባላዎች ላይ የቆመው ክፍል በደደሆ ዛፍ ቅጠል የተሠራ ጣሪያ አለው፡፡ ክፍሉ ውስጥ ከ20 የማይበልጡ ትንንሽ ድንጋዮች ላይ ኩርምት ኩርምት ብለው የተቀመጡ ተማሪዎች ይታያሉ፡፡
ደብተሮቻቸውን በየጉልበታቸው ላይ አድርገው ከፊት ለፊታቸው ያለውን መምህር ያዳምጣሉ፡፡
ከመሬት ብዙም የማይርቀው የክፍሉ ጣሪያ መምህሩን ጐንበስ ብሎ እንዲያስተምር ግድ ብሎታል፡፡ መምህሩ ለማለቅ በተቃረበ ነጭ ጠመኔ ያረጀ ሰሌዳ ላይ ቁጥሮች እየጻፈ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሒሳብ ያስተምራል፡፡
የክፍሉ ጣሪያ በሳሳበት አቅጣጫ የተቀመጡ ተማሪዎች ጸሐይ ይመታቸዋል፡፡ ተማሪዎቹ ድንጋዩ ጐርበጥ ሲያደርጋቸው ወደ አንድ ወገን ገደድ እያሉ ለመመቻቸት ይጣጣራሉ፡፡ እነዚህ በዛፍ ጥላ ስርና በዳስ የሚማሩ ተማሪዎች የመኪና ድምጽ በሰሙ ቁጥር አንገታቸውን አጠማዘው ይመለከታሉ፡፡ ግድግዳ በሌለው ክፍላቸው አቅራቢያ የሚተላለፉ መንገደኞች የሚሰነዝሩትን የለበጣ አስተያየት በዝምታ ያሳልፋሉ፡፡
አካባቢው በረዣዥም ተራሮች የተከበበ ነው፡፡ ከመኖሪያ መንደሩ ራቅ ብለው ኮረብታ ላይ ሦስት የዛፍ ጥላና የዳስ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ ክፍሎቹ ከአንደኛ ክፍል እስከ ሦስተኛ ሲሆኑ፣ የሦስቱም ክፍል ተማሪዎች በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ መምህር ይማራሉ፡፡ መምህሩ ለአንዱ ክፍል ሒሳብ የክፍል ሥራ ይሰጥና ተማሪዎቹ እስኪያጠናቅቁ አማርኛ ለማስተማር ወደ ቀጣዩ ክፍል ያቀናል፡፡ የቀረው ክፍል ተማሪዎች ደግሞ ተራቸው እስከሚደርስ ይጠባበቃሉ፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስር ከሚገኙ ሦስት የብሔረሰብ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው ዋግኽምራ ዞን ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ በሚገኙት 514 የዛፍ ጥላና የዳስ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የጎበኘነው የዋግኽምራ ዞን ዋና ከተማ ከሆነው ሰቆጣ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የጋዝጊብላ ወረዳ ውስጥ ያለውን የጽዮን ሳተላይት የዛፍ ጥላና ዳስ ክፍሎች ነው፡፡ በወረዳው ያሉ የዛፍ ጥላና ዳስ ክፍሎች በጽዮን ሳተላይት ትምህርት ቤት ስር ናቸው፡፡ ጽዮን ሳተላይት በ2002 ዓ.ም. 39 ተማሪዎች ይዞ የተጀመረ ሲሆን፣ 2006 ዓ.ም. ሦስተኛ ክፍል 41 ተማሪ፣ ሁለተኛ ክፍል 30 ተማሪዎች እንዲሁም አንደኛ ክፍል 22 ተማሪዎች ተምረውበታል፡፡
የአካባቢው የዛፍ ጥላና ዳስ ክፍሎች የሚሠሩት በተማሪዎች፣ በወላጆቻቸውና በመምህራን ነው፡፡ በየዓመቱ ከምሳና፣ ከእምቧጮ ዛፍና ከደደሆ ዛፍ ቅጠል የሚሠሩ ክፍሎች በዓመቱ አጋማሽ ላይ ቅጠላቸው ደርቆ ጸሐይ ያስገባሉ፣ በዓመቱ ማገባደጃ ላይ ደግሞ የዝናብ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ የክፍሎቹ ወለል በፀሐይ አቧራ፣ በዝናብ ጭቃ ይሆናል፡፡
አብዛኞቹ ክፍሎች በክረምት ለማገዶነት ይውሉና በበጋ እንደ አዲስ ይሠራሉ፡፡ የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪዎች እንደገለጹልን የክፍሎቹን ማገር አቃጥሎ መጠቀም በሌሎች ወረዳዎች የተለመደ ቢሆንም እነሱ በሚኖሩበት ወረዳ ቀርቷል፡፡
በአካባቢው ያሉ ተማሪዎች በዛፍ ጥላ ወይም በዳስ ስር ትምህርት ማግኘት የሚችሉት እስከ ሦስተኛ ክፍል ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ለመማር ብዙ ኪሎ ሜትሮች በእግራቸው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ርቀቱን ችለው የሚማሩ ተማሪዎች ቢኖሩም ደረጃቸውን ባልጠበቁ ክፍሎችና በውስን መምህራን የሚማሩ ናቸው፡፡
የመማሪያ ቦታ፣ የመምህራንና የትምህርት መሳሪያ እጥረትን ተቋቁመው ወደ ሰቆጣ ከተማ በማምራት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚማሩ፣ ከዚያም አልፈው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉ ተማሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ብዙሃኑ እስከ ሦስተኛ ክፍል ተምረው ያቋርጣሉ፡፡ ሦስተኛ ክፍል ድረስ የማይደርሱና ከነጭራሹ የማይማሩም በርካቶች ናቸው፡፡
በዛፍ ጥላና በዳስ የሚማሩ ተማሪዎች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ፤ የተሟላ የመማሪያ ቦታና መሳሪያ ባልተመቻቸበት የትምህርት ጥራት ምን ያህል የተጠበቀ ነው? ስንቶቹ ተማሪዎች ናቸው ችግሩን ተቋቁመው አልፈው በትምህርት ራሳቸውንና አገራቸውን የሚቀይሩት? የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲና ትምህርትን ለሁሉም የማዳረስ ዘመቻ የቱ ጋ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ያጭራል፡፡
በዛፍ ጥላ ስር ሲማሩ ካገኘናቸው አንዷ ወይዘር መንግሥቱ ናት፡፡ አሥር ዓመቷ ሲሆን የ3ኛ ክፍል ተማሪም ናት፡፡ አካባቢ ሳይንስ፣ ሒሳብ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ በአንድ መምህር የሚማሩ ሲሆን፣ ዝናብ ሲመጣ የክፍሉ ጣሪያ ስለማያስጥላቸው ሰሌዳ ላይ የሚጻፈው በእርጥበት እየጠፋ እንደሚስተጓጎሉ ትናገራለች፡፡
ሰሌዳቸው የሚቀመጠው በአስተማሪው መኖሪያ ቤት ስለሆነ በየቀኑ ጠዋት ላይ ከአስተማሪው ቤት ወደ ክፍል የማምጣትና 6፡00 ሰዓት ሲሆን መመለስ የወይዘርና ጓደኞቿ ድርሻ ነው፡፡
ወይዘር ከትውልድ ቀዬዋ ወጥታ ስለማታውቅ ትምህርት ቤት በአጠቃላይ በዛፍ ጥላ ስር ወይም በዳስ ይመስላታል፡፡ ክፍሉ አመቺ እንዳልሆነ ብትናገርም ሌላ ማነጻጸሪያ የሚሆኗት ክፍሎች ስላላየች ያሉበትን ችግሮች ከመዘርዘር ይልቅ ‹‹ትምህርቱ ሸጋ ነው›› ትላለች፡፡
ወይዘር እንደምትለው መምህሩ ከሰኞ እስከ ዓርብ ከጠዋት እስከ ቀትር ድረስ አራቱን ትምህርቶች እየለዋወጠ ያስተምራቸዋል፡፡ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ያሉት አጠገብ ለአጠገብ ስለሆነ መምህሩ በሦስቱም ክፍል እየተዘዋወረ ያስተምራል፡፡ የወይዘር አባት አርሶ አደር፤ እናቷ ደግሞ የቤት እመቤት ናቸው፡፡ ለቤቷ ሁለተኛ ልጅ ስትሆን ታላቅ እህቷ እስከ ሦስተኛ ክፍል ከተማረች በኋላ ትምህርቷን አቋርጣለች፡፡ አሁን ደግሞ ተድራለች፡፡
ወይዘር የሒሳብ ክፍለ ጊዜን ትወደዋለች፡፡ ሦስተኛ ክፍልን የጨረሰችው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት ትምህርት ስለመቀጠሏ እርግጠኛ አይደለችም፡፡ ቢሆንም ‹‹አስተማሪ መሆን እፈልጋለሁ›› ስትል ምኞቷን ትገልጻለች፡፡ የእህቷ ዕጣ ፈንታ እንደማይደርሳትና በሆነ መንገድ ትምህርቷን እንደምትቀጥልም ታምናለች፡፡
የ12 ዓመቱ ሻምበል አዳነ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ‹‹ክፍሉ ውስጥ የምንቀመጥበት ድንጋይ ይቆረቁረናል፤ መደገፊያና ማስደገፊያ ስለሌለ አዘቅዝቀን እንጽፋለን፡፡ መኪና ሲያልፍ አቧራና ጭስ ያለብሰናል፤ ከጐን ያሉት የሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ድምጽ ይረብሻል፤›› ይላል፡፡ ሻምበል እንደገለጸልን ትምህርት ቤት የሚመዘገቡት ቤተሰቦቻቸው ቅስቀሳ ከሰሙ በኋላ ሲሆን፣ ትምህርት ጀምረው የሚያቋርጡ ተማሪዎችም ብዙ ናቸው፡፡
ሻምበል ከሦስተኛ ክፍል በኋላ በጭቃ ወደተለሰኑ ክፍሎች ሄዶ እንደሚማር ከቤተሰቦቹ ሰምቷል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የዛፍ ጥላ ክፍሎች ለብርድ፣ ለአቧራና ለጨረር ፍልቅታ የዳረጓቸው ጓደኞቹ ታመው መቅረታቸውን ይናገራል፡፡ በትምህርት ወቅት ክፍሎቹ የተሠሩበት እንጨት ሲወድቅ ተማሪው ተባብሮ እንደሚያስተካክልም ገልጾልናል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች እየተሳሳቁባቸው ያልፋሉ፡፡ የሻምበል ህልም ከወይዘር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በልጅ አንደበቱ ‹‹ያልተማሩትን ለማስተማር፤ ያላወቁትን ለማሳወቅ አስተማሪ እሆናለሁ፤›› ይላል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የሚማሩ ተማሪዎች በሌሎች ክልሎችም እንዳሉ አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ በዋግኽምራ ዞን የሚገኙ መደበኛ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ከአብዛኛው ሰው የትውልድ ቀዬ ርቀው ይገኛሉ፡፡ ሩቅ ሄደው ለመማር አቅም የሌላቸው ሕፃናት ፊደል ሳይቆጥሩ ከሚቀሩ በሚል በየመንደሩ የዛፍ ጥላና ዳስ ክፍሎች ይዘጋጃሉ፡፡
አቶ ሙላቱ ሀብቱ የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው በዳስ ስር ተምሮ አልፎ ዛሬ የመንግሥት ሥራ ይዟል፡፡ ሁለተኛው ልጃቸው የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ‹‹ልጆቻችን የጭራሮ ቤት ውስጥ ይማራሉ፤ መንግሥት ይህን አስተካክሎ ወንበርና ግድግዳ ባለው ትምህርት ቤት ልጆቻችን እንዲማሩ እንፈልጋለን፤›› ይላሉ፡፡
በሌሎች አካባቢዎች እንዳስተዋሉት፤ የጋዝጊብላ ሕፃናት ከቤት ርቀው እንዳይሄዱ በመንደራቸው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት እንዲሠራላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ጐልማሳው ለዓመታት የዘለቀው የዛፍ ጥላና የዳስ ስር ትምህርት ቤት ችግርን አልፈው እንደ መጀመሪያ ልጃቸው ደመወዝተኛ የሚሆኑ ወጣቶች ጥቂት ቢሆኑም ‹‹ተስፋ ናቸው›› ይላሉ፡፡
በየዓመቱ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩት የቀበሌ አስተዳደርና መምህራን ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ ሲሆን፣ ትምህርት የሚጀመረው በህዳር ወይም ታኅሣሥ ላይ ነው፡፡ የአካባቢው (ቀበሌ 07) ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሰጠኝ ማሞ እንደሚሉት አብዛኛው ቤተሰብ ልጆቹ ከሚማሩ ይልቅ በግብርና ሥራ ቢያግዙት ይመርጣል፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተሰብ መኸር ሲደርስ ልጆችን ከትምህርት ገበታ ያስቀራል፡፡ ቅስቀሳ ተደርጎ ተማሪዎች ከተመዘገቡ በኋላም በአመቺ ሁኔታ ስለማይማሩ የትምህርት ጥራቱ የተጠበቀ አይደለም፡፡ በዛፍ ጥላና ዳስ ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራንም ዝውውር ጠይቀው ወደ ሌላ አካባቢ ይቀየራሉ፡፡ ከጥቂት ከወራት በላይ የሚቆዩ መምህራን አይገኙም፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዳንዶቹ ትምህርት ቤት ለማስገንባት አስፈላጊውን ግብዓት ለማሟላት ፈቃደኛ ቢሆኑም ገቢያቸው አነስተኛ ስለሆነ ለዓመታት ምንም ለውጥ አልመጣም፡፡ አቶ ሰጠኝ ራሳቸው በዛፍ ጥላ የተማሩ ሲሆን፣ እስከዛሬ ምንም ለውጥ አለመምጣቱ እንደሚያሳዝናቸው ይናገራሉ፡፡
ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡን የጋዝጊብላ ወረዳ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ሥራ ሒደት ዋና አስተባባሪ አቶ ካሳ ቸኮል ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው፣ በአካባቢው ካሉ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ይልቅ በዛፍ ጥላና በዳስ ስር የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡
‹‹ተማሪዎቹ ባሉበት ሁኔታ እየተማሩ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ራሳቸው ቤተ ሙከራና ቤተ መጽሐፍት የሌላቸው በመሆናቸው የትምህርት ጥራትን የወረደ ያደርገዋል፡፡ ደረጃውን ባልጠበቀ ሁኔታ የሚማሩ ተማሪዎች እንዴት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳድረው ትልቅ ደረጃ ይደርሳሉ?›› በማለት አቶ ካሳ ይጠይቃሉ፡፡
እንደ ኃላፊው፣ መንግሥት ለትምህርት የደረሰ በሙላ መማር አለበት የሚል መርህ ያለው ቢሆንም በዛፍ ጥላና በዳስ ስር ከሚቀርበው ትምህርት አኳያ መርሁ እየተጠበቀ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለማስተማር የታቀደውን ተማሪ ያህል እየተማረ አይደለም፡፡ ጥራቱን የጠበቀ መማሪያ ቦታና የትምህርት መርጃ መሣሪያ ባይኖርም ታዳጊዎች ቤት ከሚቀመጡ በተገኘው አማራጭ ቢማሩ ይሻላል የሚሉት አቶ ካሳ፤ አሁን ያለው ሁኔታ ቀስ በቀስ እንደሚቀረፍ እምነት አላቸው፡፡
አቶ ካሳ እንደገለጹልን፤ በየዓመቱ የዛፍ ጥላ ስርና ዳስ ክፍሎችን ቁጥር ለመቀነስ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የጽዮን ሳተላይት ክፍሎችን ከመኪና መንገድ ዘወር ለማድረግ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁና በቅርቡ በየጐጡ እየተዘዋወሩ ተማሪ እንዲመዘገብ እንደሚቀሰቅሱ ይናገራሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ያሉ መማሪያ ክፍሎች ወደተሻለ ቦታ ሲዘዋወሩ ከችግሮቹ ጥቂቱ እንደሚቀረፍ ይጠቁማሉ፡፡
የዋግኽምራ ዞን የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ እንደሚሉት፤ በቀጣይ ባሉ ዓመታት የሳተላይት ትምህርት ቤቶች ተቀጢላ የሆኑትን የዛፍ ጥላና ዳስ ስር ክፍሎች በማሻሻል መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ትምህርት ቤቶች ለመገንባት የአካባቢው ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር አብዛኛው ነዋሪ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክ ለማድረግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ያስፈልጋል፡፡
የአካባቢው ተማሪዎች ለመሰናዶ ትምህርት የሚያስመዘግቡት ውጤት ዝቅ ያለ መሆኑና አብዛኛው ተወላጅ አለመማሩ ከመማሪያ ክፍሎቹ ይዘት ጐን ለጐን የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ሽታው፤ ከአካባቢው ተወላጆችና በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላት ጋር እየተደረገ ያለው ምክክር መፍትሔ ይዞ የሚመጣ ይሆናል፡፡
በዛፍ ጥላ ስርና በዳስ ከሚማሩ ተማሪዎች አብዛኞቹ መምህር የመሆን ፍላጎት አላቸው፡፡ መማሪያ ክፍሎቻቸው ባይመቿቸውም ትምህርቱ እስከሚያዘልቃቸው ድረስ መማር ይመርጣሉ፡፡ ታዳጊዎቹ በትምህርት ዘርፍ በቀጣይ የሚገጥማቸውን ባያውቁም የተሻለ እንደሚመጣ በተስፋ የሚጠባበቁ ናቸው፡፡(ምንጭ: ሪፖርተር)
hassen says
ለማወቅ ያላቸው ጉጉት በጣም ነው የሚገርመው .አቦ አላህ ይርዳቸው