- “በመንገዶች አምራ በፎቆች ተውባ” የህወሃት/ኢህአዴግ ኩራት የሆነችው አዲስ አበባ
- “አገሪቱ አሁን ያለችበት ሂደት በእሳት ላይ ተጥዶ እንደሚንተከተክ ማሰሮ ትመስላለች”
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሁሉ ነገር ነች፡፡ ከተማዋ ከፖለቲካ ከተማነቷ ባሻገር የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፎች ማዕከል መሆኗ የብዙዎችን ትኩረት እንድትስብ አድርጓታል፡፡ በክልሎች የሚታየው የሥራ ዕድል ዕጦት፣ ይህን ተከትሎ የተፈጠረው ሥር የሰደደ ድህነት አዲስ አበባን የከተማ ስደት መከማቻ ማዕከል አድርጓታል፡፡
በርግጥ የከተማ ስደት ስረ-መነሻ ከቀደሙት ጊዜያቶች ጀምሮ የተለያየ መንስኤ አለው፡፡ የኢትዮጵያን የከተማ ስደት ከአገሪቱ ማህበረ-ኢኮኖሚና የፖለቲካ መዋቅር ጋር አስተሳስረው የሚያጠኑ ምሁራን የከተማ ስደትን ከኢትዮጵያ ከተሞች አመሠራረት ጋር አያይዘው የጥናት ውጤታቸውን ያቀርባሉ፡፡
በጥንቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ከገናናው የአክሱም ሥልጣኔ እስከ ዛጉዌ ላስታ ዘመን፣ ከሐረር ሱልጣኔቶች እስከ ሸዋ ነገሥታት፣ ከጎንደር ነገሥታት እስከ ዘመነ መሳፍንት በነበሩ ጊዜያት እንደነገሥታቱ አነሳስና አመጣጥ ከተሞች ተቆርቁረዋል፡፡ የከተሞችን መቆርቆር (መመስረት) ተከትሎ ከገጠር ወደ ከተማ በመፍለስ የሥነ-ህዝብ አሰፋፈሩ በጊዜ ሂደት ቅርጽ እየያዘ ቢሄድም ከነገሥታቱ መውድቅና መነሳት ጋር በተያያዘ የከተሞች ዘላቂ ዕድገት ቀጣይነት የሌለው የአንድ ወቅት የሥልጣኔ አሻራ ከመሆን የተሻገረ ሊሆን አልቻለም፡፡ አንዳንድ የነገሥታት ከተሞች ከቶውንም ከነገሥታቱ መኖሪያ (ቤተ መንግሥት) ውጪ ይህ ነው የሚባል የከተማ አሻራ የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚ ተጠቃሹ የዛጉዌን ዘመነ መንግሥት የሮሃ ላስታ ጉዳይ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በስተቀር ይህ ነው የሚባል የከተማ አሻራ የለም፡፡ የጁም ተመሳሳይ ይዘት ያለዉ ነዉ፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ጀማሪ የሆነው ዳግማዊ ቴዎድሮስ የንግሥናውን መንበር ሲቆናጠጥ፤ መቀመጫውን መቅደላ ላይ ሲያደርግ፤ የጎንደር የተሟሟቀ ከተማነት እየነጠፈ በአንፃሩ መቅደላ እየከተመች መጥታ ነበር፡፡ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ህልፈት በኋላ መቅደላ ከቶውንም እንዳልነበረች ስትጠፋ በአንፃሩ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ መናገሻ አንደርታ (መቀሌ) የከተሜነት ቅርጽ ለመያዝ በቃች፡፡
በነዚህ ጊዜያቶች ሁሉ ከነገሥታቱ መውደቅና መነሳት ጋር በተያያዘ ከተሞች ህልውናቸው ሲከስምና ሲነሳ ኖሯል፡፡ ነገሥታቱ መናገሻ ከተማ በሚያደርጓቸው ከተሞች ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አዲሱ ከተማ የመፍለስ ልማድ ነበራቸው፡፡ በወቅቱ ፍልሰቱን የሚያጠናክሩት ደግሞ ወዶ-ገብ ወታደሮች፣ አዝማሪዎች፣ የቤተ ክህነት ሰዎች፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በአነስተኛ የጉሊት ችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ እና የሲራራ ነጋዴዎችን ተከትሎ የጉልበት ሥራ የሚሰሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች አመሰራረትም ከሱልጣኔቶች አነሳስ እና ከእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮታዊ መስተጋብሮች ጋር የተያያዘ ለመሆኑ የጥናት ውጤቶች ይመሰክራሉ፡፡
ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው በዋናነት የከተማ ስደት ታሪክ ከዳግማዊ ምኒልክ የአገር ግንባታ ሂደት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን በዘርፉ ጥናት የሰሩ ምሁራን የጋራ ምልከታ ነው፡፡ በእምዬ ምኒልክ የአገር ግንባታ ሂደት አዲስ አበባን ጨምሮ አዳዲስ ከተሞች የሚመሰረቱበት ጊዜ ስለነበር፣ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለመቀጠር ብዛት ያለው ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተማ ፈልሷል፡፡
የጅቡቲ አዲስ አበባ የባቡር መስመር ዝርጋታን ተከትሎ የምስራቁ ክፍል ከደቡብ ኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) ጋር በተሳለጠ መጓጓዣ መተሳሰሩ ለፍልሰቱ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚህ የታሪክ ምዕራፍ በኋላ የከተማ ስደት ባህል እየሆነ መጣ፡፡ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት፣ ከተሜነት መስፋፋቱ እና የሥራ ክፍፍል መደባዊነት መፈጠሩ ለከተማ ፍልሰት ሌላ በር ከፋች ሆነ፡፡ በዘመነ ደርግ ጊዜያትም ለገጠሬው ወደ ከተማ መፍለስ በርካት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የባላባቶች መሬት መነጠቅ፣ የንግድ እርሻዎች መዘጋት፣ በከተሞች አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች መከፈት እና አዳዲስ ኬላዎች ሥራ መጀመራቸው ለፍልሰቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ድህረ-ደርግን ተከትሎ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት ላይ የተመሰረተው የክልሎች አከላለል ፍልሰቱን ለጊዜው የገደበው ቢመስልም በክልሎች የሚታየው ኢ-ፍትሃዊ የገቢ ልዩነት ከሥነ-ህዝብ ፖሊሲው አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ ፍልሰቱን በተለየ መልኩ ጨምሮታል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በነበሩት አስራ አምስት አመታት (እስከ ድህረ-ምርጫ 97) ድረስ “ለገጠር ፖሊሲዬ እታመናለሁ” በማለት ከተሞችን ዘንግቶ ቆይቶ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን አንፃራዊ ማህበራዊ ፍትህ ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ ይደረጉ የነበሩ ፍለስቶች ከዛሬው ጋር በቁጥር ለንፅፅር ባይቀርቡም ቀላል የማይበል ፍልሰት ነበር፡፡
ከምርጫ 97 በኋላ ገዥው ኃይል ሙሉ ትኩረቱን ከተሞች ላይ በተለይም አዲስ አበባ ላይ በማድረጉ ወትሮውንም በማህበረ-ኢኮኖሚ መስክ ራሱን ያልቻለው የገጠሩ ኢትዮጵያ ክፍል ጥልቅ ችግር ላይ ወደቀ፡፡ የገጠሩን ነዋሪ ለፍልሰት ከሚዳርጉት በርካታ ገፊ ምክንያቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ችጋር፣ ድርቅ እና ረሃብ፣ ትምህርት እና ጤና አገልግሎት፣ ያልተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ፣ የግብርና ምርት ማሽቆልቆል እና የሥራ ዕድል እጦት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ እና ተያያዥ ምክንያቶች ከገጠር ወደ ከተማ በተለይም ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ፍልሰቶች በአሁኑ ጊዜ መቆሚያ አጥተዋል፡፡
አፓርታይዳዊ የዘር ፖሊሲን በመከተል ከፋፋይና በታኝ ዘውጋዊ ልዩነቶችን፣ የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማንሳት፤ ደማቅ የልዩነት መስመር ያስመረው ገዥው ኃይል፣ በክልል ከተሞች ዜጎች በነፃነት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መስራት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል – ከትግራይ ተወላጆች በስተቀር፡፡
የአዲስ አበባ የሥራ ነፃነትም ሆነ የሥራ ዕድሎች በጫማ ጠረጋ (ሊስትሮ)፣ እንደ ማስቲካ፣ ሲጋራ፣ ሶፍት፣ የሞባይል ስልክ ካርድ፣ ትንንሽ ሸቀጣ ሸቀጦች ሽያጭ፣ የግንባታ እና የቀን ሥራዎች ላይ፣ በቤት ሰራተኝነት እና በሴተኛ አዳሪነት በመሰማራት የሚተረጎም የሥራ ነፃነት እና የሥራ ዕድል እንጂ ከዚያ የተሻገረው ትርፋማ የሥራ ዘርፍ ለትግራይ ተወላጆች እና ለገዥ መደቡ ሎሌዎች በተዋረድ ተከልለው የተቀመጡት ናቸው፡፡
ከምርጫ 97 በኋላ የአዲስ አበባ ሥነ-ህዝብ አስፋፈር (Demography)፣ የኢኮኖሚ አሰላለፍ (Formation of economy)፣ ከፖለቲካ መዋቅሩ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ባስፈነጠረው መለስ አንደበት “የነፍጠኞች ከተማ” የምትባለዋን አዲስ አበባ መዋቅራዊ ድጋፍ (state sponsor) በሆነ መልኩ በትግራይ ተወላጆች ብቻ መሙላት ከአናሳነታቸው አኳያ የማይታሰብ ሆኗል፡፡ አማራጩ የትግራይ ሰዎችን በተሻለ ማህበረ-ኢኮኖሚ ልዕልና ቦታ ላይ በማስቀመጥ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል በዕለት ተዕለት ኑሮ ባተሌ ማድረግ ለህወሓት ተመራጭ መንገድ ሆኗል፡፡ የትግራ ተወላጆች በአዲስ አበባ ከተማ ያላቸው የበላይነት ምንጩ ፖለቲካዊ ኃይል የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ፖለቲካዊ ኃይሉን ተደግፎ የኢኮኖሚ በዝባዥነት፣ ዝርፊያ፣ ቀማኝነትና ነጣቂነት የትግራይ ሰዎች መገለጫ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ የቀደመ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሥሪት በማደብዘዙ ረገድ የደቡብ ኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ከገጠር ወደ ከተማ የሚያድርጉት ስደት (ፍልሰት) ለገዥው መደብ አዋጪ አጋጣሚ ቢመስልም ማህበራዊ ቀውሱ ግን ከከተማዋ ባሻገር አደጋ ያለው ሁነት ሆኗል፡፡ የእነዚህ ወጣቶች በተለየ መልኩ ወደ አዲስ አበባ የመፍለስ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጅጉ አየተባባሰ መጥቷል፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “በግብረሰዶማዊያን የተወረረችው አዲስ አበባ!” በሚል ርዕስ ባስነበበው የዜና ሃተታ እነዚህ ወጣቶች በምን ዓይነት መልኩ ወደ ሰዶማዊነት እየገቡ እንደሆነ አስነብቧል፡፡
አዲስ አበባ ማስተናገድ ከምትችለው በላይ የህዝብ ብዛት ተከማችቶባት ይገኛል፡፡ በአንፃሩም ቢሆን ወደ ውጭ አገር የሚደረጉ ስደቶች በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የጠበቀ የሰራተኞች ፖሊሲ የተነሳ (የሳውዲ አረቢያን፣ ኳታርን፣ ኩዌትን ወዘተ አረብ አገራት እርምጃዎች ያስታውሷል) የአገር ውስጡን ሥራአጥ ቁጥር ማስተንፈሻ መንገድ (safety valve) ዘግቶታል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚሰደዱ ዜጎች ብዙውን ጊዜ ከተማ ውስጥ ሥራ በማጣት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እየታየ ያለው የማህበረ-ኢኮኖሚ ተግዳሮትም የዚህ ችግር አካል ነው፡፡ ቁጥራቸው የበዛ ታዳጊ ወጣቶች ለጎዳና ህይወት ተዳርገው ማየት የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ መፈጠርን በሚያስጠላ መልኩ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ የሥጋ-ደዌ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ነዳያን (የሚጭበረብሩ ጥቂቶች መኖራቸውን ሳንዘነጋ) የእግረኛ መንገዶችን አጣብበው ሲለምኑ ይውላሉ፡፡ “ወገን ራበኝ አጉርሱኝ አልብሱኝ”፣ “የቤት ኪራይ የምከፍለው አጣሁ”፣ “ባለቤቴ .. (ቁጥር ያላቸው) ልጆቼን ጥሎብኝ ሞተ”፣ “የማርያም አራስ ነኝ እርዱኝ”፣ “ቤቴ ለልማት በሚል ፈረሰ፤ መጠለያ ያጣሁ ችግረኛ ነኝ”፣ . . . ወዘተ የሚሉ የልመና ድምፆች የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ሞልተውት ውለው ያድራሉ፡፡
በየቤተ-እምነቱ ደጃፍ በመኮልኮል በልመና ተግባር ከተሰማሩ ዜጎች ቁጥር በእጥፍ በሚልቅ ደረጃ የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን ያጣበቡ ነዳያን ተበራክተዋል፡፡ ውሎና አዳራቸው ጎዳና ላይ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች በህብረ-ዝማሬ (በእነርሱ ቋንቋ “ቅፈላ”) አላፊ አግዳሚውን ሲለምኑ የሚውሉትም በርካታ ናቸው፡፡ የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም በሚል ቤንዚል በስፖንጅ አድርገው ወደ አፍንጫቸው በማስጠጋት የሚስቡት የጎዳና ልጆች፤ ቤንዚሉ በሚፈጥርላቸው የአዕምሮ መነቃቃት (መደፋፈር) የወንጀል ተሳታፊ ሆነው ሲገኙ ይስተዋላል፡፡
በአዲስ አበባ የኮንደሚኒየም መኖሪያ ቤቶች እና በከተማዋ ዳርቻ አካባቢዎች ተዘግተው የሚውሉ መኖሪያ ቤቶችን በቀን (ቤት) ገልብጠው የሚገቡ ሌቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተከታታይ ዘገባዎች አመላካች ናቸው፡፡ በምሽትና በሌሊት ተዝናንቶም ሆነ ማህበራዊ ጉዳይን ከውኖ በሰላም ወደ ቤት መግባት የማይታሰብበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ የሞባይል ንጥቂያና የአካል ማጉደል የወንጀል ተግባራት እየተበረከቱባት ባለችው አዲስ አበባ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት ለከተማዋ ወንጀል መበራከት ጉልህ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡
በህወሓት/ኢህአዴግ አጠራር “አተት” የተባለውን ተላላፊ (የኮሌራ) ወረርሽኝ በሽታ ያህል የዜና ሽፋን እያጣ ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ጉዳይ ከፍልሰቱ ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን የከተማዋን ሴተኛ አዳሪዎች መበራከት ተከትሎ ቫይረሱ መዛመቱን እንደቀጠለ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የግብረሰዶማዊያን መበራከት ጉዳይም ከፍልሰቱ ጋር የተያያዘ ደጋፊ ምክንያት አለው፡፡
ሩብ ክፍለ ዘመን የተሻገረው የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ የፈጠረው የፖለቲካ ነፃነት እጦት እንደተጠበቀ ሆኖ የትግራይ የኢኮኖሚ ሊሂቃንና የገዥ መደቡን ተለጣፊ ሎሌዎች ከማበልፀግ ባሻገር እንደ አገር ይህ ነው የሚባል የጋራ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ሊያካፍል አልቻለም፡፡
በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት የሚደረገው ስደት እያስከተለ ያለው ማህበራዊ ቀውስ የሚያባራ አልሆነም፡፡ ከዚህ ችግር ባልተናነሰ መልኩ በአገሪቱ የተለያዩ ገጠራማና የክልል ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ የሚያድርጉት ፍልሰት ለነባሩ ነዋሪም ሆነ በፍልሰት ከተማዋን ለሚቀላቀሉት ዜጎች የማይመች ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲፈጥር እየታየ ነው፡፡
የሥራ አጥነት መበራከት ወደ ወንጀል ድርጊት እንደሚገፋ አዲስ አበባ ውስጥ በየዕለቱ የሚመዘገቡ የወንጀል ሪከርዶች አስረጅ ምሳሌዎች ይሆናሉ፡፡ የወሲብ ንግድ፣ ልመናና የጎዳና ህይወት የማህበራዊ ቀውስ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ለአንድ ዘር ልዕልና የሚተጋው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ እስካልተነቀለ ድረስም እነዚህ ችግሮች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ይገመታል፡፡
የሥርዓቱ መክሸፍ ወይም ነውር በማያውቀው ሟቹ መለስ አነጋገር “መበስበስ” የእነዚህ እና የሌሎች ኢኮኖሚያዊ በተለይም ማኅበራዊ ችግሮች መባባስ አስረጅዎች ናቸው፡፡ የኢህአዴግ ውጤቶች ናቸው፤ የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፤ … እያለ በየዕለቱ በሚደሰኩረው መግለጫው በህወሓት ሰዎችና ሎሌዎቻቸው ከሕዝብ እየተመዘበሩ የተሰሩ ፎቆችን፤ ተከፍሎ በማያልቅ ብድር ዓመታትን መዝለቅ የማይችለውን መንገድ እና ሌሎች ጥራዝነጠቅ “የልማት ውጤቶችን” በማሳየት “ሁሉ ሰላም ነው” በማለት የግዛት ዘመኑን ለማርዘም ይተጋል፡፡ ማስጠንቀቂያ መስማትም ሆነ አለ ብሎ ማሰብም አይፈልግም፡፡ ማኅበራዊው ሰቆቃ የፖለቲካው ክሽፈት ማሳያ አድርጎ ለመውሰድ ባለመፈለግ ለማንኛውም የዜጎች የጣዕር ጩኸት ምላሹ “ጥሪ አይቀበልም” ሆኗል፡፡
በባራክ ኦባማ አስተዳደር የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ቶም ማሊኖውስኪ ባለፈው ታህሳስ ወር ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ የአገሪቱን ሁኔታ ቢዘህ መልኩ ነበር የገለጹት፡፡ “አገሪቱ አሁን ያለችበት ሂደት በእሳት ላይ ተጥዶ እንደሚንተከተክ ማሰሮ ይመስላል። እናም እንዲህ የሚንተከተክ ማሰሮ ለማስተንፈስ ያለው ምርጫ ክዳኑን ማንሳት ብቻ ነው፤ ያ ካልተደረገ መንተከተኩ አያቆምም። በዚያ ከቀጠለ ደግሞ መገንፈሉ አይቀርም። ከዚያ በኋላ የሚሆነው ሁላችንም እናውቀዋለን”፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
yalew akele says
አምላክ ሆይወይ ፍረድ ወይ ወረድ ምነው ትግስትህ በዛላቸው ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ብርቱልኝ እናንተ የህዝብ አይንና ጀሮ አመሰግናለው፡፡