የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) የተባለ የወንበዴዎች ስብስብ በምዕራባውያን አንጋሾቹ ታግዞ የምኒልክን ቤተመንግሥት ከተቆጣጠረ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቃላት እንደ እሣት እየተፉ ታሪክ ፈጽሞ ሊረሳው የማይችለውን ንግግር ያደረጉት ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ – ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ!! ስለ ኤርትራ መገንጠል እና ስለ ህወሃት የአስፈጻሚነት ተግባር የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የትንቢት ያህል፤ ሳግ እየተናነቃቸው ይህንን ነበር የተናገሩት፤
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” እጅግ መሳጭ የሆነውን ሙሉ ንግግራቸውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ በህወሓት/ኢህአዴግ ሲቪል-ወታደር ቅይጥ ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ ከተተካ የፊታችን እሁድ 26 ዓመት ይሆነዋል፡፡ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በመንግስቱ ኃይለማርያም መዳፍ ስር ሲገዛ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ ሰሞን በተስተዋለው ፖለቲካዊ ለውጦች በመታገዝ ወታደራዊው አገዛዝ ላይመለስ ተሸኝቷል፡፡
በዘውጎች መካከል ደማቅ ስታሊናዊ የልዩነት መስመር በማስመር፣ አገራዊ የጋራ ማንነትን በመቅበር አካባቢያዊ ማንነትን ያገነገነው የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞው በኋላ ኢትዮጵያን ለከፋ የርስ በርስ ጦርነትና ለብተና አመቻችቷታል፡፡ “ግንቦት 20” እንደ አገዛዝ ለውጥ ከቅርጽ ባሻገር በይዘት ደረጃ ሥር ነቀል የሥርዓት ሽግግር ማድረግ ተስኖታል፡፡ ለውጡ “ከወታደራዊ ድል” ባሻገር ያመጣው ረብ ያለው ፖለቲካዊ ማሻሻያ አለመኖሩ ከዚህም ባለፈ የዘፈቀደ ግድያና የጅምላ እስር እየጠነከረ መሄዱ “ግንቦት 20” ከደርግ ወደ ጎሣዊ ደርግ የተሻገርንበት የአገዛዝ ምዕራፍ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
በ“መስከረም 2” እና በ“ግንቦት 20” መካከል ያለው ልዩነት፣ የቀደመው ደርግ ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ዘውጎች የተውጣጡ አምባገነኖች የተዋቀረ ወታደራዊ ቡድን ሲሆን፤ የግንቦት ሃያው ተተኪ ደርግ ደግሞ በትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁንጮ አመራር ሰጪነት እና በተለጣፊ ሎሌ ድርጅቶች ጀሌነት የቆመ የሽፍታ ስብስብ መሆኑ ነው፡፡ የመስከረም ሁለቱ ደርግ፣ ለወታደራዊ ሥልጣን የበላይነት ይተጋ ነበር፡፡ በአንፃሩ የግንቦት ሃያው ደርግ ፖለቲካዊ የበላይነቱን በማስጠበቅ ለአንድ ዘር (ለትግራይ) ልዕልና የቆመ ሲቪል-ወታደር ቅይጥ አገዛዝ ነው፡፡
ለትግራይ ተወላጆች የበላይነት በሚተጋው ህወሓት የሚዘወረው የግንባሩ (ኢህአዴግ) ፖለቲካ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለራሷ ለትግራይም እንደማያዋጣ ዛሬ ላይ ያለንበት ፖለቲካ-ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ቀውስ ዋና አስረጅ ምሳሌ ነው፡፡
“ግንቦት 20” ከደርግ ወደ ጎጠኛ ደርግ የተሻገርንበት የአገዛዝ ለውጥ ምዕራፍ ነው የሚለው አገላለፅ የብዙዎችን ኢትዮጵያዊያን ሃሳብ የሚወክል ይመስለናል፡፡ “ግንቦት 20” እንደ አዲስ የአገዛዝ ምዕራፍ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር ዘርቶ ያበቀላቸው መርዛማ ፍሬዎች ሁልቆ መሳፍርት የላቸውም፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ፣ አገዛዙ ካበቀላቸው መርዛማ ፍሬዎች ውስጥ እንደአገር አፍራሽነት (መርዛማነት) ደረጃቸው ዋና ዋና መርዛማ ፍሬዎችን በመምረጥ ከአስረጅ ማሳያዎች ጋር በተከታታይ ዕትም ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
ክፍል አንድ
መርዛማ ፍሬ 1፡ የከሸፈው ፌደራሊዝም
ከህወሓት የፖለቲካ ፕሮግራም ስለተቀዳው ፌዴራሊዝም መክሸፍ ለመተማመን ቀዳሚ የሆነው አስረጅ ማሳያ በተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የተፈጥሮ ሃብት ቅርምትን መነሻ ያደረገ “የክልል ድንበር ይገባኛል” የርስ በርስ ግጭቶች መታየታቸው እና እስከ አሁንም የቀጠሉ መሆናቸው ነው፡፡
ቀድሞ ነገር ቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌዴራሊዝም መተግበር ሲጀመር የክልሎች አከላለል የአገሪቱን የቀደሙ ታሪካዊ ሁነቶች ባላገናዘበ መልኩ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ የአገዛዙን ወንበር በአያሌው የፈተነው የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ለፌዴራሊዝሙ ሃሳዊነት አንደኛዉ አስረጅ ማሳያ ነው፡፡ የወልቃይት ነባር ህዝብ በሚናገረው ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና በሌሎች መሰል ማህበራዊ ስሪቶች ከትግራዮች ይልቅ ለአማራ የሚቀርብ ሆኖ እያለ፣ ትግራይን እንደአገር በመገንባቱ ሂደት መተንፈሻ የአጎራባች አገር (ሱዳን) ድንበር ተዋሳኝነት ያስፈለገው ህወሓት፤ ወልቃይትን በትግራይ ስር ከመጠቅለልና የወልቃይት አማራዎችን ማንነት ከመጨፍለቅ ወደኋላ አላለም፡፡ ይህን ተከትሎ ዛሬ ላይ ብረት አከል ህዝባዊ አመጽ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ መገለጫ ሆኗል፡፡
ሌላኛው የፌደራሊዝሙ መክሸፍ ማሳያ ሆኖ የሚጠቀሰው በየአካባቢው በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ የእርስ በእርስ ግጭቶች ናቸው፡፡ አንዱ ማሳያ በጌድዮ እና በጉጂ ኦሮሞዎች መካከል ዛሬም ድረስ ያልበረደው ግጭት ተጠቃሽ ነው፡፡ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ እንደገና በተዋቀረው የደቡብ ክልል የተነሳ ጉጂ ወደ ኦሮሚያ፣ ጌድዮ ወደ ደቡብ ክልል እንዲሄዱ ሲገደዱ በመካከል የተፈጠረው የግጦሽ መሬትን ማዕከል የሚያደርገው የድንበር አከላለል ይገባኛል ጥያቄ ደም አፋሳሹን ግጭት ቀስቅሶታል፡፡ ይሄው ግጭት ዛሬም ድረስ በአካባቢው ድርቅ እና ረሃብ ባንዣበበ ቁጥር ያለውን ውሱን የተፈጥሮ ሃብት (ውሃ፣ የግጦሽ መሬት ወዘተ) ለመቀራመት በሚደረገው ሽሚያ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እስከተለ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከህዳር – ታህሳስ/2009 ዓ.ም. ድረስ በነበሩ ጊዜያት በሱማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ተመሳሳይ ግጭት ተነስቶ አገዛዙ ባመነው መረጃ መሰረት የ42 ዜጎች ህይወት ሲያልፍ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሊፈናቀሉ ችለዋል፡፡
ግጭቶችን ከመቀስቀስ በዘለለ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መፈናቀልን እያባባሰ የመጣው፣ አገዛዙ ከሚያራግበው የከረረ አፓርታይዳዊ የዘር ፖለቲካና ከተቸከለው ክሹፍ ፌዴራሊዝም የተነሳ ነው፡፡ አንድ ዜጋ በየትም ክልል ለመኖር የክልሉን የሥራ ቋንቋ ማወቅ ብቻውን ከአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎች እኩል ህገመንግስታዊ የሆኑትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ማግኘት እንደሚኖርበት ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይሁንና በደርግ ጊዜ በሰፈራ ፕሮግራም፣ ከደርግ ጊዜ በፊትም በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ትስስሮሽ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሰፈሩ ዜጎች ከሰላሳ አርባ አመታት በኋላ የቋንቋ ተኮሩን ፌደራሊዝም መተግበር ተከትሎ ወደ “ክልላቸው” እንዲሄዱ ግፊት መጠንከሩና ግጭት መከሰቱ አይዘነጋም፡፡
በዚህ ረገድ በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን አማሮችን፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉምዝና በበርታ፣ በበርታና በአማሮች መካከል የነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት “ነባር ነዋሪ ነን” የሚሉት ሌሎችን (በሰፈራና መሰል ወደ አካባቢው የሄዱትን) ከማህበረ-ፖለቲካዊ ተቋማትና ከኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች ለማግለል ብሎም ለማፈናቀል የተጠቀሙት የኃይል አማራጭ፣ ይህን ተከትሎ የፈሰሰው ደምና የደረሰው ማህበራዊ ቀውስ ለፌዴራሊዝሙ መክሸፍ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡
ከዓለምአቀፋዊ ትርጓሜ አኳያ ፊዴራላዊ ሥርዓት የሚገለጽበት አውድ አንዱ ከሌላው ተለይቶ የተሰጠው እውነተኛ የራስ ገዝ መብት የተቀዳጁ ቢያንስ ሁለት የአስተዳደር እርከኖችን እንዲይዝ ተደርጎ በሕገ-መንግስት የተቋቋመ ሥርዓት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙት የክልል መስተዳድሮች ተጠያቂነታቸው ለየመራጮቻቸው ሕዝብ ነው፡፡ የፌደራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ይህን የሚል ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የከሸፈ የፌደራል ሥርዓት ከላይ ከተመለከተው ጽንሰ ሃሳብ በተቃራኒው ሲተገበር ይታያል፡፡
የክልሎች ራስ ገዝ አስተዳደር በወረቀት ላይ የሰፈረ ቢሆንም በተግባር ሲፈተሽ የክልሎች እውነተኛ “ሥልጣን” ኃይል አልባና ታዛዥነት ነው፡፡ ማዕከላዊ መንግስቱን የተቆጣጠሩት የህወሓት የፖለቲካ መሃንዲሶች ለሚያወጧቸው ቀፍዳጅ ህጎች ተገዥ መሆን የክልል ባለሥልጣናቱ በወንበራቸው ላይ ለመቆየት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡ ከዚህ ፖለቲካዊ አሽከርነት የመነጨው ጉዳይ የጎንዮሽና ተዋረዳዊ ኢ-እኩልነትን ፈጥሯል፡፡ በክልልነት በተዋቀሩት ክፍለ-መንግስታት መካከል ያሉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅም ልዩነቶች ፈፅሞ የሚገናኝ አይደለም፡፡ በፖሊሲ ነክ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ከማሳደር አኳያም በክልሎች መካከል ሰፊ የአቅም ልዩነት አለ፡፡ እንደማሳያ ትግራይን ከኦሮሚያ፣ ትግራይን ከአማራ፣ ትግራይን ከደቡብ ክልል፣ ትግራይን ከሶማሌ ክልል፣ . . . ጋር ከህዝብ ብዛት፣ ከተፈጥሮ ሃብት፣ ወዘተ አኳያ ዛሬ ላይ የደረሱበትን አቅም ማነፃፀሩ ለልዩነቱ ጥሩ ሥዕል ይሰጣል፡፡
ማዕከላዊ መንግስቱን በተቆጣጠሩት የህወሓት ፖለቲከኞች ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የክልሎችን አወቃቀርና የሚያካትቷቸውን ዘውጎች እና የወል ማህበረሰቦች ራሱ ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔው አምስት ክልሎች (ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሶማሌ) ብቻ የክልልነት ደረጃ ሲያገኙ ሌሎች አራት ክልሎች (ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ ሐረሬ) ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር ተዳብለው እንደ “ክልል” ታጉረዋል፡፡ በየዘውጎቹ መካከል የሚታየው በድንበር፣ በፖለቲካዊ ውክልና እና በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚንተራሱ ግጭቶች በጊዜ ሂደት ኢትዮጵያን ለአስከፊ የርስ በርስ ጦርነትና ብተና እያመቻቿት ይገኛሉ፡፡ በዚህ መልኩ መክሸፉን ያስረገጠው የፌደራል ሥርዓት በእነ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ “ከአፍሪካ አገራት ተሞክሮዎች ያፈነገጠ አዲስ የማንነት ማበልፀጊያ አቅጣጫ” በሚል ተሞካሽቶ እንደነበር ስናስታውስ የመክሸፉ ምንጭ ከወዴት በኩል እንደሆነ እንረዳለን፡፡
መርዛማ ፍሬ 2፡ ትውልድ አምካኝ የትምህርት ፖሊሲ
በዘመነ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ትምህርት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሰረት ነው፡፡ ይህ እውነታ በዋነኝነት ዘመናችን ከተመሰረተበት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ሥርዓት ባህሪ የሚመነጭ ነው፡፡ የአለም የኃይል አሰላለፍ የሚጠይቀውን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ አስተሳሰብና ባህል በመፍጠር፤ ትምህርት መንግስታት ለሚመኙት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግና ዓብይ ሚና ይጫወታል፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት የፖለቲካ መሳሪያ ከመሆን የተሻገረ ብሔራዊ ርዕይ ሊኖረው አልቻለም፡፡ የትምህርት ፖሊሲው የአገዛዙ የፖለቲካ መጠቀሚያ፣ መምህራንም የካድሬ ያህል ፖሊሲ ፈፃሚ ሲሆኑ ይታያል፡፡ የፖሊሲ ጥያቄ ማንሳት በሁለት መስመር ደብዳቤ ከሥራ ገበታ እንደሚያሰናብት በብዙ የኢትዮጵያ መምህራን ላይ ደርሶ የታየ እውነታ ነው፡፡
ከፍተኛ የትምህርት ምሁራን እንደሚሉት የትምህርት ፖሊሲው መሰረታዊ ስህተት የትምህርት እርከን አቀማመጥ (አከፋፈል) ነው፡፡ በአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ መሰረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት (1-8) በሁለት እርከን ይከፈላል (1-4፣ 5-8)፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት (9-12) በተመሳሳይ በሁለት እርከን (9-10፣ 11-12) ተከፍሏል፡፡ በፖሊሲው መሰረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የመጀመሪያ ሳይክል (1-4) ተማሪዎች ሳይወድቁ (Free Promotion) ወደ ሚቀጥለው የክፍል ደረጃ እንዲዛወሩ ይደረጋል፡፡ በእነዚህ የክፍል ደረጃዎች ተማሪ እንዲደግም ማድረግ በፖሊሲው የተከለከለ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ (1-8) መልቀቂያ ፈተና ሚኒስትሪ በክልል ደረጃ የሚሰጠው 8ኛ ክፍል ላይ ብቻ እንዲሆን ተገድዷል፡፡ የሥርዓተ ትምህርቱን ውጤታማነት ለመፈተሽ እንኳ በመጀመሪያ ደረጃ 1ኛ ሳይክል (1-4) ማጠናቀቂያ ላይ የሚሰጥ የተማሪዎች የብቃት መመዘኛ ፈተና አለመኖሩ የአገዛዙን የትምህርት ፖሊሲ የጨበጣ ጉዞ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡
በመንግስት ደረጃ የቅድመ መደበኛ ትምህርት (Pre-School) የተዘነጋ የትምህርት እርከን ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ የተሻለ ገቢ ያላቸው ከተሜ ወላጆች ልጆቻቸውን በግል ት/ቤት የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ከሚያደርጉት በስተቀር፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ወላጆች፣ የአርሶ አደር እና አርብቶ አደር ልጆች የመደበኛ ትምህርትን 1ኛ ክፍል ላይ “ሀ” ብለው የሚጀምሩት ህፃናት ሥርዓተ ትምህርቱን የመቀበል አቅም ያንሳቸዋል፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት (9-12) በሁለት እርከን (9-10 እና11-12) የተከፈለ በመሆኑ የመጀመሪያው እርከን ማጠናቀቂያ ላይ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ በዚህ የመልቀቂያ ፈተና ላይ ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች ስደት አልያም ቦዘኔነት የህይወት ምዕራፍ አካላቸው ይሆናል፡፡ የ10ኛ ክፍል ውጤታቸው ለቅድመ ዩኒቨርሲቲ (መሰናዶ) የሚያበቃ ከሆነ ከሁለት ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ (11-12) የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ይሰጣል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በራሱ በአገዛዙም ሆነ የትምህርት ተቋማቱን በማስፋፋት ከፍተኛ እርዳታ እያደረጉ ባሉ ድርጅቶች ጭምር እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች የትምህርት ፖሊሲውን ክሽፈት የሚያስረዱ ሆነዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር የሰራዉ ዘገባ እንደሚያስረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ማጠናቀቂያ (8ኛ ክፍል)፣ የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ ሳይክል (10ኛ ክፍል) እና የሁለተኛ ደረጀ ሁለተኛ ሳይክል (12ኛ ክፍል) ፈተናዎችን የሚያልፉ ተማሪዎች 40% በላይ መሻገር አልቻለም፡፡ በዩኤስኤይድ እና በትምህርት ሚኒስቴር የጋራ ትብብር “Ethiopia Early Grade Reading Assessment” በሚል ርዕስ የወጣው ሪፖርት ደግሞ የፖሊሲውን ሥርዓተ ቀብር የሚያረዳ ነው፡፡ በስምንት ክልሎች ላይ በተዘጋጀው በዚህ ጥናት መሰረት 80% የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (1-4) ተማሪዎች በሚጠበቅባቸው ልክ ማንበብ አይችሉም፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የክፍል ደረጃ ብቻ እየቆጠሩ እና እየተገፉ አልፈው (Promote) በአማካይ ከስምንት ዓመታት በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ መሆናቸው ሲታሰብ የፖሊሲውን መርዛማነት (ትዉልድ አምካኝነት) ለመረዳት ዕድል ይሰጣል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በአለም ባንክ ከፍተኛ የትምህርት ባለሙያዎች “Secondary Education in Ethiopia; Supporting Growth and transformation” በሚል ርዕስ የተሰራው ጥናት ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገቡት መካከል 61% የሚሆኑት ከ80% በታች የሆነ ውጤት የሚያመጡ ናቸው፡፡ በቀደመው ዓመት የኤስኤይድ (USAID) የአፍሪካ ተማሪዎችን የማንበብ አቅም በተመለከተ ባወጣው የጥናት ዘገባ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የ2ኛ ክፍል ተማሪ ከሆኑት አንድ መቶ ተማሪዎች ውስጥ በአማካይ 33ቱ አንድ ቃል እንኳ ማንበብ አይችሉም፡፡ አረፍተ ነገር እና አጭር ምንባብ ማንበብ የማይችሉት ደግሞ 80% ይሆናሉ፡፡
የዚህ ሁሉ ውድቀት ሥረ-ምክንያት የሆነው በትምህርት ፖሊሲው መሰረት የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት የተማሪዎችን የመማር አቅም ያላገናዘበ መሆኑ፣ መምህራን በሥራቸው ደስተኛ አለመሆናቸው፣ የትምህርት ግብዓት አቅርቦት አለመኖር፣ የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ማጣት (ማርፈድ፣ መቅረት፣ ማቋረጥ) ወዘተ ተጠቃሽ የውድቀት ምክንያቶች ናቸው፡፡
“የትምህርት ተደራሽነት ላይ አተኩራለሁ” የሚለው አገዛዝ ተደራሽነትን አሻግሮ እያየ የትምህርት ጥራትን ሲደፈጥጥ ይታያል፡፡ ከሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ በኋላ የአገሪቱን የትምህርት ሽፋን 100% ማድረስ አልሆንልህ ብሎታል፡፡ ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ተሳትፎ ከ35 በመቶ ከፍ ማለት አልቻለም፡፡ የትምህርት ዕድልን በስፋት የሚያገኙት የከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የመጀመሪያ እርከን (9-10) የከተማ ድርሻ 86% ሲሆን፤ የገጠሩ ክፍል 14% ላይ እንደቆመ ቀርቷል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ሁለተኛ እርከን (11-12) የከተማ ድርሻ 92% ሲደርስ፤ የገጠሩ ድርሻ በሚያሳዝን መልኩ 8% ሆኗል፡፡ በዚህ መጠነ ሰፊ የሽፋን ክፍተት የተነሳ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ከ9ኛ -12ኛ ክፍል የሚማሩ የገጠር ተማሪዎች ትምህርት ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ በመምጣት በቤት ኪራይ ትምህርት ለመማር ይገደዳሉ፡፡ በዚህ እንግልት የበዛበት ማህበራዊ ውጣ ውረድ ከኢኮኖሚ አቅም ማነስ አኳያ በየአመቱ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ወጣቶቹ ህገወጥ ስደት የሞት ሸለቆ ጉዞ መሆኑን እያወቁ እንኳ ከመሰደድ ወደ ኋላ የማይሉት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ተስፋ በመቁረጣቸው የተነሳ መሆኑን ገለልተኛ ምሁራን በየጊዜው የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለዉን “የተማሩ መሃይማን” ማፍራት ዘመቻ ተቋማቱን ትዉልድ ገዳይ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚስተዋሉ የዘር ልክፍት አሰራሮች የተማሪ ዉጤት እስከ መጨመር መቀነስ የደረሰ የዉርደት ተግባር ላይ ደርሷል፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ፖለቲካ ታዛዦች የተሰገሰጉበት የትምህርት ስርዓት ዉድቀት ቅርቡ ስኬት ሩቁ ሆኗል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኝ ኮሌጅ የሚያስተምሩ መምህር ለጎልጉል እንደተናገሩት “ተማሪዎቼን በምን ቋንቋ እንደማስተምራቸው ግራ ይገባኛል፤ የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው ብዬ በእንግሊዝኛ ሳስተምራቸው በፍጹም አንግባባም፤ እንግሊዝኛው ይቅር ብዬ በአማርኛ ላስተምር ስል ሁሉም ከተለያየ ክልል የመጡ በመሆናቸውና ከክልላቸው ቋንቋ በስተቀር ሌላ ስለማይችሉ በጭራሽ የምናገረውን መስማት አይችሉም” ብለዋል፡፡
ህወሓት ይህንን መሰል ትውልድ አምካኝ የትምህርት ፖሊሲ በመላው አገር ላይ ሲተገብር የትግራይ “ምርጥ ዘሮች”ን ለማውጣት በክልሉ ለየት ያለ የትምህርት ፖሊሲ ይከተላል፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ለትግራይ ተወላጆች የተለየ የትምህርት ዕድሎች እንዲገኙ፣ በልዩ የሙያ መስኮች እንዲሠለጥኑና ያለተፎካካሪ በየሥራ መደቡ እንዲቀጠሩ፣ በውጭ አገር የተለያዩ የትምህርት ዕድሎች እንዲያገኙ፣ ወዘተ መንገዱ ሁሉ ይመቻችላቸዋል፡፡
አንድ ምሳሌ እናቅርብ፤ በበረሃ ትግሉ ዘመን ከስድስተኛ ክፍል ትምህርት ያላለፈ አንድ የህወሓት “ተጋዳላይ” ከ“ድል” በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በማስተርስ ዲግሪ ተመርቆ በሁለት የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርቶ እንደነበር በራሱ አንደበት መናገሩ ጎልጉል መረጃው አለው፡፡ ይህንን ሁሉ ለማከናወን የፈጀበት ዓመት በረሃ ከቆዩበት ጊዜ በእጅጉ ያነሰ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርነትና በመከላከያ ሚኒስቴር በኮሎኔልነት ማዕረግ የመምሪያ ኃላፊነት ላይ ተመድቦ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ለከፍተኛ የወታደር አስተዳደራዊ ትምህርት (በማስተርስ ደረጃ ለመማር) ወደ አንዱ ምዕራባዊ አገር መጥቶ “እንግሊዝኛ እንደመግባቢያ ቋንቋ” የሚል አንድ መጽሐፍ ይዞ ለፈተና ሲዘጋጅ ነበር፡፡
በኮ/ሎ ጎሹ ንግግር እናብቃ፤ “… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮትዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” እጅግ መሳጭ የሆነውን ሙሉ ንግግራቸውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
የግንቦት 20 መርዛማ ፍሬዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ በቀጣይ ዕትም ሌሎቹን እናቀርባለን፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Alula says
Non TPLF Ethiopians should be very clear. It is TPLF which is destroying Ethiopia and killing Ethiopians.
TPLF is also intensifying its tactics to mobilize Tigrian Ethiopians. TPLF is making them part of it. It simply says ‘TPLF is Tigray and Tigray is TPLF’. Well, no one else can verify that but the referred people.
Thus, three questions to Tigrians:
1. are you part of the killing machine, the looter, the lair and the traitor (banda) TPLF?
2. do you back killing and arbitrary imprisonment of innocent Ethiopians?
3. are you at the back of removing Ethiopian identity and Ethiopia?