ሁሉም ባይባልም አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋና የፖለቲካ ፕሮግራም ሶሻል ዴሞክራሲ ወይም ሊበራል ዴሞክራሲ ወይም ምርጫን ማዕከሉ ያደረገ ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲ ነው። የኢኮኖሚ ፕሮግራማቸው ደግሞ ገበያ መር ኢኮኖሚ ነው።
እነዚሁ ፓርቲዎች በምርጫ ክርክር ሲደረግ በዋናነት እያነሱ የሚከራከሩት መንግሥት ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮታል፤ የዕዝ ኢኮኖሚ ነው አገሪቱን ለችግር የዳረጋት፣ የኢኮኖሚው አካሄድ በገበያ እንጂ በመንግሥት መመራት የለበትም በሚል የከረረ ተቃውሞ በማቅረብ ሲቃወሙ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሰምተናል።
ባለፈው ሰኞ መንግሥት የአገሪቱን ዐቢይ (ማክሮ) ኢኮኖሚ ወደ ገበያ መር የሚወስድ ውሳኔ ይፋ ሲያደርግ እነዚሁ ተቃዋሚዎች “እሰይ ስለቴ ሰመረ” ባይሉም ቢያንስ ለዓመታት ሲሟገቱለት የነበረው ሃሳብ ድል አድርጎ በማየታቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ድጋፍ ሊያሰሙ የሚጠበቅ ነበር።
የሆነው ግን ይህ አይደለም። ኢትዮጵያ የሲሪላንካ ዕድል ይገጥማታል፣ የኬኒያን አቢዮት ወደ አገር ውስጥ ማስገባታችን (ኢምፖርት ማድረጋችን) ነው፤ ድሃው መኖር ሊያቆም ነው፤ የኢኮኖሚው ቀውስ አገሪቷን ሊያፈርስ ነው፤ “አብዮት ሊቀጣጠል ይችላል”፣ “መኖር የተከለከለ ሕዝብ” በመሪዎቹ ላይ ይነሳል፤ መንግሥት ሕዝቡን ሳያማክር ያወጣው ፖሊሲ ነው፤ ድንች ፍለጋ ልንወጣ እንችላለን፣ በኮሪደሩ ልማት ላይ ጋሪ ወደ መንዳት እንሄዳለን፣ ወዘተ የሚሉ ከአመክንዮ ውጪ የሆኑ አስተያየቶች በፖለቲከኞችም ፖለቲካው ባሰከራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ሲሰጥ ተሰምቷል።
ሠለጠነ በሚባለውና የመናገር ነጻነት ያለገደብ ተፈቅዷል በሚባልባቸው የምዕራቡ ዓለም አገራት ሥልጣን የሚቆጣጠረው ፓርቲ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይቀርጻል፤ እንዲያውም ብዙዎቹ በምርጫ ወቅት ነው ይህንን ፖሊሲ ይፋ የሚያደርጉት። ሥልጣን ሲይዙ ይህንኑ አሻሽለው የመንግሥታቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አድርገው ይተገብሩታል።
አሜሪካንን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የሪፓብሊካን ፓርቲ ፕሬዚዳንት የሚያወጣውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሹመኞች ያብጠለጥሉታል፤ የዴሞክራቲክ ፓርቲ የሚያወጣውንም ሪፓብሊካኖቹ እንዲሁ ያራክሱታል። አንድም ጠቃሚ ነገር እንደሌለው አድርገው ነው የሚተቹት። ከኢኮኖሚው ፖሊሲ ጠቀሜታው ይልቅ የፖለቲካ ቅኝታቸው ትንታኔያቸውን እና ምልከታቸውን ያንሻፍፈዋል።
የእኛ አገር የኢኮኖሚ ተንታኞችም የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ሰለባዎች ናቸው። ሰሞኑን የተሰሙትና ኢኮኖሚውን ማስረዳት ይችላሉ የሚባሉት ትንታኔያቸውን የሰጡት በመንግሥት ላይ ካላቸው የፖለቲካ አመለካከት አኳያ ነው። በሽግግር መንግሥት ምሥረታ የሚያምኑ፣ መንግሥትን በሕዝባዊ ዓመጽ ለመጣል የሚመኙ፣ በግላጭ ባይሆንም የትጥቅ ትግልን የሚደግፉ፣ ወዘተ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን የመንግሥትን ፖለቲካ በሚያብጠለጥሉበት የፖለቲካ አካሄድ ነው “የተቹት”። ተገማች ቢሆንም የአንዳንዶቹ ግን ከመስመር የወጣ ሆኖ ታይቷል።
ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድር ለማግኘት ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥረት ስታደርግ “የዓለም ባንክ ብድር አልሰጥም ያለው መንግሥት ተዓማኒ ስላልሆነ ነው፤ ዓለምአቀፍ አበዳሪዎች ካዝናቸውን በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቆልፈዋል፤ የኑሮው ውድነት እያሻቀበ ነው፤ ኢኮኖሚው ባፍጢሙ ሊደፋ ነው፤ አገሪቱ በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ነች፤ ወዘተ” የሚለው ወሬ አየሩን የሞላ ነበር።
የሁለቱ ዓመት ድርድር በአንድ ቢሊዮን ዶላር ስጦታ፣ 500 ሚሊዮን ዶላር የስምምነት ዱቤ እና በድምሩ በ16.6 ቢሊዮን ዶላር የዓለም ባንክ ድጋፍ ሲጠናቀቅ ወሬው ተቀየረና “አገሪቷን ሸጠው ዶላር ተቀበሉ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ባሪያ ሆነች፤ ኬኒያን ያፈረሰ የኢኮኖሚ አብዮት ድንበር ተሻግሮ ሊገባ ነው፤ ወዘተ” በሚሉ ሟርቶች ተለውጠዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ያለ ምንም ጥርጥር መንገጫገጮችን ይፈጥራል፤ የድሃው ኑሮ ይቃወሳል፤ የኑሮ ውድነት እንደሚጨመር ይጠበቃል፤ ነጋዴውም የረቀቀ የዝርፊያና የውንብድና ሥራ ውስጥ ይገባል። እነዚህ ሁሉ ተገማች ናቸው። ዋናው ጥያቄ ያለው ምን ያህል ይቆያል? በምን ያህል ጊዜ ወደ መሻሻል ይመጣል? የሚለው ነው።
ፖሊሲው ሊያመጣ የሚችላቸውን ለውጦችና ኢኮኖሚውን እንዴት እንደሚያሻሽው አንዳንድ ነጥቦችን በምሳሌ በማንሳት እንጥቀስ።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሳይንሳዊ ትንታኔ ሊጥበት የሚያዳግት አርተፊሻል፣ በመርካቶ ነጋዴና ደላላ እንደተፈለገ የሚዘወር ነው። በኢኮኖሚ መርኽ መሠረት የአቅርቦት ማነስ ዋጋ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ የሚጨምርበትን ምክንያት በብቃት ለማስረዳት ይከብዳል።
ለምሳሌ ከኒው ዮርክ ከተማና ከሌሎች የአውሮጳ ከተሞች እኩል ሊባል በሚችል ደረጃ የቤት ዋጋ አዲስ አበባ ውስጥ የናረው ለምንድነው? በተለይ ደግሞ ከአቅርቦት አኳያ በከተማዋ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ኑሮን የሚለውጥ መሠረተ ልማት (ኢንተርኔት፣ ውሃ፣ መብራት፣ …) ሳይኖር ያለማቋረጥ የቤት ዋጋ ለምን ሲጨምር ኖረ? ሠለጠኑ በሚባሉት አገራት ባሉ ከተሞች አንድ ቤት ለሕዝብ ማመላለሻ እንደ አውቶቡስና ባቡር ቅርብ ከሆነ ዋጋው ይጨምራል፤ አካባቢው የወንጀል መጠኑ ዝቅተኛ ከሆነ የቤቱ ዋጋ ይጨምራል፤ ወዘተ። የአገራችንን ግን የሚወስነው በገበያው ሳይሆን በዋነኛነት በደላላ እንደሆነ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ሁሉም ዋጋ የሚሰላው በጥቁር ገበያው የዶላር ምንዛሪ ስለሆነ ነው።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ከሁሉ በላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ቆላልፎና አስሮ ከተበተበው ትብታብ ፈትቶ ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ ይወስደዋል። ይህ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈራው የዶላር ምንዛሪ መጨመርና ያንን ተከትሎ የኑሮ ውድነት መናር ነው። የዶላር እጥረት እንዲኖርና ኢኮኖሚው በጥቁር ገበያ እንዲመራ ካደረጉት ምክንያቶች በዋንኛነት በገበያ ላይ የተመሠረተ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አለመኖር ነው። ይህም ያለፈው ሰኞ ዕለት ይፋ በሆነው የመንግሥት ፖሊሲ መፍትሔ ያገኘ ሲሆን አፈጻጸሙ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል።
ባለፉት ጊዜያት አንድ ዶላር በ58 ብር አካባቢ ይመነዘራል ሲባል የኖረ ቢሆንም ኢኮኖሚው ግን በጥቁር ገበያው ምንዛሪ ሲመራ የቆየ ለመሆኑ በዕቃዎች ላይ የሚተመነውን ዋጋ መመልከቱ በቂ ይሆናል። መንግሥት ከሚያስገባቸው በጣም የተወሰኑ ነገሮች በስተቀር ከውጪ የሚመጣ ማንኛውም ዕቃ፣ የጨረታ ውድድሮች፣ ወዘተ ታሳቢ እየተደረጉ የሚተመኑት በ58 ብር ሒሳብ ሳይሆን ከመቶ ብር በላይ በሆነው የጥቁር ገበያ ተመን ነው። ምክንያቱም የውጭ ምንዛሪ ዕጥረቱን ሲሞላ የነበረው የጥቁር ገበያው ስለሆነ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዶላር እጥረት ሊያቃልሉና ከውጪ የሚገባውን የገቢ ንግድ መስመር በማስያዝ ከወጪ ንግድ ጋር ያለውን ከፍተኛ ክፍተት ሊያጠብ የሚችል አካሄድ በፖሊሲው ላይ ተቀምጧል። የዶላር አቅርቦት መጨመርና በየቦታው ተደርገው የነበሩ ማነቆዎች መፈታት ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች የሚያመጡ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ለዘመናት ቁጥጥር ሲደረግበት የነበረው የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት በገበያው ውስጥ እንዲገኝ ካልተደረገና እጥረቱ እንደበፊቱ ከቀጠለ የኑሮ ውድነቱ ትኩሳት በእጥፍ እንደሚጨምር የሚታመን ነው። ፖሊሲው ላይ እንደተቀመጠው የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲጨምር ሊያደርጉ የሚችሉና የጥቁር ገበያውን የምንዛሪ መጠን ከገበያው ጋር የሚያቀራርቡና ብሎም የጥቁር ገበያው እንዲያሽቆለቁል የሚያደርጉ አሠራሮች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፤
- የውጭ ምንዛሪ የሚገዛባቸውና የሚሸጥባቸው በገበያው ዋጋ የሚመሩ ባንክ ያልሆኑ የውጪ ምንዛሪ ሱቆዎች መከፈት
- ሰኞ ዕለት ከዓለም ባንክ የተገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላር ስጦታና 500 ሚሊዮን ዶላር የስምምነት ዱቤ
- በኤክስፖርት ንግድ ላይ የተሰማሩ ከሚያስገቡት የውጭ ምንዛሪ በፊት ለራሳቸው የሚያስቀሩት 40% የውጭ ምንዛሪ ወደ 50% ማደጉ
- በፊት በነበረ አሠራር የግል ባንኮች ከሚያስገቡት የውጭ ምንዛሪ ግማሹን ለብሔራዊ ባንክ ያስረክቡ የነበረው አሠራር ቀርቶ ከሰኞ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የራሳቸው እንዲሆን መደረጉ፤
- ይህም በየዓመቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ ይገባ የነበረውን ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወደ ገበያው እንዲገባ የሚያደርግ በመሆኑ
- የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱና እነርሱም መጠነ ሰፊ የውጭ ምንዛሪ ይዘው የሚመጡ በመሆኑ
- ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ አካውንት በአገር ውስጥ ባንክ እንዲከፍቱ መደረጉና በሚፈልጉበት ጊዜ እንዲጠቀሙ መፈቀዱ
- ከዚህ በፊት የአገር ውስጥ ባንኮችም ይሁኑ የንግድ ተቋማት የሒሳብ (የፋይናንስ) መረጃዎቻቸውን (Balance Sheet, ወዘተ) አሳይተው ዶላር መበደር ይከለክል የነበረው አሠራር መነሳቱና ከሰኞ ጀምሮ ከውጪ አበዳሪዎች መበደር መፈቀዱ
- መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደው ብድር መከልከሉ፤ መንግሥትም በገበያው አሠራር እንዲሠራ መደረጉ
- የካፒታል ገበያ የሚከፈት መሆኑ፤ በዓለም ላይ የሚደረገው ንግድ ከቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) የሚገኝ ሳይሆን ወደ 80 በመቶ የሚሆነው ንግድ የሚደረገው አክሲዮን በካፒታል ገበያ በመግዛትና በመሸጥ በመሆኑ ጥሩ የዶላር ፍሰት የሚመጣ በመሆኑ
- በጣም ጥቂት ዕቃዎች በስተቀር በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃዎች እንዲገቡ መፈቀዱ
- ከውጪ ለሚገባ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ማነቆ የነበረው የገንዘብ ልውውጥ (currency convertibility) መፈቀዱ
- ይህ በተለይ ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልጉ የውጪ ባለሃብቶችን ተስፋ ሲያስቆርጥ የነበረ አሠራር ሲሆን ኩባንያዎች ትርፋቸውን በዲቪደንድም ሆነ በሌላ መልኩ በውጭ ምንዛሪ ወደ አገራቸው መውሰድ የሚፈልጉትን ገንዘብ እንዳያወጡ የሚከለክል ማነቆ ሆኖ በመቆየቱ
- ይህ የገንዘብ ልውውጥ (currency convertibility) መፈቀዱ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) የሚያደፋፍር፣ የዶላር አቅርቦትን የሚጨምርና ኤክስፖርትን የሚያሳድግ በመሆኑ
- በአቅርቦት ዕጥረት 50% ብቃት ብቻ ሲያመርቱ የነበሩት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገበያው በሚፈቅድላቸው ውጭ ምንዛሪ ግብዓት እያስመጡ ምርታማነታቸውን በመጨመር የወጪ ንግድን የሚስፋፉ በነሆኑ
- ይህም ወደ አገሪቱ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር የሚደርገው በመሆኑ
- ወዘተ
በተቃዋሚ ጎራ ተሰልፈው ኢኮኖሚውን ከፖለቲካ ዕሳቤ ብቻ የሚነቅፉ የሚያነሱት ዋናው ነጥብ በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው። እንደ ማስረጃም አለመረጋጋቱ የውጪ ኢንቨስትመንትን አያደፋፍርም፤ ኩባንያዎች ሊዘጉና አገር ለቅቀው ሊወጡ ይችላሉ። ኢኮኖሚው በሁለቱም በኩል ጉዳት ይደርስበታል፤ የሰላም ጉዳይ በሽግግር መንግሥት ምሥረታ ይስተካከል የሚል ክርክር የሚያቀርቡት ጥቂቶች አይደሉም።
እነዚህ ሰዎች የሚዘነጉት ወይም አውቀው የማይናገሩት ነገር ቢኖር ሰኞ ዕለት የዓለም ባንክ ከሰጠው ገንዘብ ውስጥ የባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ (Multilateral Investment Guarantee Agency (MIGA)) የሚባለውን 1.15 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ኤጀንሲ (MIGA) ከዓለም ባንክ ቡድኖች አንዱ ሲሆን በታዳጊ አገራት ውስጥ በሚደረግ ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ አበዳሪዎች ወይም ኢንቨስተሮች ሊገጥማቸው ለሚችል የፖለቲካ ኪሣራ የመድኅን ዋስትና የሚሰጥ ነው። ይህ ዓይነቱ ዋስትና የተሰጠው የውጪ ባለሃብት ወደ ኢትዮጵያ የማይመጣበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።
ከዚህ ሌላ ከዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ትብብር (The International Finance Corporation (IFC)) የተገኘው 320 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ ሌላው የዓለም ባንክ ቡድን አባል ሲሆን ዋናው ትኩረቱ በታዳጊ አገራት ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነው። የዚህ ብድር ዋናው ጥቅም በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በኢኮኖሚው መንገራገጭ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መደጎም ነው።
ከዚህ ሌላ በማዳበሪያ፣ በነዳጅ፣ በመድኃኒት እና በምግብ ዘይት ላይ ድጎማ እንደሚደረግ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን በኢኮኖሚ ማሻሻያው በቅድሚያ እንደሚጎዱ የተገመተው ዝቅተኛ ደመወዝ የሚያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ሦስት እጥፍ ወይም 300% የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። እንዲህ ዓይነቱ ለዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያስብ አካሄድ በሌሎች ሪፎርም ባደረጉ አገራት የተፈጸመ አይደለም።
የዛሬ 30 ዓመት አካባቢ ከበረኻ የመጡ ወንበዴዎች አገሪቷ በተቆጣጠሩበት ጊዜ የዓለም ባንክ የመዋቅር ማሻሻያ ፖሊሲ (Structural Adjustment Policy – SAP) በሚል በሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት የብሩን ዋጋ ከ50% በላይ እንዲወርድ (ዲቫሊዩ) ከማድረግ ባለፈ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር የመንግሥት ሠራተኛ ያባረረ እና ሌሎችንም ባልና ሚስትን ባሌና መቀሌ በመመደብ ቤተሰብን ጭምር ያፈረሰ ፖሊሲ መተግበሩ የሚዘነጋ አይደለም።
አሁን ይፋ የሆነው ፖሊሲ የሚቃወሙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚሰጡት ሃሳብ የከዚህ በፊቱን አፍራሽ ፖሊሲ ያገናዘበ ከመሆንና ፖሊሲውን ከሳይንሳዊና አመክንዮአዊ አካሄድ ከመተቸት ይልቅ አስቀየመን ከሚሉት የፖለቲካ ጽንፍ ነው። ዶ/ር ዓለማየሁ ገዳ በማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲው ብዙ እምነት እንደሌለው ከመናገር ባለፈ “እኔ ተሳስቼ ፖሊሲው ቢሠራ እመርጣለሁ” ማለቱ ሰሞኑን ተሰምቷል።
ዶ/ር ዮናስ ብሩ ደግሞ በዚሁ በማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ላይ በቅርቡ በተደረገ ቃልምልልስ የተሻሉ የማክሮ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች እንደነ ዶ/ር ዓለማየሁ ገዳ ዓይነት የኬኒያን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የቀረጹና በየጊዜው ኬኒያኖቹ የሚያማክሩት ሰው ፖሊሲውን የተቃወመ መሆኑን ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊ በነበሩበት የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ዶ/ር ዮናስ ብሩ ኢትዮጵያ የ50 ቢሊዮን ዶላር የማርሻል ፕላን ያስፈልጋታል በማለት የተናገሩ ሲሆን የወቅቱን የኬኒያን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተል ዶ/ር ዮናስ ብሩም ሆኑ እርሳቸው አድንቀው የተናገሩላቸው ዶ/ር ዓለማየሁ ገዳ በኢትዮጵያው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አለመማከራቸው ተገቢ ውሳኔ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምኅረቱ፣ በአዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመራው ገበያ ችግር ካጋጠው ባንኩ ጣልቃ እንደሚገባ አስታውቀዋል። ማሞ፣ ኢትዮጵያ ከዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ጋር የብድር ስምምነቶችን መፈራረሟን ተከትሎ፣ ከሁለቱ ተቋማት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወደ ብሔራዊ ባንክ እንደገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታስገባቸው የፍጆታ ዕቃዎች መካከል 18 በመቶዎቹ ብቻ በውጭ ምንዛሬ እንደሚመጡ የገለጡት ማሞ፣ ቀሪዎቹ ግን በትይዩ ገበያ ሲገቡ እንደቆዩ ገልጸዋል። ስለዚህ ባንኩ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ለመተግበር መዘጋጀቱንም ማሞ ተናግረዋል።
ታዋቂው የቢዝነስ ባለሙያው ኤርሚያስ አመልጋ እንዳለው ኢኮኖሚው በገበያ ሥርዓት መመራቱ በጣም የዘገየ ያውም ቢያንስ በ25 ዓመት ወደኋላ የቀረ ነው። በአገር ውስጥ ያለውን የውጪ ምንዛሪ ዕጥረት ሊያስተካክልና በበቂ ሁኔታ ክፍተቱን ሊሞሉ የሚችሉ ነጥቦችንም ያነሳል። ኤርሚያስ እንደሚለው በአገሪቱ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከሚከተሉት ሊገኝ ይችላል፤
- ከዳያስፖራ የሚገባ ክፍያ ወይም ሬሚታንስ፤
- ይህ በዓመት በትንሹ 3 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል
- የግል ባንኮች ከሚያስገቡት የውጪ ምንዛሪ ብሔራዊ ባንክ ይወስደው የነበረው 50 በመቶ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሪ መቅረት፤
- ይህም በግምት በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል
- በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃ እንዲገባ በመፈቀዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የውጪ ምንዛሪ መጠን
- በትንሹ ይገመት ከተባለ በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል
- አገር ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊም ሆነ ሌላው የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍት መፈቀዱ፤
- በዓመት 1 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ቢገመት
- የግል ባንኮችና የንግድ ተቋማት ከውጪ አበዳሪዎች ገንዘብ እንዲበደሩ መፈቀዱ፤
- ይህ በርካታ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኝ በመሆኑ፤
- በትንሹ 1 ቢሊዮን ቢባል
- ከሁሉ በላይ የካፒታል ገበያ መጀመሩ የሚስበው የውጪ ምንዛሪ መጠን በመኖሩ፤
በድምሩ በትንሹ በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ አቅርቦት ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ የሚያስችል ሲሆን ይህም ውሎ አድሮ በትኩሳት ውስጥ የኖረውን ኢኮኖሚ የሚፈውስ ጥሩ መድኃኒት ነው ሲል ኤርሚያስ በአመክንዮ ይሞግታል።
ስለዚህ “ገበያው ጠላቱ አይደለም፤ መድኃኒቱ ነው፤ ኢኮኖሚው በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ለመሞት እያቃሰተ ነበር፤ አሁን የተሰጠው የማንቂያ ኤሌክትሪክ ንዝረት (ሾክ) ነው፤ የዋጋ ንረት የሚባል ከፍተኛ ትኩሳት ይዞት ነበር፤ በሌላ አነጋገር በሽታው አራተኛ ደረጃ የደረሰ ካንሰር ነው፤ ፈጣን ቀዶ ጥገና እና የካንሰር ኬሚካል ሕክምና (ኪሞቴራፒ) እና የጨረር ሕክምና ያስፈልገዋል” ብሏል።
ብዙ ጊዜ እንደሚባለው እስካሁን ኢኮኖሚያችን በምትሃትና በደላላ ወይም በድንቁርና፣ በፍርሃትና በኋላቀርነት ሲመራ የቆየ ነበር። እንደ ኤርሚያስ አነጋገር የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲው “በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሳይሆን አዲስ መጽሐፍ ነው፤ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አእምሮና የደም ዝውውር ሊኖረው ነው፤ ከዚህ አኳያ ፖሊሲው እንከን የማይወጣለት ነው” ብሏል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply