ለሁለት ዓመታት የተደረገው ድርድር ያስገኘው ውጤት ነው
የዓለም ባንክ በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ) “የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘላቂና ሁሉን ዓቀፍ የልማት ፖሊሲ ዘመቻ” (Ethiopia First Sustainable and Inclusive Growth Development Policy Operation) በሚል ለሚጠራው የልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚሆን ድጋፍና ብድር መፍቀዱን ይፋ አድርጓል።በወጣው መግለጫ መሠረት ባንኩ የሚያደርገው ድጋፍ ሦስት ዓላማዎችን ያካተተ ነው፤
(ሀ) ለመዋቅር መልሶ ማዋቀርና ንግድን ለማሳለጥ
(ለ) በጀትን በተመለከተ ዘላቂነትንና ግልጽነትን ለማስፋፋት እና
(ሐ) የአካባቢ ጥበቃን እና ማኅበራዊ አይበገሬነትን ለማበረታታት እንደሆነ ተገልጾዋል።
በተለምዶ የዓለም ባንክ የሚባለው ቡድን ሲሆን በሥሩም የተለያዩ ድርጅቶች አሉት፤ ብድርም ሆነ ሥጦታ ሲፈቀድ የዓለም ባንክ ፈቀደ ተብሎ ቢጠቀስም ዋናውን ሚና የሚጫወቱት ገንዘቡን የሚፈቅዱት ድርጅቶች ናቸው።
ለኢትዮጵያ ከተፈቀደው ገንዘብ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር (International Development Association (IDA))፤ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ትብብር (The International Finance Corporation (IFC)) እና የባለብዙ ወገን የኢንቨስትመንት ዋስትና ኤጀንሲ (Multilateral Investment Guarantee Agency (MIGA)) የሚባሉት ሦስት ድርጅቶች ተሳትፈዋል። ለኢትዮጵያ ከተፈቀደው ገንዘብ በጣም አብላጫውን የሰጠው IDA ነው።
ዛሬ ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (IDA) የተፈቀደው ገንዘብ፤
- ቀጥተኛ ስጦታ (grant) 1 ቢሊዮን ዶላር፤
- የስምምነት ዱቤ (concessional credit) 500 ሚሊዮን ዶላር፤ ይህ ከገበያው ዋጋ በታች በሆነ ወለድ የሚከፈል ወይም በዜሮ ወለድ የሚከፈል ብድር ነው
- ማኅበሩ (IDA) ለኢትዮጵያ እሰጣለሁ ብሎ ቃል የገባው 15.5 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን
- ከዚህ ውስጥ 7 ቢሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ ለመረከብ እስከተዘጋጀች ማኅበሩ ለመስጠት እጁ ላይ ያለ ገንዘብ ነው።
- ማኅበሩ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የኢኮኖሚ ተሐድሶውን ለመደገፍ የሚረዳ ለበጀት ድጎማ የሚሆን ተጨማሪ ቃል ሊገባ ይችላል
ዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር (IDA) የሚፈቅደው ገንዘብ ለታዳጊ አገሮች የሚሰጥ ሲሆን ዋናው ባህርዩ ከገበያው ዋጋ በታች የወለድ መጠን ወይም በዜሮ የወለድ መጠን ማበደር ሲሆን ከሚሰጠው ብድር ግማሽ ያህሉ በሥጦታ መልክ የሚለገስ ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የስምምነት ዱቤ ከማኅበሩ የምታገኝ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ሥጦታ ነው።
ዛሬ ይፋ የሆነው ሌላው የገንዘብ ድጋፍ ከሁለት የባንኩ ድርጅቶች የተገኘ ነው፤
- ከዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ትብብር (The International Finance Corporation (IFC)) 320 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ ሌላው የዓለም ባንክ ቡድን አባል ሲሆን ዋናው ትኩረቱ በታዳጊ አገራት ዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነው።
- ይህ መጠን በቀጣይ ዓመታት እስከ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ሊያድግ የሚችል ነው።
- የባለብዙ ወገን ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ (Multilateral Investment Guarantee Agency (MIGA)) ከሚባለው 1.15 ቢሊዮን ዶላር፤
- ይህ ከዓለም ባንክ ቡድኖች አንዱ ሲሆን በታዳጊ አገራት ውስጥ በሚፈጸም ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ አበዳሪዎች ወይም ኢንቨስተሮች ሊገጥማቸው ለሚችል የፖለቲካ ኪሣራ የመድኅን ዋስትና የሚሰጥ ነው።
በአጠቃላይ ዛሬ ይፋ የሆነው የዓለምአቀፉ ባንክ የገንዘብ ድጎማ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የተፈቀደላት ፓኬጅ 16.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ገልጾዋል።
ባንኩ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት መካከል ለመሆን ያላትን ትልም ግምት ውስጥ በማስገባት የኢኮኖሚ ሪፎርም ወይም ማሻሻያና የበጀት ድጋፍ በማድረግ ዕገዛውን እንደሚቀጥል ዛሬ የወጣው የባንኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ያስረዳል።
ይህንን ፈር ቀዳጅ የሆነውን የዓለም ባንክ ውሳኔ ተከትሎ በቀጣይ ሌሎች አበዳሪ ተቋማት ተጨማሪ የገንዘብ ድጎማዎች እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply