ስሙ የክህደት መጠሪያ ሆነ እንጂ የስሙ ትርጉም ግሩም ነው። ይሁዳ የሚለው ቃል በእብራይስጥም “ይሁዳ” ማለት ነው፤ “ያዳ” ነው ሥርወ ቃሉ ይላሉ የሙያው ባለቤቶች። ይህ ደግሞ ትርጉሙ “ማመስገን” ማለት ነው። በግሪክም ትርጓሜው ተመሳሳይ ነው – “የተመሰገነ”፣ “ምስጉን” ማለት ነው።
“የአስቆሮቱ” የሚለው ቃል ደግሞ የክፋት መጠሪያ አይደለም። በተለምዶ “የአስቆሮቱ ይሁዳ” በማለት ከሃዲዎችን ስንጠራቸው “አስቆሮቱ” የይሁዳ የክፋት ማዕረግ ይመስለናል። ሊቃውንቱ እንደሚሉን ከሆነ ትርጉሙ “የኬሪዮት ሰው” ወይም “የአራዳ ልጅ” እንደ ማለት ነው ይላሉ። ስለዚህ በከሃዲነቱ ባናውቀው ኖሮ “ተመስገን ያራዳ ልጅ” ብለን እንጠራው ነበር። ስሙ ግን ከግብሩ ፍጹም የራቀ ነው፤ እንዲያውም ተጻራሪ።
ይሁዳ ከሃዲ ብቻ አይደለም፤ ማሳካት የሚፈልገው ዓላማ ያለውና የሚያደርገውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ነበር። ከመድኃኒዓለም ጋር አብሮ ለሦስት ዓመት ተኩል ቆይቷል፤ የጌታችንን አስተዳደርና አመራር ውስጠ ምሥጢሩን በደንብ አጥንቷል። “ሐዋርያ” ተብሎ ተጠርቷል። ሁለት፣ ሁለት ተደርገው ሲላኩ እርሱም ሁለት ጊዜ ተልኳል። አጋንንት አውጥቷል፣ ተዓምራት ሠርቷል፤ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንሰሐ ግቡ” እያለ ወንጌልን ሰብኳል!
ይሁዳ ሲነቅፍ በጭፍን አይደለም፤ ረቂቅ ነው። አዛኝና ርኅሩኅ ምስኪን ሆኖ ነው እንጂ በፈጣጣው አይደለም። ማርያም መግደላዊት እጅግ ውድ የሆነ ሽቶ በጌታችን እግር ላይ ስታፈስ “ይህ ተሸጦ ድሆችን መመገብ ይቻል ነበር” ያለው እንጂ በጭፍን አልተቃወመም። መጽሐፍ ግን ይህንን ያለው “ሌባ ስለነበር ነው” ይላል።
መምህሩን የሸጠው ለገንዘብ ብቻ ብሎ አይደለም። ዓላማው ሌላ ሆኖ “ለምን ቢዝነስ አልሠራም” በሚል ገንዘቧ የጎንዮሽ ጥቅም ማስገኛ ነበረች። መድኃኒዓለም አሳልፎ ከተሰጠ አልያዝም በማለት ያምጻል፤ ከዚያም ያንን ሙታንን የሚስነሳውን ኃይል ተጠቅሞ ሮምን ድምጥማጧ ያጠፋል፤ ከዚያም መምህሩ በዳዊት ዙፋን ሲነግሥ “ለዚህ ነጻነት ያበቃኋችሁ እኔ ነኝ” ብሎ ይሁዳ የእልፍኝ አስከልካይ ወይም አፈ ንጉሥ ወይም የንጉሥ አማካሪ ወይም አንድ የሆነ ሥልጣን ላይ እደርሳለሁ ብሎ ነበር። ሁሉም ቀርቶ መጨረሻው ፍጹም የተለየ ሆነ!
የእኛ አገር ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች የሚባሉት፣ ዩትዩበሮች፣ ወዘተ ከስማቸው ብንነሳ የብዙዎቹ ቤተሰብ ያወጣላቸው ስም በጣም ደስ የሚልና ጥሩ ትርጉም ያለው ነው። እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ነው። አሁን አሁን ግን የአንዳንዶቹ ስም እንደ ይሁዳ ለልጆቻችን የማናወጣው እየሆነ የመጣ ይመስላል። እንደው እንደ ምሳሌ ብንጠቅስ ልጁን “ሕዝቅኤል፣ ኤርምያስ” ብሎ የሚሰይም ሁለት ጊዜ ማሰቡ አይቀሬ ነው። የሌሎቹ ስም እንኳን ከድህነት ለመላቀቅ፣ ከደጋፊ ዘመድ አልባ ብቸኝነት ለማምለጥ በሚል ለምኞት ማስታገሻነት የወጡ የአጥቢያ ስሞች ስለሆኑ ሳልጠቅስ ልለፋቸው።
እነዚህ የአገራችን ይሁዳዎች እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ዓላማ ያላቸው ናቸው። በየቀኑ የሚያደርጉትን ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ መዳረሻ አላቸው። በሥራቸው የሚላላኩላቸው ጉዳይ ፈጻሚዎችም አሏቸው። በየቀኑ እየበላሁ እንዴት ዝም እላለሁ እንደሚል ውሻ እየወጡ የሚጮኹ ናቸው። ብዙዎቹ በቅርብ ሆነው ምሥጢር በመጠኑ ያጠኑና ያወቁ ናቸው። ለውጡን ተከትሎ በየሚዲያው የለውጡን ወንጌል ውስጥ ካሉት ሰዎች በላይ ሲሰብኩ የነበሩ ናቸው። “የለውጥ ዘመን መጥቷልና ከዘመነ ኢህአዴግ አገዛዝ ንሰሐ ግቡ” እያሉ በየቀኑ ስብከተ ለውጥ ሲያሰሙ፣ ውዳሴ ሲያቀርቡ ነበሩ።
በኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ዓይናቸው የታወረውን ያበሩ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ልክፍት የተያዙን በወንጌለ ለውጥ እያናዘዙ ያስወጡ፤ ከለውጡ ሊቃነ ጳጳሳት በላይ የለውጥ ፋና ወጊዎች የነበሩ ናቸው። ከባሕር ማዶ የተመኙትና በርቀት የተሳለሙት ሹመት፣ አማካሪነት፣ ቪላ ቤት፣ ቪ8፣ … ቀቢጸ ተስፋ ሆኖ እንደ ጉም ሲተንንባቸው ኢትዮጵያን ለመስቀል 30 ብር ተቀብለው እንደ ይሁዳ ሥራቸውን በምሽት እየሠሩ ነው – የጨለማውን ሥራ! ይሁዳ መምህሩን አሳልፎ ለመስጠት በአንድነት ራት ይበሉ ከነበረበት ቤት ሲወጣ መጽሐፍ ሲናገር “ሌሊትም ነበር” ይላል።
የዘመናችን ይሁዳዎች እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ለድሃ ሐዘነተኛ ሆኖ በመታየት የሚቀድማቸው የለም። ይሁዳ ሽቶው ተሸጦ ለድሆች ሊሰጥ ይችላል አለ እንጂ እኔ ለድሆች ልስጥ አላለም። እነዚህም እንዲሁ ናቸው። ሰው እየሞተ ዳቦ ቤት ለምን ይገነባል? ለዳቦ ቤት መገንቢያ የወጣውን ገንዘብ ለድሆች ብናከፋፍለው ለስንት ደሃ ሊደርስ ይችል ነበር? በማለት ይሁዳዊ አዛኝነታቸውን ያሰማሉ።
ኢትዮጵያ ስሟን ቀያሪ የሆነውን ተግባር ፈጸመች – ስንዴ ወደ ውጭ ላከች! ሲባል የስንዴ ዱቄት ከአገር ውስጥ ገበያ ጠፍቷል ይላሉ። ከዚህ በፊት ስንዴ ለመላክ እየሠራን ነው ሲባል ግን ምንም ትንፍሽ ሳይሉ የቆዩ ናቸው። ምናልባትም ስንዴው ለምርት አይደርስም ብለው ጠብቀው ይሆናል። ምርቱ መሰብሰብ ሲጀምር ግን በጦርነት እየታመሰች ያለችው ዩክሬይን ለኢትዮጵያ ስንዴ ላከች ብለው ነበር። የሚገርመው የእርዳታ እህል ተካለ ሳይሆን የተባለው “ስንዴ” በስም ተጠርቶ ነው ወሬው የተሰራጨው። መርከቧ በሶማሊያ የባሕር አደጋ ጣዮች ተዘረፈች እንዳንል እስካሁን ምንም የተሰማ ነገር የለም፤ መርከቧ ቀርታ “ስንዴው” ቢደርስ እንኳ ጥሩ ነበር።
ኢትዮጵያዊ ይሁዲዎቹ ከስንዴው ፖለቲካ በፊት የሰሜኑን ጦርነት ኢትዮጵያ እንደማታሸንፍ እና የወንበዴው ቡድን ኃይል ታላቅ እንደሆነ በየቀኑ ሲሰብኩ ነበር። የወንበዴው ቡድን ከምዕራባውያን ጋር ነውና ኢትዮጵያ አልቆላታል እያሉ ተስፋ አስቆራጭ ዲስኩር ሲለቅቁ ነበር። አጎዋ ስንሰረዝ ከበር መልስ ተገባበዙ፣ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ለቁጥር የሚታክት ስብሰባ በአገራችን ላይ ሲጠራ አልቆላችኋል ሲሉን ነበር።
የእኛዎቹ ይሁዲዎች የወንበዴው ቡድን አገልጋዮች በነበሩ ጊዜ በዕቅድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በማፍረስና በማስፈረስ ታጥቀው የሠሩ ይህንን እንደ ሜዳሊያ በጽሑፎቻቸው በግልጽ ሲሰብኩ የነበሩ፤ አሁን ደግሞ የኦርቶዶክስ ቋሚ ጠበቃ ሆነው ብቅ ያሉ፤ ጉዳዩ በሰላም ሲጠናቀቅ ግዝት ፈርተው ከካሜራ ውጪ ሲኖዶሱን ሙልጭ አድርገው የተሳደቡና አባቶችን ከፍ ዝቅ አድርገው ያዋረዱ ናቸው።
የከሸፈ፣ የተመታ፣ የትም የማያደርስ፣ የምቀኝነት፣ የውርደት ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ!
የይሁዳ ዓላማ የራስ ጥቅም እና ሲመተ-እኔ ነው! እኔ ልጠቀም፣ እኔ ልሾም፣ እኔ … እኔ … ነው። ይህ የሚፈጸመው ግን በገሃድ ሳይሆን በሕዝብ ዕንባና ደም ወንዝ ላይ ወደ ሥልጣን በመቅዘፍ ነው። እጅግ የረከሰ፣ እጅግ ኢሞራላዊ፣ እጅግ አስጸያፊ የሆነ፣ የመስተካከል እንጥፍጣፊ ተስፋ የሌለው ማንነት!
መጽሐፍ ስለ ይሁዳ መጨረሻ ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “(ሠላሳ) ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ”።
ባለማተቡ ነኝ (trinity123@aol.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
ይስሃቅ አበበ says
በተጨባጭ የነ ቁስ ከርስ ጉርስ ፈላጊና ህልመኛ ይሁዳ አክቲቪስቶችን ማንነት በትክክል የገመገክበት እውነታ ነው !! የሚያሳዝነው ግን የዋሁ ህዝባችን እነዚህን ክፉ የሴራ ተንኮል አሉባልተኞች አለመረዳቱ አለማወቁ ነው ። ዘውትር መንግስትን ማብጠልጠል ማሳነስ ለሀገር አንዳች አይጠቅምም ። በጎውንም በሚዛን የሚገልፁ አሉ እነዚህ ለኔ ለትውልድም ለሀገርም የሚያስቡ የህሊና ንፅህና ያላቸው በጎ ስዎች ናቸው ። ማድመጥም መስማትም ያለብን እነዚህን ነው ።