“… ስሙን መጥቀስ ባያስፈልግም አንድ ጎረምሳ ልንለው እንችላለን። ጃዋር ዜግነቱ አሜሪካዊ በመሆኑ የጃዋር ሚዲያ የተመዘገበው በዚህ ጎረምሳ ስም ነው። ከየአቅጣጫው የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚቀመጠው በዚሁ ልጅ ስም ነው። መኪኖችና አንዳንድ ንብረቶች የሚገዙትም በዚሁ ስም ነው። ይህ ጎረምሳ አዲስ አበባ እጅግ መንዛሪና በከፍተኛ ቅንጦት እንደሚኖር የሚያውቁት ነገረውኛል። የቄሮ አካልም አልነበረም። ቄሮ ከድል በኋላ ቤቱ ሲመለስ የጠበቀው ማሳውና መደቡ ሲሆን እነ ጃዋርና ስማቸውን የሚጠቀሙባቸው ጎረምሶች በሚሊዮኖች እየረጩ ዘመናዊ ተሽከርካሪ ይሸምታሉ፤ ንብረት ያከማቻሉ፤ ሰዎች ሰላም ሰፍኖ በተረጋጋ መልኩ እንዳያስቡ ቀውስ ይመረትላቸዋል። ልክ ከዚህ በፊት ተደርጎ እንደማይታወቅ በዓሉንም፣ ልደቱንም፣ በሚዲያ እያስጮሁ ያሳብዱታል። ይህ ወጣት የሰከነ ዕለት ለጃዋር የሚቀርብለት ጥያቄ ስለሚታወቅ ክልሉም ሆን ቄሮ አጀንዳ ገና ይፈለፈልለታል …”
በኦሮሚያ እጅግ ተስፋ ሰጪ የፖለቲካ መስተጋብር እየታየ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ እየተሸረበ ያለው የፖለቲካ ቁማር አስቀድሞ ወላፈኑ የሚገርፈው የኦሮሞን ሕዝብ በተለይም ወጣቶችን እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። አቶ ገመቹ ደንደና እንደሚሉት ግን ሳይገባቸው እንደ አቦሸማኔ የሚጋልቡት መብዛታቸው ከስጋትም በላይ ነው። ምልክቶችም እየታዩ ነው።
በተለያዩ መድረኮች በቃል ደረጃ ከሚሰማው በቀር በኦሮሚያ “ተስፋ ሰጪ” የሚባለው የፖለቲካ መስተጋብር በገቢር የሚታይ እንዳልሆነ “ተስፋ ሰንቀናል” የሚሉት ራሳቸው የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው። ቢያንስ ቢያንስ ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች ከጥቅም ባሻገር ልዩነታቸውን አስወግደውና አቻችለው በሰላማዊ መንገድ ለመፎካከር መስማማት አለመቻላቸውን እነዚሁ ወገኖች በሃፍረት የሚገልጹት ነው። ልዩነት ቢኖርም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ አለመቻልና ነፍጥ ይዞ እሰከመገዳደል መድረሳቸው የመጨረሻው መጀመሪያ ማሳያ አድርገውም ይወስዱታል።
ሕዝብን በማይወክል ደረጃ የሚራገቡ አጀንዳዎችና ፕሮፓጋንዳዎች አየሩን መሙላታቸው ዛሬ ላይ ድል ቢመስልም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ልብ የሚደርስ መረጋጋት እንዳይፈጠር ምክንያት እንደሆነ አቋም ይዘው የሚወተውቱ አሉ። ጥፋቶችን የማረም ሥራ ከተሠራ “ተስፋ ሰጪ” የሚሰኘው የፖለቲካ ጅማሮ ከተስፋ እንደሚዘል በተስፋ ላይ ተስፋ ደርበው ያምናሉ።
“ቁማር እየተቆመረ ነው” የሚሉት ወገኖች በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል ምን እየሆነ እንደሆነ ለመረዳት የሚያዳግቱ አጋጣሚዎች እየበረከቱ መሆናቸውን ያወሳሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች አስተያየት የሚሰጡ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ከራሳቸው ጉዳይ አልፈው የኦሮሞን ጥቅም እናስከብራለን የሚሉ ወገኖች በሲዳማ፣ በቅማንት፣ በአገውና በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መነከራቸው የማንን አጀንዳ እያስፈጸሙ እንደሆነ ይጠይቃሉ።
በኦሮሞ ህዝብ ስም ቅማንት ውስጥ ገብቶ እሳት መቆስቆስ፣ አገው ምድር ገብቶ ረመጥ ማራገብ፣ ሲዳማ ውስጥ ገብቶ ሕዝብ እንዲጫረስ አቅጣጫ ማስቀመጥና በሚዲያ ማራገብ፣ በራያና መሰል ጉዳዮች መነካካት ፍጹም እንደማይጠቅም የሚናገሩ እንደሚሉት፣ “አጀንዳ ተሸካሚዎች” ለኦሮሞ ሕዝብ ጠላት እየገዙለት ነው። ይህ አካሄድ የሰሜኑ ፖለቲካ ውጥረት የተነፈሰ ዕለት የኦሮሞን ሕዝብ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
እነዚህ ወገኖች ወደ ኋላ ሄደው “በእኔ ስም አይደረግም” በሚል ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም የሚፈጽመውን በደል እንዲያቆም ሲጠየቅ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዛሬም የኦሮሞ ሕዝብ፣ በተለይም ልሂቃኑ በኦሮሞ ስም የሚከናወኑትን አስከፊና ነገ ዋጋ የሚያስከፍል አካሄዶችን ልክ “በስማችን እንዲደረግ አንፈቅድም” ሊሉ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ለውጡን ወዳልሆነ አቅጣጫ በመግፋት ለውጡ እንዲጨናገፍ ሌት ከቀን ለሚታትሩ ቀበኞችን አሳልፎ ለመስጠት የሚሰሩ የኦሮሞ ልሂቃን ለውጡ የተከፈለበትን የደም ዋጋ፣ ዋጋ ቢስ እንዳያደርጉት ከሚሰጉት መካከል አንዱ አቶ ገመቹ ደንደና ናቸው።
በ“ነጻነት” ትግል ስም ተነስቶ ዛሬ በኤሌክትሮኒክስና በኅትመት ሚዲያ ባለቤትነት የሚታወቀው ጃዋር መሃመድ የዚሁ የሚፈራው የቀጣዩ ቀውስ አቀጣጣይ ነዳጅ እንደሚሆን የዋሺንግተን ዲሲ ነዋሪ አቶ ገመቹ ደንደና ለጎልጉል ተናግረዋል። ጃዋር በትግል ስም እጁን በርካታ ቦታዎች አስገብቷል። ከውጪ ኃይላት ጋር ስምምነት ፈጥሮ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ተማምሏል። ይህ እንግዲህ ከኦሮሞ ሕዝብ የተደበቀ፣ አብዛኞች ልሂቃኖችም ለጊዜው ዝምታ የመረጡበት አድሮ የሚፈነዳ የቁማር ፖለቲካው ፈንጂ ነው።
ቄሮ ወይም የኦሮሞ ወጣቶችን በማስተባበር ሊካድ የማይችል ሥራ ከሠሩት እጅግ በርካቶች መካከል አንዱ የሆነው የሆነው ጃዋር የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክን ሲጀመር የነበሩ የቦርድ አመራሮችና አጋሮቹ መቼና እንዴት ሃሳባቸውን እንደሚገልጹ ባያወቁም፣ በርካቶች ሙሉ በሙሉ መባረራቸው ያወሱት አቶ ገመቹ፣ ጃዋር የኦሮሞ ልጆችን ካኮላሹ፣ ከገደሉ፣ እንዲሰደዱ ካደረጉ፣ ንብረታቸው ከዘርፉና የህወሓት ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል። ህወሓት ስፖንሰር የሚያደርጋቸውን የቅማንት፣ የአገው ንቅናቄን በኦ.ኤም.ኤን. ከፍተኛ ሽፋን መስጠቱ የዚህ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ አመላክተዋል።
ጃዋር በሚመራው ሚዲያ ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ የግልጽነት ችግር፣ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል ዝርክርክ አሠራርና እንዳሻው ገንዘብን የማባከን ችግር እንዳልበት በውል እንደሚታወቅ የሚጠቁሙት አቶ ገመቹ፣ ኦ.ኤም.ኤን. አዲስ አበባ የተመዘገበው አንድ ጎረምሳ ስም መሆኑንን አስታውቀዋል።
“… ስሙን መጥቀስ ባያስፈልግም አንድ ጎረምሳ ልንለው እንችላለን። ጃዋር ዜግነቱ አሜሪካዊ በመሆኑ የጃዋር ሚዲያ የተመዘገበው በዚህ ጎረምሳ ስም ነው። ከየአቅጣጫው የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚቀመጠው በዚሁ ልጅ ስም ነው። መኪኖችና አንዳንድ ንብረቶች የሚገዙትም በዚሁ ስም ነው። ይህ ጎረምሳ አዲስ አበባ እጅግ መንዛሪና በከፍተኛ ቅንጦት እንደሚኖር የሚያውቁት ነገረውኛል። የቄሮ አካልም አልነበረም። ቄሮ ከድል በኋላ ቤቱ ሲመለስ የጠበቀው ማሳውና መደቡ ሲሆን እነ ጃዋርና ስማቸውን የሚጠቀሙባቸው ጎረምሶች በሚሊዮኖች እየረጩ ዘመናዊ ተሽከርካሪ ይሸምታሉ፤ ንብረት ያከማቻሉ፤ ሰዎች ሰላም ሰፍኖ በተረጋጋ መልኩ እንዳያስቡ ቀውስ ይመረትላቸዋል። ልክ ከዚህ በፊት ተደርጎ እንደማይታወቅ በዓሉንም፣ ልደቱንም፣ በሚዲያ እያስጮሁ ያሳብዱታል። ይህ ወጣት የሰከነ ዕለት ለጃዋር የሚቀርብለት ጥያቄ ስለሚታወቅ ክልሉም ሆን ቄሮ አጀንዳ ገና ይፈለፈልለታል …” ሲሉ አብራርተዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የቀድሞ የቦርድ አባላት አስተያየት እንዲሰጡ ቢጋበዙ በርካታ ምሥጢሮች እንደሚጋለጡ አክለው ገልጸዋል። የቀድሞ የቦርድ አባላት ነገሮች ሳይበላሹ እውነቱን ለህዝብ እንዲያሳውቁም ተማጽነዋል።
ጃዋር በግል ከሚሰበሰበው ሃብት በተጨማሪ በሲዳማ ከሚንቀስቀሱ የኤጄቶ መሪዎች ጋር በቅርቡ በተፈጸመው ጭፍጨፋና የዘር ማጽዳት ወንጀል ጀርባ እንዳለበት አቶ ገመቹ ተናግረዋል። የሲዳማን ነጻነት በኃይል እንዲያውጁ በገሃድ የተናገረውን ሳይሆን፣ ጃዋር የኤጄቶን የኃይል እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር መንግሥት መከላከያን ማሰማራቱ በዝርዝር በማስረዳት አመጹን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ ዕቅድ ነድፎ ንጹሃን እንዲጨፈጨፉ ዋንኛ ምክንያት መሆኑንን ለጎልጉል ቅርብ የሆኑ የሲዳማ ንቅናቄ ሰዎች ገልጸዋል። አቶ ገመቹ እንደሚሉት ጃዋር የደቡብ ክልል ወደ ትናንሽ ዞኖች የመበጣጠስ ዕቅድ እንዳለው እንደሚያውቁ አመልክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ስም በማንሳት ነጥሎ የጥላቻ ዘመቻ የሚያራምደው ጃዋር በዚህም መልኩ የህወሓትን አጀንዳ እንደሚያስፈጽም አቶ ገመቹ ያወሳሉ። የትግራይ ባይቶና ሥራ አስፈጻሚ ከኤል ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ህወሓት ከማይመስሉት ጋር አብሮ ገጥሞ ከስሯል” ሲሉ መናገራቸውን የሚያስታውሱት አቶ ገመቹ፣ ህወሓት ከኦነግ ጋር ለጀመረው ወዳጅነት ያመች ዘንድ “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል” የሚለው የዲጂታል ወያኔ ዓላማ አራማጅ ስለመሆን ጥርጥር የላቸውም።
የተለያዩ የኦሮሞ ድርጅቶች ከኦዴፓ ጋር ሊያካሂዱት የነበረውን ውህደት ከዳር ሆኖ በማጨናገፍ ጃዋር ታላቅ ሚና መጫወቱን ወዳጆቻቸው እንደሚነግሯቸው የገለጹት አቶ ገመቹ “እነ ጃዋር ቤት ለምን የሸዋ ልጆች ተሾሙ” የሚል ቅጥ ያጣ የጥላቻ ስሜት እንዳለ አልሸሸጉም። ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ አቶ ገመቹ “በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር የሚፈልግ ይምጣ። የሸዋ ልጆች በጃዋር ሚዲያ ውስጥ መድረክ የላቸውም። ሰዓት አይሰጣቸውም። በሚያሰማራቸው ሠራተኞች ውስጥም አብዛኞቹ የየትኛው አካባቢ ልጆች እንደሆኑ የሚታወቅ ነው” ይላሉ።
ጃዋር በተደጋጋሚ ሲናገር ቁርዓን በመያዝ ዶ/ር ዐቢይ እንዳይመረጡ ሕዝብ ለማሳመን እንደሚሠራ በተለያዩ ሚዲያ ላይ መጻፉንና ማየታቸውን አቶ ገመቹ ያስታውሳሉ። አያይዘውም በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድ መንግሥት በሩን በመዝጋቱና ይህ እንደማይሆን ሲያረጋገጥ ጃዋር ወደ ኦርቶዶክስ እምነት ፊቱን የማዞር ዕቅድ እንዳለው አስቀድመው መስማታቸውን አመልክተዋል። በዚህም የሰሞኑ የኦሮሞ ኦርቶዶክስ እንቅስቃሴን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።
አሁን ለጊዜው ስም መጥራት አግባብ ባለመሆኑ ይቅርታ በመጠየቅ አቶ ገመቹ፣ ጃዋር በውጪ አገር ለማመን በሚያስቸግር ደረጃ አንድ ተደማጭነት ያለውን ሚዲያና ሌሎች ግሩፖችን ስፖንሰር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት January 14, 2014 ላይ “አፈንዲ፣ ጃዋር መሐመድ እና የቴዲ አፍሮ ጉዳይ” በሚል ርዕስ አፈንዲ ሙተቂ ታሕሳስ 26/2006 የጻፈውን አትሞ ነበር። በዚህ ጽሁፍ ላይ አፈንዲ ስለ ጃዋር ሲናገር ይህንን ብሎ ነበር፤
“ይህ ሰው በጣም አጭበርባሪ ነው። የውሸት ወሬ መፈብረክ ይችልበታል። ደግነቱ የሚፈበርካቸውን ወሬዎች ሀሠትነት ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ አይፈጅም። የዚህ ሰው ሌላኛው ባህሪ ደግሞ ለሁሉም የፖለቲካ ቡድኖችና ፓርቲዎች የሚሰራ መሆኑ ነው። ሰውዬው ከላይ ሲታይ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ይመስላል። ሆኖም አብዛኛው ሰው እንደሚያውቀው ከኦፒዲኦ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋርም የጠበቀ ግንኙነት አለው። አንድ ቀን ሳያስበው ይህንን ግንኙነቱን ግልጽ ያደረገበትን ጥያቄ ጠየቀኝ። እኔ በሰጠሁት ምላሽ ሳስደነግጠው ትንሽ እንደማፈር ብሎ ዘጋው (በወቅቱ የጠየቀኝን ጥያቄ ሌላ ጊዜ ብነግራችሁ ይሻላል)። በርሱ ቤት ነገሩን የማላውቅ መስሎታል። ይሁንና በፌስቡክም ጭምር በሰፊው ሲባል የነበረ ነገር በመሆኑ ብዙም አልደነቀኝም። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሰው ከኦነግ-ቀመስ ቡድኖችም ጋር በትክክል እንደሚሰራ መረጃው አለን። ከሻዕቢያ ጋር እንደሚሰራም ውስጥ ውስጡን ይወራል። እነዚህ ግንኙነቶቹ ቀደም ብዬ የሰማኋቸው በመሆኑ ብዙም አላስገረሙኝም። በጣም የተደነቅኩት ግን “ነፍጠኛ” እያለ ቀን ከሌሊት ከሚሰድባቸው ቡድኖችም ጋር የሚሰራ መሆኑን እራሱ በነገረኝ ጊዜ ነው። የዚያን ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት (ዕለቱ ህዳር 7/2006 ነው)። “ይህ ሰው ጥቅም ካገኘ ለሰይጣንም ይሰራል ማለት ነው ለካ!” በማለት ተደመምኩበት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዚህ ሰው ጋር የማደርገውን የመልዕክት ግንኙነት ገታ ማድረግ ጀመርኩ (እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ማስረጃው በእጄ ነው ያለው)” ሙሉውን ጽሁፍ እዚህ ላይ ማንበብ ይቻላል።
ሶማሌ ክልል ላይ ዞር በል የተባለው ጃዋር በየቦታው እየዘራው ያለው ዘር በሙሉ አድሮ ኦሮሚያ ላይ የተቀበረ ፈንጂ እንደሚሆን ጥርጥር እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ገመቹ፤ ሰፊው የኦሮሞ ወጣት በርጋታ የነገሮችን አካሄድ እንዲገመግም ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሞ ልሂቃንም ከዝምታ ይልቅ እንደ አቦሸማኔ እየጋለበ ያለውን ትውልድ ራሳቸውን ነጻ አውጥተው እንዲያስተምሩት መክረዋል። ከጸብና በተግባር ሊውል ከማይችል ተስፋ ወጣቱን አላቅቆ አምርቶና ሠርቶ ሊቀየር የሚችልበትን ስትራቴጂ እንዲያስተምሩ ጥሪ አቅርበዋል።
“ከቶውንም የማይሆን” ሲሉ የተቃወሙት ግን “የሸዋ ልጆች ለምን ወደ ኃላፊነት መጡ የሚለው አካሄድ ከተራ መፈንቅለ መንግሥት የማይተናነስ በመሆን ጠንቀቅ” ሲሉ አስጠንቀቀዋል። ዘረኞችንም ኮንነዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply