
በኢትዮጵያ ደረጃ የሚታየው መድረሻውን ያስቀመጠ የሀሰተኛ መረጃ ሻሞ ወይም እርባታ ሕዝብን እንደ ዋዛ እያሳከረ፣ አገርን ለአደጋ የሚዳርግ፣ ታስቦበት፣ በዕቅድ፣ በባለሙያ፣ በበጀት፣ በድርጅት፣ በመሪ፣ በሥልጠና የሚከናወን የዘመኑ የዲጂታል ጦርነት ነው።
ሰሞኑን የፓሪስ ከተማ ክፉኛ ተንጣ ነበር። የናጣት በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ አንድ ሐሰተኛ መረጃ ሲሆን፣ መረጃው “የፓሪስ ውሃ ተመርዟልና አትጠጡ” የሚል የጅምላ ጥሪ ነበር። መረጃው የነፍስ ጉዳይ በመሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎች ክፉኛ ናጣቸው። ይህንን አሸባሪ መረጃ ለመከላከል የፓሪስ አካባቢ ኃላፊዎች መግለጫ እንዲሰጡ አስገደዳቸው። በመሆኑም አርብ ሐምሌ 12፤ 2011 (ጁላይ 19) ተመረዘ የተባለው ውሃው እንደተባለው እንዳልተመረዘና ለመጠጥም ቢሆን ምንም የማያሰጋ መሆኑን አስረግጠው ተናገሩ።
ይህ የሐሰት መረጃ ፓሪስን ለዚህ ሊያደርሳት የቻለበት ዋናው ምክንያት አንድ ACRO የተባለ ዕንባጠባቂ ድርጅት በፓሪስ ቧንቧዎች በሚተላለፈው ውሃ ውስጥ ትሪትየም (tritium) የተባለ የኑክሊየር ንጥረነገር ከሌሎች አካባቢዎች ይልቅ በብዛት ይገኛል ብሎ መዘገቡን ተከትሎ ነበር።
ይህንን ቁንጽል መረጃ በመያዝ በርካታዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፓሪስ ውሃ ተመርዟል፤ አትጠጡ የሚል መረጃ በማሰራጨት ሕዝቡን ሲያውኩ ቆዩ። በመሆኑንም የመንግሥት ኃላፊዎች በዚሁ የማኅበራዊ ሚዲያ በመውጣት ውሃው ውስጥ ከሌሎቹ አካባቢዎች መጠኑ ከፍ ያለ የትሪቲየም ንጥረነገር ቢኖረውም “ተበክሏል” የሚያስብል ደረጃ ላይ አለመድረሱን አስረዱ። ዕንባጠባቂው ድርጅትም ቢሆን ንጥረነገሩ ከሌሎች አካባቢዎች በላቀ ሁኔታ በፓሪስ አካባቢ ይታያል ቢልም ከሚገባው መጠን አልፏል ግን አላለም ነበር።
በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደዘገበው የውሸት/ሃሰት መረጃ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደ ሰደድ እሣት እንደሚስፋፋ ተናግሯል። ከፍጥነቱ በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ የመቆየትና በበርካታ ቦታዎች ለብዙ ሰዎች እንደሚዳረስ የጥናቱ ተማራማሪዎች ተናግረዋል። ሰዎች ከእውነተኛ መረጃ ወይም ዜና ይልቅ ሐሰተኛ መረጃ ለማሰራጨት በጣም ፈጣኖች እንደሆኑ መረጃው አመልክቷል።
ጥናቱን ያደረጉ ተመራማሪዎች እንደ ግብዓት አድርገው የወሰዱት እኤአ ከ2006 – 2017 ድረስ በትዊተር የተሰራጩ ወሬዎች፤ የሐሰት መረጃዎችና ሹክሹክታዎችን መሠረት በማድረግ ነበር። በዚሁ ጥናት መሠረት 126,000 ሹክሹክታዎች በ3 ሚሊዮን ሰዎች አማካይነት፣ 4.5 ሚሊዮን ጊዜ ተሰራጭቷል፤ ተራብቷል።
የሐሰት መረጃዎች ባጭር ጊዜ ውስጥ ከ1,000 እስከ 100,000 ሰዎች ዘንድ ሲደርሱ፣ የእውነተኛ መረጃ ስርጭት ግን ከ1,000 ሰዎች በላይ አይዘልም። በሌላ አገላለጽ አንድ ሐሰተኛ መረጃ በቅጽበት ጊዜ ውስጥ 1,500 ሰዎች ዘንድ ሲደርስ፣ አንድ እውነተኛ መረጃ አንባቢያን ዘንድ የሚደርሰው በሚያስገርም ሁኔታ ስድስት እጥፍ ጊዜ ወስዶበት ነው። መረጃውን በማሰራጨት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚወስደው ደግሞ ተራው ሕዝብ እንደሆነ የምርምር ዘባው አስረድቷል።
በአገራችን የለውጥ እንቅስቃሴ በመንግሥት ደረጃ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በዘመነ የትግራይ ነጻ አውጪ የ27 ዓመታት የግፍ አገዛዝ ዘመናት እምብዛም የማይታወቀው የሐሰት መረጃና ዜና በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስቡክና ዩትዩብ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ብዙዎቻችን የምንመሰክረው ጉዳይ ነው። በእነዚህ የሐሰት መረጃዎች አማካኝነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ክቡር የሰው ልጆች ህይወት እንደጠፋ፣ ንብረት እንደ ወደመ፣ ሰላም እንደ ደፈረሰ፣ አገራችን እንደታወከች፣ ወዘተ የሚክድ የለም።
የሃሰት መረጃ ለምን በረከተ? ከአፋኙ ዘመነ ህወሓት ይልቅ አሁን ለምን ሚዲያው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሃሰት መረጃ ተሞላ? በዕቅድ የሚካሄድ የዲጂታል ጥቃት ውጤት ነው? ወይስ እንደው በዘፈቀደ የሆነ ተግባር ነው? በርካታ ገንዘብ የሚፈስበት ፕሮጀክት? ወይስ ጥቂት ግለሰቦች ከማኅበራዊ ሚዲያ ከሚገኘው ትርፍ ራሳቸውን ለማበልጸግ የሚያደርጉት የግል ፍላጎት ላይ የተተከለ የሳንቲም ለቀማ አባዜ? አገር ለማፍረስ የሚካሄድ የተቀነባበረ ተግባር? ወይስ የመንግሥትን ሸፍጥ ለማጋለጥ የሚደረግ የሚዲያ አርበኝነት? የለውጡን እንቅስቃሴ ማክሸፍ ዓላማቸው አድርገው በተነሱ የሚካሄድ ረቂቅ ሤራ? ወይስ “እውነትን እንዘግባለን” በሚል ፍካሬ ሳያውቁት የሌሎች ዓላማና ግብ ያላቸው ሴረኞች ቀጥተኛ መጠቀሚያና ሰለባ የመሆን ውሳኔ? ወዘተ። ጥያቄው ብዙ ነው። ጠያቂዎቹም በርካታ ናቸው።

ይህ ብቻ አይደለም ሌላም የጥያቄውና የአዙሪቱ መነሻ አለ። የትግራይ ነጻ አውጪ ባላሰበው ሁኔታ አገሪቱን እንዲነዳ ዕድል ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ መሪዎቹ ባደባባይ ህዝብን ሲቀጥፉ፣ ዓይናቸውን ታጥበው ሃሰታቸውና ሸፍጣቸውን በሌላ ሸፍጥ ሲያስተባብሉ፣ አገርን በሚያክልና አገራዊ እሴት ባላቸው ታሪካዊ ንብረትና ማንነት ላይ ሲሻቀጡ በነበረበት የ27 ዓመታት የክሽፈት ዘመን ለምን የሃሰት ዜናን የማስተባበል ተቃራኒ ሤራ ልክ አሁን ባለው ደረጃ አልተስፋፋም? ዛሬ በንፅፅር ሚዲያው ክፍት በሆነበት ዘመን የጠራ መረጃ ለህዝብ ማድረስ እየተቻለ ዓላማ ያላቸው የሃሰተኛ ዜና ዘገባዎች ለምን ጎልተው ወጡ? ማንስ ነው የሚያመርታቸው? በምን ያህል የድርጅትና የስትራቴጂ ነዳፊዎች ዘገባዎቹ ተመርተው ይከፋፈላሉ? ማን ላይ ነው መሠረታዊ የማነጣጠሪያ መውጊያቸው የሚያርፈው? አንዳንድ ቁልፍ ጉዳዮች ሲነሱ እንዴት ተጠልፈው ወደ ሤራው ቋት እንዲገቡ ይደረጋሉ? የሚሉትን ዜጎች በጥሞና የመመርመር ፈቃደኛነቱ ካላቸው ቲያትሩ ዕርቃን የሚሆን የተገለጠ ምሥጢር ነው። “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል” እንዲሉ ነውና!!

ባለፉት ጥቂት ቀናት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “ኢህአዴግ ውስጥ እኔ ብቻ ልደመጥ የሚል የኦሮሞ ጽንፈኛ ኃይል ተነስቷል … ወደ ዋሻው ካልተመለሰ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች” በሚል ሪፖርተር ላይ ተናገረ ተብሎ በየሚዲያው የተሰራጨው የሃሰት መረጃ እንደሆነ ታውቋል። መረጃው በፎቶሾፕ ተጠናክሮ በሪፖርተር ታፔላ ተቀናብሮ ሲቀርብ በርካታዎች እውነተኛ ነው በማለት አሰራጭተውታል። ከደብረጽዮን ባህርይና ህወሓት ከሚከተለው ፀረ ለውጥ አቋም አኳያ መረጃውን ትክክል ነው ብሎ ለመቀበል ብዙም የሚያዳግት አልነበረም። የመረጃው አሰራጪዎችም የተጠቀሙት ይህንኑ እሳቤ ጠንቀቀው ስለሚያውቁት ነው ማለት ይቻላል።
አገር ለማዳን የሃሰት መረጃ ላይ ዘመቻ ከወጡ አገር ወዳዶች መካከል የሪፖርተሩ ዳዊት እንደሻው ይህንን ስለ ደብረጽዮን የተሰራጨውን መረጃ በተመለከተ ሲጽፍ ፎቶው “ከሳምንት በፊት ከታተመዉ ጋዜጣ የተወሰደ ነዉ፣ የወጣዉን ዕትም እና ተመሳሳይ የቅፅ ቁጥር በመጠቀም የተቀናበረ (photoshop) ነዉ” ይላል። ሲቀጥልም “ሪፖርተር ጋዜጣ የተመሠረተበት ዓመት ጳጉሜ 6 ቀን 1987 ዓ.ም ሲሆን በግራ በኩል በምታዩት የሀሰት ምስል 21987 ተመሰረተ ተብሎ ተለጥፏል” በማለት የመረጃውን ሃሰተኛነት አጋልጧል።

ይህ እንግዲህ ስፍር ቁጥር ከሌላቸውና በአገራችን ሕዝብ ዘንድ ከተሰራጩ የሃሰት መረጃዎች አንዱ መሆኑ ነው። ከዚህ በፊት እጅግ በርካታ መረጃዎች ከሀሰተኛና በፎቶሾፕ ከተሰሩ ምስሎች ጋር ተቀነባብረው ወጥተዋል። ከጠ/ሚ/ር ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ፣ ቀንና ቁጥር እንዲሁም ማኅተም ያለው ደብዳቤ ዶ/ር ብርሃኑ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ሆኖ ተሾመ በሚል ከወጣው ሃሰተኛ መረጃ ጀምሮ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና ለደም መፋሰስ የሚጋብዙ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መረጃዎች በተለይ በፌስቡክ ሲሰራጩ ቆይተዋል። በዚህም ድርጊት በሚዲያው ዓለም ተዓማኒነት አለን ከሚሉት የዳያስፖራ የሚዲያ አውታሮች ጀምሮ እስከ ራሳቸውን “አክቲቪስት” ብለው የሚጠሩ ጭምር አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ተሳታፊ ሆነው አንሾካሽከውታል፤ አሰራጭተውታል። የሚገርመው ማንሾካሾክ ታላቅ ተግባር ተደርጎ በኢትዮያዊያን ስም አደባባይ ሲያሸልምም ታይቷል። ይህንን ያስተዋሉ ባይበዙም ሃፍረታቸውን በመልዕክት ሳጥናችን ልከዋል።
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው እንዲህ ዓይነቶቹን አድራሻ አልባ ግጭት ጫሪ መረጃዎችን የሚያወጡት ኃይሎች የራሳቸው የሆነ ዓላማ እንዳላቸው ለመገመት ቢቻልም የፈጠራውን መረጃ የሚያራቡና የሚያከፋፍሉት ሌሎች “እኔ የትኩስ መረጃ ባለቤት ነኝ”፤ “እውነትን ብቻ እንዘግባለን”፤ “የ … ገጻችንን ላይክ፣ ሰብስክራይብ፣ ታግ፣ ሼር አድርጉ” በማለት ከማኅበራዊ ሚዲያ ማስታወቂያ በሚገኝ “ገቢ” ራሳቸውን “ብልጥ ዲጂታል ጋዜጠኛ” ያደረጉና ኑሯቸውን በዚያ የመሠረቱ እንደሆኑ አይካድም፤ እነሱም አይስተባብሉም። አንዳንዶቹም በርካታ ድረገጾችንና የማኅበራዊ ድረገጽ አካውንቶችን በመክፈት “በሥፍራው የሚገኘው ዘጋቢያችን” እያሉ ከአንዱ ገጻቸው ወደሌላኛው መረጃ በማገለባበጥ የራሳቸውን ገጽ እንደ ምንጭ በመጠቀም አገር አፍራሾችና “ዲጂታል ኪስ አውላቂዎች” መሆናቸውን ያረጋግጡልናል።

ይህ ጉዳይ እጅግ ያሳሰበው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በመጋቢት ወር የማኅበራዊ ሚዲያን አጠቃቀም በተመለከተ ለሕዝቡ ማሳሰቢያ አዘል መግለጫ ሰጥቶ ነበር። ያም ሆኖ ጉዳዩ ይበልጡኑ እየተባባሰ እንጂ እየበረደ አልመጣም። የባለሥልጣናትን ንግግር ሳይለፉ ከመንግሥት ሚዲያ በማውረድ (ዳውንሎድ በማድርግ) እና በመቆራረጥ፣ ለበጎ የተሰነዘሩ ሃሳቦችን ስም እየጠሩ እገሌ እገሌን “ነገረው፣ አጠጣው፣ አፈረጠው፣ አዋረደው፣ አስገባለት፣ ዘነጠለው፣…” የሚል የ“ጮኸ” ርዕስ በመስጠት የሪፖርቱን ወይም የንግግሩን ዓላማ በማሳት ወይም ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ ርዕስ በመስጠት ምንጭ ያለውን መረጃ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የመምራት ልምድ ሃይ የሚለው ማጣቱም ሌላው ችግር ነው።

ሰሞኑን ወደተሰራጨ አንድ መረጃ እናምራ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገዳዮች መሪ ነው” የሚለውን ጨምሮ በርካታ የነቀፌታና ጥላቻ አዘል ትችት በዶ/ር ዐቢይ ላይ የሰጡት ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው በማለት ዘ-ሃበሻ በፊትለፊት ገጹ መዘገቡና ይህንኑ ተከትሎ የማኅበራዊ ገጾች ዜናውን ማራባታቸው ቀውስ ፈጥሮ ነበር። ዘ-ሐበሻ “ዜናውን” ያሰራጨው ከሳተናው ድረገጽ ላይ በመጥቀስ ነው። ሁለቱም ድረገጾች “እህትማማች” እንደሆኑ እዚህ ላይ ልብ ይሏል።
ባልተጣራ ምንጭ ዶ/ር ደረጀ በሰነዘሩት ትችት ሳቢያ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው የሚለው ዜና “ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ በዐቢይ አህመድ ከተቀነባበረባቸው የሞት ድግስ መትረፋቸው እየተሰማ ነው። ትናንት እሁድ ጭንብል የለበሱ ገዳዮች በመኪና ደፍጥጠው እንዲገሏቸው የተጠነሰሰው ሴራ የሁለት ጎዳና ተዳዳሪዎችን ህይወት እና የመኪና ግጭቶችን በማስተናገድ ተጠናቋል” በሚል ሳምሶን ያይሉ በሚባሉና በሌሎች የማኅበራዊ ገጽ “አርበኞች” ተሰራጭቶ ነበር።

ዘ-ሐበሻ “ምንጮቼ” ያላቸው ክፍሎች እነዚህ ይሁኑ ሌላ በግልጽ ባይታወቅም፣ ዜናው መሰራጨቱን ተከትሎ በዶ/ሩ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ባልደረቦች ዘንድ ቀላል የማይባል ችግር እንደፈጠረ ለማወቅ ተችሏል።
ይህንን የፈጠራ ዜና ለማሰራጨት የተፈለገበት ልዩ ምክንያት ይፋ ባይሆንም፣ ዜናው አገሪቱ ውስጥ መረጋጋት እንዳይፈጠር ሆን ብለው በጀት መድበው የሚሠሩ አካላት ያደረጉት ለመሆኑ ግን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፤ ጥቂት የማይባሉም ቁጣቸውን ገልጸዋል።
ሃሰተኛ ዜናዎችን እያሳደዱ ከሚያመክኑ ዜጎች መካከል አንዱ የሆነው ኤሊያስ መሠረት የፈጠራው ዜና መሰራጨቱን ተከትሎ ዜናውን እያራገቡ ላሉ፣ በዜናው ለተደናገጡ ወገኖች ምላሽ ይሆን ዘንድ ተጎዱ የተባሉትን ዶ/ር ደረጀ በማነጋገር ትክክለኛውን መረጃ አሰራጭቷል። ይህንን ነበር ያለው፤ “ዶ/ር ደረጄን ቅድም ስለዚህ ዜና ጉዳይ ሳወራቸው (እንዲህ ብለውኛል) “የሚገርምህ ምናለ ቲቪ ላይ ቀርቤ ባላወራሁ ነው ያሰኘኝ። ቤተሰብ እና ጓደኞቼ በጣም ነው የደነገጡት። ይህ ጭካኔ ነው። ሕዝቡ ግን የሃሰት ዜና እነማን እያሰራጩ እንደሆነ በዚሁ ይገንዘብ” ብለውኛል።
ዶ/ር ደረጀ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባሳለፉት ትዕዛዝ መሠረት ማስክ ባጠለቁ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች በመኪና ግድያ ሊፈጸምባቸው እንደነበር ምንጮች ጠቅሶ የዘገበው ድረገጽ ሳተናው ሲሆን እህት “የሙያ አጋሩ” ዘ-ሐበሻ ደግሞ ዜናውን እንዳለ አውርዶታል። ሆኖም ዜናው የውሸት እንደሆነ ይፋ ከተደረገ በኋላ ዘ-ሐበሻ ይህንን ብሎ ነበር፤ “በሳተናውና በዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ በዶ/ር ደረጀ ዘለቀ ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገ የሚለው ዜና በስህተት የተለጠፈ ስለሆነ አንባቢዎቻችንን ስለተደረገው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን” ብሏል። ይሁን እንጂ ዶ/ር ደረጀ ምንም የደረሰባቸው አደጋም ሆነ የአደጋ ሙከራ አለመኖሩን በይቅርታው ሃረግ ውስጥ አላካተተም።
ዜናው የፈጠራ ወይም የሃሰት ሆኖ ሳለ ዘ-ሐበሻ “በስህተት የተለጠፈ” ሲል ስህተቱን በማሳነስና በሌላ ሶስተኛ ወገን እንደተደረገ አድርጎ ማቅረቡ ይቅርታውን ሰባራ እንደሚያደርገው ለሙያው ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ። የተሰራጨውን የሃሰት ዜና ተከትሎ እውነተኛ ቀውስ ቢደርስ፤ ግለሰቡ ጥቃት ደረሰባቸው በሚል የተነሳሳ ኃይል አፀፋ ቢመልስ፤ ወዘተ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው ሚዲያ ማስተባበያውን ሃሰተኛውን ዜና ባሰራጨበት መጠንና ድምጸት ልክ ሊሠራው በተገባ ነበር።

የኢትዮጵያዊያን ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በቅርቡ አትላንታ በተካሄደበት ወቅት የዘ-ሐበሻ አዘጋጅ “ሌት ተቀን እንቅልፉን በመሰዋት መረጃ በመስጠት ተመስግኗል”። አቶ አበበ ባልቻ ሽልማት ያበረከተለት የዘ-ሐበሻ ባለቤት ከተወደሰበት ሥራው አንዱና ትልቅ ተደርጎ የተወሰደው ከሐሰተኛ ዜና ረድፍ የሚመደበው “ሹክሹክታ” የሚለው ዝግጅቱ ነው። ይህ በየማኅበራዊ ገጾች ላይ የሚሰራጨው መረጃ አልባ ሃሜቶችን መሠረት ያደረገ ዝግጅት ለሽልማት የሚያበቃ መሆኑ የአዘጋጅ ኮሚቴ (ፌዴሬሽኑም ካለበት) የሽልማት መፈርት፣ ሽልማቱ ምንን ለማበረታት እንደሆነና ዓላማው ምን እንደሆነ ሽልማቱን ተከትሎ ሊቀርቡ የሚችሉ ጥያቄዎች ናቸው። ወይስ በያዝከው የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ቀጥልበት ማለት ይሆን? (በርግጥ የዶ/ር ደረጀ ሃሰተኛ ዜና ከመውጣቱ በፊት ሽልማቱ መሰጠቱ ግልጽ ነው፤ ሆኖም ይህ የዘ-ሐበሻ ሹክሹክታ ዓምድ በቅርቡ ጋብቻውን የፈጸመ የመብት ተሟጋችን መረጃ ያለባለቤቱ ፈቃድ ከሠርጉ አዘጋጅ በወዳጅነት ስም በመውሰድ ካሰራጨ በኋላ በባለጉዳዩ ተቃውሞ ከዩትዩብ ስለመውረዱን ጎልጉል መረጃ አለው)።
ሆኖም ግን “ሹክሹክታ” በራሱ የሚያሸልም ሆኖ ከሌሎች መቅረቡ፣ በተለይም በሙያው ከገዘፉና ዘመን ተሻጋሪ በሆነው ሥራቸው ትውልድ ሲያስታውሳቸው የሚኖሩ ሥመጥሮች የዚህ ሽልማት ተሳታፊ ሆነው መቅረባቸው፤ የመንግሥት ተወካይ (አምባሳደር) የሆኑትና ከወራት በፊት የጠ/ሚ/ሩ ፕሬስ ኃላፊ የነበሩት ፍጹም አረጋ መገኘታቸው ጉዳዩን ውስብስብ አርድጎታል። ይህ መሥፈርቱ ምን እንደሆነ ያልታወቀ የወዳጅነት ሙገሳና ሽልማት በተመለከተ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሌሎች የሚልኩልን ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን። ዘ ሃበሻም የሚለው ካለ እናስተናግዳለን። እዚህ ላይ ይህንን ያነሳነው ለማሳያ እንዲሆን እንጂ ሌሎች በርካታ ችግሮች በማወቅም ይሁን ከላይ እንደተባለው ሆን ተብሎ በተለያዩ ሚዲያ እንደሚሰራጭ እሙን ነው።

ሃሰተኛ ዜናን ለመከላከልና ሕዝብን ከዚህ ሱስ ነጻ ለማውጣት የሚተጉ ባለሙያዎች በየጊዜው እንደ ሰደድ እሣት እየተሰራጨ የመጣውን ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚከተሉትን ሀሳቦች ይለግሳሉ። እነዚህ ነጥቦች በቅርቡ (ጁላይ 18፤2019) በሳይኮሎጂ ቱዴይ ላይ የወጣ ነው፤
· ሁሉንም መጠራጠር፤ የትኛውንም መረጃ ቢሆን 100 እርግጠኛ ነው ብሎ አለመቀበል፤ መጠን ያላለፈ ጥርጥር ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም
· ምንጩን ማጣራት፤ የመረጃው ባለቤት ማን እንደሆነ መጠየቅ፣ እንደዚህ ዓይነት መረጃ ለማውጣት የተፈለገበትን ምክንያት ለማወቅ መሞከር፣ ለምሳሌ ስለ ህወሓት የሚያጠና አይጋ ፎረም ላይ ስለ ህወሓት ቅድስና የተጻፈውን እንደ ማስረጃ አድርጎ መውሰድ ከንቱነት ነው
· ጉግል አምላክ አይደለም፤ ጉግል ላይ ተፈላጊ መረጃ ማግኘት ይቻላል፤ ሆኖም በጉግል የሚጎለጎል ሁሉ ሙሉ ተዓማኒ መረጃ አድርጎ መውሰድ የዋኅነት ነው
· ሰከን ማለት፤ የዜና በተለይ የሃሰተኛና ሐሜታዊ ዜና ዋና ባህርዩ ፍጥነት ነው፤ ሳያመዛዝኑ መስማት ወይም ማንበብና ለሌላው ማስተላለፍ፤ ስለዚህ የትኛውንም መረጃ ወደሌላ ከማስተላለፍ በፊት በሰከነ መንፈስ ማንበብና ማሰላሰል
· ሌሎችስ ምን ይላሉ ብሎ መጠየቅ፤ አንድ መረጃ በአንድ ሚዲያ ከወጣ በኋላ ሌሎች የሚዲያ አውታሮች ስለ መረጃው ወይም በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ምን እንዳሉ ማጣራት
· በአስተያየትና በዜና፣ በሐሜት አዘል መረጃና በእውነተኛ፣ በግምታዊ አስተሳሰብና መሬት በረገጠ አሠራር መካከል ያለውን ልዩነት በቅድሚያ መረዳት፤ አስተያየት፣ ወሬ፣ ሹክሹክታ፣ ሐሜት፣ መላምት፣ ወዘተ ዜና አይደለም
· ርዕስ በማንበብ ብቻ አለመወሰን፤ በርካታ ሰዎች ዝርዝር መረጃውን እስከመጨረሻው ድረስ ሳይሆን የሚያነቡት ርዕሱን ብቻ በማየት የራሳቸው ድምዳሜ ላይ ነው የሚደርሱት፤ ይህንን የሚውቁ ጮሌዎች ርዕሱን በማጦዝ ቀልብ በመሳብ የሃሰት መረጃቸውን እንደሚያሰራጩ መረዳት

· የወሬ (የዜና) ሱሰኛ አለመሆን፤ በርካታዎች “ዛሬ ደግሞ ምን አዲስ ነገር አለ” በማለት ወሬ ፍለጋ በማኅበራዊ ገጾች ላይ ጊዜያቸውን ስለሚያጠፉ ይህንን የሚውቁ ብልጦች የመረጃ ዶፍ በማዝነብ አሰሱንም ገሰሱንም ስለሚያወርዱባቸው ሰለባ ለመሆን የተጋለጡ ናቸው፤ በ2017ዓም Nature Human Behaviour ያወጣው ጥናት እንደሚጠቁመው ወሬ አነፍናፊዎችና “ዛሬ ምን አዲስ ነገር አለ” ባዮች እንደ ሰደድ እሣት ለሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎች ተጋላጭና የቅድሚያ ተጠቂዎች ናቸው፤ እነዚህን ጠቃሚ ምክሮች ብቻ መከተል ከበርካታ ችግር ራስንና አገርን ለመታደግ ያበቃል። ከሁሉም በላይ ምንም ይሁን ምን ቢያንስ ቢያንስ ጊዜ ወስዶ ሙሉውን ማንበብ ራስንና ሌሎች ከአደጋ ይጠብቃልና ልብ እንበል።
አገራችን በተለያየ ጽንፍ እየተናጠች ነው። አገር በማፍረስ ጉዳይ ላይ የተጠመዱ ወገኖች ጥቂት የማይባለውን የመረጃ ተጠቃሚ በሃሰት መረጃ እያወዛገቡት ይገኛል። ይህንኑ መረጃ ተቀብለው በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም ለግል የኢንተርኔት ገቢ ሲባል በሰበር ዜና ስም እያሰራጩ ያሉት ዝም ማለት አገር ለማፍረስ ቀንተሌት ከሚተጉት ተለይተው ሊታዩ አይችሉም። ስለዚህ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሕዝብን የመምከርና የማነጽ ኃላፊነት አለባቸው። ሚዲያውም “ወሬ” ከማጦዝ ሰከን ብሎ ይህ ሁሉ መሆን የሚችለው አገር ስትኖር እንደሆነ መገንዘብ ይገባዋል። አገር ከፈረሰች በኋላ “ሰበርም” ሆነ “ትኩስ” ዜና ወይም “እጃችን የገባ ምሥጢርም” ሆነ “ሹክሹክታ” ዋጋ አይኖራቸውም፤ ለፈረሰ አገር ዜናም ሆነ የሃሜት ዜና ወይም ሹክሹክታ (ጎሲፕ) ማንም ጆሮ አይሰጥም። እናም ከ“ሻሞ” እንጠበቅ።
ለተቆርቋሪ ዜጎች – አገራችን በዚህ መልኩ ሤረኞች መጥነውና ደቁሰው ከማኅበራዊው፣ ከኢኮኖሚው፣ ከፖለቲካው፣ ከመዝናኛው ጎዳይ የሃሰት መርዝ እያመረቱ አገር አልባ ሊያደርጉን ሲባቱ አገር ወዳዶች ስለምን ዝም ትላላቹህ? የእናነት ዝምታ ለሴረኞች የሐሰተኛ መረጃ ወረርሺኝ ዳርጎናልና ድምጻችሁን እንድታሰሙ። በሚበጀውና በሚያመቻቹህ መንገድ ሤራውን ለማክሸፍ ያለ ቀስቃሽ እንድትተጉ በመጪው ትውልድና በአገራችን ስም እንማጸናለን።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
የሐሰት ዜና የሚያስተላልፈው ጋጤኛ ሆነ ፅሁፉን የፈቀደው Editor in Chief ተጠያቂ መሆን አለባቸው። የጋጤኛነትን professionalism ያልጠበቀ የጋዜጠኝነት ሙያ የእውነተኛውን ጋዜጠኞች አይወክልም ።በነዚህ ተራ ጋዜጠኞች የጋዜጠኞች ማህበር ቢኖር ከስራቸው እንዲታገዱ ማድረግ ይችል ነበረ። የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ተቋቁሞ የጋጠኞች Work ethics በማርቀቅ በአገሪቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ወጥ መመሪያ ማውጣት እና ለጥሩ ጋዜጠኞች እውቅና መስጠት ብልሹን ጋዜጠኛ ደግሞ መገድ መቻል አለባቸው።
What can I say ? blessed u !!
በቅድሚያ ጎልጉልን ወሸኔ ለሆነው ጥቃሚ ምክር ያዘለ ጽሁፍ አመሰግናለሁ። ጊዜው መሸ እና ተረሳኝ እንጂ የሃገራችን ባህታዊያኖች ስለ ዓለም ፍጻሜ ተጠይቀው መልስ ሲሰጡ ልጅ ሆኜ ትዝ ይለኛል። የዋልድባው መናኝ በመባል ይታወቁ የነበሩት እንዲህ በማለት መልስ መስጠታቸውን አስታውሳለሁ። “የዓለም ፍጻሜ አንተ ስትሞት ነው” ሲሉ ሌላው ደግሞ ብዙ ተከታይና አድናቂ የነበራቸው “ዓለም የምትፈታው በእሳትም በውሃም አይደለም በወሬ ነው” ማለታቸው ትዝ ይለኛል። ይህ ያለንበት ዘመን እጅግ የተወሳሰበ የውሸት የወሬ አውታርን የተላበሰ ነው። ድሮ በሃሜትም በሌላም ወሬው ከስፍራ ስፍራ ለመድረስ ቀናትን ይፈጅ ነበር። እንሆ አሁን አዲስ አበባ ላይ የሆነው ወይም በፈጠራ ወሬ ቀለም የተቀባው ለዓለም ሁሉ በኢንተርኔት አገልግሎት በኩል ይነዛና የሰው ቤት ያምሳል፤ እንቅልፍ ይነሳል፤ ሰውን ያጨቃጭቃል አልፎ ተርፎ ግጭት በሃገርና በውጭ ያቀጣጥላል። ሁሉ ሰበር ዜና አቅራቢ በሆነበት በዚህ ህመምተኛ አለም ከሳሽና ፍርድ ሰጪው የጅምላ አስተሳሰብ በመሆኑ ፍትህ እና ርትዕ እየተገፉ ለወገኔ፤ ለዘሬ፤ ለቋንቋዬ ለሃይማኖቴ ወ.ዘ. ተ በሚል ወልጋዳ የፓለቲካ እይታ የሰው ልጅ ይታመሳል።
የተወናበደ ወሬ ለፓለቲከኞች ተቆፍሮ የወጣ ወርቅ ነው። መልካም አንጥረኛና ባለሙያ ያን ወርቅ አሳምሮ ጌጣ ጌጥ እንደሚሰራው ሁሉ የፈጠራ ወሬም እንዲሁ ለጀሮና ለአይን እንዲመች ተደርጎ ይሰራል፤ የዋህና ያልተረዳውን ህዝብ ያስበረግጋል፤ ያጋጫል። አላማው እውነተኛው ነገር እንዳይታወቅ ማድረግ ስለሆነ ሁሌም ማምከኛ ዜዴዎችን ለጀሮ ያደርሳል። ልብ ያለው በሶሻል ሚዲያና በሌሎችም አንቴና ተከል የዜና ማሰራጫዎች የሚተላለፈውን አይቶና አዳምጦ የዜናውን ምንጭ ተረድቶ ከሰፈር ወሬ ያላለፈውንና መረጃ አልባ የሆነውን ቁራንቁር ነገር ቆሻሻ መሆኑን መረዳት ይገባዋል። መንግሥትም የውሸት ወሬ በውጭና በሃገር የሚያናፍሱትን ሁሉ ህግ በማበጀት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለሚያስተላልፉት ወሬ መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ አለበት። ያለበለዚያ ሞተ፤ ተነሳ፤ ታሰረ፤ ሃገር ጥሎ ኮበለለ፤ ወያኔና የአማራ አመራሮች ተጋጩ ወ.ዘ.ተ በማለት ህዝባችንን ወደ ከፋ መከራ ሊያስገቡት የሚከጅሉ የወሬ አናፋሾች ሁሉ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል። የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና የማህበራዊ ድህረ ገጽ ባለቤቶች በየ ድህረ ገጾቻቸው ላይ ለሚያርፉ ከፋፋይና አባይ፤ ህዝብ አዋኪ ጽሁፎችና ቪዲዮዎች ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል እላለሁ።
Those engaging in disinformation are
aligned with Tplf. The rest are after
making money. The solution?:
Unsubscribe. Report. Start a group
blog to fight back.