ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ምንም ጊዜ የማይቀየር፣ ሊስተባበል የማይችልና ልዩ የሆነ መለያ አላቸው። ይህም ለክህደትና ለመሸጥ፣ በኢትዮጵያውያን አገላለጽ ለባንዳነት የተጋለጡ ወይም መደምደሚያቸው ባንዳነት ነው። ሌሎቹን እንተዋቸውና በአገራችን ዋና ምስክር የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግን) ማንሳት ይበቃል። ጥሩም መከራከሪያ የሚቀርብበት የዘመኑ አፍላ ታሪክ ነው።
ቃለ ምልልሱ ከተካሄደ ቆይቷል። ሰሞኑን ግን የሩሲያ መንግሥት ቲቪ በድጋሚ ሲያሳየው ነበር። ጋዜጠኛው ቭላዲሚር ፑቲንን ይጠይቃል። ይህን የቆየ ቃለ መጠይቅ ማስተላለፍ የተፈለገው በቀድሞ ወጥ ቀቃይ የሚመራውና አሁን ቫግነር የተባለው ኢመደበኛ አደረጃጀት ከሩስያ መከላከያ ጋር የገባበትን መፈታተን ተከትሎ ነው።
ጥያቄ – ይቅርታ ታደርጋለህ?
ፑቲን – አዎ፤ ግን ለሁሉም አይደለም፤
ጥያቄ – ይቅር ለማለት የማይቻለው እንዴት ያለው ነው?
ፑቲን – ክህደት፣ የአገር ክህደት …
በቫግነርና በቀላቢው የሩስያ መንግሥት መካከል ተፈጠረ የተባለው ልዩነት በየቀኑ፣ ሰዓታትና ደቂቃዎች ውስጥ የሚቀያየር መረጃ የሚሰማበት በመሆኑ ከላይ እንደተገለጸው ስለ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ባህርይ ለማሳየትና እንደ አገር ጥንቃቄ ለመውሰድ በሚያተኩረው አሳብ ላይ ትኩረት ማድረግ የጽሁፉን ዓላማ ለመረዳት እንደሚበጀ አስቀድመን ለማሳወቅ እንወዳለን።
ኢመደበኛው ትህነግ
ባንዳው ትህነግ ለመሸጥ፣ ለመለወጥ፣ ቅጥረኛ ለመሆን፣ ለባንዳነትና ከሃጂነት ራሱን ያበቃ የትግራይ ህዝብ ላይ የተንጠለጠለ ድርጅት ሲጠነሰስ፣ ፈጣሪዎቹ ሲፈጥሩት፣ የኢሳያስ አፈወርቂን በረከት ሲቀበል፣ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራና ተላላኪዎች ድጋፍ መንግሥት ሲሆን፣ መንግሥት ሆኖ በሚጸየፋትና እንድትፈርስ አድርጎ በገነባት አገር ስም አፍሪካን ሲመራ፣ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ሲቀመጥ … ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የሚል ስም ላይ ተክሎ ከተሸከመው መርዝ ጋር የመረቀዘው ትህነግ የኢመደበኛ አደረጃጀት ማሳያና ማስተማሪያ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ መደርደር አያስፈልግም።
ለውጡን ተከትሎ ወደ ትግራይ ከፈረጠጠ በኋላ እልፍ አዕላፍ ወታደር መልምሎ በልዩ ኃይል ስም ቀድሞ ከነበረው ኃይል በላይ በኢመደበኛ ሠራዊት ክንዱን አሳበጠ። እየዛተና እያሴረ ቆይቶ መከላከያ ሠራዊታችንን ቀደም ሲል በዘረጋው “ጠቅልል” የተሰኘ መዋቅሩ አማካይነት ድንገት አጠቃ። ኢመደበኛ አደረጃጀቱን ተጠቅሞ በክህደት የአገር መከላከያን ማረዱንና መጨፍጨፉን በኩራት አስታወቀ። በደቂቃዎች ውስጥ መከላከያን ማረዱን ዓይኑን በጨው አጥቦ ተረከልን። ኢትዮጵያ ያላትን አሟጣ የትግራይ ክልልን ለመጠበቅ የገዛችውን መሳሪያ ዘረፈ። አስዘረፈ። ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ የመከላከያ አቅሟን አነካከተው።
ይህን ሲያደርግ ግብጽን ጨምሮ ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የክህደት ውል ፈርሞ እንደነበር የዛሬው የክልሉ መሪ አቶ ጌታቸው ደጋግመው ነግረውናል። በዱቄትና ስንዴ ስም መሳሪያ፣ በአውሮፕላን ትጥቅ ሲያጓጉዙ የነበሩት ጌቶቹ ሊያድኑት ያልቻለው ትህነግ በህዝብ ቁጣና “እምቢ” ባይነት እንዳይነሳ ሆኖ ተደቆሰ። እንዳያንሰራራ ሆኖ ነተበ። ያ ሁሉ ጥጋቡ እና ኢመደበኛ ሠራዊቱ አመድ ለብሶ “አድኑኝ” ዘፈነ።
ይህ ሻዕቢያ ሲወልደው ጀምሮ ባንዳ የነበረ ድርጅት አማራና አፋርን ወርሮ ዘርፈ። አወደማቸው። ገደላቸው። እንሳሳና ዛፍ ሳይቀር ጨፈጨፈ። እጃቸውን የሰጡ እንደመሰከሩት “ሂዱና አማራን ውረሩ፣ ዝረፉ፣ የቻላችሁትን ሁሉ ውሰዱ” ተብለው ነበር የተባሉትን ለማድረግ ወደ ወረራ የገቡት። ለሰሚም ለተመላካችም በሚዘገንን መልኩ የትግራይን ህዝብ አስጨርሶ ዛሬም ሃፍረት የማይሰማው ኢመደበኛው ትህነግ የባንዳነት ማሳያ ስለመሆኑ ይህን መጥቀሱ ይበቃል።
የአገራችን ኢመደበኞች
ወደ አገራችን ስንመለስ በየክልሉ የተመሰረቱት ህገመንግሥቱ የማይደግፋቸው የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች እንዲመክኑ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ምሁራን፣ ፓርቲዎች ወዘተ ሲወተውቱ እንደነበር ይታወሳል። ባለፉት አራት ዓመታት ትህነግን እየመከተ ሰፊ መከላከያ የገነባው መንግሥት “አሁን ጊዜው ደርሷል” በሚል ኢመደበኛ የሚባሉ የሰፈር አደረጃጀቶችና ልዩ ኃይሎች ከስመው ልክ ፑቲን እንዳቀረቡት ሶስት አማራጮችን በማዘጋጀት ወደ ዋናው ዕዝ ቋት እንዲገቡ ሲታወጅ እምቢታው ከምን የመነጨ እንደሆነ በርጋታ ለማስላት ይህ አጋጣሚ ጥሩ መማሪያ ይሆናል።
ሻዕቢያ ከተጸነሰሰበት ጊዜ አንስቶ ትህነግን አደራጀና ላከብን። ትህነግን ገዝቶ፣ ከታሪካዊ ጠላቶቻችንና ከወቅቱ የርዕዮተ ዓለም መዛነፍ ጋር ተዳምሮ ባገኘው ወርቃማ አጋጣሚ የማንፈልገውን መንግሥት ጫነብን፣ ወይም አስጫነብን። በፈጠራቸው ተላላኪዎቹ አንገታችንን ቆርጦ ባህር ዓልባ ምድር አደረገን። ባንዶች ሸጡን። ፍጥረታቸው ለዚሁ ነበርና የተፈጠሩበትን ዓላማ አሳኩ። ውላቸው ሲያበቃ ….
ሻዕቢያ ከትህነግ ጋር ሲባላ ኦነግን ማሰልጠን ጀመረ። የትግራይ አማጺም መለመለ። ለውጡን ተከትሎ የኦነግን ሰራዊት በትግራይና በኡጋንዳ ላከብን። አሁን ደግሞ ከነማን ጋር ተሻርኮ እንደሆነ ጊዜ ጠብቆ ይፋ የሚሆን ቢሆንም ለመሸጥ የሚመቹ ሚሊሻዎችን እያስለጠነ እንዳለ፣ አስለጥኖ እንደሚልክ ይታወቃል።
እዚህም እዚያም ህጋዊ አደረጃጀትን በመቃወም፣ የሚደረጉት ፍትጊያዎችና የተገዙ ሚዲያዎች ጩኸት፣ ከሸኔ ጋር በመናበብ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና አገሪቱን የማወክ፣ ንጹሃንን የመግደል፣ የማፈንና የማፈናቀል ተግባር ራሱ መንግሥት ጉያው ውስጥ ካሉ ባንዶች ጋር ተዳምሮ ሁሉም የሌሎች ዓላማ አስፈጻሚ ናቸውና ረጋ ብሎ ማሰብና መላ መፈለግ ግድ ነው።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ጦራቸው እንደተፈረካከሰ ተደርጎ ሚዲያው ዜናውን ሲያጮህ የሚታወሰን ነገር ቢኖር ትህነግ በተላላኪነት ኢትዮጵያን ሲያፈርስና ሲወጋ እኛ ላይ ሲዘንብ የነበረውን የተቀነባበረ የሚዲያ ዘመቻ ነው። ዛሬም የኢትዮጵያን መከላከያ ዳግም ለመበተንና አገሪቱን የተላላኪዎች መፈንጫ ለማድረግ ቅንጣቢ ለቃሚ ሚዲያዎች የሚያካሂዱት ዘመቻ የባንዳዎቹ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆናቸውን ነው።
ኢመደበኛ አደረጃጀቶች እግራቸው የገባበት ቦታ ሁሉ አገር ፈርሷል። ሕዝብ ተበትኗል። እልቂቱ ተነገሮ የሚያልቅ አይደለም። እናም ይህን መፍቀድ ሌላ የመን፣ ሌላ ሊቢያ፣ ሌላ ሲሪያ፣ ሌላ ኢራቅ፣ ሌላ አፍጋኒስታን፣ ሌላ ሶማሊያ ከመሆን ውጭ ሌላ ውጤት አይኖረውም። የሱዳኑ ማፊያ ደግሞ የሰሞኑ ማሳያ ነው።
የሱዳኑ ኢመደበኛ ጡንቸኛ – የዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ቡድን
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ (አር. ኤስ. ኤፍ.) ኃይል ዋና አዛዥ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ እስከ አፍንጫው የታጠቀው ኃይላቸው ሱዳንን አንድ ቀን ወደ ዓመድነት ለመቀየር የተቀመጠ ኢመደበኛ አደረጃጀት ነበር። ይህ ከቀለም ጋር የተጣላ መሪ ኃይሉን ወደ ህጋዊ መስመር እንዲያስገባ ሲጠየቅ “እንዴት ተደርጎ” በሚል አሁን እንደሚሰማውና እንደሚታየው ሱዳንን የደም መሬት አድርጓታል።
ጉዳዩ የተነሳው ሱዳንን እየመሩ ያሉት ጄኔራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃንን በአግባቡ ወደ ሥልጣን መጥተዋል፣ ወይም ደግሞ የሚደገፉ ናቸው ለማለት ሳይሆን ኢመደበኛ አደረጃጀት ሱዳንን እንዴት እንደበላት ለማሳየት ነው።
ዛሬ በሱዳን ግጭት ከሶስት ሺህ በላይ ንጹሃን ተገድለዋል። በአገር ውስጥ ብቻ ከ2.2 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ተፈናቅለዋል። 25 ሚሊዮን ህዝብ ዕለታዊ ዕርዳታ ፈላጊ ሆኗል። ዳርፉር የቆሰሉ ወደ ህክምና መሄድ አልቻሉም። በዳርፉር አስከሬን በየስፍራው የሚያነሳው አጥቷል … ይህ ሁሉ የሆነው በኢመደበኛ መንገድ ጡንቻቸውን ያፈረጠመውና ከሚደግፉት የማዕድን ነጋዴዎች ጋር በመሆን እንዴት ወደ ህጋዊ መስመር እገባለሁ በሚል ባፈነገጠ ማፍያ አማካይነት ነው። ትህነግ ጡንቻውን አሳብጦ፣ እስከ አፍንጫው ታጥቆ ወረራ ሲፈጸም የሞቱትን፣ የተፈናቀሉትን፣ የወደመውን ማሰብ እዚህ ላይ ልብ ይሏል።
አሁን ምን እየሆነ ነው?
አሁንም በአገራችን ኦነግም ይሁን ሸኔ ይሁን ህጋዊ መስመርን አንቀበልም ካሉ ታጣቂዎች ጀርባ ልዩ ዓላማ ያላቸው የሚያሰለጥኗቸው፣ የሚያስታጥቋቸው፣ በጎረቤት አገርና በየጫካው እያስታጠቁ የሚያፈሷቸው፣ በጀት የሚበጅቱላቸው፣ እንዳሻቸው የሚሾፍሯቸው፣ ለባንዳነትና ክህደት ያመቻቿቸው ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ናቸው።
እዚህም እዚያም የፈሉትና ሲሻቸው በብሄር፣ ሲሻቸው በኢትዮጵያ ስም የሚከለሉት የአገራችን ኢመደበኛ አደረጃጀቶች የሚያሳዩት ምልክትና እያከናወኑ ያሉት ሁሉ በሌሎች አገሮች በኢመደበኛነት ተደራጅተው አገራቸውን ከበሉ፣ ህዝባቸውን ለመከራና ዕልቂት ከዳረጉ፣ ንብረት ካደቀቁ፣ ንጹሃንን በማፈን ከሚያሰቃዩ፣ በዕገታ ሃብት ከሚያሰባስቡ፣ የመንግሥትና የግለሰብ ንብረትን ከሚዘርፉት የሚለዩት በዕድሜና በስያሜ ካልሆነ ልዩነት የለውም።
እነሱኑ ሌት ከቀን በማጀገን የሚያላዝኑትም እንጥፍጣፊ ለቃሚዎች “ኢመደበኛ አደረጃጀት ወይም ሞት” የሚሉበት ምክንያትም አገሪቱ የጎበዝ አለቃ መፈንጫ እንድትሆንና ተንኮታኩታ እንድትወድቅ ስለተከፈላቸው ብቻ እንደሆነ ከሌሎቹ ተመሳሳይ አደረጃጀቶች ልምድ ያየነው ሃቅ ነው።
ከላይ እንዳልነው ኢመደበኛ አደረጃጀት ሲባል ከፍጥረቱ እስከሞቱ ታሪኩ የሚደመደመው ለጥቅም በመሸጥ፣ በባንዳነትና በከሃጂነት ነው። ለምን? ቢባል ሲፈጠር ጀምሮ አፈጣጠሩ ይህን እንዲሆን ታስቦ በመሆኑ ነው። በኢመደበኛነት የተደራጁ ተላላኪዎች ጡንቻቸውን አሳድገው ሲያበቁ የተቀጠሩበትን ዓላማ ያስፈጽማሉ። ይኸው ፈርሰው፣ ተበትነው፣ ወደ አፈርነት ተቀይረው እየከሰሙ ያሉ አገሮች በቂ ምስክር ናቸው። የመን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ የዛሬዋ ሱዳን ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።
ይቭጌኒ ፕሪጎዢን፡ አገር የካደ ወይስ አገር የታደገ የኢመደበኛ ኃይል መሪ?
ፕሪጎዢን የቀድሞ ታሪካቸው እንደሚመለክተው በሌብነት ተይዘው ለዓመታት ታስረው የነበሩና ከዚያ በኋላ በምግብ ዝግጅት የክሬምሊን ዋና ምግብ ሠሪ (ሼፍ) የነበሩ፤ ለነጆርጅ ደብሊው ቡሽ ሳይቀር በሞስኮ ለተደረገላቸው ግብዣ መስተንግዶ ያደረጉ፤ የፑቲን የቅርብ ወዳጅና ታማኝ፤ በሃብትም በልጽገው ስመጥር የሆኑ ናቸው። የቫግነር ቡድናቸውም ለፑቲን ባለውለታና በዩክሬይን ብዙ ሥራ የሠራ ነው። በእርግጥ ፕሪጎዢን ከድተዋል?
በምዕራቡ ሚዲያ “መፈንቅለ መንግሥት”፤ የፕሬዚዳንት ለውጥ፤ … እየተባለ ብዙ ሲወራለት የነበረው የቫግነር ቡድን ግስጋሴ ባላንጣ ሆነው በተሳሉት ፑቲንና ፕሪጎዢን መካከል ግን ይህ ነው የሚባል እሰጥ አገባ አልተሰማም። ፑቲን “ተክደናል” ብለው ሲናገሩ አንድ ጊዜም እንኳን የፕሪጎዢንን ስም አልጠሩም። ፕሪጎዢንም በደል ደርሶብናል፤ ወደ ሞስኮ እየገሰገስን ነው ባሉበት ጊዜ ፑቲንን በስም ጠርተው አንዴ እንኳን አልወቀሱም።
ከዚህ ሌላ ግስጋሴው ሲገታ ፕሪጎዢን በቤላሩስ ፕሬዚዳንት አማካኝነት መላ እየተፈለገ ነው በማለት ከተናገሩ በኋላ እርሳቸው ወደ ቤላሩስ ሄደው እንዲኖሩ እና የዓመጽ ግስጋሴው እንዲገታ መደረጉ ይፋ ሆነ። ይህ ሲሆን ከሩሲያ በአጸፋው የተሰማው ፕሪጎዢን በምንም ዓይነት ወንጀል እንደማይጠየቁ፤ የቫግነር ቡድን ወታደሮችም በሰላም የሩሲያን መከላከያ ኃይል እንዲቀላቀሉ ያካተተ ሶስት አማራጭ ቀርቦ ነገሩ መቋጨቱ መሆኑ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ውሳኔ ነበር።
ያለፈው ሁለት ሳምንት መጨረሻ በምዕራቡ ዓለምና በሩሲያ መካከል የተከሰተው ውዝግብ እስካሁን ይህ ነው የሚባል መሬት የወረደ ትንታኔ ሊሰጥበት ያልቻለ ምሥጢራዊ ብቻ ሳይሆን ግራ አጋቢ ፈጣን ትዕይንት ሆኖ ነው ያለፈው፡፡ ከትዕይንቱ በፊት ግን ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የራሺያና የዩክሬይን ጦርነት ጋር ተያይዞ ከወደ ፔንታጎን የተሰማ ዜና ነበር፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ሳብሪና ሲንግ ፔንታጎን በሒሳብ ስህተት 6.2 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬይን ጦርነት በሚል መውሰዱን ይፋ አደረጉ፡፡ ይህ የተከሰተው የዛሬ ሳምንት ነበር፡፡ ቃል አቀባይዋ ቀለል አድርገው ሲናገሩ ያሉት፤ የጦር መሣሪያ ዋጋ ስናሰላ ባለፈው (2022) 2.6 ቢሊዮን ዶላር፣ በዚህ ዓመት (2023) ደግሞ 3.6 ቢሊዮን ዶላር በትርፍ ደምረን ነው፡፡ ገንዘቡንም ወደ ግምጃ ቤት ቋት እንመልሳለን ሳይሆን ያሉት ዩክሬይን በሩሲያ ላይ ለምታደርገው መልሶ ማጥቃት ዘመቻ “አስፈላጊ ነው ለምንለው ጉዳይ እናውለዋለን” ነበር ያሉት፡፡
“ክህደትን ይቅር አልልም” የሚሉት ፑቲን በፕሪጎዢን የፈጸሙባቸውን ታላቅ ክህደት እንዴት “ይቅር” አሉ? እንዲያውም አንድ የፓርላማ አባላት “ፕሪጎዢን በአደባባይ መረሸን አለባቸው” እያሉ ሲናገሩ ጠላቶቻቸውን በመርዝም ይሁን በሌላ ለማጥፋት ምህረት የሌላቸው ፑቲን እንዴት ለፕሪጎዢን ሲሆን ብጹዕ ወቅዱስ ሆኑ? የቤላሩስ ፕሬዚዳንት የፑቲን ቀኝ እጅ እንደመሆናቸው በፑቲን ላይ የመንግሥት ግልበጣ ሞክረዋል ተብሎ በምዕራቡ ሚዲያ የተዘፈነላቸው ፕሪጎዢን እንዴት ሆኖ ነው ቤላሩስ (ሌላዋ ሩሲያ) ጥገኝነት ሲሰጣቸው “እሺ” ብለው የሚቀበሉት? ለመሞት ወይስ ለመኖር? ወይስ የዕድሜ ልክ ሰላይ የሆኑት ፑቲን ከወዳጃቸው ፕሪጎዢን ጋር የቀመሩት የ6.2 ቢሊዮን ዶላር ሤራ ይኖር ይሆን? በእኛው አገር ቋንቋ እነ አሜሪካ በፑቲንና በፕሪጎዢን ምሥጢራዊ ዕቅድ የ6.2 ሚሊዮን ዶላር ሿ ሿ ተሠርተው ይሆን?!
የአሜሪካ ዜግነት ያላትና ሩሲያ ተወልዳ ያደገችው፤ በአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ እንዲሁም በፔንታጎን ወታደራዊ ስለላ ሥራ ላይ ተሰማርታ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለችው ረቤካ ኮፍለር “ይህ ፑቲንና ፕሪጎዢን የቀመሩት ድራማ ነው” የምትለው ለዚህ ይሆን? ይህቺው ሴት ፎክስ ኒውስ ላይ ቀርባ “የእኔ የስለላ ትንታኔ እንደሚጠቁመው ይህ ፑቲንና ፕሪጎዢን የተወኑት ዓይነተኛ የሆነ የውሸት ሠንደቅ ዘመቻ (false flag operation) ነው። ፕሪጎዢን ደደብ አይደለም፤ የቀድሞ ወንጀለኛና በጣም ጎበዝ ሰው ነው፤ ከእስር ቤት ሲወጣ ሕይወቱን ከሆት ዶግ ሻጭነት በበርካታ ሚሊዮን ዶላር ወደ ሚንቀሳቀስ የምግብ አቅራቢ ድርጅት ባለቤትነት የተቀየረ፤ ለፑቲን እና ለክሬምሊን ምግብ የሚያቀርብ ሰው ነው” ስትል በሙያዋ መነጥር ጉዳዩን ያየችበትን አግባብ ልክ እንደ እኛ “ሿሿ” የሚለውን ቃል ባትጠቀምም አመሳስላ በድራማ ስም ስላዋለች።
“ሃምሳ ሺህ ሠራዊት በዩክሬይን የሚመራ እንዲህ ያለው ሰው ምንድነው ያደረገው?” ስትል ሬቤካ ትጠይቃለች። በድንገት ወደ ሞስኮ እየገሰገሰ ይሄድ የነበረውን ሠራዊቱን አስቁሞ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ስምምነት ላይ በመድረስ ጦሩን መለሰ? በማለት ሬቤካ ኮፍለር ዳግም ትጠይቃለች። አስከትላም “ይሄ የተቀነባበረ ሤራ ነው፤ ፑቲን የምዕራቡ ዓለም እየተዳከመ ነው እንዲለው ይፈልጋል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ጦሩ እየከዳው ነው፤ እንዲያውም ዓመጽ እየተነሳበት እንዲባልለት ይፈልጋል። ከዚያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፤ ሠራዊት ይመለምላል፤ ኃይሉን ያስተባብርና እንደገና መልሶ ማጥቃት ያደርጋል፤ ከዚህ ሌላ ይህንን ተከትሎ የወንጀል ሬኮርድ ያለባቸው ሳይቀሩ መከላከያን እንዲቀላቀሉ ፑቲን ትዕዛዝ አስተላልፏል” በማለት የምልከታዋን ድምዳሜ ትሰጣለች።
ይህ ሁሉ ስለ ፑቲን የሚናገረው ብዙ ነገር አለ። እንደ ኮፍለር ትንታኔ ከሆነ ይህንን ክስተት ተጠቅሞ ፑቲን መከላከያውን ሊያጸዳ እንደሚችል ይነገራል። የመከላከያ ሚኒስትሩን ሰርጊዬ ሾይጉን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የወታደር መሪዎች ይህንን ክስተት ሰበብ በማድረግ ከሥልጣናቸው ሊወገዱ ይችላሉ። ከዚህ ሲያልፍ የቫግነር ቡድን መከላከያን መቀላቀሉ ፑቲንን ኃይል እንዲያስተባርና ተጠናክሮ እንደሚያጠቃ የሚረዳው እንደሆነም አመልክታለች።
መላ ምቱ ብዙ ነው። ሩሲያን ተቆጣጥሮ አዲስ ፕሬዚዳንት ይሾማሉ ተብለው የተነገረላቸው የቫግነር መሪ ቤላሩስ ከትመው ጦራቸው የመሳሪያ ርክክብ ሲያደርግ ታይቷል። ወደ ቤላሩስ የገባው ቀሪው የቫግነር ኃይል ደግሞ ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ሊሸመጥጥ እንደሚችል የፍርሃቻ ዜና ከኔቶ ዋና ጸሃፊ ተሰምቷል። ከዚህ ሌላ ከቤላሩስ ጋር ድንበር የሚጋሩት ፖላንድና ሉትዌኒያ የኔቶ አባል አገራት እንደመሆናቸው የቫግነር ወታራዊ ቡድን በቅርብ ርቀት መከሰቱ ኔቶ አገራቱን ተጠቅሞ በሩሲያ ላይ ሊፈጽም የሚፈልገውን የሚገታ ደፋር አካሄድ ነው ተብሏል። ይህንኑ የኔቶን ግስጋሴ ለመግታት ታሳቢ ባያደረገ ውሳኔ ፑቲን ለቤላሩሱ ፕሬዚዳንት ታክቲካል የኑክሊየር መሣሪያ ማስታጠቃቸው አብሮ የሚጠቀስ ነው።
ፑቲን የቫግነር ኃይል በመከላከያ ዕዝ ስር እንዲሆን በዋናነት ያሰቡበትና የወሰኑበትን ቁልፍ ምክንያት እንዲህ ነው ብለው የገለጹ ባይኖሩም የተሞዳሞዱ የጦር መኮንኖች መኖራቸው ግን እየተሰማ ነው። ሁሉም ፋኖ አገር ወዳድና ላገሩ ሟች እንዳልሆነው ሁሉ ከቫግነር ግሩፕም ለምዕራቡ ዓለም ያጎበደዱ ከሃዲዎች እንደሚኖሩ ፍንጭ አለ። ለዚህም ይመስል ይህን ራሳቸው ያደራጁትን ኢመደበኛ ኃይል ወደ አንድ ዕዝ ቋት እንዲገባ ዛሬ ላይ የወሰኑት ምን መረጃ ደርሷቸው ይሆን?
እኛም ኢትዮጵያዊ፣ ፑቲንም ፑቲን
ከላይ ለማለት እንደተሞከረው ተቀጣሪ ኢመደበኛ ኃይሎች ዓላማቸውን የሚያሳኩት በአገር ፍርስራሽ ላይ ሲቆሙ ነው። ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሳንዘልቅ ቅርባችን በየመን፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ፣ አሁን ደግሞ በሱዳን የታየው ይህ ሃቅና የቅጥረኞች ስኬት ነው።
ሲከፋፈሉ ቢከዳዱም ትህነግ የሚባለው እንግዴ ልጅ የሻዕቢያና የሌሎች አጀንዳ አስፈጻሚ ድርጅት ነበር፤ አሁንም ነው። ወደፊትም … ትህነግ የተፈጠረበትን ዓላማውን ወደ ማገባደዱ ሲደርስ ያደረገው ነገር ቢኖር የአለቆቹን ድጋፍ አሰባስቦ፣ በዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች እየተዘመረለት፣ በትልቁ ድርጅት ሽፋን ተደርጎለት አማራና አፋር ላይ እንዳደረገው አገሪቱን አመድ፣ ህዝቧንም መና አስገብቶ በውድቀቷ ላይ ሊደንስ ነበር። ይህ ፈጠራ ሳይሆን “ታላቋ ትግራይ” የምትገነባው ኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እንደሆነ ራሱ ትህነግ ሲተርክልን ነበር። ግና ኢትዮጵያ አምላክ አላትና፣ የሚያነቡ ልጆች አላሳጣትምና፣ አንድ ሆና አመከነች።
አሁን በምዕራባውያን “አሸባሪ” የሚል ስም ባለቤት የሆነው የቫግነር መሪ ወደ ሞስኮ እንደሚሄድ ባስታወቀ ቅጽበት የአውሮፓውያኑና የአሜሪካ ወዳጅ ሆኖ ተዘመረለት። የኢመደበኛ አደረጃጀት ፍጻሜ የሚታወቅ ነውና “ሩስያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አመራች” የሚል ዓለም ሁሉ በቅብብሎሽ ሰበር ተናጠች። እንደ አቅሚቲ አሞሌ፣ አዋዜ፣ 150፣ 630፣ ጎበዚ፣ መሲ፣ ሔኒ፣ ወዘተ የሚባሉት የኛዎቹ የዩቲዩብ ገበያተኞች የቫግነርን ግስጋሴ የፖለቲካው አካሄድ ምኑም ሳይገባቸው “ሰበር” እያሉ ያልገባቸውን ለፈፉ።
አፍታም ሳይቆይ ነገሩ ሁሉ ውሃ ፈሰሰበት። ፑቲን ግን በአንድ ድንጋይ ስንት ወፍ እንደመቱ የምዕራቡ ዓለም ጭምር የገባው አይመስልም። ኢመደበኛው የቫግነር መሪ ይቭጌኒ ፕሪጎዢን ቤላሩስ ጥገኛ መሆናቸው ተሰማ። ወደ ሞስኮ ሄዶ መንግሥት ይገለብጣል የተባለው ታጣቂም ወደ ነበረበት ተመለሰ፤ በቀጣይም የመከላከያ አንድ አካል ይሆናል። ሦስት አማራጭ ቀርቦ ትግበራ ተጀመሯል። በሰፊ ፕሮፓጋንዳ የታጀበው ዩክሬን በሩሲያ ጦር ላይ ያቀደችው መልሶ ማጥቃት የእምቧይ ካብ ሆነ። የቫግነርም የግል ወታደራዊ ቡድን ኢመደበኛ እንደመሆኑ ባንዳ ሳይሆን እንደ ሐቀኛው ፋኖ አገር የታደገ ባለውለታ ሆኗል።
ለጊዜው እዚህ ላይ ነው ያለነው። ፑቲን ፑቲን ስለሆኑ አልፈውታል፣ እኛም እንደ አገር ስለተነሳን ተርፈናል። ኢመደበኞች ሃቀኛ ከሆኑ ውዳሴ እንደማይፈልገው አገር ወዳዱ ፋኖ አገር ለመታደግ ዋጋ የሚከፍሉ የቁርጥ ልጆች ናቸው እንጂ ክላሽ ታቅፈው ለማኅበራዊ ሚዲያ ማድመቂያ የሚውሉ ወይም መሸታ ቤት የአዝማሪ ውዳሴ ቁጭ ብለው የሚቀበሉ አይደሉም። ሐቅ ዓልባ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ለከፍተኛው ተጫራች የሚያገለግሉ፣ ላገራቸው መከላከያ ክብር የሌላቸው፣ ለከፈላቸው ሁሉ የሚሠሩ፣ አገራቸውን ለመሸጥ ከማንም ጋር የሚሠለፉ፣ ሞራለቢስ የአገር ነቀርሳዎች ናቸው። ምንም ይሁን ምን የማይታመኑ ባንዶች ናቸው! ይኸው ነው። የተባለው ሁሉ ታሪክ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ዕይታችንና ገጠመኛችን ነውና እንመርመር!!
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply