
መለስ ዜናዊ ከስሙ ጀምሮ ሁሉ ነገሩ የውሸት ወይም ፌክ ነው። ላደረሰብን ግፍ እንክሰሰው እንኳን ብንል በየትኛው ስሙ ነው ፍርድ ቤት የምናቆመው የነበረው? ደግነቱ ከዚህ ሁሉ በፊት ወደ ዕረፍቱ ሄዶ እኛንም አሳረፈን።
መለስ የዕውቀት ችግር አልነበረውም፤ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ከሥር መሠረቱ በነጻ አስተምራዋለች። ንጉሡም ሰው ነው፤ ነገ ሀገር ይጠቅማል ብለው ሸልመውታል ይባላል። ግን ያልታከመና ሥር የሰደደ የበታችነት ስሜት የነበረው፣ አስተሳሰቡ ደሃ የሆነ ሰው ነበር። በዚህ ደሃ አስተሳሰቡ ነበር ኢትዮጵያን ለመምራት ሥልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠው። ሥልጣን፣ ሃብት፣ ድሎት፣ ወዘተ ቢመጣም አስተሳሰብ ደሃ ከሆነ ችግሩ ውስብስብና መፍትሔ ዓልባ ነው የሚሆነው።
መለስ ኢትዮጵያን በጣም ነበር የሚጠላት፤ ለማፍረስ ይፈልግ ነበር ለማለት ብዙም አያስደፍርም። ነገርግን ልክ እንደ ፖለቲካ ወላጅ አባቱ የሻዕቢያው ኢሳያስ ኢትዮጵያ ተዳክማና ደህይታ ማየት የዘወትሩ ምኞቱና ሕልሙ ነበር። ይህንንም ገና ሥልጣን ከመያዙ ጀምሮ በዕቅድ የሠራበት፤ ሕልሙንም ዕውን ያደረገበት ጉዞ ነበር።
ወደ ሥልጣን ሲመጣ ትህነግ የሚለውን የድርጅቱን ስም መለወጥ አልፈለገም። የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር የተባለውን የአሸባሪና የወንበዴዎች ስብስብ እየመራ አዲስ አበባ ገባ። በነጻ አውጪ ድርጅት ስምም የሚጠላትን አገር “አገሪቱ” እያለ መራ፤ “አገራችን ኢትዮጵያ” ለማለት እንደተጸየፈ ሞት ወሰደው። ደሃ አስተሳሰብ ቶሎ ካልተፋቱት እስከ መቃብር ነው ፍቅሩ።
መለስ ኤርትራ በግድ እንድትገነጠል አደረገ፤ በኤርትራ መገንጠል ዋና ትኩረት ያደረገው አሰብን ለኤርትራ ለመስጠትና ኢትዮጵያን ወደብ ዓልባ አድርጎ ማደኽየት ነው። እንዳሰበውም አደረገውና በቀን ሦስት ሚሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ እንድትከፍል አደረጋት፤ በዓመት አይደለም በቀን፤ 3,000,000 ብር አይደለም፤ ሦስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በቀን!! ከዚህ ተነስተን ላለፉት 30+ ዓመታት ስንት እንደከፈልን መገመት አያዳግትም።
መለስ ድሃ አስተሳሰቡን ሲናገሩበት አይወድም፤ ያልተፈወሰ የበታችነት ስሜት የተጠናወተው ስለነበር የማይወደውን መከራከሪያ ለሚያመጡ ሰዎች የሚሰጠው ምላሽ በየጊዜው ልኩን ያሳበቀበት ሆኖ አልፏል። ለምሳሌ አሰብን በማጣታችን የኢኮኖሚ ጉዳት ይደርስብናል ወይ ተብሎ ሲጠየቅ፤ አሰብን ማጣት በኢኮኖሚው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አያደርስም፤ ምንም ለውጥ አያመጣም፤ ኤርትራውያን ከፈለጉ ግመሎቻቸውን ያጠጡበት ነበር ያለው። ምስጋና ለፈጣሪ ይግባውና አሁን ትክክለኛ ባለቤቶቹ የአፋር ግመሎች ከቀይ ባሕር የሚጠጡበት ዘመን ላይ እንገኛለን።
የመለስ ውዳቂ፣ ተራ ምቀኝነት የተሞላበት፣ አይደለም የአገር መሪ ከማንም ሰው የማይጠበቅ አስተሳሰቡ የታየው በባድመ ጦርነት ወቅት ነበር። የግል ጠባቂው/አጃቢው የነበረው ሚኪ ራያ በጦርነቱ ወቅት አስመራ እየሄደ ኢሳያስን እጅ ሲነሳና በሰላም እንጨርሰው እያለ ሲለምን ነበር ብሎ ሰሞኑን ነግሮናል። እንዲያውም ኢሳያስ መለስ ዜናዊን “ጨምላቃ” ብሎ ሲሰድበው፤ መለስም ጭንቅላቱን እንዳዘቀዘቀ ድምፅ ሳያሰማ ስድቧን ጠጥቶ እንደወጣ ሚኪ ራያ ነግሮናል። ለነገሩ ለመለስ ዓይነት ነውር ቀለቡ ይህ ሽልማት ነው፤ ምክንያቱም የኢሳያስ ስድብ ለመለስ እንደ ቡራኬ ስለሆነ።
ይኸው የባድመ ጦርነት ካበቃ በኋላ ወደ አልጀርስ ስምምነት ለማድረግ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ምሑራን እና ጠበቆች አሰብን ለማስመለስ አሁን ነው ጊዜውና ሙግቱን በጠንካራ ማስረጃ እናቅርብ፤ ክፍያም አንፈልግም፤ ለአገራችን በነጻ እናገልግል ብለው ቢጠይቁም መለስ “እናንተን አልፈልግም” ብሎ የውጭ አገር ዜጎችን በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ቀጥሮ አሰብ ለኢትዮጵያ እንዳትሰጥ እንዲያደርጉ በርትቶ ነበር የሠራው። ይህንን መለስ ነው እንግዲህ ደጋፊና አምላኪዎቹ “world class mind” እያሉ ከሙታን መንደር እንደ ዓልአዛር እንዲነሳላቸው የሚያንቆለጳጵሱት።
የአስተሳሰብ ደሃ የሆነው መለስ ኢትዮጵያን ደሃ ማድረግ የተለማደው ትግራይ ላይ ነው። በ17ቱ ዓመት የበረሃ ውንብድና ዘመኑ እሱና ወንበዴ ጓደኞቹ ለትግራይ ተብሎ በዕርዳታ የተላከ ዘይት፣ እህል እና ዱቄት የትግራይ ሕዝብ እንዳያገኝ በማድረግ እንዲሰቃይና እንዲሞት ያደረጉ፤ እንታገልለታለን ለሚሉት ሕዝብ 50 ዓመት ሙሉ ሰቆቃን የጋቱ ጨካኞች ናቸው። ከዚህ አንጻር አሰብን በማጣት የሚደርስብ የኢኮኖሚ ጉዳት ለመለስ ደስታው ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያን አዳክሞና የትግራይ ተመጽዋች አድርጎ ታላቋን ትግራይ ሲመሠርት አሰብን ከኢትዮጵያ ከመቀበል ይልቅ ከኤርትራ ለመውሰድ ይቀላል ብሎ የራሱን ወንበዴ ጓደኞቹን ያሳመነው መለስ ነው። አሁን ግን ዘመን መጣ፣ ምርኮ የሚመለስበት ዘመን፣ የፈረሰው ባሕር ኃይላችን በደማችን የቀላውን ቀይ ባሕርን የሚቆጣጠርበት ዕድሜ ላይ ደረስን፤ አለመሞት ደጉ ይህን አሳየን።
መለስ የድሃ አስተሳሰቡን ውጪ አገር ሲሄድና ፈረንጆችን ሲያገኝ በጣም ጎልቶ ይታይበታል። አሽከራቸው፣ ተላላኪያቸውና ጉዳይ ፈጻሚያቸው ስለነበር፤ ለራሱ ክብር ነስቶ አገራችንን ክብር ያሳጣ ወራዳ ሰው ስለነበር ውጪ አገር ሲሄድ ሎሌነቱን በገሃድ ይታይበታል። አፍቃሪ ትህነጉ ቴዎድሮስ ጸጋዬ “ህወሃት ለመገርደድ ወይም ለግርድና የተፈጠረ ነው፤ ለሻዕቢያ ሲገረደድ ነው የኖረው፤ አሁንም በዚያው ነው የሚቀጥለው” በማለት የተናገረውን እዚህ ላይ መጥቀስ የመለስን እና የፈረንጅ አለቆቹን ግንኙነት በጥሩ የሚገልጥ ነው። ትህነግ ይኸው ቴዎድሮስ የተናገረው አባባል አልለቅ ብሎት የመለስ ሌጋሲ አስቀጣዮቹ እነ ደብረጽዮን ገደለን፣ ጨፈጨፈን፣ አረደን፣ ሴቶቻችንን ደፈረ፣ ዘረፈን፣ … ሲሉት ለነበረው ሻዕቢያ ወደውና ፈቅደው “እየተገረደዱ” ነው። መለስም ለፈረንጅ ጌቶቹ እንዲሁ ነበር፤ የአስተሳሰብ ድህነት ማለት ይህ ነው።

መለስ ውጪ አገራት ሄዶና “ተገርድዶ” ሲመለስ በጣም ሼም የሚሰማው ሰው ነበር። ይህንን ኻፍረቱን ለመሸፈንም ወደ አገር ሲመለስ መወራጨት ይጀምራል። ቶሎ ብሎ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ወይም የፓርላማ ስብሰባ ላይ በመከሰት ሕዝቡን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዎችን፣ በአቅራቢያው ያሉትን ወንበዴ ጓደኞቹን፣ … ምንም የሚቀረው የለም አፉ እንዳመጣለት ይሳደባል። ሁኔታው “እኔ ለጌቶቼ እንደተገረደድሁ እናንተም ለኔ ትገረደዳላችሁ” ይመስላል። ይህ ነው እንግዲህ በደጋፊዎቹ “world class mind” የተባለለት መለስ።
መለስ በዚህ የወረደ የበታችነት አስተሳሰቡ ከዘረኝነት ጀምሮ ጥሎልን የሄደው የድንቁርና ኮተትና ዝባዝንኬ ለኢትዮጵያ ቆፍሮ የሄደው ጉድጓድ ነው። በዚህ ትውልድ ሙሉ በሙሉ መደፈን ባይችልም ሥራው ግን ተጀምሯል። መለስንና ትህነግን የሚያስታውሱን እዚህ ጉድጓድ ውስጥ እየተቀበሩ በምትኩ ኢትዮጵያዊነት እየጎላና እያበበ መሄዱ አይቀሬ ነው።
መለስ ዜናዊ ደሃ አስተሳሰብ የተጠናወተው፤ በበታችነት ስሜት የተሰቃየ ተራ ሆኖ ኢትዮጵያን ተራ ያደረገ ነበር። ስለ እርሱ ይህንን ያህል ከተባለ ይበቃዋል። የሌላኛው መሪ ወግ ግን በአንድ ዐርፍተ ነገር ይጠቃለላል፤ ግንቦት 20ን ተራ የሥራ ቀን አደረገልን። (ነሐሴ ፲፬ ነኝ ከ፬ ኪሎ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የጅል መንጋ ሲንጋጋ ጊዜው መሽቶ ነጋ
ትላንትን በዛሬ መዝኖ ግጠሙኝ አለ ፎክሮ
ጊዜው ተለውጦ ተቀይጦ የሰው መልኩ ሁሉ ተረስቶ
አውሬ መሰለ ባህሪው ተለውጦ
የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ብሎ ታቅፎ
ተመልሶ ይቧቀሳል ደም ተጠምቶ
በልቶ አዳሪ የታደለ ጦም አዳሪ ያልታደለ
ተገናኙ በሜዳ ላይ በወረፋ ሊሯሯጡ
በእሳት ቋንቋ ሊናገሩ፤ ጊዜ ዘሞ ሲራኮቱ
ሃገር ቤትም ተቃጠሉ
ዜሮ ጅምር ዜሮ ድምር
ሁሉም ባዶ ሆነ ድሉ።
Just non-sens… and then who are you