
በፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የመንግሥት ብቃት መሥሪያ ቤት (Department of Government Efficiency – DOGE) ኃላፊ ሆነው የተሾሙት የዓለማችን አንደኛ ባለጸጋ ኤሎን መስክ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ (ቪኦኤ) እንዲዘጋ ሲሉ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው አስታወቁ።
ከሁለት ቀን በፊት የፕሬዚዳንት ትራምፕ የልዩ ተልዕኮዎች ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ሪቻርድ ግሬኔል “የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮና የነጻ አውሮጳ ሬዲዮ (Radio Free Europe/Radio Liberty) በአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች የሚደጎሙ የሚዲያ አውታሮች ናቸው፤ በእነዚህ አውታሮች ውስጥ የሞሉት የግራ ክንፍ አክቲቪስቶች ናቸው፤ … ከነዚህ ጋዜጠኞች ጋር ለዓሥርተ ዓመታት ሠርቻለሁ፤ ለእነርሱ ሥራው ያለፈውን ዘመን ቅርስ የማስጠበቅ ዓይነት ነው፤ መንግሥት የሚደጉማቸው የሚዲያ አውታሮች አያስፈልጉንም” ብለው ነበር።
እኚሁ ልዩ መልዕክተኛ ለተናገሩት ኤሎን መስክ በኤክስ ገጻቸው ሲመልሱ “እኔም እስማማለሁ፤ መዘጋት ነው ያለባቸው፤ አውሮጳ አሁን ነጻ ሆናለች፤ ማንም የሚያዳምጣቸው የለም፤ እዚያ የተሰገሰጉት አክራሪ የግራ ክንፍ ጽንፈኛ ዕብዶች ናቸው። ስለ ለራሳቸው ነው እያወሩ ያሉት ግን ለዚህ ተግባራቸው አንድ ቢሊዮን የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ገንዘብ በየዓመቱ ያቃጥላሉ” ሲሉ ተግባራቸውን ከሚያባክኑት ሃብት ጋር በማወዳደር ገልጸዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የአሜሪካ መንግሥት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ለተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በየዓመቱ የሚከፍሉትን የገንዘብ መጠን ይፋ አወጥቶ ነበር። ይህ ለየሚዲያው ለአባልነት (subscription) በሚል ከመንግሥት የሚከፈለው ገንዘብ በተለይ ባለፈው ሳምንት ለፖለቲኮ (Politico) ለተባለው ሚዲያ በ2024 ዓም ከስምንት ሚሊዮን ዶላር በላይ (ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ) መከፈሉ ይፋ ከተደረገ በኋላ መንግሥት ለማንኛውም ሚዲያ የሚከፍለው ክፍያ መቆም አለበት ሲባል ቆይቷል።
በዚህ ምክንያት ከፖለቲኮ በተጨማሪ ለአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤሊያስ መሠረት ሲሠራበት የነበረው)፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ወዘተ የአሜሪካ መንግሥት የሚፈጽመው (የsubscription) ክፍያ መቆም እንዳለበት ኤሎን መስክ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ልዩ መልዕክተኛው “እንዲያውም ሳይውል ሳያድር ነው መቆም ያለበት” ሲሉ የኤሎን መስክን አቋም አጉልተው ተናግረዋል።
የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በ1942 ዓም (እኤአ)፣ የነጻ አውሮጳ ሬዲዮ ደግም በ1949 ዓም (እኤአ) የተቋቋሙ ሲሆን ሁለቱም በአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ የሚደጎሙ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተደጋጋሚ ከደረሰባቸው ነቀፋ በኋላ ግን የአሜሪካ መንግሥት በቀጥታ የሚደጉማቸው የሚዲያ ተቋማት ሆነዋል።
የነጻ አውሮጳ ሬዲዮ በተለይ ትኩረት የሚያደርገው በምሥራቅ አውሮጳ፣ ማዕከላዊ ኢሲያ፣ ካውኬዢያ (ከቀድሞ የሶቪየት ኅብረት የተገነጠሉት አገራት) እና በመካከለኛው ምስራቅ ነው። ሬዲዮ ጣቢያው ለ23 አገራት በ27 ቋንቋዎች ፕሮግራሙን የሚያቀርብ ሲሆን ዓመታዊ በጀቱ ከመቶ አርባ ሚሊዮን ዶላር በላይ (ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ) ነው።
የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ መላውን ዓለም የሚሸፍን ሲሆን ፕሮግራሞቹን በ48 ቋንቋዎች የሚያቀርብ ነው። ያለፈው ዓመት (2024) በጀቱ 944 ሚሊዮን ዶላር የጠየቀ ቢሆንም መጠነኛ ቅነሳ ተደርጎበት 857 ሚሊዮን ዶላር (110 ቢሊዮን ብር) ተሰጥቶታል።
የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ በበርካታ አገራት የፖለቲካ ነውጥ እንዲነሳ በመደገፍና በማስተባበር እንዲሁም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ተቋም ነው። ሠራተኞቹም በዚሁ የተቋሙ መርህ መሠረት የተሰጣቸውን ወይም የተላለፈላቸውን የቀጣሪው አገር አቋም ለማራመድ ወስነውና ለሕጉ ፈርመው የሚሠሩ ናቸው። አገራቸው ላይም ቢሆን የሚፈጸም ማንኛውም የአሜሪካ ፍላጎት ተግባራዊ ከማድረግ ወደኋላ አይሉም።
ይህንን አካሄድ የተረዳችው ሩሲያ የዛሬ ዓመት አካባቢ የነጻ አውሮጳ ሬዲዮን “የማያስፈልግ ድርጅት” ብላ በመሰየም የአገሪቱ የፍትሕ ሚኒስቴር መ/ቤት በሬዲዮ ጣቢያው የሚሠሩትን ጋዜጠኞችና ሌሎች ሠራተኞች፣ ለጣቢያው የገንዘብ ድጎማ የሚያደርጉትንና በሚዲያው ቃለመጠይቅ የተደረገላቸውን ሁሉ በማጋለጥ ክስ መመሥረቷን ገልጻ ነበር።
ባለፉት ሥርዓቶች ከኢትዮጵያ ተሞክሮ አንጻር ሲፈተሽ የታየውም ይኸው ከላይ የተገለጸው አገርን ለሌላ ጥቅም በቅጥረኛነት እስከ መስጠት የደረሰ “ጋዜጠኛነት” ነው። እዚህ ላይ በቪኦኤ በየቀኑ በአማርኛ በሚተላለፈው ፕሮግራሙ ላይ የሚቀርበው ርዕሰ አንቀጽ “ይህ የአሜሪካንን መንግሥት አቋም የሚያንጸባርቅ ነው” በሚል ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ማስታወሱ በቂ ማረጋገጫ ነው።
የደርግ መንግሥት እንዲወድቅና የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር ትህነግ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ቪኦኤ ከሲአይኤ ጋር በመሆን በእነመለስ ዜናዊ የሚመራውን የትግራይ ነጻ አውጪ ወንበዴ ቡድን ሲደግፍና የሚዲያ ሽፋን ሲሰጣቸው መቆየቱን ማስረጃ ጠቅሰው የሚናገሩ፤ “ተግባሩ ለገንዘብ ሲባል የአገር ጥቅም፣ ሉዓላዊትና ክብርን መሸጥ በመሆኑ በአደባባይ እንደ ሌሎች የሽብርና ክህደት ወንጀሎች በእኩል ተቆጥሮ ሊፈረጅ ይገባዋል” በሚል ክስ ሲያሰሙ መቆየታቸው አይዘነጋም።
የትግራይ ወንበዴ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከፈጸመ በኋላ በተገባው የኅልውና ጦርነት ቪኦኤ የመንግሥትን ኃይል የሚያዳክም፣ በተቃራኒው ደግሞ የወንበዴውን ቡድን የሚደግፍ ዘገባ በተደጋጋሚ፣ በሥልትና በመመጋገብ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ክፉ የፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ተልዕኮውን ሲፈጽም ቆይቷል።
የኢትዮጵያን ማናቸውንም መልካም ዜናዎች በሤራ በማጀል የሚያቀርበው ቪኦኤ፣ ኤለን መስክ እንዳሉት በውስጡ “የተሰገሰጉት” አማርኛ፣ ትግሪኛና ኦሮሚኛ ተናጋሪ ቅጥረኛ “ኢትዮጵያውያን” አማካይነት ምን ያህል አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ እያመረቱ ለማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚቀልቡ በወጉ ለሚረዱ የመዘጋቱ ዜና የላቀ ትርጉም ሰጥቷቸዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታትም በተለይ በኦሮሚያ ራሱን የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት ብሎ የሚጠራውን የሸኔ ጨካኝና አራጅ ቡድን መሪ የሆነውን ጃል መሮ በተደጋጋሚ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ሕዝብን የመጨፍጨፍ ፍላጎቱን እንዲያሳካ፣ መንግሥትን የመበጥበጥ ዓላማውን እንዲያካሂድና መርዘኛ ፕሮፓጋንዳውን በይፋ እንዲነዛ በተለይ በጽዮን ግርማ በኩል ከፍተኛ ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበር ይታወቃል።
በጡረታ ከተገለሉት መካከል ተመሳሳይ ዓላማ ባላቸው የአገር ውስጥ ባንዳዎች የክብር ካባ በስጦታ ተበርክቶላቸው የዩቲዩብ ምድብተኛ መሆናቸውን የሚያስታውሱ፣ ቪኦኤ ከተዘጋ ቅጥረኞቹ ክፍት ወደ ሆነው የትርምስ መድረክ በይፋ እንደሚቀላቀሉ ከወዲሁ ግምት የሰጡ አሉ። ቪኦኤም በዳያስፖራ የሚገኙ “አክቲቪስቶች” እንደሚያደርጉት የዩትዩብ ሚዲያ ወደመሆን “እንደሚያድግ” ይጠበቃል።
በቪኦኤና በጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ውስጥ የሚሠሩት “ጋዜጠኞች” ለተቀጠሩበት መንግሥት የሚያገለግሉ፣ አገራቸውን የካዱ ባንዳዎች ናቸው በሚል በጎልጉል ዓቋም ተወስዶ የተጻፈው ርዕሰ አንቀጽ እዚህ ላይ ይገኛል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ያወጣናቸውን ጥቂት ዘገባዎች ከዚህ በታች አስቀምጠናል፤
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
በየዓመቱ የካቲት 13 ቀን የራዲዪ ቀን ተብሎ ይከበራል። ግን ዛሬ ላይ ሬዲዪ የሚያዳምጠው የአለም ህዝብ ምን ያህሉ ነው? በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከፌስቡክ፤ ከቲክቶክና ከሌሎች ጊዜ አባካኝና ስመ ሳንቲም አስቆጣሪ ድህረገጾች ጋር አንገቱን ደፍቶ ሲቆፍር ስለሚውል ለራዲዪ ዘገባ ጊዜ ያለው አይመስለኝም። ቢኖረውም ላፍታ ያዳመጠውን ነገር ልብ ብሎ መልሶ መድገም አይችልም። ADHD (Scattered minds) በሽታ የተለከፈው ቤቱ ይቁጠረው። ይባስ ብሎ አሁን ደግሞ ጆሮ ላይ የሚደረጉ የድምጽ ማዳመጫ ነገሮች ሁሉ የወጣቱን የመስማት ችሎታ እየቀነሱና እያደነቆሩት እንደሆነ አዳዲስ ጥናቶች ያመላክታሉ። ስልጣኔ መስሎት ጆሮው ላይ አይጥ የመሰለ ነገር ወትፎ የሚቦጣረቀው ሁሉ ቆይቶ ያልገመተው ገመና እንደሚገጥመው እየተነገረን ነው። ግራም ነፈሰ ቀኝ ወደ አሜሪካ ራዲዪ ይዘጋል ማለት ጉዳይ ስንመለስ በእኔ እምነት ማለፊያ ነው ባይ ነኝ።
የፕሮፓጋንዳ ሥራ ከሰው ጋር አብሮ የቆየ ብልሃት ቢሆንም የህትመት፤ የራዲዪና የቴሌቪዥን አሁን ደግሞ information superhighway ወደ Mass confusion ተሸጋግሮ ጥቂትም እንኳን ቢሆን እውነትን ከበዛው ውሸት እንዳንለይ እንቅፏት እየሆነ ይገኛል። ሃገራትም እነዚህን የመገናኛና የማማቻ መስመሮች ለራሳቸው የመኖርና የፓለቲካ ጥቅም ቀለም እየቀባቡ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። የአሜሪካ ሆነ የሌሎች ሃገሮች የራዲዪ አገልግሎት ከዚህ የተለየ ዓላማ የለውም። አሜሪካ የራሷን ጥቅም እንደምታስቀድም በግልጽ ስለምትናገር የተደበቀ ነገር የላትም። እንደ እኛ ያለው የሙት ስብስብ ደግሞ ቋንቋዬና ብሄሬ እያለ እድሜ ልክ ሲያላዝን አይኑ ጨልሞ፤ ጉልበቱ ደክሞ ወደ ሞት ይሄዳል። የአሜሪካ የአማርኛውም ሆነ ሌላው የራዲዪ ጣቢያ አገልግሎት ራስን አጉልቶ ሌላውን በፕሮፓጋንዳ ከማደንዘዝ ጋር የያያዘ ስልት አራማጅ ነው። የሚገርመው የትግርኛና የኦሮምኛ ቋንቋ ክፍል እያሉ ሲያሰራጩ ያልገባው ለቋንቋው ተናጋሪ የተጨነቁ ሊመስለው ይችላል። ግን አይደለም። በቁስላችን ስንጥር ለመስደድ እንጂ!
ፕ/ትራምፕ ከሚያተራምሰው ሺህ ጉዳይ መካከል ይህንም የራዲዪ ጣቢያ ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ቢዘጋው እሰይ ያሰኛል እንጂ እንባ የሚያስፈስስ ነገር የለውም። እያየነው አይደል በኢንተርኔት ላይ ሁሉ ዜና አቅራቢና ተንታኝ ሆኖ ሲቦጫረቅ! የዓለማችን ነገር የተጣረሰና ማንም አምኖ ወደ ልቡ የማይወስደው በሆነበት ሰአት እንኳን በራዲዪ የተነገረው ቀርቶ ቆጥረህ እፊቱ ላይ ያስረከብከውን ነገርም የማያምን ትውልድ የተዘራበት ጊዜ ነው። ግን ይህ ለ70+ አመታት ሰላም የመሰለው የዓለማችን ጉዳይ እንደ ገሞራ እሳት አንዴ ይፈነዳና ዛሬ ላይ የጣቷ ጥፍር ተሰንጥቆባት እንባ የምታፈሰው የቤት እመቤትና ጮማ ቆርጦ በውስኪ የሚያወራርደው የጊዜው ድሎተኛ የምጥ ቀን ስትመጣ ምን ይሆኑ ይሆን? ያኔ ምንም አይነት ፕሮፓጋንዳ ምንም አይነት የለበጣ ንግግር ወይም ወታደራዊ ጉልበት ከለላ አይሆንም። በጨለማው ቀን እንደበላህ ሩጥ ነው የሚሆነው ጉዳዪ። ጊዜ እያለ ዘር፤ ቋንቋንና ሃይማኖትን ተገን ሳናረግ ለተጨቆኑና ለተገፉ እንቁም። የፈጠራ ፕሮፓጋንዳውና ሰውን ደም እያቃቡ ሽርፍራፊ ሳንቲም ለቀማው ይብቃን!