በጦር መሣሪያ ንግድ፣ በኮንትሮባንድ፣ በዝርፊያ፣ ጦር በማደራጀትና በከፍተኛ ዕዳ የተዘፈቁት አቶ ወርቁ አይተነው ከአምስት ወር በፊት አገር ለቀው የወጡት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው እንደሆነ የጎልጉል ታማኝ ምንጮች ገለጹ።
“ሚዲያ ጋላቢው” የሚባሉት አቶ ወርቁ አይተነው የኅልውናውን ጦርነት “ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል ነበር” የሚሉ ይኸው “ሠርግና ምላሽ ወደ ሐዘን ተቀይሮባቸው እንዲሰወሩ አድርጓቸዋል” ሲሉ ይገልጻሉ። እነዚህ ለአቶ ወርቁ ቅርብ የሆኑ ወገኖች እንደሚሉት ሪፖርተርን ጨምሮ ዘመኑ ያፈላቸው ሚዲያዎች ሕዝብን ሲያደናግሩና የማይጨበጥ መረጃ ሲረጩ መቆየታቸው ሳያንስ “አቶ ወርቁ አገር ውስጥ መኖር ባለመቻላቸው ተሰደዱ” ሲሉ የከፋይ ጋላቢያቸው አፍ ሆነዋል።
“ሲፈልግ አራክሶና አፍንጫ ይዞ የሚሞግተው የዋልታው ስሜነህ ባይፈርስ ከወርቁ አይተነውን ጋር ባደረገው የሦስት ክፍል ጭውውቱ ስለተነከሩበት ዕዳና ዝርፊያ ይጠይቃቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ይልቁንም ወርቁን የዓለም ፖለቲካ ተንታኝ አድርጎ መታየቱ ሰውየው ምን ያህል ሚዲያን እንደሚጋልቡ ማሳያ ነው” የሚሉት ታዛቢዎች፣ አቶ ወርቁ በዚሁ የሚድያ ጋላቢነታቸው ራሳቸውን ለጋስ፣ አገር ወዳድ፣ የአማራ ተቆርቋሪ፣ ጀግና፣ የልማት አርበኛ፣ የድሆች አባት፣ ወዘተ አድርገው ቢያቀርቡም እውነታው ግን ሊደበቅ የማይቻል የአደባባይ ሃቅ ነው።
ወርቁ አይተነው “ትግሉን ተቀላቅያለሁ አሉ” በሚል የተረጨው ዜና ወርቁ አይተነው ለጊዜው ዱባይ አስቀምጠው ሳለ “የማይታወቅ አገር ራሳቸውን ሰወሩ” በሚል ማጣፈጫ መቅረቡ ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ፈገግ አሰኝቷል። እኤአ መስከረም 10 ቀን 2023 (September 10, 2023) “አቶ አገኘሁ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ዋጋ እንደሚከፍሉ ተሰማ” በሚል የጎልጉል ዜና ሥር አቶ ወርቁ ቆሞ ቀሩን የዘይት ፋብሪካ ሸጠው ዱባይ መሸሸጋቸውን ጠቁመን ነበር።
በዘገባችን “…የአቶ ወርቁ አይተነው ተስካር፣ ሠርግ፣ ልደት፣ ትንታና እንጥሻ ሳይቀር በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች (ማኅበራዊውን ጨምሮ) የገጽታና ስም ግንባታ ተሰርቶላቸዋል” ስንል በሚዲያ ስም የሚጠሩትን ክፍሎች ህጸጽ ለመጠቆም ሞክረን ነበር።
በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካቸውን ሸጠው ዕዳቸውን ሳይከፍሉ ዱባይ እንደከተሙ የሚነገርላቸው አቶ ወርቁ አይተነው ተመርቆ በቆመው ፋብሪካቸው ስም ከፍተኛ ገንዘብ መበደራቸው የሚታወስ ነው። ከተመረቀበት ቀን ጀምሮ አንድም ሊትር ማምረት ያልቻለው የዘይት ፋብሪካ ጉዳይ ዜና መሆን ሲገባው ከሕዝብ የተዘረፉትን ሃብት እየተረጩ የሚደግሱት ቅንጡ ሠርግና ምላሽ ዜና ለሚያደርጉ መረጃ አካፍለን ነበር። እነዚሁ ተጋላቢ ሚዲያዎች “አቶ ወርቁ ትግሉን ተቀላቀልኩ አሉ። ከአገር ኮበለሉ” ብለው በሰበር ዜና ከመጮሃቸው በፊት ዕዳ ያጎበጠውን ድርጅታቸውን ሸጠው ዱባይ መቀመጣቸውን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጠቁሞ ነበር።
“ሃቁ ይህ ነው” የሚሉ ወርቁ አይተነው የዘይት ፋብሪካቸውን አቶ ገብሬ ለሚባሉ ኤርትራዊ በ35 ሚሊዮን ዩሮ ሸጠዋል። የሽያጭ ስምምነታቸውን የጨረሱ ቢሆንም ንብረቱን የገዙት ባለሃብት ሙሉ ርክክብ እንዳላደረጉ ጉዳዩን የሚከታተሉ ያስረዳሉ። ከግዢው ጎን ለጎን “አቶ ገብሬ ማን ናቸው?” የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።
“በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ብር የሚያፈሱ የኤርትራ ባለሃብት ከየት ተገኙ? በዚህ ደረጃ ከአቶ ወርቁ ጋር የሚያገናኛቸውስ ንግድ ብቻ ነው ወይስ ሌሎች ከዚያ ያለፈ ይሆን?” የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ መበራከታቸው ከሽያጩ ጎን ለጎን ሌላ ዜና ሆኗል። “ሻዕቢያ በረሃ እያለም ሆነ አሁን መንግሥት ሆኖ በግለሰቦች ስም እንደሚነግድና ዶላር አጠባ ላይ በሙሉ ኃይሉ እንደሚሰራ ይታወቃል፣ ይህ ምሥጢር አይደለም” የሚሉ አቶ ገብሬም የዚሁ የቆየ የሻዕቢያ ልምድ ውጤት ወይም አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ ከግምት በላይ የሆነ አስተያየት እየተሰጠ ነው።
አቶ ገብሬ ፋብሪካውን የገዙት ኢትዮጵያ ዘይት አምርተው ወደ ኤርትራ ለመላክ በማሰብ ይሁን በሌላ ዕቅድ በውል የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ሽያጩን አስመልክቶ ከመንግሥት ወገን ምንም አለመባሉ፣ ሪፖርተርን ጨምሮ የመንግሥትና ራሳቸውን ሚዲያ የሚሉ ተጋላቢ ጥቅመኞች በፋብሪካው ሽያጭና በአቶ ወርቁ አይተነው የዕዳ ክምር ዙሪያ ዝምታን መምረጣቸው “እኔ ከተከፈለኝ የአገር ሃብት ገደለ ይግባ” የሚል ዕምነት እንዳላቸው ማሳያ እንደሆነ አመላካች ሆኗል።
“ሚዲያ ጋላቢው” የሚባሉት አቶ ወርቁ አይተነው ከተለያዩ ባንኮች ከሰባት ቢሊዮን የሚልቅ ብር በብድር መውሰዳቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ ውስጥ መረጃው ያላቸው ሹም ለጎልጉል ጠቁመዋል። ከባንክ አካባቢም ለማጣራት እንደተሞከረው በትክክል አኻዙን ባይገልጹም “ብዙ ነው፤ በቢልዮን” የሚል ጥቆማ የሰጡን አሉ። አቶ ወርቁ አላቸው የሚባለው ንብረት ሁሉ የባንክ ዕዳ መያዣ ሲሆን “የራሴ” የሚሉት ከዕዳ የጸዳ ንብረት (asset) እንደሌላቸው የቅርብ ሰዎቻቸውና አብሮ አደጎቻቸው ይገልጻሉ።
የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አማራና አፋርን መውረሩን ተከትሎ በተነሳው ሕዝባዊ ቁጣና ማዕበል ውስጥ ተዋንያን ሆነው ብቅ ያሉት አቶ ወርቁ ጦርነቱን ተከትሎ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ገለልተኛ የሆኑ የክልሉ አመራሮች ይናገራሉ። “አትደናገሩ” የሚሉ መረጃ አቀባዮቻችን የአቶ ወርቁ ኩብለላ ፍርሃቻ ነው። “እገደላለሁ” ብለው ይፈራሉ። እንዲያውም “ግድያ ተሞከረብኝ” ሲሉ የሰሙ እንዳሉ የሚናገሩ አሉ።
የሰሊጥ ዝርፊያና የኮንትሮባንድ ጀብድ
“አቶ ወርቁ የትምህርት ደረጃ?” ብላ ትጠይቃለች ቅጽ የምትሞላው ሠራተኛ። “ልበ ብርሃን በይው፤ የማሪያም ምሩቅ” ሲሉ ይመልሳሉ አቶ ወርቁ። የሠራተኛዋ ማንነት ለመድበቅ ሲባል ቦታውንና መሥሪያ ቤቱን ከመግለጽ እንቆጠባለን። አቶ ወርቁ ቀለም ያልገባቸው የብቸና መናኸሪያ ፈዳላ ነበሩ። ብቸና ለያዥ ለገናዥ ያስቸገሩ ዱርዬ እንደነበሩ ጓደኞቻቸው ይመሰክራሉ። አቶ ወርቁ በወንጀል ታስረው ማረሚያ ከወረዱ በኋላ እስር ቤት ውስጥ ሆነው በጀመሩት የድለላ ሥራ ገንዘብ መሰብሰብ ጀመሩ። በዘመነ ትህነግ እስር ቤት ሆነው እስከ ፍርድ ቤት የሚዘልቅ ግንኙነት ዘርግተው ጉዳይ በማስፈጸምና አደራዳሪ በመሆን ገንዘብ ማግኘት የጀመሩት አቶ ወርቁ በዚሁ ሥራቸው የበርካታ ሃብታሞችን “የባንክ ባለዕዳ ናቸው” ኪስ አውልቀዋል።
ከእስር እንደተፈቱ አቋቋማቸው የተቀየረው አቶ ወርቁ ከትህነግ ሰዎች ጋር ተጋምደው ንግድ ገቡ። አሁን ልክ እሳቸው ሚዲያውን እንደሚጋልቡት በወቅቱ የትህነግ ሰዎች እሳቸውን ይጋልቧቸው ነበርና እስር ቤት የጀመሩትን ድለላና አቀባባይነት ገፍተውበት ገንዘብ አገኙ። ብድርም መውሰድ ጀመሩ። ሃብታም ተባሉ።
ትህነግ በመከላከያ ላይ ክህደት ፈጽሞ በተቀሰቀሰው ጦርነት በአነስተኛ ኃይል በሁለት ሳምንት ውስጥ መከላከያ ዳግም ተደራጅቶ በድሮን በመታገዝ መቀሌን ዳግም ሲቆጣጠር፣ አቶ ወርቁ አሁን ስማቸው ከማይጠቀስ የክልሉ ባለሥልጣናትና ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን በሁመራና ወልቃይት የሚገኙ መጋዘኖችን በመስበር ሰሊጥ አግዘዋል።
አቶ ወርቁ ራሳቸው ቆመው መኪና በማሰለፍ ሰሊጥ ወደ ሱዳንና ወደ ግል መጋዘናቸው አጓጉዘዋል። በኮንትሮባንድ ወደ ሱዳን፣ በሕጋዊ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ያጓጓዙት ሰሊጥ ከፍተኛ ሃብት እንዳስገኘላቸው በቅርብ የሚያውቁ ምስክሮች ይናገራሉ።
ለኤክስፖርት የተዘጋጀ ሰሊጥ ዝርፊያ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሌሎች ቢኖሩም፣ አቶ ወርቁ ግን በልዩ ሁኔታ ታጣቂ ኃይል አሰማርተው በተደራጀ መልኩ ከፍተኛ ዘረፋ መፈጸማቸውን መካድ የሚችል እንደሌለ የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ። በዚሁ ሳቢያ የትግራይ ባለሃብቶች አቶ ወርቁ ላይ ቂም ይዘዋል። በጦርነቱ ወቅትም የትህነግ ሚዲያዎች ስም እየጠሩ “ዘራፊ” በሚል የትም ሊያመልጡ እንደማይችሉ ይዝቱባቸው ነበር። እናም አሁን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ የትግራይ ሰዎች፣ የትህነግ ሃብታሞች ወደ ሥራቸው እየተመለሱ በመሆኑ አቶ ወርቁ ሥጋት ገብቷቸው፣ “እገደላለሁ” በሚል ፍርሃቻ ራሳቸውን እንደሰወሩ ለመረዳት ተችሏል።
“ፍንገላ” የአቶ ወርቁ ሿሿ
አቶ ወርቁ “ፍንገላ” በሚባለው ሌብነት ይከሰሳሉ። የሚከሷቸው “ወርቁ አይተነው ሿሿ ሠርቶናል” ይላሉ። “ላም አለኝ በሰማይ …” የሚል ስያሜ የተሰጠው ዘይት ፋብሪካ “ገና ለገና አምርቶ አከፋፋይ ያደርገኛል” በሚል ጉጉት በደብረ ማርቆስ ባልጩት ጸጉራቸውን የተላጩ ጥቂት አይደሉም።
አንድ ጉራጌ አካባቢ ዘይት ለማከፋፈል ቅድሚያ 2 ሚልዮን ብር የከፈለ ጠቦት ባለሃብት “ለማን አቤት ይባላል? ብዙ ነጋዴ ተንሰፍስፎ ተበላ” ሲል መፈንገሉን ይገልጻል።
አቶ ወርቁ በቀን አንድ ሚሊየን 350 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው የተናገሩለት ፋብሪካ ለአንድ ሺህ 500 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ሥራ መጀመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበት ይፋ መሆኑ ይታወሳል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ በሶስት ፈረቃ ማምረት ሲጀምር ለ6 ሺህ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኝ በወቅቱ ተመልክቶ ነበር። ይህን የንግድ ማስታወቂያ የሰሙ በሰልፍ አከፋፋይ ለመሆን ከባንክ ተበድረው አቶ ወርቁ ካዝና ካስገቡ ሶስት ዓመት በኋላ ነው “የሚዲያ ያለህ” ሲሉ ሿሿ መሠራታቸውን እያስተጋቡ ያሉት። ሚዲያው ግን የወርቁ አይተነው ፈረስ ሆኖ ጆሮውን ደፍኖ ሽምጥ እየተጋለበ ነው። ከሕዝብ ሮሮ ይልቅ ወርቁ አይተነውን የትግል መሪ ለማድረግ የተሰጠውን የቤት ሥራ በትጋት እየሠራ ነው።
የመሣሪያ ዘረፋና ጦር ግንባታ
“ፊደል ምን ያደርጋል” የሚሉት አቶ ወርቁ አይተነው ለውጡን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሰሊጥ ብቻ ሳይሆን መሣሪያ መዝረፋቸው፣ በመሣሪያ ንግድ ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑ እሳቸው ያደራጁት ለነበረው ኃይል ቅርብ የሆኑ ወገኖች አመልክተዋል።
መከላከያ ወደ መቀለ ሲገሰግስ በተለያዩ መጋዘኖች ውስጥ የነበሩ በርካታ የጦር መጋዘኖችን አሰብረው ዝርፊያ እንደፈጸሙ እማኞች ይናገራሉ። ወቅቱ ግርግርና ለውጡም ያልረጋበት በመሆኑ አቶ ወርቁ መሣሪያ በገፍ በማስጋዝ ዘመነ ካሴና ማስረሻ ሰጠኝ ለሚያደራጁት ታጣቂ አስታጥቀዋል። በኮንትሮባንድ ለሚነገዱም አከፋፍለዋል።
ለመከላከያ ሠንጋና ፉርኖ ዱቄት በማቅረብ ዜና ሲደለቅላቸው የነበሩት አቶ ወርቁ ከመሣሪያ ንግድ ጠቀም ያለ ገንዘብ መሰብሰባቸውን በሥራው የተሳተፉ ይመሰክራሉ። አንዴ መንግሥት ደጅ፣ አንዴ ወደ ጫካ እያማተሩ መረጋጋት ተስኗቸው የነበሩት አቶ ወርቁ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ድምጻቸው ከሚዲያ ባልተጠበቀ መልኩ የጠፋው በተለያዩ ወንጀሎች በመነከራቸው ሳቢያ እንደሆነ የሚናገሩ በሚኖሩበት ከተማ ደጋፊዎቻቸው ኮሽታ ከሰሙ ወጥተው እንዲታደጓቸው ዝግጅት እንደነበር መረጃ እየወጣባቸው ነው። በቂ ታጣቂ ኃይልም ማዘጋጀታቸው ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።
በሸራቶን አዲስ አንድ ግብዣ ላይ “ታንክ ሳይቀር ከአማራ ክልል እንዳይወጣ መመሪያ ሰጥቻለሁ” በሚል ለአንድ ተጋላቢ ሚዲያ መናገራቸውን የሰሙ እንዳሉት፣ ይህን ሁሉ ቢፈጽሙም መንግሥት በቦሌ አየር ማረፊያ ከአገር እንዲወጡ መፍቀዱ እንጂ “አገር ውስጥ መኖር ባለመቻሌ ከአገር ወጣሁ” ማለታቸው ዜና ሊሆን ባልተገባ ነበር። ትክክለኛው ሰበር ዜና እጅግ በርካታ የባንክ ዕዳ ያለባቸው ወርቁ አይተነው እንዴት በቦሌ ተፈቅዶላቸው ወጡ? የተባበራቸው የመንግሥት ሹመኛስ ማነው? የሚለው ሊሆን ይገባ ነበር ይላሉ ለጎልጉል መረጃው ያቀበሉ ወገኖች።
“ትግሉን ተቀላቅያለሁ“
ወርቁ አይተነው በዝርፊያና በብድር ካከማቹት ሃብት ላይ በጀት የሚቆርጡለት ሠራዊት በአንድ ገዳም አቅራቢያ ማደራጀታቸውና ስልጠና እየወሰዱ እንደነበር ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።
የትግራይን ወረራ መቀልበስ ላይ ትኩረት በተደረገበት ወቅት፣ ይህንኑ ወቅታዊ ጉዳይ ምሽግ አድርገው እላፊ የሄዱት አቶ ወርቁ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ዕንቅልፍ ማጣታቸው በገደምዳሜ ሲነገር ነበር።
ከፍተኛ ዕዳ የሚጮህባቸው “ባለሃብቱ” መበደር እንጂ መክፈል እንደማይወዱ እንደ ወግ ቢነገርባቸውም፣ ውስጡን የሚያውቁ ከተማ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ከሚሰበስቡት ጎራ እንዳሉበት በስፋት ይሰማል። እናም በብድር የሚወስዱትን ብር የውጭ ምንዛሬ ለቀማ ላይ ያውሉታል የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ይህ እየተሰማ ባለበት ነው “ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ችግር ገጥሟቸዋል” በሚል የአማራ ክልል ሃዘን ተቀምጦላቸው የነበረው።
አቶ ወርቁ የተለያዩ ባንኮች በብድር ስላጠቡና የብድር ጣሪያ ላይ ስለደረሱ ተጨማሪ ብድር ማግኘት ሲከለከሉ ቆይተዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ባለሃብቱን ለመርዳት ቢጨንቀን ጸደይ ባንክ ከተባለው የአማረ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ብድር እንዲፈቀድላቸው ተደረገ። ዋናዎቹን ባንኮች አልበው ሲያበቁ፣ ድሆች ከሚደጎሙበት የብድር ተቋም ተሰልፈው የወሰዱት አቶ ወርቁ፣ ከአነስተኛና ጥቃቅን ብድር ተቋም ድጋፍ እንደተደረገላቸው ለመደበቀ ሌላ “ላም አለኝ በሰማይ…” ዜናዎችን ማናፈስ ጀመሩ።
አቶ ወርቁ አይተነው ግምቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚዘልቅ በቀን 12 ሺህ ቶን ሲሚንቶ የሚያመርት የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ስራ መጀመራቸውን በሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ ኦገስት 20, 2022 ዕትም ታወጀላቸው። ከዩቲዩብ ወደ ሪፖርተር ሽግግር ያደረጉት አቶ ወርቁ ግንባታውን “ታይቶ የማይታወቅ” ሲል አገነነላቸው። ሪፖርተርም መጋለቡን በሚያሳብቅ ደረጃ ሁለት ዓመት ሙሉ አንድ ሊትር ያላመረት ዘይት ፋብሪካን “አምስት ቢሊዮን ወጪ የወጣበት” ሲል የዜናው ማስደገፊያ አድርጎ በስኬት አወሳው።
ደብሊው ኤ የሚባለው ይህ የሲሚንቶ ፋብሪካ በ150 ሄክታር መሬት ላይ ተንጣሎ የሚገነባና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ስርጭት እንደሚዛወር ጊዜ ቆጥሮ የተጀመረ ፕሮጀክት እንደነበረም የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ምን ደረጃ እንደደረሰ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
አቶ ወርቁ በተመሳሳይ በሪፖርተር ጋዜጣ በኩል በአቪየሽን ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ተገልጾላቸው ነበር። አቶ ወርቁ ይህን ካስታወቁ በኋላ በተከታታይ ፕሮጀክታቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይፋ አልሆነም። “ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንዲሉ የአቶ ወርቁን የአቪየሽን ኢንቨስትመንት ዜና ጎጃሜዎች “ዲስኩራም” ሲሉ ተርተውበታል።
“ኩታራም እያለ እንዲሁ ትርትር ነበር” ሲሉ ብቸና የሚያውቋቸው አቶ ወርቁን ይገልጿቸዋል። “እምድር አልሆን ብሎት ወርቁ ሰማይ ወጣ፤ መውጣቱ ባልከፋ መውረጃ እንዳያጣ” ሲሉ የገጠሙባቸውም ነበሩ።
በአገራቸው የማይደራደሩ፣ ሃቀኛ፣ ሌብነትን የሚጠሉ፣ ደግ፣ ለጋስ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ሕዝብ የሚወደዱ ወዘተ እየተባለ የሚዘገብላቸው አቶ ወርቁ አይተነው “ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ባለመቻላቸው ለጊዜው በስም ያልተገለጸ አገር ራሳቸውን ሰወሩ” የሚለውና ጎልጉል ቀድሞ ያስታወቀው እዳሪ መረጃ ዛሬ ላይ ሰበር የሆነው ከላይ ለተመለከቱት አቶ ወርቁ ነው።
አቶ ወርቁ መታገል ከፈለጉ ከማርቆስ ቆልቆል ብሎ እሳቸው ካደራጁት፣ ወይም አዴት ካለው ዘመነ ካሴ አለያም በቋሪት አቅጣጫ ከአቶ ክርስቲያን ቤሰቦች ግርጌ ካለው እስክንድር ነጋ ጋር መቀላቀልና ሰበር ዜናውን እውነተኛ ሰበር ሊያደርጉት እንደሚገባ የሚጠቁሙ፣ “አይ ወርቁ” ሲሉ ሲያልቅ አይምር ዘፍነዋል።
ከግለሰብ እስከ ባንክ ኪስ ያወለቁት አቶ ወርቁ አይተነው፣ ሰባት ቢሊዮን የሚሆን የአገር ሃብት ተሸክመው፣ ዕዳ የሚጮህበትን ፋብሪካ ሸጠው ምንም ንብረት አገር ውስጥ ሳያኖሩ መጥፋታቸው የዝርፊያ ሰበር ዜና ሊሆን ሲገባው “የማይታወቅ አገር ሆነው ታጋይ ሆኑ” በሚል ጩኸት መረጨቱ አስገራሚ ሆኗል።
ከላይ በጥቂቱ የተገለጹት አቶ ወርቁ በእነ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ መሳይ መኮንን፣ ደረጀ … ከሚመራው የአማራ ክልል እንቅስቃሴ ጋር መወገናቸው “እኛ ያለቅደስነው የአማራ ንቅናቄ ውግዝ ነው” በሚሉት በ360 ክንፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥባቸው ሆኗል።
በተለያዩ አካላት ከተለያዩ አካባቢዎች ምሪትና ካርታ የሚታደለው የአማራ ክልል ጦርነት ጎን ለጎን “የትግሉ ባለቤት እኔ ነኝ” የሚል ግብግብ እያስተናገደ ነው። 360 አቶ ወርቁን “ወዮልህ” ሲል፣ አቶ ወርቁ በበኩላቸው “የድምጽ ማስረጃ አለኝ። ውርድ ከራስ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ መጠቋቆምና ማስፈራራት እየተወረወረ ባለበት ወቅት ነው “ትግሉን ተቀላቀልኩ አሉ” በሚል አቶ ወርቁ ሰበር የሆኑት።
ዜናውን የሰሙ እንዳሉት አቶ ወርቁ ኤርትራ ካልገቡ በቀር በዝርፊያና የፋይናንስ ወንጀል መንግሥት ከፈለገ በዓለም ዓቀፍ ስምምነት መሰረት ሊያዛቸው እንደሚችል እየገለጹ ነው። እነዚህ ወገኖች ሚዲያዎችን “እስኪ አገር የምትወዱ ከሆነ ከወርቁ ጀርባ ያለውን ሌብነት ይፋ አውጡ” ሲሉ ይጠይቃሉ። አያይዘውም “የዘርና የጎጥ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ሚዲያዎችም የሌቦች መመሸጊያ ናቸው” በማለት ብዙም እንበማይጠብቁ ይገልጻሉ።
“ይልቁኑም” ይላሉ እነዚህ ወገኖች፣ “ይልቁኑም አቶ ወርቁ አይተነው እየተቆለጳጰሱ በቪኦኤና ዶቺቬለ ዘገባ ይቀርብላቸዋል። ቢቢሲ ደግሞ ‘ከባለሃብቱ ስደት ጀርባ አምስት ነጥቦች’ ብሎ ያረገርግላቸዋል። የባንክ ወሬ ነጋሪ እንዳለው የሚገልጸው ዋዜማ ደግሞ ‘አቶ ወርቁ ምንም ዕዳ እንደሌለባቸው ምንጮች ነገሩኝ’ ሲልላቸው ኢንሳይደርና አዲስ ሪፖርተር በበኩላቸው ‘ ወርቁ አይተነው ትግሉን ከተቀላቀሉ በኋላ በትግሉ ሜዳ ሞራል በደመና ተመስሎ ወረደ’ የሚል ዜና በተደጋጋሚ እንሰማለን” ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
መቼ ነው እውነት ያለበት ወሬ የምትለጥፉት? አዎን ማን ይሙት በኢትዮጵያ ምድር ከዝርፊያና ከውንብድና ጋር ያልተቆራኘ ይገኛል? እንኳን በዘሩና በቋንቋው ክልሉልን ተገን አርጎ የሚፋለመው ይቅርና ዓለም አቀፋዊ እይታ አለን በዲሞክራሲ ከእኛ በላይ ላሳር የሚሉን እንኳን ከሶስት ነገሮች ማምለጥ አልቻሉም። ዓለሙ ሁሉ እንደገማ ለመረዳት ከራስ መጀመር ነው። በሌላው ላይ እያመላከቱ እኔን ስሙ የሚሉን ናቸው አሁን ሃገሪቱን የሚያምሷት። ሲጀመር በሃበሻ ምድር ቀምቶ፤ አታሎ፤ ሰርቆ የማይበላ የለም። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሰዎች የሚደርስባቸውን አፈናና ገመና ማየቱ ብቻ በቂ ይሆናል።
ያለፈ ነገርን ልክ ትላንት እንደሆነ በማስመሰል የሰውን ስም ማጠልሸት ያው የሃበሻው ወረርሽኝ ፓለቲካ እርስ በእርሳችን እንድንገዳደል ያደርጋል እንጂ ለእርቅና ሰላም የሰውን ልብ አያዘጋጅም። እሳት ሆን ብሎ ለመለኮስ ወይም የተለኮሰውን ላይ ቤንዚን ለማርከፍከፍ ዛሬ ብሄርን የሚሰድቡ ሆዳሞች ሆን ብለው እርስ በእርሳችን እንድንተላለቅ የሚሹ ለመሆኑ ቃልና ተግባራቸው ያሳያል። እኔ የምትሉትን ባለጠጋ አላውቀውም። ላውቀውም አልፈልግም። በኢትዪጵያም ሆነ በዓለም ዙሪያ በእጅ ሳሄድ፤ ሳያጭበረብር፤ ሳያማታና ሳያታልል ባለሃብት የሆነ የለም። አንድ ጋ ሲያተርፉ ሌላው ጋ መዝረፋቸውን መረዳት ተገቢ ነው። ሌላው ቀርቶ አበዳሪ ሃገሮችና የዓለም ባንክ ለወዲያኛው ዓለም አይደለም የሚያበድሩት። ለዝርፊያ ለማመቻቸት እንጂ። ስለዚህ ሁሉ ዘራፊ ነው። ልዪነቱ ከፍታውና ዝቅታው የሚጠቀሙበት ዘዴና የሚነገድበት ህዝብና ሃገር ነው።
ስለሆነም ወደ ሰላም፤ ወደ አንድነትና መተሳሰብ የሚያመጣንን መንገድ መፈለግና ሃሳብ ማካፈል እንጂ ይሄ አውራ ጣቴ ከአመልካች እጣቴ ትበልጣለች የሚሉት ፓለቲካ ከመታመም የሚመነጭ መርዝ ነው። የሃገሪቱ ችግር ትሻል ቀርታ ሁሌ ትብስ እንዲሉ ከመከራ ወደ ከፋ መከራ መሸጋገሯ ነው። ባለሃብቱ ሃገር ጥለው የፈረጠጡበትን ጉዳይ ራሳቸው ያውቃሉ። ግን በምድሪቱ የመፈርጠጥና የሚገባበት ሃገር ቢገኝ ባለጠጋም በለው ድሃ የሚቀር ሰው ያለ አይመስለኝም። ችግሩ ብሷል። መከራው ዶፍ ሆኗል። ዘረኞች ሰክረዋል፤ ፍትህ ጠፍቷል። እና ሰዎች ከዚህች ምድር ቢኮበልሉ ኡኡ የሚያስኝ አንዳች ነገር የለም። የዚህ ድህረ ገጽ አዝማሚያ አፍቃሪ መንግስት ነው። ይህ ደግሞ የድህረ ገጽን ገጽታ የሚያጠለሽ ሚዛናዊነት የጎደለው ጉዳይ ነው። መንግስት ይመጣል፤ መንግስት ይሄዳል። ከእውነት ጋር መቆም ግን የመንግስት መንሸራተት አያሳስበውም። የጠ/ሚሩ የመደመር ሂሳብ መቀነስ መሆኑን በተግባር እያየን ስለሆነ በሚነገረንና በሚወራው ሳይሆን በምድር ላይ በሚገኘው እውነታ እንመራ። በቃኝ!
Editor says
ሰላም Tesfa
በቅድሚያ የድረገጻችን ተሳታፊ ስለሆኑና በየጊዜው አስተያየተዎን ስለሚያጋሩን እናመሰግናለን።
እንደሚታወቀው እስካሁን በርስዎ አስተያየቶች ላይ ምንም ያልን ባንሆንም በዚህ ዘገባ ሥር የጻፉትን አንብበን ዝም ማለት ስላልቻልን ጥቂት ለማለት ወደድን።
አስተያየትዎን የጀመሩት “መቼ ነው እውነት ያለበት ወሬ የምትለጥፉት?” በሚል ውንጀላ ነው። ይህ አባባል እውነተኛ ነገር ለጥፈን የማናውቅ የሚያስመስል ችኩልና ስሜታዊ ማጠቃለያ ነው። ሲቀጥል “እኔ የምትሉትን ባለጠጋ አላውቀውም” ብለዋል። ታዲያ ስለማያውቁት ሰው የተጻፈን ዘገባ በምን ዕውቀት ነው ሐሰተኛ መረጃ ነው ብለው ለመፈረጅ የበቁት?
እኛ ስለ አቶ ወርቁ በርካታ መረጃ ቢኖረንም በጣም አንጥረንና ጠቃሚ ነው ያልነውን ብቻ ነው የጻፍነው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በማያውቁት ጉዳይ አስተያየት ከመስጠትና አላስፈላጊ ፍረጃ ውስጥ ከመግባት ለመቆጠብ መጀመሪያ ማንበብና መረዳት፤ ከተቻለም ዝምታን መተግበር ዐዋቂነት ይመስለናል።
ቸር እንሰንብት
አርታኢው