የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር አሜሪካ ስልክ ደውለው መረጃ አሳልፈው በመስጠታቸው ዋጋ የሚያስከፍል ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተሰማ። አፈጉባዔው እንደተቀጣሪ ሪፖርተር በአሜሪካዊ ዜግነት አማራ ክልል ሆኖ ዜና ሲያሰራጭ የነበረው አቶ ተዋቸው ደርሶ የመታሰሩን ዜና ነው በስልክ ያሳበቁት። አቶ ተዋቸው መታሰሩን ዘሃበሻ “ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለሥልጣን ነገሩኝ” ሲል ነው የዘገበው።
በዚሁ መነሻ አቶ ተዋቸውን አስመልክቶ መረጃ ለማሰባሰብ የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ባደረገው ማጣራት በቀጥታ ለእስር የዳረገው ምክንያት ባይታወቅም፣ የግንኙነት ሰንሰለቱን ተከትሎ በርካታ መረጃ እንደተገኘበት ለማወቅ ተችሏል። ሰላማዊ መንገድን አማራጭ አድርገው ከማይከተሉ ኃይላት አመራሮች ጋር ግንኙነት አለው የሚለው ግን ለመታሰሩ ከተነገሩት ምክንያቶች ገዝፎ የወጣው ሆኗል።
በዘመነ ትህነግ የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የአንድ ባለስልጣን ሹፌር የነበረው አቶ ተዋቸው፣ ኢንሳ ሲሠራ ቆይቶ ትህነግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ወደ አሜሪካ አቅንቷል። በቅርብ ኢንሳ ሲሠራ የሚያውቁት ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ በግል ከሚያውቃቸው በተለይም ከብአዴን ሰዎች ጋር ተዋቸው ደርሶ የነበረው ግንኙነት የጠበቀ እንደነበር ይናገራሉ፤ በስም ጠቅሰውም ገልጸዋል። በወቅቱ ትህነግ ላይ መጠነሰፊ ተቃውሞዎች ይሰሙ ከነበረበት አሜሪካ ምን ዓይነት መረጃ ተዋቸው ይልክ እንደነበር የመረጃው ባለቤቶች ባያውቁም የተዋቸው ግኙነት ግን ከትላልቆቹ ጋር እንደነበር ጠቁመዋል።
ከለውጡ በኋላም የትህነግ ወረራን ተከትሎ ተዋቸው አገር ውስጥ ባለው ትሥሥር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የዘሃበሻ ዘጋቢ ተብሎ ግንባር በመሄድ ቦታዎችን ለይቶ የሚጠቁሙ የፎቶ፣ የቪዲዮና የጽሑፍ መረጃ ወደ አሜሪካ ይልክ እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ጎን ለጎን አንዳንድ የጦር መረጃዎችን አዲስ አበባ ለሚገኙ ሌሎች ወገኖች ያደርስ እንደነበር ስለ እርሱ የሚያውቁ አመልክተዋል።
ጦርነቱን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ፣ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ከአቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስና ከበርካታ የአማራ ብልጽግና ካድሬዎች ጋር ቤታቸው ድረስ እስከመሄድ የደረሰ ቅርርብ የነበረው አቶ ተዋቸው፣ በተለይ ከአቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር ጥብቅ ወዳጅ እንደሆነ በቂ መረጃዎች አሉ።
አቶ ተዋቸው በፖሊስ መያዙን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ ወደ አሜሪካ ስልክ ደውለው ስለ ጓደኛቸው መታሰር መናገራቸውን ጎልጉል የማያወላዳ መረጃ አግኝቷል። አቶ አገኘሁ ካላቸው ኃላፊነት አንጻር ስልክ እየደወሉ ወሬ አመላላሽ እንዲሆኑ ያስገደዳቸው ጉዳይ ምን እንደሆነ ለጊዜው ያልገለጹት የዜናው አቀባዮች “ውሎ አድሮ ይሰማል” ሲሉ አልፈውታል።
ከሁለት ዓመት በፊት አቶ ተዋቸው በባህር ዳር ከተማ በኢንቨስትመንት ስም ሰፊ መሬት (8 ሄክታር) የወሰደ መሆኑን የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች መረጃ አስደግፈው ይገልጻሉ። ይህም የሆነው አቶ አገኘሁ የክልሉ መሪ በነበሩበት ወቅት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ አቶ ተዋቸው የባለሃብቱ ወርቁ አይተነው የቅርብ ጓደኛ እንደሆነ የሚያውቁ፣ የአቶ ወርቁ አይተነው ተስካር፣ ሠርግ፣ ልደት፣ ትንታና እንጥሻ ሳይቀር በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች (ማኅበራዊውን ጨምሮ) ሰፊ ሽፋን እንዲያገኝ ተዋቸው ደርሶ ድልድይ ሆኖ ይሠራ እንደነበር፣ ለዚህም የገጽታና ስም ግንባታ ሥራ ጠቀም ያለ ክፍያ ይሰጠው እንደነበር በቅርብ የሚያውቁ የሚዲያ ሰዎች ለጎልጉል የአዲስ አበባ ተባባሪ ዘጋቢ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካቸውን ሸጠው ዕዳቸውን ሳይከፍሉ ዱባይ እንደከተሙ የሚነገርላቸው አቶ ወርቁ አይተነው ተመርቆ በቆመው ፋብሪካቸው ስም ከፍተኛ ገንዘብ መበደራቸው የሚታወስ ነው። ከተመረቀ ጀምሮ አንድም ሊትር ማምረት ያልቻለው የዘይት ፋብሪካ ጉዳይ ዜና መሆን ሲገባው በሕዝብ ሃብት የአቶ ወርቁ ሠርግና ምላሻቸው በየሚዲያው ሲዘዋወር የነበረው በአቶ ተዋቸው አማካይነት እንደሆነ የጎልጉል ተባባሪ ሪፖርት ያስረዳል።
“የዘሐበሻ ዘጋቢ፣ ተዋቸው ደርሶ በፌደራል ፖሊሶች ተይዞ አዲስ አበባ ሜክሲኮ በሚገኘው ጽ/ቤት መታሰሩን ለቤተሰብ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገልፀውልናል” ሲል ዘሃበሻ ዜናውን አስቀድሞ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። አያይዞም “ተዋቸው ከሚኖርበት አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት የሕግ ማስከበርን ዘመቻ ጥሪ ተቀብሎ ነበር ወደ ሀገር ቤት የገባው። በየግንባሩ በመዝመት ለዘሐበሻ መረጃ ሲያቀብል እንደነበር ይታወሳል” ሲል ገልጿል።
ዘሃበሻ “አንድ ስማቸውን ለመግለፅ ያልፈለጉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ በሂደቱ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ምክንያቱም ተዋቸው ለሀገር እያደረገ ባለው አስተዋፅኦ በሌሎች ወገኖች በስርአቱ ካድሬነት የተፈረጀ ሰው ነው። የመንግሥት የፀጥታ አካላት ደግሞ በእሰር ያዋክቡታል። ማንም ሰው እየተነሳ የፈለገውን ማሰር የሚችልበት ስርአት እየተፈጠረ ስለመጣ ማናችንም ላለመታሰራችን ዋስትና የለንም ይላሉ” ሲል “አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊ” እንደነገሩት ገልጾ ጽፏል።
ዘሃበሻ የእስሩን ምክንያት አላስታወቀም። የጠቀሳቸው ባለሥልጣንም ስለ እስሩ ምክንያት የሰጡት መረጃ ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም። ዘሀበሻ የሥራ አጋሩን እስር አስመልክቶ የሚያወጣው አዲስ መረጃ ካለ ወደፊት የምናካትት ይሆናል።
ጎልጉል ባሰባሰበው መረጃ በርካታ ፍንጮች ቢኖሩም መረጃ የሰጡ ወገኖች ለጊዜው ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ከመግባት መቆጠብ እንደሚገባ ባሳሰቡት መሠረት ከዚህ በላይ መሄድ አልተቻለም።
አቶ አገኘሁ ከበርካታ ፋታ የማይሰጥና አጣዳፊ አገራዊ ጉዳዮች ይልቅ የአንድ ግለሰብ መታሰር ለምን እንዳስጨነቃቸውና ስማቸውን ሳይጠቅሱ መረጃውን በስልክ ለሚዲያ እስከመስጠት ሊያደርሳቸው የቻለበትን ምክንያት ለማወቅ ተባባሪያችን ከራሳቸው ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
አቶ ተዋቸው ከመታሰሩ በፊት በተለይም በባህር ዳር ከተማ ከሰዎች ጋር ሆኖ ባለበት ጊዜያት የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ስም እየጠራ “እከሌ ደወለልኝ” በሚል ክንደ ብርቱ እንደሆነ የማሳየትና፣ በዚሁ ሳቢያ የማስፈራራት ልማድ እንደነበረው የመታሰሩን ዜና የሰሙ ገልጸዋል። ድርጊቱ ሰፊ መነሻና መዳረሻ ያለው በመሆኑ ጎልጉል ወደፊት ጥቅል ሪፖርት ያቀርባል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply