በተለይ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ብሎ የሚጠራውን መቀሌ የመሸገውን የወንበዴዎች ስብስብ (ትህነግን) እያገለገሉ ስለመሆኑ ከሚያቀርቡት ያልተመጣጠነ መረጃ መረዳት አያዳግትም። ለዚህም ይመስላል የተጠቀሱት ሚዲያዎች በተለይም የጀርመን ድምጽ ተቃውሞ እየቀረበበት ይገኛል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ መረጃ አቀባይ እንዳለው “አለቃና ተቆጣጣሪ ያለ አይመስልም” ሲል በተጠቀሱት ሚዲያዎች ከሚሰሩ ዜና አቅራቢዎች ጋር ቅርብ መሆኑንን የጠቀሰ አስተያየት ሰጪ እንደነገረው ይገልጻል።
የአንድ ጋዜጣ ኤዲተር እንደነበር ገልጾ አስተያየት የሰጠው ባለሙያ “ሚዲያዎቹ አንዳንድ ጊዜ የሚያቀርቧቸው፣ በተለይም ከክልል ሪፖርተሮቻቸው የሚተላለፉት መረጃዎች ያስደነግጡኛል። ሁሉም እንዳሻቸው ሪፖርት የሚያቀርቡና የኤዲተሮች ሚና የሚታይባቸው አይመስሉም። አንዳንዴ እጅግ አስፈሪና ሆን ተብሎ የሚተላለፉ የጽንፈኛና የፖለቲካ ድርጅት ማስታወቂያ የሚመስሉ ሪፖርቶች ያጋጥሙኛል” ሲል ሃሳቡን ገልጿል።
“በቅርቡ ጃልመሮ የተባለው የኦነግ ሸኔ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ መንግሥት ካጋለጠና የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ገዳዮችም ኦነግ ሸኔ መሆኑ ሲገለጽ፣ ቪኦኤ ማስተባበያ መሥራቱ ዕድሜ ልኬን የማልረሳው ስህተት ነው” ሲል እንደ ዜጋ ቅሬታውን ጭምር ባለሙያው ያስረዳል። አያይዞም ዛሬ ትህነግ “መንግሥት የለም” በሚል በተደጋጋሚ የሚቀርቡ መረጃዎች ቢያንስ የሌሎችን ክልሎች ኅልውና የሚያጣጥል በመሆኑ ክልሎቹ መጠየቅ እንዳለባቸው አመልክቶ “ሚዲያዎቹ እጅግ የተሰላቹ ወይም ደንታቢስ የሆኑ አለያም አንድ የማይታወቅ ችግር አለባቸው” ሲል ተናግሯል።
ህወሓት ብቻውን “መንግሥት የለም” እያለ ራሱ ሕገወጥ ሆኖ ስለ ሕግ መከበር ሲናገር ሌሎቹ ክልሎች ግን የመንግሥትን መኖር ተቀብለው ከፌዴራል መንግሥት ጋር አብረው እየሠሩ መሆናቸው የሚዲያዎቹን ትኩረት አለመሳቡ አጠያያቂ ነው። እንደ ሚዲያ ከአጠቃላይ ኢትዮጵያ እንዴት የአንድ ክልል ጥያቄ ብቻ የሌሎቹን ሆሉ ደፍጥጦ የዜና ርዕስ ሊሆን ይችላል? ወገንተኝነትና አድሏዊነትንስ አያሳይም? በማለት የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም።
አዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ አካባቢ የሚኖረው የጋምቤላ ክልል ተወላጅ ኦኬሎ ለጎልጉል ሲናገር የሚያስቀድመው ጥያቄ ነው። “አሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥት ተጣልተዋል? አሜሪካ አሁን ያለውን መንግሥት ለማውረድ ትፈልጋለች?” ይልና ራሱ ይመልሳል “ይልቁንም ድጋፍ እያደረገችና እያገዘች ነው”።
እንደ ኦኬሎ ገለጻ የአሜሪካ መንግሥት በግልጽ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጎን ከቆመ ቪኦኤ እንደ አንድ የአሜሪካ መንግሥት ተቋም የኢትዮጵያን መንግሥት ኅልውና አደጋ ላይ የሚጥል ፕሮፓጋንዳ ወይም የኢትዮጵያን መንግሥት ለማጥፋት አይሠራም። እርስበርሱ ይጋጫል፤ ባንድ በኩል ዕርዳታ እየሰጡ በሌላ በሚዲያቸው የተቃውሞ ፕሮፓጋንዳ ሊነዙ አይችሉም። ምክንያቱም ቪኦኤ የሚያንጸባርቀው የአሜሪካንን መንግሥት አቋ ነው። ስለዚህ አሁን በቪኦኤ ውስጥ የሚታየው የተሳከረ አሠራር የግለሰቦች አቋም ነጸብራቅ በመሆኑ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው ማሳወቅ ግድ ነው።
የጀርመን ድምጽ ሙሉ በሙሉ ተንጋዶ ከሙያዊ ምግባር የወጣ በመሆኑ ለረዥም ጊዜ አዳምጦ እንደማያውቅ የገለጸው ኦኬሎ፣ “ቪኦኤ ጃልመሮ የሃጫሉን ግድያ እንዲያስተባብል የጋበዘው ዕለት ነው በግል ለሚዲያው ያለኝ ክብር የሞተብኝ፤ በርካታ ንጹሃንን ጫካ ገብቶ የሚያስጨፈጭፍ ወንበዴ በኦሮሞ ልጆች ሳይቀር በተተፋበት ወቅት ቪኦኤ እንዴት ዕድሉን ሰጠው? ለምንስ በደንብ አልተሞገተም? እሱን በዚያን ወቅት ማነጋገር ለምን አስፈለገ? የሚሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡለት ቪኦኤ መልስ የለውም” በማለት ከዚያ የዘለለ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግ አስታውቋል።
ግርማ ገበየሁ ደግሞ የመንግሥትን የሕዝብ ግንኙነት ደካማነት ያነሳል። የተጠቀሱት ሚዲያዎች በተለይም ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ፈር እየለቀቀ የመጣ የትህነግ ድምጽ መሆናቸውን ማጋለጥና ህዝብ ሚናቸውን እንዲለይ ማድረግ ይገባዋል። አክቲቪስትና አገር ወዳድ ምሁራኖችም ሙያዊ ትችት ሊያቀርቡ ይገባል ይላል።
ግርማ እንደሚለው ትህነግ የመቃወም መብቱና ያሻውን የመናገር ዕድል ሊነፈገው አይገባም። በዚያው መጠን ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ክልሎች ዕድል መንፈግ ግን አግባብ አይሆንም። ሪፖርቱንም ዋጋ ያሳጠዋል።
ትህነግ “መንግሥት የለም። የመንግሥት ሚና ያከትማል” በማለት መናገሩ ችግር ባይኖረውም ሌሎች የፌደራል መንግሥት አካል የሆኑትን ልክ እንደ ትህነግ ሁሉ “መንግሥት አለ፤ እኛ መንግሥት ነን” በማለት ለትህነግ አስተያየት የአጸፋ መልስ መስጠት አለባቸው። ወይም ሃሳባቸውን ሊገልጹ ግድ ነው። ግርማ አያይዞም ሚዲያዎቹ ራሳቸውን ቢመረምሩና የሚያቀርቧቸውን የክልል ሪፖርተርቶች አየር ላይ ከመዋላቸው በፊት ሊያመጣጥኗቸው እንደሚገባ መክሯል።
እነዚህ ሁለት የሚዲያ ዘርፎች ባሉበት አገራት የሚመሯው ተቋማት በግብር ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ ናቸው። የአሜሪካና የጀርመን መንግሥታት በአቋም ደረጃ እየተከተሉት ያሉት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አብሮ መሥራት ነው። ታዲያ ለምን ይሆን እነዚህ የሚዲያ ድርጅቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚተጉ ድርጅቶች ይህንን ያህል ሽፋን የሚሰጡት?
እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በተለይ ግብር እየከፈለ በአሜሪካና በጀርመን የሚኖረው ዳያስፖራ ሁለቱ የሚዲያ ተቋማት ለሚገኙበት አገር እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። ይህንን በማድረግ የትህነግን ድብቅ አጀንዳ ማጋለጥና ማስቆም ይቻላል ብለው የሚምኑት ጥቂቶች አይደሉም።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Tesfa says
ጊዜው ቆየ እንጂ አንድ ቦታ የሥራ ማስታወቂያ አይቶ ለቃለ መጠየቅ የገባ ሰው የቆየ የስራ ልምድህ ምንድን ነው ተብሎ ሲጠየቅ ትንሽ አሰብ አረገና እረኝነት በማለት ሲመልስ ለቃለ መጠየቁ የተቀመጡት ሶስት ሰዎች ከት ብለው ሳቁ። እሱም ቆጣ ብሎ ምን ያስቃል። የረጅም ጊዜ የስራ ልምድ አላችሁ ለረጅም ጊዜ የሰራሁት የበግ እረኛ ሆኜ ነው አላቸው። ሰለጠን ያሉት ቃለ መጠየቅ አቅራቢዎች ግን ጭራሽ አልተረድትም። መማር መደንቆር መሆኑን አሁን በተለያዬ መንገዶች ስረዳ ይህ ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ ለብቻዬ ፈገግ ያረገኛል። አንድ ጊዜ ደግሞ ፒያሳ አካባቢ ከጓድኞቼ ጋር እየሄድን ራቅ ብሎ የቆመ ሰው ከት ብሎ ለብቻው እያወራ ይስቃል። አንደኛው ጓደኛችን ውይ ምስኪን አብዶ መሆን አለበት ሲል ሌላው ቀበል አድርጎ ያበድክ አንተ ነህ እሱ የሚስቀውና የሚጮኽው ለአንተ ያልታየህ ወልል ብሎ ታይቶት እንደሆነ በምን ታውቃለህ ሲለው ዝምታው ትዝ ይለኛል። ሌላ አንድ ነገር ልጨምር እና ተዛባ ወደ ተባለው የጀርመንና የአሜሪካ የሬዲዮ ዘገባ ስርጭት እመለሳለሁ። አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ቁጭ ብለን ሻሂ እየጠጣን አንድ ጢሙ የረዘመ ልብሶቹ ያልገጠሙት መልከ መልካም ሰው ከጎናችን ካለው መቀመጫ ላይ ተቀመጠ። ከዚያ በጎኑ ከቆመው ጋዜጣና መጽሄት መካከል ታይም የሚለውን አነሳና ዝቅዝቆ ያነበው ጀመር። አንድ እሱን የሚያውቅ ሰው ዘው ብሎ ገባና እንዴ ዘቅዝቀህ እኮ ነው የምታነበው ቢለው ለእኔ የሚገባኝ እንደዚህ ሳነበው ነው በማለት ሁላችንም አሳቀን። ያ ሰው በአንድ እውቅ የአሜሪካ የትምህርት ተቋም በፊዚክስ ፒ ኤች ዲ ያለው መሆኑን ቆይተን ነው የተረዳነው። ህይወት እንዲህ ናት።
አሁን ያለንበት ዓለም ለዜና ስርጭት የሚበጅ አይደለም። ግማሹ የፈጠራ፤ ሌላው የተቀዳ፤ ቀሪው ደግሞ ሆን ተብሎ ሌላውን ለማምታታት የሚናፈስ ለመሆኑ እማኝ አያስፈልግም። የሚገርመው ይሻላሉ የተባሉት የዜና ስርጭት አውታሮች ሁሉ ከቀጥታም ሆነ ከተዘዋዋሪ የመንግስትና የኮርፖሬሽን ተጽኖ ነጻ አለመሆናቸው ነው። ስበር ዜና/መረጃ ተብሎ የሚነበብልን በማር የተለወሰ ውሸት ሆኖ እናገኘዋለን። ለነጻነትና ለህዝቦች እኩልነት ተብሎ የሚደለቀው ከበሮና የሚከረከረው ክራር የህዝባችን እንባ የሚያባብስ ሌላውን ከቀሪው ጋር የሚያላትም ጭራሽ የእውነት ጠብታ የሌለበት የውሸት ፈጠራ ቅምር እንደሆነ ወዲያውኑ ወይም ዘግይቶ ይገባናል። data analytics coupled with corporatocracy and surveillance capitalism ተንከባሎና ተበጥሮ ሲቀርብ ዜናውም ሆነ የኢኮኖሚ እድገቱ የጧት ጤዛ እንደሆነ አይናችን እያየ ነው። ትላንት አስፈራርተውም ሆነ አታለውና ሰርቀው ራሳቸውን ቆንጮ ላይ አስቀምጠው ሲያምሱ የነበሩ ሃያላን መንግስታት ዛሬ ከጎናቸው በእኩልነት የሚቆሙ ሃገሮች በመብዛታቸው ተደናግጠዋል። የቻይና ሳይታሰብ አሜሪካን ለመቀደም ካልሆነም አቻ ለመሆን የምታደርገው ሩጫ ፍርሃት ለቆባቸዋል። በብራዚል፤ በህንድ፤ በፓኪስታን፤ በኢራን በሌሎችም ሃገሮች ሰው ንቃቱ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የፈጠራ ወሬአቸውም ኢላማውን በታዳጊ ሃገሮች ላይ ይበልጥ ማፋፋሙ አይቀርም። እኛ ያንኑ የፈጠራ ወሬ ሰምተን እንዘጥ እንዘጥ ማለታችንና ከአጥፊ ሃይሎችና በዘር ከሰከሩ የጎሳ ፓለቲከኞች ጋር መሰለፍ እብደቱን ሰማይ አድርሶታል። አለም በሁለት ካምፕ ተከፍላ በነበረ ጊዜ ” አለም የሰርቶ አደሮች ትሆናለች” በማለት ሲያፋክሩ የነበሩ ሙታኖች ናቸው ዛሬ በቋንቋዬ ካልሆነ እቃ አልሽጥም ላናግርህም አልፈልግም የሚሉት። ቋንቋው ወንዝ የሚያሻግር ቢሆን ኑሮ እንዴት ማለፊያ ነበር። ግን አይደለም። ይህ ማለት ሰው በሚገባው ቋንቋ አይገልገል ማለት አይደለም። መዳብ በእጁ ይዞ ግን ወርቅ ነው ማለት ማበል ነው። የጀርመኑም ሆነ የአሜሪካው የወሬ አናፋሽ አውታሮች ያው እንደ ደሮ ከተቆለለው ገለባ ሲጪሩ ቆይተው ካገኙት እንክርዳድንና ቀኑ ብሩህ ከሆነም አንዳንድ ስንዴ ነክ ወሬዎችን ማናፈሳቸው ለመኖር የሚደረግ መፍጨርጨር እንጂ አለማችን አሁን ባለው ሁኔታ በማንም ይሁን በምንም የዜና አውታር ያልተዛባ ዜና ያቀርባሉ ተብሎ መጠበቅ ራስን ማታለል ነው። አፍሪቃዊውን ፈተና የባሰ የሚያደርገው ደግሞ ዘር፤ ቋንቋና ሃይማኖትን ተገን ያደረገ የተዛባ ዜናና ፍትጊያ ነው፡፡ የወያኔው አቶ ጌታቸው ረዳ “እኛ ኢትዮጵያን አናድንም” የሚለን የትግራይን ህዝብን እያወናበደ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ያሰቡትን ሴራ እውን ለማድረግ እንዲመቻቸው ነው። ከሆነ ማን እንደሚጎዳ ጊዜ ያሳየናል። ሰው በቆፈረው ጉድጓድ ወድቆ ሲጎድ ከማየት የበለጠ የሚያሳዝን ነገር የለም። ያው ግን ገጣሚው እንዳለው እውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ጉድጓድ እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር ብሎናል። እውነት በእርግጥ አለች? በቃኝ!
መለስ በላይ says
ይህን ጹሁፍ በግርድፉ ኣንብ ቤው በጣም ወድጄዋለሁ
እባክህ ንገራቸው ልክ ልክኣቸውን ደደቦችቢሆኑም ትንሽ ቢስማቸው!!!
ኣመሰግንሃለሁ ቀጥል እባክህ!!!
ዘረ-ያዕቖብ says
ምንም እንኳን ሂትለርና ሙሶሎኒ ጓደኞች ሆነው እያሉ (ለጓደኝነታቸው ምልክት፣ ሙሶሎኒ ኒትቸን በኩፉኛ ይወደው ስለነበረ፣-ጉልበተኛ ይደምስስ animalizm theories politics አቀንቃኞች- ሂትለር ሞሶሎኒን በጎበኘበት ጊዜ፣ የኒትቸን ጠቅላላ ስራዎችን (መፃህፍትን) እንደ ስጦታ ይዞለት ቀረበ) ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ግን በመጀመርያ ስዓታት አካባቢ ላይ በማሾለክ ሂትለር ለኢትዮጵያ ተልካሻ የመሳርያ “እርዳታ” አድርጎላት ነበር:: “እርዳታው” ግን ለኢትዮጵያ ታስቦላት ሳይሆን የሙሶሎኒን ድል ለማዘጋየት ታስቦ ነበር:: መለትም የአሻጥር እርዳታ ብቻ ነው ሊባል የሚችለውና፣ ይሄ ታክቲክ ደግሞ እስካሁንም አለና ማንኛሽም ሳትመነጥሪ መጠርጠርን አትርሺ…………………!!