በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ የሰላም መደፍረስ እና የጸጥታ ሥጋቶችን ለመቀልበስ ትኩረት እያደረገ በነበረበት ወቅት በሕገ-ወጥ የማዕድን ምርትና ዝውውር የተሰማሩ አካላት በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎችና አሸባሪ ቡድኖች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠር በኢኮኖሚው መስክ አስተዋፅዖ ባላቸው የማዕድን ምርቶች በተለይም በወርቅ ላይ ያተኮረ ዝርፊያ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡
የማዕድን ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የነበረው ድርሻ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ወደ ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት እንዳይሸጋገሩ ችግሮችን የሚለይና መፍትሄ የሚያስቀምጥ ሀገር አቀፍ ካውንስል ተቋቁሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል፡፡
ካውንስሉ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የድርሻውን ስምሪት በመውሰድ በተለይም ከወርቅ ምርት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችንና የጥቅም ትስስሮችን በተመለከተ ጥልቅ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱንም ነው የገለጸው።
ጥናቱን መነሻ በማድረግም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በጥናቱ እንደለየው ቁልፍ የማዕድን ሀብቶች ኢኮኖሚውን እንደ ሀገር ለመደገፍ እምቅ አቅም ያላቸው ቢሆንም የምርት ሂደቱና ግብይቱ ሕጋዊ ስርዓትን ተከትሎ እየተካሄደ እንዳልነበረ ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡
በተለይም ወርቅን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ከማምረት ባሻገር የሀገሪቱን ሕጋዊ ሥርዓት በመከተል ወደ ብሔራዊ ባንክ ከማስገባት ይልቅ ከሽብር ቡድኖችና ለሕገ-ወጥ ድርጊቱ ተባባሪ ከሆኑ አካላት ጋር በመቀናጀት በሀገር ሀብት ላይ ዘረፋ ሲፈጸምና ሀገራዊ የደኅንነት ሥጋቱ እንዲባባስ አስተዋጽዖ ሲያደርግ እንደነበርም ተደርሶበታል ነው ያለው፡፡
እምቅ የማዕድን ሀብት ከሚገኝባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የሆነ የምርትና የግብይት ችግር የሚታይበት መሆኑ በጥናቱ መለየቱንም አብራርቷል።
በባህላዊ መንገድ ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል ሶጂር፣ ሽምብል፣ እሌኒ እና ኑኑ የተባሉ አራት ወርቅ አምራች ማህበራት ከውጭ ዜጎች ጋር በጥቅም በመተሳሰር የሀገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ የወርቅ ማዕድኑን በሕገ-ወጥ መንገድ በማምረትና ከሀገር ውጭ በስውር በማስተላለፍ ወንጀል በተባባሪነት መሰማራታቸው እንደተደረሰበት ገልጿል።
የእነዚህ ማህበራት አመራሮችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የጥቅም ተጋሪዎቻቸውም በሕገ-ወጥ መንገድ የተመረተው ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዳይገባ ድርሻ እንደነበራቸው በመረጃ ስምሪትና ክትትል ታውቋል ነው ያለው፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው የተቀናጀ ክትትልና ኦፕሬሽን 28 የቻይና እና አንድ የሱዳን ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም ሁለት በሕገ-ወጥ ድርጊቱ ተባባሪ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የማህበራቱ ሥራ አስኪያጆች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አረጋግጧል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ወደ ሀገር ውስጥ በሕጋዊ ሽፋን ቢገቡም በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው፤ ባልተፈቀደላቸው የሥራ መስክ መሰማራታቸው እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ በወርቅ ምርት፣ ግብይትና ወደ ውጪ ሀገር የማስተላለፍ ተግባር ላይ ሲሳተፉ እንደነበር ማረጋገጥ እንደተቻለ አብራርቷል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከልም ሱዚህን ወይም ሱዛን በመባል የምትታወቀው ቻይናዊት ግለሰብ በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይቱ ተግባር ቁልፍ ሚና እንደነበራት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል አረጋግጧል፡፡
ግለሰቧ ሌሎች ቻይናውያን ግብረ አበሮቿን ሞስ (MOSS) የተባለ ስያሜ ባለው የእብነበረድ ኩባንያ ሽፋን ሰነድ በማዘጋጀት በሕገ ወጡ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ፤ የሎጀስቲክ አቅርቦት በማመቻቸት እንዲሁም ደመወዛቸውን ወደ ሀገራቸው በመላከ ሕገ-ወጥ የወርቅ ምርትና ግብይቱን በበላይነት ስትመራ እንደነበርም ገልጿል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቱሪስት፣ በሥራ፣ በኢንቨስትመንትና በጊዜያዊ ቪዛ አማካኝነት ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት የኢሚግሬሽን ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገ-ወጥ መልኩ የመኖሪያ ፈቃድ አሠርተው በኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖሩ እንደነበር በተወሰደው እርምጃ በሕግ ቁጥጥር ስር ሲውሉ በኢግዚቢትነት ከተያዙት ሰነዶች ማረጋገጡንም ጠቅሷል፡፡
ከተጠርጣሪዎች የውጭ ዜጎች መካከል 23ቱ ከዚህ ቀደም በፈጸሟቸው የተለያዩ የማጭበርበር ተግባሮች ምክንያት በፍርድ ቤት ተከሰው በዋስትና የወጡ ቢሆንም፤ በድጋሚ በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ተሠማርተው መገኘታቸው በተደረገው የማጣራት ሥራ መታወቁንም ተናግሯል፡፡
በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪ ቻይናውያን ወደ ሀገር ውስጥ የገቡበት ሁኔታን በሚመለከት በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ለማጣራት እንደተቻለው ግለሰቦቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በማዕድን ኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት እንዳልሆነ መረጋገጡንም ነው ያብራራው።
ከኤምባሲው ጋር በመነጋገርም በወንጀሉ ተሳትፎ የነበራቸው ቻይናውያን ከሀገር እንዲባረሩ መደረጋቸውን ገልጿል።
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉ ግለሰቦችም በእነ ሱዛን የሚመራው የቻይናዎቹ ሕገ-ወጥ ወርቅ የማምረትና የማስተላለፍ ተግባር ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት የነበረበትን የወርቅ መጠን በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ይልቅ የእነርሱን ትርፍ ብቻ ማዕከል ያደረገ መሆኑን በማንሳት፡፡
በዘርፉ የሚታየውን ሕገወጥነት ለመግታት እርምጃ መውሰድ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን እንደጨመረ አሃዛዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የብሔራዊ ባንክን ወክሎ ወርቅ በመረከብ ላይ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሶሳ ቅርንጫፍ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ሀገር አቀፍ ካውንስሉ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ባሉት ጊዜያት በሳምንት ወደ ባንኩ የሚገባው የወርቅ መጠን ዝቅተኛ ነበር፡፡ አሁን ግን በሳምንት እስከ 10 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ባንክ እየገባ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሶሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስዩም ገብሬ ስለመጣው ለውጥና ለዚህ ምክንያት ስለሆኑት ጉዳዮች ያብራራሉ፡፡
በሕገ-ወጥ መንገድ ሲመረት የነበረው የወርቅ ማዕድን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ከማስከተሉም ባሻገር በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩም በጥናቱ ተመላክቷል፡፡
በተለይም ወጣቶች በወርቅ ማምረት ዘርፍ የነበራቸውን የሥራ ዕድልና ተጠቃሚነት በማሳጣት ለስደትና ለማኅበራዊ ቀውስ እየዳረጋቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በተያያዘም የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ለኅብረተሰቡ ጥቅም፣ ለውጥና ተስፋ ከማምጣት ይልቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግራቸው እንዲባባስ ማድረጉም ነው የተነገረው፡፡
ሕገ-ወጥ ተግባሩ ደቅኖት ከነበረው ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ አደጋ ባሻገር የአካባቢ ብክለት ሲደርስ እንደነበር የጥናቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
በሕገ-ወጥ የወርቅ ምርት የተሠማሩት ቻይናውያን የተመረተውን ወርቅ የተለያዩ ኬሚካሎችን በመጠቀምና ሌላ ቁስ በማስመሰል ከሀገር በማስወጣት የወንጀል ድርጊት ከመሰማራታቸው ባሻገር፤ በምርት ሂደት የሚጠቀሙበት ኬሚካል በአካባቢው ስነ-ምሕዳርና በነዋሪዎች ላይ የረጅም ጊዜ ጉዳትና ተፅዕኖ የሚያስከትል መሆኑም ተረጋግጧል።
መንግሥት የማዕድን ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሕገ-ወጥ የምርትና የግብይት ስርዓቶችን በመፈተሽ መውሰድ ከጀመረው የእርምት እርምጃ ጎን ለጎን በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በሚመራው ካውንስል የወርቅ ምርቱ እና ግብይቱ ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ እንዲፈፀም በቅንጅት እየተሠራ ነው ብሏል፡፡
በቀጣይም የውጭ ሀገር ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ በወርቅ ምርት፣ ግብይትና ማስተላለፍ እንዲሰማሩ ያደረጉ ማህበራትና አመራሮች በወንጀል ድርጊታቸው እንደሚጠየቁ በመግለጽ፤ ተመሳሳይ ድርጊት በሚፈጽሙ ሌሎች አካላት ላይ የሚደረገው ክትትልም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አረጋግጧል፡፡
ኅብረተሰቡ በሕገ -ወጥ ድርጊቱ ላይ የተሰማሩ የውጭ ዜጎችን በማጋለጥና መረጃ በመስጠት በኩል ለነበረው የላቀ አስተዋጽዖ ምስጋና በማቅረብ፤ በቀጣይም ከማዕድን ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለሀገር እድገትና የዜጎችን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችል አግባብ ለመምራትና ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል በሚደረገው ስምሪት ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል፡፡ (ኢዜአ)
ከሁለት ወር በፊት ታከለ ኡማ ከማዕድን ሚኒስቴር ሥልጣኑ ከተነሳ በኋላ የመዐድን ሌቦች እየተያዙ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል። “ታከለ ከተነሳ በኋላ የመዐድን ሌቦች እየተያዙ ነው” በሚል ርዕስ የወጣው የዜና ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply