በማዕድን ዘርፍ ለማልማት ፈቃድ ከወሰዱ 250 መካከል እየሠሩ ያሉት 8% ብቻ ናቸው
ብዙ ሃሜታ የሚነሳበትን የመዐድን ሚኒስቴርን ሲመራ የነበረው ታከለ ዑማ በበርካታ የሌብነት ወንጀል ብዙ ሲባለበት ቢቆይም አገር ለቅቆ መውጣቱ ይታወቃል። የእርሱን ከአገር መልቀቅ ተከትሎ ከመዐድን ሚኒስቴር አካባቢ የሚሰሙት መረጃዎች መሥሪያ ቤቱ ምን ያህል ሲመዘበር እንደቆየ አመላካች ሆኗል። የተያዙት ግለሰቦችም ስለዚህ ጉዳይና እስከ መንግሥት መዋቅር ስለ ዘለቀውን የሌብነት መስተጋብርም የሚሉት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።
በየቤኒሻንጉል ጉሙዝ በማዕድን ልማት ለመሰማራት ፈቃድ ከወሰዱ ከ250 በላይ አልሚዎች መካከል ወደ ሥራ የገቡት 20 ብቻ እንደሆኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ በሕገ ወጥ መንገድ ወርቅ ሲያዘዋውሩ የተገኙ 45 የውጭ አገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል አሕመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ካሉት ማዕድናት የወርቅ ምርት ቀዳሚ ሲሆን የድንጋይ ከሰልና እብነበረድም በክልሉ ካሉ እምቅ የማዕድን ሀብቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።
ክልሉ ካለው የማዕድን ሀብት አንጻር የሚፈለገውን ጥቅም እያገኘ እንዳልሆነ የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፤ መንግሥት ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ 35 በመቶ ማበረታቻ ቢሰጥም በሚፈለገው ልክ አልገባም ብለዋል። በዚህ አመት የተገኘው የወርቅ ገቢ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው፤ ወርቅ አምርተው በቀጥታ ባንክ እንደሚያስገቡ ውል ወስደው ወደ ሥራ የገቡት ከ200 በላይ የሚሆኑ ፈቃድ የተሰጣቸው የወርቅ አዘዋዋሪዎች አሉ ሲሉም አክለዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት ወርቅ ለማስገባት ባንክ ቤት ገብተው እንደማያውቁ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ካሚል ገለጻ፤ በክለልሉ በወርቅ ማምረትና አዘዋዋሪነት ፈቃድ ከተሰጣቸው ውስጥ የትኞቹ ወደ ባንክ አስገቡ፣ የትኞቹስ አላስገቡም የሚል የልየታ ሥራ በመሥራት ወደ ባንክ ባላስገቡት አካላት በፈቃድ አስተዳደር መመሪያ ደንቡ መሠረት እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል። ሥራ ውስጥ ያልገቡትንም በቀጣይ ወደ ሥራ ለማስገባት ቢሮው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ነው።
ሕገ ወጥ የወርቅ ዝውውሩ በጌጥ መልክና ሌሎች ስውር ዘዴዎችን በመጠቀም የሚከናወን ነው ያሉት አቶ ካሚል፤ ሕገ ወጥ ዝውውር በመደረጉ በወርቅ ምርት ላይ የተገኘው ገቢ ዝቅተኛ ሆኗል። የቁጥጥር ሥርዓቱም በልኩ አልነበረም። ስለዚህ አሁን ላይ በወርቅ ምርት ላይ የገቡ አልሚዎችን ቁጥጥር ማጠናከር አንዱ እርምጃ ነው። በተጨማሪም በተለያዩ ኬላዎች፣ ከክልሉ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል፤ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሕገወጥ መንገድ የሚካሄደው ሕገ ወጥ የወርቅ ዝውውር መቆጣጠር ላይ ቀጣይ ትኩረት የተሰጠው እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፤ ፈተናው በወርቅ አዘዋዋሪዎችና አምራቾች ላይ ወደ ባንክ ከሚያስገቡ ይልቅ በሕገ ወጥ መንገድ የተሻለ ገቢ ስለሚያገኙ ለቁጥጥር አንዱ ፈታኝ የሆነ ጉዳይ ነው። ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለማግኘት መቸገር፣ አየር መንገድም የፍተሻ ማሽን እንዳይለየው የሚያስችል ኬሚካል እየቀቡ የሚያዘዋውሩ ስላሉና ወርቅ በባህሪው ትንሽ ስለሆነ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።
አቶ ካሚል 45 የውጭ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት ምርመራ ቡድን እየታየ ነው። ሌሎች 5 ሰዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤትና በአስተዳደራዊ መንገድ ታይቷል ነው ያሉት።
የእምነበረድና የድንጋይ ከሰል ምርት ፍቃድ ከወሰዱ ከ250 በላይ አልሚዎች 20 ያክሉ ብቻ ወደ ሥራ መግባታቸውን የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው፤ ሌሎች ሥራ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም መግባት አልቻሉም። ሥራ ውስጥ መግባት ያልቻሉበት ዋና ምክንያት በፀጥታ ስጋት ሲሆን ይህም ከክልሉ ውጪ ባሉ መንገዶች ላይ የሚፈጠር ነው። በክልሉ ግን ጠረፋማ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር አብዛኛው አካባቢ ላይ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር ባለመኖሩ ማሠራት የሚችል ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ባለፉት ወራት በማዕድን ዘርፍ በልዩ አነስተኛ የወርቅ ማህበራት፣ በእምነበረድና በድንጋይ ከሰል ሥራ ለ2 ሺህ 250 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ1ሺህ 765 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎች እና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡ (ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ሌላውም ሰርቆ ሲጠግብ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ይሻገራል። ታከለ የት እንዳለ ታውቃላችሁ? በሃገር ውስጥ የለም። የወረፋ ዘረፋ ነው የተያዘው። በእውነት በብልጽግናው መንግስት የምንሰማው የቃላት ድርደራና እውነት እየተላለፉ ተቸግረናል። ትላንት አበጀህ ያሉት አሁን ላይ ጠ/ሚሩን አይንህ ላፈር የሚሉትም ለዚህ ይመስለኛል። ለመሆኑ የሚታሰረው፤ የሚደበደበው፤ ቤቱ የሚፈርስበት፤ የሚገደለው፤ ቋንቋ አትችልም ተብሎ ከሥራ የሚባረረው ስንቱ ነው? ይህ ግፍ ሁሉ የሚደርሰውስ በማን ላይ ነው። ዛሬ ጎንደር – ወረታ ላይ መንገደኞች ወደ ባህርዳር እንዳሄድ ያገቷቸው ቋንቋቸውን የአካባቢው ሰው የማይረዳው የኦሮሞ ታጣቂዎች ናቸው። ሃገሪቱ በዘር ፓለቲከኞች ባቢሎን ሆናለች። ከየት ተነስተን ወዴት እየሄድን ነው? ምን እያሰብን ምን እያደረግን ነው? ዋ በህዋላ የማይበርድ እሳት ይለኮስና አመድ ታቅፈን እንዳንቀር እሰጋለሁ።
ዛሬ ገነት አስማማው – የየኔታ ቱብ ጋዜጠኛን ለእርድ እንደሚጎተት ፍየል እያስለፈለፉ አፍነው የወሰዷት በምን ወንጀል ይሆን? በዚያ ላይ ስድቡ፤ ዝልፊያው፤ ጥፊው ይህ ነው የአብይ መንግስት። እንደ ወያኔ ድርቡሽ። ያለምንም ቅድመ ዝግጅትና ምክክር የአማራ ልዪ ሃይል ትጥቅ መፍታት አለበት በመባሉ ተከበው ተታኩሰው የሞቱ እንዳሉ እየተወራ ነው። ይህ እውነት ከሆነ እጅግ ያሳዝናል። ያ ከሰራዊቱ በፊት ቀድሞ ከወያኔ እሳት ያዳነውን የአማራ ልዪ ሃይልና ፓሊስ እንዲሁም ሚሊሻ ሻሬ በሃገሪቱ ሰራዊት ማስገደልና ማሳደድ ይቅር የማይባል ወንጀል ነው። ስለዚህ ሌባን ሌባ እየተካው (የጠገበው በተራበ እየተተካ) ትላንት የገረፈው መልሶ ስልጣን ላይ ቁጭ እያለ፤ ያኔ የታሰሩት ዛሬም እየታሰሩ ሃገር ለውጥ ናት ላይ ማለት በጭራሽ የማይመስል ጫወታ ነው። ለመሆኑ ጋዜጠኛዋን ያፈኗት ፓሊሶች ዘርና ጾታን እየጠቀሱ እንዲሰድቧት ማን ፈቀደ? ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ያሉት አበው ግፈኞች ሲፈነጩ ተመልክተው ነው። የምድሪቱ ፓለቲካ የመገዳደል ፓለቲካ ነው። በንጉሱ ጊዜ በላይ ዘለቀ አንገት ላይ ገመድ ሲገባ ቆሞው ያዪ በወረፋ እነርሱም እንዳልሆኑ ሆነዋል። የያኔው ሻለቃ በህዋላ ጄ/መንግስቱ ንዋይም በላይ ዘለቀ ሲሰቀል ቆሞ ያየ ነበር። እሱም በወረፋው ያው በዓላማው አንገቱ ላይ ገመድ ገብቷል። ባጭሩ ከታህሳስ ግርግር ጀመሮ አሁን እስካለንበት የአፓርታይድ ፓለቲካ ድረስ ሥራችን ሁሉ ገድሎ መሞትና መገዳደል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ የወያኔን አመራር የጠላው በጭካኔአቸው እንጂ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው አልነበረም። አሁን እነርሱን ተክተው ምድሪቱን የሚፈነጩባት የኦሮሞ ፓለቲከኞች ግባቸው ምን ይሆን? አሁን ማን ይሙት ስብሃት ነጋና ጭፍራዎቹን ከሥር የፈታ መንግስት ዛሬ ላይ እስር ቤት የሚያስቀረው ሰው ይኖራል? ግን ፓለቲካው ወልጋዳ ነው። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ህሳቤ ገና ብዙ መዘዝ ይመጣል። ስለዚህ ይህ ጉቦኛ ተያዘ፤ ያ ከሃገር ኮበለለ፤ ይህ ደግሞ ተሰወረ እየተባለ የሚወራው እኛኑ ለማደናገር እንጂ ሌብነትና ሃበሻ ተራርቀው አያውቁም። እህቱን፤ ወንድሙን እናቱን የሚያታልል በቁሳዊ ፍቅር አይኑ የታወረ ሃገርን ሳይሆን ራስን ለማበልጸግ ከሚሯሯጥ የጎጥ ፓለቲካ ሰካራም ጋር ምንም አይነት ሃገራዊ አንድነትና ህብረት አይገኝም። ያኔ ጠ/ሚሩ ወደ ስልጣን ላይ ሲወጣ የዘፈናችሁ፤ ጮቤ የረገጣችሁ፤ የሃገሪቱን ብሩህ ተስፋ ያያችሁ አሁን መጨለሙን ስታዪ ምን ትሉን ይሆን? ጠብቁ ገና ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል። በዘርና በቋንቋ በክልል የተከፋፈለ ሃገር ህብረ ብሄራዊነት የሌለው የሎሚ ካብ ነው። ይናዳል። ብዙዎችን ይበላል። ፍልሚያው በመኖርና ባለመኖር መካከል ስለሆነ ሁሉም ነገር በጊዜ ካልተስተካከለ የሁሉንም አይን አጥፍቶ የእውራን መንደር ይፈጥራል። ያኔ ማን ተመሪ ማን መሪ እንደሚሆን እናያለን። ግፍ በሃበሻ ምድር መቆም አለበት። የሰው እንባ የማያቋርጥ ጅረት የሆነባት ምድር ከዪክሬን ቀጥላ ኢትዮጵያ ናት። በቃኝ!