የግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ሴራ እና ተንኮል መጋለጫ፣ የሩብ ምዕተ ዓመት አምባገነናዊ አገዛዝ መሸኛ፣ የሦስት አስርት ዓመታት የጨለማ ጉዞ ምዕራፍ መቋጫ እና የአዲሱ ትውልድ የነጻነት አደራ ርክክብ ትናንት በቅርቡ የተስተዋለ ክስተት ነበር፡፡ እልፎች ማንነታችን ይከበር ብለው አደባባይ ድረስ ዘልቀው በመውጣት የከበረ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ከተፈጥሯዊ ነጻነት ባሻገር የጠየቋቸው እና ለትግል የሚያበቁ አያሌ ምክንያቶች ነበሯቸው፡፡
ማኀበረሰባዊ ማንነትን የሚያስቀጥል ትግል ደግሞ በትውልድ ቅብብሎሽ መካከል የሚጸና የነጻነት መርከብ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለማንነት መከበር በሚደረግ ትግል ውስጥ ውስኖች እንደ አብሪ ኮከብ ጎልተው ቢታዩም የትግሉ ባለቤት እና ሞተር ግን ሕዝብ መኾኑ አይካድም፡፡ የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ ሕዝብ የዘመናት የነጻነት ትግል መልህቅ በታሪክ አጋጣሚ በአዲሱ ትውልድ መዳፍ ውስጥ ገብቷል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በጀቱ የሕዝብ ቁጭት እና ብሶት ነው ያሉት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ናቸው፡፡ የወልቃይት ወረዳ በቅርቡ ያስገነባቸውን የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አጠናቆ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓተ ላይ የተገኙት የዞኑ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኅላፊው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብን ለዘመናት ሞት፣ ስደት እና እንግልት ከዳረጉት የህወሐት ፖለቲካዊ ሸፍጦች መካከል አንዱ ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት አለመኖር እንደነበር አንስተዋል፡፡
ለዘመናት በማንነቱ ምክንያት ፍትሐዊ ልማት ናፍቆት የኖረ ሕዝብ በጥረቱ የሠራውን የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በማየት ትናንት የበደሉን ሁሉ ሊሸልሙን እና ሊያመሰግኑን በተገባ ነበር ብለዋል፡፡
ወልቃይት ጠገዴ በርካታ የመልማት ጸጋዎች እና አቅሞች ያሉት አካባቢ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በህወሃት አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ ውስጥ እንዲቆይ በመገደዱ ለከፋ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኀበራዊ ስብራቶች እንዲዳረግ አድርጎት እንደቆየ ኮሎኔል ደመቀ አንስተዋል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በተለያዩ የትግል ስልቶች እና አማራጮች የተጫነበት የባዕድ ማንነት እንደማይገልጸው ተናግሯል፡፡ ነገር ግን የነበረው ሥርዓት ነባር ባለእርስቶችን አፈናቅሎ የእኔ ነው የሚለውን ማኀበረሰብ ማጽናት በመኾኑ የሕዝብን ጥያቄ በኃይል ለማፈን ብዙ እርቀት ተጉዞ ነበር፡፡
የወልቃት ወረዳ ማዕከል የኾነችው ወፍ አርግፍ ከተመሠረተች አያሌ ዓመታትን ብታስቆጥርም ይህ ነው የሚባል የመሠረተ ልማት ግንባታ የላትም፡፡ ኮሎኔል ደመቀ እንደሚሉት በከተማዋ መካከል አልፎ የሚሄደው የአስፓልት መንገድ የተሠራበት ዓላማ ግልጽ ቢኾንም ወፍ አርግፍን ሳይነካ እንዲያልፍ ለማድረግ የተሠራውን ሴራ ሕዝብ ያውቀዋል ብለዋል፡፡ በሕዝብ እምቢተኝነት መንገዱ በከተማዋ መካከል አልፎ እንዲሄድ ቢገደዱም፡፡
ኮሎኔል ደመቀ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ የነበረውን መዋቅራዊ ሴራ በሚገባ ተረድቷል ነው ያሉት፡፡ “የማንንም ርስት አልፈን አልነካንም፤ ያስመለስነውም ለረጂም ጊዜ ታግለንና መስዋእትነት ከፍለን ማንነታችንን ነው” ብለዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ የወልቃይትን እውነት መመስከር እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ እና አሥተዳደር አሁን በሙሉ አቅሙ ልማት ላይ ነው፡፡
“ከማንም ጋር ግጭት አንፈልግም በማንነታችን ላይ ግን ዳግም ለአፍታ እንኳን ተዘናግተን የተራዘመ መከራ እና ባርነት ለመቀበል ፍጹም የማንፈቅድ መኾኑን ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኅላፊው፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር በሀገረ አሜሪካ ገብቶ የሚነዛውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እየሰማን ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የትግራይ ሕዝብ በውሸት መመራት ይበቃኛል ማለት አለበት ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይ መገናኛ ብዙኀኖች ሳይቀር የሚሰብኩትን እና የሚጎስሙትን የጦርነት ነጋሪት ሊገነዘበው እንደሚገባም ኮሎኔል ደመቀ ተናግረዋል፡፡
ህወሃት አካባቢውን የግጭት ቀጠና ለማድረግ የሚሠሩትን ዘርፈ ብዙ ሙከራ በሚገባ እናውቃለን ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ። የተለየ ሃሳብ እና ፍላጎት ያለው ሁሉ ሃሳቡን አደባባይ አውጥቶ ይሞግት፤ ሃሳብ ያሸነፍል ወይም ይሸነፋል፡፡
ይሁን እንጅ ውስጥ ለውስጥ መሄድ እና የአካባቢውን ሕዝብ ዳግም የማያባራ ዋጋ ለማስከፈል የሚደረግ የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ ተገቢነት የለውም ብለዋል፡፡ (አሚኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Miherete Tibebe says
WOW!!!!
Tesfa says
እግዚአብሄር ለዚህች ዓለም ግድ የለውም – ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ። መልካም አባባል ነው። ዓለምን የሚሾፍሯት ጉልበተኞች ነው። በተለይ በሃበሻዋ ምድር ከትውልድ ትውልድ ሰዎች እንባ የሚያፈሱባት፤ ስቃይ የሚቀበሉባት፤ ሁሌም አካኪ ዘራፍ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚባልባት የግፍ መሬት ለመሆኗ ካለፈው ታሪክዋ ተነስቶ አሁን ጣራ ላይ የወጣውን ሰው በሰው ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ማየት መረጃ ይሆናል። እልፍ ጦር መዛዥ፤ እልፍ ቃል እየደረደሩ ለሃገር ነው የሚሉ እቡዪች፤ ከዚያም አልፎ ለብሄሩ ነፍጥ አንስቶ ዝንተ ዓለም ሃተፍ ተፍ ያለው ሁሉ ተመልሶ የከፋ የድር አራዊት ሲሆን አይናችን አፍጠን አይተናል። እያየንም ነው።
አሁን እንሆ በአማራ ክልል የሚሆነው ሁሉ ምንም ለአማራ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም መሆኑን ከአሁኑ መረዳት ይቻላል። አማራ አማራውን እየገደለና እያስገደለ ለአማራ ህዝብ ቆመናል ማለት ቧልት ነው። በዚህ ፍጅት ትርፍ ያላቸው ኦነግና ወያኔ እንዲሁም የሃገሪቱን ሰላም ጭራሽ የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ብቻ ናቸው። ፋኖ ከተማን ተቆጣጠረ ይህን ምሽግ ሰበረ እያሉ ሰውን ለሞት ማመቻቸት ተገቢ አይደለም። ፌዴራል መንግስቱ ያለውን ሁሉ ሃይል ከተጠቀመ ተራራ ላይ መውጣት፤ ምሽግ ውስጥ መደበቅ፤ ወይም ጫካ ውስጥ መወሸቅ አያድንም። ፋኖ የፓለቲካ ጥያቄ ካለው ይህን ለመንግስትና ለዓለም ህዝብ ግልጽ አድርጎ ማስረዳት አለበት። ይህ ሲባል መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ ተጽኖ አላደረግም። አማራ በዘርና በቋንቋው እየተሰቃዬ አይደለም ለማለት አይደለም። ኦነግ በአማራ ህዝብ ላይ የሰራውና የሚሰራው ዶኮሜንት የተደረገ ተግባር ስለሆነ ዓሊ ሊባል አይችልም። የብልጽግናው መንግስት ወደ ልቡ ተመልሶ በምክክርና ነገሮችን በማርገብ ፋንታ ልክ ከወያኔ ጋር 3 ጊዜ እንደተፋለመው አሁንም ህግ አስከብራለሁ በሚል ሽፋን ህዝብን ማመሳቀል ዛሬን ብቻ ማየት ብቻ ይሆናል። የተገፋ ህዝብ ሆ ብሎ ሲነሳ ምንም ምንም አያስቆመውም።
የብልጽግናው መንግስት እልፍ ጊዜ በወልቃይትና በሌሎች የአማራ ቦታዎች ከመወሻከት ይልቅ እውነቱን ይዞ ቦታና ስፍራው ለአማራ ህዝብ ማስረከብ ነው። ከዚህ በዘለለ ወያኔን ለማስደስት የሚደረገው መገለባበጥ ሁሉ ህዝብን ለእልቂት የሚዳርግ ነው። አሁን በአማራ ክልል የሚደረገውም ወረራ አማራውን አዳክሞ ለወያኔ ለማስረከብ የታለመ እንደሆነ ማመን አያዳግትም። ውጊያው ለምን በአማራ ክልል ሆነ? የሚሞተውና የሚታሰረው ለምን አማሮች ብቻ ሆኑ? ፍርሃቱ ከየት የመነጨ ነው? ከላይ ኮ/ሉ እንዳሉት ከማንም ጋር ግጭት አይጠቅምም። ግን ወያኔ በወልቃይት ህዝብ ላይ ያደረሰውን ግፍ ያየ ዳግም ከወያኔ ሥር ከመሆን ተፋልሞ መሞትን ይመርጣል። ወያኔ በወልቃይት ህዝብ ላይ የፈጸመው በደል ጀኖሳይድ ነው። ግን ለጥቁር ደም ማን ገዶት? ለዚያውም ጥቁርን ጥቁር ሲገድለው እፎይታ እንጂ ማን ለምን ብሎ ይጠይቃልና! በማጠቃለያው ፋኖ ቋሚ መግለጫና አላማ ለህዝብና ለመንግስት ይፋ ሊያረግ ይገባል ዝም ብሎ በለውና በይው ለማንም አይጠቅምም። ሞት ይብቃ፤ ሰላም ለሃገራችን ይሁን!