
ሃራ ወይም ነጻ ተብሎ በሚጠራው መሬት ላይ ሠፍሮ የሚገኘው “የትግራይ የሰላም ኃይሎች” (TPF) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል በያዝነው ዓመት መጨረሻ ሙሉ ትግራይን እንደሚቆጣጠር አስታወቀ። “ጸጥተኛ” ብለው ለሚጠሩት አቢዮት ሠራዊቱ እየተዘጋጀ እንደሆነም ተነግሯል።
ይህ የተገለጸው በፈረንሳይኛ ቋንቋ በድረገጽ የሚታተመውና አፍሪክ XXI (Afrique XXI) የተባለው ጋዜጣ ከጥቂት ቀናት በፊት በትግራይ ላይ በሠራው ዘገባ ነው። ዘገባው በሃራ ምድር የሰፈሩትን የትግራይ የሰላም ኃይል/ቲፒኤፍ ተብለው ከሚጠሩት ታጣቂዎች ጋር ቃለ ምልልስ ካደረገ በኋላ ነው።
የሰላም ኃይሉ አባላት በአብዛኛው ከዚህ በፊት በትህነግ ሥር ከነበረው የትግራይ መከላከያ ኃይል ወይም ቲዲኤፍ (TDF) ከሚባለው ከድተው የወጡ ናቸው። በተለይ ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በብዛት ከቲዲኤፍ እየኮበለሉ ወደ አፋር ምድር ሲገቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ባጭር ጊዜ ውስጥም በዕዝ የተደራጁ ሲሆን ማረጋገጥ ባይቻልም ከፌዴራል መንግሥቱም ሥልታዊ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን ዘገባው አመልክቷል። ዋና ዓላማቸውም አሁን ላይ ከሻዕቢያ ጋር የገጠመውንና ሕጋዊ ማንነቱ በምርጫ ቦርድ የተገፈፈውን ትህነግን ከሥልጣን ማስወገድ ነው።
ሸዊት ቢተው ጋዜጣው ካነጋገራቸው መካከል አንዷ ናት፣ “እዚህ የሚታዩ ባይሆኑም በሁሉም ቦታ ግን ወታደሮች አሉን” ስትል ቦታ እያመላከተች መብራሪያ መስጠቷን ጋዜጣው ዘግቧል። በአፋር ምድር ሆና ከጋዜጣው ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገችው ሸዊት “በሬጂመንቶች መካከል ውድድር እያካሄድን ነው” በማለት በስፍራው ከፍተኛ ፀሐይ ቃጠሎ ምክንያት ጠዋትና ማታ ላይ ስለሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ገልጻለች።
ሸዊት “ናፅናት” ተብሎ የሚጠራው ፓርቲ የቀድሞ አመራር አባል የነበረች ሲሆን አባቷ ቢተው ቀደም ሲል በትህነግ ውስጥ ነባር ከፍተኛ አመራር ነበር። ጋዜጣው እንዳለው ሸዊት የሰላም ኃይል ተብሎ በተቋቋመው የታጣቂዎች ቡድን አመሠራረት ላይ ተሳትፎ አላት።
ሌላው ጋዜጣው ያነጋገረው ሔኖክ ተስፋይ የተባለ የቀድሞ የቲዲኤፍ አባል “በጦርነቱ ጊዜ በምዕራብና በሰሜን ያሉትን ግዛቶች መልሰን መውሰድ ይገባን ነበር” ይላል። “ነገር ግን አዛዦቻችን በስሱ እንኳን እንዳንጠይቅ አስቆሙን፤ የነርሱ ብቸኛ ዓላማ ወደ አዲስ አበባ በመገስገስ ሥልጣን መልሶ መያዝ ነበር። ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ኮሎኔሎቹና ጄነራሎቹ የትህነግ ወታደሮች እንደምንሆን ነበር የነገሩን፤ እኛ ግን የተዋጋነው ትህነግን ለመታደግ ሳይሆን የትግራይን ሕዝብ ለመታደግ ነበር” ሲል ለጋዜጣው ያስረዳል።

የጌታቸው ረዳ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሆኖ መሾም በትግራይ ለውጥ እንዳመጣ በሦስት ጥይት የቆሰለው ሔኖክ ይናገራል። “በፊት ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ስናደርግ ይደበድቡን፣ ያሰቃዩን፣ ያዋርዱን ነበር። ለዚህም ነው ብዙ የትግራይ ልጅ እየተማረረ አገሩ ለቅቆ ወደ ሊቢያ ወይም አረብ አገር የተሰደደው” ይላል ሔኖክ። አክሎም “ጌታቸው ከመጣ በኋላ ግን የተለየ ነገር አሳየን። በምንም ዓይነት እንደፈለጉ ማሰር እንዳይኖር አደረገ፤ በነጻነት እንድንናገር ፈቀደልን” በማለት ልዩነቱን አመላክቷል።
“ጌታቸው የፈቀደው ነጻነት ያልተስማማቸው የፈረሰው ትህነግ መሪዎች አካሄዱን ለማስቆም ቆርጠው ተነሱ። በደብረጽዮን መሪነትና በሻዕቢያ አዝማችነት በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ጌታቸው ከሥልጣኑ በመፈንቀሉ ከሞት አምልጦ ወደ አዲስ አበባ ገባ” በማለት ሔኖክ ለጋዜጣው አስረድቷል።
በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ የሚናገረው የ42 ዓመቱ የሒሳብ መምህር ካህሳይ ኪዳኔ ደግሞ “የትህነግ ሰዎች ከከተማ ውጪ አውጥተው ደበደቡን፤ ያ አልበቃ ብሏቸው እንደሚገድሉን አስፈራሩን” ይላል። ይህ ሲሆን የዚያኑ ጊዜ ብረት አንስቶ ወደ ሃራ ምድር መግባቱን አመልክቷል።
የሰላም ኃይሉ አመራሮች በሥራቸው ያለውን ታጣቂ ቁጥር ይህ ነው ብለው ለመናገር ባይፈልጉም በብዙ መቶዎች በአንዳንዶችም ግምት በሺዎች የሚቆጠሩ የሰላም ኃይሉን እንደተቀላቀሉ ይናገራሉ።
አብዛኛው ኃይል በአፋር ምድር የሚገኝ ሲሆን ከመቀሌ 110 ኪሜ ርቀት በስተምስራቅ ላይ በምትገኘው ላኮራ ተብላ በምትጠራው ቦታ ላይ ያለውን ኃይል የምታዝዘው ሸዊት ቢተው ሁለት የሰላም ኃይል ግምባሮች በአፋር፣ ሦስተኛው ደግሞ በምዕራብ በኩል ወደ ሽሬ ቀረብ ብሎ እንደሚገኝ ታስረዳለች።
ከእነዚህ ሦስት ግምባሮች “የጸጥታ አብዮት” በማለት የሚጠሩትን ዘመቻ ለማካሄድ የሰላም ኃይሉ በዝግጅት ላይ እንዳለ ይናገራሉ። “በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ትግራይን በሙሉ እንቆጣጠራለን” ትላለች ሸዊት። በሌላ አነጋገር የሰላም ኃይሉ አዲሱን ዓመት ትግራይ ለማክበር ማቀዱን ነው እየተናገረ ያለው።
ጋዜጣው ቃለ ምልልሱን ያደረገው የሰኔ ወር ከማለቁ በፊት ሲሆን ቃለ ምልልሱ ከተደረገ ከሁለት ሳምንት በኋላ የሰላም ኃይሉ ከአፋር እየለቀቀ የመጨረሻውን ጥቃት ለመሰንዘር ወደ ትግራይ ዘልቆ መግባቱ ተመልክቷል።
የሰላም ኃይሉ ዋና መሪዎች ኃይላቸው ሙሉ በሙሉ ትግራይ ውስጥ እንደሚገኝ ከሳምንታት በፊት ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
በተደጋጋሚ እንደተሰማው ከጦርነቱ ማብቂያ ጀምሮ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሙስና ወይም የወርቅ ንግድ ውንጀላዎች መስፋፋታቸው ወታደራዊ አለመግባባቶችን አባብሰዋል። “የትህነግ አባላት በጦርነቱ ወቅት የተዘረፉ ዕቃዎችን በመሸጥ ትርፍ አግኝተዋል። ያኔ መናገር አልቻልንም፣ ከሰላም ስምምነት በኋላ ግን ወደ ወርቅና መዳብ ማዕድን ንግድ ገቡ” ስትል ሸዊት ቢተው በምሬት ትናግራለች።
በግጭቱ ወቅት የአካባቢው አስተዳደር መፍረሱ ሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች ከትህነግ ባለሥልጣናትና አዛዦች ጋር በመመሳጠር በግልፅ አብረው መሥራት ጀመሩ።
ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በተከሰተው በተኩስ አቁም ወቅት ከተመዘገቡት 270,000 የቲዲኤፍ አባላት መካከል ከ20,000 የሚያንሱ አሁንም በሥራ ላይ መሆናቸውን ጋዜጣው አመልክቷል።
በጦርነቱ ውስጥ የተሳተፈና ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ ያልተገለጸ ምሑር “እኛ ቲዲኤፍ የተቀላቀልንበት ምክንያት ሁኔታው አስገዳጅ ስለነበር እንጂ፣ እንደ ኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰለጠነ ሠራዊት አልነበረም” ይላል። እውነታው ግን በወቅቱ ከቤተሰብ በምርቃትና በሽልማት ወደ ጦር ሜዳ ሲላኩ እንደነበር ራሳቸው ያሰራጩትና የሰጡት ወኔ የተሞላ ምስክርነት ሕያው ነው።
“ቲዲኤፍ ምንም ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ዓላማ የለውም” የሚል አዲስ ትርክት የተሰማበት ይህ ሪፖርት፣ አሁን ላይ ቲዲኤፍን ተቀላቅለው የነበሩ በርካታ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች፣ መምህራን እና የቡድኑ አባል የሆኑ ተማሪዎች ለቅቀው ወጥተዋል። ጥለው ከወጡት ውስጥ አብዛኞቹ አሁንም ቃል የተገባውን 90,000 ብር (600 ዶላር) ካሳ ይጠብቃሉ። በዚህ ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ የማቋቋም (ዲዲአር) ፕሮግራም እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 48,308 የሚጠጉት የተጠቀሰውን ገንዘብ የወሰዱ ናቸው። ሁለት መቶ ሺህ የሚሆኑት እስካሁን ሳንቲም አልተቀበሉም።
ቲዲኤፍ ውስጥ ያሉትን በተመለከተ አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ተመራማሪ ሲናገር “ወታደራዊ ውሳኔዎችን በተመለከተ ቲዲኤፍ ውስጥ ያሉት ተምታቶባቸዋል። ምክያቱም ወደቤታቸው መመለስ አይችሉም፤ አንዳንዶቹ ቤታቸው ፈርሷል፤ አንዳንዶቹ ከተፈናቀሉበት መኖሪያቸው መመልስ አይችሉም። አንዳንዶቹ ቤተሰቦቻቸው ሞተዋል። በዚህ ምክንያት የመጠጥና አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ ወይም ሱሰኛ ሆነዋል” ብሏል።
ተመራማሪው አክሎ ሲያስረዳ እነዚህ የቲዲኤፍ ታጣቂዎች ምንም እንኳን ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ውስጥ ሆነው በግራ መጋባት ውስጥ ቢሆኑም ልባቸው አፋር ሃራ መሬት ካለው ኃይል ጋር ነው።
የአራትና የሁለት ዓመት ልጆቿን መቀሌ ትታ የመጣችው የቀድሞ ፖሊስ ሠራዊት አባል የሃያ ዘጠኝ ዓመቷ ገነት ወልደሥላሴ ለጋዜጣው ስትናገር፣ “ልጆቻቸውን በጦርነቱ ያጡ እናቶች አይቻለሁ፣ ልጆቻቸው ቢኖሩ ኖሮ ይጦሯቸው ነበር። ትህነግ ለእነዚህ እናቶች እግዚአብሔርን ያጥናችሁ እንኳን አላላቸውም። የእኛ ቀዳሚ አጀንዳ ትህነግን መገርሰስ ነው። ከማስወገድ ባሻገር አመራሩ ወደ ፍርድ ማቅረብ ነው ዕቅዳችን። ይህ ደግሞ ኃይል አይጠይቅም። መፍትሔውም ጦርነት ውስጥ በመግባት ሳይሆን በአመራር፣ በሰላምና በሀሳብ በማሸነፍ ነው” ስትል ተናግራለች።
በቅርቡ በጌታቸው ረዳ የተመሠረተው ስምረት ፓርቲ ከቲፒኤፍ ጋር በጥምረት እየሠራ ይገኛል። ይህንን አስመልክቶ የፓርቲው ቃል አቀባይ የሆነው ረዳኢ ሃለፎም “(ከቲፒኤፍ) ጋር የምንለያይ ቢሆንም ግባቸውን እኛም እንጋራለን፤ የነሱ ሕልም ቀጣይ ደም መፋሰስን ማስቀረት ስለሆነ ከትግራይ ጋር የተስማማ ነው” ይላል።
“ትህነግ በቅርቡ በፈቃዱ ከሥልጣኑ ይለቅቅ ይሆናል፤ አለበለዚያ ግን ከፌዴራል ጋር ሆነን በግድ እንዲለቁ እናደርጋለን” ይላል የ29 ዓመቱ ዮሐንስ ወልዳይ። ይህንኑ ሃሳብ በማጠናከር ሸዊት ቢተው ስትናገር “በርግጥ ፍርሃት አለብኝ – ትግራይ እስካሁን አልፈወሰችም፤ እኛ ጦርነት አንፈልግም፤ ግን ደግሞ ምንም አማራጭ የለንም … ሚሊዮኖችን ለመታደግ ጥቂት መቶዎች መሰዋታቸው አስፈላጊ ይሆናል” ትላለች።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ



አሳዛኙ የሃበሻ ፓለቲካ መልኩን እየቀየረና እያስቀየረ እንሆ ዛሬም ግብ ግብ ላይ ነው። መቼ ይሆን በንግግር ነገሮችን ፈትተን በሰላም ወጥተን የምንገባው? ዝንተ ዓለም የባሩድ ሽታ እንዳሸተቱ መኖር እንዴት ባለ ስሌት ነው መኖር የሚባለው? በቅርቡ የኤርትራው የእድሜ ልክ መሪ በሰጠው ትረካ አሁንም ያዙኝ ልቀቁኝ ኢትዮጵያ ልትወረኝ ነው እያለ የራሱን የውስጥ ችግር መሸፈኛና የዓረቡን ዓለም ድጋፍ መለመኛ ሰበብ ስለሚሆንለት ይመቸው። ተናግሮ የማይደክመው የውሽት ቋትና ጥቁር ጠል የሆነው ትራምፕ ስለ ግድቡ ይህን ተናገረ ብለው ሰዎች ሲቀባጥሩ መስማት ያሳዝናል። ትራፕ የማይገባበት የዓለም ጉዳይ የለም። ግን ከእውቀትና ከመረዳት ሳይሆን እንዲሁ በነሲብ ከማውራት ነው። በዚህ ሰው ዙሪያ ገና ብዙ ነገር እናያለን። ግን እርሱ ያለውን እንደ ገደል ማሚቶ እየተቀበሉ ማስተጋባት ወይም በተናገረው ምክንያት እንቅልፍ ማጣት ጭራሽ አያስፈልግም። የውድቀት መጀመሪያ ትዕቢት ነው። ዝም ብሎ ለጠበቀ ብዙ ነገር እናያለን እንሰማለን። አሜሪካ የተማታባት ሃገር ሆናለችና!
ታዲያ የትግራይ ታጣቂዎች ለሁለት ተሰንጥቀው አንድ ሌላውን ናና ግጠመኝ ማለቱ የሚያሳዝን እንጂ እሰየው የሚያሰኝ ጉዳይ አይደለም። ትላንት ያለቁት የትግራይ ልጆች ተረስተው እንደገና ጦርነትን ለመጫር በዚህም ሆነ በዚያ በኩል ሃተፍተፍ ማለት የህዝባችን ሰቆቃ ጣራ ለማውጣት የሚደረግ እብደት ነው። አማራም ታጣቂ/ኦሮሞውም ታጣቂ/ሌላውም እንዳሻው በሆነባት በዚህች የሃበሻ ምድር ላይ ቀኑ መቸ ነው ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ አንገቱን ቀና አርጎ ሰርቶ የሚኖረው? የመቀሌው ወያኔ ከሻቢያ መጠጋቱ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ እንጂ ሁለቱ ነቀዞች በበረሃም ይሁን በገጠር ተስማምተው አያውቅም። ግን ያው የሞት ድግስ ለመደገስ ሁሌም ይግባባሉ። ስናሳዝን። ያለ ጦርነት ሙያ የሌለን ጅሎች። ወንድምና እህታችን ገድለን በአስከሬናቸው ላይ እያጨበጨብን የምንዘፍን የቁም ሙቶች። እኔ ባደኩበት ባህል ጎረቤት እንኳን ሃዘን ላይ ከሆነ ሬዲዪ አይከፈትም ነበር። እነዚህ አውሬዎች ከበቀሉ በህዋላ ሰው በሰውነቱ መለካቱ ቀርቶ ብሄርና ቋንቋው መለያው ሆነ። የእንስሳት ዓለም ይሉሃል ይሄ ነው።
ጥቁሩ ዓለም ቡጢ ጨብጦ ኑና ላሳያችሁ ከማለት ይልቅ ራሱን ፈትሾ ለሰላም እጥፍ መንገድ ሂዶ ለሃገርና ለወገን ሲባል ነገርን በይቅርታ ለውጦ ቢራመድ የት በደረሰ ነበር። ግን ያ አልሆነም። ጊዜው የሚፎከርበት ጊዜ ሳይሆን የምናፍርበት ጊዜ ነው። ህዝባችን በቀን አንዴ እንኳን በልቶ ማደር ያቃተው ጊዜ ላይ ነን። ስለሆነም በሃራ ምድር ያሉት ታጣቂዎችም ሆኑ የደብረጽዪን ቡችሎች ባይናከሱ ይመረጣል። ግን ወያኔ ያለ ጦርነት መኖር አይችልም። ከባህር እንደ ወጣ አሳ መተንፈስ የሚሳነው ወያኔ ሰላም ሲኖር ነው። ጦርነት ጠማቂው ወያኔ ለትግራይ ህዝብ መከራ አዝናቢና ለሃገር በሽታ ነው። ይሁን በዚህም በዚያም ፎክሩ/አፋክሩ ተፋለሙ/ተገዳደሉ/ትርፉ ባዶ ነው የሚሆነው። ሰው በሃገሩ ላይ ተቀምጦ ሃራ መሬትና የጠላት ይዞታ እያለ ሲያወራ አያሳዝንም። ነው ወይስ ጣሊያን ለ3ኛ ጊዜ ወረረን? የቁም ሙቶች እኛ ነን። የሞቱት ይህን ጉድ አያዪምና ህያዋን ናቸው። በመጨረሻም መፋተግ/መገዳደል እንደማይረባ አንድ ነገር ላካፍላችሁና ይብቃኝ።
እነርሱም ይላሉ ከተኮስን አንስትም። እኛም እንላለን ቃታ አናስከፍትም
ይሄን ብለን ብለን የተገናኘን ቀን አሞራ ተሰብሰብ ትበላለህ ድለት!