የኢትዮጵያ ሕዝብ እራሱ በመረጠው መንግሥት እንዲተዳደር ይነሳ የነበረው ጥያቄ፤ ከ50 ዓመታት በላይ በተደረገ ትግልና በተከፈለ ከፍተኛ መስዋዕትነት በሰኔ 2013 ምላሽ አግኝቷል። ምንም እንኳን ምርጫው አንዳንድ መሰናክሎች ቢያጋጥሙትም፤ ገለልተኛና ተአማኒ በሆነ የምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመንግሥት ሥልጣን ምርጫ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብና በበርካታ ሃገራዊና አለም አቀፍ ተቋማት ፍትሃዊና ሚዛናዊ ምርጫ ነው ቢባልም፤ ይህ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ አይደለም የሚሉ ግን አልጠፉም።
የሕወኃት መራሹ መንግሥት ተወግዶ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤ ከሕዝብ ያገኙት ድጋፍ በሃገራችን ታይቶ የማይታወቅ ድጋፍ ነበር። በጊዜ ሂደት ግን፤ ፍላጎታቸው ያልረካ በርካቶች ከለውጡ ባቡር ላይ ተንጠባጥበው፤ ትላንት “ዐብይን አትንኩ” እያሉ ሲያሸማቅቁን የነበሩ ሰዎች፤ ዛሬ ሥርዓቱን ጥላሸት ሲቀቡ ማየትና፤ ምሁራዊ ሸፍጥ በተሞላበት የሃሰት ትርከት፤ ‘ዐብይን ከሥልጣን እናወርዳለን’ በሚል ቅዠት በሃገር ውስጥ ትርምስ ለመፍጠርና በተለይም በአማራው እና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ቅራኔ በመፍጠር አማራና ኦሮሞ እርስ በእርሱ እንዲገዳደል የሚደግሱትን ድግስ ማየት የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን በዝምታ ሊታለፍ የማይገባም መሆኑን ይህ ፀሃፍ በጽኑ ያምናል።
እነዚህ ኢ-ዲሞክራሲያዊና ጽንፈኛ ኃይሎች፤ የዶ/ር ዐብይ መራሹን መንግሥት የሚጠሉበት ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም፤ ግባቸው አንድ ነው (መቃወምና መጥላት ለየቅል ነው)። ይህም ሕዝብ የመረጠውን መንግሥት በነውጥ እና በጦርነት ለማውረድ አሥፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ነው። ዓላማቸውንም ለማሳካት በብሔር፤ በሃይማኖትም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች በሕዝቡ መካክል መከፋፈል በመፍጠር እርሰ በእርሱ እንዲገዳደል ማድረግና በዚህ ትርምስ መካከል እኛ እንፈልገዋለን የሚሉት ኃይል ሥልጣን እንዲይዝ ማድረግ ነው። እነዚህ ኃይሎች እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ቅዠት ውስጥ ለመግባታቸው፤ በየጊዜው በየዩቲዩቡ የሚለፍፉትና በየድኅረ ገጾች የሚለጥፏቸው ጽሁፎች ያሳብቃሉ።
የእነዚህ ኃይሎች በተለያየ መንገድ የሚረጩት ፕሮፖጋንዳና የሚለቁት እውነት የሚመስል ግን ሃሰተኛ መረጃ፤ በርካታ ለሃገራቸው የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያውያንን እያሳሳተ ለመሆኑ፤ በተለያዩ ማህበራዊ ገፆች የሚሰጡ አስተያየቶችንና የበርካቶችን ቁጣ ማየት ብቻ ይበቃል። በተለይም ከሃገሩ ርቆ የሚገኘው ቅን ዜጋ በሚሳሳላት ሃገሩ ውስጥ ክፉ ሲሰራ የሚከፋውና የሚቆጣ በመሆኑ፤ የዚህን ቅን ዜጋ ስሜት ለመኮርኮር እየተሄደበት ያለው ርቀት በትክክለኛ መረጃ ሊጋለጥ ይገባዋል። ብዙዎች በተለያየ ምክንያት “እምነት ከጣሉባቸው” ሰዎች የሚነገረውን ነገር ሳይጠይቁና ሳይመረምሩ እውነት ነው ብለው በመቀበላቸው በሃገራቸው ጉዳይ ተስፋ እየቆረጡ ሲመጡም እያየን ነው። አንዳንዶች ደግሞ እውነቱንም ቢያውቁ እነዚህን ኢ-ዲሞክራሲያዊና ጽንፈኛ ኃይሎች በአደባባይ ለመሞገት አልደፈሩም። አንዳንዶች፤ የእነዚህን አደገኛ ኃይሎች የጭቃ ጅራፍ በመፍራት ዝምታን ሲመርጡ፤ አንዳንዶች ደግሞ አካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር “ላለመቀያየም” ወይም ‘የእኔ ብቻ መናገር ለውጥ አያመጣም በሚል ስሜት’ እራሳቸውን ከሃገራቸው ጉዳይ ለማግለል ወስነዋል።
ይህ ጽሁፍ በርካታ ነገሮችን የሚያነሳ በመሆኑ በአንድ ክፍል ብቻ ማጠናቀቅ ሙሉ ስዕል ስለማይሰጥ፤ ቢያንስ በአራት ክፍል የሚከፈል ይሆናል። ጽሁፉ፤ ከሻለቃ ዳዊት፤ እስከ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ ከነባር ዩቲዩበር፤ አዲስ እስከተፈለፈለው ዩቲዩበር፤ የሚሰራጨውን እውነት የመሰለ የሃሰት መረጃን አንድ በአንድ በእውነተኛ መረጃ ይሞግታል። በተለይ፤ ለሃገር አስበው ሳይሆን፤ በግል ቂምና በሌላ ግል ምክንያታቸው፤ በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱትንና የከሸፈ ዘመቻቸውንም ያጋልጣል። ኢትዮጵያ ውስጥ መነሳት ያለባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን፤ የሃይማኖት፤ የብሔር እና ሌሎች ልዩነቶችን ጠልፈውና በጥላቻ ጠምቀው ያልሆን የፖለቲካ ይዘት በመሰጠት የሚፈበርኩትን የሃሰት ትርከት፤ ከህግ እና ከአስተዳደራዊ አውድ ጋር በማያያዝ በጭብጥ ይሞግታል።
በመጨረሻም፤ የብልጽግና መራሹ መንግሥት፤ ጥንካሬ፤ ጉድለቶች፤ ጥፋቶች፤ ዕድሎች፤ እና በአመራሩ ድክመት በሃገር ላይ የተደቀኑ ሥጋቶችን ይመለከታል። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያውያን አሁን የተጀመረውን የለውጥ ሂደትና የዲሞክራሲያዊ ሥልተ ሥርዓት ግንባታ ጅማሮ፤ በማስቀጠል፤ ሃገር ከማንም ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ በላይ መሆኗን በጽኑ በመገንዘብ ከአሁን በኋላ በሃገራችን፤ ሥልጣን በምርጫ እንጂ በነውጥና በጦርነት መሆን እንደሌለበት፤ ሃገራችን ከነውጥና ከግጭት አዙሪት ልትወጣ የምትችልበትን፤ ዜጎች በሃገራችን ጉዳይ ማድረግ የሚጠበቅብንን፤ ለግለሰብ፤ ለፓርቲ፤ ለብሄር ወይም ለግል ጥቅም ብቻ ሳይሆን፤ ለእውነትና ለሃገር በመቆም፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ሃገር እንድናስረክብ የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረብ ጽሁፉ ይጠናቀቃል።
የዲሞክራሲ ሥልተ ስርዓት፤
ዲሞክራሲ ማለት፤ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ማለት ነው። ብዙዎች፤ “ዲሞክራሲ” የሚለውን እሳቤ በተጣመመ መልኩ ይረዱታል። በአንድ ሃገር በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ሁሌም ልክ ይሰራል፤ ወይም የዜጎቹን ጥያቄ ሁሉ በብቃት ይመልሳል ማለት አይደለም። በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ሃገራቸውን አደጋ ላይ የጣሉና ሕዝባቸውን ለውድቀት የዳረጉ በርካታ መሪዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ግን ሕጉ እስከፈቀደላቸው ጊዜ ድረስ በሥልጣን የመቆየት መብት አላቸው። በበርካታ ሀገየራት ዛሬ እንደምናየው፤ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎችና ፓርቲዎች፤ የሃገራቸውን ሕገ መንግሥት ከሕዝብ ፈቃድ ውጭ በመቀየር፤ የዲሞክራሲያዊ ስልተ ሥርዓትን በማፍረስ አምባገነን ይሆናሉ። የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሕዝብ የተመረጡ፤ ግን አሜሪካንን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱና፤ በመጨረሻም፤ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ስርዓቱን በጉልበት ለመቀየር የሞከሩ ናቸው። የአሜሪካ ተቋማት ጠንካራ ባይሆኑ ኖሮ፤ ዛሬ አሜሪካ አምባገነናዊ መንግስት የነገሰባት ወይም የቀውስ ሃገር በሆነች ነበር። መቼም ቢሆን፤ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት ከሕግ ውጭ እራሱን አምባገነን ሲያደርግ፤ በንቃት በሃገራቸው በሚሳተፉ ሰዎች ተቃውሞ ሊደረግበትና፤ ሕዝብንም በማነሳሳት አስፈላጊው ትግል ሊደረግ ይገባል። የትራምፕ አስተዳደር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው።
በአሁኑ ሰዓት በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ ለመሆኑ፤ ሕዝቡ በምርጫው ከማረጋገጡ በተጨማሪ እንደ አውሮፕ አቆጣጠር በ2021 በተደጋጋም አደባባይ በመውጣት ለምዕራባውያን መንግስታት ባስተላለፈው መልዕክት “መንግሥታችንን የመረጥነው እኛ ነን” “በሕዝብ ከተመረጠ መንግሥት ላይ እጃችሁን አንሱ” “ዐብይ በሕዝብ የተመረጠ ነው” የሚሉ መፈክሮችን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሲስተጋባ ነበር። ዛሬ አንድ አንድ “ያኮረፉ” አክትቪስቶች፤ የብልጽግና መንግሥት በሕዝብ አልተመረጠም የሚል የጉንጫ አልፋ ክርክር ለማድረግ ቢዳዳቸውም። በሁሉም መመዘኛ፤ ኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዳላት በጭብጥ የተረጋገጠ ነው። ስለዚህ በዚህ ላይ ጊዜ አላጠፋም።
ይህ መንግሥት፤ በሕግ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ተላልፎ፤ ዲሞክራሲያዊ ስልተ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር እስካልፈፀመ ድረስ፤ በኃይል ለማስወገድ የሚደረግ ሙከራ በምንም መልኩ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ማስወገድ ከተፈለገ፤ በሕግና በሕግ ብቻ ሊወርዱበት የሚችሉበት አግባብ መንገድ አለ። ሕዝብ ካልፈለጋቸው፤ በፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ በሕዝብ እንደራሴዎች በሚሰጥ ድምጽ ከሥልጣን ሊወርዱ ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ግን፤ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ያለባቸው፤ በምርጫና በምርጫ ብቻ ነው። ማናችንም መገንዘብ ያለብን፤ በሕዝብ ተመርጦ የሚመጣ መንግሥት ሁሌም አብላጫው ሰው የሚፈልገውን ውሳኔ ይወስናል ማለት አይደለም። አንዳንዴ ለሃገር ሲባል፤ ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ይኖራሉ። የተሳሳት ፖሊሲ የሚከተሉበትና ሕዝብን የሚጎዳም ውሳኔ የሚወስኑበት ወቅት አለ። የመንግሥት ፖሊሲዎች፤ በላብራቶሪ ሙከራ የሚደረግባቸው አይደሉም። ጉዳታቸውና ጥቅማቸው የሚታወቀው፤ በተግባር ሲፈተኑ ነው (አሜሪካ በ2008 (እ.አ.አ.) ያጋጠማት ቀውስ እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል።
ሕዝባችን አመራሩን የማይፈልግ ከሆነ በምርጫ ከሥልጣን ሊያስወግደው ይችላል። በዲሞክራሲያዊ ስልተ ሥርዓት ውስጥ ሁሌም አሸናፊ ሊሆን የሚገባው 50+1 ያገኘ የፖለቲካ ኃይል ነው። በአሁን ወቅት በተለያየ ምክንያት፤ ከለውጡ ባቡር ላይ የተንጠባጠቡ ሰዎች ቢኖሩም፤ የተጀመረው የዲሞክራሲያዊ ሥልተ ሥርዓቱን ለማደናቀፍ ተግተው እየሰሩ ያሉ ግን ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች፤ አቅም ፈጥረው በተዘጋጀው የምርጫ ሂደት፤ መንግሥት ለመቀየር ከመሥራት ይልቅ፤ ዓላማቸው በሃገር ውስጥ ሁከት በመፍጠር፤ በብሔሮች መካከል የማይታረቅ ቅራኔ እንዲኖር በማድረግ በሚፈጠረው የደም ጎርፍ ተንሳፈው እነሱ ወይም እነሱን መሰል የፖለቲካ ኃይል ወደ ሥልጣን ይመጣል ብለው በቅዠት አለም ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች በራስ የማይተማመኑ በመሆናቸው፤ የምዕራባውያን ጌቶቻቸውን በመማፀን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በረሃብና በጦርነት ለመቅጣትና በዚህም ሕዝብ አምፆ ይነሳል በሚል እምነት ተግተው በመስራት፤ ለራሳቸውና መሰሎቻቸው የሥልጣን በር ይከፈታል ብለው ያምናሉ። እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ደንታ የሌላቸው፤ በግላቸው ቂም የቋጠሩና፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምዕራባውያን ቀና ደፋ የሚል መንግሥት እንዲቋቋም ተግተው የሚሰሩ ናቸው። ለሕዝብ ድምጽ፤ ለሕዝብ ፍላጎትና ዲሞክራሲያዊ ስልተ ሥርዓት ግድ የላቸም።
የኢ-ዲሞክራሲና የጽንፈኛው ኃይል “መሪዎች” የሻለቃ ዳዊትና የዶ/ር ዮናስ ብሩ ያልተቀደሰና ያለአቻ ጋብቻ፤
ይህንን የጽንፈኛና የኢ-ዲሞክራሲ ኃይሎች የሞት ሽረት ትግል ለመምራት ወገባቸውን አሰር አድርገው የተነሱት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስና ዶ/ር ዮናስ ብሩ የፈጠሩት ያልተቀደሰና ያለ አቻ ጋብቻ፤ አቅጣጫውና ዓላማው አንድና አንድ ብቻ ነው። ማንኛውም ዋጋ ተከፍሎ ዐብይን ከሥልጣን ማንሳት የሚል ቅዠት። በነገሬ ላይ እነዚህ ሰዎች ከትግሉ ሜዳ ርቀው በተመቻቻ ወንበር ላይ ተቀምጠው “ትግሉን የሚመሩ እንጂ” ወድ ለኮሱት እሳት የመጠጋት ዓላማና እቅድ እንደሌላቸው ሊሰመርበት ይገባል። እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ከዓመት ተኩል ገደማ በፊት “የፖለቲካ ባላንጣ” ሆነው የታዩ ቢሆንም፤ ዛሬ ግን በተለያየ አቅጣጫ ወደ አንድ መንገድ እየተጓዙ ይገኛሉ። የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው፤ እነዚህ ሁለት ሰዎች፤ በሕዝብ መከራ በመነገድ፤ በሃገራችን የማያባራ ግጭት ለመፍጠርና ሃገራችንን “የደም መሬት” መሆኗ እንዲቀጥል በአንድ እሳቤ የሚሰሩ መሆናቸው ነው። ሁለቱም በሃሰት ትርከት የተካኑ በመሆናቸው፤ የተሳሳቱ መረጃዎችን እንደ እውነት በማቅረብ፤ ጥቁሩን ነጭ እንደሆነ ለማሳመን በመሞከር የሚጽፏቸው የሃሰት ትርከቶች በየዩቲኡቡ የሚለቋቸው ንግግሮች፤ እንኳን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከተማረ፤ ከ6ተኛ ክፍል ተማሪ የማይጠበቅ መሆኑ፤ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያሳዩት ምሁራዊ ሸፍጥ (intellectual dishonesty) እነሱ በሚፈጥሩት ግጭት ለሚሞተው ንፁህ ዜጋ ምንም ርህራሄ የሌላቸው መሆናቸውን ያሳብቃል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ1930ዎቹ (የአውሮፓ ዘመን አቆጣጠር) የጀርመን ፖለቲካ ብዙ ነገር መማር የሚችልበት የታሪክ ሂደት ላይ ነው። አዶልፍ ሂትለር እና የፀረ ዲሞክራሲ ኃይል ጽንፈኞች፤ ጀርመን ላይ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሄዱበት መንገድ ከእነዚህ ሰዎች የሚለየው በአንድ መልክ ብቻ ነው። በ1920ዎቹ በዓለም ላይ የነበረውን የኢኮኖሚ ቀውስና ችግር ተጠቅመው፤ አዶልፍ ሂትለር እና የናዚ ፓርቲው፤ በአይሁዶች ላይ ከፍተኛ የጥላቻ መርዛቸውን በማሰራጨት፤ በሕዝብ መደመጥ ማግኘት ቻሉ። በወቅቱም በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ከሥልጣን በሃይል ማውረድ እንችላለን በሚል ቅዠት፤ በህዳር 1923 ዓም (እ.አ.አ) በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ሞከሩ፤ ይህ ግን ሳይሳካላቸው ቀረ። ከዚህ በኋላ ነው፤ የናዚ ፓርቲ በምርጫ ሥልጣን ለመያዝ በምርጫ መሳተፍ የጀመረው። በ1934 (እ.አ.አ) በጀርመን ለምክር ቤት ምርጫ የተወዳደረው የናዚ ፓርቲ 32% መቀመጫ በማግኘቱ፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጣምራ ፈጥሮ መንግሥት ለመመስረት ሳይፈቅድ ቀረ። ሆኖም ሂትለር ምክር ቤቱን እንዳይሰራ ጠፍንጎ በመያዝ፤ ቻንስለር ሆኖ ካልተሾመ በስተቀር፤ ከማንም ጋር ተባብሮ እንደማይሰራ ለፕሬዝዳንቱ በማያሻም ሁኔታ በመግለፁ፤ ፕሬዝዳንቱም አማራጭ በማጣታቸው፤ ሂተልርን ቻንስለር አድርገው መረጡት። ፕሬዝዳንቱ ከሞቱም በኋላ፤ ሂትለር በምርጫ ሳይሆን፤ የጀርመንን ሕገ መንግሥት በመጣስ እራሱን መሪ አድርጎ ሾመ። ይህም፤ ለጀርመን ሕዝብ ውርደትና ለጀርመን መንግሥት ውድቀት ምክንያት ሆኗል።
ዛሬ የኦሮሞን ሕዝብ እንደ ሕዝብ በማስጠላት፤ ሌላውን ሕዝብ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በማነሳሳት፤ ሥልጣን በጉልበት እንዲያዝ ሃሳባቸውን ለሕዝብ የሚያጋሩት ዳዊት ወልደጊዮርጊስና ዮናስ ብሩ፤ ከሂትለር የተለየ ሃሳብ አላቸው ብዬ ለመገመት አልችልም። ዚያድባሬ፤ ሻእብያ፤ ወያኔና ኦነግ፤ ከሂትለር የፖለቲካ ደብተር ላይ የገነጠሏትን እኩይ እሳቤ ተጠቅመው፤ በነዙት ጸረ አማራ ፕሮፖጋንዳቸው፤ በአማራው ሕዝባችን ላይ ከፍተኛ በደል እንዲፈፀም አድርገዋል። በዚህም የተነሳ ዛሬ ድረስ በአማራው ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ሲፈፀም እናያለን። ትላንት አማራን እየጠላ እንዲያድግ የተደረገው የኦሮሞ ወጣት በሃገር ላይ ያደረሰውን ጉዳት አይተን ትምህርት እንደመውሰድና ዘር ተኮር የጥላቻን ፖለቲካ እንደመጠየፍ፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ ለኢትዮጵያ ችግር ምክንያቱ አማራው ነው ብለው ድል አግኘተዋል ከሚል እሳቤና ሂትለር ለጀርመናውያን ችግር ምንጮቹ አይሁዶች ናቸው በሚል ትርከት አይሁዶችን በማስጠላት፤ የተወሰነውን የጀርመን ሕዝብ ድጋፍ አግኝቷል ከሚል እይታ፤ ዛሬም በፀረ ኦሮሞ ትርከት ስኬት እናገኛለን ብለው በሚያስቡ እንደ ዳዊትና ዮናስ ባሉ ጽንፈኞ የሚመራ ቡድንች አገራችንን አድጋ ላይ እየጣሉ ነው።
ሂትለር በተወሰነ ደረጃ በእንደዚህ ዓይነት የዘር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካው፤ ድጋፍ በማግኘቱ ነበር፤ በሕዝብ የተመረጠውን የጀርመን መንግሥት በኃይል ከሥልጣን ለማውረድ የሞከረው። ይህ ሳይሳካ ሲቀር፤ ምርጫን ተጠቅሞ ፓርቲው ባሸነፈው ወንበር፤ ለጀርመን ሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ከመሥራት ይልቅ፤ የራሱን የጥላቻ ፖለቲካ ተግባራዊ የሚያደርግበትን መንገድ በመፈለጉ፤ የጀርመንን ፕሬዝዳንት አስጨንቆ ቻንስለር ሆኖ ተሾመ። በተሰጠው ሥልጣን ግን ሕዝብንና ሃገርን ከማገልገል ይልቅ፤ የራሱን የበቀል በትር፤ በሚጠላቸው አይሁዳውያን ላይ ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን፤ ለሁለተኛ ዓለም ጦርነት መነሳት ምክንያት ሆነ። በሃገራችን በጽንፈኞች የሚመራው ቡድን፤ ከዚህ የተለየ አላማ የሌለው በመሆኑ፤ የአደጋውን ደወል መደወል አስፈላጊ ነው። ዛሬ በሃገራችን የምናያቸው ጽንፈኛ ኃይሎች፤ በሚቻል መንገድ ሁሉ ሥልጣን ተቆናጠው፤ የሚፈልጉት የሚጠሉትን የኦሮሞ ሕዝብ መበቀል ነው። በጽንፈኛ ኦሮሞዎች የተጠቃውንና እየተጠቃ ያለውን የአማራ ሕዝብ በደል በመኮርኮር አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ በሚነዟቸው የሃሰት ፕሮፖጋንዳዎች የሚችሉትን ያህል ሰው በማሳሳትና በማደናገር ሌሎች ኢትዮጵያውያን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በማነሣሳት ኢትዮጵያን የንፁሃን ደም ያለገደብ የሚፈስባት ሃገር ለማድረግና፤ ይህ ሲሆንም ምዕራባውያን ጣልቃ ገብተው፤ ሕዝብ የመረጠውን መንግሥት አውርደው በእኛ ወይም በመሰሎቻችን ይተካሉ የሚል የቅዥት እምነት ስላላቸው፤ በየነ መርቦችንና የአየር ሞገዶችን በሃሰት ትርከታቸው፤ ያጨናንቃሉ። የኢትዮጵያን ሕዝብ ያጋጠመውን ፈተና ሊወጣ የሚችልበትን ትክክለኛ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፤ ለተጎዳውና ለተፈናቀለው ሕዝብ እርዳታ ከማሰባሰብ ይልቅ፤ እኩይ ቅዠታቸው እንዲሳካ፤ የበለጠ ችግር ይፈጥራሉ፤ ለመሳርያ መግዣ ገንዘብ ያሰባስባሉ።
ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፤ እራሳቸውን የሥልጣን ቁንጮ ለማድረግ ከአሜሪካ የስለላ ድርጅት ጋር ሲስሩ ወደ 40 ዓመታት ተቆጥረዋል። እኝህ ሰው ዛሬ አስብለታለሁ የሚሉትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠረውን የአማራ ሕዝብ፤ በጭካኔ በጠኔ ፈጅተው ለምዕራባውያን ያደሩ ለመሆናቸው ታሪካቸው ይናገራል። በእኝህ ሰው ስግብግብነትና ደካማነት፤ ኢትዮጵያ ምርጥ ጄነራሎቿን አጥታለች፤ በበርካታ ድርጅቶች ውስጥ እጃቸውን በማስገባት፤ ለብዙ ድርጅቶች መፍረስ ምክንያት የሆኑ ሰው ናቸው። ወያኔ ለ 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ረግጦ ሲገዛ እስከ 11ኛው ስዓት ድረስ ድምፃቸውን አጥፍተው የነበሩ ናቸው። በአንድ በኩል መንግሥቱ ኃይለማርያምን በአደባባይ እንደ ጠላት ሲያብጠለጥሏቸው፤ በሌላ በኩል ለመንግሥቱ በሚጽፉት ሚስጥራዊ ደብዳቤ “የምንግዜም ታማኝ አገልጋዮ” በሚል ፊርማቸውን ያሰፍራሉ። እኝህ ሰው በሚጽፏቸው የሃሰት ትርከቶችና በሚሰጧቸው ቃለ ምልልሶች፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት ተግተው ሲሰሩ ቆይተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከዓመት ተኩል በፊት ገደማ ድረስ የሻለቃ ዳዊት “የፖለቲካ ባላንጣ” የነበሩትና፤ ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት ለማግኘት፤ ከሚገባው በላይ ሲንጠራሩ የነበሩት ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ ካለፉት ሰባት ወራት ጀምሮ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን፤ “ጠላት” መሆናቸው ብዙዎችን አስገርሟል። እኝህ ሰው ቂም እንደቋጠሩና ጥላቻቸውም መረን የለቀቀ እንዲሆን ያደረገው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዶ/ር ዮናስ ከተባረሩበት የአለም ባንክ እንዲመለሱ ለማገዝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው የሚሉ በርካቶች አሉ። ይህ ፀሃፊም ይህን ሃሳብ ይጋራል። ዶ/ር ዮናስ ይህንን ወቀሳ ለማስተባበል በፌስቡክ ገፃቸው ያቀረቡት አመክንዮም ውኃ የሚቋጥር አይደለም። ዶ/ር ዮናስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእሳቸው የግል ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ከቨርጂንያው ገቨርነር፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፃፈውን ደብዳቤ በማጋራት፤ ይህ ከሆነ በኋላና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሳቸውን ለመርዳት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ቢያውቁም፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሃገራቸውን በሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ እንዲያግዙ ተጠይቀው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ሳያኮርፉ፤ በመንግሥት የተጠየቁትን እገዛ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
በዚህ ፀሃፊ እምነት፤ ዶ/ር ዮናስ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው የተጠየቁትን የፈፀሙት (ይህ እውነት ከሆነ፤ በርካታ የዶ/ር ዮናስ መረጃዎች እውነት እንዳልሆኑ፤ በዚህ ጽሁፍ መረጃ ይቀርባል) አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዶ/ር ዮናስ ወደ ተባረሩበት የዓለም ባንክ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥረት ያደርጋሉ ከሚል እምነት ተነስተው ነው ብሎ ይህ ፀሃፊ ያምናል። ምክንያቱም፤ የዶ/ር ዓብይ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመት በላይ የሥልጣን ዘመኑ ከሚከተለው ፖሊሲ፤ እስከ አሁን የተለየ የፖሊሲ ለውጥ አላደረገም። ላለፉት አምስት ዓመታት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲተቹ የነበሩ ዜጎች ላይ የስድብ ውርጅብኝ ሲያዘንቡ የነበረ ሰው አሁን ምን የተለየ ነገር አይተው ነው መረን የለቀቀ ጥላቻ የሚያንጸባርቁት፤ አለፍ ብሎም ሃገር የሚጎዳ ሥራ የሚሰሩት ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ሌላው ቀርቶ እኝህ ሰው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረት ከሳቡ ጥቂት ኢኮኖሚስቶች መሃል ሆነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ቦርድ አባል ብቻ ሳይሆኑ ጊዜያዊ መሪም ሆነው አገልግለዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ይህ 16 አባላት ያሉት ቦርድ እርስ በእርሱ በሥልጣን ሲሻኮት፤ አንድ የረባ ነገር እንኳን ለመሥራት ባለመቻሉ፤ ዶ/ር ዮናስ በብስጭት ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን፤ “Thinking Class And The Dumbing Down Of A Nation” በሚለው ጽሁፋቸው አብስረውናል። እኝህ 16 ሰዎችን ለመምራት አቅም የተሳናቸው ሰው፤ 120 ሚልዮን ሕዝብን ከነተወሳሰበ ችግሩ ለመምራት የሚጥርን ሰው በጥላቻ ሲኮንኑ እንደማየት አስገራሚ ነገር የለም።
ዶ/ር ዮናስ ከረሜላ እንደተነጠቀ ሕፃን ለምን እዚህም እዚያም እየረገጡ ሙሾ እንደሚያወርዱና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ ዓለም ባንክ ሥራቸው እንዲመለሱ ካለመጣራቸው ጋር እንዴት እንደሚገናኝ በዚህ ጽሁፍ ይብራራል። እኝህ ሰው፤ ጩኸታቸውና ትግላቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደንታ እንደሌላቸው በሚጽፏቸው በርካታ ጽሁፍ አሳይተውናል። “ትል አትክልትን ሲበላ አትክልትን መስሎ ነው” እንዲሉ፤ እኝህ ሰው እንደ በርካታ ጽንፈኞች፤ የኢትዮጵያን ባንዲራ ጭንብላቸው ቢያደርጉም፤ እጸየፈዋለሁ የሚሉትን ጎጠኝነት የማይጸየፉ፤ ኦሮሞ ጠል ጎጠኛ ለመሆናቸው ስራቸው ምስክር ነው። አንድ ተማርኩ ከሚል ሰው የማይጠበቅ በመረጃ ያልተደገፈ፤ አንድ ሰው የጻፈውን ጽሁፍ እንደ አጠቃላይ የአንድ ብሔር እሳቤ አድርገው ለማሳመን ያቀረቡት ጽሁፍ፤ እኝህ ሰው የሚፈልጉትን ለማሳካት ምን ያክል ወደ ታች ርቀው ቁልቁል እንደሚወርዱ ቁልጫ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ቶማሥ ጃፈርሰን “አንድ ጊዜ የዋሸ ሰው ደግሞ ለመዋሸት አይከብደውም” ይላል። እኝህ ሰው ለረጅም ጊዜ፤ ከአለም ባንክ ሥራዬ የተባረርኩት “ጥቁር በመሆኔ ነው” ሲሉን ብዙዎቻችን አምነን ተቀብለናቸው፤ በዓለም ባንክ አመራር ላይ የውግዘት ናዳ አውርደናል። እሳቸው ግን ሙሉውን እውነት አልነገሩነም። ምዕራባውያን፤ አንድ ትርከት ሁለት ገጽታዎች አሉት ይላሉ። ብዙዎቻችን የዶ/ር ዮናስን ትርከት ብቻ ተቀብለን፤ የሌላውን ወገን ትርከት እንኳን ሳንሰማ፤ በዓለም ባንክ ድርጊት ቅር ተሰኝተናል። እዚህ ጽሁፍ ላይ የዓለም ባንክን ጉዳይ የማነሳው፤ የዶ/ር ዮናስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያላቸው ጥላቻና ሃገርን አደጋ ላይ ለመጣል የሚነዙት አደገኛ የሃሰት ትርከት ከዚህ ጋር የሚያያዝ እንጂ ከሃገር ጥቅም ጋር የማይገናኝ መሆኑን ለማሳየት ነው።
አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። ሻለቃ ዳዊትና ዶ/ር ዮናስ ከነጽንፈኛና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አጋሮቻቸው ጋር ሆነው ጦርነት ያወጁት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ነው። በዚህ ላይ ይህ ጸሃፊ ምንም ብዥታ የለበትም። ዳዊት በጦር ሜዳ ለመዋጋት ሲያደራጁ፤ ዮናስ በኢኮኖሚ ጦርነት ለመክፈት ተግተው እየሰሩ ነው። ዳዊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ረዘም ያለ ታሪክ ስላላቸው፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ለምን ጦርነት እንዳወጁ በመግለጽ፤ ይህን ለማሳካት የሚያሰራጩትን የሃሰት ትርከት ከቀደም ታሪካቸው ጋር በማያያዝ በመረጃ እሞግታለሁ። ዳዊት በፖለቲካ ታሪካቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፀሙትን በደልና፤ አሁን ነውጥ ለመፍጠርና የመረጡት የመሳሪያ ትግል ጦርነት እንዴት ወደ ውድቀት እንደሚያመራም፤ ሃሳቤን እሰነዝራለሁ። እኔ እስከማውቀው ድረስ ዶ/ር ዮናስ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ናቸው። የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ “ኮኪ አቢሰሎም” በሚል የብዕር ሰም EEDN በተባለ ኔትዎርክ ጽሁፋቸውን ከማየት ውጭ፤ ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስለነበራቸው ተሳትፎ አላውቅም። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1980ዎቹ ለተራበው ሕዝባችን በዋሽንግተን አካባቢ እርዳታ ስናሰባስብም ሆነ፤ ከ1991 (ኣ.አ.አ) አቆጣጠር ጀምሮ የሕወሃትን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ በውጭ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ የተጋጋለ የፖለቲካ እንቃቃሴ ሲካሄድ በቦታው አልነበሩም። እኝህ ሰው በወቅቱ ነዋሪነታቸው ዋሽንግተን አካባቢ ነበር። በዚህ አጭር የፖለቲካ ታሪካቸው እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ፤ ለኢትዮጵያ እንደ ሃገር ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ሲስነዝሩና ሲያስተምሩ የነበረ ቢሆንም፤ የፖለቲካ አውዱንም የበለጠ መርዛማና ለውይይት የማይመች አድርገውታል። ሰዎች፤ እሳቸው በሚሰነዝሩት ሃሳብ ላይ የተለየ ሃሳብ ካንፀባረቁ፤ እነዚህን ሰዎች ለማዋረድ፤ የሚሄዱበት መንገድና፤ ማንም ሃሳባቸውን እንዳይሞግት የሚገነቡት በዘለፋ የታጠረ የእሾህ አጥር፤ “ፈሪ ፍርሃቱን ሲሸፍን ደረቱን ይነፋል” የሚለውን ሃገራዊ ብሒል የሚያስታውስ ነው።
ከጥቂት ወራት ጀምሮ ግን፤ እኝህ ሰው ከአጋሮቻቸው ጋር፤ በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ጦርነት በማወጅ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በችግር እንዲማቅቅ ተግተው እየሰሩ ነው። እኝህ ሰው፤ በተደጋጋሚ የሚያሰራጯቸው ጽሁፎች፤ ከእውነት የራቁ መረጃዎችን የያዙ፤ እውነታቸው ተጣም የቀረቡና፤ በኦሮሞ ጥላቻ ላይ ያውጠነጠነ መሆኑንም በመረጃ እሞግታለሁ። እኝህ ሰው፤ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጁት፤ ከዓለም ባንክ ሥራቸው ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በዓለም ባንክ ለምን ሥራቸውን አጡ፤ ሥራቸውን ካጡ በኋላስ፤ የዓለም ባንክ አቤቱታቸውን ለመፍታት የሄደበት መንገድ ምን እንደሆነ፤ በመጨረሻም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጣልቃ ገብተው ዮናስ ወደ ዓለም ባንክ ሥራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ሲጠየቁ “እምቢ አሉ” ከሚል ብስጭት፤ ዮናስ ለዶ/ር ዐብይ የነበራቸው ድጋፍ እንዴት ወደ ጥላቻ እንደተቀየረና “ዐብይን ለመበቀል” ሃገርን ወደ ሚጎዳ የሃሰት ትርከት እንዴት እንደተሸጋገረ በመረጃ በዚህ ጽሁፍ ይቀርባል።
ዮናስ ከዓለም ባንክ ጋር ያላቸውን ታሪክ ስንመለከት፤ የዓለም ባንክን ለመበቀልና የተቋሙን ሥም ለማጉደፍ ረጅም መንገድ ሄደዋል። ምንም እንኳን የዓለም ባንክ በማያሻማ ሁኔታ ወደ ሥራ እንደማይመልሳቸው የገለፀላቸው በ2005 (እ.አ.አ) ቢሆንም፤ በጠበቃቸው፤ በቀድሞው የቨርጂንያ ዓቃቤ ህግ፤ ኬነት ኩቺኒሊ (Kenneth Cuccinelli) አማካኝነት እንደ ጄሲ ጃክሰን ያሉ ተሟጋቾችን፤ ስመ ጥር የሆኑ ፖለቲከኞችን፤ እንዲሁም እንደ ዋሽንግተን ታይምስ ያሉ ጋዜጦችን፤ በመጠቀም የዓለም ባንክ ላይ ግፊት እንዲደረግ ብዙ ጥረዋል። ሌላው ቀርቶ ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡ ለማድረግ ተሞክረዋል። ይህ ጤናማ ያልሆን ችክታ (obsession) ዛሬ ወደ የምናየው ጤናማ ያልሆነ ወደ ፀረ “ዐብይ” ችክታ ተቀይሯል። እኝህ ሰው፤ የዓለም ባንክ ከሥራ ካባረራቸው ከ 14 ዓመታት በኋላ፤ በ2019 (እ.አ.አ) ለዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት የላኩት ኢሜል የእሳቤያቸውን አደገኛነት የሚያሳይና (እዚህ አልገልፀውም) የዓለም ባንክን የረበሸ እንደነበር የዓለም ባንክ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልፆታል።
ዛሬ ዶ/ር ዮናስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚያቀነቅኑት እሳቤ፤ በሃሰት መረጃዎች የተሞላ፤ ከበቀል የተወለደ፤ አደገኛ መሆኑን በመረጃ አስደግፌ በክፍል ሁለት ላይ አቀርባለሁ። በክፍል ሁለትም፤ የሻለቃ ዳዊትን የተደጋጋመ የሃገር ክህደት፤ ዛሬም ለምዕራባውያን እንድንንበረከክና፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምዕራባውያን ቀና ደፋ የሚል መንግሥት ለመመስረት እንጂ ለአማራም ሕዝብ ሆነ ለማንም ግድ የሌላቸው፤ ከምዕራብውያን የስለላ ድርጅት ጋር በመመሳጠር የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት ተግተው የሚሰሩ መሆናቸውንም በጽሁፌ አሳያለሁ።
ክፍል 2 ይቀጥላል። ቸር ይግጠመን።
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ ሰኔ 17 2015
ማርቆስ ዳዊት says
ምን አለ እውነት ግራም ቀኝም ያለውን ብትጽፍ? ይህ እኮ የመንግሥት ትርክት ነው መሬት ላይ ያለውን ይሕግ ጥሰት የፍትህ አልባነት ሙሰኝነትን ሞት መፈናቀል መዘረፍ መንገላታት መጨፍጨፍ መታፈንን መታሰርን ተጠያቂነት አለመኖርን የማያሳይ ነው ።
ሣህሉ says
በኢትዮጵያ ያለዉን ፓለቲካ እንዴት ልንረዳው እንደሚገባ የሚያመላክቱ መልካም ሃሣቦች/ትንታኔዎች ቀርበውበታል። በጎሣ መነጽር እየተመሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ይሁን እንወክለዋለን ለሚሉት ጎሣ የሚተርፍ ጥቅም እናመጣለን ማለት የሚሆን አይደለም። ጉዳቱ ግን ብዙ ነው። አይተነዋል። በአገራችንም ፣ ከአገር ውጭም። ሕዝብ ሳይሆን ግለሰቦች የሚገኑበት፣ የሚበለጽጉበት ሁኔታ ግን ይኖራል። መሪ ነን የሚሉ ወገኖች ጎሣን እንደ መወጣጫ ተጠቅመው የሚያርፉት ግን የራሳቸው ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ነው። ፀሐፊው ይህን ማሳየት ችሎአል። ምስጋና ይገባዋል። ጽሑፉ ያጠነጠነባቸው ሁለቱ ግለሰቦች ግን “መሪዎች” ሊባሉ የበቁ አይደሉም። ዳዊት በራሱ ቆሞ መሪ ሆኖ አያውቅም። የዳዊት ተከታዮች ነን የሚሉ ሰዎች ስለመኖራቸውም የሚታወቅ የለም። ስለ ራሱም ቢሆን ሌላው ከሚያወራለት ራሱ ስለራሱ የሚያወራ የበዛ ነው። አሁን እንክዋን በእስክንድር ሥር ሆኖ ለማገልገል ፈቃደኛ ሆኖ ያለ ነው። እስከሰራለት ድረስ። የውጭ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት ሰው ስለመሆኑ ግን ማስረዳት ይቻላል። ከአሁን ቀደም የታየ ስለሆነ። መሪ አይሁን እንጂ የተወሰነ የማወክ አቅም ያለዉ ሰዉ ነው። ዶክተሩም የሚያጋጩ ሃሣቦቹን የሜፈልጉ ተቅዋማት የሚጠቀሙበት ከመሆን ባለፈ መሪ ለመባል የሚያስችለውን ሥራ በመሥራት የታወቀ አይደለም። ሁለቱም በተለይ በውጭ ድርጅቶች ውስጥ በሚያውቅዋቸው ሰዎች አማካኝነት አገር ጎጂ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህም ፀሐፊው ቢያተኮርባቸው/ጥፋታቸውን ቢያሳይባቸው ተገቢ ነው። በሃሣብም ይሁን በድርጅታዊ አቅም ” መሪ ” ሊባሉ የሚችሉ ስላልሆኑ በልካቸው ቢገለጡ የለማለት ነው።
Solomon says
Your analysis is perfect. I do agree with you 100%. Keep up the good work! Many of the so called ‘you tuber’ motive is either money or personal vendetta, some are looking for cheap popularity…I am not endorsing some of the weakness of the current government either. If the government is weak and irresponsible then the opposition should work harder to change it in a peaceful and legal manner when election comes not by such bloodshed and chaos. We have been killing each other for ages and we need to break such vicious cycle, not just continuing the cycle. What Dr. Yonas and his circle doing is continuing the cycle…either for vendetta or cheap popularity. The good news is that (Dr. Yonas and his circle) will vanishes into thin air as they don’t have the truth with them, as they do not represent constituencies on the groud in Ethiopia, they are dishonest, phony, and they do not have anything to contribute for the wellbeing of the Ethiopian who are facing the daily reality in Ethiopia. What they are doing is political chicanery…eventually they will vanish into thin air…
Tesfa says
ይህ እጅግ የሚያስገርም ከእውነት የራቀ ጽሁፍ ነው። ሲጀመር አንድ መሪ ስለተመረጠ ባህሪውና አገዛዙ አይፈተሽ ወይም አይወገዝ የሚል ነገር የለም። በመሬት ላይ ያለውን እውነት በመክዳት እንዲህ ያለ ሽፍንፍንና አማቺ ሃሳብ ማቅረብ አሁን ሃገራችን ላለችበት አጣብቂኝ ብልሃት ሳይሆን እሳት ቆስቋሽ ነው። እኔ አንተ በስም እየጠቀስክ እንዲህና እንዲያ ስለምትላቸው ሰዎች ቆመው ያሉት ስለራሳቸው መከራከር ስለሚችሉ አልፌዋለሁ። ለመሆኑ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ ስለሚደረገው አፈና፤ ግድያ፤ እስራትና ድብደባ አልፎ ተርፎም ማፈናቀልና ቤት ማፍረስ የምታውቀው የቱን ያህል ነው? ይገባኛል የሶሻል ሚዲያና የሌሎችም ለትርፍ ወሬ አነፍናፊዎችን በመተው እውነቱን መፈተሽና በዚያ ላይ ብቻ ለህዝባችን ሰቆቃ ዘርና ጎሳን፤ ሃይማኖትን ተገን ሳያረጉ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ እንደመሆን በዘፈቀደ ሰውን እየኮነኑ በማይጨበጥ ዓለም ገብቶ መቦጫረቅ ሃሳቡን የልጆች ጫወታ ያደርገዋል።
ጠ/ሚሩ ያበጁትም ያፈረሱትም ነገር አለ። በብልጽግናው አመራር እልፍ ሰዎች ጦም እያደሩ ነው። እልፎች እየሞቱና እየተሰደድ ነው። ትላንት የራሱን ወታደር በተኛበት ያረደውንና ካሚዪን በላዪ ላይ የነዳውን ጊንጡን ወያኔን አቅፎ በዚህም በዚያም አማራና የአማራ ልጆችን በማሳደድ ላይ ያለው ለሃገር አንድነትና ለህዝቦች ሰላም በማሰብ አይደለም። ግፍ በምድሪቱ ያለቅጥ እየፈሰሰ ሊወድቅ በመንገዳገድ ላይ ላለ መንግስት ጥብቅና መቆም ነጭ ለባሽ መሆን ነው። ለከረፋው የሃበሻ ፓለቲካ መድሃኒቱ እሳት ነው ብለው በቅርብና በሩቅ እሳት እንዲለኮስና ህዝባችን እፎይታ እንዳያገኝ ግፊት የሚያደርጉ እብዶች ብዙ ናቸው። ግን እሳት አመድ እንጂ ሌላ ትርፍ አስገኝቶ አያውቅም። የብሄር ነጻነት ታጋይ ነን የሚሉትም የእድር ጡሩንባ ነፊዎች ከእውነት የራቁ፤ ያለፈ ታሪክ የማይደግፋቸው ባጭሩ ዝናብ የሌለው ደመናዎች ናቸው። 30 ዓመት ሙሉ እልፍ ሰው ያለቀበትና ንብረት የወደመበት የኤርትራው ሃገር መሆን ያስገኘው ሰው ቀየውን እየጣለ መሰደድ ሆኗል። ትላንት ኢትዮጵያ በቃችን፤ ቅኝ ግዛት አርጋን እያሉ ረግጠዋት የሄድት ኤርትራዊያን ዛሬ ተመልሰው መጠለያ ያደረጓት ይህችን መከረኛ ሃገር ነው። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን እንዲያ ተዋርፈው ደ/ሱዳን ከስመ ነጻነቱ በህዋላም እርስ በእርስ እየተናቆሩ መሆኑ የአፍሪቃን የብሄር ነጻነት ጥያቄን የውስልትና ፓለቲካ አድርጎታል። ከቁራሽ የተረፈችው ሱዳን ደግሞ ሃገር መሆኗ እያከተመ ነው። ስለሆነም የሃበሻ የብሄርተኝነት ፓለቲካ የውሻ ፓለቲካ ነው። ዛሬ ጊዜ ሰጠን በማለት በወረፋቸው ወያኔን ተክተው ሰውን ሰቆቃ ውስጥ የሚከቱት የኦሮሞ ጽንፈኛና አፍራሽ ሃይሎች ከታሪክ የማይማሩ በራሳቸው እይታ የተሳከሩ የመከራ ዶፍ አዝናቢ ስብስቦች ናቸው። እንግዲህ አቶ ጥበበ በሃሳብ የተሟገተላቸው የደም ሰዎች እነዚሁ የዶ/ር አብይን መንግስት የሙጥኝ ያሉ በራሳቸው ማሰብ የተሳናቸውን የጅምላ ቱልቱላዎችን ነው። አንድ ሰው ለመግደል ህንጻውን ማቃጠል – በአዲስ አበባ እልፍ ቤት ሲፈርስና ሰው ሲፈናቀል የት ነህ? ጄ/ጻድቃን ቤተሰቡን አሜሪካ ሂዶ እንዲጠይቅ ሲፈቀድለት የታመመው ጄ/ተፈራ ማሞ መከልከሉ ከምን የመነጨ ነው? ዛሬ በአዲስ አበባ እስር ቤቶች የሞሉት በአማራ ተወላጆች መሆኑ ሚስጢሩን ትረዳለህ? ወይስ በእውን ህገመንግስት ለመናድ የተደረገ እንቅስቃሴ አለ? ልክ እንደ ወያኔ ዘመን በፈጠራ ክስ ሰውን ዘብጥያ ማውረድ፤ ገድሎ ማልቀስ የተለመደ የሃበሻ የፓለቲካ ድራማ ነው። ግን በዚህ የአስረሽ ምቺው ፓለቲካ አንድም አትራፊ አይኖርም። ለጊዜው በዝርፊያው፤ በእገታው፤ በጉቦውና በክራይ ሰብሳቢነት ሰው ሃብታም ሊሆን ይችላል። እልፍ እያለቀሰ ሃብት አእምሮ ላለው ፍጡር እንቅልፍ ይነሳል።
ባጭሩ ጸሃፊው ሁለተኛ ክፍል አለኝ ብሏል ያንም በጊዜው ሲለጠፍ እናያለን። ለአሁኑ ግን ነገራችን ሁሉ ሊታይ ሊዳሰስ በሚችለው እውነታ ላይ ተመርኩዘን ሃሳብ ብናጋራ የተሻለ ይመስለኛል። አሳባቂው ፓለቲካ ያኔም ሰውን አጨራርሷል አሁንም እያስጨረሰ ነው። ለማንም አይበጅም። በጎው ነገር ለሰው ልጆች ልዕልና እውነትን ተመርኩዞ ግፈኞችንና ጠበንጃ አንጋቾችን በሃሳብም ሆነ በመረጡት መንገድ መፋለም የተሻለ ይመስለኛል። በቃኝ!