
በኢህአዴግ የተሰየሙት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በሰኔ ወር መገባደጃ አካባቢ ወደ አሜሪካ ጉዞ እንደሚያደርጉ ታወቀ። በቆይታቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ በተለይ በሰላማዊ መንገድ ትግል ከሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ጋር በግልና በቡድን በመገናኘት ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ተነግሯል።
በህወሓት/ኢህአዴግ ስያሜ የጠቅላዩን መንበር የተቆናጠጡት ዓቢይ አህመድ ላለፉት በርካታ ሳምንታት በአገር ውስጥ እና በአጎራባች አገራት ጉብኝቶችን ሲደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቀጣይ የተያዘው መርሃግብር ወደ አውሮጳና አሜሪካ ጉዞ ማድረግ እንደሚሆን መረጃዎች ሲወጡ ነበር። ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ የጠቅላይ ሚ/ሩ የአሜሪካ ጉብኝት መረጃ ቀደም ብሎ የደረሰው ቢሆንም በወቅቱ የተባለው በሰኔ ወር መገባደጃ ወይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ንግግር ለማድረግ በመስከረም አካባቢ ሲመጡ ሊሆን ይችላል የሚለው ነበር።
ዛጎል ታማኝ ምንጮቼ ያደረሱኝ መረጃ ነው በሚል በድረገጹ ላይ እንደገለጸው ጠ/ሚ/ሩ “ሰኔ 26 ወይም 27 ወደ አሜሪካ እንደሚያቀኑ” ተናግሯል። ሲቀጥልም የዓቢይ አህመድ ጉብኝት “በአሜሪካ በኩል ሙሉ ድጋፍ ያለውና አስፈላጊው ሁሉ ትብብር የሚደረግለት” መሆኑን አስታውቋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አዙሪት ያሳሰባት አሜሪካ በአገሪቱ የሰከነ የፖለቲካ ለውጥ እንዲኖር፣ ለዚሁም ተግባራዊነት ድጋፍ የምታደርግ፣ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ይህንን ለውጥ የማይቀበል ከሆነ ኮሮጆውን እስከማድረቅ የሚያደርስ እርምጃ እንደምትወስድ እያስጠነቀቀች መቆየቷ ይታወሳል። በሂደት ላይ ያሉ የህግ ጉዳዮችም አሉ። በዚሁ ቅኝት መሰረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የአሜሪካ ጉዞ በዲያስፖራውና በመንግሥት በኩል ያለውን ልዩነት ለማርገብ፣ የወደፊቱን የለውጥ ሂደት የማስረዳትና በዝርዝር የማሳየት እንዲሁም አፋኝ የሚባሉት ህጎችን አስመልክቶ የሚደረገውን ማሻሻል በይፋ የማሳወቅ ነው። ተያይዞም አገራቸው መግባት ለሚፈልጉ በይፋ ዋስትና የሚሰጥ ግብዣ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።”
ጊዜው ሲደርስ የሚታወቅ ቢሆንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉብኝት ወቅት በዳስፖራው ፖለቲካ ላይ በጉልህ የሚታወቁ በተለይም በሰላማዊ (ነውጥ አልባ) መንገድ ትግላቸውን ለዓመታት ሲያካሂዱ ከነበሩ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጋር ይገናኛሉ ተብሏል። እነዚህም በድርጅት ተደራጅተውም ይሁን በግላቸው በአገራቸው ጉዳይ ላይ የሚወተውቱትን እንደሚካትት ታውቋል።
“በዚሁ መሰረት ውይይቱ ከመዘላለፍ፣ ከሁከትና ውጤት ከማያስገኝ እንከኖች የጸዳ ይሆን ዘንድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንን” ዛጎል የመረጃ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። ሲቀጥልም “(የዜናው አቀባዮች) ስለ አጠቃላዩ ዝግጅት ከመናገራቸው ውጪ ስለሚደረገው ዝግጅት በዝርዝር አላብራሩም፤ የአሜሪካ ሚና ምን እንደሚሆንም አላስታወቁም” ብሏል።
የጠቅላዩን ጉዞ በአዎንታዊ መልኩ የሚመለከቱ ወገኖች ጉብኝቱን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ለበጎ ውጤት እንጠቀምበት በማለት ይመክራሉ። ጠቅላይ ሚ/ር ዓቢይ አህመድ የዳያስፖራውን ኃይል በሚገባ የተገነዘቡና ይህንንም በአደባባይ የተናገሩ መሆናቸውን የሚጠቅሱ ክፍሎች ዳያስፖራው ካለው ሙሉ የመናገር መብት አኳያ አገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ በድፍረት ሊናገር የማይችለውን በማንሳት ለወገኑ ያለውን ተቆርቋሪነት ማሳየት ይገባል ይላሉ። ከዚህ በፊት የህወሓት ኃላፊዎች በድብቅ መጥተው በድብቅ መሄዳቸው አግባብነት የለውም በሚል ትልቅ ተቃውሞ ይደርስባቸው እንደነበር የሚያስታውሱ ወገኖች በገሃድ እንወያይ የሚል መሪ ሲመጣ በጭፍን ከመቃወም ይልቅ “እኛም የምንፈልገው ይህንን ነበር” በሚል በሰከነ መንፈስ የጉብኝቱ አካል መሆን ይገባቸዋል በማለት ሃሳብ ይሰጣሉ።
ጉብኝቱ ዋሽንግቶን ዲሲ በሚገኘው ኤምባሲ የበላይ ኃላፊነት የሚቀናበር ከመሆኑ አኳያ እዚያ ያሉት የህወሓት ሎሌዎች ውይይቱንም ሆነ ስብሰባውን በዳስፖራው ስም በደጋፊዎቻቸውና በአፍቃሪ ህወሓቶች ጠለፋ እንዳያካሂዱበት ካሁኑ ጠንቅቆ በመጠበቅ አስፈላጊውን የቤት ሥራ መሥራት እንደሚገባ ጎልጉል ያነጋገራቸው የዳያስፖራ አካል ተናግረዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
በምን ነጥብ ላይ?? በህገ መንግሥቱ? በመሬት ሥሪት? በክልላዊ ኣስተዳደር?