
በ116ኛው የሠራዊት ቀን ሲከበር ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበትን ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” በማለት ቀኑ ለምን እንደተመረጠ ይፋ አደረጉ።
ከዚህ ሌላ ፊልድ ማርሻሉ በንግግራቸው፤
ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ከጀግኖች የተረከብናትን ኢትዮጵያ እንደተከበረች እና ማንነቷ እንደተጠበቀ ለማስቀጠል ወታደራዊ ዝግጁነታችንን አሳድገንና ቁመናችንን አዘምነን ማንኛውንም ተልዕኮ በላቀ ብቃት ለመፈጸም ሠራዊቱ ዝግጁ መሆኑን አሣውቀዋል።
የሠራዊቱ አባላት የተሠጣቸውን ታላቅ አደራ በድል ለመወጣት የመፈጸም ብቃታቸውን በማሣደግ በዓላማ ጽናታቸው እንዲቀጥሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳስበዋል፡፡
ሠራዊቱ ሀገሩን እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ረገድ ሄላፊነቱን በብቃት እየተወጣ መሆኑን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የታጠቁ ኃይሎችን እና ኢ- መደበኛ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት እየተሠራ ያለው በሱዳን የተከሰተው ችግር በኢትዮጵያም እንዳይደገም በማሰብ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
የምድር ሃይል፣ የአየር ሃይል ፣ የባሕር ሃይል እና የሳይበር ኃይሎቻችንንም ዘመኑን እና ኢትዮጵያን በሚመጥኑ መልኩ እየገነባን የተሻለ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ ችለናልም ብለዋል።
የካቲት 7 ቀን 1987 ዓ.ም የሠራዊት ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑ ወገንተኝነት የፈጠረው አንዱ ታሪካዊ ስህተት መሆኑንም አንስተዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተሳሳተውን ውሳኔ በማሥተካከል የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊት እንደ ተቋም የተመሠረተበት ቀን ጥቅምት 15 እንዲሆን መወሠኑን ተናግረዋል። በመሆኑም “ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበትን ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላን) የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር አድርገው የሾሙበት እና ሠራዊቱ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን መሠረት የጣሉበት መሆኑን የጠቆሙት ፊልድ ማርሻሉ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሠራዊቱ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እንዲቀረፅ በሳል አመራርነት ሰጥተዋል ብለዋል።
116ኛው የሠራዊት ቀን ለሀገራቸው በየዘመናቱ መስዋዕት የከፈሉ ጀግኖችን የምንዘክርበት ቃላችንን የምናድስበት እና ይበልጥ ለማንኛውም ተልዕኮ የምንነሳሳበት ዕለት ነው። (የመከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply