የካቲት 13፣ 2009 ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸውና የጎንደር ከተማ ከንቲባ ተቀባ ተባባል በአንድነት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን ባንጋገሩበት ወቅት ገዱ አንዳርጋቸው “መንግሥት የለም” እየተባለ የሚነገረውን የሚያረጋግጥ አስተያየት መስጠቱ ተስማ።
እንደ ፋና ዘገባ ከሆነ ከተሰብሳቢው ለደመቀ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውለታል፡፡ ፋና ይፋ ባያደርገውም በውይይቱ የከረሩ ጉዳዮች መነሳታቸው ከአንዳንድ ምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡
ደመቀ በገለጻው “ጥልቅ ተሃድሶ፤ መልካም አስተዳደር፤ የህዝብ ተሳትፎ፤ …” በማለት ተሰብሳቢውን ለማሳመን ጥረት ቢያደርግም የተቻለው እንዳልሆነ ፋና ራሱ ከዘገበው ለመረዳት ቻላል፡፡
“… ተሃድሶው አንዱን አመራር ወደ ሌላ ስፍራ ከመቀየር የዘለለ ለውጥ እያመጣ አይደለም” የሚል አስተያየት ከውይይቱ ተሳታፊዎች መነሳቱን የጠቆመው የፋና ዜና ለዚህ ጥያቄ ደመቀም ሆነ ገዱ ወይም ከንቲባው የመለሱትን አልዘገበም።
ሁለቱ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት መድረኩ ላይ እርስበርሱ የሚጣረስ ሃሳብ ሲሰጡ ተሰምተዋል፡፡ ደመቀ “ባለፉት ወራትም ሀገሪቱ ወደነበረችበት ሰላም መመለስ ችላለች” በማለት ቢናገርም ገዱ አንዳርጋቸው በበኩሉ፥ “ባለፉት ስድስት ወራት በጎንደር የኢንቨስትመንት ጥያቄ ቀንሷል፤ ስለ ጎንደር የሚነሱ አሉባልታዎችን ወደጎን በመተው የከተማዋን ገፅታ መቀየር ይኖርብናል” በማለት የደመቀን “ሰላም ነው” ንግግር ውጤት አልባ አድርጎታል።
ከዚህ በተጨማሪም ገዱ አስተዳድረዋለሁ በሚለው ክልል እርሱ “አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች” በማለት የጠቀሳቸው “የሚጠበቅባቸውን ግብር እየከፈሉ” አይደሉም በማለት መናገሩን የዜና ዘገባው አስረድቷል።
“መንግሥት ባለበት እና የመንግሥት መዋቅር ባለበት ቦታ ሕግ አለ፤ በሕጉ መሠረት ግብር ይሰበሰባል፤ ነገር ግን በሕዝብ አስተሳሰብ ውስጥ መዋቅር ፈርሷል፤ መንግሥት የለም፤ ወዘተ የመሳሰሉ አስተሳሰቦች በሚሰርጹበት ጊዜ ህዝብ እንደዜጋ የሚጠበቅበትን ግብር አልከፍልም ወደማለት ይሄዳል” በማለት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሕግ ባለሙ ለጎልጉል አስያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ የገዱ አንዳርጋቸው ንግግር ጎልጉል (የካቲት 13፤ 2009ዓም፤ February 20, 2017) ከሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ መረጃ በመሰብሰብ ያጠናቀረውን ዘገባ የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ ዘገባው ህንን ይል ነበር፤
“… በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያላቸዉን ስፍራዎች በተለይም ታች አርማጭሆ፣ ምዕራብ አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣ መተማ፣ ወገራ፣ ምዕራብና ምስራቅ በለሳ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በዋናነት የእምቢተኛነቱ እምብርት እንደሆኑ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በዝርዝር ባይገለጽም ጎጃም አንዳንድ አካባቢዎችና ሰሜን ሸዋ የኅቡዕ ጥቃት እንደሚፈጸም ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። በሰሜኑ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ ወረዳዎች ከአርሶ አደሮች መሰብሰብ የነበረበት የ2008 ዓ.ም የመሬት ግብር እና የማዳበሪያ ዕዳ እስካሁን ሊሰበሰብ አለመቻሉ ትልቁ የመዋቅር መሰበር አመላካች ተደርጎ መወሰዱን የጎልጉል የአካባቢው መረጃ አቀባይ አስታውቋል። መረጃ አቀባዩ እንዳለው ራቅ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች የማህበራዊ ተቋማት (ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የግብርና ጣቢያዎች) ወደ ቀድሞ መደበኛ ሥራቸዉ መመለስ አልተቻላቸውም።”
ከበርካታ ቦታዎች ውጥረት ውስጥ የገባው ህወሃት/ኢህአዴግ መጪውን የማሟያ ምርጫ ለማለፍ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጋ ይገኛል፡፡ በዳያስፖራ ያለው ኃይል ተባብሮ መሥራት አቅቶት ነው እንጂ ከሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በኋላ ይህንንም ያህል አይቆይም የተባለለት ህወሃት/ኢህአዴግ ዕርቅ፣ ሽምግልና፣ ድርድር፣ አብሮ መሥራት፣ ህዝባዊ ተሳትፎ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ … የመሳሰሉ ዕቅዶችን ወጥኖ ሕዝቡን ለማሳመን እየጣረ ነው፡፡
በአማራና በኦሮሚያ በግፍ ያፈሰሰውን ደም በገንዘብ መተካት የሚችል ይመስል ለወጣቶች ሥራ ዕድል እፈጥራለሁ እያለ ነው፡፡ በዚሁ ጎንደር ላይ በተደረገው ስብሰባ እነ ደመቀ በመላው ኢትዮጵያ 3ሚሊዮን፤ በአማራ ክልል ደግሞ ለ800 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል እንፈጥራለን በማለት ህዝቡን ለመደለል ሲሞክሩ ተሰምተዋል።
የዛሬ ዓመት አካባቢ ህወሃት/ኢህአዴግ በኦሮሚያ ላፈሰሰው ደም በ2.4 ቢሊዮን ብር ሥራአጥ ወጣቶችን ባለሃብት አደርጋለሁ በማለት በኦህዴድ በኩል ሲያስነግር መቆየቱ የተዘገበ ጉዳይ ነበር፡፡
“መንግሥት የለም” የሚለው አካሄድ በሕዝቡ ዘንድ የፈጠረው የስነልቦና ተጽዕኖ ህወሃት/ኢህአዴግን ክፉኛ ችግር እንደሆነበት ከተለያዩ ቦታዎች የሚሰሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply