በጋምቤላ የአኙዋክ ተወላጆች ተጨፍጭፈውና ከመሬታቸው ተፈናቅለው “ለሰፋፊ እርሻ” በሚል ሲቸበቸብ ከነበረው መሬት “ወደ ሥራ የገባው” 15በመቶው ብቻ መሆኑን ህወሃት/ኢህአዴግ አስታወቀ፡፡ ለ“እርሻ ልማት” በሚል 5ቢሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷል፡፡ የመሬት ካርታ “ከቢሮ ውጪ በመኖሪያ ቤቶችና በጫት ቤት ውስጥ” ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊ የነበረው ኢሳያስ ባህረ ከሥልጣኑ የተነሳው “ብድር በመስጠቱ ሂደት ለተወሰኑ የባለሃብቶች ቡድን በማድላቱ ነው” ተባለ፡፡ በጋምቤላ በደል ደረሰብን በማለት አቤቱታ ያሰሙ የትግራይ “ባለሃብቶች” ለሃይለማርያም የቀረበው ሪፖርት “የተዛባ ነው” አሉ፡፡
በጋምቤላ ይህ ነው የማይባል ግፍና የዘር ማጽዳት ተካሂዶ ከምስኪን ረዳተቢሶች የተነጠቀው መሬት ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ገና ከጅምሩ አሠራሩ ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ በተለያዩ ሪፖርቶች ሲነገረው የነበረው ህወሃት/ኢህአዴግ የጋምቤላ አኙዋኮችን ከምድራቸው ላይ በማጥፋት መሬታቸውን ከነጠቀ በኋላ “ሰፋፊ እርሻ” በሚል አንዱን ሔክታር መሬት በሃያ (20) ብር ሲቸበችበው ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 3ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከነዋሪዎች እየተነጠቀ፣ ደን እየተጨፈጨፈ፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ የህወሃት/ኢህአዴግንና የደጋፊዎቹን ኪስ ሲያደልብ ድርጊቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ሲነገር “እኛን የሚያሳስበን በሊዝ ያልሸጥነው መሬት ነው” በማለት ሞት እንደ ቡሽ ክዳን በድንገት የነቀለው መለስ ተናግሮ ነበር፡፡
ስምንት ዓመታት ተቆጥረው፣ የሰው ነፍስ ከትንኝ ያነሰ ደረጃ ወርዶ፣ በግፍ ተጨፍጭፎ፣ ቀሪው ኑሮው ተመሳቅሎ፣ መሬቱ ተነጥቆ፣ ወደማይፈልግበት ቦታ በግዳጅ ሰፈራ ተወስዶ፣ የተፈጥሮው ደን ተጨፍጭፎ፣ ኑሮው ከሞት በታች ከሆነ በኋላ ህወሃት/ኢህአዴግ አደረግሁ ባለው ጥናት መሬቱም፣ ብድሩም ከንቱ ሆኗል፤ “ኢንቨስተሮቹ” ገንዘቡን አባክነውታል፤ “ለመንግሥት” የገባ ጥቅም የለም፤ ትርፉ ኪሣራ ነው ብሏል፡፡
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት (ታህሳስ 10 እና ታህሳስ 11) ለሃይለማርያም ደሳለኝ ሪፖርት ቀረበ በማለት ፋና እንደዘገበው ከሆነ በጋምቤላ እየተከናወነ ነው ሲባል የቆየው የሰፋፊ መሬት ኢንቨስትመንት ከሽፏል፡፡ በጋምቤላ በሰፋፊ እርሻ ስም ከተሰጠው “630 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ወደ ስራ የገባው ከ15.5 በመቶ” ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በእርሻ ንግዱ ላይ የተሰማሩ ተብለው የተጠቀሱት “ባለሃብቶች” 780 የነበሩ ቢሆንም አሁን ወጣ በተባለው ሪፖርት 623 ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡ 157ቱ እንደ ኮንዶሚኒየም ጠፉ ባይባልም “በመረጃ ልውውጥ ክፍተት” ያልተገኙ ተብለው በሙያዊ ቃል ተገልጸዋል፡፡ እነዚህ 157 “ባለሃብቶች” ብድር ይወሰዱ፤ መሬት ይረከቡ፤ የፋና ዜና አልጠቀሰም፡፡
ባለፈው “የጋምቤላ እርሻ ባለሐብቶች የሕብረት ሥራ ማኅበር” አቤቱታ አሰሙ በተባለበት ወቅት የማህበሩ ኃላፊ አቶ የማነ አብዛኛው በጋምቤላ በእርሻ የተሰማራው “ባለሃብት ባጋጣሚ የትግራይ ተወላጅ” መሆኑን ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲገዛ የነበረው ኢሳያስ ባህረ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ከ623ቱ “ባለሃብቶች” መካከል 200ው 4.96 ቢሊዮን ብር ከባንኩ ወስደዋል፡፡ ከእነዚሁ “623 ባለሃብቶች ውስጥ ለ381 ባለሃብቶች ከ45 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተደራርቦ” የተሰጠ ሲሆን ባንኩም ለእነዚሁ ድራቢ መሬት ለወሰዱ “ባለሃብቶች” ድራቢ ብድር ሰጥቷል፡፡
ብድሩ ሲፈቀድ በብድሩ ማመልከቻ ላይ ብድሩ የሚውልበት ዝርዝር ይጠቀሳል፤ ይህም ማለት ብድሩ የተሰጠው “ለመሬት ልማት፣ ለማሽነሪ ግዥ፣ ለካምፕ ግንባታ እና ለስራ ማስኬጃ የተሰጠ ሲሆን፥ ከአጠቃላዩ ብድር ውስጥ” 2 ቢሊየን ብሩ “ለመሬት ልማት ተብሎ ለ194 ባለሃብቶች ተሰጥቷል” በማለት ሪፖርቱ ማስረዳቱን ፋና ዘግቧል።
“ባለሃብቶቹ በዚህ ገንዘብ 314 ሺህ 645 ሄክታር መሬት እንዲያለሙ ቢጠበቅም (እነርሱ) ያለሙት ግን 55 ሺህ ሄክታሩን” ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ሰፋፊ እርሻ እናለማለን ብለው መሬትም ብድርም ሲወስዱ ከነበሩት 623 “ባለሃብቶች” መካከል 40 በመቶ ያህሉ (242ቱ) “ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚዎች ናቸው”።
ይህ ሁሉ ብር የት ገባ? “ባለሃብቶቹስ” ምን እያደረጉ ነው? በመሬት ስም የወሰዱትንስ ብር ምን “ሠሩበት”?
አሉ፣ ያለማሉ፣ ይሠራሉ፣ ይለፋሉ፣ ልማታዊ ዜጎች ናቸው የተባለላቸው 29ኙ “ባለሃብቶች በስፍራው አልተገኙም”፡፡ ይህ ብቻ አይደለም “14 ባለሙያዎች ተሳተፉበት” የተባለው ጥናት “በሰፋፊ እርሻ” ስም ከተፈቀደው 5 ቢሊዮን ብድር ውስጥ 25በመቶው ማለትም “ለሥራ ማስኬጃ” በሚል የተለቀቀው “1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለምን አላማ እንደዋለ ለመተንተን” አልቻለም፡፡ ለመተንተን ያልተቻለው ገንዘቡ እንዳይተነተኑ ልዩ ፈቃድ በተሰጣቸው ወይም በማይተነተኑ የህወሃት “የመሬት ከበርቴዎች” እጅ ስለገባ ይሆን? ምንም የተባለ ነገር የለም!
“የጥልቅ ተሃድሶ” መንፈስ የተጠናወተው የተባለለት ሪፖርት ሌላም ጉዳይ “አጋልጧል”፡፡ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ለእርሻ ልማት ብቻ እንዲገቡ ከተደረጉት “565 ትራክተሮች ውስጥ መስክ ላይ የተገኘው 312፣ ከ731 ማረሻ የተገኘው 523፣ ከ261 ፒክ አፕ ተሽከርካሪ የተገኘው 102፣ ከ62 ዶዘር 42 ብቻ የተገኘ” ነው ይላል፡፡ በእንግሊዝኛ የሚታተመው አዲስ ፎርቹን እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ “ከ242ቱ የቀረጥ ነጻ ዕድል ከተሰጣቸው ባለሃብቶች” መካከል አንድ ስሙ ያልታወቀ “ልማታዊ ባለሃብት” 78 መኪናዎችን ሳንቲም ቀረጥ ሳይከፍል ማስገባቱን ዘግቧል፡፡ ፎርቹን ያነጋገረው የባንኩ ከፍተኛ አመራር “መኪናዎቹ ሊሸጡ አይችሉም፤ ምክንያቱም ሲገቡ ባንኩ ይመዘግባል ስለዚህ ይህ ሊከሰት አይችልም” ካለ በኋላ “ይህ ሊሆን የሚችለው ገና ከጅምሩ መኪናዎቹ ሲገቡ ካልተመዘገቡ ነው” በማለት ለማስተባበል ሞክሯል፡፡
መሬት አለማለሁ፣ ምርት አመርታለሁ ብሎ ከባንክ ብድር የወሰደ ሌላው “ባለሃብት” “ከ261 ሜትሪክ ቶን በላይ ብረት ከቀረጥ ነጻ አስገብተው ብረቱ በቦታው አልተገኘም” ተብሎለታል። ሌላኛው ደግሞ በእርሻው ላይ ካምፕ ለመሥራት በሚል ከ3 ሚሊዮን በላይ የብድር ብር ከፍሎ 500ቶን ብረት ወደ አገር ውስጥ ካስገባ በኋላ ሳይጠቀምበት እዚያው ቀርቷል፡፡
የኢሳያስ ባህረ ጉዳይ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲመራ የቆየውና በመሬት ጉዳይ ከከበሩ ቁልፍ የህወሃት ሰዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ኢሳያስ ባህረ ነው፡፡ በጋምቤላ የአኙዋክ ወገኖች በግፍ ከተጨፈጨፉ በኋላ ህወሃት ሁኔታውን “አረጋግቻለሁ” በማለት መሬቱን በሊዝ መቸብቸብ ሲጀምር ኢሳያስ ደግሞ የብድሩ ቸብቻቢ ነበር፡፡ ይህ መሆን ከጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኢሳያስም ባንኩን ለስምንት ዓመታት መርቷል፡፡
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ለመሬት ልማት በሚል ብድር ሲፈቅድ የኖረው ኢሳያስ ለሪፖርተር በሰጠው ቃል አልሚዎች ከግብርና መሬት አስተዳደር በክልል ውክልና የወሰዱትን መሬት ለማልማት ወይም በቀጥታ ከክልል የወሰዱትን መሬት “ለማልማት አስፈላጊ መሥፈርቶች አሟልተው ሲቀርቡ ባንኩ ብድር ይሰጣል” ብሏል፡፡ ነገር ግን ይፋ ተደረገ በተባለው የምርመራ ሪፖርት መሠረት ኢሳያስ “መሥፈርቶች” ካላቸው አንዱ የሆነው የመሬት ካርታ “ከቢሮ ውጪ መኖርያ ቤት ብሎም በጫት ቤቶች ውስጥም ጭምር” እየተሠራ ለብድር ማስፈቀጃነት ቀርቦ ብድር መፈቀዱን መስክሯል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን “ግለሰቦች በአራጣ የተበደሩትን ገንዘብና የራሳቸው ያልሆነ ንብረትን ለባንክ ብድር አላማ ሲያቀርቡ ከመንግስት አካላት ድጋፍ ነበራቸው” በማለት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ይህንን ለማስፈጸምና ብድር ለማስፈቀድ አስፈላጊ በሆነው የመሬት አሰጣጥ ላይ “የመንግስት ባለስልጣናትና ባለሀብቶች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ነበራቸው” ሲል ሪፖርቱ ቢናገርም እነዚህ በመለስ አነጋገር “የመንግሥት ሌቦች” እነማን እንደሆኑ ሪፖርቱ ማስረዳቱን ፋና አልዘገበም፡፡
የዛሬ ወር አካባቢ “የእርሻ መሬቶች፣ እንዲሁም ብድርን በተመለከተ የተፈጠሩ ችግሮች ላይ በተሰናዳ ጥናት ላይ ለመነጋገር” በሚል ከላይ አሁን ይፋ የሆነው ሪፖርት ለሃይለማርያም ቀርቦለት ነበር፡፡ ዋናው አጀንዳ በጋምቤላ ከሰፋፊ እርሻዎች ጋር በተያያዘ ያለውን ብልሹ አሠራር ለመገምገም ሲሆን እንደ ሪፖርተር ዘገባ ኢሳያስ ባህረን ጨምሮ በሚኒስትርነትና በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ የኢህአዴግ ሹሞች ተገኝተዋል፡፡ ግምገማው ጠዋት ከተካሄደ በኋላ ከሰዓት ኢሳያስ ባህረ በቀጭን ደብዳቤ ከሥልጣኑ ተነስቷል፡፡ “የተነሳሁበት ምክንያት ግልጽ አልሆነልኝም” ያለው ኢሳያስ “ባንኩ በትኩስ ኃይል እንዲመራ ለማድረግ” ይሆናል የተነሳሁት በማለት ከሥራ የተባረረበትን ምክንያት አቅጣጫ ለማስቀየር ሞክሯል፡፡ አዲስ ፎርቹን ባተመው ዜና መሠረት ኢሳያስ ባህረ ከሥልጣኑ የተነሳው “ብድር በመስጠቱ ሂደት ለተወሰኑ የባለሃብቶች ቡድን በማድላቱ ነው” ብሏል፡፡ ኢሳያስ ባህረ በጌታሁን ናና ተተክቷል፡፡
“የጋምቤላ እርሻ ባለሐብቶች የሕብረት ሥራ ማኅበር” ሊቀመንበር የሆኑት አቶ የማነ ሰይፉ ባለፈው ሳምንት ለቪኦኤ የትግራይ ዘጋቢ በሰጡት ቃል አንድ ሺህ የሚሆኑ በጋምቤላ ሰፋፊ እርሻ ላይ የተሰማሩ የትግራይ ተወላጆች በማንነታችን ብቻ በደል ደርሶብናል ብለዋል፡፡ ሊቀመንበሩ በግልጽ ባይናገሩትም ከኢሳያስ ባህረ መነሳት በኋላ ብድር ተቋርጦባቸዋል፣ ሄክታር 30 ብር ግብር ይከፍሉ የነበረው አሁን በቅጽበት ወደ 111 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል፤ የባንክ ብድር ወለድም ከ8.5 ወደ 12.5 ከፍ ተደርጎባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው “በማንነታችን ሳቢያ /ትግሬ ስለሆን” እና እኛን አክስሮ ከጫወታ ውጪ ለማድረግ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
አቶ የማነ “በደል” ደረሰብን በማለት ገለጻ የሰጡበት መሬት ከ400 በላይ አኙዋኮች የተጨፈጨፉበትና በሺዎች የሚቆጠሩ ቀያቸውን ጥለው በግዳጅ የተፈናቀሉበትን ነው፡፡
በጋምቤላ “የሰፋፊ እርሻ መሬት” የምርመራ ሪፖርት ይፋ ከሆነ በኋላ አቶ የማነ ለፎርቹን በላኩት ኢሜይል ዘገባው “የማያስተማምን፣ ያልተረጋገጠ” በማለት በሪፖርቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም “ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያሳስት ዘገባ ነው ያቀረበው” ብለዋል፡፡
“ሙስናን እዋጋለሁ” እያለ የሚፎክረው ህወሃት/ኢህአዴግ ይህ የአሁኑ “ዘመቻው” አዲስ አይደለም፡፡ የቅርቡን ብንጠቅስ ዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ “ዋናዎቹን ሌቦች ትቶ ሙስናን በስንጥር” መጀመሩን ጎልጉል ዘግቦ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በዋቢነት ያቀረብነው ጠቅላይ ኦዲተር 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ በማለት ባቀረበው ሪፖርት ላይ በመመርኮዝ ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላም የሚታየው ነገር እየባሰ መሄዱን እንጂ መሻሻሉን አይደለም፡፡ አሁንም ለሰፋፊ እርሻዎቹ ሥር የሰደደ ችግር መፍትሔ ሆኖ የቀረበው “የፌዴራል መንግስት በውክልና ከክልሎች መሬት ተረክቦ” ማስተዳደሩን ማስቀረት ነው ተብሏል፡፡ በሌላ አነጋገር የህወሃት ሰዎች በፌዴራል ሥልጣን ላይ ሆነው በየክልሉ መሬት መቸብቸባቸውን ትተው በየክልሉ በሚኖሯቸው ወኪሎቻቸው ችብቸባውን ይቀጥሉ እንደማለት ነው፡፡
በጋምቤላ የአኙዋክ ወገኖች ከትንኝ ባነሰ ሁኔታ በመለስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ እንዲሁም በሌሎች የህወሃት አመራሮች ትዕዛዝ አስፈጻሚነት የተፈጸመው ጭፍጨፋ ፍትህ ሳያገኝ ስለ መልካም አስተዳደርም ሆነ ስለ ሙስና የሚወራው ከጉንጭ አልፋ ግምገማና ከሪፖርት አያልፍም በማለት ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸው ይናገራሉ፡፡ ዋና ዋናዎቹ “የመንግሥት ሌቦች” ላለፉት 25 ዓመታት አገሪቱን እንደመዥገር ተጣብቀው እየመጠመጡ እያሉ ሙስናን እዋጋለሁ ማለት ከህጻን ልጅ ጨዋታ ያላለፈ ነው በማለት እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ምግባረ ብልሹዎቹ የመልካም አስተዳደር ሰባኪዎች መሆን እንደማይችሉት ሁሉ በሙስና “የበሰበሱት” ዋንኛ የመሬት ከበርቴዎች የሙስና ፊት አውራሪዎች ሊሆኑ አይችሉም፤ የሙስናው “ሻርኮች” እስካልተደፈሩ ድረስ ህወሃት/ኢህአዴግ “በጥልቀት” ሳይሆን የሚታደሰው በጥልቀት ወደ ጥልቁ ነው የሚሄደው ይላሉ፡፡ (የመግቢያ ፎቶ: Photo: አጄም ኦጋላ National Geographic)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Tesfa says
ከቁርስራሽ የተረፈችው ሃገራችን ዛሬ የገባችበት ገመና አዕላፍ ነው። በውጭ እድገት አለ፤ ሰው ኑሮው ተሻሽሎአል እየተባለ በወያኔ ሚዲያ ይዘመርልናል። ውስጠ ነገሩ ግን ሃገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ የሌላት፤ በስልጣን ላይ ያለው የወያኔ መንጋ እንደፈለገ የሚፈነጭባት፤ በዛው ዙሪያ ፍርፋሪ ለቃሚዎች ደፋ ቀና የሚሉባት አሸንክታቧዋ የበዛ አንገት የሌላት ሃገር ናት። ባጭሩ በምድሪቱ አራዊቶች ሳይቀሩ መጠለያ ያጡበት ፍርድ የጎደለባት በዘርና በጎሳ ሰው የተሰለፈባት በአስረሽ ሚቸው የሰከረች ሃገር።
በጋምቤላና በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች የደን ምንጠራና የመሬት ዝርፊያ የጎዳው የአካባቢውን ኑዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የምድሩን ገጸ ባህሪና በዚያው የተከለሉትን እንስሳት ጭምር ነው። የሚያሳዝነው ነገር ግን የደን ምንጠራውን ጭርሰው የሚዘራው ነገር ግራ እንደገባው ገበሬ መሬቱን ባዶ በማሳደራቸው በዝናብና በነፋስ ለሙ መሬት መራቆቱ ነው። በጥቅሉ የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት የሚቀራመቱት የወያኔ አለቆችና ጭፍሮቻቸው ያለዛም በወያኔ በጎ ፍቃድ ከዚህም ከዛም የተሰባሰቡ የህንድ፤የአረብና ሌሎችም ባለሃብት ተብየዎች ናቸው። ግፍ የማይፈራው ወያኔ መግደል፤ ማሰር፤ ማፈንና መሰወር የተካነበት የፓለቲካ ዘይቤው በመሆኑ ለሰው ልጆች ስብዕናም ሆነ ለድር አራዊት የሚያዝን ልብ የለውም። የጠራ አእምሮ ላለው ይህ ተግዳሮት ሃገርንም አምራች ነኝ የሚለውንም የማይጠቅም፡ ተልካሻ ሃሳብ እንደሆነ ከጅምሩ መረዳት ይቻላል።
ያዘው ጥለፈው በለው ግደለው ቀማው ስንል ሌላው ዓለም ጥሎን ሄደ። ልክ እንደ ድንጋይ ዘመን ጎሳ፤ ዘር፤ ቋንቋና ረብ የሌለውን የሃይማኖት ሽፋን ተገን አርገን ለእልፈተ አለም ስንቆሳቆስ በዚያ ሳቢያ የነደደው እሳት አንድን በልቶ ሌላውን ሲተካው ህዝባችን የሰላምንና የዲሞክራሲን ጮራ ሳያይ ጀምበር እየገባች ወጥታ፤ ዘመናትን ቆጥረናል። የህዝባችን ሰቆቃ ማቆሚያው መቼ ይሆን? ሰው በዘሩ ሳይሆን በማንነቱ ራሱን አቀንቶ የሃገር ዜጋ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ እይታ የሚኖረው መቼ ይሆን? ያ ቀን ይናፍቀኛል። ይመጣ ይሆን? ጠብቆ ማየት ነው!
Negash says
Your web page is not opening properly
This started happening just in the last week or two. I tried different browsers, with the same result. Once you click on the link to read a story, it appears to be loading the page, but gets stuck. You may want to look into it.
Thanks
Editor says
Many thanks Negash for letting us know this. We are looking into the matter. We will inform you when done. Hope you will check it and get us some feedback then.
Kindest regards,
Editor