ጌታቸው ረዳ በድምጸ ወያኔ በርካታ ምሥጢር ይፋ አድርገዋል፤ ወደ ሚዲያ የወጣበት አንዱ ምክንያት “በስብሰባ ላይ መናገር ስላልቻልሁ” ነው በማለት ተናግሯል። ደብረጽዮንን ጨምሮ የተለያዩ የትህነግ አመራሮችም ሆኑ የወታደር አዛዦች የፕሪቶሪያውን ስምምነት “ባክህን አድነን ፈርም፤ አለበለዚያ ወደ ቆላ ተምቤን ልንሄድ ነው” እያሉ ይገፉት እንደነበር ገልጾዋል። እነ ደብረጽዮን ይህን ባደረጉ ማግስት “ከጀግና ወደ ባንዳ ወደ ይሁዳ” እንዳወረዱትም ጌታቸው በግልጽ አመልክቷል። የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ደብረጽዮን በየቦታው እየዞረ “በቅልጥማችን ወይም በጉልበታችን ፌዴራል መንግሥትን ወደ ጠረጴዛ አመጣነው” ሲል ተደምጧል።
በነጻ ሚዲያ ላይ ከስዩም ተሾመ ጋር ውይይት ያደረገው አርአያ ተስፋማርያም ሌላ የሰጠው መረጃ አለ፤ “በ3ኛው ዙር መከላከያ መቀሌ ሊገባ ሲል እየገሰገሰ ሳለ መከላከያ ሚር ለአንድ ከፍተኛ የጦር መኮንን ከትግራይ ጦር መሪዎች ተደወለ፤ ደዋዩ ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሣኤ ነው (ሰሜን ዕዝን መትቶ ወደ ሱዳን የሄደው ነው)፤ ሽሬ ላይ ብዙ ፎቅ አለው፤ ገርጂም ላይ ፎቅ አለው” ይላል አርአያ። ሲቀጥልም “ተወልደ እባካችሁ ወደ መቀሌ እንዳትገቡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ እንደራደራለን ብሎ የመከላከያውን ሰው ይለምናል፤ የመከላከያ አዛዡ “መሣሪያ ትፈታላችሁ? እጃችሁን ትሰጣላችሁ?” ሲሉት ተወልደ “አዎ” አለ፤ አዛዡ ተወልደን ሌላ ጠየቁት “እስካሁን የሞተውን ልትነግረኝ ትችላለህ?” በማለት።
ለተጠየቀው ሲመልስም “ተወልደም እኔ ጋር በኦርኔል የተመዘገበ አምስት መቶ ሺህ (500,000) ሞቷል፤ ከኦርኔል ውጪ ስድስት መቶ ሺህ (600,000) በድምሩ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ወጣት ሞቷል ብሎ ይመልሳል።”
በትህነግና በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር መካከል የተፈጠረውን ልዩነትና ልዩነት መካረሩን ተከትሎ ጌታቸው ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በትህነግ ከፍተኛ በጀት ተመድቦ ስሙ እንዲጠፋ ዘመቻ እየተካሄደበት መሆኑንን አመልክቷል።
ትህነግ ወደ ጦርነት እንዲገባ 84 ገጽ ሰነድ የጻፈው ዓለም ገብረዋህድ “ጌታቸው ተፈጭቶም ቢሆን መሪ መሆን የማይችል ነው” በማለት የተናገረ ሲሆን፤ መቀሌ ላይ ቤት ለቤት እየዞሩ “ጌታቸው ባንዳ ነው፤ ከሃዲ ነው፤ ትግራይን አፍርሷል፤ ይሁዳ ነው” ብለው ጽሑፍ በመጻፍ ትህነጎች ፕሮፓጋንዳ ሠርተውበታል።
ዳግም ጦርነትን አብዝቶ እየተቃወመ ያለው ጌታቸው የትግራይ ሕዝብና ካድሬው እንዲያውቀው የሰጠው ከሁለት ሰዓት የዘለቀ መግለጫ አሁን ላይ ያለው ልዩነት የሥልጣን ሽኩቻ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። አሁን የተከፋፈሉበት ዋና ምክንያት ለምን ጦርነት ገባን? ምን ውጤት አመጣ? ማነው ኃላፊነት የሚወስደው? የሚለው ጉዳይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያለው ሁኔታ ለግምገማ እንዲቀርብ ነው ጌታቸው የሚፈልገው ነው፤ ይህ ሁኔታ ግን ሰዎችን በኃላፊነት እንደሚያስጠይቅ ስለተረዱ እነ ደብረጽዮን መጀመሪያ ፓርቲያችንን እናድን በሚል ሽፋን ጌታቸውን “ባንዳና ከሃዲ” ነው ተብሎ ተፈረጀ።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ከሃያ አራት ሺህ በላይ ቁስለኛ ይዘው እንደነበር ያመለከተው ጌታቸው፣ የተደረገው የሰላም አማራጭ ስምምነት ትጥቅ መፍታት፣ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለመከላከያ መልቀቅ፣ ሁሉም የትግራይ ተፎካካሪ ኃይሎች ያሉበት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም፣ እንደነበር ጌታቸው ያስታውሳል። ይህ ንግግር አሁን ላይ የተቋቋመው የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር በውሉ መሠረት እንዳልሆነና የፈዴራሉ መንግሥት በሆደ ሰፊነት አውቆ ዝም ማለቱን ሲናገር ለነበረው ማረጋገጫ ሆኗል።
“የተደራደርከውን የተቀመጥከው ከጥቁሮች ጋር ነው” በሚል የትግራይን ህዝብ የታደገውን፣ አድነን በማለት ሲማጸኑ የነበሩትን ሁሉ ነፍስ ያተረፈውን ስምምነት የማራከስ ተግባራት ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ጌታቸው አስረድቷል።
የትህነግ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖው ሳለ አስተያየት እንዳይጥ የተከለከለበትን የትህነግ ግምገማ “ሃሳብ የነጠፈበት” ሲሉ የተቸው ጌታቸው የፕሪቶሪያው ስምምነት ባይፈረም ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። በወቅቱ አመራሮቹን አግኝቻለሁ። “ጦሩ ፈርሷል ብለውኛል። ተመልሰው ማገገም አይችሉም። ነገሮች አብቆቶላቸዋል” ሲል በወቅቱ የጻፉትን የውጭ ሚዲያዎች ያስታወሰው የጌታቸው ንግግር፣ ዛሬ “ባንዳ” የተባለት ይህን አደጋ ከቀለበሰ በኋላ መሆኑንን አመልክቷል።
በሌላ በኩል ደብረጽዮን የክልሉ አስተዳዳሪ መሆን በጣም ፈልጎ እንደነበር ምንጮቹ ዋቢ አድርጎ አርአያ ተናግሯል። በመጀመሪያው ላይ የማስተዳደሩ ሥልጣን እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን ይህ ግን ከፌዴራል መንግሥትም በኩል ተቀባይነት አላገኘም። በኋላ ግን ሥልጣኑ ለጌታቸው ከተሰጠና እርሱም እነ ፈትለወርቅ (ሞኖጆሪኖ) እና የመሳሰሉት የትህነግ መሪዎች ከሥልጣናቸው ካባረራቸው በኋላ በምክትልነት ነው የምሠራው እንጂ የመሪነት ሥልጣን አልፈልግም ሲል የነበረው ጻድቃን ገብረትንሣኤ የመሪነቱ ሥልጣን እንዲሰጠው የፌዴራል መንግሥቱን በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ተከልክሏል።
ደብረጽዮን ግን ጌታቸው በሥልጣን ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ቦታው እንዲሰጠው በብዙ ውትወታ የጠየቀ መሆኑን አርአያ ይናገራል። እንዲያውም 10 ጊዜ አማላጅ በመላክ የወተወተ ሲሆን አልሳካ ሲለው “እኔ ቢያንስ ዐቢይን እንደ ጌታቸው አልተሳደብኩም፤ ለምን ግን ሥልጣን ከለከሉኝ” ብሏል። አርአያ እንደሚለው “እነ ደብረጽዮን መንግሥትን የጠየቁት ነገር ቢኖር ጌታቸውን አውርዱልን፤ ህወሃትን እንተዋለን፤ ብልጽግና እንሆናለን፤ ብቻ ጌታቸውን አውርዱልን” ብለው መለመናቸውና ይህም በድምጽ ማስረጃ የተረጋገጠ እንደሆነ አርአያ ተናግሯል።
በሌላ በኩል ቢቢሲ “ትግራይ ተጀምሮ ወደ አማራና አፋር ክልል እየተስፋፋ የሄደው” ሲል የሚገልጸው፣ “ትህነግ በወረራ አፋርና አማራ ክልል ድረስ በመዝለቁ” በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ በመጠየቅ ከዚህ በታች አስቀምጠነዋል።
ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ለመቋጨት በተካሄደው የፕሪቶሪያ ድርድር የትግራይ ተወካይ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን “መንግሥትን የሚያፈርስ ስምምነት ፈርመሃል” ሲል ህወሓት እንደወቀሳቸው ተናገሩ።
የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የመቋጨት ስምምነት የክልሉን መንግሥት እንዲያፈርስ እንዳደረገው እና ይሄንንም ተግባራዊ አድርገዋል ተብለው በፓርቲያቸው መተቸታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በህወሓት እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር መካከል ቅራኔዎች እየታዩ ባሉበት ወቅት ነው አቶ ጌታቸው ሰኞ ሐምሌ 22/ 2016 ዓ.ም. ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለተለያዩ ጉዳዮች ተናገረዋል።
ህወሓት “የተደራጀ ስም የማጥፋት ሥራዎች” ሲያካሂድብኝ ቆይቷል ሲሉት አቶ ጌታቸው “በውስጣዊ አለመግባባቶች፣ በፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ምክንያት፣ አንዱ የጀመረውን እንቅስቀሴ ሌላው ስም ስለሚሰጠው” ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን መሥራት አልተቻለውም ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው ለሁለት ሰዓት ከሩብ ያህል ባደረጉት ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ በፕሪቶሪያው ስምምነት፣ በህወሓት ሕጋዊነት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፋፊ ልዩነቶች ተከስተው አለመግባባት መፈጠሩን ግልጽ አድርገዋል።
በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው እና ለመቶ ሺዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው ጦርነትን የቋጨውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ አፈሙዞች ጸጥ ብለዋል።
የጦርነቱን መቋጨት አስመልክቶ የትግራይ አመራሮች ወደ “ከተማ በመመለስ” ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ትግል እንድናካሂድ ዕድል ሰጥቶናል ብለዋል።
ህወሓትን በመወከል የፕሪቶሪያውን ስምምነት ከፈረሙት የትግራይ ክልል ልዑካን አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው፣ በአሁኑ ወቅት “መንግሥትን [የክልሉን] የሚያፈርስ ስምምነት ፈርመህ መጥተሃል” ተብለው በከፍተኛ የድርጅቱ አመራሮች እየተወቀስኩ ነው ብለዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ፣ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ ማስፈታት፣ መበተን እና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ማዋሃድ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግን ያካትታል።
በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት የክልሉ መዲናን እንዲቆጣጠር እና የትግራይ አመራሮች እራሳቸውን ‘የተመረጠ መንግሥት’ ብለው መጥራት እንዲያቆሙ እንዲሁም ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመሠረት የሚያደርግ ነበር።
አቶ ጌታቸው ረዳ በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በህወሓት መካከል የሻከረውን ግንኙነት ይፋ ባደረጉበት በዚህ ከድምጺ ወያነ ጋር ባደረጉት ቆይታቸው ስለቀረቡባቸው ወቀሳዎች ተናግረዋል።
“አሁን መንግሥት አፍርሰው ነው የመጡት እየተባልን ነው። ያኔ ጉዳዩ የመንግሥትነት አልነበረም፤ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ በፌደራል ሠራዊት ስር እንዲገባ እጃችሁን ስጡ ስንባል ነው የነበረው። በወቅቱ የህወሓት ሊቀመንበር [ደብረጽዮን ገብረሚካኤል] ‘ዛሬ ካልፈረማችሁ ወደ በረሃ መውጣታችን ነው’ ብሎኛል” የሚሉት አቶ ጌታቸው አሁን የሚወቅሷቸው አካላት ስምምነቱን እንዲፈርሙ እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
አክለውም “የፕሪቶሪያን ስምምነት በምንፈርምበት ሰዓት ምን ዓይነት ጭንቅ ውስጥ እንደነበርን አስታውሰዋለሁ።አሁን ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኋላ ያኔ ስምምነቱ ካልተፈረመ አደጋ ላይ እንወድቃለን ሲል የነበረው አካል ‘መንግሥት እንድታፈርሱ ሥልጣን አልሰጠናችሁም – ስህተት ነው’ ሲል ከጅምሩ አልተቀበለውም ነበር ማለት ነው” ብለዋል።
ይህም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የስምምነቱ አተገባበር የሚጠይቃቸውን ሥራዎች እንዳይሠራ እክል እንደሆነበት በማንሳትም ወቅሰዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት በትግራይ ክልል ምርጫ እስኪካሄድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት የሚያዝ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አድርገው እንደሾሟቸው ይታወሳል።
በወቅቱም በህወሓት አመራሮች መካከል የሥልጣን ፍትጊያ እንደነበርና ኃላፊነቱን ከመቀበላቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ “በእኔ ላይ ያነጣጠሩ” ያሏቸው የስም ማጥፋት ዘመቻዎች መካሄድ መጀመራቸውን እና እርሳቸው የሚመረጧቸው የካቢኔ አባላትን የማቋቋም ዕድል እንዳላገኙ ተናግረዋል።
“በአመራሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያውቁት ጽሑፍ ተዘጋጅቶ በአንድ ቀን ከጀግና ወደ ባንዳ ወረድኩኝ።በዚህ ጽሑፍ ቤት ለቤት ቅስቀሳ ተደርጎበታል” በማለት የህወሓትን ጽህፈት ቤት በሚመሩ ግለሰቦች እና በድርጅቱ ውስጥ በሚገኙ አመራሮች የተቀነባባረ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተካሄደባቸው በመግለጽ ከሰዋል።
“በመሆኑም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከጅምሩ አንስቶ ካቢኔ ከመምረጥ ጀምሮ እስከ ታች ወርዶ እንዲንቀሳቀስ እንዳያስችለው በችግር የተተበተበ ሆኗል” በማለት የአስተዳደሩ ዋነኛ ትኩረት መሆን የሚገባው ያሉት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች መልስ እንዲያገኙ ማድረግ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ባለፈው መስከረም ወር በሰጡት ተመሳሳይ መግለጫ አስተዳደራቸው በዞኖች እና በወረዳዎች መንቀሳቀስ አለመቻሉን እንዲሁም ተቀባይነት እንዳያገኝ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል።
በተጨማሪ አቶ ጌታቸው ህወሓት በቅርቡ ያካሂደዋል ተብሎ ስለሚጠበቀው የድርጅቱ ጉባኤን የሚመለከት አስተያየት ሰጥተዋል።
ድርጅቱ ጉባኤ መካሄድ አለበት እንዲሁም ‘መሟላት ያለባቸው’ ሕጋዊ አሠራሮች ሳይሟሉ መካሄድ የለበትም የሚል አቋም ባላቸው አባላቶቹ ተከፋፍሎ ይገኛል።
በዚህ ከፍተኛ ክፍፍል ውስጥ ባለበት ወቅት ህወሓት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከማግኘቱ በፊት ሊያካሂደው እንደማይገባ የተገለጸውን ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆኑን ተገልጿል።
የጉባኤው አላማ በድርጅቱ ውስጥ ‘በተሰባሰቡ ከፍተኛ አመራሮች ተጠልፏል’ ያለው የህወሓት ቁጥጥር ኮሚሽን አባላቶቹ ከአዘጋጅ ኮሚቴ ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረጉ ይታወሳል።
ድርጅቱ እስከአሁን ባካሄዳቸው ረጃጅም ስብሰባዎች “ወሳኝ የሕዝብ አጀንዳ ሲያነሳ አይተን አናውቅም። የሥልጣን ሽኩቻ ነው ያለው። ማን ስለምን ወደ ሥልጣን መጣ? በምን አጋጣሚስ መውረድ አለበት” በሚል ችግር ውስጥ ወድቋል ሲሉ አቶ ጌታቸው በቃለ መጠይቃቸው ላይ ጠቅሰዋል።
አሁን ያለው የድርጅቱ መሠረታዊ ችግር ሥልጣን እንደሆነ በመግለጽ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ሁሉም የነበረውን ለማስቀጠል፣ በሥልጣን ላይ እያሉ በተፈጸሙ ስህተቶች ከተጠያቂነት ለማምለጥ እየተሯሯጡ ነው” በማለት ‘ያጡትን ሥልጣን ለማስመለስ፣ ሥልጣን ቀምቶኛል የሚለውን ደግሞ ለማስወገድ’ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ጉባኤው በአመራሩ ውስጥ ያሉ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚታረሙበት መሆን አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ድርጅቱ “ጊዜው የሚጠይቀውን ሃሳብ ማመንጨት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
“ሃሳብ በሌለበት የሚደረገው ጉባኤ ላይ የሚመረጠው ኃይል ምን ላይ ተመሥርቶ ነው ትግራይን የሚያስተዳድረው? የተቀሩት የፕሪቶሪያ ጉዳዮች በምንድን ነው የሚያስፈጽማቸው?” በማለትም ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቱ ይጠይቃሉ።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባኤ ከማካሄዱ በፊት “በሕጋዊ መንገድ መመዝገብ እንዳለበት” ማሳሰባቸው ይታወሳል።
አክለውም የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መንግሥታቸው ያከናወናቸውን ሥራዎች ለተቃዋሚዎቻቸው በመጥቀስ “ሕግ ያሻሻልነው ህወሓት እና መሰል ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ሕጋዊ ፓርቲ እንዲሆኑ [ነው]” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት የሕግ ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ነበረ።
የምርጫ ሕጉን ያሻሻለው ይህ የአዋጅ ማሻሻያ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።
ማሻሻያው የፖለቲካ ቡድኑ “ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።
ከማሻሻያ አዋጁ መጽደቅ በኋላ ንግግሮች መደረጋቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ምርጫ ቦርድ ሥራውን ሠርቶ፣ የሚያጣራውን አጣርቶ በተሟላ መንገድ እንዲፈቅድላቸው። ዐቃቤ ሕግ ለምርጫ ቦርድ [ደብዳቤ] መጻፍ ነበረበት ጽፈናል” ብለዋል።
ዐቢይ ይህን ቢሉም ግን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ፤ “ይህ የአዋጅ ማሻሻያ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን እንደ አዲስ ለመመዝገብ የሚያስችል” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አማኑኤል አክለውም፤ “ወደ ምርጫ ቦርድ አመልክተን በዚያ አዋጅ መሠረት እንድንስተናገድ ነው የሚፈልጉት። እኛ ወደ ምርጫ ቦርድ ቴክኒካል ወደ ሆነው ጉዳይ እንደ አዲስ ለመመዝገብ ማመልከት ሳይሆን ፖለቲካሊ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለማስመለስ የሚያስችል ፖለቲካዊ ውሳኔ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው” ሲሉ የፓርቲያቸው ውሳኔ አስረድተዋል።
የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቅርቡ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በአዋጁ መሠረት ለመመዝገብ ወደ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ማስገባታቸውን በመግለጽ በ15 ቀናት ውስጥ መልስ እንጠብቃለን ብለዋል።
ሆኖም በጠቀሱት ጊዜ ውስጥ ፍቃድ ካልተሰጣቸው ‘ፍቃድ አልሰጣችሁንም’ የሚል መልስ ይዘው ጉባኤውን እንደሚያካሂዱ ተናግረዋል።
ደብረጽዮን ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው መረጃ በግልጽ እንደሚያሳየው በአዲሱ አዋጅ መሠረት ለመመዝገብ ጥያቄ ማቅረቡንና “ህወሐት እንደ አዲስ ለመመዝገብ የተስማማ” መሆኑን የሚገልጽ ነው። በሌላ አነጋገር ህወሐት በአዲስ መልክ ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሲሰጠው በኢትዮጵያ ውስጥ በዕድሜ በጣም ትንሹና ጨቅላ ፓርቲ ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ዶ/ር፣ እንጅኒየር ገለ መሌ የሚል የስም ልጣፍ ይዘው ከሃገራችን ገበሬ ያነሰ አስተሳሰብ ያላቸው እልፎች ናቸው። እነዚህ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ሁልጊዜ በህዝብ ስም እየነገድና እያስነገድ የብዙሃንን ደም እንዳፈሰሱና እንዳስፈሰሱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። የሃበሻ ፓለቲካ ብላና አብላኝ ነው። ለዚህ ነው ሃገሪቱ ከከፋ ማጥ ወደ ጥልቅ አረንቋ ሁልጊዜ የምትወድቀው። የትግራይ ህዝብን ነጻ አወጣለሁ በማለት ጠበንጃ አንግቦ በሻቢያ ሰልጥኖ ከሻቢያ ጎን ተዋግቶ ለስልጣን የበቃው ወያኔ ሳያስበው በብልጽግና ስልጣኑን ከተነጠቀ ወዲህ ለተንኮል ተኝቶ አያውቅም። አሁን መቀሌ ላይ ተወሽቆ አንዴ የ 50 ቀን ሌላ ጊዜ የሳምንታት ስብሰባ የሚያደርገው ወያኔ ባርነት ትግራይ ውስጡ ሰላም የሌለው፤ እጅ በደም የተነከረ፤ ዛሬ ድረስ በድብቅ እስር ቤቶች እልፎችን የሚያሰቃይ የሰው ሰቆቃን የማይረዳ የማፊያ ቡድን ነው። ይህ ድርጅት በሌላ ሰላምን በተላበሰ ሃይል ካልተተካ ምንም አይነት ስብሰባ ያድርጉ ከብልጽግናም ሆነ ከራሳቸው ጋር ፍጽም ሰላም አይኖራቸውም።
የትግራይን ድሃ አደጎች በጦርነት ያስፈጀው ወያኔ ፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚገባው ሃገር አፍራሽና ሃገር ሺያጭ ስብስብ ነው። ይህ አባባል የማይዋጥለት ካለ ታሪካቸውን ከበረሃ እስከ ከተማ ፈልፍሎ መረዳት ነው። በትግራይ ቴሌቪዥን የሚነገረው የውሽት ጋጋታ ለራሱ ለትግራይ ህዝብ የማይዋጥለት እንደሆነ የየቀኑ ቀልዶች ያመላክታሉ። ጌታቸው ረዳ በቅርብ ጊዜ በሰጠው ቃለ መጠየቅ “በአንድ ጊዜ ከጀግና ታጋይ ወደ ባንዳ አወረድኝ” ብሏል። ይህ ጉዳይ የገባው ዛሬ ነው እንዴ? እነ ዶ/ር አታክልቲ ቀጸላና ሌሎች ሲገደሉ ጌታቸው የት ነበር? በወያኔ የፓለቲካ ስልት አብረን በሰላም እንኑር የክልል ነገር ዋጋ ይብሉ የሚሉ ሃሳቦች ሁሉ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች ሃሳብ በማድረግ የፓለቲካ ንግድ ሲፈጽምበት ኑሯል። አሁንም የትግራይን ህዝብ በድንበር ሂሳብ እያሳበበ ለራሱ የመሰንበቻ የፓለቲካ ትብታብ ሲያሰላ እንደሚውል የትግራይ ህዝብ መሪ ነን የሚሉት የሚሰጡትን አማቺ መግለጫዎች ማዳመጥ ይበጃል። ጌታቸውን ወያኔ እንደ አሮጌ ጣሳ ረግጦ ለማለፍ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ገና ብዙ መፋለምን በወያኔዎች መሃል እንመለከታለን።
ከላይ በተጻፈው ወያኔ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የፈረሙትን አሁንም በዚሁ ሰነድ መሰረት ነገሮች ይተግበሩ የሚሉትን ሁሉ አሁን ላይ ለመቀልበስና የከፋ ስም ለመስጠት መሞከሩ በባህሪው ያለ እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም። ወያኔ ለመኖር የሰው ደም መፍሰስ አለበት። እንዳልሰከነ ቃልቻ ሁልጊዜ ከበሮና ክራር እያስመቱ ሰውን ወደ እሳት የሚማግድ እነዚህ የቁም ሙቶች አሁንም እርስ በእርስ እንድንጨራረስ ይሻሉ። ግን የትግራይ ህዝብ ሞትና ደም ሰልችቶታል። ዋ አንድ ቀን ሆ ብሎ ከተነሣ የወያኔ አለቆችና አለቅላቂዎች ከዚያ ጥቃት የሚያድናቸው ምድራዊ ሃይል አይኖርም። በዚህ ይባል በዚያ ወያኔ በትግራይም ውስጥ ሆነ ከትግራይ ውጭ በሰላም መኖር አይችልም። የብልጽግናው መንግስትም ልክ በተደጋጋሚ በወያኔ ጭልፊቶች የሾኬ ጠለፋ እንደወደቀው ሁሉ ወያኔ አሜሪካን ከጀርባ አድርጎ ብልጽግና አይኑን አፍጦ ወያኔ እንደሚያታልለው ብዙ አመላካች ነገሮች ነበሩም አሉም። ወያኔ ሺህ ጊዜ ለስብሰባ ቢቀመጥ፤ እልፍ መግለጫ ቢያወጣ፤ ለትግራይ ህዝብ ወዘተ እያለ ቢለፍ ከቃል ያለፈ ለትግራይ ህዝብ የሚያደርገው ያደረገውም ነገር የለም። የብሄርተኞች በሽታ ይህ ነው። ለራስ ብቻ መኖር። በህዝብና በሃገር ስም መነገድ። ደብረጽዪን የክፋቱ ሁሉ ቁንጮ እንጂ ለሰላም የቆመ ግለሰብ አይደለም። ዘመድ አዝማድን ሚስትና ልጅን ከሃገር አስወጥቶ አሁንም በትግራይ የገበሬና የድሃ ልጆች ደም ለመንገድ ስለ ስልጣን ያወራል። አይበቃም። ጉልበታችሁ ደክሞ፤ ጥርሳቹሁ ወልቆ፤ ጸጉራቹሁ ተመልጦም ዛሬም ለእኔ ብቻ ማለትና ሰውን ማሰቃየት አይቆምም? ወያኔ የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው። በአስቸኳይ በሌላ አዲስ እይታ ባለው ሃይል ይተካ! ያ ካልሆነ የሃገሪቱ ችግርና የትግራይ ህዝብ መከራ ከአሁኑ እንደሚከፋ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። ስልጣን በቃን በሉ!