
አዲስ አበባ ላይ ታላቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ በብዙዎች ተስፋ የተጣለበት ባልደራስ ባለፈው በተካሄደው ምርጫ የአዲስ አበባ ሕዝብ ድምጽ ነፍጎት አንድም ወንበር በአዲስ አበባ ምክር ቤትም ይሁን በተወካዮች ምክርቤት ሳያገኝ መቅረቱ ደጋፊዎቹን ተስፋ ያስቆረጠና አንገት ያስደፋ ክስተት ነበር።
ከሁሉ በላይ በአድናቂዎቹ “ታላቁ እስክንድር“ እየተባለ የሚጠራውና በትንሹ ለ10 ጊዜ ያህል በዘመነ ትህነግ እየተከሰሰ እስርቤት ሲንገላታ የኖረው እስክንድር ነጋ እስርቤት እያለ ምርጫውን እንዲወዳደር ቢደረግም በብልፅግና ተወዳዳሪ ተሸንፎ ሳይመረጥ መቅረቱ ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ ሆኖ አልፏል።
በኢትዮጵያ ሕግ በፓርቲነት ተመዝግቦ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ የሚለው ባልደራስ ከፓርቲ ፖለቲካ ወጣ ባለ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ የጠላትን ሃሳብ የሚደግፍና የሚያበረታታ፣ የወገንን ሞራል፣ ቅስም የሚሰብርና የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ዜና ትላንት ለጥፎ ነበር። የተለጠፈው ዜና ይህንን ይመስላል፤
በዚህ ልጥፍ ያዘኑና ለሕዝብና አገር ኅልውና ቀን ተሌት የሚለፉ ወገኖች ባልደራስን ተው፣ ከመንግሥት ጋር ቁርሾ ቢኖርህም እንዲህ የወረደ ተግባር አታድርግ ብለው ገስጸውታል።
ሌሎች ጎልጉል በግል ያነጋገራቸው ደጋፊዎቹ ደግሞ በድርጊቱ ማፈራቸውን የገለፁ ሲሆን ባልደራስ ከተነሳበት ዓላማ ወጥቶ የበረከት ስምዖንን ልጅ ኤርሚያስ ለገሠን ምክትል ኃላፊ አድርጎ የሾመ ጊዜ ራሳቸውን ከድርጅቱ ማግለላቸውን ጠቅሰው ባልደራስ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በመጣል ሊጠየቅ፣ ከተቻለም ሊከሰስ ይገባዋል ብለዋል::
ሲቀጥሉም ይህንን የመሰለ ተግባር የሚፈጽሙት፣ ከነእስክንድር ጋር ሆነው የሚሠሩትና ለግብፅ ሎሌ የሆኑት እነ ኤርሚያስ ናቸው፤ እስክንድርን በዚህ የክህደት ሥራ ውስጥ ማየታችን አንገታችንን አስደፍቶናል ብለዋል።
የባልደራስን ልጥፍ በተመለከተ ጌታቸው ሸፈራው ይህንን ብሏል፤
ባልደራሶች! በቀላሉ አትገመቱ! ዜናውን ለሚዲያ ተውት!
ባልደራስ መአት ነገር በፌስቡክ ገፁ ይለጥፋል። በአዲስ አበባ ጉዳይ ብዙ ነገር ይሰራል የተባለው ፓርቲ የሚያስገምቱትን የተራ አክቲቪስት መልዕክቶች ሲያጋራ ይውላል። ባልደራሶች ይህን ብታስተካክሉ ጥሩ ነው።
ለምሳሌ ከስር ያለውን ዜና መመልከት ይቻላል። የዜናው ምንጭ ከሱዳን ነው። የሱዳን መገናኛ ብዙሃን አገራቸው ውስጥ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት እያደረጉ ነው። ለዚህም በቅርቡ ከባድ መሳርያዎችን እየተኮሰ ያለው የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያን ሰራዊት ቦታ እንዳስለቀቀ አድርገው የሚዘግቡት ነው። እነሱ የሉአላዊነት ጉዳይ አንስተው አቅጣጫ ማስቀየር ፈልገዋል። ሮይተርስም ከእነሱ ነው የወሰደው።
ባልደራስ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው። ለመታየት ሲል ሲያገኛቸው የከረመውን ፋኖዎች ሱዳን ድንበር ነው ያሉት። ለእነሱ ደውሎ ማረጋገጥ ይችል ነበር። ለእነሱም ባይደውል ከሱዳን ጎንደር ያለ መአት ምንጭ ይቀርበው ነበር። ማረጋገጥ ይችል ነበር።
ብስለት ቢታከልበት ደግሞ መሰል ዜና ትርጉም የለውም። የሱዳኖች ቅኝት ነው። ይህን ተርጉሞ መዘገብ ብስለት ማጣት ነው። ስራቸውም አይደለም።
ባልደራስ የሆነ ያልሆነውን እያጋራ በደጋፊዎቹም ጭምር ከሚገመት ሌላ ስራ ቢሰራ ይሻለዋል። ለምሳሌ በዚህ ዜና ጉዳይ መንግስትን ምን እየሆነ ነው ብሎ ቢጠይቅ፣ የአገር ሉአላዊነት የሚያስከብር መንግስት አይደለም ብሎ ቢተች ወዘተ የተገባ ነው። እንዲህ ያለ ዜና ግን ባልደራስን መዘባበቻ ያደርገዋል።
የግድ ዜና ካልሰራን ካላችሁ ደግሞ የወገን ዜና እንዲህ አይሰራም። ሱዳን ተጨማሪ የኢትዮጵያን መሬት ከያዘች ወረራ ነው የሚሆነው። ወረራ ነው የሚባለው።
ባልደራስ የሚባለውን ፓርቲ በአዲስአበባ ጉዳይ ብዙ ነገር ይሰራል የሚል ግምት ነበረኝ ይላል በቴሌግራም ገጹ ላይ ምልከታውን የጻፈው ታደለ ጥበቡ። ተራ አክቲቪስት እንኳን ይጽፈዋል ተብሎ የማይመገት እንደዚህ ያለ የውሸት መረጃ ማሰራጨቱ ምናልባትም ድርጅቱ ራሱን ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ጊዜ ይመስለኛል። ፓርቲው ላይ የሚና መደበላለቅ እያየሁ ነው። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልደራስ እንደ ፓርቲ ሳይሆን “ባልደራስ ብዙሃን መገናኛ” እየመሰለኝ ነው። ዛሬ ደግሞ የዘገበውን መረጃ ለማረጋገጥ እዛው ድንበር አካባቢ ያሉ ፋኖዎችን ጠይቄ አንዱ “እዛው እኮ ነኝ” ብሎ በቁጣ ነበር የመለሰልኝ።
ባልደራስ የዜና ምንጭ አድርጎ የወሰደው ሮይተርስን ነው። የሮይተርስ የዜና ምንጭ ደግሞ ከሱዳን ነው። ከትናንት ጀምሮ በሱዳን የተነሳውን ተቃውሞ ለማርገብ ከሱዳን በኩል የሱዳን ሠራዊት፣ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ማስለቀቅ እንደቻለ ዘገባዎች ሊወጡ ይችላሉ። ደግሞም የሚጠበቅ ነው።ተደጋጋሚ የውሸት ዜናዎችም ተሰራጭተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ባልደራስ ድንበር አካባቢ ያሉ ፋኖዎችን እንኳን ጠይቆ እውነቱን ማረጋገጥ ሲገባው ከጠላት በኩል የወጣን መረጃ ተርጉሞ ማሰራጨቱ ከማስገረምም በላይ ሀላፊነት የጎደለው ዘገባ ነው።በነገራችን ላይ ሥራውም አይደለም። ምናልባት የተባለው መረጃ ትክክለኛ ቢሆን እንኳን ባልደራስ እንደ ፓርቲ መጠየቅ ያለበት የአገሪቱ ሉዓላዊነት የማስከበር ግዴታ ያለበት መንግሥት እርምጃ ባለመወሰዱ መጠየቅና መተቸት ነበር።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply