
- የእስክንድር አፋሕድ ጥሪ አቀረበ
ለበርካታ ወራት ኅብረት ለመፍጠር ታስቦ ሲሠራበት የቆየው የአማራ ፋኖ ኅብረት በቋራ ጎንደር መመሥረቱ ተሰምቷል። የኅብረቱ ዓላማና ግብ ወደ አንድነትን ለማምጣትና የተቀናጀ ጥቃት ለመሰንዘር ሳይሆን ዓቅምን አስተባብሮ ለድርድር ለመቅረብ የታለመ እንደሆነ እየተነገረ ነው። እስክንድር ነጋ የሚመራው አፋሕድ ባወጣው መግለጫ “ከተቻለ እንዋሃድ፣ ካልሆነም አንቀናጅ ካልሆነ ቢያንስ እናበብ” ብሏል።
ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከወሎና ከጎጃም የተሰባሰቡ የፋኖ አመራሮች ባደረጉት ውይይት አንድ የፋኖ አደረጃጀት መመሥረታቸውን ተናግረዋል። ስሙንም አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በማለት መሰየማቸውን አስታውቀዋል።
የወጣው መግለጫ እንደሚለው “የአማራ ፋኖ በጎጃም፣ የአማራ ፋኖ በወሎ (ቤተ – አማራ)፣ የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር እና የአማራ ፋኖ በሸዋ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ ቋራ-ጎንደር ባደረጉት ቀናትን የወሰደ መስራች ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 01 ቀን 2017 ዓ.ም የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (Amhara Fano National Force) የተሰኘ ድርጅት” መመሥረታቸውን ይፋ አድርጓል።
አወቃቀሩን በተመለከተም፤ “የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል አወቃቀር ጠቅላላ ጉባኤ፣ ማዕከላዊ ምክር ቤት፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንዲሁም የአባት አርበኞች ምክር ቤትን አካቶ ሕገ ደንብ በማፅደቅ ተቋቁሟል። የአባት አርበኞች ምክር ቤትን አርበኛ መሳፍንት ተስፉ እንዲመሩት መሥራች ድርጅቶቹ” መስማማታቸውን መግለጫው አስረድቷል።
አዲሱ የፋኖ ኅብረት ትህነግ ይመራበት የነበረውን ዓይነት የጋራ አመራር መርህ የሚከተል መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው መግለጫ ለተግባራዊነቱም 13 መሪዎች ያሉበት የድርጅቱን “ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የዲፕሎማሲ እና የአስተዳደር ሥራዎች” የሚመራ “ማዕከላዊ ኮማንድ” መመሥረቱን አስታውቋል።
ይህ በ13 መሪዎች የሚመራው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ፤
“1ኛ. አርበኛ ዘመነ ካሴ
2ኛ. አርበኛ ሐብቴ ወልዴ
3ኛ. አርበኛ ምሬ ወዳጆ
4ኛ. አርበኛ ደሳለኝ ሲያስብሸዋ
5ኛ. አርበኛ አስረስ ማረ ዳምጤ
6ኛ. አርበኛ ሔኖክ አዲሴ
7ኛ. ጀነራል ተፈራ ማሞ
8ኛ. አርበኛ ዝናቡ ልንገረው
9ኛ. አርበኛ ድርሳን ብርሃኔ
10ኛ. አርበኛ አስቻለው በለጠ
11ኛ. አርበኛ ሳሙኤል ባለዕድል
12ኛ. አርበኛ ማርከው መንግሥቴ
13ኛ. አርበኛ አከበር ስመኘው”
ከሥነአስተዳደር መርህ እና በተለይ ጥቅብ የዕዝ ሠንሠለትን መከተል ከሚያስገድደው ወታደራዊ አወቃቀር አኳያ በ13 መሪዎች የሚመራ ድርጅት ተቋማዊ ቁመና ይዞ ለመቀጠል እጅግ እንደሚከብደው አስተያየት ሲሰጥ ተሰምቷል።
ከዚህ ሌላ ግን የፋኖው ኅብረት የተመሠረተው በመንግሥት ላይ ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር ሳይሆን ዋንኛው ዓላማ ድርድር በሚካሄድበት ጊዜ ወንበር ለማግኘት እንደሆነ የፋኖን አካሄድ በቅርብ የሚከታተሉ ለጎልጉል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተለይ እስክንድር የሚመራውና አፋሕድ ተብሎ የሚጠራው አደረጃጀት ኅብረት በመፍጠር የቀዳሚነቱን ሥፍራ በመያዙ ለድርድር ጥሩ ወንበር እያመቻቸ እንደሆነ ሲነገር የቆየ ሁኔታ ነው። በቅርብ በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ድምፅ እስክንድር ወደ ኤርትራ አንድ የድርጅቱን ከፍተኛ ኃላፊ መላኩን እና ከሻዕቢያ ጋር በመነጋገር አስመራ ላይ ቢሮ እንዲከፈትለት ሲጠይቅ ተሰምቷል።
በዚህ የድምፅ መረጃ መሠረት እስክንድር ቢሮ እንዲከፈትለት፣ ኮማንዶ እንዲሰለጥልለት እና ከባድ መሣሪያ ተኳሽ የጠየቀ ሲሆን በምትኩ አሰብን እንደማይጠይቅ እንዲያውም የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት እንደሆነ ተናግሯል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን አሁን ካለው የተበታተነ የፋኖ አደረጃጀት እርሱ የሚመራው የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኝ፣ ለማንኛውም ጉዳይ የተሰባሰበ መሆኑን በመግለጽ የተናገረው እነ ዘመነ የሚመሩት የተበታተነውን ፋኖ በእጅጉ ያሳሰበና ያስቆጣ ሆኗል።
ከጥቂት ወራት በፊት “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” በማለት ከእስክንድር ጋር አብሮ የሚሠራው አበበ ጢሞ ማስታወቁን ጎልጉል ዘግቦ ነበር።
የእስክንድር የመቅደም አካሄድ የገባቸው የእነ ዘመነ ቡድን ቢሮ በመክፈትም ሆነ ለድርድር ራሳቸውን በማዘጋጀት ወደኋላ መቅረታቸው በመገንዘብ በአፋጣኝ ኅብረት በመፍጠር ለድርድር ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ስምምነት ላይ በመድረሳቸው አሁን የመሠረቱትን በ13 ሰዎች የሚመራ የፋኖ አደረጃጀት ለመመሥረት በቅተዋል። በዚህ ሁኔታ በቀጣይ ከመንግሥት ጋር በሚደረጉ ድርድሮች ከተቻለ ከእስክንድር ፋኖ ጋር ካልሆነም ራሱን ወክሎ አዲሱ የፋኖ አደረጃጀት ለመቅረብ እየተንደረደ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርብ ከሚከታተሉ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በአማራ ክልል የተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በውጊያ ላይ ከሚገኙት የፋኖ አደረጃጀቶች አንዱ ጋር የተነጋገረ መሆኑ ገልጾ ነበር። ይህም የእስክንድር ፋኖ እንደሆነ በሰፊው የሚታመንበት ሲሆን በዚህም ረገድ እስክንድር ቀዳሚ ሆኖ መገኘቱ የእነ ዘመነን ቡድን የመቀደም መንፈስ ውስጥ እንዳስገባቸው ጫካ ከገቡትም ጭምር ሲነገር ተሰምቷል።
“ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው” በሚል ርዕስ ባጋራነው የዜና ዘገባ ከጦርነት በስተቀር ሁሉንም አማራጭ የተጠቀመው ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ላይ ያቀደው ባለመሳካቱ መጨረሻው እና አይቀሬው አማራጭ ዲፕሎማሲና ድርድር እንደሆነ በግምገማው ያመነበት ጉዳይ ነው። የእነ ዘመነ ካሤን ቡድን በሁሉም መስክ የሚያግዘው ሻዕቢያ ዕገዛውን አጠናክሮ መቀጠል ባለመቻሉ ድርድርን ጊዜ መግዣ ወይም እጅ መስጫ አድርጎ አቅርቧል።
መሪ ዓልባው የእነ ዘመነም ቡድን ገና አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው ተጠናክሮ ከመሥራት ይልቅ የመፍረስ ወይም የመበታተን አደጋ ውስጥ እንዳለ አፈትልከው የሚወጡ የድምፅ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይ ዘመነ የአዲሱ ፋኖ አደረጃጀት መሪ ሆኖ ባለመውጣቱ “በጎንደሬ አንመራም” የሚሉ ድምፆች የተሰሙ ሲሆን ካስፈለገም “ባሕር ዳርን ይዘን እንገነጠላለን” እንጂ ጎጃም ካልመራ በፍጹም በስብስቡ አንቀጥልም ያሉም አሉ።
ባለፈው ወር በአማራ ክልል ከሚገኙ 263 ወረዳዎች በሙሉ የተመረጡ ከ4,500 በላይ ከ10 የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ልየታ ላይ በመሳተፍ የክልሉን ሕዝብ አንኳር አጀንዳዎች ማቅረባቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት የምክክር ኮሚሺኑ ኃላፊዎች እንደተናገሩት ከፋኖ ታጣቂዎች አንዱ ስብስብ ጋር መነጋገራቸውና የትኛው እንደሆነ ለመግለጽ እንደማይችሉ በመናገር በጠቃሚ ጉዳዮች መምከራቸውን አስታውቀዋል። በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነው ይህ የእስክንድር አፋሕድ እንደሆነ የታመነ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አፋሕድ አዲስ የተመሠረተውን የፋኖ አደረጃጀት ዜና በደስታ የተቀበለው መሆኑ ገልጾዋል። “ለአንድ ዓመት ጥቂት በቀረው የድርጅታችን ዕድሜ የነበረውን ሂደት ስንገመግም፣ ብዙ ውጣ ዉረድ እንደነበረው የምናስታውሰው ነው። ይህም ያስተማረን አንድ ነገር ቢኖር፣ የሁለት ድርጅቶች መመሥረት ስኬት የሚሆነው፣ ሁለቱ ድርጅቶች ከተቻለ በተዋሃደ፣ ካልሆነም በተቀናጀ፣ ይህም ካልሆነ ቢያንስ ቢያንስ በተናበበ አካሄድ ትግሉን ሲመሩት ብቻ መሆኑን ነው” በማለት በተለይ እኛ ከተመሠረትን “አንድ ዓመት” ሊሞላን ነው የሚለውን በመጥቀስ አሁን ከተመሠረተው የፋኖ ኅብረት አፋሕድ ቀዳሚነት እንዳለው ጠቅሷል።
ከዚህና ከሌሎች ጉዳዮች አንጻር ሲታይ፤ አዲስ የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ወደ ድርድር በሚደረገው ጉዞ የበይ ተመልካች ከመሆን ለመዳንና በድርድር ጠረጴዛው ላይ አንዲትም ብትሆን ወንበር ለማግኘት አስቦ የተመሠረተ ነው ለማለት ይቻላል። ጎልጉል ያነጋገራቸው በትግሉ ውስጥ ያሉትም ሆነ ከትግሉ ውጪ ያሉ የፋኖን አካሄድ የሚከታተሉ የሚናገሩት ይህንኑ የሚያጸና ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply