
ሰሞኑን በሸዋ አካባቢ በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ቡድን መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታወቀ። በእስክንድር ነጋ የሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ባለበት እንደሚቀጥል፣ ሌሎች አደረጃጀቶች ለመቀላቀል ከፈለጉ በራሳቸው ተደራጅተው ወደ አሕፋድ እንዲመጡ ተጠየቀ።
ከጥቂት ቀናት በፊት በሸዋ ፋኖ አደረጃጀቶች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት መከሰቱን እና ተዋጊዎችም መሞታቸውን በፋኖ ውስጥ ያሉት አዋጊዎች ገልጸዋል።
ጉዳዩ የተከሰተው በደብረሲና አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን የራምቦ ክፍለጦርን ወደ ሬማ እንዲሄድ በተደረገው ውሳኔ ነው። ውሳኔው የተላለፈው በወታደራዊ አመራሮች ሳይሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ የተፈጸመ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ።
ሬማ በሚባለው አካባቢ እንደሚንቀሳቀስ የሚታወቀው በአጼ ፋሲል ክፍለጦር ሥር የሚገኘው የቀስተ ንብ ብርጌድ ነው። ብርጌዱ የራምቦ ክፍለጦር ወደ ሬማ እንደተላከ ሲሰማ “አንድ ሆናችሁ በወታደራዊ ውሳኔ ተዋጊውን ብትመሩ ይሻላል፤ እናንተ በመጀመሪያ አንድ ሁኑ” በሚል ውሳኔውን ውድቅ ያደርገዋል።
የራምቦ ብርጌድ ግን በተሰጠው ፖለቲካዊ ትዕዛዝ መሠረት ወደ ቀስተ ንብ ብርጌድ አካባቢ በመግባት የተኩስ ልውውጥ ካደረገ በኋላ የቀስተ ንብ ብርጌድ አባላትን አፍኖ ወሰደ፤ የተወሰነውን አካባቢ ተቆጣጠረ። ቀስተ ንብ በደረሰበት ጉዳት ሲያፈገፍግ በመካከል የአካባቢው ሕዝብ የራምቦ ክፍለጦር በቀስተ ንብ ላይ ባደረሰው ጉዳት እጅግ ተማርረው ራምቦዎችን ከአካባቢያቸው እንዲወጡ ግፊት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል።
በዚህ ክፍፍል ምክንያት በሁለቱም የፋኖ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ከተለያዩ የፋኖ መረጃ አቀባዮች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በእስክንድር ሥር የሚመራው የአማራ ፋኖ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ቃል አቀባይ የሆነው አበበ ፋንታው ጢሞ በሰጠው መግለጫ መሠረት “አንድ ተቋም ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ቢመጡ ከዚያ አንድ ላይ ለመሆን እንሞክራለን ብሏል”።
ይህ የአበበ ጢሞ ንግግር የእስክንድር ፋኖ አደረጃጀት የሸዋ የበላይ እንደሆነና ሌሎች በዚህ አደረጃጃት ውስጥ ያልገቡ ቢገቡ የሚሻል ሲሆን ካልፈለጉ ግን በራሳቸው አንድ ኅብረት ፈጥረው ወደ እስክንድር የፋኖ ኅብረት መቀላቀል ይችላሉ የሚል እንደሆነ የፋኖን ጉዳይ የሚከታተሉ ይናገራሉ።
ይህ ዓይነቱ የተቸከለ አካሄድ በፋኖ ውስጥ ሊፈጠር የሚገባውን ኅብረት ተስፋ እንዳኖረው የሚያደርግ ሲሆን በሌላ በኩል እስክንድር ዓቅም እያገኘና ምናልባትም ወደ ድርድር በፍጥነት እየተጓዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ነው ተብሏል።
በተለይ በሰሞኑ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በባሕር ዳር የአጀንዳ ማሰባሰብ ባደረገበት ወቅት ለታጠቁ ኃይሎች በፈለጉት መንገድ ለውይይት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ እስክንድር ወደ ድርድር እያቀና ሊሆን ይችላል በቃል አቀባዩ በኩል “ሁላችሁም ወደ እኔ ኑ” የሚለውን ጥሪ ያስተላለፈው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ የመከላከያ ሠራዊት መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም በቴሌግራም ገጹ ባወጣው ዜና በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ የአየር ወለድ ክፍለጦር ሻለቃ ሁለት ሻምበሎች በወሰዱት ድንገተኛ አሰሳ እና ፍተሻ በርካታ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ እና ተተኳሻ መያዛቸውን የሻለቃው አዛዥ ሻለቃ የሽዋስ እንዳለ ጠቅሶ ዘግቧል።
“በአረንጎዳ፣ ቡዩ እና ፊጥራ ዙሪያ በሶስቱ ቀበሌዎች ከሰላም ወዳድ ኅብረተሰብ በደረሰው መረጃ መሠረት የጠላት ኃይል ሠራዊቱ ወደ ግዳጅ ሲሰማራ መሳሪያውን ደብቆ ኅብረተሰቡ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን እና ሠራዊቱ ሲንቀሳቀስ መሳሪያውን ከደበቀበት በማውጣት ሕዝቡን በማስጨነቅ መዋጮ የሚሰበስብበት፣ ዝርፊያና እገታ የሚፈፅምበት መሆኑን ሕዝቡ መረጃውን እንዳደረሰ ሻለቃ የሽዋስ እንዳለ ገልፀዋል” ይላል የመከላከያ የዜና ዘገባ።
ሲቀጥልም፤ “ይህን መሠረት በማድረግም ሰሞኑን የአየር ወለድ ክፍለጦር በሪማ፣ በጀማ ወንዝ እና ወንጭት ወንዞች አካባቢ ባደረገው ዘመቻ ራሱን ራምቦ ክፍለጦር ብሎ የሚጠራው የፅንፈኛ ስብስብ መደምሰሱንና የተረፈው ተበታትኖ መሸሸቱን የአየር ወለድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ማቴዎስ ማዴቦ” ተናግረዋል ሲል ዘግቧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
በሃገራችን የቆየም ሆነ የአጭር ጊዜ ታሪክ ውስጥ ሰዎች ስለ ሃገርም ሆነ ስለ ግል ጉዳይ አንድ ላይ መክረው ሳይሸራረፉ አብረው አንድ ላይ የዘለቁበት የታሪክ ምዕራፍ የለም። ደርግ ከጅምሩ እስከ ማብቂያው አንድ አንድን እየሰለቀጠ ነው ለሻቢያና ለወያኔ አሳልፈው ሃገሪቱን የሰጡት። ወያኔና ሻቢያም ከበረህ አስከ ከተማ ሲፋለጡና አንድ አንድን ሲበላው ዛሬ ላሉበት የዳግም ጦርነት ሽርጉድ ደርሰዋል። እንዲያውም ሰውን ለራት ጠርቶ፤ በስብሰባ ስም ሰብስቦ ባልታሰበ ጊዜ በእንበለ ፍርድ ሰውን በጥይት ደብድቦ መፍጀት ተለምዷል። ለእናት ሃገራቸው ዳር ድንበር በበረሃና በረሃብ ተሰቃይተው ነጻነቷ የተጠበቀ ሃገር ያስረከቡን ውድ ልጆቿን የምትበላ ምድር ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ሹምባሻውና ለጠላት ወሬ አቀባዪ ባለጊዜ ሆኖ ስንቶቹን እንደገፋ ታሪክ ጽፎ ይዞታል። የዛሬው ታሪካችንም ከዚህ ቢከፋ እንጂ የተሻለ ነገር የለውም።
የጎጃሙ በላይ ዘለቀ ከእነ ወንድሙ ሲንጠለጠል ቆመው ያዪት እነ ጄ/መንግስቱ ንዋይና ሌሎች የጊዜው ባለስልጣኖች እልፈታቸውን ሰው ልብ ሊል ይገባል። መንግስቱም ወንድሙም ባልተሳካ የመንግስት ግልበጣ ሞትን ቀመሱ። ከታህሳሱ ግርግር በህዋላ የንጉሱን አልጋ ለማቆየት ደፋ ቀና ያሉትን ደግሞ ደርግ ሰብስቦ ያለምንም ርህራሄ አጭዶ አፈርና ኖራ አለበሳቸው። አብረው የንጉሱን ሞትና የንጉሱን ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች የፈጅት ደግሞ በዚህም በዚያም ሞታቸው አይቀሬ ሆኖ ተሻግረዋል። የዚህ ሁሉ ጉዳይ ዋና መሰረቱ “ ሃበሻ በየወንዙ ሲማማል” የኖረና የሚኖር ህዝብ ነው። ጥርጣሬአችንና ጥላቻችን መሰረት የለሽና በስማ በለው አልፎ ተርፎም ትርክት የተላበሰ በመሆኑ እውነቱን መርምሮ የመረዳት ብልሃቱም ሆነ ትግስቱ የለንም። በዚህ የተነሳ የምንደነግጠው በራሳችን ጥላ ነው። ያ ሲሆን ደግሞ ጥይት ወደ ሰውና ወደ ሰማይ ማንጣጣት እንደ ጀግንነት ይቆጠራል።
አሁን ጊዜው ዘመነ ተብሎ ሰው ሰየጠነና እንሆ በማንነትና በክልል እያሳበብን እንጫረሳለን። ይበለን አውቀን የማንታረም ሁልጊዜ ያዘው ጥለፈው የሚቀናን በጎሳና በብሄር የተሳከርን ነንና። ተምረናል፤ እገሌ ተብለናል የምንል ሁሉ በዚህ በሽታ ክፉኛ ተጠቅተን ይኽው እንሆ በቅርብ እና በሩቅ እሳት ቆስቋሾች ሆነናል። በየትኛውም ስሌት የሰው ልጅ ሰው ከመሆኑ ውጭ በዘሩና በብሄሩ ነገርን ካሰላ ጤነኝነቱ ቀርቷል። እሱ የእኔ ናቸው ብሎ ካመናቸው ውጭ የቆሙትን እንደ ጠላት ፈርጆ ሁሌ ሲያሯሩጥና ሲሯሯጥ ይኖራል እንጂ ሰላምን ለራስም ሆነ ለሌላ አያስገኝም። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ ፋኖ የአማራን ህዝብ ነጻ ማውጣት ቀርቶ ራሱን ነጻ ያላወጣ የክፉዎች ስብስብ ነው በማለት ገና ከጅምሩ አቋሜን ግልጽ ያደረኩት። ይኸው እነርሱም ጊዜው ደረሰና በሃሳብ ተከፋፍለው ጠበንጃ ተማዘው ልክ እንደ ወያኔና ሻቢያ በመገዳደል ላይ ይገኛሉ። ምንም አይነት የፓለቲካ ልዪነት ይኑር አብሮህ በረሃ ለበረሃ የሚንከራተት ወንድምና እህትህን መገደል መኖር አልነበረበትም። ኢህአፓና ወያኔ አንጃ እያሉ፤ ሻቢያ የሌሊት ወፍ እያለ እንዳጠፋቸው ሁሉ ፋኖም እርስ በርስ መነካከሱ አስገራሚ አይሆንም። ሰምተናል፤ አንበናል ኦነግ/ሽኔም እርስ በእርሱ እንደሚፋለም። እንግዲህ ያለፈውን አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ ለተመለከተው ተግባራችን ያዘው ጥለፈው፤ በይውና በላት ነው። የሚያሳዝነው የሙት ጊዜ የፓለቲካ ቋንቋን እየተጠቀሙ “ታጋይ እንጂ ትግል አይሞትም” ሲሉን አለማፈራቸው። ለምን ትግል አይሞት ድብን ብሎ ነው የሚሞተው። “አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር” ያሉን ወስላቶች አሁን የት አሉ? እልፎችን የበላው የሶቪዬቶች ሶሻሊም ከየት ገባ? Understanding Contemporary Ethiopia -Monarchy, Revolution and the Legacy of Meles Zenawi – Gérard Prunier and Éloi Ficquet በመጽሃፋቸው ላይ የሃበሻን የፓለቲካ ውስብስብነትና ጨለማዊ እይታውን ለማሳየት ጥረዋል። ከ15 ዓመት በፊት Gérard Prunier – The Real Eritrea በሚል አርዕስት ገና ያኔ ስለ ኤርትራ መንግስት የሰጠውን ሙሉ ዝግጅት ዪቱብ ላይ ፈልጎ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። ፓለቲካችን የተጣረሰና የመበላላት ፓለቲካ እንደነበረና አሁንም እንደሆነ ለመረዳት ይጠቅማልና። አውቃለሁ በየአለማቱ ተሸጉጦ Leave Eritrea for the Eritreans የሚሉ ቱልቱላዎች እንዳሉ። ግን እነዚህ በሁለት ቢላዋ የሚበሉ ለኤርትራ ህዝብ ምንም የማገዳቸው ሆዳም ካድሬዎች ናቸው። ችግሩ ዛሬም በኤርትራ ባሳ እንጂ አልተሻለምና! እንግዲህ ፋኖ፤ ኦነግ/ሸኔ፤ ወያኔ፤ የሻቢያ ተቃዋሚ ሃይሎች ሻቢያ ራሱ ይህን የጦርነት አባዜ በመተው ለሰላም ጊዜ እስካልሰጡ ድረስ መገዳደላችን ቋሚ ነው። በዚህ ላይ ብልጽግና ከጉራ፤ ደረስኩብህ፤ ያዝኩህ ከሚለው መንጣጣት ይልቅ የሰላም መንገድን መርጦ ያሰረና ያፈናቸውን በመፍታት የሃገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማስከርበር የብሄርን ኮፍያ አሽቅንጥሮ በመያዝ ለህዝባችን ሰላምና መረጋጋት ያለውን ሁሉ ቢጠቀም ወሸኔ ይሆናል እላለሁ። በተረፈ ፋኖም ሆነ ኦነግ/ሸኔ ወይም ወያኔ ወደ አንድነት ይመጣሉ ብየ አላስብም። እየተናኮሩ እያናኮሩ ይኖራሉ እንጂ! በቃ ማለት የሚችለው ህዝብ ነው። ሌላው ሁሉ ያዘው ልቀቀው የልጆች የገመድ ጉተታ ጫዋታ ነው። አብሮ መውደቅ!