
በትግራይ የተኩስ ማቆም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ያኮረፈው ሻዕቢያ ከግብጽ በወሰደው ውክልና “አንጃ” ከሚባለው የትህነግ ውስን ኃይልና በአማራ ኦሮሚያ ክልል ጠብ መንጃ ካነሱ ኃይሎች ጋር ግንባር ገጥሞ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ሊከፍት ያሰበውን ውጊያ በአቅም ማነስና ምድር ላይ ባሉ እውነታዎች አስገዳጅነት ለማራዘም መወሰኑ ተሰማ።
የኤርትራን የጦርነት ዝግጅት ከውስጥና ከውጭ የሚከታተሉ የኢትዮሪቪው የመረጃ ሰዎች እንዳሉት፣ ከግብጽ በወሰደው ውክልናና ከግል ስጋቱ በመነሳት ከኤርትራ ውጭ በኢትዮጵያ ግዛት ሊጀመር ያሰበውን ጦርነት ለማቆየት የወሰነው ምድር ላይ ባሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሳቢያ ዓቅሙ እንደማይፈቅድ ተረድቶ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት “ጦርነት አንፈልግም። ከነኩን ግን ምላሹ የከፋ ይሆናል” ማለቱ የሚታወስ ነው።
እንደ ዜናው ሰዎች ከሆነ የመጀመሪያው ምክንያት በትግራይ አሁን ላይ የተፈጠረው “ጦርነት በቃን” የሚለው የሕዝብ ድምጽ፣ የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች “አንዋጋም” በሚል መክዳታቸውና አሁንም እየከዱ መሆናቸው፣ ውስን የታጣቂዎቹ አመራሮች እንጂ ሁሉም ከሻዕቢያ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚደግፉ አለመሆናቸው ጦርነቱ ቢጀመር ኢትዮጵያ ምድር ተወስኖ ይቀራል የሚለውን ስሌት መና አድርጎታል።
ግብጽን እየታዘዘ ቀጠናውን የጦርነት ዐውድማ ለማድረግ ሶማሊያንና ሶማሊያ ውስጥ ያሉ የሽብር ቡድኖችን በመያዝ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሻዕቢያ ያሰበውን ጦርነት ተባብረው የሚገፉበት ከሆነ አሜሪካ ማዕቀብ ለማድረግ እያጤነች መሆኑ ሌላ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል።
እስከ ዛሬ ድረስ በአሸባሪዎች ሊስት ውስጥ ያለው ትህነግ አዛውንት አመራሮች በስጋት ፍሬን በመያዛቸው ሳቢያ በግለት የተጀመረው የጦርነት ሩጫ አባርዶታል። ይህንኑ ተከትሎ ትህነግ ውስጥ ማፈግፈግ መታየቱ ከሻዕቢያ በኩል ቅሬታ በማነሳቱ የድርድር አማራጭ ለመያዝ ማሰቡ ተሰምቷል።
ጦርነቱን በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሱዳን አቅጣጫ ለጥጦ በዘመቻ በአንድ ላይ ለማካሄድና የመንግሥትን ኃይል ለመበተን ካይሮ ላይ የተነደፈው የማጥቃት ስልት፣ ሙሉ መረጃ ከጦርነቱ አሰላለፍ ጋር መንግሥት እጅ መግባቱን የገለጹት የዜናው አቀባዮች፣ በኦሮሚያ የሸኔ ኃይል በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ፣ ከጎጃም የፋኖ እንቅስቃሴ ውጭ በሌሎች አካባቢ ያሉት የፋኖ መሪዎች ለጥሪው ሙሉ ምላሽ አለመስጠታቸውና መቃወማቸው፣ በሱዳን በኩልም ያልተጠበቀ ምክንያት መቅረቡ ሻዕቢያ ካለው አቅም ጋር ተዳምሮ ጦርነት ስለማያዋጣ ከተገኘ የዲፕሎማሲውን አግባብ መከተል ወደሚለው አማራጭ ለመዞር እያማተረ መሆኑን ገልጸዋል።
በግብጽ፣ ኤርትራና ሱዳን በመሸገ የትህነግ ተዋጊዎች የሚደገፈው የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ካርቱም ነጻ መውጣቷን ቢያውጁም፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ያለ ውጊያ ለቅቆ መውጣቱ ኃይሉን ባሻው ወቅት መልሶ ሊያንቀሳቅስ እንሚችል ስጋት አለ።
ካርቱምን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን የለቀቀው ለስልታዊ ማፈግፈግ እንደሆነ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እየገለጸ ከመሆኑ አንጻር ሱዳን ሻዕቢያ በሚፈልገው መጠን ምቹ አልሆነችም። እንደ መረጃ ምንጮቹ ቀደም ሲል በተገለጸው ምክንያት ሱዳን ግብጽ በሻዕቢያ በኩል እንድተተገብረው የታቀደላት ዕቅድ መፈጸም አትችልም። በአስመራ የሰሞኑ የሁለቱ መሪዎች ውይይት እዚሁ ላይ ያተኮረ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከቶ አፍሪካ ኅብረት ባስራጨው መግለጫ፤ በሱዳን እልቂቱ አሳሳቢ ሆኗል። ግጭቱም እየተባባሰ ነው። በተለይም በኤል ፋሸር፣ በሰሜን ዳርፉር እና በዘምዘም የሚባሉ አካባቢዎችን በመጥቀስ አፍሪካ ህብረት በሊቀመንበሩ አማካይነት ስጋቱን አኑሯል። በዚህ መሰሉ የዕርስ በዕርስ ጦርነት እየታመሰች ያለች አገር የኢሳያስን አጀንዳ ጀርባ ለመሸከም አለመቻሏ ሻዕቢያን አቅም አልባ እንዳደረገው ተጨባጭ ያሉትን ምክንያት ገልጸው የዜናው ሰዎች ተናግረዋል።
“ከሱዳንና ከምዕራብ የትግራይ አቅጣጫ ወልቃይትን ለማስለቀቅ ጊዜው አሁን ነው” የሚሉ ወገኖች አሁን ላይ ጋብ ያሉበት ትክክለኛ ምክንያት ባይታወቅም ከዚሁ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል የዜናው ሰዎች ገልጸዋል።
ሆርን ሪቪው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጨክነው ሀገራቸውን ወደ ጦርነት ውስጥ ከከተቱ ሊከሰት የሚችለውን ሲተነብይ ወታደራዊ ሽንፈትን ብቻ ሳይሆን ሊቀለበስ የማይችል የግዛት ለውጥ ወይም አሁን የያዙትን ቅርጽ የጠበቀች ኤርትራ እንደማትኖራቸው ነው።
በድፍን ዓለም የተደገፈችውንና ሩሲያ ያጥለቀለቀቻትን ዩክሬን ጠቅሶ ኤርትራ ብቻዋን የቆመች አገር መሆኗን ያወሳው ሆርን አፍሪካ በዘገባው ኢሳያስ ጦርነቱን ከለኮሱ ለሚደርስባቸው ሁሉ ተከራካሪ ድምጽ እንደሌላቸው አመልክቷል።
ከሶስት አስርት ዓመት በላይ ኤርትራን በወታደራዊ አስተዳደር ጨምድዶ፣ ኢኮኖሚውን አንቆ፣ የያዘው የኢሳያስ አገዛዝ ቀደም ባለው የጦርነት ሙቀትና ጥድፊያ መቀጠል ያልቻለበትን ምክንያት ጠቅሰው ዜናውን ያጋሩን እንዳሉት ሻዕቢያ አሁን ላይ አቅሙ እንደማይችል አምኗል። በርካታ ለሻዕቢያና ለአለቃቸው ግብጽ “አመቺ” ተብለው የነበሩ ጉዳዮች መልካቸውን ቀይረዋል። በዚህም ላይ ኢትዮጵያ ግዙፍ ሠራዊት፣ ዘመናዊ መሣሪያና ከፍተኛ የተባለ የአየር ላይ ብልጫ ስላላት ሻዕቢያ ጦርነቱን እንደማይቋቋም በስፋት አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ሰሞኑን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ የጸጥታና የደህንነት ምክር ቤት ስም ባይጠቅስም በማኅበራዊ ሚዲያ አዝማቾች ፕሮፓጋንዳ የታጀቡት የውጭና የውስጥ ኃይሎችን ማጽዳት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማስታወቁ፣ የባህር በር የማግኘትን መብትን በተጀመረው ግለት እንደሚቀጥል ማስታወቁና በሳምንት ውስጥ ከመቶ ሃያ ሺህ በላይ ሰራዊት ማስመረቁ፣ ይፋ ባይሆንም የአገሪቱ የወታደር አቅም መቶ ሺዎችን መዝለሉ የሻዕቢያን ስጋት አጉልቶታል።
ሻዕቢያ በጅምላ ለውትድርና ክተት ማጥራቱን ፣የጉዞ እገዳ በመጣልና መጠባበቂያ ክምችት በማሰባሰብ ወታደራዊ ዝግጅቱን አስቀድሞ ማጠናከሩ ከወራት በፊት ይፋ መደረጉ አይዘነጋም። ከዝግጅቱ ጎን ለጎን ከስደት የተረፈው አነስተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ባለቤት መሆኗ ተተኪ አቅማ ስላሳጣው፣ ዘመን ያለፈባቸው የሶቪየት ሰራሽ መሳሪያዎች በዘለለ ዘመናዊ ትጥቅ ስለሌለው፣ ኢኮኖሚው የደቀቀ በመሆኑ፣ ከአጠቃላይ አገራዊ አቅም ጋር ተዳምሮ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጦርነትን የመሸከም አቅም አልባ መሆንና የውስጥ አፈናው የፈጠረው መሰላቸት አንድ ላይ ተዳምሮ ጦርነቱ ከተከፈተ ሽንፈት ብቻ ሳይሆን የካርታ ቅርጽ የሚያስቀይር ውጤት ሊኖረው እንደሚችል የሚሰጠው አስተያየት እንደቀጠለ ነው።
መንግሥት ከትህነግ ጋር የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ በይፋ ቅር መሰነታቸው በሚቀርቧቸው የአማርኛ ሚዲያዎች በስፋት መገለጹ አይዘነጋም። በጦርነቱም ወቅት በትግራይ ከፍተኛ ወንጀል፣ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጅማላና የተናጠል ግድያ ከፈጸመ ኃይል ጋር ዛሬ ላይ እየተደረገ ያለው ስምምነት በትግራይ ክፈተኛ ተቃውሞ እያስነሳ እንደሆነ የሚታውቀ ነው።
ድርድርም ሆነ ማናቸውም የንግድ ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ያስታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ሻዕቢያ እየከጀለ ላለው የውይይት ጥያቄ በሩ ክፍት እንደሆነ የዜናው ምንጮች አመልክተዋል። ይሁን እንጂ የባህር በር ህጋዊ መብት ጉዳይ ግን የንግግሩ የማይቀየር ቁልፍ አጀንዳ ነው። ኢትዮጵያ የባህር በሯን በሤራ ተዘርፋለች የሚለውን የኖረ ቁጭት አጀንዳ ያደርገው መንግሥት በያዘው አቋም ሕዝብ ድጋፍ እየሰጠው ነው።
በተቃራኒ ልክ እንደ ሻዕቢያ ሁሉ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ አኩርፈው መንግሥት ላይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የጀመሩ በግልጽ “አብይን ለመጣል ከኤርትራም ሆነ ከማናቸውን አካላት ጋር እንሰራለን” እያሉ ነው። እነዚህ ክፍሎች የኢትዮጵያ ህልውናና ቁልፍ ብሔራዊ ጥቅሟ ላይ እየተማማሉ ያሉ ጥቂት የሚዲያና የታጣቂ ኃይል አመራሮች ናቸው።
በተመሳሳይ ዜና አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መሪነታቸው ሙሉ የሻዕቢያን ዕቅድና ግንኙነት ጠንቀቀው ያውቁ እንደነበርና፣ ከበቂ በላይ ማስረጃና መረጃ እንደነበራቸው የሚያውቁ ሌላው ሻዕቢያን ያበሳጨ ጉዳይ ነው። አቶ ጌታቸው በረሃ ሆነው ጦርነቱን በፕሮፓጋንዳ ሲመሩ ትህነግ በሱዳን፣ በጅቡኢና ሶማሊያ የነበረውን ሴል እንዴት ይጠቀም እንደነበር ስለሚያውቁ ይህም ሌላ ስጋት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። (ኢትዮሪቪው)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply