በ2016 ዓም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 684 ሺህ 205 ተማሪዎች ያለፉት 36 ሺህ 409 ወይም 5.4 በመቶ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከትላንት በስቲያ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ከዚህ በታች ያለውን መረጃ ያሰባሰብነው ከመንግሥታዊ ሚዲያና ከቲክቫህ ነው።
- በአጠቃላይ 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ሲሆን በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ 4 ትምህርት ቤቶች ከሐረሪ ክልል ውጭ ሁሉም ክልሎች ላይ አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አመላክተዋል።
- በአጠቃላይ ከፍተኛ ውጤት ከ500 በላይ ያመጡ ተማሪዎች ባለፈው ዓመት 273 የነበሩ ሲሆን በአሁኑ 1ሺ 220 ተማሪዎች ከ500 በላይ ያመጡ ናቸው ተብሏል።
- እንዲሁም በዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱት ውስጥ 5.4 በመቶ ፈተናውን አልፈዋል ይህም ማለት 36 ሺ 4 መቶ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ማለፊያ ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡
- የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛው ውጤት የተመዘገበው በትግራይ ነው፡፡
- በክልሉ ቓላሚኖ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነ ልጅ ከ700 ፈተና 675 በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገቡ ተነግሯል፡፡
- በአዲስ አበባ የካቴድራል ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነች ልጅ ከ600 ውጤት 575 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች።
- ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ሴቶች ሲሆኑ በተፈጥሮ ሳይንስ ካቴድራል ትምህርት ቤት 575 ከ600 እና በማኅበራዊ ሳይንስ ኢትዮ ፓረንትስ ትምህርት ቤት 538 ማስመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡
- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 21 በመቶ (ከ10ሺ በላይ) ተማሪዎችን ከክልሎች ደግሞ ሐረር 337 እና ኦሮሚያ 8ሺ በላይ ተማሪዎች ማለፋቸውን እንዲሁም ሁሉም ክልሎች ከአምናው የተሻለ ተማሪዎችን ማሳለፋቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
- በዘንድሮ ዓመትም የሬሜዲያል ፈተና የሚኖር ሲሆን የተፈታኞች ቁጥር ግን ከአምናው ቁጥር እንደሚቀንስ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
- ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ሀገራዊ አማካኝ ውጤት (mean) 29.76 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው÷ የዘንድሮው ከፍተኛ ውጤት ከ700ው 675 መሆኑን እና ይህም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ከፍተኛ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
- ከፍተኛ አማካይ ውጤት (66.1 በመቶ) የተመዘገበው በአዳሪ ትምህርት ቤቶች መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተናግረዋል፡፡
- ከፍተኛ አማካይ ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች፤
- አዳሪ ትምህርት ቤቶች
- ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች
- የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች
- መንግሥታዊ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶች
- የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኦንላይን እና በወረቀት የተሰጠ ሲሆን፤ ፈተናውን በኦንላይን ከወሰዱት መካከል 26.6 በመቶ የሚሆኑት የማለፊያ ውጤት አምጥተዋል።
- ዘንድሮ 30 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን በኦንላይን የወሰዱ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓመት እስከ 150 ሺህ ተማሪዎች በኦንላይን ፈተናውን እንዲወስዱ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል።
- “በ2016 ትምህርት ዘመን በወረቀትና በበይነ መረብ የተሰጠው ፈተና ውጤት እንድምታው ሲታይ ከ2014 ዓ/ም 30,034 (3.3%) ፣ ከ2015 ዓ/ም 27,267 (3.2%) … (ዘንድሮ 5.4%) መሆኑ እያሽቆለቆለ እየሄደ ያለው ጉዞ የተገታ እና መጠነኛ የመሻሻል አዝማሚያ ያሳየ ቢሆንም አሁንም 50% እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተፈታኞች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው” በማለት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
- በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የነበረው የደንብ መተላለፍ ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
- የደንብ ጥሰት የፈጸሙ 313 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ውጤታቸው እንደተሰረዘ ገልጸዋል።
- በአማራ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ፈተና እንደሚወስዱ የትምህርት ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply