ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት የወርቅ ምርት “በከፍተኛ መጠን” መቀነሱን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ተናገሩ። የባንኩ ገዢ በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ጥብቅ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊስ መከተል አለመቻሉን ገልጸዋል።
ዶ/ር ይናገር ይህን ያሉት የብሔራዊ ባንክን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት፤ ለፓርላማ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሐሙስ ህዳር 29 ባቀረቡበት ወቅት ነው። የባንኩ ገዢ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ በሩብ ዓመቱ የነበረውን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ዳስሰዋል።
የሩብ ዓመቱ የወጪ ንግድ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር “መጠነኛ ጭማሪ” ማሳየቱን ያነሱት ዶ/ር ይናገር፤ ገቢው “በተወሰኑ ዘርፎች ላይ” የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል። ሀገሪቱ ላገኘችው ገቢ “ከፍተኛውን ድርሻ” የያዙት አበባ እና ቡና መሆናቸውን የጠቆሙት የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ በሌሎች ምርቶች ግን “አነስተኛ አፈጻጸም” መመዝገቡን አስረድተዋል።
አነስተኛ አፈጻጸም አላቸው ከተባሉ እና ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ ምርቶች ግንባር ቀደሙ ወርቅ ነው። “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወርቅ ምርት በከፍተኛ መጠን ቀንሷል” ያሉት ዶ/ር ይናገር፤ ሀገሪቱ ባለፈው ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ ያቀረበችው የወርቅ መጠን ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያን ኢንሳንደር)
የዛሬ ዓመት የማዕድን ሚኒስትሩ እንዲሁ ተመሳሳይ መረጃ አካፍለው እንደነበር ይታወሳል። ያኔም ያሉት የወርቅ ገቢ መጠን የቀነሰ ብቻ ሳይሆን ወደ ባንክ እየገባ ያለው የወርቅ መጠን እጅግ ዝቅተኛና በሚታሰበው መጠን እንዳልገባ ነው።
ሸኔ የሚንቀሳቀስበትና የጉሙዝ ታጣቂዎች ግፍ የሚፈጽሙባቸው ቦታዎች ከፍተኛ የወርቅ ክምችት እንዳለና ወርቅ በሕገወጥ መንገድ እየተመረተ ወደ ውጪ በሕገወጥ መንገድ እንደሚወጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በቅርቡ ፕሬዚዳንት ሳህለወቅር ዘውዴ የማዕድን ሥራ ለከፍተኛ ወንጀል የተጋለጠና ባግባቡ ካልተያዘ ችግር ፈጣሪ እንደሚሆን መጠቆማቸው ይታወሳል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply