- “ስንደመር እናሸንፋለን፣ አንድ ካልሆን እንጠፋለን” የለማ መገርሳ ተማጽንዖ!!
ኦህዴድ በድንገት ያካሄደውን “ስትራቴጂክ” የተባለ የአመራር ሽግሽግ አስመልክቶ ለማ መገርሳ በሰጠው መግለጫ በተደጋጋሚ “አንድ ካልሆንን እንጠፋለን፤ ስንደመር እናሸንፋለን” ማለቱን በማስታወስ ህወሓት ኦህዴድን ለመበተን እየሠራ መሆኑን በተደጋጋሚ ለጎልጉል መረጃ የሚሰጡት የኢህአዴግ ሰዎች ተናገሩ። ወታደራዊ አገዛዙ በትሩን በኦህዴድ አመራሮች ላይ እያሳረፈ ነው።
የጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የአዲስ አበባ ዘጋቢ የመረጃ ሰዎቹን ዋቢ በማድረግ እንደገለጸው የኦህዴድ መፍጠን ህወሓትን አበሳጭቷል። በድንገት ኦህዴድ ሽግሽግ ከማድረጉ በፊት የህወሓት ቅርብና ታማኝ የሚባሉ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን አባርሯል፤ አግዷል። እንዲሁም ዝቅ በማድረግ አቅም አልባ አድርጓቸዋል።
የማጽዳቱ ሥራ ጅምር እንደሆነና ወደፊትም በተለያዩ መዋቅሮች ማሻሻል በማድረግ ኦህዴድን በአዲስ የመሥራት ዕቅድ እንዳለ ለማ መገርሣ በቃለ ምልልሱ አመልክቷል። ይህንን አካሄድ ለጥንቃቄ ሲባል የሚደረግ መሆኑንን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ።
ህወሓት እንዴት ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን እንደሚበላ ጠንቅቀው የሚያውቁትና ተሳታፊ የነበሩት የኦህዴድ አዲስ አመራሮች ከቅርብ ጊዜ በኋላ እየያዙ የመጡት አቋም የራስ ምታት የሆነበት ህወሓት፣ ቢነቃበትም አመራሩን በኃይል ለማንበርከክና ድርጅቱን ለመበተን እየሠራ መሆኑ ተሰምቷል። እንቅስቃሴውን የሚረዱት የአሁኖቹ የኦህዴድ አመራሮች ግን “የወሰድነው እርምጃ ሁሉ ህዝባችንን ተማምነን ነው፤ በህዝባችን እንመካለን” በሚል በራሳቸው መገናኛ “እኛም አውቀናል…” አይነት ምላሽ መስጠታቸውን ጉዳዩን የሚከታተሉ ይገልጻሉ።
ለጎልጉል ዘጋቢ መረጃ የሰጡት ክፍሎች እንዳሉት ህወሓት በአስቸኳይ አዋጅ ስም ወታደራዊ አስተዳደሩን በመጠቀም በኦሮሚያ የመካከለኛ አመራሮች ላይ በትሩን ማሳረፍ መጀመሩን የታሰሩትን ስም በመጥቀስ ዘርዝረዋል። በተጨማሪም ገጠር ድረስ በመግባት በፈረሰው መዋቅር ላይ ህወሓት አመራር መስጠት ጀምሯል። የዓይን ምስክሮች እንደሚሉት ጠብመንጃ አንጋቾች አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ የተረከቡበት ደረጃ ደርሰዋል። አዲስ አመራርም ማደራጀት ጀምረዋል። በአንጻሩ ግን አዳዲስ አመራሮችን ማደራጀት መጀመሩ ካሁን በኋላ ኦሮሚያ ላይ እንደማይሠራ ተጠቁሟል።
ከወራት በፊት በ“ጥልቅ ተሃድሶ” ስም ከኦሮሚያ ከሁለት ሺህ በላይ አባላቱን ያገደውና ያባረረው ኦህዴድ ከ3000 በላይ ሚሊሺያ እንደመለመለ የኮማንድ ፖስቱ ፀሐፊ ሲራጅ ፈርጌሳ ባወጀበት ወቅት ሁሉም ሰላም፣ ሁሉም አማን እንደሆነ አመልክቶ ነበር።
በስልጤ ዞን በነፍስ ማጥፋት የሚወነጀለው ሲራጅ፤ ይህንን ባለ በቀናት ልዩነት ውስጥ ኦህዴድ መክዳቱን ያረጋገጠ ክልል-ዓቀፍ ተቃውሞ አገረሸ። እነ ሲራጅ ህወሓትን ለማስደሰት በህጻናት፣ በታዳጊዎችና በአዛውንቶች ደም የተነከረው እጃቸው ሳይጠግግ ዳግም በደም መጨማለቅ ጀምረዋል። በነቀምት፣ በደንቢ ዶሎና በባሌ ደም እያፈሰሱ ነው። ይህንን የተቃወሙ የኦህዴድ የአካባቢው አመራሮች ታስረዋል። የት እንደተወሰዱም አይታወቅም።
የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ጉዳዩን በመቃወም የታሰሩት እንዲፈቱ ጠይቀዋል። በዚህ መሰሉ ውጥንቅጡ የወጣ አካሄድ የሚዳክረው ህወሓት የኦህዴድና የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጫና ለመፍጠር የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተቀምጧል። የጎልጉል መረጃ አቀባዮች እንደሚሉት ነገ (አርብ) የሚደረገው የኢህአዴግ ሸንጎ (“ፓርላማ)” ፍትጊያ እንደሚኖርው ያሰጋው ህወሓት አቻ ፓርቲዎቹ ለድርጅታቸው መርህና ቃል ለገቡለት ዲሲፒሊን እንዲገዙ መወትወቱ የተፈራውን እንደማያስቀረው ነው።
ለጀርመን ድምጽ ቃለ ምልልስ የሰጡ የፓርላማ አባሎች እንዳሉት ጉዳዩ የመደገፍና የመቃወም ሳይሆን በቂ ማብራሪያ እንደሚጠይቁ፣ ማብራሪያው የሚያሳምን ሊሆን እንደሚገባው፣ ይህ ሳይሆን ድጋፍ ለመስጠት እንደሚቸገሩ አመልክተዋል። በሌላ አነጋገር “ማመን መቻል” አለብን ሲሉ ተደምጠዋል።
የጎልጉል ዘጋቢ ያነጋገራቸው የድርጅት ሰዎች አርብ የሚደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማጸደቅ ስብሰባ በቀጥታ ለህዝብ እንዲተላለፍ ኦህዴድ ጠይቋል። ይህም በህወሃት በኩል ተቃውሞ ቢያስነሳም መጨረሻው ግን ምን እንደሆነ ገና አልታወቀም።
እዚህ ድረስ የተካረሩት ህወሓትና ኦህዴድ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን ለመገመት ቢያስቸግርም፣ ኦህዴድ ዶ/ር መረራ ከሚመሩት የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግሬስ (ኦህኮ) ጋር በማንኛውም ጉዳይ ድርድር ለማድረግ፣ ለመወያየትና ስምምነት ለመፈጠር ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ መሆኑንና በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባ በከፍተኛ አመራሩ አማካይነት አመልክቷል።
ህወሃት “አሸባሪ” ብሎ ሲያሰቃያቸው ከነበሩት አካላት ጋር በሁሉም ጉዳዮች ለመደራደር በሩን መበርገዱን ይፋ ያደረገው ኦህዴድ የፓርላማ አባላቱን በማስተባበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት እንዲከፍልም ማሳሰቢያ እየቀረበለት ነው። የኦሮሞ አክቲቪስቶች፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ለመላው የፓርላማ አባላት እንዲያስቡበት እየመከሩና እያስጠነቀቁም ነው። በተለይም የጉዳዩ ዋና ባለቤት “ቄሮ” የኦሮሚያ ወኪሎችን (“የፓርላማ አባላትን”) ክፉኛ አስጠንቅቋል።
አዋጁ በድምጽ ብልጫ እንዳያልፍ የአማራ ክልል ወኪሎችም ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። እጅን ማውጣት “አፋችንን ለጉሙን፣ ግደሉን፣ እሰሩን ማለት ፍጹም ከህዝብ ጋር መቆራረጥ ነው” ሲሉም ስለወደፊቱ እንዲያስቡ ምክር አዘል ማሳሰቢያ አክለዋል።
ህወሓትና በህዝብ ጫና የተወጠረው ኦህዴድ፣ አቋሙን ወደ ህዝብ ያጋደለው ኦህዴድ፣ ስልታዊ አካሄድ መከተሉን ያወጀው ኦህዴድ፣ መጨረሻው ምን ይሆን? በኢህአዴግ የድርጅት መርህ መሠረት በድምጽ ብላጫ በማዕከላዊ ኮሚቴ የሚወሰነውን ውሳኔ ማስፈጸም የየድርጅቶቹ እና በድርጅቶቹ ጥላ ሥር የተመረጡ የፓርላማ አባላትና ምድብተኛ ባለስልጣኖች ግዴታ ነው። እናም ኦህዴድ የሞት መንገድ መሆኑንን በሚገነዘበው መንገድ “ለመርህ” ብቻ ሲል ከተቃቃረው ህወሓት ጋር አብሮ ይቀጥላል ወይስ በግልጽ ኢህአዴግን በመሰናበት ወደ ህዝብ ይቀላቀላል (ራሱን ይችላል)?
የጎልጉል ዘጋቢ እንደሚለው ህወሓት የነከሰውን ጥርስ መቼም ሰላማያላቅቀው ኦህዴድ ዙሩን ማክረር እንደሚጠበቅበት አምነው የመጣውን ለመቀበል የተዘጋጁ አሉ። በተመሳሳይ ደግሞ ሁኔታው ሂደት በመሆኑ ከማክረር በስልት መሥራቱ እንደሚበጅ የሚናገሩም አሉ። ይህ ክፍተት ድርጅቱን ለመሰነጠቅ ለታሰበው ሤራ የሚያመች ደረጃ ላይ ነው ብለው ግን አያምኑም። ከዚህ በላይ የሚያሰጋው ግን የኃይል ጉዳይ እንዳይነሳ ነው። አቶ አለማየሁ አቶምሳን በአጭሩ ያስቀረው መርዝም አለ!!
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Mulugeta Andargie says
በሰንጠቅ??? ሚኖ ባኪህ?? ጋብሬል ሲንጢቅ!! ያርጋል!
Petros says
idiot!
ወንድወሰን says
ሀለቃ በትኔ፣
እውነተኛ ቀለምሽ እየተንጠባጠበ ነው!
Eyerus says
እኔን የሚገርመኝ
ክፉዎች በክፋታቸው
የተለያየ ስልት እያወጡ
የመግደል ሥራቸውን
በወታደራዊ ኃይል
የበለጠ ለመቀጠል ሲዘጋጁ!
ኦሆዴዶች ሕዝባቸውን ለማትረፍ
የተለያየ ስልት እየነደፉ ሳለ
የመሪዎችን ስም ማጠልሸት
ዋሾዎች ሥራቸውን ጀመሩ በሃሰት!
ብአዴን ምን ነካው
የመረጠው ዝም ማለት?
የደመቀ ባህሪ ተጋባበት?
ወይስ እንዳይናገር የጠ/ሚኒስቴርነት ጉርሻ ቃል ተገባለ?
አሁንም ምርጫቸው ከሆነ አሻንጉሊነት?
ይብላኝላቸው ስልጣኑ በሕዝብ እጅ የገባ እለት
ሕዋት ትግራይ እናንተስ መቸ ይሆን አደብ የምትገዙት?
እየሆነ ካለው ሁኔታስ መቼ ይሆን የምትማሩት?
ሁልጊዜ ያለእኛ ስለማይሆን ተውን እንቀጥለበት?
እያላችሁን ነው እኮ በምድሪቱ ላይ እኛ ብቻ እንንገሥበት!
ተወስኗልና እኛ ለመግደል ሌላው ለመሞት!
የትግራይ ሕዝብ ሚናስ በዚህ የሞት የሽረት ወቅት ምን ሊሆን ይገባው ነበር?
ዝምታ ወይስ የልጆቹን አውሬነት መቃዎም??? ምርጫ ሊኖርህ ይገባል እኮ ! ኧረ መቐለ፣ ማይጨው፣ እንደርታ፣ አገው፣ አጋሜ ወዘተ አስተውል??
አለም says
ጎልጉል፣
ጉዳዩ ያለው የኦሮሞና የአማራ ቄሮ ጋ ነው። ሕዝብ ተነስቷል፤ ትግሉ እየተጧጧፈ ነው። ህወሓት ያንን ማብረድ እንደማይቻለው አውቆታል። መቀጠል ያለበትና መቋረጥ የለለበት ለዚህ ነው። መሪ የሚወጣውና እነ ለማ ብርታት የሚያገኙት ከኋላቸው ሕዝብ ሲነሳ ብቻ ነው። ህወሓት ለማወናበድ ይሞክራል፤ ትግሉ ከቀጠለ ግን ተስፋ የለውም። በነገራችን ላይ ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ሌላ ወሬና ውዥንብር ትቶ ውስጥ ባሉት ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ ለዓለም ማስታወቅ ይኖርበታል።