የአገራችን “ሃብታሞች” ወግ ከፍቶ ውስጡን ላየው ያስደነግጣል። “ገንዘብ ባለበት ሁሉ ጩኸት አለ” የሚለው አባባል በተለይ በኢትዮጵያ እውነት እንደሆነ ማረጋገጫም ነው። ጎልጉል ባገኘው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ሲጋልቡ የነበሩ አካላት፣ አሁን ላይ “ይህ ለምን ቀረብን?” ወይም “ገና ለገና ሊቀርብን ነው” በሚል ሥጋት አንድ ላይ አገር እየናጡ ነው።
ከዚህ ቀደም “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አእምሮና የደም ዝውውር ሊኖረው ነው” በሚል ርዕስ ስለ አዲሱ ማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ስንዘግብ ውሳኔው “በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ሳይሆን አዲስ መጽሐፍ ነው፤ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አእምሮና የደም ዝውውር ሊኖረው ነው፤ ከዚህ አኳያ ፖሊሲው እንከን የማይወጣለት ነው” በሚል አቶ ኤርሚያስ አመልጋን ጠቅሰን እንደነበር ይታወሳል።
ይህን ዘገባ ተከትሎ የአዲስ አበባ ተባባሪያችን ባገኘነው መረጃ የተደራጁ ወይም በደም የተገናኙ የባንኩን ክፍለ ኢኮኖሚ፣ የመንግሥትን የፋይናንስ ሥርዓትና የአገሪቱን የገንዘብ ዝውውር አንቀው እንዴት አድርገው እንደሚጋልቡት የሚያሳይ ነው።
ጉዳዩ እንደዚህ ነው፤ … ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ደም ቆጥረው፣ አካባቢ ወስነው፣ ዝምድናና አምቻ ለክተው አንድ የተመረጠ ግለሰብን ወይም ነጋዴን ለማገዝ ይታቀዳል። መረጃው እንደሚያሳየው ዕቅዱ ሲታቀድ ለዚያ የተመረጠ ነጋዴ ወይም ያገር ልጅ ብር ይዋጣለትና መቶ ሚሊዮን ገደማ የሚገመት ንብረት ወይም ቤቶች ወይም ሕንጻ እንዲገዛ ይደረጋል።
እንደ ጎልጉል መረጃ ሰዎች ብቻ ሳይሆን መንግሥትና ለባንኮች አሠራር ቅርብ የሆኑ በተደጋጋሚ እንደሚሉት ዘርፉ በሰፈር፣ በአካባቢ፣ በዘርና በክልል የታጠረ በዘመናዊ ዓለም ዘመናዊ አሠራርን በዘርና ደም ቀብቶ የሚንቀሳቀስ ኋላ ቀር የቤተሰብ ማኅበር ዓይነት ነው። ብዙዎች እንደሚሉት አብዛኞቹ ባንኮች በቅርቡ ዕጣ ፈንታቸው መደርመስ እንደሆነ የሚናገሩትም በዚሁ የአፈጣጠራቸውና የአሠራራቸው ባህርይ መነሻነት ትክክለኛ ባንኮች ወደ አገር ቤት ሲገቡ ተወዳዳሪ ሊሆኑ ስለማይችሉ ነው። ይህ እንደሚሆን በድፍረት የሚናገሩ ወገኖች በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ በጣት ለሚቆጠሩ ባለሃብቶች ብድሩን በማይመጥን መያዣ አሁን ያሉት ባንኮች ማበደራቸውን አብነት ያደርጋሉ። ሌሎችም ምክንያቶች አሏቸው።
እናም በዚሁ የደም ወይም የዘር ወይም የአምቻ ቆጠራ ንብረት የተገዛለት “ታዳጊ ባለሃብት” ያንን መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት አስይዞ መቶ ሚሊዮን ብር ከባንክ እንዲበደር የባንኮቹ አፈጠጠር ጭምር ስለሚፈቅድ በዕቅዱ መሠረት ይበደራል።
የብድሩ ሒደት በድል ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የተበደረውን ብር ሌላ ባንክ ቆልፎ ያስቀምጥና በዓመት አስራ አራት ሚሊዮን ብር ወለድ ይቀበልበታል። አስቡት ቅጠል ሳይበጥስ፣ አንድ ብር ግብር ሳያስገባ አስራ አራት ሚሊዮን ብር ቋቱ ይከታል። ይህ የመጀመሪያውና ቀላሉ የሃብት መሰብሰቢያ መንደርደሪያ ነው። ሲያዩት ሕጋዊ ነው።
የመጀመሪያውን ዕቅድ ካሳኩ በኋላ ወደ ቀጣዩ ይዛወራሉ። መረጃውን ያደረሱት ሕግና አሠራር ጠቅሰው እንደሚሉት አንድ ነጋዴ መቶ ሚሊዮን ብር ካለው እና አስመጪ ከሆነ በዓመት ስድስት መቶ ሺህ ዶላር ከባንክ እንዲወስድ ይፈቀድለታል። በዚሁ አሠራር መሠረት ዶላሩን ለመውሰድ የአስመጪ ፈቃድ ያወጣና ትንሽ ዕቃ ከውጭ በማስመጣት የስድስት መቶሺ ዶላር ፍቃዱን ይረከባል።
በዓመት 600 ሺህ ዶላር የሚያስገኘው ፈቃድ ታዳጊው ባለሃብት እጅ ሲገባ “እልል በቅምጤ” ይዘፈናል። ከዚያም ከባንኩና ከሌላ አነስተኛ አስመጪዎች ጋር በመነጋገር ዶላሩን እያወጣ በጥቁር ገበያ ዋጋ ይሸጥላቸዋል። በዚሁ ሕጋዊ ፈቃድ ሕግን እየጨፈለቀ፣ ለባንኩ ኃላፊዎች ጉቦ በመክፈል ንግዱ ይከናወናል። በዚሁ አግባብ በትንሹ እስከ ሠላሳ ሚሊዮን ብር ያገኝበታል።
አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ሰሞኑን ሲናገር እንደነበረው አስመጪዎች ከባንኮች ዶላር የሚገዙበት ዋጋ ከጥቁር ገበያው ዋጋ በላይ ነው፤ ምክንያቱም ከእያንዳንዱ ዶላር በትንሹ 50 ብር በትርፍ ይታሰብበታል ብሎ ነበር። በመሆኑም ይህ 600 ሺህ የተፈቀደለት “ነጋዴ” ከባንኩ ኃላፊዎች ጋር “በመነጋገር” ለእነርሱ የደንቡን አድርሶ አንዱን ዶላር ውጪ አውጥቶ ሲሸጠው ቢያንስ 50 ብር ያተርፍበታል።
ይህ “ወጠጤ” ባለሃብት “ማን ነው፣ ከየት አመጣው” የሚለው ጉምጉምታ በወጉ ሳይሰማ ይህ ሰው፣ ምንም ሥራ ሳይሠራ ገቢው ሽቅብ ይምዘገዘጋል። በዓመት የሚያገኘው ገቢ ከላይ በተገለጸው አግባብ ከአንድ ባንክ የተበደረውን ብድር ሌላ ባንክ ወስዶ በመቀርቀር ብቻ በወለድ ከሚያገኘው አስራ አራት ሚሊዮን ብር ጋር ተደምሮ አርባ አራት ሚሊዮን ብር ይሆንለታል።
በመቶ ሚሊዮን የገዛው ንብረት እየተከራየ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ያስገባለታል ቢባል እና ይህንን ለኑሮው፤ “ለወጪዎቹ” መሸፈኛ ያውለዋል ብለን ብንወስድና የተወሰነ ትርፍ ብናስብ ባጠቃላይ በዓመት ይህ ወጠጤ ባለሃብት እስከ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ምንም ሳይለፋ ገቢ ማግኘት እንደሚችል የአዲስ አበባ ተባባሪያችን መረጃ ያስረዳል።
በመዋጮ ብር ንብረት ተገዝቶለት ከባንክ ለተበደረው መቶ ሚሊዮን ብር በየዓመቱ ሃያ ሚሊዮን አካባቢ ወለድ ጨምሮ መክፈል እንዳለበት ውል ያስገድደዋል። ይህ ሲቀነስ ሰላሳ ሚሊዮን አካባቢ እጁ ላይ ይቀራል። ሲጀምር ዕቅድና ሂሳብ ተሰልቶ መቶ ሚሊዮን ላበደሩት ዘመዶቹ ከሰላሳ ሚሊዮኑ ቢያንስ ሃያውን ቢከፍላቸው እስከ አምስት ዓመት ውስጥ ዕዳውን ይዘጋል።
ከዚያ በኋላ በያመቱ ቢያንስ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ምንም ሳይሠራ እየሰበሰበ በተራው ቤተሰቡን በተመሳሳይ ያደራጃል። ንብረት እየገዛ ያገላብጣል። ዋጋ እንዳሻቸው ከሚሰቅሉት ማኅበርተኞች ጋር አብሮ ኑሮ ያጦዛል። የጥቁር ገበያውን በተፈለገው ዋጋ ያንረዋል፤ በኮንትሮባንድ ንግድ በቀላሉ ይሰማራል፤ ሌሎችም ለአገር የሚያሰጉ “የንግድ ተግባራትን” ይፈጽማል።
ብር በማገላበጥ ብቻ ግብር የማይከፍልበት፣ ቫት የሌለው ትርፍ እየሰበሰበ የሚኖረው ወጠጤ ባለሃብት፣ ራሱን የመከላከያ ሚዲያም እንደሁኔታው ይከፍታል፤ የዩትዩብ ወሬኛ፣ የፌስቡክ ለፍላፊ፣ የቲክቶክ አርበኛ በያይነቱ ያሰማራል፤ ከዚህ ሁሉ በነጻ ከመጣ ትርፍ ፍርፋሪውን ለሚጮኹለት ቢወረውር ጥቅሙን እያሰበ ነው። ታላላቆቹ ሠራዊት ስለሚያደራጁ እሱ የሳይበር አውሬ ያረባና እንዳሻው የሚዘርፍበት መንገድ እንዳይነካ በደቦ ውግዘት እንዲሰራጭ እያደረገ አገር ያተራምሳል። አገር ስትበላ የኖረችውና የሚዲያው ሁሉ ቅጥ የጠፋበት ጩኸት መልኩ ይህ ነው ።
ይህ የመቶ ሚሊዮን ብር ስሌት ነው። ብሩ ባደገ ቁጥር ገቢው እንዴት እንደሚያድግ ማስላት ዘረፋውን ወገግ አድርጎ ያሳያል። እዚህ ላይ በሩጫ አዘጋጅነት ተመዝገበው ለካኔቴራ ማስመጫ በሚል ዶላር ወስደው ከአደይ አበባ ጨርቃጨርቅ ጥብቆ የሚገዙና የማስታወቂያ ገቢ የሚሰበስቡትንም ሲከፈቱ የሚያሳፍሩ አካላት እንዳሉ ማሰብ እንደሚያሻ፣ ወደፊትም አስፈላጊ ሲሆን ዝርዝር የሚቀርብበት ጉዳይ እንደሆነ የዜናው ባለቤቶች ይገልጻሉ።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ገበያው ላይ የተረጨውን ብር በዲጂታል ግብይትና ብድር ላይ ሸምቀቆ በማበጀት ሲሰበስብ የኖረው መንግሥት አዲሱን የዶላር ፖሊሲ ማውጣቱን ተከትሎ በሚከፍሏቸው ሚዲያዎቻቸው አማካይነት በደቦ ጫጫታ ያስነሱት ጥቅማቸው ስለሚነካ ለመሆኑ ከላይ የሰፈረው ሕገወጥ የሃብት መሰብሰቢያ መንገድ በራሱ አንድ በቂ ማሳያ ነው።
ያለ አንዳች ድካም ይህንን ያህል ንጹህ ትርፍ ሲያግበሰብሱ የኖሩት ወጠጤ ሃብታሞች ባደራጇቸው ሚዲያዎችና የማኅበራዊ ገጾች ሽብር ሲያስነሱ ነገሩ ያልገባቸው የዝርፊያው ሰለባዎች አብረው እንዲጮሁ አድርገዋል። ይህንን ለመተግበር ደግሞ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ … ማንኛውንም ማንነት እስከ ግድያ ድረስ በመፈጸም ሕዝብ እንዲቆጣ፣ ሥርዓት እንዲናጋ፣ … የተገኘውን መንገድ ሁሉ ይጠቀማሉ፤ ጉዳዩ የሚሊዮኖች ጨዋታ መሆኑን ልብ ይሏል።
የገንዘብ ፖሊሲው የወጣ ሰሞን ለዚህ ነው ስለ ኢኮኖሚው ጉዳይ አንዳች እውቀት የሌላቸው ተቀላቢ ሚዲያዎቻቸው ያለ ሃፍረት የማያውቁትን ጉዳይ አንሰተው ትንታኔ ለመስጠት ሲውተረተሩ የታየውና እየታየ ያለው “በሕዝብ ቁስል እንጨት ስደድበት” በሚለው ከከርሳቸው የሚመነጭ ብሒል መነሻ እንደሆነ ጉዳዩን በትነው የሚያውቁት አስረድተዋል።
እነዚህ ዓይነ ደረቆች ውሸቱን እውነት አድርገው ሕዝቡን ያወዛግቡታል። ሆድ እንዲብሰው፣ እንዲቆጣና እነሱ ከርሳቸው እንዳይጎድል አስበው የሚጠምቁትን ሤራ እንዲጋት ያስገድዱታል። ይህን የተረዱ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዋና ደረጃ የተጠሉት በፖለቲከኞች ሳይሆን በወጠጤና ደንዳና የዘረፋ ተዋናይ ሌባ “ሃብታሞች” ነው።
በዚህ መልኩ ዋጋ አንረው፣ ኑሮውን አጉነው፣ ግሽበት እንዲያይል ምክንያት ሆነው የሰበሰቡትን ሃብት ወደ ቋሚ ንብረት በመለወጥ ዘመቻ መረባረባቸው በአገሪቱ የቤትና፣ የመሬት ዋጋ በብርሃን ፍጥነት እንዲተኮስ አደረገ። የታየውን ይህን አስደንጋጭ የዋጋ ንረት በመረጃ አስደግፈው የሚናገሩት የዘርፉ ምሥጢር አዋቂዎች እንደሚሉት፣ አብዛኞቹ የሪል ስቴት አልሚዎች አሁን ላይ በዩቲዩቡ የሚጮሁትና በየቴሌግራሙ ቻናል ማስታወቂያ የሚያወጡት ያላሰቡት ስለገጠማቸውና ሃያ በመቶ ካሽ ከፍሎ የሚገዛ ደንበኛ ባለማግኘታቸው ነው።
ያከማቹትን ንብረት ሕንጻ ጭምር ሸጠው ብድራቸውን ለመክፈል ቢፈልጉም ገዢ ማግኘት አልቻሉም። አሁን ላይ የሕንጻና የቤት ዋጋ እያሽቆለቆለ መሆኑን የሚገልጹት የመረጃው ሰዎች፣ በቅርቡ በአንዳንድ ሪል ስቴቶች አካባቢ ባንኮች የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ እንደሚያወጡ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ከዚህ በፊት ብድር የማሸጋሸጊያ ዕድል ስድስት ጊዜ ነበር፤ በአዲሱ ፖሊሲ ግን ወደ ሁለት ወርዷል፤ በርካታዎቹ ባለሃብቶች ደግሞ ስድስቱንም ቀርጥፈውታል። ከዚህ በኋላ በግድ ብድራቸውን መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
መፍትሔውም ሁለት ነው፤ አንደኛው የብር ዋጋ ይወድቃል ብለው ብራቸውን ወደ ዶላር እየቀየሩ ያስቀመጡትን ወደ ብር እየቀየሩ መጠቀም ነው። ይህ በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የዶላር መጠን በመጨመር የምንዛሬ መጠኑን ዝቅ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ካልሆነም ሁለተኛው “አማራጭ” ንብረታቸውን በሐራጅ እንዲሸጥ መፍቀድ ነው። ከዚህ አኳያ በመጪው ዓመት (2017) በርካታ የሐራጅ ሽያጭ የሚታይበት ዓመት ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።
“ብር የሌለበት ፖለቲካ በስልሳዎቹ ቀረ” የሚሉ ወገኖች የኢትዮጵያን ሁኔታ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር ያገናኙታል። የኬኔዲ ጠላቶች ፖለቲከኞች ብቻ አልነበሩም። ነገር ግን በጠላቶቻቸው ሽፋኑ ፖለቲካ ተደርጎ ቀረበ እንጂ። የማፊያ ሰዎች፣ የዕጽ አስተላላፊዎች፣ አሻጥረኛ ትልልቅ ነጋዴዎች፣ የቬይትናምን ጦርነት አስቆማለሁ በማለታቸው ያኮረፉና የወታደራዊ ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ሰዎች፣ ወዘተ ከፖለቲከኞቹ ውጪ ተጠቃሾች ነበሩ።
ኬኔዲ ወንድማቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አድርገው የማፊያና የውንብድና ሥራዎችን የሚሠሩ ሁሉ ወደ ሕግ አግባብ በማምጣት ኔትዎርካቸውን መበጣጠስ ጀምረው ነበር። የተቀናጀ የወንጀል ተግባራትን ይፈጽሙ የነበሩት የኩባ ማፊያዎች በኬኔዲ አስተዳደር ከፍተኛ ጥቃት እየተሰነዘረባቸውና እየፈራረሱ የነበረ መሆኑ ሌላው ተጠቃሽ ነው። እነዚህ ሁሉ ጥቅማቸው የተነካባቸው የኬኔዲ ጠላቶች ሆኑ፤ እንዳሁኑ የማኅበራዊ ሚዲያ በዚያን ዘመን ቢኖር ምናልባት ኬኔዲ በጥይት ሳይሆን በፌስቡክና በዩትዩብ “ጥይቶች” ይገደሉ ነበር።
በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተከሰተውም ከዚህ በብዙ አይለይም። እጅግ ግፈኛ፣ ዘረኛ፣ ከፋፋይ፣ ወንበዴና መሠሪ በሆነው የትህነግ 30 የሰቆቃ ዓመታት በመንግሥት ተቋማት ሕግ ወጥቶላቸው ረቂቅ ግፎች ሲፈጸሙ እንዳልነበር ትህነግ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ በተለያዩ እንደ አሸን በፈሉ ቡድኖች እጅግ ሰቅጣጭ እና ሕዝብ ስሜት ውስጥ እንዲገባ ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ለመመልከት በቃን።
በወያኔ የግፍ አገዛዝ ዘመን ታይተውና ተሰምተው እንዲሁም ተከስተው የማያውቁ ሰቆቃዎች ወያኔ ከሥልጣን ከለቀቀ በኋላ ልክ ጊዜ ተሞልቶላቸው እንደተቀበሩ ፈንጂዎች ለምን በየቦታው ፈነዳዱ? ለዚህ ጥያቄ አሁን መልስ አንሰጥም፤ ግን የወንበዴው ትህነግ አመራሮች በየጊዜው ሲሉ የነበሩትን ለማስታወስ እንጠቅሳለን፤ “እኛ ከሥልጣን ከለቀቅን አገሪቷ ትፈራርሳለች፤ ትፈነዳለች” እያሉ ነበር ሲያስፈራሩን የነበረው።
ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ መሠረት እኤአ በ2022/2023 በነበረው ዓመት የባንኩ ኢንዱስትሪ ለባለሃብቶች ያበደረው 1.9 ትሪሊዮን ብር ነበር። ከዚህ ብር ውስጥ ሩብ ያህሉን አካባቢ ማለትም 23.5 በመቶውን የተበደሩት 10 (አስር) ግለሰቦች ብቻ ሲሆኑ የወሰዱት የብድር መጠንም 450 ቢሊዮን ብር ነው። በሌላ አነጋገር እያንዳንዳቸው በነፍስወከፍ 45 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወስደዋል ማለት ነው። ገንዘብ ባለበት ጩኸት አለ፤ በየዕለቱ በየማኅበራዊ ሚዲያ የሚበተነው መርዝ ባዶ ፖለቲካ አይደለም፤ እያንዳንዱ የማኅበራዊ ሚዲያ ፖስት፣ ወሬ፣ አሉባልታ፣ የሐሰት ዜና፣ ወዘተ አገር የታለበችበት የደም ገንዘብ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tasserw Assefa says
መሬቱን አሲዞ የተበደረውን ሌላ ባንክ እስቀምጦ ወለድ የሚበላው ሰው፣ ላበደርው ባንክ እሱም በተራው ወለድ ይከፍላል፣ ባንኮች ላስቀማጮች የሚከፍሉት ወለድ ላብደሩት የሚጠይቁት ወለድ ስለሚበልጥ፣ እንዴት ሊያተርፍ ይችላል?
Editor says
Tasserw Assefa
ለአስተያየቱ እናመሰግናለን፤ ያልኸውን ግን ጠቅሰን ጽፈናል፤ ደግመህ አንብበው።