ውሳኔ ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢ ነው፤ የህግ ባለሙያዎች
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ መንግስት “ሸኔ” እና “ህወሓት” ቡድንን በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ለማድረግ መዘጋጀቱ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም ብለዋል፡፡
እንዲህ አይነት ፍረጃ የቀድሞ መንግስትም ሲያደርገው የነበረ ነዉ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህ ዓይነቱ ፍረጃ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆን እዚህ ደረጃ ላይ አንደርስም ነበር፤ ይህም ተግባር ቀድሞ ከነበረው መንግስት የተለየ ነው ብዬ አላስብም ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፡፡
“ሸኔ የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ የለም፣ በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን በተዘዋዋሪ መጥራት ይመስለኛል የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ በዚህ ስም ራሱን የሚጠራ ድርጅት በሌለበት፣ መንግስት ግን በኦሮሚያ አካባቢ በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ኢላማ ያደረገ ስያሜ ይመስለኛል” ብለዋል፡፡
ቀድሞ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ኦነግ ሸኔ ብለው የሚጠሩትን ሸኔ ብቻ ማለቱ ለውጥ አይኖረውም ወይ በሚል ለቀረበላቸዉ ጥያቄ፣ ፕሮፌሰር መረራ ብዙም ለውጥ እንደማይኖረው ጠቅሰው “ድሮም ቢሆን ኦነግ ሸኔ ሲባል በዛ ስም የእኛንም ሆነ የኦነግን አባላት ጨምሮ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ይታሰሩ ነበር፤ አሁንም ቢሆን ያ ነው እየቀጠለ ያለዉ ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአቶ ዳውድ ኢብሳ በሚመራው ኦነግ ቃልአቀባይ የሆኑት አቶ በቴ ኦርጌሳ እኛን ከሸኔ ጋር የሚያገናኘን ነገር የለም ማለታቸዉ ይታወሳል፡፡
ሌላኛው በአቶ አራርሳ ቢቂላ የሚመራውን ኦነግ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው ሸኔ በመንግሥት ሰዎች ፕሮፓጋንዳ የተፈጠረ ነው” ካሉ በኋላ ኦነግ የሚለው ስም ከዚህ ተቀጥሎ እንዳይጠራ እየተነጋገርን ነው፤ ምክንያቱም እኛ ከሸኔ ጋር ግንኙነት የለንም፤ የታጠቀ ሰራዊትም የለንም ብለዋል፡፡
አቶ ቀጀላ እንዳሉት ቀደም ሲል ሸኔ ማለት የስራ አስፈጻሚ አባላት የሚጠሩበት እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ግን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሚል እየተጠራ መሆኑን ነግረዉናል፡፡
በጂጅጋ ዮኒቨርስቲ የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጓዴ ለጣቢያችን እንዳሉት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ቀድሞ ኦነግ ‘ሸኔ’ በመባል የሚጠሩት ቡድኖች ህዝባዊ መሰረት ያላቸው እና ብሔር ተኩር ፖለቲካ ስርአትን የሚከተሉ በመሆናቸው ነገሩን ከባድ አድርገውታል ብለዋል፡፡
በዚህ የተነሳም ሀገር ታምሳለች፤ ንጹሀን ዜጎች ህይታቸው አልፏል ንብረት ውድሟል፤አሁን ላይ ግን እንዲህ መቀጠል አይቻልም ነዉ ያሉት፡፡
የሀገር በር ከፍተን መከላከያን መተን ለውጭ ሀይል ሰጥተናል፤ ስለዚህ እነዚህን ሀይሎች ከዚህ በኋላ መፈረጁ የሚጠቅመው እነኚህን ሀይሎች ለመታገል፤ ለመዋጋት እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ ምክንያት ይሰጣል ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡
ከዚህ ባሻገርም ከእነዚህ ሀይሎች ጋር በገንዘብም ሆነ በኢንፎርሚሽን አሊያም በቁሳቁስ፤ በአመለካከት ቢሆን ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ለማራቅ ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል ሲሉ አክለዋል፡፡
ከእነዚህ ሀይሎች በላይ አሸባሪ የለም የሚሉት የህግ አማካሪው አቶ ሰለሞን፣ ወለጋ እና አጣዬ ላይ ምን እየተፈጠረ እንዳለ ይታወቃል፤አሁንም ቢሆን ከእነዚህ ሀይሎች በላይ የገዛ ሀገሩን እያሸበረ ያለ አካል የለም ነዉ ያሉት፡፡
ወሳኔው ከመዘግየቱ ውጪ ተገቢነት ያለው ነው ብለዋል፡፡
ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የሚናገሩት የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጥፋተኛውን ከህዝብ እየለዩ ለመቅጣት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረዉ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በአገር ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የውጪ አካል ለማስታረቅ ወይም ለመደራደር የሚያደርገውን ጥረት ወንጀል እንደሚያደርገውም ያስረዳሉ።
በተለይም አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ የውጪ መንግሥታት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በስምምነት እንዲቋጭ ሲያቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመዝጋት የታሰበ ይመስላልም ሲሉም አስረድተዋል። (በያይኔአበባ ሻምበል -Ethio FM 107.8)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply