የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ በመዲናዋ ካይሮና በአጎራባች ከተሞች ዛሬ (ሰኞ) ተካሄደ። በካይሮ ዳርቻ በምትገኘው የጊዛ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች የተቃውሞ ትዕይንት ያካሄዱት የፀጥታ ኃይሎችን ማስጠንቀቂያ በመጣስ ነው።
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ካሰሙት መፈክር መካከል “ሲሲ ውጣ” እና “ሕዝብ አገዛዙን መገልበጥ ይፈልጋል” (“Sisi out” and “The people want to overthrow the regime”)የሚሉት የማኅበራዊ ሚዲያውን አጨናንቀውት ውለዋል።
ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ከመንግሥት ተቃውሞ በላይ አንድ የፖሊስ መኪናን ያቃጠሉ ሲሆን በፖሊስ ላይ ድንጋይ የወረወሩበት ድርጊትን የሚያሳይ ቪዲዮም በማህበራዊ ሚዲያ ተለቋል። አልጀዚራ በዘገባው እንዳመለከተው የአሁኑ ተቃውሞ ከመቀስቀሱ በፊትም የፀጥታ ኃይሎች በርካታ ተቃዋሚ ግብፃዊያንን ይዘው ማሰራቸው ተነግሯል።
የግብፅ መንግሥት በታላላቅ ከተሞች የፀጥታ ሀይሎችን እያሰማራ መሆኑ ተሰምቷል። በአገሪቱ የፀጥታ ሀይሎቹ በታላላቅ ከተሞች መሰማራት የጀመሩት የፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል ሲሲን አስተዳደር የሚያወግዝ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት እንደሆነ ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል።
ሰልፉ የተጠራው መንግሥት ያደርሰዋል ያለው የአስተዳደር ብልሹነት በማጋለጥ የሚታወቅ የቀድሞ የመከላከያ ኮንትራክተር መሐመድ ዓሊ በተባለ ግለሰብ በስደት በውጭ አገር በሚኖር እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል። ባለፈው ዓመትም የግብፅ መንግስት በሙስና ውስጥ ተዘፍቆ ሀገሪቱን ለከፋ እግር እንደዳረጋት የሚያሳይ መረጃን መሐመድ ይፋ አድርጎ ነበር።
በወቅቱ የሀገሪቱ መንግሥት ተቃውሞውን ለማብረድ ቢያንስ 4ሺ ሰዎችን ማሰሩን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል። መሐመድ ዓሊ በተለይም በከፍተኛ ሹሞች ይፈፀማል የሚባለውን ምዝበራ በማጋለጥ ታዋቂነትን ያፈራ እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል።
ዛሬ ለተቃውሞ ወደ አደባባይ የወጡ ግብጻዊያን የፕሬዝዳንት አብድል ፈታህ አልሲሲ መኖሪያ ቤትን ማቃጠላቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ጨምሮ ዘግቧል። በግብፅ ስዊዝ፣ ካፈር ኤል ዳዋር፣ በናይል ዴልታ፣ ካይሮ፣ አሌክሳንድሪያ እና አስዋን ከተማ ውስጥ አልሲሲ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ሰልፍ ተነስቷል።
የግብፅ ፀጥታ ኃይሎች በሰልፈኞች ላይ ያደረሱትን ጥቃት ተከትሎም አስዋን ውስጥ የሚገኘው የፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት በሰልፈኞች ተቃጥሏል ነው የተባለው። ፀረ-አል ሲሲ ተቃዋሚዎቹም በፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩና የፖሊስ ሀይሉም ሲያፈገፍግ የሚያሳዩ ምስሎችም በማህበራዊ ትሥሥር ገፆች ላይ እየተዘዋወረ አንደሚገኝም ዘገባው ጠቅሷል።
በዋና ከተማዋ ካይሮም ካፌዎችን ለአድማ በከፊል ዝግ መሆናቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። የተቃውሞ ሰልፉም መሀመድ አሊ የተባለ አክቲቪስት በሀገሪቱ ያለውን ፍትህ መጓደል ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲያቃወምና ሀገሩን እንዲታደግ በጠራው ሰልፍ መሰረት የተካሄደ መሆኑንም ዘገባው ጠቅሷል። መንግሥትን በመቃወም ሰልፍ እየተካሄደባቸው በሚገኙ አካባቢዎች ከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር እንዳለ አልጀዚራ ዘግቧል። በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ ከስልጣን ይውረዱ የሚሉ መፈክሮችን የሚያሰሙ እና ባነሮችን የያዙ ተቃዋሚዎች አሳይተዋል።
የቀድሞ የመከላከያ ኮንትራክተር መሀመድ አሊ ባለፈው ዓመት የነበረውን ተቃውሞ ለማስታወስ በትናትናው ዕለት ተመሳሳይ ተቃውሞ እንዲካሄድ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው ከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር እየተደረገ የሚገኘው።
በተመሳሳይ የጸጥታ ኃይሎቹ ከተቃውሞ ጋር ተያይዞ ታዋቂ ፖለቲከኞች እና አክትቪስቶችን ማሰራቸው ተነግሯል። እንዲሁም ተቃውሞ በበረታባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የካፌ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲዘጉ መደረጉም ታውቋል። ባለፈው ዓመት ባልተለመደ ሁኔታ በሺህዎች የሚቆጠሩ ግብፃዊያን ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ከስልጣን እንዲለቁ ለመጠየቀ ተቃውሞ ሰልፍ ባካሄዱበት ጊዜ መንግሥት ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ከ2 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ማሰሩ መረጃዎች አመልክተዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply