• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የትግራይ አበጋዞች ፍልሚያ

September 11, 2024 03:32 pm by Editor 1 Comment

የሕወሓትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመሩትን ንትርካቸውን በመቀጠል፣ አሁን ደግሞ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ መወዛገብ ጀመሩ። የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ፕሪቶሪያ የተላከው ልዑክ ያልተወያዩበትን መስማማቱን ሲገልጹ፣ ልዑኩን የመሩት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ልዑኩ ወደ ፕሪቶሪያ የሄደው ስለመንግሥትነት ጉዳዮች ለመወያየት ሳይሆን ተኩስ ለማስቆም መሆኑንና በዚያው መሠረት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አስታውቀዋል።

ሕወሓት ስምምነቱን እንዲፈርሙ የመረጣቸው ልዑካን ስህተት መፈጸማቸው የተናገሩት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ በዚህም ምክንያት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት መጀመር የነበረበት ፖለቲካዊ ውይይት እስካሁን አለመጀመሩንና የክልሉም ሉዓላዊነት አለመረጋገጡን አስታውቀዋል።

አቶ ጌታቸው በበኩላቸው ሰሞኑን ለርዕዮት ሚዲያ እንደገለጹት፣ በወቅቱ ስምምነቱን እንዲፈርም የተላከው ልዑክ በስምምነቱ ዙሪያ ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል፡ ይህንንም ለአሜሪካ መንግሥት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለአፍሪካ ኅብረት በደብዳቤ መገለጹን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን፣ “ስምምነቱን ለመፈራረም ወደ ፕሪቶሪያ የሄድነው ስለመንግሥትነት ጉዳዮች ለመወያየት ሳይሆን፣ ተኩስ ለማስቆም ነበር።  ይህንንም የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በደንብ ያውቃል፤” ብለዋል።

ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ የመፍታት ጉዳይ ከጦርነቱ በኋላ ብቻ ሳይሆን ከጦርነቱ በፊትም የነበረ የድርጅቱ አቋም መሆኑን ገልጸዋል።  

የሰላም ጉዳይ በዋነኝነት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ገልጸው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መቋጨቱን አስታውሰዋል። ይሁንና በወቅቱ ስምምነቱን እንዲፈርም የተላከው ልዑካን ቡድን ከስምምነት ሊደርስባቸው የማይገቡ ጉዳዮች ላይ በመስማማቱ ትልቅ ስህተት መፈጸሙን ተናግረዋል። ልዑኩ ተኩስ እንዲቆም የመደራደር ኃላፊነት ቢሰጠውም የውሉን አቅጣጫ የመቀየር መብት አልተሰጠውም ሲሉ አስምረዋል።

የውሉን አቅጣጫ ከቀየሩት ጉዳዮች መካከል ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፌደራል መንግሥት ሥር እንዲተዳደር የወጣው ደንብ ነው ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ “ይህ በፍፁም ያልተስማማንበት ብቻ ሳይሆን ያልተወያየንበትም ጭምር ነው፤” ብለዋል።  

“የፌደራል መንግሥት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት አሠራር ቢኖርም፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዚህ ደረጃ ለፌደራሉ መንግሥት ተጠሪ እንዲሆን የተስማሙበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፣ አፈጻጸም ላይም ችግር እየፈጠረ ነው፤” ሲሉ አብራርተዋል።

አፈጻጸሙ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ቅርርብ እንዲፈጠርና ከዚህ ቀደም የነበሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ በማለም የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴም ስምምነቱ ላይ የሌሉ ውሳኔዎችን እያሳለፈ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

በጦርነቱ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ምርኮኛ ወታደሮችም በክልሉ የፀጥታ ኃይል ሥር ምርመራ ሲካሄድባቸው መቆየቱን የገለጹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ሰፊ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ 400 ገደማ የሚሆኑት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተወንጅለው በፀጥታ ኃይሉ ሥር እንዲቆዩ ቢደረግም፣ ያለ ምንም ተጠያቂነት እንዲለቀቁ መደረጉን ተናግረዋል። ሒደቱ ስህተት መሆኑንና በምዕራብ ትግራይ ግፍ የፈጸሙ አካላትም በስምምነቱ መሠረት እስካሁን ተጠያቂ አለመደረጋቸውን ነው ያከሉት። ጉዳዩን በሚመለከት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል የተሰጠው ምላሽ የወታደሮቹ መዝገብ ወደ ፌዴራሉ መንግሥት ተልኮ በፌዴራል ደረጃ ይታያል የሚል እንደሆነ ጠቁመው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተጠያቂነትን ጉዳይ ችላ እንዳለው ማሳያ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ሕወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ ዓላማ እንዳለው በሌላኛው ቡድን በኩል በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ “አሥር ጊዜ የውሉን ጉዳይ የሚያነሱት ውጤት ማምጣት ስላቃታቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፤” ሲሉም ተደምጠዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ እየተደረገ ያለው እልህን ብቻ ማዕከል ያደረገ አካሄድ ተቋማዊ አሠራርን የሚያፈርስ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፣ “ከዚህም ባለፈ አቅማችን እንዲዳከም እያደረገን ነው፤” ብለዋል። ከ14ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ውዝግብ አስታውሰው፣ ድርጅታዊ ጉባዔ ማካሄድ ከጦርነት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለና ነገር ግን ጦርነት ሊቀሰቀስ ነው በሚል ሐሰተኛ ዘመቻ ሕዝቡ እንዲሸበር እየተደረገ ነው ብለዋል። 

“እኛ የኤርትራ መንግሥትን ጨምሮ ከየትኛውም አካል ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለንም። እልህን ብቻ ማዕከል ያደረገ አካሄድ ተቋማዊ አሠራርን ከማፍረስ ባለፈ አቅማችንንም እያዳከመ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፤” ብለዋል።

“ተነጋግረህ ካልተስማማህ በሌላ ጊዜ እንገናኝ ብለን ትለያያለህ። ይህ ደግሞ ከሌላ ዙር ውጊያ በኋላ የሚሆን ነው። ስለዚህ ተኩሱን የግድ ማስቆም ነበረብን። የፌዴራል መንግሥት ተወካዮች ብዙ ነገሮችን ሊጠይቁን ይችላሉ። ነገር ግን ደግሞ በቋሚነት ነው ተኩስ ማስቆም ያለብን በማለት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አልተወያየንም፤” ሲሉ የነበረውን ሁነት አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የፕሪቶሪያ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት የፌዴራል መንግሥት በጦርነቱ የበላይነት እንዳለው ያምን በነበረበትና መቀሌን ከብቤያለሁ እያለ በነበረበት ወቅት፣ እንዲሁም ውጊያ ባልተቋረጠበት ሁኔታ ለድርድር መቀመጣቸው እጅግ በውስብስብ ሁኔታዎች የታጀበ እንደነበር የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የፌደራል መንግሥት ሕወሓት እጅ እንዲሰጥ ለማድረግ ለድርድር መቅረቡን አስታውሰዋል። ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ “እጅ ስጡ፣ እጅ መስጠት የዓለም መጨረሻ አይደለም” ያሉ ቢሆንም፣ ብዙ ውጣ ውረዶች መታለፍ እንደነበረባቸውና ነገር ግን ተኩስ ለማስቆም መደረግ ወይም መታለፍ ያለባቸው ነገሮች በሙሉ መደረጋቸውን አብራርተዋል። ሁኔታው ካለፈ በኋላ የሚብጠለጠለውን ያህል ቀላል እንዳልነበር ጠቅሰው፣ ለልዑኩ የተሰጠውን ተኩስ የማስቆም ኃላፊነት ብቻ መወጣቱን አክለዋል።

“ተኩስ ለማስቆም ትጥቅ አውርዱ ከተባልን እሺ ማለት እንጂ አይ ትጥቅ አላረግፍም ብለህ ተኩስ ልታስቆም አትችልም። እያንዳንዱ ነገር ሒደት አለው፣ የሠራዊታችንን አቅምም መዝነን የግድ ተኩስ ማስቆም ነበረብን፤” ብለዋል። 

ክፍፍሉ ከወራት በፊት መሰማት የጀመረው ሕወሓት 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ ተከትሎ ለሁለት የመከፈሉ ጉዳይ አደባባይ ከወጣ ሰነባብቷል። ድርጅቱ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከጉባዔው ራሳቸውን ያገለሉትን አባላቱን ሲያግድ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በበኩሉ ሹም ሽሮችን ማካሄዱን ቀጥሏል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፀጥታ ዘርፍ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የተለያዩ መዋቅሮች የሚያደርጋቸውን የምደባ ለውጦች ማቆም አለበት በማለት ከሁለት ቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስበዋል። ምደባዎችንና ሽግሽጎችን ማቆም የሚያስፈልገው፣ በክልሉ ያለው ፖለቲካዊ ችግር እየተባባሰ በመሄዱ እንደሆነም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በክልሉ የተጀመሩ ከላይኛው እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር የሚደረጉ ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በመናገር፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፀጥታ ዘርፍ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ሌተና ጄነራል ታደሰ ወረደ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የተለያዩ መዋቅሮች የሚያደርጋቸውን የምደባ ለውጦች ማቆም አለበት፤” በማለት ለሰጡት ማሳሰቢያ ምላሽ ሰጥው፣ ይህ ማለት ግን ሁሉንም አመራር በአዲስ መተካት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ባለፉት ሳምንታት ሲካሄዱ የቆዩት ሕዝባዊ ስብሰባዎችም የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ መልኩ እንደሚቀጥሉ ጠቁመው በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ግን የፀጥታ ችግሮች እንደነበሩ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

ሌተና ጄኔራል ታደሰ አክለውም ፖለቲካዊ ችግሩ በዚህ ከቀጠለ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አካባቢ ካሉ የትግራይ ተወላጆች እጅ ወጥቶ ለሦስተኛ ወገን መጠቀሚያና መግቢያ ቀዳዳ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። በክልሉ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሠልፍ ማድረግ ጉዳት አለው ያሉት ሌተና ጀኔራል ታደሰ፣ ሠልፍ ማድረግ ታግዶ እንደሚቆይም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ክልከላ ባለበት እንዲቆይ የተወሰነው አምባገነናዊ አካሄድን ለመከተል ሳይሆን፣ እየተባባሱ የመጡትን ችግሮች ለማርገብ እንደሆነም አክለዋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በተለይም ከ14ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በኋላ ከሕወሓት ጋር የገባበትን ውዝግብ ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ ወረዳዎች ያሉ አመራሮችን ምደባ ለውጥ ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ጄኔራሉ በበኩላቸው፣ “በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል የሚደረጉት ሹም ሽሮች ሕገ መንግሥቱን የሚጥሱና ያለውንም ክፍፍል የሚያባብሱ ናቸው። በሕዝቡ ላይ ሥጋት እየፈጠሩ ነው፤” ብለዋል።

ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ በርካታ ስብሰባዎች እየተካሄዱ እንደሆነ የገለጹት የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው፣ ማንኛውም ስብሰባ ወደ ፀጥታ ችግር የሚያመራ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል። በክልሉ የተፈጠረው ችግር ፖለቲካዊ እስከሆነ ድረስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ነው የሚሻው ብለው፣ ስም በማጥፋት ዘመቻም ሆነ በሌላ አላስፈላጊ መንገድ የሚፈታ እንዳልሆነ በመገንዘብ ከሕገወጥ አካሄዶች መቆጠብ እንደሚገባ አስጠንቅቀዋል።  

‹ለሁለት የተከፈሉትን የሕወሓት አመራሮች በተቻለ መጠን ለማስማማት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸው፣ ጥረቱ ካልተሳካ ግን ልዩነታቸውን አክብረው በሕጉ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል ብለዋል። ከዚህ ውጪ ያለው አካሄድ ግን ቀይ መስመርን ማለፍ ስለሚሆን መገታት አለበት ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ባሻገር በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ከወራት በፊት የተጀመረውን ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ተግባር በሚመለከት፣ “የትግራይና የአማራ ሕዝቦችን ዘላቂ ግንኙነት የሚጎዳ ማንኛውም እንቅስቃሴ መቆም አለበት፤” በማለት ያስገነዘቡት ሌተና ጄኔራል ታደሰ፣ መሰል እንቅስቃሴ ትርጉም አልባ በመሆኑ ካለፈው መማር እንደሚገባ አሳስበዋል። “በጠመንጃ የሚወሰድ መሬትም ሆነ የሚቀየር ድንበር የለም። ስለሆነም በአማራ ክልል በኩል ያሉ ታጣቂዎች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፤” ብለዋል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሒደት ከወራት በፊት የተጀመረ ቢሆንም፣ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ እንዲያስጠብቅ ኃላፊነት የተሰጠው የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን ሕወሓትና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል። የአማራ ክልል በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። (በልዋም አታክልቲ፤ ሪፖርተር)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Politics, Slider Tagged With: debretsion, getachew reda, operation dismantle tplf, tadesse worede

Reader Interactions

Comments

  1. Tesfa says

    September 14, 2024 08:07 am at 8:07 am

    እውቁ የግጥምና የመጽሃፍት ደራሲ Charles Bukowski በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር። “Find what you love and let it kill you.” ወያኔ ያለ ግርግርና ጠበንጃ አንድ ቀን ማደር አይችልም። አሁን ለሁለት ተሰንጥቆ አውራ ጣት ከአመልካች እጣት ይበልጣል የሚለው ወያኔ ፍትህ በምድሪቱ ቢኖር መኖር የማይኖርበት ድርጅት ነው። ግን በዘፈቀደ በምትመራ ሃገር ላይ አንጋች ብቻ የነገሰበት በመሆኑ እንሆ ዛሬም በትግራይ ህዝብ ስም የራሳቸውን መኖር ለማረጋገጥ ይነግዳሉ። ያለፈው መከራና እልቂት አልበቃ ብሎ ዛሬም በፈጸሙትና ባስፈጸሙት ሰቆቃ ሳያፍሩ ሚዲያ ፊት እየወጡ ፍሬ የለሽ የማደናገሪያ ሃሳብ ሲዘሩ ማየት ወቸው ጉድ ስልጣን ከአናት ላይ ወቶ ቤት ሲሰራ ሰውን በቁም ማሳበድን እያየን ነው። መግለጫና ማብራሪያ እያሉ በየወቅቱ የሚይስተላልፉት አንደናጋሪና አደንቋሪ ቱልቱላ እንኳን የትግራይን ህዝብ ሃበሳ ሊቀርፍ ቀርቶ ዛሬ ላይ እነርሱን ራሳቸውን እያናከሳቸው ይገኛል። የእነርሱ መባላት ማለፊያ ነው። ግን በእነርሱ ጦስ አፈር ገፊውና ደሃው የትግራይ ህዝብ የቁም ስቅሉን ማየቱ እጅግ ያንገፈግፋል። ለሃገሬ ለወገኔ ምን ሰራሁ፤ ከአምናና ታቻምናው ዘንድሮ ምን ነገር ለህዝቡ ሰራን ቢባል ኑሮ አይዞአችሁ ከጎናችሁ ነን በርቱ በጎደለ እንመካከራለን ያስብል ነበር። ግን እኔ ነኝ አውራው አንተ አይደለህም በሚል የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ወያኔ ስለ ትግራይ ህዝብ ሰላምና ጤንነት በጎ ነገር ያስባል ማለት ውስልትና ነው።
    የሚያሳዝነው በዓለም ላይ በዚህም በዚያም የተበተነው ሃበሻ ከእውነት ጋር መጣላቱ ነው። አካፋን አካፋ እንደማለት ግፍ አፍጦ እያያቸው ለወያኔ በዚህም በዚያም ድጋፍ የሚያደርጉ የፓለቲካ ቁማርተኞች የህዝባችን መከራ አባሱት እንጂ እንዲጠገን አልረድትም። ዋሽንግተን ላይ ተቀምጦ “ኤርትራ ለኤርትራዊያን ብቻ” ይላል ደንቆሮው ሃበሻ። ያልገባው ነገር ግን ኤርትራዊያን ምድሪቱን እየሸሹ ከብዙ መከራና ፍዳ በህዋላ መጠለያ እንዳገኙ ነው። አንድ የብራዚል ሰው ጋር ስንጫወት እንዲህ አለኝ። ወደ 33 የሚጠጉት የላቲን አሜሪካ ሃገሮች የሁለት ነገሮች ውጤት ናቸው አለኝ። ምንና ምን ስለው የቅኝ ግዛትና የስደተኞች ሲለኝ ግራ ገባኝ። ለምሳሌ አለ ብራዚል ውስጥ በስደት የመጡ ጀርመኖች (የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ትራፊዎች) ብራዚል ውስጥ ላለው እድገት ከፍተኛ አስተዋጾ አላቸው። ይህ በጀርመኖች ብቻ ሳይሆን በጣሊያኖች፤ በጃፓኖች ለምሳሌ Alberto Kenya Fujimori Inomoto ፔሩን ለ 10 ዓመታት የገዛው ከጃፓናዊ ቤተሰብ የተወለደ ነው በማለት የቅኝ ገዥዎች ውጤት የሆነውን የስፓንሽ ቋንቋና ስለ ፓርቹጋል አጫውተኝና እናንተ መንቃት ያለባችሁ ስብጥር፤ ዝንቅ ህዝብ ሲኖር የፈጠራ ጉልበት እንደሚጠነክር ነው በማለት ሃሳቡን አጋራኝ። ግን የእኛው በባዶ ቤት ተቀምጦ የሚንቀባረረው ለምን ይሆን? የክልልና የቋንቋ ፓለቲካስ ለማን ይጠቅማል? ግን ዘመናቸውን ሁሉ የበታችነት ለሚሰማቸው እውነት ራሷ ሥጋ ለብሳ ብትከራከርም አሜን አይሉም። አይናቸው ታውሯል። ጀሮአቸው ደንቁሮአል። የቀረው ምላሳቸው ብቻ በመሆኑ በመሸ ጊዜ ላይ ቆመው ዛሬም ተንኮል ይሽርባሉ። ለዚህ ነው ያው በቆፈሩት ጉድጓድ እነርሱም መግባታቸውን ከበፊቱ ይልቅ ቅርብ የሚያደርገው። ስለሆነም ወያኔዎችና የዘር ሰካራም የሃገራችን ፓለቲከኞች የመረጡት ነገር ይገድላቸዋልና ጠብቆ ማየት ነው።

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule