* ሚዲያው አስቀድሞ ዝግጅት አድርጎበታል
ቀሲስ በላይን ግንባር አድርጎ አፍሪካ ኅብረትን ለመዝረፍ የተወጠነው ሤራ መክሸፉ አርብ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለሳልሶ ይፋ አድርጎታል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃላ አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ “ጉዳዩ በሕግ ያለ ነው። ዝርዝር ልንናገር አንችልም። የተሞከረው ጥቃት ግን ከሽፏል። ጉዳዩ ወደ ሌላ ደረጃ ሳያልፍ ወይም ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር ተችሏል” ማለታቸው ጉዳዩ ሤራ መሆኑን ያመላክታል።
“ከኅብረቱ ጋር ባደረግነው ቀጥተኛ ውይይት ይህ አይነት እሳቤ በተቋሙ ውስጥ እንደሌለ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል” ሲሉ በመግለጫቸው ያመለከቱት አቶ ነቢዩ ጉዳዩ ሕግ የያዘው በመሆኑ ዝርዝር ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል። የጎልጉል የአዲስ አበባ ተባባሪ ዜናው ከተሰማበትና ሪፖርተር ጋዜጣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ሁለት የተለያዩ ዜናዎች ካሰራጨ በኋላ የተለያዩ አካላትንና ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎችን ለማነጋገር ሞክሯል።
ተባባሪያችን መረጃዉን ጠቅሶ እንዳለው ከሆነ አጀንዳውና ሤራው በቀሲስ በላይ ተግባር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ተዓማኒነት የሌለው አድርጎ በማሳየት “አፍሪካ ኅብረት የውጭ ምንዛሬ አካውንቱን ወደ ሌላ አገር ሊያዘዋውር ነው” የሚለውን ዜና ማራገብ ነበር። እንደመረጃው ከሆነ ለጊዜው ስማቸው የማይጠቀሱ ስድስት ሚዲያ አውታሮች ጉዳዩን በፍጥነት እንዲያራቡ የሤራው አቀናባሪዎች አስቀድመው ዝግጅት አድርገዋል።
“ነጻ ፕሬስን” ተገን አድርገው የሚሠሩትና በዚሁ ጥላ ሥር የሚርመሰመሱትን አካላት ለዚሁ ሤራ ያዘጋጀው ይህ “ተራና ሊሳካ የማይችል” የተባለ የዝርፊያ ሙከራ ቀድሞ በሚፈለገው መልኩ በእንግሊዝኛ ያሰራጨው ሪፖርተር የሤራው አካል ይሁን አይሁን መረጃውን በዝርዝር የሰጡት ክፍሎች አላስታወቁም። ይሁን እንጂ ሪፖርተር በአማርኛ ዘገባ ያልጻፈውን “ዋና ተፈላጊ አስኳል ጉዳይ” በእንግሊዝኛ ማቅረቡ ብዙ መልዕክቶች እንዳሉት በርካታ አስተያየት ሰጪዎች በቁጣና በትችት ገልጸዋል።
ዜናውን ከሪፖርተር እንግሊዘኛ ወስደው ያራቡትን ጨምሮ ለዚሁ ተግባር የተዘጋጁት ሌሎች ሽፋናቸው ሚዲያ የሆኑ ዜናውን በሚፈለገው መጠን ያላሰራጩት ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ኃላፊዎች ዘንድ ወዲያውኑ ቅሬታ በመነሳቱ እንደሆነ የጎልጉል የአዲስ አበባ ተባባሪ ሰምቷል።
ባለፉት ሦስት ዐሥርተ ዓመታት የትህነግ ኃይሎች አፍሪካ ኅብረት ውስጥ በብዛት መሰግሰጋቸውን ያወሱት የዜናው ባለቤቶች ይህ ሤራ በነዚሁ አካላት የተገመደና ሆን ብለው “የተከበሩ” የሚባሉ የቤተ ክህነት ሰው በመጠቀም ሤራውን ክብደት እንዲኖረው ማድረጋቸውን ያክላሉ። የሤራውን አካሄድ በውል የተረዱት ወገኖች እንደሚሉት ስማቸው ሳይጠቅስ ለሪፖርተር መረጃ እንዲሰጠው ያደረጉት እነዚሁ ወገኖች ናቸው ይላሉ። ሪፖርተር በእንግሊዝኛ ባወጣው ዘገባ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአፍሪካ ኅብረት ምንጭ ኅብረቱ የባንክ አካውንቱን ወደ ሌላ አገር በማድረግ ሃሳብ ላይ ወስኗል ብለው እንደነገሩት ዘግቦ ነበር።
ዜናው ይፋ ከሆነ ጀምሮ ቀሲስ በላይን አፍሪካ ኅብረት ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይዘዋቸው የሄዱት ሰዎች ማንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ዘገባዎች አለመሰማታቸው፣ ፖሊስ በፍርድ ቤት አፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ያሉትን የካሜራ መረጃዎች ከመጠየቁ ጋር አንድ ላይ ተዳምሮ “ከጀርባ ያሉት እነማን ናቸው?” የሚለውን ጉዳይ እንደሚያጎላው ጉዳዩን በአንክሮ የሚከታተሉ ይገልጻሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ “ጉዳዩ በሕግ ተይዟል” ሲሉ ለጊዜው ዝምታ ቢመርጡም፣ ጎልጉል ባለው መረጃ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ሙሉ መረጃውን አግኝተውታል። ቀድሞውንም “ኅብረቱ የውጭ ምንዛሬ አካውንቱን ወደ ሌላ አገር ሊያዘዋውር ነው” ለሚለው የሤራ ዜና ሲባል እንጂ በተግባር ዝርፊያ ሊከናውን እንደማይችል ተረድተው ሤራውን የከወኑትን አካላት ቀሲስ በላይ ፍርድ ቤት በቀረቡ ዕለት ለምን ለችሎቱ ይፋ አላደረጉም በሚል ለሚነሳው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ይህ መረጃ አድሮ ይፋ እንደሚሆን የዜናው ባለቤቶች አክለው አስታውቀዋል።
ሪፖርተር በዚህ ርቀት ዜናውን የሠራበት፤ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ያወጣው ዘገባ የተለያየ የሆነበት፤ ከዚህ በፊትም እንደዚሁ ዓይነት በሤራ የተገመዱ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ ሲያወጣ መቆየቱ፤ ወዘተ ትያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች ሆነዋል። ለአብነት ከሚጠቀሱት መካከል አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የተመሠረተ ቀን እጅግ በርካታ ጉዳዮች በአፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎም ሆነ በዋነው ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን የተነገሩ ቢሆንም ሪፖርተር ግን የዜናው ዋና ሃሳብ ያልሆነውን አጀንዳ በማንሳት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ መንግሥት ጣልቃ ከገባብን ሥልጣኔን እለቃለሁ አሉ በሚል ርዕስ ከጥሩ ገላጭ ፎቶ ጋር ያወጣው የተንሻፈፈ ዘገባ አንዱ ተጠቃሽ ነው።
ከሁሉ በላይ የሚዲያው ኃላፊ በቅርቡ ከተመሠረተው የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ጋር ያለው ቁርኝት ይሆን ሪፖርተርን ለዚህ ዓይነት ሙያዊ ሥነምግባር የጎደለው ዘገባዎች እንዲያወጣ ያደረገው የሚለው ሌላ የሚነሳ ጥያቄ ሆኗል። ይህ ዓይነት የጥቅም ግጭት (conflict of interest) ካለ በገለልተኛ ወገን ጉዳዮች የሚታዩበት አግባብ ሊኖር ይገባል የሚል የመከራከሪያ ሃሳብ የሚያቀርቡ መኖራቸውን መረጃ አቀባያችን ጠቁሟል።
የጀርመን ድምጽ የተንሻፈፈውን የሪፖርተር ዘገባ በተመለከተ የዘገበውን ከዚህ በታች አቅርበናል፤
የአፍሪቃ ሕብረት “የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ወደ ሌላ ሀገር ሊያዘዋውር ነው” በሚል የተሰራጨው መረጃ “የተሳሳተ” ነው ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ (አርብ) አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የአፍሪቃ ሕብረት በግቢው ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳቡ ላይ በሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ለማዘዋወር የተደረገበትን ሙከራ ተከትሎ መሰል መረጃዎች ቢወጡም “ከሕብረቱ ጋር ባደረግነው ቀጥተኛ ውይይት ይህ አይነት እሳቤ በተቋሙ ውስጥ እንደሌለ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕብረቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት “በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለው የድርጅቱ ሒሳብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተጠበቀ እንደሆነ” የሕብረቱ ኃላፊዎች መናገራቸውንም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ዐዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ተቀማጭ በሆነው አሕጉራዊው ድርጅት የአፍሪቃ ሕብረት ዋና ግቢ ውስጥ በሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በመቅረብ፣ “ከሕብረቱ የክፍያ ሰነድ ጋር ተመሳስለው የተዘጋጁ” በተባሉ ሀሰተኛ ሰነዶች በመጠቀም ከሕብረቱ የባንክ ሒሳብ ወደ ሌላ ሒሳብ ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማዘዋወር ሲሞክሩ መያዛቸውን ተከትሎ፤ በሀገር ውስጥ ተነባቢ የሆነው The Report የእንግሊዝኛው ጋዜጣ፤ በስም ያልተጠቀሱ የአፍሪቃ ሕብረት የገንዘብ ባለሙያዎችን ዋቢ አድርጎ ሕብረቱ የውጭ ምንዛሪ ሒሳቡን ከኢትዮጵያ ሊያዘዋውር መሆኑን እንደገለፁለት ዘግቧል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከሕብረቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ መወያየታቸውን የገለፁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢዩ ተድላ መረጃው “ትክክለኛ አይደለም” ብለዋል። የተፈጠረው ክስተት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያስከተለው ተጽዕኖ ስለመኖር አለመኖሩ የጠየቅናቸው ቃል ዐቀባዩ “ጉዳዩ በሕግ ያለ ነው። ዝርዝር ልንናገር አንችልም። የተሞከረው ጥቃት ግን ከሽፏል። ጉዳዩ ወደ ሌላ ደረጃ ሳያልፍ ወይም ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር ተችሏል” በማለት መልሰዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply