“አማራውም ሆነ አፋሩ ምንም ዓይነት የኅልውና አደጋ አላጋጠመውም፤ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም በትህነግ የደረሰበት ችግር የለም፤ አማራውም ሆነ አፋሩ በትህነግ በጅምላ አልተጨፈጨፈም፤ ማይካድራ፣ ጭና፣ አጋምሳ፣ ጋሊኮማ፣ ወዘተ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተፈጸመ ጭፍጨፋ ነው እንጂ በዲሲፒሊን የታነጸው ትህነግ እንዲህ ዓይነት ግፍ አይፈጽምም፣ በአጠቃላይ “ሒሳብ እናወራርድብሃለን” የተባለው የአማራው ሕዝብ በትህነግ ምንም ግፍ አልደረሰበትም፤ ወልቃይት የምዕራብ ትግራይ አካል ነው፣ ራያም የትግራይ ነው፤ ወዘተ። ስለዚህ ትህነግ ሳትሞት በሽግግር መንግሥት ምሥረታ የአፍ ለአፍ ትንፋሽ እንስጣትና እንታደጋት”።
ልደቱ አያሌው
ትህነግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ሲገባ ለመታደግ ከሚረባረቡት “ቅምጥ” ቡድኖች መካከል በቀዳሚነት የሚሰለፈው ልደቱ አያሌው ነው። ከእርሱ ሌላ የቀድሞ የትህነግ አመራሮች፣ ተዋርደው ወይም አኩርፈው ተባርረው የወጡ እንደ ስዬ አብርሃ፣ ጻድቃን ገ/ትንሳይ፣ አበበ ተ/ሃይማኖት ወዘተ ዓይነቶች ትህነግ በነፍስ ግቢና ውጪ ውስጥ ሲሆን ለመታደግ ከጎሬያቸው ብቅ ይላሉ። የእነዚህኞቹ “ዘር ከልጓም፣ የዘሬ ያንዘርዝረኝ” እንደሚባለው ባይገርምም “የወሎ ቡግና ተወላጅ ነኝ” የሚለው ልደቱ አያሌው ለትህነግ ያለው ታማኝነት ግን የዲኤንኤ ምርመራ የሚያስፈልገው ይመስላል።
ፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስ መዐሕድ ብለው የአማራ ሕዝብ ከተጋረደበት የኅልውና አደጋ ለመታደግ ፓርቲ በመሠረቱና ትህነግን ሰንገው በያዙበት ጊዜ በወጣት ክንፍ ውስጥ በመግባት ለፕሮፌሰር ዐሥራት መታሠርም ሆነ ለመዐሕድ መክሸፍ ትልቁን ድርሻ የተጫወተው ልደቱ እንደሆነ የፓርቲው አመራሮች ዜጎች ትን እስኪለን በመረጃና በማስረጃ ነግረውናል።
ቀጣዩ የልደቱ ፕሮጀክት ከትህነግ ደኅንነትና ከበረከት ስምዖን ጋር በመመሳጠር ተቃዋሚ መሰል የራሱን ፓርቲ መመሥረት ነበር። ባለፈው በቁጥጥር ሥር ውሎ በነበረበት ጊዜ ከትህነግ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ምክትል ዳይሬክተሩ “ራስህን ጠብቅበት” ብሎ ሽጉጥ እንደሰጠው ራሱ በአንደበቱ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ተናግሯል። ሌሎቹ ተቃዋሚዎች ሌት ከቀን በትህነግ ሽጉጥ ሲታደኑ በነበሩበት ጊዜ ልደቱ ራሱን የሚጠብቅበት ሽጉጥ ነበረው። የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሆኖ ከማን ነው ራሱን የሚጠብቀው? ሽጉጥ ከሰጠው ትህነግ ወይስ ትህነግን እየተፋለሙ ከነበሩት ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች? ልደቱ አያሌው በአደባባይ፣ ህግ ፊት፣ ራሱን ነጻ ለማውጣት ሲል የተናዘዘው እውነት!! ነገ መልሶ ሊልሰው የማይችለው ተግባሩ!!
በቀጣይ የ1997 ምርጫ ወቅት ትህነግ በዝረራ ተሸንፎ ወደ መቃብር እየወረደ ባለበት ጊዜ የቅንጅትን የድል ጉዞ በማጨናገፍና ለትህነግ ፖለቲካዊ ትንሣኤ በማምጣት ከፍተኛ ሚና የተጫወተው ልደቱ አያሌው ነበር። ልደቱ ብዙ ተዓምር የሚባል ነገር አላደረገም፤ ፓርቲዎቹ ሲቀናጁና ወደ ስምምነት ሲደርሱ የራሱን ፓርቲ ማኅተም አላስረክብም ነው ያለው። ይህ የልደቱ ውሳኔ ቅንጅትን እንዳይቀናጅ አድርጎ በሕዝብ ድምጽና ስሜት ላይ “የመቀናጆ በሬ ሲመሽ ወደቤቱ” የሚል ዘፈን አስደረደረ። ቅንጅት እንዲያሟሟ ያሤረው ልደቱ ያንን የመሰለ የሕዝብ ትግል አጨንግፎ እሱ ወደ “ክህደቱ” የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማማ ላይ ተሰቀለ።
በቅንጅት ክህደት ፋይሉን ያልዘጋው ልደቱ፣ “ሦስተኛ አማራጭ” ብሎ ዳግም ከተከሰተበት የማደናበሪያ ፖለቲካው ጎን ለጎን ትህነግ በተሸበረ ጊዜ ከበረከት ስምዖን ጋር በመሆን የነፍስ አድን ዘመቻ ቋሚ ተሰላፊ ነበር። በዚሁ ቁመናው በርካታ ውለታ ለትህነግ የሠራ ቢሆንም ዋናውና የቅርብ ጊዜ ተግባሩ ግን ሕዝባዊ ለውጥ የመጣ ጊዜ የተርመጠበጠበት ቅጥረኛነቱ ይጎላል።
ትህነግ የህዝብ ክንድ አውላልቋት ከአራት ኪሎ ወደ መቀሌ በሄደችበት ጊዜ ፓርቲ በማቋቋም፣ መቀሌ ድረስ በመሄድና አማራጭ ሃሳብ በማቅረብ፣ የሽግግር መንግሥት ሃሳብ ከትህነግ ጋር በማቅረብ፣ ትህነግ የሚነዳቸው ሌሎች የዘር ፓርቲዎች በፌዴራሊስት ስም እንዲቋቋም በማገዝ፣ የሽግግር መንግሥት ጽሁፍ በተደጋጋሚ በማውጣት፣ “ከመስከረም ሃያ በኋላ መንግሥት የለም” በማለት ሕዝብ እንዲሸበር በማድረግ፣ ወዘተ ትህነግን ለመታደግ እጅግ ብዙ ጥሯል።
በመጨረሻ ከቀድሞው ፓርቲው በመባረሩ ምክንያት ሌላ ፓርቲ ለመመሥረት አስቦ ጥቂት የሚባል ፊርማዎች ለማሰባሰብ ባለመቻሉ ምርጫ ቦርድ ካሳናበተው በኋላ ከሌላኛው መሰሉ ይልቃል ጌትነት (ባለፈው በተደረገው ምርጫ ኢትዮጵያን ለ50 ክልል የመከፋፈል “አማራጭ” ይዞ ተወዳድሮ፣ ሁለት ድምጽ ያገኘ መሆኑ ልብ ይሏል) ጋር “የእባካችሁ አስገቡኝ” ጥያቄ አቅርቦ እንደ ሆድ ዕቃ ተህዋስ በጥገኝነት ቆይቶ ነበር። ሳይሳካ ቀርቶ ለዐቅመ ምርጫ እንደማይቀርብና ትህነግንም በፈለገው መልኩ መታደግ እንደማይችል ሲረዳ “ከምርጫው ራሴን አግልያለሁ” አለ።
“በታምሜአለሁ” ሰበብ ከአገር የወጣው ልደቱ፣ ትህነግ የጀግናው መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላትን በግፍ ሲጨፈጭፍ፣ የክህደቱን ጭፍጨፋ “መብረቃዊ ጥቃት” በማለት ወዳጁ ሴኩቱሬ በአደባባይ ሲደሰኩር፣ ልደቱ አንዳችም አልተነፈሰም። ቁብም አልሰጠውም። የአገር መከላከያ በግፍና በክህደት መታረዱ በአለቆቹ፣ ምን አልባትም እሱ በሚያውቀው ደረጃ ስለተፈጸመ ልሳኑ ተቀረቀረ።
ይህ ብቻ አይደለም። አገርን ከዳር እስከዳር ባስቆጣው ክህደት ሳቢያ ትህነግ በሁለት ሳምንት ውስጥ ተቀጥቅጦ ልክ ሲገባ አጅሬ አንዳች አላለም። በቀጣይም ጨፍጫፊውና ሊጥ ሳይቀር ዘራፊው ትህነግ “ከአማራ ሕዝብ ጋር ሒሳብ አወራርዳለሁ” በማለት ያካሄደውን ወረራ ለመቀልበስ አማራና ወዳጆች አንድ ሆነው “የኅልውና ጦርነት” በከፈቱበት ጊዜ “የወሎ ቡግናው ልጅ” አሁንም አልተነፈሰም ነበር። ትህነግ “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ፣ ያንንም ለመፈጸም ሲዖልም ቢሆን እገባለሁ” ሲል ልደቱ አንዳች አላለልም። ወሎ በትህነግ ስትወድም፣ ስትበዘበዝና ስትታመስ፤ ጎንደር ከምድገጽ እንዲጠፋ ትህነግ ያለ የሌለ ኃይሉን ሲያሰማራባት፣ በትህነግ “ግልቢያ” አራት ኪሎ ከዋሽንግተን የታየው ልደቱ “ጦርነት ይቁምና የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” አላለም።
መከረኛ የትግራይ ወጣቶችን በገፍ አሰማርቶ መላው አማራና አፋር ክልል ላይ እንደ ጉንዳን ሲርመሰመስ የነበረው ትህነግ፣ በግፍ ሲጨማለቅ፣ በኃጢያት ሲጠመቅ፣ ዓመድና ዱቄት ሥር እየተንከባለለ ንጹህ አርሶ አደሮችን ሲያተራምስ፣ ሲገድል፣ ሲደፍርና በክፋት ሲገለማ፣ ድመት ሳይቀር ሲገድልና ከተማ ዓመድ ሲያደርግ፣ በርኩስት ኩይሳ ላይ ተቀምጦ የህጻናት፣ አዛውንትና ቀሳውስት ደም ሲጋት፣ በደቦ እህቶቻችንን ሲደፍር ልደቱ አያሌው ልቡን በፔስ ሜከር አስደግፎ ከትህነግ የውጭ ኃይሎች ጋር ምን ይገምድ እንደነበር የምናውቅ እናውቃለን። ከሁላችንም በላይ ደግሞ እሱ ያውቃል። የተካነበት ሥራው ነውና።
ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡት የጸጥታ ኃይሎች፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖ እንዲሁም መላው ኅብረተሰብ “ትህነግን ሳናጠፋ እርሻም አናርስም፣ ንግድም አንነግድም፣ ቤታችን አንመለሰም” ብለው በቁርጠኝነት ሲዘምቱና አንጸባራቂ ድል ሲቀዳጁ፤ በባዶ ተስፋ ልቡ አብጦ ህጻናትን ወደ ጦርነት ሲማግድ የነበረው ትህነግ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን ጭፍሮቹን ሲያጣና ወደ ሞቱ ሲቃረብ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ልደቱ አያሌው በወዳጆቹ እነ 360 ሰዎች አጋፋሪነት ብቅ ብሏል። ነገሩ “የአይጥ ምስክር …” እንዲሉ!!
እንደበቀቀን በሚያነበው አንባቢ ከሃያ ደቂቃ በላይ የሚፈጀው የልደቱ ትህነግን የማዳን ተማጽንዖ ሃሳብ ለማስረዳት መስመር በመስመር መሄዱ አስፈላጊ አይደለም ብቻ ሳይሆን ለዐቅመቢስነቱና ድንቁርናው ክብር መስጠት ይሆናል። ልደቱ ለማለትና ለመከወን የፈለገው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት አንቀጾች ይገኛል። ለኢትዮጵያ እንደ አገር ሆኖ መቀጠል ብቸኛው መፍትሔው አሁንም ትህነግ የሚሳተፍበት የሽግግር መንግሥት ነው ለማለት ሲያኮበኩብ እንዲህ ነው ያለው፤
“ያሁኑ ጦርነት ሁላችንንም የጋራ ተሸናፊ ከማድረግ ውጪ የተለየ ፋይዳ አይኖረውም … ጦርነቱ የሚያሳካው አንድም አገራዊ ውጤት የለም፤ … ጦርነቱ ምንም ዓይነት አዎንታዊ አስተዋጽዖ የለውም … ጦርነቱ በጥላቻ የምንገዛና በአስተሳሰብ ደካማ የመሆናችን ውጤት ነው እንጂ በራሱ የችግራችን ምንጭ አይደለም፤ … የአሁኑ ጦርነት አገር ተረካቢውን በገፍ የሚቀጥፍ ውጤቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን አሟጥጦ የሚያጠፋና አገሪቱን የሚበትን ከመሆን ውጪ ምንም ዓይነት በጎ ውጤት አይኖረውም፤ … አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ለመውጣት አዲስ የሽግግር መንግሥት ከማቋቋም ውጪ ሌላ አማራጭ ችግሩን መፍታት አይችልም ”።
ባጭሩ አማራውም ሆነ አፋሩ ምንም ዓይነት የኅልውና አደጋ አላጋጠመውም፤ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም በትህነግ የደረሰበት ችግር የለም፤ አማራውም ሆነ አፋሩ በትህነግ በጅምላ አልተጨፈጨፈም፤ ማይካድራ፣ አጋምሳ፣ ጭና፣ ጋሊኮማ፣ ወዘተ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተፈጸመ ጭፍጨፋ ነው እንጂ በዲሲፒሊን የታነጸው ትህነግ እንዲህ ዓይነት ግፍ አይፈጽምም፣ በአጠቃላይ “ሒሳብ እናወራርድብሃለን” የተባለው የአማራው ሕዝብ በትህነግ ምንም ግፍ አልደረሰበትም፤ ወልቃይት የምዕራብ ትግራይ ነው፣ ራያም የትግራይ ነው፤ ወዘተ በማለት ነው ልደቱ ሃሳቡን ያቀረበው። ስለዚህ ትህነግ ሳትሞት በሽግግር መንግሥት ምሥረታ አፍ ለአፍ ትንፋሽ እንስጣትና እንታደጋት እያለ ነው ልደቱ ያለው።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ሁሉ ዋናውና ቀንደኛው ዐቢይ አሕመድ የተባለ ኢትዮጵያን ለመምራት የማይችል ዐቅመቢስ ደካማ ነው፤ እርሱ በፓርቲው አመራሮች መወገድ አለበት፤ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አይችልም፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን በትንሽዋ መንደር በሻሻ ስለሆነ የተመረጠው የበሻሻ አስተዳዳሪ ይሁን (መለስ ዜናዊ ከአድዋ ተመርጦ እንደመጣ ዘንግቶ)፤ በቀጣይ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም፤ ትህነግ የሽግግሩ አባል ይሁን፣ ይህንን ፓርቲው የማይቀበል ከሆነ ዐቢይ አሕመድ ከመስከረም 24 በፊት በመፈንቅለ መንግሥት መወገድ አለበት። ይህ ባጭሩ ላለፉት 2 ዓመታት በላይ በትህነግ ዲጂታል ሠራዊት (ዲጂታል ወያኔ) አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ ሲተገበር የነበረው “እረኛውን ምታ መንጋው ይበተናል” መርሕ ግልባጭ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።
እዚህ ላይ አንድ ሃቅ ማንሳት ግድ ይላል። ክርስቶስ “የእኔ የሆኑትን ባካሄዳቸው አውቃቸዋለሁ” እንዳለው ከለውጡ በኋላ የትህነግ ኃይል ያቋቋመው ዲጂታል ወያኔም ሆነ ቀድመው የተገዙ እንደ ልደቱ ዓይነት ተውሳኮች፣ እንደ ኤርሚያስ ያለ ጋጋኖ፣ እንደ ታምራት ያለ “ስኳር” ላሽ፣ እንደ ያሬድ ጥበቡ ዓይነት ዳፍንታም፣ እንድ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ያለ እፉኚት ወዘተ ሁሉም “የፖለቲካ መፍትሔ” እያሉ አፋቸውን የሚከፍቱት በእረኛው ስምና ማንነት ላይ በማጠንጠን ነው። እረኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ከአራት ኪሎ ወጥቶ ሊጥ ጠጪና ዱቄት ላሽ ከሆነው ትህነግ ጀምሮ ከላይ የተጠቀሱት ተላላኪዎቹ ሁሉ ዞረው የሚሰጡት የመጨረሻ “መፍትሔ” እረኛው (ዐቢይ) ይመታ የሚል ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ አነጣጥረው ሁሉንም ዓይነት በትር የሚያወርዱት ቅጥረኞች መለያቸው “እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” ነው።
ትህነጉ ልደቱ ይህንን ሁሉ በጽሁፉ ሲያትት ወደ 6 ወይም 7 የሚሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብቃቶችን የሚያሳዩ ነጥቦችን ከዘረዘረ በኋላ ነበር። በምቀኝነትና በጥላቻ የተመራ ካልሆነ በስተቀር አንድ ሰው ያከወናቸውን በጣም ልዩ የሆኑ ነጥቦችን ጠቅሶ “ለወደፊቱ ግን ብቁ አይደለህም፤ ከሥልጣንህ ውረድ” ማለት የልብ ሳይሆን የአእምሮ በሽታ አመላካች ነው። ከዚያም በላይ ደግሞ የልደቱ ፖለቲካ ከትህነግ ሰፈር እየተለካ የሚሰጥ “አንደርቢ” ነው።
ልደቱ ለ360 “በተለይ” ሲል አሳስቦ ባስቸኳይ እንዲነበብለት በላከው ጽሁፍ ያቀረበው የተላላኪነት ቅዠት ሲቋጭ፣ መፍትሔው ተቀባይነት ካላገኘ ዶ/ር ዐቢይ በመፈንቀል መንግሥት መወገዳቸው አማራጭ ይሆናል ብሏል። ከላይ እንደተባለው ልደቱ መከላከያ ሠራዊት ሊታረድ ሲታሰብም ሊያውቅ እንደሚችል ካለን ግንዛቤ አንጻር ትህነግ ከሞት አፋፍ እንዲነሳና ነፍስ እንዲዘራ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት መወገድ አለበት የሚል ነው።
ካለው ተጨባጭ ሁኔታና ልደቱ በደኅንነት ተቋማት ውስጥ ይሠራ እንደነበር በማስረጃ ያረጋገጡ የቀድሞ ኃላፊዎች እንደመሰከሩት ልደቱ፣ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት መስከረም 24 ቀን እንደ አዲስ መቋቋሙ ይፋ ከሆነ “መፈንቅለ መንግሥት” እንደሚጠብቀው አስቀድሞ መናገሩ በዋዛ የሚታይ አይሆንም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በመነጋገር ጉዳዩን በጥልቀት ሊመለከተውና ችግር ከመፈጠሩ በፊት አስቀድሞ መላ ሊለው የሚገባው ጉዳይ ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ማስታወሻ፤ ልደቱ “ቢበቃው” በሚል “ሳትታመም” ብሎ የዋዜማ ብዕረኛ መስፍን ይህንን ምክር ቢጤ (10 Oct 2018) ለልደቱ ለግሶ ነበር።
Tesfa says
በእውነት አቶ ልደቱ አያሌው ከላይ በጥቅስ መካከል ያስቀመጣችሁትን አረፍተ ነገር ተናግሮ ከሆነ ታሟል እንጂ ጤነኛ አይደለም። ይህን የምለው በሁለት ነገሮች ላይ ተመርኩዤ ነው። አንደኛ ወያኔ ከጅምሩ ጀምሮ የአማራን ህዝብ ያጠፋ፤ የሃገር ሃብት የሰረቀና የሸጠ፤ እልፍ ሰዎችን በስልጣን ላይ እያለ ያሰቃየና የገደለ ለመሆኑ ከአቶ ልደቱ የበለጠ የሚረዳ ፓለቲከኛ ያለ አይመስለኝም። ለምን ቢባል እዚያው በሃገሩ ከጎናቸው ቆሞም ሆነ ተሰልፎ አይቷልና። ሁለተኛው ነጥብ የትግሬ ጠባብ ብሄርተኞቹ በስልጣን ላይ እያሉ ሃገር ሰላም ነበር። በጅምላ ሰው አይገደለም ነበር ስለሚለው ሃሳብ የፓለቲካ ንፉዝነቱን ያሳያል እንጂ እውነት የለበትም። ዛሬም ሆነ ትላንት እርስ በርስ የሚያባላን እኮ ያው የወያኔ ሴራ ነው። አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው የእብደት ጦርነት ራሱ ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው። እውነትን ለማየት ለፈለገ ሰው እንደ ወያኔ ያለ አጥፊ ሃይል በምድሪቱ በቅሎ አያውቅም። ወያኔ ከጣሊያን ወራሪዎች ይከፋል። የአማራውን ሰብል፤ ከብቶቹና ቤቱን ለምን አፈራረሱት ብዬ የጠየኩት አንድ የፓለቲካ ትምህርት አዋዊ ሲናገር። መልሱ ቀላል ነው። ወያኔ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ይጠቀማል። ሰው ሲራብና ሲራቆት በመንግስት ላይ ይነሳል ብሎ ስለሚያስብ ይህን ጥፋት ይሰራል። ባንጻሩ የእርዳታ እህል እንዳይገባ መንግስት ከለከለ እያለ ሲያጓራ የአፋርን ክልል ወሮ መንገድ እንዲዘጋ ያደረገው ራሱ ነው። የትግራይን ህዝብ ለፓለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ። የሚያሳዝነው እህል ሊያደርሱ የተላኩ የጭነት መኪኖች እንኳን እንዲመለሱ አላደረገም። ይህን የሙታን ስብስብ ነው አቶ ልደቱ አያሌው የሚደግፈው? ተናግሮት ከሆነ እጅና እግሩ ተይዞ ጸበል ቢወሰድ ይሻለዋል። የሸፍጥ ፓለቲካ ለሸፋጭም ሸፋጩን ለሚከተልም አይጠቅምም። ዝም ብሎ መገላበጥ ነው።
ባጭሩ የሃበሻው ፓለቲካ የእብዶች ስብስብ የሚንጋጉበት፤ ከሥራ ይልቅ የቃላት ድርደራ የበዛበት፤ ዝምታን እንደመምረጥና የልብ በልብ ሙያ እንደመሰራት በወልና በግል የሚያቅራሩበት፤ የሰውን ሰውነት ከመረዳት ይልቅ ከየትኛው ጎሳና ክልል ነህ በማለት ሰልፍ የምናበጅበት አሻሮ ፓለቲካ ነው። የጠራሁ አማራ፤ የጠራሁ ትግሬ ገለ መሌ መባሉ ሁሉ በሳይንስ የማይደገፍ እውነትነት የሌለው የእብዶች ቱልቱላ ነው። ህዝባችን የተቀላቀለ፤ አብሮ ሲኖርና ሲፋተግ የኖረ ለመሆኑ በየጊዜው ከምናየው የአሁንና ያለፉ ተግዳሮቶችና ገጠመኞች የያዘው ጥለፈው ፓለቲካ ብቻ መረዳት ይቻላል። ያለፈውም ታሪካችን ከሞላ ጎደል የአሁኑን ይመስላል። በቅድመ አያቶቻችን በአያቶቻችን ደጃፍ ላይ ስንት ሰው አልፏል? ግን በዘሩ ለሰከረ የጠባብ ብሄርተኛ ቡድን እንዲህ አይነቱ ስሌት አይዋጥለትም። ከወርቃማው ህዝብ ተወልዷልና። ሌላው ሁሉ ነሃስ አፈር ነው ለሰካራሙ ፓለቲከኛ! አንድ ጊዜ አንድ እብድ አዲስ አበባ ፒያሳ ላይ ቆሞ ከት ብሎ ይስቃል። አብረው በጎኑ የሚያልፉ ሁለት ጓደኞች ደግሞ እርስ በእርስ ተያዪና አንደኛው ለአንደኛው ምን እንዲይህ ያንከተክተዋል የሚያስቅ ሳይኖር ቢለው ዝም በል “ለአንተ ያልታየህ ታይቶት ቢሆን ነው” እንዳለው ነው። አቶ ልደቱ በህልም ዓለም ካልሆነ በስተቀር ወያኔ ድሮም ዛሬም የሃገር ነቀርሳ መሆኑን አይዘነጋውም። እውቁ ገጣሚና ባለ ቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያሙሌ) እንዲህ ብሎ ነበር።
ስንቱን ዞረው ዞረው
መጡ ተመልሰው
በመከራ ጽዋ በቃል ተከልሰው።
በምንም አይነት የሂሳብ ቅመራ ወያኔ ለሃገርና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይበጅ ነበር ብሎ መከራከር አይቻልም። ያው ግን ከስሩ ፍርፋሪ ለቃሚ ለሆኑ የፓለቲካ እብዶች ጥቅም ነውና ውሻ በበላበት ይጮሃል በመሆኑ ከመጮህ አልፈው ለመናከስ መከጀላቸው የጅልነታቸውን ጣራ መንካት ያሳያል። አታድርስ ነው። በቃኝ!
gihaile says
ኣቶ ልደቱ ኣይልም ኣይባልም። እንደ እስስት ቀለሙን የሚለዋውጥ ሰው በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ልደቱና መመረራ ጉዲና ናቸው። ብር ከሳዩኣቸው እናትንም ኣባትንም ከማጥፋት የማይመለሱ ቢሆኑም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ምንም ደንታ የየሌላቸው የስልጣን ረሃብና ጥማታቸው ያልረከ ስግብግቦች ናቸው። መሪ ለመሆንና ስልጣን ለማግኘት የማይሉት፣የማያደርጉትና የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ስለዚህ ልደቱ ሳሙና በመሆኑ ከእጅና ከከልብስ ማጠብ በኋላ እንዲሚያልቅና ኣረፋ ደፍቆ እንደሚጠፋ ነገር ነው።
ከነዚህ የፓለቲካ ነጋዴዎች መጠንቀቅ ተገቢ ነው። የሕወኣት ጁንታ ደጋፊ ሁሉ የሰው ዘር የሌለበት አጋንንት ካልሆነ በቀር በሰው ስቃይ የሚደሰት ድርጅትንና መሪዎቹን መደገፍ ማለት ሂትለርን መልሶ ስልጣን ያዝ ማለት ነው።
የለምጨኑ says
ልደቱ ከህወሓት የከበደ፣ይቅር የማይሉት የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ጠላት ነው። በምን አይነት አመክንዮ ነው ህወሓት ከዚህ ሁሉ ዘር ጭፍጨፋ ዝርፊያ የደቦ ወሲባዊ ጥቃት እና እጥፍ ቶ መጥፋት በሗላ የሽግግር መንግሥት መስራች አባል የሚሆነው ?