“የቀረው ደግሞ ወደ ትግራይ ሄደን የቀሩትን ማምጣት ነው”
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በንግግር እና ውይይት መፈታቱ ተገልጿል።
ቤተክርስቲያኗ ያጋጠማትን ፈተና ለመፍታት የሃይማኖት አባቶቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ምክክር አድርገዋል።
በውይይታቸውም አንድነትን የሚያፀና እና አገልግሎትን የሚያሰፋ መንገድ መከተል ተገቢ መሆኑን በማመን ከስምምነት መደረሱን የሃይማኖት አባቶች ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።
ከቋንቋ ጋር በተገናኘ የሚነሡ ሐሳቦችን ለመመለስ ቤተክርስቲያን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንድትቀጥል ከመግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በበጀት እና በሰው ኃይል ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶታል።
በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እምነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና ዩኒቨርስቲዎች እንዲጠናከሩ እና ቤተ እምነትን ለትውልድ ለማሻገር መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች በጥናት እና በአሠራር መፍታት እንደሚገባም መተማመን መፈጠሩ በመግለጫው ተጠቁሟል።
የስምምነቱ አንኳር ነጥቦች፤
“ስምምነቱ ማስገደጃ ሆኖ የቀረበ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ስርዓት ቀኖና ባከበረና ባስከበረ ሙልኩ የተከናወነ ነው” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አብርሃም።
ከሰሞኑ ያጋጠመውን ፈተና ለመፍታት ከሁለቱም ወገን ያሉ አባቶች ተገናኝተው ምክክር ማድረጋቸውና ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
የስምምነቱ ዋና ነጥቦች
የካቲት 8 ቀን 2015 ባደረግነው ውይይት የሚከተሉትን የመግባቢያ ሐሳቦች ላይ ደርሰናል።
1. በኦሮሚያ ክልል በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት፤ ቅዳሴ እና ሌሎችም አገልግሎቶች እንዲሰጡ የተጀመረው ሥራ የሕዝቡን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ እንዲጠናከር። ለዚህም ከዚህ በፊት ከተደረገው በተጨማሪ አስፈላጊው በጀትና የሰው ኃይል እንዲመደብ፤
2 በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች የተዳከመ አብያተ ክርስቲያናት ቋንቋውን በሚያውቁ አገልጋዮችና በአገልግሎት እንዲጠናክሩ አስፈላጊው ዕቅድ ተዘጋጅቶ ከበፊቱ በበለጠ ተገቢው በጀትና የሰው ኃይል እንዲመደብ፤
3. በኦሮሚያ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚያገለግሉ ቋንቋውን የሚያውቁ አገልጋዮችን የሚያሰለጥኑ ኮሌጆች እና ማልጠኛዎች እንዲከፈቱ፤ የተከፈቱትም እንዲጠናከሩ እንዲደረግ፤
4. ለኦሮሚያ አህጉረ ስብከት በቂ የሆነ የኦሮምኛ ቋንቋን የሚያውቁና በቋንቋው የሚያገለግሉ ኤጲስቆጶሳት በቀጣይ የግንቦት (ርክበ ካህናት ተወስኖ እንዲሾሙ)፤
5. ሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እና ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ቀደመ ሀገረ ስብከትና የክህነት ማዕረጋቸው እንዲመለሱ፤
6. በሦስቱ አባቶች የተሾሙት አባቶች ቀድሞ ወደነበሩት የክህነት ማዕረግ ይመለሳሉ። ከእነርሱ ውስጥ በቤተ ክስቲያን ሕግና ሥርዓት የሚያሟሉት እንደገና በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሾሙ ይደረጋል።
7. በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በፋይናንስ፣ በምደባ፤ በቅጥር የሚታዩ ክፍተቶችን በጥናት የወንጌል አገልግሎትን በሚያጠናክር መልክ እናሻሽላለን።
8. የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የበለጠ ለማጠናከርና ለትውልድ አርአያ የሚሆን ቤተ ክህነት እንዲኖረን ለማድረግ አሠራራችንን በጥናት አሻሽለን ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ እናሻግራለን።
9. ጥላቻን የሚያባበሱ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይገባል። ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶች፣ መምህራን እና አባቶች ፍቅርን ከሚያጠፋ፣ ጥላቻን ከሚያበዛና መለያየትን ከሚያሰፋ ነገር ሁሉ እንዲቆጠቡ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን። ይሄንን ተግባር ሆን ብለው የሚያደርጉትንም እናወግዛለን።
10. የገጠመን ፈተና ይበልጥ ውስጣችንን ለመፈተሽ፣ አንድነታችንን ለማጠናከር፤ ወንጌልን የበለጠ ለመስበክና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስፋፋት ለበጎ እንጠቀምበታለን።
በመጨረሻም ፍቅር፣ ይቅርታ እና አንድነት እንዲመጣ የደከማችሁትን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን። ዋጋችሁንም እግዚአብሔር እንዲከፍላችሁ እንጸልያለን።
በስምምነቱ ወቅት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ጠንካራ ቤተክርስቲያን፣ ሌላ ሺህ ዘመን ሙሽራው እስኪመጣ የምትቆይ ቤተክርስቲያን እናድርጋት … ብለን ተስማምተን የጋራ መግለጫ አውጥተን ይህ ሁሉ ድግስ አባታችን ጋር ሳይደርስ እንዴት ይቀራል ብለን ነው የመጣነው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ጥበበኛ፣ ሰፊ ልብ ያላቸው፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች እንዳሉ አይቻለሁ፤ … በውጪ እንደሚባለው አይደለም፤ ብዙ ልባቸው የሰፋ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ጥሩ ልብ ያላቸው፣ ለአገራቸው ለቤተክርስቲያናቸው የሚቀኑ አባቶች እንዳሉ ለማወቅ ችያለሁ፤ ይህ መታደል ነው፤ ሁሉ አገር ይህ ዓይነት ዕድል የላቸውም፤ … የዛሬው ተሳክቷል፤ የቀረው ደግሞ ወደ ትግራይ ሄደን የቀሩትን ማምጣት ነው” ብለዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
የመግባቢያ ነጥቦቹ እንደ አስርተ ቃላቱ አሥር መሆናቸው ታስቦበት ይሁን አጋጣሚ ባይገባኝም በየሰበቡ ከመገዳደል ስምምነቱ እስካዳነ ድረስ መልካም ነው ብሎ ማለፉ ይሻላል እና አልፈዋለሁ፡፡ የሃገራችን የፓለቲካ ችግር ጅምሩ ላይ አይደለም፡፡ ሁሌ አንድን ገፍትረው ስልጣን ላይ ቁጢጥ ሲሉ ቃላቸው ማር ነው፡፡ መነገጃቸው ህዝብ፤ የሃገር አንድነትና ሃይማኖት ናቸው፡፡ ጭንቁ የሚመጣው መሃሉ ላይ ነው፡፡ ያለምንም ደም እንከንዋ ይውደም ተብሎ ነበር አይደል፡፡ መቸም አታድርስ ነው፡፡ አይጣል ይላሉ የሃገሬ ሰዎች በሰው ላይ ከበድ ያለ ነገር ሲደርስ ለራሳቸውም እድል ፈንታ አዝነው ፈጣሪዬ የምችለው ስጠኝ በማለት ሰማይ ሰማይ እያዪ ይማጠናሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፓለቲካ እጃቸውን ያስገቡ ሁሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምችለው ስጠኝ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚያውም ከእሳቱ ከተረፉ!
በሃገራችን ውስጥ ለነበረውና አሁንም ላለው ቆሻሻ ፓለቲካ መንግስታት ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡ ራሱ ተጠያቂ ነው፡፡ የሚናገረው ሌላ ተግባሩ ሌላ፡፡ እግዚኦ ሲል ውሎ የሰው ቤት ዘረፋ ላይ የሚሰማራ፤ ምንም መጠለያ የሌላቸውን የሚያጠቃ፤ በዘሩና በቋንቋው ተሰልፎ ሰውን እየመረጠ አንገት የሚቀመጥል የእብድ ስብስብ የሞላበት ሃገር ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት በሃበሻዋ ምድር የእብዶችን ቁጥር እትዬ ለሌ ላይ የሰቀለው፡፡
ሰው በሰውነቱ ተመዝኖ፤ በሃገሪቱ ክፍል በፈለገበት ተዘዋውሮ የመኖር፤ የመስራት፤ የመማር መብቱ እስካልተጠበቀ ድረስ ኢትዮጵያ ማለት በክልል አፓርታይድ የተቆለፈች በቋንቋቸው የሰከሩ የሚያንገላቷት ምድር ናት፡፡ ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ በአለም የታሪክ መዝገብ ላይ እንደ እንግሊዝ መንግስት ያለ በሰው ልጆች ላይ ጭካኔን ያደረሰ መንግስት የለም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ቋንቋቸው በአለም ላይ ከሚሰራባቸው ቋንቋዎች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞአል፡፡ በሃበሻ ምድር ዝም ብሎ በሆነ ባልሆነው ነገር መቦጫረቅ ሰውን ለመከራ ከመዳረጉ ሌላ የሚያመጣው አንድም ፍትሃዊ ነገር የለም፡፡ ባጭሩ በአማርኛ ተሰበከ፤ በኦሮምኛ ተቀደሰ ዋናው አምልኮው ላይ ነው፡፡ ችግሩ ይህን የቋንቋ ፓለቲካ ወደ ትጥቅ ትግል እያስገቡ ሊያፋልሙን የሚሹት የያኔና የአሁን ጠላቶቻችን አርፈው አይተኙምና ያው ሞኞችን እያስታጠቁ ለወገንህ ነው በማለት ያጫርሱናል፡፡ መቼ ነው የምንነቃው የሰው ተላላኪ ከመሆን? እየዘረፉና እያሽበሩ መኖር እውን የብሄር ጥያቄ ትግል ነው? ጭራሽ! ታሪክ የሚያሳየን የበረሃ አሸባሪዎች የከተማ አለቆች ሲሆኑም የከፋ አረመኔዎች እንደሆኑ ነውና!
ዛሬ በዪክሬንና በራሺያ ባለው ግጭት የተነሳ አሜሪካንና የአውሮፓ ህብረትን ወደ ጎን በማድረግ ወደ ራሺያ የሚጠጉ ሃገሮች ቁጥር ከፍ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ የሚበልጡትም በአፍሪቃ አህጉር ያሉ ሃገሮች አፍቃሪ ራሺያ እየሆኑ ነው፡፡ ይህ የጅል እሳቤ ነው፡፡ ነጩ ኣለም ተፋልሞ ወደ ስምምነት ሲመጣ ጥቁሩን ኣለም ዞር ብሎ አያይም፡፡ አሁን በሱዳን፤ በኤርትራና በሌሎች ሃገሮች እየተዘዋወረ ዲስኩር የሚያሰማው የራሺያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ እንጂ ፍሬ የለሽ ዲስኩር ነው፡፡ አፍሪቃ የጦር መሳሪያ አያስፈልጋትም፡፡ የሚያስፈልጋት ሰላም፤ የእርሻና የቴክኖሎጂ ግኝቶች እንጂ፡፡ ያው እንደለመድት ሁለቱ ዝሆኖች ሲፋለሙ እኛው በመሃል እንጨፈለቃለን፡፡ ፓለቲካ የወስላቶች ገቢያ ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ሱማሊያን ሲያላትሙ ራሺያና አሜሪካ ስፍራ እየተለዋወጡ ነበር፡፡ ልብ ያለው ያስተውል፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ዲስኩር ከሃይማኖት አባቶች መታረቅ ጋር ምን አገናኘው ይል ይሆናል አንባቢ፡፡ እኮ ሰከን በል፡፡ በደንብ ነው የሚገናኘው፡፡ በምድረ አፍሪቃ እሳት የሚቀጣጠለው በውጭ ሃይሎች አነሳሽነት፤ በሃገር በቀል ጅሎች ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለመናድ ብዙ ድንጋይ ፈንቅለው ጊንጥ እየነደፋቸው አሁን ላይ ብለው ብለው በሃይማኖት ሳቢያ ሰው እንዲጫረስ ከህዋላ ሆነው እሳቱን የሚያነድት የውጭ ሃይሎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤ/ክ ማናወጥ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይመቻቸዋልና፡፡ ለሃገር ቤት ፍጆታ አማራው እንዲህ ብሎ ኦሮሞው ያን አርጎ በማለት ወሬውን እናናፍሳለን፡፡ ጥልቅ ሚስጢሩ ግን ሌላ ነው፡፡ መመርመር፤ መጠንቀቅ፤ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ዛሬ Deepfake and Artificial Intelligence በአንድ ላይ ተጣምረው የፈጠራው ወሬ በቪዲዪና በሌላ መልኩ በማንሸራሸር ሰውን ያማታሉ፡፡ ዛሬ ዜና የሚባለው በየቀኑ የሚነገረን ሳይሆን ሳይነገር የቀረው ነው፡፡ ልብ ያለው ያስተውላል፡፡ ጀሮ ያለው ይሰማል፤ ይመዝናል፤ አይን ያለው አይቶ ይፈርዳል፡፡ ዛሬ ሃገራችን የሚያስፈልጋት ሰላምና መረጋጋት እንጂ በየጎጡ ጠበንጃ ይዞ እንዘጥ እንዘጥ የሚል በዘርና በቋንቋ የሰከረ ፓለቲከኛ አይደለም፡፡ በቅርቡ ታደሰ ወረደ በትግራይ ጉዳይ ላይ ገለጣ ሲሰጥ የሃዘን ልብስ ለብሳ የተቀመጠችውን አንዲት ወገናችን ሳይ ማን ሙቶባት ይሆን? በምንስ ሞተ በማለት የእሷን መከራ ሳሰላስል ታደሰ ወረደ በአማርኛና በትግርኛ የሰጠውን መግለጫ ልቤ ሳላስገባው ጉዳዪ አለቀ፡፡ መቼ ነው ሰው በሃዘንና በመከራ ጥቁር መልበስ የሚያቆመው? ያ ቀን ይመጣ ይሆን? አላውቅም፡፡ ለዛሬው የሰላሙ ስምምነት ወሸኔ ነው፡፡ ዘላቂነት ይኑረው፡፡ በቃኝ!