
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሲሲቲቪ እና በድሮን የታገዘ የጸጥታ ጥበቃ ስራዎችን ሊያከናውን መሆኑን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚስያችሉ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀም መሆኑን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማሟላት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀይላን አብዲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የወንጀል መከላከል ስራን በሲሲ ቲቪ ካሜራ የተደገፈ እንዲሆን ማድረግ፣ ዘመናዊ የመገናኛ ራዲዮችን መጠቀም እንዲሁም ለወንጀል ምርመራ የሚስያፈልጉ በተለይ ለፎረንሲክ ምርመራ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን፣ መሳሪያዎች፣ ሶፍትዌሮችን በማሟላት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ፖሊስ በሀገሪቱ የሚከናወኑ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን፣ ስብሰባዎችን ደህንነት ይቆጣጠር የነበረው በአካል ነበር ያሉት አቶ ጀይላን በቀጣይ የቁጥጥር ሥራዉን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግና ድሮን ለመጠቀም መታቀዱንም ነግረውናል።
የጎረቤት ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የራሳቸው ሄሊኮፕተር አላቸው ያሉት አቶ ጀይላን ተቋሙ የራሱ ሄሊኮፕተር እንዲኖረውና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ የፖሊስ ተቋም እንዲሆን በለውጥ አቅጣጫው ላይ ተቀምጧልም ብለውናል።
ኮሚሽኑ የለውጥ ስራዎቹንና የትኩረት አቀጣጫዎቹን የሚያስተዋውቅበትን ፕሮግራም ከመስከረም 19 እስከ 20 ማዘጋጀቱን ከአቶ ጀይላን የሰማን ሲሆን በዕለቱም የፖሊስ ቀን ከራስ በላይ ለህዝብና ለሀገር መስራት በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ነግረውናል።
አቶ ጀይላን እንዳሉን የበዓሉ ዓላማ ፖሊስ የሀገሪቱንና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው፣ በቀጣይስ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ለማዊ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል።
ዓላማውን ለማሳካትም በዛሬው እለት በአምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የፓናል ውይይት የሚደረግ ሲሆን ነገ ደግሞ በመስቀል አደባባይ በፖሊስ አባላት በሚደረግ የሰልፍ ትርኢትና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የፖሊስ ቀን ተከብሮ እንደሚውልም ከዳይሬክተሩ ሰምተናል። (ትግስት ዘላለም፤ ኢትዮ ኤፍ ኤም)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply