
”ነገሮች ተበላሽተዋል” በሚል የፋኖ አሰባሳቢ ኮሚቴ ናቸው የሚባሉት ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ከመስከረም ጋር በስልክ ያደረጉትን ንግግር ይፋ በሆነ ማግስት በሰሜን ወሎ ዞን አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበልና ይፋዊ ይቅርታ በማቅረብ ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለሳቸውን የአማራ ክልል አስታወቀ።
ክልሉን ጠቅሶ የአማራ ማስ ሚዲያ ይፋ እንዳደረገው በሰሜን ወሎ ዞን አካባቢ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ አባላት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበልና ይፋዊ ይቅርታ በማቅረብ ወደ መደበኛ ህይወታቸው ተመልሰዋል ብሏል።
“ተታለን ነው” በሚል ሽማግሌ የላኩትን የሰሜን ወሎ ፋኖዎች ጥያቄ ለመቀበል የአገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች
- ከዚህ በኋላ ምንም አይነት መንገድ እንዳይዘጋ፣
- ምንም አይነት የታጠቀ አካል ከተማ ውስጥ እንዳናገኝ እርቅም ይሁን ግጭት ከከተማ ውጭ ጫካ ላይ ይሁን፣
- አፈሙዝ ወደ መከላከያ ሰራዊት እንዳያዞሩ ሠራዊቱ የሚላቸውን ትዕዛዝ አክብረው ይቀመጡ፣
- የመከላከያን ጥቁር ክላሽ ሰብስበው ያስረክቡን በሚል ቅድመ ሁኔታ ካስቀመጠ በኋላ የሽምግልና ሂደቱን እንዲያስቀጥሉ ተስማምተው ሽምግልና ለመጡት ሽማግሌዎቹ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነበር
የአማራ ክልል መንግሥት ከዚህ በፊት በግላቸው ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን በማወያየት ወደ መደበኛ የጸጥታ አደረጃጀት እንዲገቡ ወይም ደግሞ ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። በዚህ ጥረቱም በርካታዎች ጥሪውን ሲቀበሉ ያፈነገጡና የተበተኑ መኖራቸውን አስታውቀው ነበር።
ነገር ግን በቅርቡ በሰሜን ወሎ ዞን አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች የመንግሥትን ጥሪ ባለመቀበል ከመከላከያ ጋር ወደ ግጭት የገቡ መሆኑም ይታወሳል። ሆኖም በቅርቡ የፋኖ አባላቱ ይፋዊ ይቅርታ በመጠየቅ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን በማሳወቅ ከክልሉ መንግሥት እና ከመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገው ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ መስማማታቸውን የክልሉ መንግሥት እንዳስታወቀ አሚኮ ዘግቧል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ በግንባር ቀደምትነት መርቷል የሚባለው የሰሜን ወሎ ፋኖ መሪ ምሬ ወዳጆ የባለወልድ አባቶችን ሽምግልና መላኩ ተሰምቷል። ምሬ ወዳጆ ከልዩ ኃይሉ እና ከህዝቡ ድጋፍ አገኛለው በሚል ወደ ግጭት ቢገባም ባሰበው ልክ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ለመከላከያ ሰራዊት ሽምግልና መላኩን ከስፍራው መረጃ ያላቸው አመልክተዋል። በዚህ ሽምግልና የተሳትፉ የባለወልድ አባቶችም “ጦርነት በቃን፣ ከዚህ በላይ ጦርነት ውስጥ መቆየት አንፈልግም” ብለው ምሬን የገሰፁ መሆኑን እና መከላከያ ሰራዊትም ኢመደበኛ አደረጄጀቱ ትጥቁን ለመከላከያ አስረክቦ ወደ መደበኛ ህይወቱ ወይም በመዋቅር እንዲካተት ስምምነት መድረሱ ታውቋል።
ከይቅርታውና ስምምነቱ በኋላ ምሬ በይቅርታ መመለሱን ተናግሯል። እጅግ በርካታ መስዋዕትነት ከጓዶቹ ጋር ሆኖ ሲከፍል የቆየው ምሬ ሠራዊቱን ለመመገብ እስኪያቅተው ድረስ ተቸገርሁ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ የደረሰለት ወገን እንደሌለ ምሬን በቅርብ የሚያውቁ ይመሰክራሉ። አሁን ሳያውቅ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ያደረጉትን ኃይሎች ወደ ጎን ብሎ የአገሩን ሕግ ለማክበር ቃል ገብቷል።
ከጀግናው ፋኖ ምሬ ጋር አብሮ የገባው ሌላው ፋኖ ሲናገር እንደትደመጠው በስ ህተት ጎዳና መሄዳቸውን ገልጾ የአገር መከላከያና አመስግኖና ይቅርታ ጠይቆ መመለሱን በሰጠው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
አበው ሲተርቱ ” አማኝ ውሻውን የከዳ ውሻ ይሆናል” አሁን ማን ይሙት ፋኖና መከላከያ መገዳደል ነበረባቸው? ይህ የእብደት ፍሬ ነው። ግን ሰው በዘርና በቋንቋው ሰክሮ ዓለምን ማየት ሲሳነው የሚያስበውና የሚያደርገው ነገር ሁሉ ከራሱ አፍንጫ አይርቅም። ትላንት በአንድ ጉድጓድ አበረው ወያኔን እንዳልተፋለሙ አሁን ከሁለቱም ወገን የሰው ህይወት መጥፋቱ የሚያሳየው የፓለቲካውን ጥልፍልፍነት ነው። በመረጃ ሳይሆን በፈጠራ ወሬ እየተመሩ የሰው ህይወት ማጥፋት ምን የሚሉት መሰልጠን ነው? ግራም ነፈሰ ቀኝ የሃገሪቱ የመከራ ዝናብ አንዴ ሲቆም ሌላ ጊዜ ሲዘንብ ያ ጎርፍ የሚወስደውን እየወሰደ ነጻ እናወጣሃለን የምንለው ያ አርሶ አደር ገበሬውን እያፈናቀልንና እየገደልን እኛም በወረፋ ሟቾች እንሆናለን።
አሁን እንሆ በተነሳው ግርግር ሰራተኞቼ ሞቱብኝ የሚለው ተመድ ወደዚያ የሚያመላልሰውን እርዳታ እንዳቆመ ተናግሯል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትግራይ ለተጎጂዎች የተከማቸው ለብዙ ሺህ ህዝብ የታሰበው ምግብ ተዘረፈብኝ በማለት ኡኡታ አሰምቷል። ወያኔና ዝርፊያ ተለያይተው ባያውቁም ከራሱ ህዝብ አፍ ላይ የሚቀማ ድርጅት ከወያኔ ሌላ በምድራችን የለም። በአንድ በኩል ሰፍሮ አስረክቦ ዞር ብሎ ይህን ያህሉን ጋግራችሁ፤ ቆልታችሁ ወይም ሰፍራችሁ መልሱ የሚል የአረመኔ ስብስብ ነው። ወያኔ እያለ የትግራይ ህዝብ ሰላም አያገኝም የምንለው በዚህና በሌሎችም ተጨባጭ ነገሮች በመነሳት እንጂ በጭፍን ጥላቻ አይደለም።
ሰሞኑን የአማራ ልዪ ሃይልን ለማፍረስ በተደረገው ግብግብ የተጎዳው ህዝቡ እንጂ አለቆቻችን አይደሉም። Tribal Armies በዓለም ላይ የጠቀሙበት ጊዜ የለም። ሩቅ ወደ ሆነው የኢራን ታሪክ እንኳን ስንጓዝ ብሄራዊነትንና አንድነትን ለማጠናከር መጀመሪያ ያደረጉት ይህን የዘርና የጎሳ ስብስብ ሰራዊት መልክ ማስያዝ ነበር። ስለሆነም የጠ/ሚሩ አላማ መልካም ሆኖ እያለ አፈጻጸሙ ግን ሽምድምድ ነው። እባብ ያየ በገመድ ይደነግጣል እንዲሉ ወያኔ በጎን ሆኖ በሚያቅራራበት ምድር ላይ አንድን ሃይል ብቻ ትጥቅ አውርድ ማለት ድጋሚ እልቂት እንደመጋበዝ ነው። በፕርቶሪያውና በናይሮቢ የተደረገውን ስምምነት ማስፈጸም የመንግስት ተግባር ነው። ሰው መሳሪያ የሚታጠቀው ራሱንና ቤተስቡን ብሎም ሃገሩን ለመከላከል እንጂ ሃገሩ ሰላም ከሆነ ሁሉ በህግ የሚፈረደ ከሆነ ጠበንጃ መሸከሙ በከተማም ሆነ በገጠር አላስፈላጊ በሆነ ነበር። ግን ህግ መዳኘት ሲያቅተው፤ ጉልበታሞች ደሃውን ሲጨቁኑና ሲቀሙ ቆሞ የሚያይ እንስሳ እንጂ ሰው አይደለም። ስለዚህ እንደተባለው የብሄር ስብስቡ ሃይል ፈርሶ ሃገራዊ አቋም ቢኖረው ደስ የሚለው ሁሉንም እንጂ አንድን ክልል ብቻ አይደለም። ስለዚህ መተማመን፤ መመካከር፤ ከጀብደኝነትና ጥይት ወደ ሰውም ሆነ ወደ ሰማይ እየተኮሱ ከመፎከር በረጋ መንገድ ነገሮችን በማየት ለሰላም እጅን መስጠት አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ ነው። አሁን በፋኖና በመከላከያ በሰሜን ወሎ አካባቢ ተደረገ የተባለውም ስምምነት ወሸኔ ነው።
ይሁን እንጂ መንግስት መንገድን ማስተካከል ያለበት ሁኔታም እየታየ ነው። ሁሉም ራሱን ጋዜጠኛና ጦማሪ ብሎ ስለሰየመ ሰሚ አለው ማለት አይቻልም። እርግጥ ነው ዛሬ በሶሻል ሚዲያና በሌሎችም የዜናና የክፋት ማሰራጫ መንገዶች ሰዎች የፈጠራ ወሬ እየነዙ ህዝብን የሚያደናግሩ ሞልተዋል። ግን ሁሉም አይደሉም። ትክክለኛውን ነገርም ለህዝብ የሚያቀርቡ አሉ። ታዲያ የጠ/ሚሩ መንግስት ይህንም ያንም ጊዜ በሰጣቸው ወታደሮቹ እያፈነ መደብደብ፤ ማሰር፤ ማንገላታት ተገቢ አይደለም። ይህ ነገሮችን ያባብሳል እንጂ ሰላምን አያመጣም። አልፎ ተርፎ የውሸት ክስ በመመስረት ሰዎችን ዘብጥያ ማውረድም ትክክል አይደለም። ወያኔንና ጭፍሮቹን የፈታ መንግስት አሁን በዚህም በዚያም እያዋከበ የሚያስራቸውና ደብድቦ የሚለቃቸው ሰዎች ሁሉ ግፍ በመሆኑ ከዚህ ተግባሩ ሊገታ ይገባል። የሚያሳዝነው ፓሊስ እነዚህንና መሰል ወንጀል ሰርተዋል የተባሉትን ሰዎች ከያዘ በህዋላ መረጃ ለማሰባሰብ ጊዜ መጠየቁ ነው። ሲጀመር መረጃ ሳይኖርህና ሳይሟላ ለምን ሰው ይታሰራል? የሚያጠቡ እናቶችን እስር ቤት አስገብቶ ማሰር ብልጽግናን ከሚመኝ መንግስት የሚጠበቅ አይደለም።
ታሪክ አስተማሪ ነው። በማሰር፤ በመግረፍ፤ በመሰወር፤ በመግደል ቢሆን ኑሮ ከደርግና ከወያኔ የከፋ በምድሪቱ ላይ አልነበረም። ግን ሁለቱም የሮም አወዳደቅን ነው የወደቁት። ሰውን በማሰቃየትና በማንገላታት የሚፈጠር ሰላምም ሆነ ሃገሪቱን ከጥፋት የመከላከል ዘይቤ አይኖርም። የዛሬው አሳሪ የነገ ታሳሪ፤ የዛሬው ገራፊ የነገው ተገራፊ እንደሆነ ያለፈ ታሪክ አስረግጦ ያስረዳል። ስለዚህ ሰውን በዘርና በቋንቋው እየመረጡ ማንገላታትና ቤቱን መናድ ግፍ የግፍ ግፍም ነው። መንግስት ነኝ የሚል የሰው ልጆችን መብት ከዚህም ይሁን ከዚያ ነገድ ሊያስጠብቅ ይገባዋል። በመንግስት ላይ አሜኔታ ያለው ህዝብ እንኳን ጠበንጃ ድላ ይዞ ወደ ውጭ አይወጣም። ፓሊሱ፤ ጦሩ ሌላም የህግ ክፍል ሰላምና ጸጥታውን ስለሚያስጠብቅለት። አሁን ሃገሪቱ በገባችበት የፓለቲካ አዙሪት አንድ አትርፎ ሌላው ከሰሮ የሚቀጥል የመሰላቸው ሁሉ የጅብ ፍቅር እስኪቸግር እንዲሉ አሁን ሆያ ሆየ አብረው የሚረግጡት ነው ተመልሰው ጠላት የሚሆኑት። አትራፊ አይኖርም። በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፓለቲካ አካሄድ ሁሉን እውርና ጉንድሽ የሚያደርግ በመሆኑ በጥልቅ ሊታሰብበትና ቀን የሰጣቸው ባለስልጣኖች ህዝብም ከማስጨነቅና ከማንገላታት ሊቆጠቡ ይገባል። ስለሆነም በየሥርቻው በየሰበቡ የታሰሩትን ሁሉ በመልቀቅ በሙሉ ይቅርታ ጉዞውን ወደ ልማትና ግንባታ መመለስ ያለበት መንግስት ነው። ከላይ ፋኖም ሰራዊቱን ይቅርታ መጠየቁ መልካም ጅመራ ነውና በጋራ እየተመካከሩ ለሃገርና ለወገን የሚጠቅመውን ማድረግ ነው። ባጭሩ ሃገሪቱ ያላት አንድና አንድ የመከላከያ ሰራዊት ነው። ሌላው ሁሉ አርሶና ሰርቶ አዳሪ ሃገር በጠላት በተወረረች ጊዜ ስንቁንና ያለውን ይዞ ከጦሩ ጎን የሚሰለፍ እንጂ በራሱ የራሱ የሆነ ሰራዊት አይደለም። አይጥ ከጠፋ ድመት አይፈለግምና ሰራዊቱም የሃገሪቱን ጠላቶችና ሰላም አደፍራሾች ፈልጎ ሥፍራቸውን ማስያዝ ይኖርበታል። በተረፈ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ለሃገሬ ህዝቦች ሰላምን እመኛለሁ። መገዳደል ይቁም!