
ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የአማራ ምክርቤት ስብሰባ ላይ የሰላ ሒስ የሰነዘሩት የምክር ቤት አባል ዮሐንስ ቧያለው ያለመከሰስ መብት ተነስቶ በአገር ክህደትና በመሳሰሉ ወንጀሎች እንዲቀጡ ጥያቄ መቅረብ ጀምሯል። አቶ ዮሐንስ ከስብሰባው በኋላ ሲናገሩ ተሰምተዋል በተባለው የድምጽ ቅጂ በአገር ክህደት ሊያስጠይቃቸው ይገባል የሚል ሃሳብ እየተሰጠ ነው።
አቶ ዮሐንስ ቧያለው ከጥቂት ቀናት በፊት በተጠናቀቀው የአማራ ክልል ምክርቤት ስብሰባ ላይ ግማሽ ሰዓት ያህል በመውሰድ በክልሉ አሉ ያሏቸውን ችግሮች በዝርዝር ሲያስረዱ ተሰምተዋል። እንደ እርሳቸው አገላለጽና ግምገማ ክልሉ ምንም የሚጠቀስ ውጤታማ ሥራ አልሠራም። ወደፊትም አይሠራም፣ ባጭሩ ክልሉና አመራሩ ከሸፏል ነው ያሉት።
በተለይ ንግግራቸው ሲጀምሩ ስብሰባው ቀጥታ ሊተላለፍ እንደሚገባና አፈጉባዔዋ ይህንን በመፍቀድ ታሪክ መሥራት እንዳለባቸው፣ ይህን ካልፈቀዱ በታሪክ ተጠያቂ እንደሚሆኑ በማሸማቀቅ ወይም ለማኅበራዊ ሚዲያ አንገዋለው በመስጠት ነበር። ይህን ብለው ጀምረው በንግግራቸው መካከል መልሰው “አለመተላለፉ ጥሩ ነው የልብ የልባችን እንድንናገር ያደርገናል” ሲሉ ተሰምተዋል። ይህ በቀጥተኛ “የገፊና ጎታች ሤራ” ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል እንደሆነ ተመልክቷል። (ጎልጉል በዚህ የገፊና ጎታች ሤራ ላይ “በገፊና ጎታች ሤራ ከመፈንቅለ ሲኖዶስ እስከ መፈንቅለ መንግሥት” በሚል ርዕስ ያቀረበውን ዘገባ ማንበቡ በቂ መረጃ ይሰጣል)
በክልሉ የሰላም መታጣት በተመለከተ መከላከያ የአማራ ክልልን እያጠቃና ሕዝቡን እያሸበረ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዮሐንስ በኦሮሚያ ከኦነግ (ሸኔ) ጋር እንደተደረገው ዓይነት የሰላም ድርድር መደረግ እንዳለበት ምክረሃሳብ ሰጥተዋል። ሲያጠናክሩም ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋልን እንደ ሽመልስ አብዲሣ ይህንን የሰላም ሃሳብ ይፋ እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸዋል። ሙሉ ንግግራቸው እዚህ ላይ ይገኛል።
ዮሐንስ ቧያለው ከአንድ አክቲቪስት ባልተናነሰ መልኩ ከፌደራል እስከ ክልል መንግሥት ድረስ ያለውን አሠራር አንድም መልካም ነገር እንደተሠራ ሳይጠቅሱ ካብጠለጠሉ በኋላ ወዲያው ስበሰባው ሲያልቅ ስልክ የደወሉት ሥምሪት እና አመራር ለመሥጠት ወደ ኮማንድ ማዕከላቸው ነበር።
በተለወጠ ስልክ የደወሉት ዮሐንስ በንግግራቸው በሽምቅ ውጊያ ሕዝብ እያሸበረ ላለው ታጣቂ ቡድን አመራር፣ አቅጣጫ እና ሞራል ሰጥተዋል። የአቶ ዮሐንስ ቧያለው ድምጽ ነው ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ሙሉ ንግግራቸው ከዚህ በታች ይገኛል።
ከዚህ ሾልኮ ከወጣው የስልክ ልውውጥ በኋላ ጎልጉል ያነጋገራቸው እና አስተያየታቸውን በውስጥ መስመር የሰጡ እንዳሉት “ዮሐንስ ቧያለው የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፤ መከሰስ አለባቸው” ያሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የመናገር መብታቸውን ነው የተጠቀሙት በሚል ሲያሞግሱዋቸው ተደምጠዋል። እነዚህ ወገኖች በምክር ቤቱ የተናገሩትን እንደመብት ቢቆጥሩም ወዲያው ይፋ በሆነው የስልክ ንግግራቸው ላይ ግን ደፍረው “መብታቸው ነው” ሲሉ አልተሰማም።
አቶ ዮሐንስ መከሰስ እንዳለባቸው የጠቆሙ እንደሚሉት ከሆነ በስልክ መመሪያ ሲሰጡና ሪፖርት ሲቀበሉት ለነበረው አንድ አመራር “የአገር መከላከያ ስምሪትን፣ አቅጣጫ፣ አካሄድ፣ አዝማች ጀነራል ስም ድረስ መረጃ ሰጥተዋል፤ ይህንን ማድረግ የቻሉት ባላቸው ሥልጣን መረጃ ስለሚደርሳቸው ነው” የሚለውን ጉዳይ አስቀድመዋል። የአገር መከላከያን ምሥጢርና አሰላለፍ እንዴት እንዳገኙትም በጥብቅ ትሥሥራቸው የት ድረስ እንደሆነ ሊመረመር እንደሚገባም እነዚህ ክፍሎች ይጠቅሳሉ። አቶ ዮሐንስ የአገር መከላከያ ስምሪትና ዕቅድን ብቻ ሳይሆን በሰላም ድርድር ስም እንቅስቃሴው ለጊዜው እንዲገታ ማስደረጋቸውን መግለጻቸው እሳቸውን መሰሎች የሌላ አጀንዳ አስፈጻሚ ስለመኖራቸው ማሳያ መሆኑንንም አክለዋል።
“የሰላም ንግግሩን ለማክሸፍ በግልጽ ሰነድ አዘጋጃለሁ” ሲሉ የሚገልጹት ክፍሎች አቶ ዮሐንስ “የሽብር ተግባሩ እንዲቀጥል ጊዜ መግዛት እንዳለባቸውና ለዚያም እንደሚሠሩ ተናግረዋል። አሸባሪዎቹ እንዳይያዙና እንዴት እንደሚያመልጡም መመሪያ ሰጥተዋል” ሲሉ ይህ ዜና እስከታተመበት ሰዓት ድረስ “የእኔ ድምጽ አይደለም” ብለው አለማስተባበላቸውን እንደ መረጃ ያመላክታሉ።
“አሸባሪዎቹ የሽብር ተግባራቸውን እንዲቅጥሉ የሚያስችል የአምስት አምስት አደረጃጀት በመጠቆም ከዐውደ ውጊያው ወጥተው ወደ ሕዝቡ እንዲቀላቀሉ የሽብር መመሪያ ሰጥተዋል” ሲሉ አቶ ዮሐንስ ሊከሰሱ እንደሚገባ የሚጠቁሙት እነዚህ ክፍሎች “እንቅስቃሴውን እንቆጣጠረዋለን” ሲሉ በምክር ቤቱ የተላለፈውን የሰላም ማስፈን አካሄድ ማምከኛ አዘጋጅተው እንደሚያሰራጩ ገልጸዋል። በሌላኛው ጥግ የሚገኘው አድማጭም መመሪያውን መቀበሉን አረጋግጧል” ይላሉ።
በስልክ ልውውጡ የሚሰማው የተዋጊዎቹ አመራር ቅድሚያ ሪፖርት ሲያቀርብ መከበባቸውንና የስልክ ልውውጡ እስኪደረስ ድረስ ከከበባው መውጣት እንዳልቻሉ ሲያስታውቁ “ትልቁስ?” ሲሉ ዋናውን የጣታቂዎቹ መሪ ደኅንነት ደጋግመው ሲጠይቁ የተሰሙት አቶ ዮሐንስ አንድ እግራቸው ከመንግሥት፣ አንድ እግራቸው መመሪያ ከሚሰጡት የሽብር ቡድን ጋር በአመራር ሰጪነት ሲረግጡ እንደቆዩ፣ አሁንም እየሰሩ እንዳለ ማረጋገጫ በመሆኑ በበርካታ ወንጀሎች ከመጠየቅ እንደማይድኑ እነዚሁ ወገኖች ይጠቁማሉ።
የሩቁን ለጊዜው በመተው “በዚህ ዓይነት መልኩ አመራር የሚሰጡ ዮሐንስ ቧያለው፤ ከአቶ ግርማ የሺጥላ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ባልታወቁ ሰዎች” እየተባሉ ለተገደሉ የፓርቲ ሰዎች የዮሐንስ ቧያለው ድርሻ እስከ ምን ድረስ ነው የሚለው መመርመር አለበት የሚሉም አሉ። ምክንያቱም ዮሐንስ ቧያለው በተለይ በፓርቲው ውስጥ ያላቸውን ሥፍራ ምን ያህሉን ተጠቅመው ለእኩይ ተግባር አዋሉት የሚለው ሊጠየቅ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም በስልክ ሲነጋገሩ ስለ መከላከያ ስምሪት እንደሰጡት ዓይነት መረጃ ለእነ ግርማ የሺጥላ መገደልም አልሰጡም ለማለት የሚከብድ በመሆኑ ነው” የሚሉት ወገኖች “ዮሐንስ ቧያለው ባላቸው የፓርቲ ቦታ ተጠቅመው ታጣቂዎቹ መከላከያን እንዲያጠቁ በዚህ ልክ ለታጣቂዎቹ መመሪያ ከሰጡ ለሌሎቹም ግድያ ተመሳሳይ መመሪያ ወይም መረጃ አልሰጡም ለማለት ያቅታል” የሚል መሞገቻ ያቀርባሉ።
በምክርቤት ስለ ሰላም እያወሩ፣ ስለ ሰላምና ውይይት እየተማጸኑ፣ አንድ ስለመሆንና ስለ ክልሉ ሕዝብ ደኅንነት እየወተወቱ በተሰሙ ሰዓታት ውስጥ ሰላም የማይመጣበትን ይልቁንም ጦርነትና ግድያ የሚቀጥልበትን የድርጊት ዕቅድ እስከማዘጋጀት የሚሠሩ እንደሆኑ በራሳቸው አንደበት በማረጋገጣቸው፣ በምክር ቤት በድምጽ ተሸንፈው እንጂ ሌላ አጀንዳ ይዘው ገብተው እንደነበር ማረጋገጣቸው የአካሄዳቸውን አደገኛነት የሚያመላክት እንደሆነ ጠቅሰው ለክስ የሚያበቃቸው በቂ መረጃ እንደሆነ ያመለክታሉ።
ያለ አንዳች መንገራገር በምክር ቤቱ ያሰሙት ዲስኩር በማኅበራዊ ገጾችና “የአማራ ተቆርቋሪ ነን” በሚሉ ክፍሎች ሲባሉ የከረሙትን አሳቦች ጭማቂ እንደሆነ የገለጹት እነዚህ ወገኖች፣ ልክ ዲጂታል ወያኔን እንደሚመራው ጌታቸው ረዳ የማኅበራዊ ገጾችና የዩቲዩብ አምደኞች አጀንዳ ቀራጭ፣ አጀንዳ ተካይ አቶ ዮሐንስ እንደሆኑ ማሳያ በመሆኑ በዚህ አግባብ ምርመራ ቢደረግ በተደጋጋሚ ለመጫረስ ጫፍ ደርሰው ከከሸፉት አጀንዳዎች ጀርባ ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላካች ነው ባይ ናቸው።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ብቻ ትጥቅ እንዲፈታ መደረጉን ሲገልጹ ሌሎች ክልሎች ኦሮሚያን ጨምሮ ትጥቅ እንዳልፈቱ ማስታወቃቸው ኢመደበኛ ሃይል እንዲስፋፋ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ መሆኑ፣ በምንም ዓይነት ማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑና በመላው አገሪቱ ሰርቶ በሰላም የሚኖረውን የአማራ ሕዝብ ስጋት ላይ የሚጥል፣ የሚያጋጭ እንዲሁም ጥርጣሬ ላይ የሚጥል እንደሆነ ተመልክቷል። አተኩረው በመረጃና ማስረጃ ስም ጠቅሰው ማረጋገጫ ሳይሰጡ በደፈናው የጊዜው አክቲቪስት ዓይነት ባህርይ ያሳዩት አቶ ዮሐንስ “ይህን በተናገሩ ሰዓታት ውስጥ ትጥቅ ፈታ ካሉት ጋር ይሁን ከሌላ እሳቸው ከሚያውቁት ብረት ያነሳ ኃይል መሪ ጋር ያደረጉት ንግግር ደም አፍሳሽ ተግባር ውስጥ እንደተነከሩ ያሳያል።
“የእነ ዶክተር አምባቸው አጥንት ይወጋናል” ሲሉ የተናገሩትን “ወርቃማ አጋጣሚ” ያሉት ክፍሎች “አማራ ክልል በህቡዕ ከተደራጀው ኃይል ጋር እነማን ግንኙነት እንደነበራችሁ፣ ማን ሲያደራጅና ሲያነቃ እንደነበር፣ ማን ከክልሉ አስተዳደር አፈንግጦ ጥቃት እንደፈጸመ፣ ማን በአካባቢና በመንደር አስልቶ አማራ ክልልን መሪ አልባ ለማድረግ እንደተነሳ ወደኋላ ተኪዶ ምርመራ ተደርጎ በግልጽ ለህዝብ እንዲቀርብ የሚገፋፋ በመሆኑ ክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት አቋም እንዲይዙ ጠይቀዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊትን ስም በማራከስና የአማራን ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ምንም ዋጋና መስዋዕት እንዳልከፈለ በመቁጠር “ወራሪና አተራማሽ ኃይል” ተደርጎ በዮሐንስ ቧያለው በገሃድ መቅረቡ የአገር ክህደት በመሆኑ የመከላከያ አመራር ራሱን እንዲያስከብር እነዚሁ ወገኖች ጨምረው አሳስበዋል። ኢትዮጵያን አቅፎና ደግፎ የያዘውን ብቸኛ ኃይል በዚህ ደረጃ ማራከስና ከአማራ ክልል ለቆ እንዲወጣ መጠይቅ ምን ድብቅ አጀንዳ እንዳለው ለጊዜው ግልጽ ባይሆንላቸውም፣ መከላከያ አማራ ክልልን ለቆ ቢወጣ በቀጣይ ምን እንደሚሆን ለማሰብ እንደማይከብድ በደፈናው አመልክተዋል።
እስክንድር ነጋ በምክትልነት የሚመራው የሻለቃ ዳዊት ኃይል አማራ ክልል በይፋ ጠብመንጃ ማንሳቱን ራሱ እስክንድርን ጨምሮ በርካታ ከድርጅቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎችና “አንቂዎቻቸው” ሲገልጹ መሰንበታቸው ይታወሳል። እነዚህ ወገኖች ይኸው ኃይል የሚገድላቸውን የአካባቢ ባለሥልጣናት የቅድሚያ ግድያና የግድያ ዝርዝር በማቅረብ በ”ድል ዜናነት” የሚያቀርቡ እንደሆነ የሚያስታውሱ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ዱካቸውን ቢከተሏቸው ብዙ ጉዳዮች እንደሚጠሩ አመልክተዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
እንዲህ ነው የሃገራችን ፓለቲካ! ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል አይነት። በመሰረቱ ድምጽ ጥራት የሌለው ከዚህም ከዚያም ተለቅሞ የተገናኘና ለይቶ ይህን እናደርጋለን በማለት ከመንግስት ጋር የሚጋጭ ነገር አልሰማሁበትም። በቅርብ ጊዜ ተናገሩት ተብሎ በይፋ ከተለቀቀው በምኑም አይለይም። አቶ ዪሃንስ የራሱን አቋምና እይታ ስለ ብልጽግናው መንግስት በግልጽ አስረድቶናል። ጌታቸው ረዳን፤ ስብሃት ነጋን በጦሩ ላይ በቁማቸው መኪና የነድትን ግፈኞችና የኦሮሞ ጥርቅም ብሄርተኞች የበደሉትንና የሚፈጽሙትን ረስቶ እንዲህ ያለ ወልጋዳ ሃሳብ በአንድ ግለሰብ ላይ ማተኮር ጅልነት ነው። ግን አማራው ዛሬም ወደፊትም ይሳደዳል። ገድሎ ቀብር ላይ ማልቀስ፤ ሃዘን መድረስ የተለመደ የፓለቲካ ሸፍጥ በሆነባት ያስርሽ ምቺው ምድር እንዲህ አይነቱ ውንጀላ የሚጠበቅ እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። ደርግም ወያኔም ተጠቅመውበታል። ግን ከመፈንገል አላተረፋቸውም። ልብ ያለው መንግስትን መጠየቅ ያለበት በጠበንጃ አፈሙዝ ህዝብን ለዝንተ ዓለም አስለቅሶና አንበርክኮ መኖር ይቻላል ወይ ነው? ዛሬ የብልጽግናው መንግስት ወያኔንና አሜሪካን ለማስደሰት የአማራን ትጥቅ መቀማት መፈለጉ ያቀደውን አጀንዳ በግልጽ ያሳያል። አማራን ትጥቅ በማስፈታት ወያኔን በማስታጠቅ ወልቃይትን፤ ጠለምትንና ራያን ለትግራይ አሳልፎ ለመስጠት የታሰበ ነው።
አንዴ በደቡብ አፍሪቃ ሌላ ጊዜ በኬንያ ከወያኔ ጋር ስለ ሰላም የመከረው የብልጽግናው ስብስብ አንድም የስምምነቱ ጉዳይ እንዳልተፈጸመ ቋሚ የሚያውቀው ነው። ወያኔን እያቀፉ ከሰራዊቱ ጎን በጭንቁ ሰአት የወደቁ ወገኖችን እያደኑ ማሰርና መሰወር ብሎም መግደል ድርቡሽነት ነው። በሰሜን እዝ ላይ የደረሰው ግፍ፤ ወያኔ በ3 ጊዜ ወረራው በወሎ፤ ጎንደር፤ አፋርና ሽዋ ያደረሰው እልቂትና ዘረፋ ለብልጽግናው መንግስት ደንታ አይሰጠውም። የስንቱ ቤት ፈረሰ፤ ስንቱ ህይወቱን አጣ፤ ስንቱን እቃና ማሽን ወያኔ ተሸክሞ መቀሌ ይዞት ገባ፤ ስንት ባንክ ተዘረፈ፤ በገንዘብ ለውጥ ሳቢያ በአውሮፕላን ተጭኖ መቀሌ የተራገፈው በቢሊዪን የሚቆጠር ብር የት ደረሰ? ይህንና ያን በምንም ሂሳብ ብልጽግና ማስላት አይፈልግም። እንደ ተሸወደ ይረዳልና! አሁን አዲሱ የብልጽግና ዘፈን አማራን ማዳከም ነው።
ይህም ተባለ ሌላ ልክ እውቅ የአማራ ልጆች እየተለቀሙ እስር ቤት እንደተጣሉት ሌሎችም በዚህም በዚያም ሳቢያ ግድያ እንደተፈጸመባቸው የታወቀ ነው። አሸባሪው ኦነግ/ብልጽግና አንድ ሰው ለመያዝ አዲስ አበባ ውስጥ 30 ወታደር ከነትጥቁ የሚልኩ እብዶች ያሉበት ነው። ሰዎቹ ፓሊስ ጣቢያ ትፈለጋላችሁ ቢባሉ መቅረብ ሲችሉ ቤተሰብንና ከባቢን ለማስደንገጥ አሁን እንዘጥ እረጭ የማለቱ ወረፋ በኦሮሞ ላይ ወድቋል። ግን ትርፍ አልባ ነው። ስለዚህ አቶ ዪሃንስንም በዚህም በዚያም በማሳበብ መከራና ስቃይ እንደሚያደርሱበት የታወቀ ነው። ከለፋም አፈር መልሰውበት ለቅሶ ይቀመጣሉ። አሁን ማን ይሙት ጄ/ጻረ መኮነንን የገደለው እስር ቤት ያለው ተራ ወታደር ነው? የፓለቲካ ድራማው ብዙ ነው። ግን ገዳዪን ገዳይ ሲገድለው፤ አሳሪውን ባለተራ ሲጠፍረው፤ አሳዳጅን ሌላ ባለ ጊዜ ሲያሯሩጠው በሃበሻ ምድር የክፋት የድግግሞሽ ፓለቲካ ስንጫወት እድሜአችን ከንፎ እኛም እንኖራለን ስንል እናንቀላፋለን። አይ ሃገር ሁሌ ያዘው ጥለፈው ሲያስጠላ!